በምስጢረ ጥምቀት ምስጢረ ሥላሴ ተገለጠ
በቅዱሳት መጻሕፍት በጉልህ ተመዝግቦ እንደምናገኘው አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስከ 30 ዓመቱ ድረስ ለእናቱ ለ ቅድስት ድንግል ማርያም እየታዘዛትና እየተላላከ አደገ ( ሉቃ 2፣) በ30 ዓመቱ ግን ሰማይና ምድር በመሀል እጆቹ የተያዙ አምላክ እንደ ተራ ሰዎች በፈለገ ሄኖን በማዕዶት ዮርዳኖስ ለመጠመቅ ሄደ በጥንተ ፍጥረት የእግዚአብሔር መንፈስ በውሀ ላይ ሰፎ ነበር (ዘፍ፩፣፪) በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ከሶስቱ ቅዱስ አንዱ ቅዱስ ከባህርይ አባቱ ከአብ ከባህርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ የተካከለ እሱ መድሐኔዓለም ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ በባህረ ዮርዳኖስ በመጠመቅ ለውኃ የበለጠ ኃይል ሰጠው :የባርነት ደብዳቤ በዮርዳኖስ ነበርና ዕዳ በደላችን ይደመስስ ዘንድ በባህረ ዮርዳኖስ በትህትና በባሪያው እጅ ይጠመቅ ዘንድ ወደ ውሃው ገባ፡፡







