Thursday, November 7, 2013

ኢትኀልዩ (አትጨነቁ) ማቴ 6፡25




ኢትኀልዩ (አትጨነቁ) ማቴ 6፡25



ይህንን የማጽናኛ የዋስትና ቃል የተናገረ በጊዜና በዘመን የሚሸነፈው ራሱም በውጥረት በሃሣብ የሚኖረው ደካማው ፍጥረት አልያም ወንበራቸው የሚገለበጠው ሥልጣናቸው የሚሻረው ምድራዊ ነገስታት ሳይሆኑ የሲኦልን ድል መንሳት አስወግዶ ጨለማውን በብርሃን የገለጠ የሞትን መውጊያ የሰበረ የመኖራችን ምስጢር የነገስታት ንጉስ የገዥዎች ገዥ ሲሰጥ የማይሳሳ ሰጥቶ የማይነሣ ብርቱ መደገፊያና የማይሰበር ምርኩዝ መድኅን ዓለም ክርስቶስ ነው፡፡





Tuesday, November 5, 2013

ደብዳቤ



ደብዳቤ
ደብዳቤ ከዘመድ ከወዳጅ ወይም ከተለያየ ሥፍራ በየጊዜው ይደርሰን ይሆናል አሊያም ተፅፎልን ላያውቅ ይችላል፣ ሆኖም ግን ደርሶናል ብለን እናስብና… በወረቀት ላይ በቀለም የፃፍነው ደብዳቤያችንን ወደ ፖስታ ቤት ለመላክ ከመውሠዳችን በፊት ፖስታ ቴምብር ወይም መግዣ ገንዘብ ማዘጋጀት አለብን፡፡ ከዚያ በኋላ የተፃፈውን ደብዳቤ አሽገን በላዩ አድራሻውን ጽፈን ቴምብር ከለጠፍን በኋላ ወደ ተላከለት ሰው እንዲደርስ የፖስታ መሠብሰቢያ ሣጥን ውስጥ እንከታለን የፖስታ ቤት ሠራተኛውም ምልክት (ማህተም) አድርጎ ይልከዋል፡፡ ጉዞ ወደ ተቀባይ…… ከቀናት በኋላ ተቀባይ ይደርሰዋል ምንም ይሁን ምን ደብዳቤ ከወዳጅ ከዘመድ በተለይም ከሚወዱት ሰው ሲመጣ ያስደስታልና ደስ ይለዋል…. ፖስታውን ከፍቶ ያነባል መልዕክቱ እስኪፈፀምም ድረስ ይሁን ለትዝታና ለማስታወሻነት ደብዳቤው ሥፍራ ተሰጥቶት ይቀመጣል፡፡ ደብዳቤ መንፈሳዊ አስተማሪ ከመሆኑ ባሻገር ምሳሌ ነው ከእግዚአብሔር ወደ ዓለም በፖስታ ወይም በሥጋዊ ሰውነት ውስጥ ታሽገን የተላክን ደብዳቤዎች ነን ‹‹በእጃቹ አበጃጅቶ የሠራን በመዳፉ የቀረፀን እርሱ ነውና እርሱ ፈጠረን እርሱ ሰራን›› ‹‹ሐዋርያውም ለክብሩ እንሆን ዘንድ ከዘመናት በፊት በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን ነው ያለው›› እኛ ፍጥረቱ ነንና እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን (ኤፌ 2፡10)

የብዙኀን እናት (እመ ብዙኀን)



 

የብዙኀን እናት (እመ ብዙኀን)
ቀዳሚት ሔዋን ‹‹እመ ሕያዋን›› የሕያዋን ሁሉ እናት (ዘፍ 3፡20) ተብላ ትጠራበት የነበረውና በኋላ ግን ባለማመኗ እና ባለመታዘዟ ምክንያት ያጣችው የክብር ስሟና የእናትነት ማዕረግ በዳግማዊት (አዲሲቷ) ሔዋን በድንግል ማርያም አማካይነት በመመለሱ ድንግል ማርያም በነገረ ድኅነት ውስጥ ያላትን ወሳኝ ድርሻ ከማሳየቱም ባሻገር የብዙኀን (የሕያዋን) እናት መሆኗን አረጋግጧል፡፡
ልዑለ ባሕርይ እግዚአብሔር በአንተና በሴቲቱ በዘርህና በዘርዋ መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል አንተም ሰኮናውን ትቀጠቅጣለህ (ዘፍ 3፡15) በማለት የተናገረው ይህ የትንቢት ተስፋ ሰውን ወዳጅ የሆነው አምላክ ለሰው ልጆች ያለውን አምላካዊ አድኅኖት ዕቅድና በጎ ፈቃድ የሚገልጥ መሪ የተስፋ ቃል ነው፡፡








Monday, November 4, 2013

የቅዱሳን አማላጅነት በአፀደ -ሥጋ





የቅዱሳን አማላጅነት በአፀደ -ሥጋ
 የአማላጅነት ትምህርት በዘመነ አበው በህገ ልቡና፣ በዘመነ ኦሪት በመጻሕፍተ ብሉያት በዘመነ ሐዲስ በመጻህፍተ ሐዲሳት የነበረና አሁንም ያለ ወደፊትም የሚቀጥል ትምህርት እንጂ ከጊዜ በኃላ ድንገት የመጣ አይደለም፡፡ ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናችንም የቅዱሳት መጻሕፍትን የሐዋርያትንና የሊቃውንትን ትምህርትና ትውፊት ታስተምራለች፡፡ አማላጅነት እግዚአብሔር የሚፈቅደውና የሚወደው እንጂ ሰው ሰራሽ ልማዳዊ ወግ አይደለም ከቤተክርስቲያን ታሪክ እንደምንረዳው ክርስትና ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ የአማላጅነት ትምህርት ያለ እንጂ በኋላ ጊዜ ብቅ ያለ አይደለም፡፡








Saturday, November 2, 2013

ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕሪ አምላክ ነው





ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕሪ አምላክ ነው
የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክረስቶስን የባሕሪ አምላክነት ሐዋርያት በሰፊው አስተምረውናል፡፡ በየዘመኑ የተነሱ ሊቃውንትም አሟልተውና አስፍተው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል ነገር ግን ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆርንቶስ ክርስቲያኖች እንደፃፈው (1ቆሮ 1፡24) የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ጥበብ በመሆኑ ለሰነፎች ሊረዳቸው አልቻለም፡፡ ጥበብን የሚረዳ ልባሞች እንጂ ሰነፎች አይደሉምና፡፡ በተለይም የሰው ጥበብ የእግዚአብሔርን ጥበብ ሊመረምር አይችልም ከሰው ጥበብ ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ስለሚጠበብ በእምነት ልባሞች የሆኑ እንጂ በሥጋዊ ጥበብ ልባሞች የሆኑ የዋጃቸውን አምላክ ማወቅ አልቻሉም የፍጡራን ጥበብ ፍጥረታትን እንጂ ፈጣሪን መርምሮ መረዳት አልቻሉም፡፡ በቀደሙት ዘመናት አይሁድ ቀጥሎም ክርስትናን ከተቀበሉት ወገን አርዮስና ተከታዮቹ ከ325 ዓ.ም ቀደም ብለው ጀምረው በሥጋዊ ጥበብ ሊያውቁት በመሞከራቸው በእምነት ያውቁት የነበረውን የባሕሪይ አምላክ ክርስቶስን አጥተውታል፡፡ አሁንም በዚህ ዘመን ክርስቶስን በሥጋዊ ጥበብ ለማግኘት በሚደረግ ጥረት ሰለባ የሆኑ ጥቂቶች አይደሉም፡፡

Thursday, October 31, 2013

ባልንጀራዬ ማነው? ሉቃ 10፡29



 


ባልንጀራዬ ማነው? ሉቃ 10፡29
ምንም እንኳን ሁሉም ሰው ከአንድ የአዳም ዘር የተገኘ ቢሆንም ሲወርድ ሲዋረድ በመጣው የሰው ልጆች በአከባቢ በቋንቋ ፣ በአኗኗር ፣ በባሕል ወዘተ መለያየት እንዲሁም የቁጥር መብዛት የተነሣ፤ እስከተወሰነ የዘር ግንድ ድረስ ያለውን የሥጋ ዘመዴ ብሎ ሲጠራ ሌላውን ደግሞ ባዕድ ይለዋል፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው ብቻውን ወይም የሥጋ ዘመዴ ካላቸው ጋር ብቻ ስለማይኖር በአጠቃላይ በማኅበራዊ ሕይወቱ፣ በሥራው ፣ በትምህርቱ ከብዙ ዓይነት ሰዎች ጋር ይገናኛል አብሮም ይኖራል፡፡ በእነዚህ አጋጣሚዎችም በሃሳብ፣ በዓላማ ከሚመስሉት ጋር ባልጀርነትን (ጓደኝነትን) ይመሠርታ፡፡ በብዙ አጋጣሚ እንደሚታየውና በጽኑ ፍቅር ላይ የተመሠረተ ጓደኝነት ከሆነ ከሥጋ ዝምድና ቢበልጥ እንጂ የማያንስ ችግርን ደስታን ምስጢርን በጋራ የሚካፈሉበት፣ ለአንተ ለአንቺ የሚባባሉበት ትልቅ የሕይወት ክፍል ነው፡፡

Tuesday, October 29, 2013

‹‹እነሆ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና ተጭኖ ወደ ግብፅ ይመጣል›› (ኢሳ 19-1)

ክፍል ሦስት     

ሰባዓ ሰገል ከሩቅ ምስራቅ ተነስተው ‹‹የተወለደው የአይሁድ ንጉስ ወዴት ነው?›› እያሉ በመጡ ጊዜ ሄሮድስ ደነገጠ ‹‹ንጉስማ ከሆነ ንጉሥ ሳይገድል ይነግሳልን?›› ብሎ የካህናትንም አለቆች ሰበሰበ ክርስቶስ ወዴት እንዲወለድ ጠየቃቸው በቤተልሔም መሆኑን ነገሩት ከዚያ በኋላ ሰብአ ሰገልን ጠርቶ ከአገኙት ተመልሰው እንዲነግሩትና ሄዶ እንደሚሰግድለት መክሮ ላካቸው፡፡ እነርሱ ግን ወደ ሄሮድስ እንዳይመጡ በሕልም ተረድተው በሌላ መንገድ ወደ አገራቸው ሄዱ፡፡ ለዮሴፍም መልአክ በሕልም ታይቶ ሕፃኑንና እናቱን ይዞ ወደ ግብፅ እንዲሸሽ አደረገው (ማቴ 2፡15) እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ጌታችንን አዝላ ፀሐይና ብርድ እየተፈራረቀባት የአሸዋው ግለት የመንገዱ ርዝመት ሳይበግራት ከእየሩሳሌም ተነስታ እስከ ግብፅና ኢትዮጵያ ድረስ ለሦስት ዓመታት ያህል በመንከራተትና ልጇን ከሚፈታተኑ ጠላቶች ሁሉ አቅፋ ሸፍና በመከለሏ ደመና ተብላለች፡፡ ከዚህም የተነሣ አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን ወደ ግብፅና ኢትዮጵያ ተሰደደ ለሚለው ጥያቄ ይህ የኢሳይያስ የትንቢት ቃል ‹‹እነሆ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና ተጭኖ ወደ ግብፅ ይመጣል›› (ኢሳ 19-1) የሚለው አንዱና የመጀመሪያው ምክንያት ነው፡፡