Wednesday, January 27, 2016

ሊቀ ሰማዕታት ፀሐይ ዘልዳ ቅዱስ ጊዮርጊስ፡-


                                 
    ሊቀ ሰማዕታት ፀሐይ ዘልዳ ቅዱስ ጊዮርጊስ፡-
     ጊዮርጊስ ማለት ‹‹ኮከብ ብሩህ፣ ፀሐይ›› ማለት ነው፡፡ ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ሀገሩ ፍልስጤም ልዩ ስሟ ልዳ ሲሆን የተወለደው በ277 ዓ.ም ጥር 20 ቀን ነው፡፡ አባቱ ዞሮንቶስ ወይም አንስጣስዮስ የ...ልዳ መኳንንት ሆኖ ተሹሞ ይኖር ነበር፤ እናቱ ቴዎብስታ ወይም አቅሌስያ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ሌላ ማርታና እስያ የሚባሉ ሁለት ሴት ልጆችን ወልዳለች፡፡

    ቅዱስ ጊዮርጊስ ዐሥር ዓመት በሆመው ጊዜ አባቱ ስለሞተ ሌላ ደግ ክርስቲያናዊ መስፍን ወስዶ አሳደገው፡፡ መድፍኑም በጦር ኃይል አሰለጠነው፡፡ ሃያ ዓመትም በሞላው ጊዜ መስፍኑ የ15 ዓመት ቆንጆ ልጅ ነበረችውና እርሷን አግብቶ ሀብቴን ወርሶ ይኑር ብሎ ድግስ ሲያስደግስ ጌታችን ቅዱስ ጊዮርጊስን ለዚህ አላጨውምና የመስፍኑን ነፍስ ወሰደ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም ኀዘኑን ጨርሶ ወደ ቤሩት ሀገር ሄደ፡፡ በቤሩት ደራጎንን ያመልኩና ሴት ልጆቻቸውን ይገብሩለት ስለነበር ሰማዕቱ ደራጎኑን በኃይለ መስቀል ድል ነስቶት ሕዝቡን ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር አስገብቷቸዋል፡፡
    ወደፋርስ ቢመለስ ዱድያኖስ ሰባ ነገሥታት ሰብስቦ ሰባ ጣዖታት አቁሞ ሲሰግድ ሲያሰግድ ቢያገኛቸው ለሃይማኖቱ ቀናዒ ነውና ከቤተመንግስቱ ገብቶ በከሃዲያኑ ሰባው ነገሥታት ፊት ክርስቲያን መሆኑን በመመስከር የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት መሰከረ፡፡ ዱድያኖስም ማንነቱን ከተረዳ በኋላ ‹‹አንተማ የኛ ነህ በዐሥር አህጉር ላይ እሾምሃለሁ የኔን አምላክ አጵሎንን አምልክ›› አለው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም ‹‹ሹመት ሽልማትህ ለአንተ ይሁን እኔ አምላኬ ኢየሱስ ክርስቶስን አልክደውም›› አለው፡፡ በዚህ ጊዜ ዱድያኖስ እጅግ ተናዶ ብዙ አሠቃቂ መከራዎችን አደረሰበት፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን ጌታችንን ‹‹ይህን ከሃዲ እስካሳፍረው ድረስ ነፍሴን አትውሰዳት›› በማለት መከራውን ይታገስ ዘንድ ለመነው፡፡ እግዚአብሔርም ጸሎቱን ሰምቶ ፈቃዱን ይፈጽምለት ብዙ በመከራው ሁሉ ጽናትን ሰጥቶታል፡፡ ሦስት ጊዜም ከሞት አስነሥቶታል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም የደረሱበት እጅግ አሠቃቂ መከራዎች የሰው ኅሊና ሊያስባቸው እንኳን የማይችላቸው ናቸው፡፡
    በመጀመሪያም ዱድያኖስ በእንጨት ላይ ካሰቀለው በኋላ ሥጋውን በመቃን አስፈተተው፣ ረጃጅም ችንካሮች ያሉበት የብረት ጫማ አጫምቶት ሂድ አለው፡፡ ጌታችንም ቅዱስ ሚካኤልን ልኮለት ፈውሶታል፡፡ ዳግመኛም በሰባ ችንካሮች አስቸንክሮ በእሳት አስተኩሶ አናቱን በመዶሻ አስቀጥቅጦ በሆዱ ላይ የደንጊያ ምሰሶ አሳስሮ እንዲያንከባልሉት አደረገ፡፡ ሥጋውንም በመጋዝ አስተልትሎ ጨው ነሰነሰበት፡፡ ሥጋውም ተቆራርጦ መሬት ላይ ወደቀ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈቀ ሌሊት በእጁ ዳስሶ ከፈወሰውና ‹‹ገና ስድስት ዓመት ለስሜ ትጋደላለህ፣ 3 ጊዜ ትሞታለህ፣ በ4ኛውም ታርፋለህ›› ካለው በኋላ በመከራውም ሁሉ እርሱ እንደማይለየው ነገረው፡፡
    ዱድያኖስ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከዚያ ካደረሰበት አሠቃቂ መከራዎች ሁሉ ድኑ ፍጹም ጤነኛ መሆኑን በተመለከተ ጊዜ እጅግ ደንግጦ ‹‹የሚያሸንፍልኝ ቢኖር ብዙ ወርቅ እሰጠዋለሁ›› ብሎ ተናገረ፡፡ አትናስዮስ የተባለ መሰርይ አንዲትን ላም በጆሮዋ ሲያንሾካሹክባት ለሁለት ተሰንጥቃ ስትሞት ለንጉሡ አሳየውና ቅዱስ ጊዮርጊስን እንዲሚያሸንፍ ምልክት አሳየ፡፡ ንጉሡም ያሸንፍልኛል ብሎ ደስ አለው፡፡ መሰርይውም ሆድ በጥብጦ አንጀት ቆራርጦ የሚገድል መርዝ ቀምሞ አስማተ ሰይጣን ደግሞበት እንዲጠጣው ለቅዱስ ጊዮርጊስ ሰጠው። ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን ስመ እግዚአብሔርን ጠርቶ ቢጠጣው እንደ ጨረቃ ደምቆ እንደ አበባ አሸብርቆ ተገኝቷል፡፡ በዚህም ጊዜ ጠንቋዩ ማረኝ ብሎ ከእግሩ ሥር ወደቀ፡፡
    ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን በመንኰራኩር አስፈጭቶ ከትልቅ ጉድጓድ ጥሎት ደንጊያ ዘግቶበት አትሞበት ሄደ፡፡ ጌታችንም የተፈጨውን የቅዱስ ጊዮርጊስ ሥጋ በእጁ ዳስሶ ፈውሶታል፡፡ ወደ ከሃዲውም ንጉሥ ተመልሶ ‹‹አምላኬ ከሞት አዳነኝ›› በማለት መሰከረ፡፡ ንጉሡም ዳግመኛ በብረት አልጋ አስቸንክሮ ከበታቹ እሳት አነደደበት ነገር ግን እሳቱ ደሙ ሲንጠባጠብበት ጠፍቷል፡፡ ጌታችንም ፈወሰው፡፡ ከዚህም በኋላ ዱድያኖስ ቅዱስ ጊዮርጊስን ‹‹ኢየሱስ አምላክ መሆኑን አሳየኝ›› ቢለው የለመለሙትን ዕፅ አድርቆ፣ የደረቁትን ደግሞ አለምልሞ፣ ከሞቱ 430 ዓመት የሆናቸውን ሙታንን አስነሥሰቶ አሳይቶታል፡፡ ነገር ግን ንጉሡ ልቡ ክፉ ነውና በርኃብና በጽም ይሙት ብሎ ምንም ከሌላት መበለት ቤት አሳስሮታል። እርሷም የሚቀመስ ስትፈልግ ቤቷን በእህል አትረፍርፎ የታሰረበትን ግንድ ማለትም የቤቱን ምሰሶ አለምልሞታል፡፡ ልጇም ጆሮው የማይሰማ ነበርና ፈወሰላት፡፡ መበለቲቷንም ከነልጆቿ አጥምቆአቸው መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ከእስራቱ ፈትቶት ተመልሷል፡፡
    ዳግመኛም ንጉሡ ዱድያኖስ ጭፍሮቹን ‹‹በመንኰራኩር ፈጭታችሁ አጥንቱን ደብረ ይድራስ ተራራ ላይ ወስዳችሁ ዝሩት›› ብሎ አዘዛቸው፡፡ ጭፍሮቹም የቅዱስ ጊዮርጊስን ሥጋ በመንኰራኩር ፈጭተው ወስደው በተራራው ላይ ቢረጩት ሥጋው ያረፈበት ሳር፣ ቅጠሉ፣ ደንጊያው፣ እንጨቱ ሁሉ ‹‹ጊዮርጊስ ቅዱሱ ለእግዚአብሔር፣ ጊዮርጊስ ሰማዕቱ ለእግዚአብሔር›› እያሉ አመስግነዋል፡፡ አሁንም ጌታችን ለሦስተኛ ጊዜ ከሞት አስነሣውና ሥጋውን ፈጭተው በተራራም ላይ ሥጋውን በትነውት ወደ ንጉሡ የሚመለሱትን ወታደሮች በመንገድ ከኋላቸው ሄዶ ደረሰባቸውና ‹‹ቆዩኝ ጠብቁኝ›› አላቸው፡፡ እነርሱም እጅግ ደንግጠው ይህ እንዴት እንደሆነ ሲጠይቁት ‹‹አምላኬ ከሞት አዳነኝ›› አላቸው፡፡ ጭፍሮቹም እጅግ ደንግጠው ከእግሩ ስር ወድቀው ይቅር በለን ብለው በአምላኩ እንደሚያምኑ መሰከሩለት፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም ከመሬት ላይ ውሃ አመንጭቶ በጸሎት ጌታችንን ቢጠይቅ ቅዱስ ዮሐንስ መጥቶ አጥምቋቸዋል፡፡ እነርሱም በንጉሣቸው ፊት ሄደው ስለጌታችን በመመስከር በሰማዕትነት ዐርፈዋል፡፡ ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዐፅሙ ተቃጥሎ አጥንቱ ተፈጭቶ በደብረ ይድራስ ተራራ ላይ የተበተነው በዛሬዋ ዕለት ነው፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን በጸሎቱ ይማረን፤ የዓሥራት አገሩን ቅድስት ኢትዮጵያን ይጠብቅልን፡፡
    /////////////////////
    የመጀመሪያው የአፍሪካ ሐዋርያ ቅዱስ አቤላክ (ባኮስ)፡- ይኽም ጃንደረባ በመጀመሪያ የኢትዮጵያ ንግሥት የሆነችው የህንደኬ የገንዘቧ ሁሉ ኃላፊና አዛዥ የነበረ ነው፡፡ ከአባቱ እብነ መላክ ከእናቱ ስሂነ ሕይወት ታኅሣሥ 29 ቀን ተወለደ፡፡ ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ ወደ ኢየሩሳሌም በመጓዝ ለበዓለ ፋሲካ በቤተ መቅደስ ይሰግዱ እንደነበረው ሁሉ ይኽም ጃንደረባ ከ4 ሺህ ማይልስ በላይ ተጉዞ ኢየሩሳሌምን ተሳልሞ በመለስ ላይ ነበረ፡፡ ከኢየሩሳሌም ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ የነቢዩ ኢሳይያስን መጽሐፍ በተለይም ስለ ጌታችን መከራ መስቀል በዝርዝር የሚናገረውን ክፍል 53ኛውን ምዕራፍ ያነብ ነበር ነገር ግን ጃንደረባው ስለማን እንደሚናገር አልገባውም ነበር፡፡ በዚህም ጊዜ እግዚአብሔር በአካባቢው ወንጌልን ይሰብክ የነበረውን ሐዋርያውን ቅዱስ ፊሊጶስን ላከለት፡፡ እርሱም ጃንደረባው ያነበው የነበረውን መጽሐፍ ተረጎመለት፣ የከበረች ወንጌልን ሰበከለት፣ በመጨረሻም አጠመቀው፡፡ ሐዋርያው ባጠመቀውም ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በጃንደረባው ላይ ወረደ፡፡ ይኽም ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ የሐዋርያት ሥራ ላይ እንዲህ ተብሎ ነው የተጻፈው፡-
    ‹‹የጌታም መልአክ ፊልጶስን ‹ተነሥተህ በደቡብ በኩል ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ ወደሚያወርደው ምድረ በዳ ወደ ሆነ መንገድ ሂድ› አለው፤ ተነሥቶም ሄደ፡፡ እነሆም ህንደኬ የተባለች የኢትዮጵያ ንግሥት አዛዥና ጃንደረባ የነበረ በገንዘቧም ሁሉ የሠለጠነ አንድ የኢትዮጵያ ሰው ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ነበር፤ ሲመለስም በሰረገላ ተቀምጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ ነበር፡፡ መንፈስም ፊልጶስን ‹ወደዚህ ሰረገላ ቅረብና ተገናኝ› አለው፡፡ ፊልጶስም ሮጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ሲያነብ ሰማና ‹በውኑ የምታነበውን ታስተውለዋለህን?› አለው፡፡ እርሱም ‹የሚመራኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል?› አለው፡፡ ወጥቶም ከእርሱ ጋር ይቀመጥ ዘንድ ፊልጶስን ለመነው፡፡ ያነበውም የነበረ የመጽሐፉ ክፍል ይህ ነበረ፡- ‹እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፣ የበግ ጠቦትም በሸላቹ ፊት ዝም እንደሚል እንዲሁ አፉን አልከፈተም፡፡ በውርደቱ ፍርዱ ተወገደ፤ ሕይወቱ ከምድር ተወግዳለችና ትውልዱንስ ማን ይናገራል?› ጃንደረባውም ለፊልጶስ መልሶ ‹እባክህ ነቢዩ ይህን ስለ ማን ይናገራል? ስለ ራሱ ነውን ወይስ ስለ ሌላ?› አለው፡፡ ፊልጶስም አፉን ከፈተ ከዚህም መጽሐፍ ጀምሮ ስለ ኢየሱስ ወንጌልን ሰበከለት፡፡ በመንገድም ሲሄዱ ወደ ውኃ ደረሱ፤ ጃንደረባውም ‹እነሆ ውኃ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድር ነው?› አለው፡፡ ፊልጶስም ‹በፍጹም ልብህ ብታምን ተፈቅዶአል› አለው፡፡ መልሶም ‹ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ አምናለሁ› አለ፡፡ ሰረገላውም ይቆም ዘንድ አዘዘ፣ ፊልጶስና ጃንደረባው ሁለቱም ወደ ውኃ ወረዱ፣ አጠመቀውም፡፡ ከውኃውም ከወጡ በኋላ የጌታ መንፈስ ፊልጶስን ነጠቀው፤ ጃንደረባውም ሁለተኛ አላየውም፤ ደስ ብሎት መንገዱን ይሄድ ነበርና፡፡ ፊልጶስ ግን በአዛጦን ተገኘ፣ ወደ ቂሣርያም እስኪመጣ ድረስ እየዞረ በከተማዎች ሁሉ ወንጌልን ይሰብክ ነበር፡፡›› ሐዋ 8፡26-40፡፡
    ይህን ለእኛ ለኢትዮጵያውን እጅግ የሚያኮራን ታሪካችን ነው፡፡ ዛሬ በእጃችን ላይ በመገኘው መጽሐፍ ውስጥ ባይኖርም በቆዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥራዞች ላይ ግን ሐዋርያው ቅዱስ ፊሊጶስ ጃንደረባውን ባጠመቀውም ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በኢትዮጵያው ጃንደረባ ላይ እንደወረደ ተጽፏል፡፡ (ዝኒ ከማሁ ገጽ 87፣ v.39.cord.alexand. in bible reg. angl-alique plures codd.mss)
    ሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስ ጃንደረባውን ያጠመቀበት ወንዝ ‹‹ቤተ ሳሮን›› በተባለችውና እስከዛሬም ድረስ ከኢየሩሳሌም 20 ማይልስ ርቀት በምትገኘው መንደር በኬብሮን መካከል ባለው ኮረብታ ሥር የሚመነጭ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን የታሪክ ጸሐፊ የሆነው ሊቁ ቅዱስ ጀሮም ጃንደረባውን ‹‹የኢትዮጵያውያን ሐዋርያ›› በማለት ይጠራዋል፡፡ በሰፊው ለኢትዮጵያውያን ወንጌልን የሰበከ እርሱ ነውና፡፡
    ሐዋርያው ባኮስ (አቤላክ) ከዚየሩሳሌም ወንጌልን ተምሮና ተጠምቆ ወደ አክሱም እንደተመለሰ በመጀመሪያ ያጠመቀው ንግሥቲቷን ሕንደኬን ነው፡፡ ከእርሷም በኋላ መኳንንቱና መሳፍንቱ ሁሉ አምነው በባኮስ እጅ ተጠመቁ፡፡ ይኸውም በ34 ዓ.ም ነው፡፡ ከዚህም በኋላ ባኮስ እስከ ኑብያ ድረስ ሄዶ ወንጌልን ሰብኮ ብዙዎችን አሳምኖ አጥምቋል፡፡ በዚህም ጊዜ ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በባኮስ እየተሰጠ የነበረውን የወንጌል ብርሃን የበለጠ እንዲበራ አድርጓል፡፡ ከጃንደረባውም ጋር ሆነው በብዙ ቦታዎች አብረው ወንጌልን ሰብከው አምልኮተ ጣዖትን አጥፍተዋል፡፡
    ከዚህም በኋላ ባኮስ ወደ የመን በመሄድ በዚያም ክርስትናን በማስተማር ብዙዎችን አሳምኖ ካጠመቀ በኋላ ወደ ፐርሺያ ከዚያም ወደ ሕንድ በመሄድ ሐዋርያዊ አገልግሎቱን ፈጽሟል፡፡ በመጨረሻም ጥንት ታፕሮባና (taprobana) ዛሬ ሲሎን በምትባለው ደሴት ወንጌልን በማስተማር ላይ እያለ በሰማዕትነት እንዳረፈ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ (lives of the most eminent fathers of the church, page 87.) በሌላም በኩል ሐዋርያው ባኮስ (አቤላክ) ከመጠመቁ በፊት 35 ዓመት ከተጠመቀ በኋላ ደግሞ 41 ዓመት ኖሮ በኢየሩሳሌምም 3 ዓመት ተቀምጦ ወንጌልን ዞሮ ካስተማረ በኋላ በመጨረሻ በ79 ዓመቱ ጥር 18 ቀን በሰሜን ተራራዎች ላይ ቅዱስ ያሬድ በተሰወረበት ቦታ እንደተሰወረ ሊቀ ብርሃናት መርቆሬዎስ አረጋ ጽፈዋል፡፡
    መጽሐፍ ቅዱሱ እንደሚመሰክረው ‹‹መንፈስም ፊልጶስን ‹ወደዚህ ሰረገላ ቅረብና ተገናኝ› አለው፡፡ ፊልጶስም ሮጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ሲያነብ ኢትዮጵያዊውን ጃንደረባ አገኘው›› ተብሎ እንደተጻፈ (ሐዋ 8፡27) የእኛ የኢትዮጵያዊውን የመጀመሪያው መምህራኖቻችን ሐዋርያት ናቸው፣ ኢትዮጵያም ድረስ መጥተው ወንጌልን የሰበኩ ብዙ ሐዋርያት አሉና፡፡ እነሱንም ለእኛ ወንጌልን እንዲሰብኩ የላከልን ራሱ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ የዛሬን አያደርገውና በጌታችን የተመረጡ የከበሩ ሐዋርያት እንኳን ወንጌልን በዓለም ለመስበክ ገና ከኢየሩሳሌም ባልወጡበት ወቅት በ34 ዓ.ም ነው ቅድስት አገራችን ኢትዮጵያ በክርስቶስ አምና ወንጌልን የተቀበለችው፡፡ በምድሪቱም ላይ ወንጌል መነገር የጀመረው ከዚሁ ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ ዛሬ ግን ማንም ሥጋዊ አስተሳሰብ ብቻ ያለው ሁሉ ለሥጋዊ ጥቅሙ ሲል የተለየ ወንጌልን በመስበክ ‹‹የሱሴ›› የሚል የስም ታፔላ ብቻ እየለጠፈ ሕዝባችንን በተዘዋዋሪ መንገድ የሰይጣን ተገዥ አደረገው፡፡ አሁን አሁንማ ጭራሽ ፓስተሮቻቸው ሕዝቡን ካስካዱትና ማንነቱን ካሳጡት በኋላ ፈጽሞ አእምሮ እንደሌለው እንስሳ ይጫወቱበት ጀመር፡፡ በየአዳራሹ ግቢ ውስጥ ሲፈልጉ ሳር ያስግጡታል፣ ሲፈልጉ እባብ ያስበሉታል፣ ራቁቱን ወለል ላይ እያስተኙ በጫማቸው ይረግጡታል፣ አልፎም ተርፎ የእርኩሰታቸውና የብልግናቸው ተባባሪ በማድረግ ‹‹ቅዱስ ወተት ነው›› እያሉ የወንድ የዘር ፈሳሻቸውን ያጠጡታል፡፡
    ያገሬ ልጅ…. አእምሮ እንደሌለው እንስሳ ሆነህ ለሰይጣን ተላልፈህ እንደተሰጠህ አትቅር እባክህ! ትንቢቶችም የሚፈጸሙብህ ሆነህ በነፍስህ ለዘለዓለም አትጎዳ፡፡ እነሆም የከበሩ ሐዋርያት “በግልፅ በኋለኞቹ ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጠውን የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ ሃይማኖትን ይክዳሉ” /1ኛ ጢሞ 4:1/ ብለው የነገሩህ አስታውስና የካድካትን የመጀመሪያዋን እውነተኛዋን ሃይማኖትህን መርምራት-እርሷ ብቸኛ የነፍስ መዳኛ መንገድ ናትና፡፡
    “ሐሰተኞች ነቢያት ደግሞ በሕዝቡ መካከል ነበሩ እንዲሁም በመካከላችሁ ደግሞ ሐሰተኞች አስተማሪዎች ይሆናሉ፤ እነርሱም የዋጃቸውን ጌታ እንኳ ክደው የሚፈጥንን ጥፋት በራሳቸው ላይ እየሳቡ የሚያጠፋ ኑፋቄን አሹልከው ያገባሉ” /2ኛ ጴጥ 2:1/ ተብሎም እንደተነገረ ልብህ በክፉዎች ከሃድያን የኑፋቄ ጦር እንደተወጋ አይቅር፡፡ “ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሡበት ዘመን ይመጣልና፤ ነገር ግን ጆሮቻቸውን የሚያሳክክ ስለሆነ፥ እንደ ገዛ ምኞታቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ያከማቻሉ። እውነትንም ከመስማት ጆሮቻቸውን ይመልሳሉ፥ ወደ ተረትም ፈቀቅ ይላሉ” /2ኛ ጢሞ4÷3/ ፤ “ጢሞቴዎስ ልጄ ሆይ፥ አስቀድሞ ስለ አንተ እንደ ተነገረው ትንቢት፥ በእርሱ መልካም ጦርነት ትዋጋ ዘንድ ይህችን ትእዛዝ አደራ እሰጥሃለሁ፤ እምነትና በጎ ሕሊና ይኑርህ፥ አንዳንዶች ሕሊናን ጥለው፥ መርከብ አለ መሪ እንደሚጠፋ፥ በእምነት ነገር ጠፍተዋልና” /1ኛ ጢሞ 1÷19/፤ “በቅዱሳን ነቢያትም ቀድሞ የተባለውን ቃል በሐዋርያቶቻችሁም ያገኛችኋትን የጌታንና የመድኃኒትን ትእዛዝ እንድታስቡ በሁለቱ እያሳሰብኋችሁ ቅን ልቡናችሁን አነቃቃለሁ። በመጨረሻው ዘመን እንደ ራሳቸው ምኞት የሚመላለሱ ዘባቾች በመዘበት እንዲመጡ ይህን በፊት እወቁ” /2ኛ ጴጥ 3:2/ እያሉ የከበሩ ሐዋርያት አስቀድመው የተናገሩትን ለመስተዋል ዐይነ ልቡናህን አብራው እንጂ እንደታወርክና ለሰይጣን ተላልፈህ እንደተሰጠህ አትቅር፡፡ እንደ ገዛ ምኞትህ ለራስህ መምህር ያደረካቸው እነርሱ በክርስቶስ ስም የሚነግዱ ዘባቾችና ርጉማን ስለዘሆኑ ነው ዛሬ በየአዳራሹ ሳር እያስጋጡ እባብ እያስበሉ ርቃንህን ወለል ላይ እያስተኙ የሚረግጡህ! እነርሱ መርከብ አለ መሪ እንደሚጠፋ በእምነት ነገር ፈጽመው ስለጠፉ ነው ዛሬ አንተንም በተዘዋዋሪ መንገድ ‹‹የሱሴ›› በሚል የስም ሽፋን ብቻ አምላክ የለሽ ያደረጉህ!!!
    ‹‹የመጀመሪያ እምነታችንን እስከመጨረሻው አጽንተን ብንጠብቅ ያን ጊዜ የክርስቶስ ተካፋዮች ሆነናልና›› (ዕብ 3፡14) ተብሎም እንደተጻፈ በዚህች የመጀመሪያ ሃይማኖት ጸንተህ ካላገኘህ በከንቱ ትደክማለህ እንጂ ክርስቶስ አያውቅህም፡፡ በመጨረሻው ፍርዱም ‹‹አላውቃችሁም… እናንተ አመጸኞች..›› ብሎ እንደሚፈርድ የተናገረው ራሱ ጌታችን በአንደበቱ ነው፡፡ ‹‹በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ ‹ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ! የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም፡፡ በዚያ ቀን ብዙዎች ‹ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ! በስምህ ትንቢት ልተናገርንምን በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን?› ይሉኛል፡፡ የዚያን ጊዜም ‹ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች ከእኔ ራቁ› ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ፡፡ ስለዚህ ይህን ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው ሁሉ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራ ልባም ሰውን ይመስላል፡፡›› ማቴ 7፡21-24፡፡ በዚህም መሠረት በፍርድ ጊዜ ‹‹አላቅቃችሁም›› የሚባሉት አመጸኞቹኮ በስሙ ብዙ ተአምራትን ያሳዩና ወንጌልን የሰበኩ ናቸው፡፡ ከክብር ባለቤት ከአምላካችን ከጌታችን የሚሰጣቸው መልስ ግን ‹‹ፈጽሞ አላውቃችሁም›› የሚል ነው፡፡ ከዚያም ሲያገለግሉት ለኖሩት ለሰጣንና ለመልእክተኞቹ ወደተዘጋጀላቸው ወደ ዘላለም ሥቃይ የጋዛሉ፡፡ ሚስኪኑ የሀገሬ ልጅ ያን ጊዜ አንተኮ ‹‹ጌታ ሆይ በስምህ ስጨፍርልህ ኖሬአለሁ…›› ከሚል ያለፈ ግብር አይኖርህም፡፡ በየአዳራሹ ከዚህ ያለፈ ነገር የለህምና፡፡ የክርስቶስ ተካፋይ ትሆን ዘንድ የምትሻስ ከሆነ የመጀመሪያ እምነትህን እስከመጨረሻው አጽና! ካለዚያ ስም አጠራርህ ፈጽሞ አይታወቅም፡፡ በዚህ ክፉ ዘመን የሚፈለግብህ ሰማዕትነት ቢኖር በእምነት ጸንቶ መገኘት ብቻ ነው፡፡ አሁን በዚህ ዘመን በቃል ሰይፍ እየታረድህ አምላክህን ከምትክድ ‹‹አንገትህን ለሰይፍ ሰውነትን ለእሳት›› የሚባልበት የድሮው ዘመን ሰማዕትነት በተሻለህ ነበር!!!
    አምላከ ቅዱሳን እስከመጨረሻው በመጀመሪያዋና በእውነተኛዋ እምነታችን ጸንተን መንግሥቱን የምንወርስ ያድርገን፡፡
    (ምንጭ፡ ገድለ ቅዱስ ጊዮርጊስ

No comments:

Post a Comment