Thursday, October 9, 2014

ሥዕል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን


 

                              ሥዕል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
ከክርስትና በፊት ሥዕል በቤተ አሕዛብም ሆነ በቤተ አይሁድ የታወቀና ከአምልኮት ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ በቤተ አሕዛብ ዕንጨት ጠርቦ ደንጊያ አለዝቦ ማምለክ የተለመደ ነበር፡፡ እንዲያውም የሮማ ነገሥታት አማልክት ተብለው ከመመለካቸው በላይ ከሞቱ በኋላ ሥዕላቸው በደንጊያና በዕንጨት እየተቀረጸ ሲመለኩ መኖራቸው በታሪክ ይታወቃል፡፡ ክርስትና በመጣ ጊዜም ከክርስትና ጋር ያጣላቸው ይኸው ልማዳቸው ነው፡፡ በክርስትና ትምህርት ይህ አምልኮ ጣዖት ነውና፤ በቤተ አይሁድም እንደ አሕዛብ ሳይሆን በታቦተ ሕጉ በጽላተ ኪዳኑ ላይ ሥዕለ ኪሩብን እንዲስል ራሱ እግዚአብሔር ሙሴን አዝዞት ነበር፡፡

እነዚህ የኪሩቤል ሥዕሎች ከታቦቱ አይለዩም፡፡ ምክንያቱም ታቦት የእግዚአብሔር መገለጫ ዙፋን ስለሆነ የመንበረ ጸባኦት አምሳል ነው፡፡ ሥዕለ ኪሩቤልም የጸወርተ መንበር ኪሩቤል አምሳል ናቸውና የሚሳሉትም እንደሚናተፍ አውራ ዶሮ ሆነው ነው፡፡ የንጉሥ አንጋች ንጉሡ በተቀመጠበት በዙፋኑ ፊት ነቃ፣ ቆጣ፤ ብሎ እንደሚቆም፡፡

ሥዕል በቤተ ክርስቲያን የተጀመረበት ግን ከዚህ የተለየ ታሪካዊ ምክንያት አለው፡፡ በጥንታውያን ክርስቲያኖች ዘንድ የሥዕል ክብር እንዴት ተጀመረ፡፡ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደ ተገለጠው የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ትምህርታቸውን ያስፋፉት ዋሻ ፈልፍለው ጉድጓድ ቆፍረው በዋሻ በፍርክታ ውስጥ ነው፡፡ ካታኮምብ (ብበበ ምድር) ይሉታል፤ በዚህ ዋሻ ውስጥ የሰማዕታትን ዓፅም እየሰበሰቡ ጸሎት ይጸልዩ ትምህርት ያስተምሩ ነበር፡፡ በዚሁ ውስጥ ብዙ አማኞች እየመጡ የማኅበራቸው አባል መሆን ጀመሩ በዚህ ጊዜ የክርስትናን ትምህርት አስፋፍቶ ለመስጠት በቂ መጻሕፍት አልነበሩም፡፡ እንደልብ ወጥቶ ለመፈለግና ለማዘጋጀት ነፃነት ስላልነበራቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንዳንድ ምሳሌዎችን በሥዕል እያሠፈሩ ማስተማር ጀመሩ፡፡ በዚህ ሁኔታ ሥዕል ማስተማሪያ ሆኖ ቆይቷል፡ ሥዕሎችም የሚሳሉት በምሳሌነት "ሲምቦል" ሲሆን የሚሳሉትም በአመድና በከሰል በዋሻው ዙሪያ ነው፡፡ በዋሻው ፊት ለፊት ላይ (በአፈ ጽዮን) የሚስሉት እረኛው በጉን እንደ ተሸከመ አድርገው ነው፡፡ "ክርስቶስ ያመኑበትን ሁሉ በሱም አምነው የሚሞቱትን ሁሉ የሚያድናቸው ቸርና ታማኝ ጠባቂ መሆኑን ለማስረዳት" ሌላው ሥዕላቸውን የሚጀመሩት በብሉይ ኪዳን ታሪክ ነው፡፡ ለምሳሌ የቀደሙ ሰዎች አዳምና ሔዋን እንዴት እንደተሳሳቱና ያሳታቸውንም እባብ በመካከላቸው እንዳለ አድርገው ይስሏቸው ነበር፡፡ በምሕላና በጸሎት ላይ ያለች የምዕመንን ነፍስ በመርከብ ውስጥ ያለውን ኖኅን አስመስለው ይስሏት ነበር፡፡ የአቤልን መስዋዕት የክርስቶስ መስዋዕትነት ምሳሌ በውሃ ተጠምቆ መዳንን ወይም መዳን በጥምቀት መሆኑን ሲገልጡ ሙሴ በበትሩ ደንጊያውን መትቶ ለተጠሙ እስራኤል ውሃ ማፍለቁን የሰማዕታትና የምእመናን መከራና ትዕግስት የኢዮብ መከራና ትዕግስት ምሳሌ የምእመናን በዚህ ዓለም መኖር የእስራኤል ጉዞ በሐቅለ ሲና "የሙሴ ደብረ ሲና መውጣት አምላኩንም ማየት፤ የምእመናን ክብርና ልዕልና፡፡ "ሠለስቱ ደቂቅ በእሳት ውስጥ ከገብርኤል ጋር ምእመናን በዚህ በመከራ ቢሰቃዩም ታዳጊ መልአክ የማይለያቸው ለመሆናቸው ምሳሌ" "ኤልያስ ሐሜለቱን ለኤልሳዕ ጥሎ ሲያርግ ክርስቶስ በረከቱን ለምእመናን ሰጥቶ ማረጉ፤ ምእመናን በሱ አምነው ገነት መንግስተ ሰማያት መግባታቸው" "ዳንኤል በገበ አናብስት ሰማዕታት በዓላውያን ሸንጎ" ጦቢት ከዓሣው ጋር ምእመኑ ከአዳኙ ከክርስቶስ ጋር "በጥንት ግሪኮች ዓሳ ሲሉ፡- "ኢኽቲስ" ይላሉ፡፡ የዚህ ፊደር እያንዳንዱ ምህጻረ ቃልነት አለው፡፡ ኢ-ኢየሱስ፣ ኸ-ኸርስቶስ፣ ቴ-ቴው ኢዮስ፤ (የእግዚአብሔር ልጅ) ስ-ሶቴር፤ ("መድኅን") አዳኝ፤ በተገናኝ፡- "ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር መድኅን" ማለት ነው፡፡ "ሶስና ከሁለት ዳኞች ጋር ሰማዕታት በዐላውያን ነገስታት ፊት" "ዮናስ ወደ ባሕር ሲጣል፤ አንበሪ ዮናስን በየብስ ሲተፋው የነበረባት ጎጆ በዱባ ቅጠል ተሸፍና ዮናስም በጣም ተደስቶ በኋላም በደረቀችበት ጊዜ በጣም አዝኖ፡- ይህም ሁሉ አንድ ላይ ሆኖ የክርስቶስን ሞትና ትንሳኤ፤ ከዚያም የሙታንን ትንሣኤ ያስረዳል፡፡"

የሐዲስ ኪዳንንም ታሪክ እንደዚሁ በግበበ ምድር ውስጥ ይስሉት ነበር፡፡ "የገብርኤል ብስራት የጌታ በቤተ ልሔም ዘይሁዳ መወለድ፤ የሰብአ ሰገል ስግደትና አምኃ ሕፃኑን ለታቀፈችው ለድንግል ማርያም አምኃውን ሲያስረክቡ፤ የምድረ ግብፅ ስደት፤ ዮሴፍና ሰሎሜ ጓዛቸውን ተሸክመው አብረው ሲሰደዱ፤ የጌታ ጥምቀትና የሶስቱ ዓመት ትምህርት ከተአምራት ጋር፤ የቃና ሠርግ፤ የዕውሩ ዓይን፤ የመጻጉዕ መዳን፤ ልብሱን ስትዳስስ ደሟ የደረቀላት ሴት (እንተ ደም ይውኀዛ) የአምስቱ እንጀራና የሁለቱ ዓሣ ቡራኬ ለአምስት ሺህ ሰው መመገብና ዐስራ ሁለት ቅርጫት ማትረፍ ሳምራዊት ማድጋዋን ተሸክማ ወይም ውኃውን ከዐዘቅቱ በሸንከሎዋ ስትስብ፤ ጌታ ሳምራዊትን ሲያነጋግር፤ የሰነፎቹን የብልሆቹ ደናግል ሁኔታ የጴጥሮስ ክህደትና ጸጸት የይሁዳ ክህደትና መምህሩን አሳልፎ መስጠት በመጨረሻም ሞቱና ትንሣኤው ማርያም መግደደላዊትና የተነሣው ክርስቶስ እመቤታችን ምስለ ፍቁር ወልዳ በግራዋ በኩል ኢሳይያስ ወደሷ እያመለከተ፡- "ናሁ ድንግል ትፀንስ ወትወልድ ወልደ ብዬ የተናገርሁላት ይቺ ናት እንደማለት ነው፡፡" ይህንና ይህን የመሳሰሉ ሌሎችም ሥዕሎች በጥንት የክርስቲያኖች መሸሸጊያ ዋሻዎች በከሰልና ባመድ ተስለው ተገኝተዋል ይህን ሁሉ ያደርጉ የነበር በፊት እንደ ተባለው የሃይማኖታቸውን ታሪክ ለማስተማር ነው፡፡

ከዚህ ሌላ የምእመናንን ልቡና ለማጽናናት በሰማዕትነት የሞቱት ወንድሞቻቸው ዐጽም ባረፈበት አኳያ አሟሟታቸውንም በሥዕል ይገልጹት ነበር፡፡ በዚህ አኳኋን የሥዕል ክብር በቤተ ክርስቲያን እንደተጠበቀ እስከ ስምንተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ድረስ ከቆየ በኋላ በሥዕል ምክንያት በሮምና በቢዛንታይን ግዛት በሚኖሩ ምእመናን ዘንድ አለመግባባት ተፈጠረ፡፡ ለዚህም አለመግባባት ዋናው ምክንያት አንዳንድ ክርስቲያኖች ሥዕል ከመውደዳቸው የተነሳ ሥዕሎችን አማልክት ናቸው እስከማለት ደርሰው ነበር፡፡ (ኢኮኖላትሪያ) ሌሎቹ ደግሞ ወደ ሌላ ጎን በማጋደል ሥዕሎችን ጨርሰን ማጥፋት አለብን ብለው የከረረ የተቃውሞ በር ከፈቱ (ኢኮኖማሂያ) በመካከሉ ደግሞ እንደ ነዚያም ሳያመልኩ እንደነዚህም በጥላቻ ሳይመነችኩ የጥንቱን ትምህርት ተከትለው ሥዕሎችን የሚወዱና የሚያከብሩ ምእመናን ነበሩ ነገር ግን በዘመኑ የነበሩት ገዥዎች ሥዕል ማጥፋት አለብን የሚለውን ክፍል ስለ ደገፉ ቤተ ክርስቲያን ለብዙ ዘመን ያቆየቻቸው ቅርሶቿ የቤተ ክርስቲያንን ጥንታዊ ኪነ ጥበብ የሚያሳዩ ሥዕሎች ሁሉ በእሳት ጋዩ፡ ብዙ ምእመናንም በዚሁ ምክንያት አለቁ፡፡ የሥዕሎቹ መጥፋት ጉዳይ በባለ ሥልጣኖች ቢደገፍም ሥዕሎቻችን አይቃጠሉብን የሚለው ክፍል እያየለ ድምፁም እየተሰማ ሄደ፤ እንዲያውም ጠቡ እየተባባሰ ሄዶ የሮምንና የቢዛንታይንን መንግስት የሚያናጋው ሆነ፡፡

ይህን በክርስቲያኖች መካከል የተነሳ ብጥብጥ በጉልበት ሳይሆን ሁለቱንም ክፍሎች በሚያግባባ የጋራ ሐሳብ ላይ ለመድረስ፤ ጠቡ በተነሣበት አካባቢ የነበሩ የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች በ፯፻፹፯ ዓ.ም ጉባኤ አድርገው እንደ ሁለቱም ሳይሆን ማለት እንደ ሥዕል አምላኪዎችና እንደ ሥዕል አጥፊዎች ሳይሆን ስለ ሥዕል ክብርና ስግደት የሚገባውን ቀኖና ሠርተዋል፡፡ ከዚህም ጉባኤ በኋላ በማከታተል የተነሡ የሮማን የቢዛንታይን (መለካውያን ሊቃውንት) ስለ ሥዕል ክብርና የት መጣ አያሌ መጻሕፍትን ጽፈዋል፡፡ ለምሳሌ በዚያው ዘመን በዚያው አካባቢ የነበረው ስመ ጥር ሊቅ ዮሐንስ ዘደማስቆ ስለሥዕል ብዙ ቀዋሚ ጠቃሚ የሆኑ መጻሕፍት ጽፏል፡፡ ዮሐንስ ዘደማስቆ እንደሚለው ሥዕል በቤተክርስቲያን ሁለት ዓይነት ጥቅም አለው ከነዚህም አንዱ በዋሻው እንደነበሩት ክርስቲያኖች ተአምራት ነክ የቅዱሳት መጻሕፍትን ታሪኮች ማንበብ ለማይችሉ ሰዎች ለማስረዳት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሃይማኖቱን ሳይፈር ሳያፍር መስክሮ በሰማዕትነት የሞተ ወይም ስለ ዓለምና ስለ ራሱ በመጸለይ መላ ሕይወቱን ከፍትወታት፤ ከእኩያት ከአጋንንት ጋር በመጋደል ያሳለፈውን ሰማዕት ወይም ጻድቅ በሥዕል ለማስታወስ በሥዕሉም አማካይነት እያንዳንዱ ምእመን ለሥዕሉ ባለቤት ያለውን ክብርና ፍቅር ለመግለጥ ነው፡፡

በሥዕል ፊት ቁሞ መጸለይ ከባለ ሥዕሉ ረድኤት በረከት ምልጃ መለመን መማጠን ነው፡፡ ለሥዕል መስገድ ሥዕልን መሳም ደግሞ በፊት የሥዕል ተዋጊዎች ወይም ጸረ ሥዕሎች (ኢኮኖሚኺ) እንደሚሉት ዛሬም ብዙ ጸረ ማርያሞች እንደሚያጥላሉት ለጣኦት መስገድ ጣዖት መሳም አይደለም፡፡ ከላይ እንደገለጥነው በሥዕሉ አማካይነት ለሥዕሉ ባለቤተ ክብርንና ፍቅርን ለመግለጽ ነው፡፡ ይኸውም የቤተ ክርስቲያን ሕልውና ከታወቀበት ጊዜ ጀምሮ የነበረ ጥንታዊ ትውፊት ነው፡፡ (Traditiona) ነው፡፡ በእምነትና በፍቅር የሆነ ነገር ደግሞ ያንፃል እንጂ አይንድም፡፡ የእግዚአብሔር መንግስት የሚወርሰው በፍጹም እምነት ቅንነት በተሞላበት ፍቅርና ትሕትና እንጂ በተጥባበ ነገር (Ration Alism) አይደለምና፡፡

በምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት ትውፊት መሠረት ሥዕል የሚሳለው በቀለም ነው፡፡ ላቲኖች ግን ቅርጽ ይቀርጻሉ፡፡ ስለሥዕል ክብር በቤተ ክርስቲያን ስለተጀመረበትም ምክንያት በመጠኑ ገልጠናል፡፡ አሁን ደግሞ ስለ ሥዕል ከተነሳ ዘንድ አከራካሪ ስለሆነው የጌታና የእመቤታችን ሥዕል የትመጣ እንደዚሁ የቤተ ክርስቲያንን ትውፊት መሠረት በማድረግ በመጠኑ እንገልጣለን፡፡

ስለጌታ ሥዕል ብዙ ታሪኮችና ትውፊታዊ ትምህርቶች ይነገራሉ፡፡ በዚሁ መሠረት ለመጀመሪያ ጊዜ የጌታን ሥዕል የሣለው ዮሐንስ ወንጌላዊ ነው ይባላል፡፡ ታሪኩም ከሞላ ጎደል እንደሚከተለው ነው፡፡ ከ፲፬-፴፯ ዓ.ም ሮምን ይገዛ የነበረው ጢባርዮስ ቄሳር ነው፡፡ በሱ ዘመነ መንግስት ነው ጌታ የተሰቀለው፤ ይኸው ጢባርዮስ ቄሳር የሚወደው አንድ ልጅ ነበረው፡፡ እሱው ሞተበት ጢባርዮስ በልጁ መሞት በጣም አዝኖ ፌሳውን ሳያስቀብር ሰነበተ ከጥቂት ቀንም በኋላ ጌታ በኢየሩሳሌም ያደረገው የነበረውን ታምራት ያውቅ ስለነበር፤ "ከጢባርዮስ ቄሳር ምድራዊ ንጉስ የተላከች ጦማር (መልእክት) ለጌታ ለኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሠ ሰማይ ወምድር ትድረስ" ብሎ ልጁን እንዲያስነሳለት የምልጃ የልመና ጽሑፍ ጽፎ ይህችን መልዕክትና የልጁን ሬሳ ወስደው ጎልጎታ(የጌታ መቃብር) ላይ እንዲያኖሩለት ባለወጎቹን ላከ፡፡ እነሱም ሔደው ደብዳቤዪቱንና ሬሳውን በጌታ መቃብር ላይ ሲያኖሩት ሬሳው አፈፍ ብሎ ተነሥቷል፡፡ ጢባርዮስም ከደስታው ብዛት የተነሳ የጌታን ውለታ ለመክፈል የዚህንስ ሰው እናቱን አምጡልኝ እኔ ቋሚ ለጓሚ ሚስቴ ገረድ ደንገጥር ሁነን እናገለግላታለን ብሎ እንደገና ሰው ቢልክ የድንግል ማርያም ክብር ሰማያዊ እንጂ ምድራዊ ስላልሆነ ተሰውራባቸው አላገኟትም፡፡ ጢባርዮስ ግን ተስፋ እንዳይቆርጥ ዮሐንስ ወንጌላዊ በዕለተ ዓርብ በመስቀሉ ላይ እንዳየው አድርጎ ከለሜዳ አስታጥቆ ጌታን ሥሎለታል፡፡ ስለ ሥዕሉ እውነተኛነትም ለማረጋገጥ ዮሐንስ የሳለው ይህ ሥዕል "አይሁድ በኢየሩሳሌም እንደ ሰቀሉኝ አንተ ደግሞ ሁለተኛ ሰቀልከኝ?" የሚል ድምፅ አሰምቷል፡፡ ስሎ ሲጨርስ ዮሐንስ ቢስመው ከንፈሩ ከስዕሉ ጋር ተጣብቆ ቆይቷል፡፡ ይህ ሁሉ ከስዕሉ የታየው ተአምራት ነው፡፡ "አይሁድ የሰቀሉት ራቁቱን ነበር ከለሜዳ አስታጥቆ መሳል የተጀመረው ከዚያ ወዲህ ነው" እያሉ የሀገራችን ሊቃውንት ይተርካሉ፡፡

ስለጌታ ሥዕል ሁለተኛው ምንጭ (መነሻ) ጲላጦስ ለጢባርዮስ ቄሳር ስለ ጌታና ስለእናቱ እመቤታችን የላከው ሥዕላዊ መግለጫም አለ፡፡ ጲላጦስ በቅዱስ መጽሐፍ እንደሚታወቀው በፍልስጥኤም የሮም መንግስት እንደራሴ የነበረና በጌታም ሞት የፈረደ ነው፡፡ ወደ ጢባርዮስ ቄሳር የላከው መልዕክት እንደሚከተለው ነው፡፡ "ለጢባርዮስ ቄሣር፤ ሰላም ላንተ ይህን ኢየሱስ ስለሚባለው ሰው ግርማዊነትህ ለማወቅ የጠየቀውን ለማሟላት ከዚህ የሚከተለውን እጽፍልሃለሁ፡፡ በዚህ እኔን እንደራሴህ አድርገህ በሾምኸኝ በፍልስጥኤም ምድር እጅግ በጣም የተለየ መልክና ሥልጣን ያለው አንድ ሰው ተነስቷል፡፡ ታላቅ መምህርና ነቢይም ነው ይሉታል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ግን የእግዚአብሔር ልጅ ነው ይላሉ፡፡ ስሙ ኢየሱስ ይባላል እንደ እውነቱ ከሆነ ቄሳር ሆይ ይህ ኢየሱስ የተባለ ክርስቶስ በየጊዜው ድንቅ ድንቅ ተአምራት ያደርጋል ሙታንን ያስነሳል፤ ድውያንን ከማናቸውም ደዌና ሕመም ይፈውሳል፡፡ ከዚህም ጋር ጥልቅና መንፈሳዊ በሆነ ትምህርቱ መላዋን ኢየሩሳሌምን አስደንቋታል፡፡ አቋሙ አካሉ ግርማ ያለውና መልኩም አንጸባራቂ ጸጋ የተሞላበት በመሆኑ ማናቸውም የሚያየው ሁሉ ይወደዋል ይፈራዋልም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ቀላ ያለው መልኩና መሐል ለመሐል ተከፍሎ የሚታየው ጽሕሙ የሚሰጠው ውበት ፍጹም ግምት የሌለው ነው፡፡ የፊቱ ቅርጽ መልአካውያን አይኖቹና የጥቁር ወርቃማ ጠጉሮቹም አወራረድ በሚሰጡት የተንጸባረቀ ውበት ማንም ሰው ቢሆን ለረጅም ጊዜ አተኩሮ ሊመለከተው አይችልም፡፡ የሚመስለው እናቱን ነው፡፡ እሷም ደግሞ በዚህ ክፍለ ሀገር በማንም ላይ ያልታየ ውበትና የትሕትና መልክ ያላት ናት፡፡ ቆራጥ ከባድና የሚያከራክሩ ንግግሮቹም በውስጣቸው የሚገኘው ፍጹም የሆነ የመንፈስ ልዕልናን የዕውቀት መጠናቸው ከታላላቅ ዐዋቂዎች ተብለው ከሚገመቱት ሰዎች እጅግ አድርጎ የራቀ የጠለቀ ምስጢር አላቸው፡፡ በተግሣጽና በእዝናት ጊዜም በጣም ኃይለኛ ነው፡፡ በማስተማርና በማበረታታት ጊዜ ደግሞ ትሑት ተወዳጅና ልብ የሚመስጥ ነው፡፡ ራሱን ሳይከናነብና መጫሚያ ሳይጫማ በእግሩ ይሔዳል፡፡ በሩቅ የሚያዩት አንዳንዶች ይስቁበታል፤ ነገር ግን ወደፊቱ ሲቆሙና ሲቀርቡ በመንቀጥቀጥ ያደንቁታል፡፡ ማንም ቢሆን ሲስቅ አየሁት የሚል የለም፡፡ ነገር ግን ብዙዎች ሲያለቅስ አይተውታል፡፡ የቀረቡት ሁሉ ብዙ ሥራና ፈውስ ማግኘታቸውን ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ገዥና ተገዥ ሁሉም (ባባቴ ፊት) በእግዚአብሔር ፊት እኩል ናቸው፡፡ ምንም ልዩነት የላቸውም ብሎ ስለሚያስተምር የግርማዊነትህ አጥፊ ሳይሆን አይቀርም በማለት ብዙ ሰዎች እየመጡ ይነግሩኛል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ብታዝዘኝ ወዲያውኑ ትእዛዝህ የሚፈጸም ይሆናል፡፡ ጤናሁን፤ ፒ ሌንቱሎ"

በቤተ ክርስቲያን አባቶች የታሪክ መዝገብ ደግሞ ስለ ጌታ ሥዕል በተአምራታዊ አገላለጥ የተጻፉ ብዙ አስተያየቶች አሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊ አውሳብዮስ እንደጻፈው አብጋር የተባለው የዑር ንጉሥ ከደዌው የተፈወሰው የጌታን ሥዕል ባየ ጊዜ ነው ይላል፡፡ ሙሉው ታሪክ እንደሚከተለው ነው፡፡ "አብጋር" ስመ መንግስት ነው፡፡ ዓፄ ጃንሆይ እንደማለት "አባጋር፡፡ እንዲሉ ዛር አንጋሹን፡፡ ኡር በእመስጰጦምያ የምትገኝ ትንሽ ከተማ ናት፡፡ ጽርዓውያን "ኤዴሣ" ይሏታል፡፡ በኛም "ሮሐ" ትባላለች፡፡ አብጋሮች በዑር መንገሥ የጀመሩት ከጌታ ልደት በፊት ከ፻፴፪-፪፻፲፮ ከጌታ ልደት በኋላ ነው፡፡ በጌታ ጊዜ የነበረው አብጋር ዮካማ (ዑካማ) ይባል ነበር አምስተኛው ወይም ሰባተኛው አብጋር ነው፡፡ ይህ አብጋር ዮካማ ከጌታ ጋር ይጻጻፍ እንደነበር አውሳብዮስ ይተርካል፡፡ አውሳብዮስ ታሪኩን ሰፋ በማድረግ ሲያብራራ እንዲህ ይላል፡፡ በማይድን በሽታ ተይዞ የሚሠቃይ በኤፍራጥስ ወንዝ በላይ የነገሠ አብጋር ንጉስ ነበር፡፡ በዘመኑ ለነበረው ለጌታ ለኢየሱስ ክርስቶስ መልእክት (ጦማር) ጽፎ የግል ታማኙ ለነበረው ለግምጃ ቤቱ ሹም ሰጥቶ ወደ ኢየሩሳሌም ላከው ይህ ሰው በአብጋር ቤተ መንግስት ሥዕል በመሳል የታወቀ ነበር፡፡ ደብዳቤው እንዲህ የሚል ነው፡፡

"ስለ አንተና ስለምታደርገው ተአምራት እሰማለሁ፤ ያንተ ማዳን እንደሌሎቹ ዐቀበተ ሥራይ ሥርምሰህ፤ ቅጠል በጥሰህ አይደለም፡፡ አንተ ያዳንኸው ተረፈ ደዌ የለበትም፡፡ እንደሰማሁት ዕውራን እንዲያዩ ታደርጋለህ መጻጉዓን ጉልበታቸው ቀንቶላቸው እንዲራመዱ ታደርጋለህ ልሙጻንን ታነጻለህ ርኩሳን መናፍስትን ታሳድዳለህ በማይድን በሽታ የተያዙትን በምሕረትህ ትፈውሳቸዋለህ ሙታንን ታነሳለህ፡፡ ስለዚህ ወደኔ እንድትመጣና ከዚህ ከሚያሰቃየኝ ደዌዬ እንድትገላግለኝ፤ ለእኔም ምሕረት እንዲደርሰኝ ይህችን የልመና ደብዳቤ ጻፍሑልህ፡፡ አይሁድ ባንተ ላይ ክፉ ነገር እንዳሰቡና ክፉ ሊያደርጉብህም እንደከጀሉ እሰማለሁ፡፡ ከተማዬ በጣም ትንሽ ናት፤ ትነስ እንጂ በጣም ውብ ናት ለሁለታችን ትበቃናለች፤ እባክህ ና፡፡" የሚል ደብዳቤ ጽፎ ለጌታ ላከለት፡፡ ጌታም የሚከተለውን መለሰለት፡፡ "አብጋር ሆይ ሳታየኝ ስላመንህብኝ ብፁዕ ክቡር ነህ፤ ስለእኔ ተጽፏልና የሚያዩኝ እንዲንቁኝ የማያዩኝ ግን እንዲያምኑብኝ፡፡ ከሔድሁ በኋላ ከደዌህ እንዲፈውስህና ላንተና ለቤተ ሰዎችህም የሕይወትን ቃል እንዲያስተምራችሁ ከደቀመዛሙርቴ አንዱን እልክልሃለሁ፡፡ ከተማህም የተባረከች ትሆናለች፤ ጠላቶች አይገዟትም፡፡" ብሎ መልስ ላከለት፡፡ ጌታ ካረገ በኋላ ከአስራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ ቶማስ (ዕፃው በእስያ ስለነበር) ከሰብአ አርድእት አንዱን ታዴዎስን ወደ ዑር ላከው፤ ታዴዎስም እዚያ እንደደረሰ ለጊዜው ያረፈው ጥንት በፍልስጥኤም በሚያውቀው በአንድ አይሁዳዊ ቤት ነበር፡፡ ከዚያ ሁኖ በማስተማርና ተአምራት በማድረግ ጥቂት እንደቆየ በቤተ መንግስትም ዜናው ተሰማ፡፡ ወዲያውም ተጠርቶ ወደ ቤተ ምነግስት ሔደ፡፡ ታዴዎስ ገና ሲገባ ንጉሱ አብጋር አስደናቂ ግርማ በታዴዎስ ገጽ ላይ አየ፡፡ በቤተ መንግስቱ የነበሩት ባለሟሎቹና የወንድ መኳንንት የሴት ወይዛዝርት ግን ምንም እንኳ ለአብጋር የተገለጸው ባይገለጽላቸው፤ ታዴዎስ እዚያ በመገኘቱ አንክሮና ተመስጦ ሳያድርባቸው አልቀረም፡፡ ንጉሱና ታዴዎስ ሲወያዩ ከቆዩ በኋላ በመጨረሻ ተዴዎስ፤ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እጄን አጭንብሃለሁ ብሎ እጁን ጫነበት፤ በዚህ ጊዜ አብጋር ከነበረበት ሁሉ ደዌ ተፈወሰ፡፡ ታዴዎስም የሕይወትን ቃል እያስተማረ በዚያች ቦታ ብዙ ቆየ፡፡ የከተማዪቱም ነዋሪዎች ክርስቲያኖች ሆኑ አውሳብዮስ ታሪኩን እዚሁ ላይ ያበቃል፡፡

ሌሎች የኋላ አባቶች ግን ይህን ታሪክ ሳይለውጡ አብጋር ወደ ጌታ የላከው ሰው ሰዓሊ ስለነበር ወዲያው ጌታን ሲያይ ልቡ ስለተመሰጠ ስዕሉን በንድፍ ለማስቀረት ፈለገ፡፡ ጌታን በሚያነጋግርበት ጊዜ ዓይኑን ጣል እያደረገ የጌታን ገጽ በወረቀት ነድፎት ነበር፡፡ ወደ ሀገሩ ሲመለስ ያንን ለአብጋር አሳየው፤ እሱም ባየው ጊዜ በፍጹም እምነት ከመሬት ወድቆ ሰገደ ያን ጊዜም ከደዌው ተፈወሰ ይላሉ፡፡ ከዚህ በማያያዝ ይህ ሥዕል ገባሬ ተአምር ስለሆነ ሁሉ ሊሰግድለት ይገባል ብሎ በሕዝብ መሰብሰቢያ ዐደባባይ ከፍ ያለ ቦታ አበጅቶ እዚያ ላይ እንዲሰቅል አዘዘ፡፡ "በአብጋርና በልጁ ዘመነ መንግስት ሁሉም እየመጣ ለዚህ ሥዕል ሲሰግድ ኑሯል፡፡

አውሳብዮስ ዘቂሳርያ ስለጌታ ሥዕል ሌላ ምንጭ ያመለክተናል፤ እሱ እንደሚለው "በወንጌል የታወቀችው እንተ ደም ይውኅዛ ውለታ ለመክፈል ስትል የቅርጽ ሐውልት አሠርታለት ነበር ይላል፡፡ የቤሮኒኪም ታሪክ ለጌታ ሥዕል ጥሩ መነሻ ነው፡፡ ጌታ በዕለተ ዓርብ ደሙን እያንጠፈጠፈ መስቀሉን ተሸክሞ ወደ ጎልጎታ በሚወጣበት ጊዜ መስቀሉ ከብዶት ደሙ ዓይኑን ጋርዶት አይታ ልቧ በሐዘን ስለተነካ ከተከተሉት አንዷ ቤሮኒኪ ሻሿን አውልቃ ፊቱን እንዲያድፍበት ወረወረችለት፤ አድፎ ሲመልስላት ገጹ ከሻሿ ላይ ታትሞበት ቀረ ይባላል፡፡ ስለጌታ ሥዕል መነሻ ታሪካዊና ተአምራታዊ ምንጮች ብዙ አሉ፡፡

ዮሐንስ ወንጌላዊና ጴጥሮስ በባዶው መቃብር ውስጥ ገብተው ያዩት ጌታ ተገንዝቦት የነበረው ከፈንና (ሰበን) መጠምጠሚያ ላይ የጌታ አካል ታትሞበት ነበር፡፡ የሚል የቤተ ክርስቲያን ትውፊት አለ፡፡ ስለጌታ ሥዕል ከየት መጣ ከሚሉ በከፊሉ ይህ ነው፡፡

ስለ እመቤታችን ሥዕል ደግሞ መጀመሪያ የሳላት ሉቃስ ነው ይባላል፡፡ በኛም በቤተ ክርስቲያን ያሉት የመዝሙርና የጸሎት መጻሕፍት የእመቤታችንን ሥዕል ሉቃስ መሳሉን ይናገራሉ፡፡

"ሰላም ለስዕልኪ እንተ ሠዓላ በእዱ ሉቃስ ጠቢብ እምወንጌላውያን አሐዱ

 

 
 

No comments:

Post a Comment