የብዙኀን እናት (እመ ብዙኀን)
ቀዳሚት ሔዋን ‹‹እመ ሕያዋን›› የሕያዋን ሁሉ እናት (ዘፍ 3፡20) ተብላ ትጠራበት የነበረውና በኋላ ግን ባለማመኗ እና
ባለመታዘዟ ምክንያት ያጣችው የክብር ስሟና የእናትነት ማዕረግ በዳግማዊት (አዲሲቷ) ሔዋን በድንግል ማርያም አማካይነት በመመለሱ
ድንግል ማርያም በነገረ ድኅነት ውስጥ ያላትን ወሳኝ ድርሻ ከማሳየቱም ባሻገር የብዙኀን (የሕያዋን) እናት መሆኗን አረጋግጧል፡፡
ልዑለ ባሕርይ እግዚአብሔር በአንተና በሴቲቱ በዘርህና በዘርዋ መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል አንተም
ሰኮናውን ትቀጠቅጣለህ (ዘፍ 3፡15) በማለት የተናገረው ይህ የትንቢት ተስፋ ሰውን ወዳጅ የሆነው አምላክ ለሰው ልጆች ያለውን
አምላካዊ አድኅኖት ዕቅድና በጎ ፈቃድ የሚገልጥ መሪ የተስፋ ቃል ነው፡፡






