Wednesday, November 20, 2013

ኢየሱስ ክርስቶስ በሐዋርያዊትና ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

ኢየሱስ ክርስቶስ፦ በሐዋርያዊትና ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን





ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ፦ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት፤
 (ክፍል ፩)

ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናት፤ ምክንያቱም የአንድ የክርስቶስ አካል ናትና። ይህች የክርስቶስ አካል የሆነች ቤተ ክርስርስቲያን መሠረቷም ጉልላቷም ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ይህንንም ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ፦ «እርሱም (ክርስቶስ)ከሁሉ በፊት ነው፤ (ለዘመኑ ጥንት የሌለው ቀዳማዊ ነው)፤. . . እርሱም የአካሉ ማለትም የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፤. . . እርስዋም አካሉና ሁሉን በሁሉ የሚሞላ የእርሱ ሙላቱ ናት፤» ሲል ገልጦአታል። ኤፌ ፩፥፳፫፣ ቈላ ፩፥፲፰። በተጨማሪም በቆሮንቶስ መልእክቱ ላይ «የእግዚአብሔር ጸጋ እንደተሰጠኝ መጠን እንደ ብልሃተኛ የአናጺ አለቃ መሠረትን መሠረትሁ፥ ሌላውም በላዩ ያንጻል። እያንዳንዱ ግን በእርሱ ላይ እንዴት እንዲያንጽ ይጠንቀቅ። ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ ሊመሠርት አይችልምና፤ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።» ብሎአል። ፩ኛ ቆሮ ፫፥፲-፲፩።
በክርስቶስ ደም ላይ የተመሠረተችው ይህች ሐዋርያዊትና ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያዪቱ ቤተ ክርስቲያን ናት። የሐዋ ፳፥፳፰፣ ዕብ ፫፥፲፬። በመሆኑም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የምታስተምረው ትምህርት ሁሉ እውነት ነው። ምክንያቱም እውነት የባሕርይ ገንዘቡ ከሆነ ከእውነተኛው ምንጭ የተቀዳ ነውና። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «ለእናንተ ደግሞ አሳልፌ የሰጠሁትን እኔ ከጌታ ተቀብያለሁና፤» ሲለ እንደተናገረ ቤተ ክርስቲያንም ለእኛ ያስተላለፈችው ከጌታ የተቀበለችውን ንጹሕ ትምህርት ነው። ፩ኛ ቆሮ ፲፩፥፳፫። ይኸውም በዓይኖቿ ያየችውን፥ በጆሮዎቿ የሰማችውን ፥በእጆቿም የዳሰሰችውን ነው። ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ፦ «ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን፥ በዓይኖቻችን ያየነውን፥ የተመለከትነውንም፥ እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፤ ሕይወትም ተገለጠ፤ አይተንማል፥ እንመሰክርማለን፥ ከአብ ዘንድ የነበረውንም (ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በቅድምና የነበረውን፥ ፈጥሮም የሚገዛውን) ለእኛም የተገለጠውን (በመለኰት ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ሳይለይ በተለየ አካሉ ከሰማየ ሰማያት በመውረድ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ በመወለድ ሰው ሆኖ የታየውን) የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን፤ » ያለው። ፩ኛ ዮሐ ፩፥፩-፫። ስለሆነም፥ የቅዱሳን ሐዋርያትን ትምህርት በመያዟ፥ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን የምትባለው ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፥ ክርስቶስን በቅዱሳን ሐዋርያት ዓይኖች አይታዋለች፥ በጆሮዎቻቸው ሰምታዋለች፥ በእጆቻቸውም ዳስሰዋለች። ይህም፦ ቤተ ክርስቲያንን ብፅዕት ያሰኛታል። ምክንያቱም ጌታ ደቀመዛሙርቱን፦ «የእናንተ ግን ዓይኖቻችሁ ስለሚያዩ፥ ጆሮዎቻችሁም ስለሚሰሙ ብፁዓን ናቸው፤» ብሎአቸዋልና። ማቴ ፲፫፥፲፮።

Friday, November 15, 2013

አቤቱ የሆነብንን አስብ





አቤቱ የሆነብንን አስብ
ይህን የሰቆቃና የተማጽኖ ልመና ወደ እግዚአብሔር ያቀረበ ታላቁ ነቢይ ኤርሚያስ ሲሆን ኤርሚያስ ማለት የቃሉ ትርጉም እግዚአብሔር ከፍ ያደርጋል እግዚአብሔር ያነሳል ማለት ነው፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር ከወደቅንበት አዘቅት ከተጣልንበት መከራ ያንሳን ከፍ ከፍ ያድርገን፡፡
ዘመኑ ክብር ከእስራኤል የለቀቀበት የይሁዳ (የእስራኤል) ክፋት የባሰበት ፍርድ የተጓደለበት ደሀ የተበደለበት አምልኮ ጣዖትና ክህደት በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል የተስፋፋበት ክፉ ዘመን ነበር፤ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ያ ዘመን ከዛሬው ከኢትዮጵያውያን ዘመን ጋራ የሚመሳሰልበትን አመስጥረው ያስተምራሉ፡፡
ዛሬም ከእኛ ከኢትዮጵያውያን ክብር ጓድሏል መተማመን ጠፍቷል ወንድም በወንድሙ ላይ እተነሣ ፍቅር በመካከላችን ቅዝቅዟል ፍርድ ተጓድሏል ደሀ ተበድሏል በገዛ ሀገራችን ሳይቀር እንደ መጻተኛ የሰሜኑ፣ በደቡብ፣ የምስራቁ ከምዕራብ ተዘዋውሮ እንዳይሰራ ጎጆ ቀልሶ ኑሮ መሥርቶ ወልዶና ከብዶ እንዳይኖር በዘረኝነት አጥር ተከልሎ በገዛ ሀገሩ ስደተኛ በባዕድም ሀገር በአሕዛብም ምድር ሳይቀር ከርታታና ተስፋ ቢስ ሆነናልና፡፡



Wednesday, November 13, 2013

ክፍል ሁለት ‹‹የእግዚአብሔር ቃል›



ክፍል ሁለት
 ‹‹የእግዚአብሔር ቃል›
                           






                                                      2/ የእግዚአብሔር ቃል እግዚአብሔር ነው
እግዚአብሔር የሚለው ስም የተወደደ ፣ የተቀባ ወይም የግብር ስም ያይደለ የባህርይ ስም ነው፡፡ እግዚአብሔር በየቋንቋው የተለያዩ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ስሞች አሉት፤ ነገር ግን ሁሉም ባሕርያዊ ስለሆኑ እና እግዚአብሔርም በባሕሪው አንድ ስለሆነ በአንድነት ፈጥሮ በሚገዛበት በባሕሪይ የግብር ስሙ በመጥራት ይተባበራሉ ወይም አንድ ይሆናሉ በየአንዳንዱ ቋንቋ ውስጥ ያለውን የእግዚአብሔርን ስም ትርጉም ብንመረምር የምናገኘው እያንዳንዳቸው እግዚአብሔርን የሚጠሩት በኃያልነት፣ በፈጣሪነት፣ በዘላለማዊነት፣ በቸርነትና ሁሉን አድራጊነት መሆኑ ነው ስለዚህ ይህን መሆን የሚቻለው ፍጡር ባለመኖር ለእግዚአብሔር ብቸኛ የባሕሪ ስሙ ሲሆን ለፍጡር ሊሰጡት የማይገባ ቢሰጡትም የማይስማማው ነው፡፡ ይህም በመሆኑ በየቋንቋው ያለ የእግዚአብሔር ስሞች ባሕሪውን ይገልጣሉ፤ እንደ ስሞቹ እንደሚሰራም ያረጋግጣሉ፡፡ (ዘፀ 15፡3 ፣ አሞ 4፡13)
እግዚአብሔር የሚለው ስም የአብ የወልድ የመንፍስ ቅዱስ የወል መጠሪያ ስም ነው የአንፆኪያው ሊቀጳጳስ ቅዱስ ባስሊዮስ ‹‹እኔስ እግዚአብሔር ባልኩ ጊዜ ስለ አብ ስለወልድ ስለ መንፈስ ቅዱስ ነው›› እንዲል እግዚአብሔር የሥላሴ የአንድነትም የሦስትነትም መገለጫ ነው ‹‹እግዚአብሔርም እንዲህ አለ ሰውን በመልካችን እንደምሳሌአችን እንፍጠር›› ዘፍ 1፡26 ቅዱስ አትናቲዎስም ‹‹አብ አምላክ ነው፣ ወልድ አምላክ ነው መንፈስ ቅዱስ አምላክ ነው ስንል እግዚአብሔር አምላክ ነው ማለታችን ነው›› በማለት ነው ያስተማረው፡፡




Friday, November 8, 2013

የቅዱሳን አማላጅነት በአፀደ ነፍስ




የቅዱሳን አማላጅነት በአፀደ ነፍስ
ባለፈው ጽሑፋችን አማላጅነት ከመቼ ጀምሮ እንደነበረ የአማላጅነት ትርጉም ቅዱሳን በአፀደ ስጋ እንደሚያማልዱ እግዚአብሔር የወዳጆቹን ጸሎት እንደሚስማና የለመኑትን ሁሉ እንደሚፈጽሙላቸው አይተናል በዚህ ክፍል ደግሞ ቅዱሳን በአፀደ ነፍስ ማማለድ ይችላሉን? ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመስጠት እንሞክራለን፤ ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ያስችለን ዘንድ አስቀድመን የሰውን ተፈጥሮና ከሞት በኋላ የሚገጥመውን ሁኔታ ምን እንደሚመስል በመግቢያት እናያለን፡፡
የሰው ልጅ በአርአያ ስላሴ የተፈጠረ ክቡር ፍጡር ነው (ዘፍ 1፡26) ሰው ሥጋው ከምድር አፈር የተሠራ ቢሆንም ሥጋ ብቻ አይደለም ከሥጋ ጋር የተዋሃደች ነፍስ ደግሞ አለችው ፡፡ ስለዚህ ሰው በሥጋው የሚራብ የሚጠማ የሚበላ የሚጠጣ የሚደክም የሚታመም የሚዋለድና የሚሞት ሲሆን በነፍሱ ደግሞ የማይሞት የማይራብ የማይፈርስ የማይበሰብስ አሳቢ አዋቂ ተናጋሪ ሕያው ነው፡፡ ሰው ሲሞት ሥጋው ወደ ተፈጠረበት አፈርነቱ ይመለሳል ይፈርሳል ይበሰብሳል ነፍሱ ግን ሕያው ስለሆነች እንደ ስራዋ ወደ ገነት ወይም ወደ ሲዖል ትሄዳለች፡፡ በዚህ መሠረት ቅዱሳን ሥጋቸው በምድር እግዚአብሔር ከፈቀደላቸው ሥፍራ ሲቀበር ነፍሳቸው ደግሞ በገነት ውስጥ እንደመላእክት በደስታ ይኖራሉ፡፡



‹‹የእግዚአብሔር ቃል›



‹‹የእግዚአብር ቃል›
በዚህ ርእስ ውስጥ የእግዚአብሔር ቃል ስንል ከሶስቱ ቅዱስ አንዱን ቅዱስ ለዘመኑ ጥንት ወይም ፍፃሜ የሌለውና የእግዚአብሔር ልጅ እግዚአብሔር ስለሆነው ስለ ጌታችን ስለ መድሃኒታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡
ለባሕርይ አባቱ ለአብና ለባሕርይ ህይወቱ ለመንፈስ ቅዱስ ቃል ለሆነውንና በቅድምና በልዕልና ስለነበረው የዘመኑ ፍፃሜ በሆነ ጊዜ የተቆጠረው ሱባኤ ሲያበቃ የተነገረው ትንቢት ሲደርስ ፀጋና እውነትን ተመልቶ በእኛ ስላደረው አካላዊ ቃል (ሎጎስ) ወልድ ማንነት ለመፃፍ ፈልገን ነው፡፡
ወንጌላዊውና ሐዋርያው ቅዱስ ዮሀንስ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ‹‹በመጀመሪያ ቃል ነበረ፣ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፣ ቃልም እግዚአብሄር ነበረ፣ ይህም በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፣ ሁሉ በእርሱ ሆነ ከሆነውም አንዳች እንኳ ያለ እርሱ አልሆነም፡፡››(ዮሐ 1፣1-2) ‹‹ቃልም ስጋ ሆነ ፀጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ አንድ ልጅም በአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነውን ክብሩን አየን››(ዮሐ 1፣14)በማለት አስተምሮናል፡፡












Thursday, November 7, 2013

ኢትኀልዩ (አትጨነቁ) ማቴ 6፡25




ኢትኀልዩ (አትጨነቁ) ማቴ 6፡25



ይህንን የማጽናኛ የዋስትና ቃል የተናገረ በጊዜና በዘመን የሚሸነፈው ራሱም በውጥረት በሃሣብ የሚኖረው ደካማው ፍጥረት አልያም ወንበራቸው የሚገለበጠው ሥልጣናቸው የሚሻረው ምድራዊ ነገስታት ሳይሆኑ የሲኦልን ድል መንሳት አስወግዶ ጨለማውን በብርሃን የገለጠ የሞትን መውጊያ የሰበረ የመኖራችን ምስጢር የነገስታት ንጉስ የገዥዎች ገዥ ሲሰጥ የማይሳሳ ሰጥቶ የማይነሣ ብርቱ መደገፊያና የማይሰበር ምርኩዝ መድኅን ዓለም ክርስቶስ ነው፡፡





Tuesday, November 5, 2013

ደብዳቤ



ደብዳቤ
ደብዳቤ ከዘመድ ከወዳጅ ወይም ከተለያየ ሥፍራ በየጊዜው ይደርሰን ይሆናል አሊያም ተፅፎልን ላያውቅ ይችላል፣ ሆኖም ግን ደርሶናል ብለን እናስብና… በወረቀት ላይ በቀለም የፃፍነው ደብዳቤያችንን ወደ ፖስታ ቤት ለመላክ ከመውሠዳችን በፊት ፖስታ ቴምብር ወይም መግዣ ገንዘብ ማዘጋጀት አለብን፡፡ ከዚያ በኋላ የተፃፈውን ደብዳቤ አሽገን በላዩ አድራሻውን ጽፈን ቴምብር ከለጠፍን በኋላ ወደ ተላከለት ሰው እንዲደርስ የፖስታ መሠብሰቢያ ሣጥን ውስጥ እንከታለን የፖስታ ቤት ሠራተኛውም ምልክት (ማህተም) አድርጎ ይልከዋል፡፡ ጉዞ ወደ ተቀባይ…… ከቀናት በኋላ ተቀባይ ይደርሰዋል ምንም ይሁን ምን ደብዳቤ ከወዳጅ ከዘመድ በተለይም ከሚወዱት ሰው ሲመጣ ያስደስታልና ደስ ይለዋል…. ፖስታውን ከፍቶ ያነባል መልዕክቱ እስኪፈፀምም ድረስ ይሁን ለትዝታና ለማስታወሻነት ደብዳቤው ሥፍራ ተሰጥቶት ይቀመጣል፡፡ ደብዳቤ መንፈሳዊ አስተማሪ ከመሆኑ ባሻገር ምሳሌ ነው ከእግዚአብሔር ወደ ዓለም በፖስታ ወይም በሥጋዊ ሰውነት ውስጥ ታሽገን የተላክን ደብዳቤዎች ነን ‹‹በእጃቹ አበጃጅቶ የሠራን በመዳፉ የቀረፀን እርሱ ነውና እርሱ ፈጠረን እርሱ ሰራን›› ‹‹ሐዋርያውም ለክብሩ እንሆን ዘንድ ከዘመናት በፊት በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን ነው ያለው›› እኛ ፍጥረቱ ነንና እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን (ኤፌ 2፡10)