Saturday, January 30, 2016

የሰሞኑ የሚዲያዎች ግርግር


ሰሞኑን የተለያዩ ድረ ገፆችን ካጨናነቁት አርእስተ ጉዳዮች መካከል አንዱ “አቡነ” መልከጼዴቅ በኦርጋንና በተመሳሳይ ዘመናዊ የሙዚቃ መሣርያዎች ስለ መዘመር የተናገሩት ንግግር ነው። ንግግራቸውን ተከትለው ለብዙ ዓመታት ደብቀውት የነበረውን አቋማቸውን በርካታ የኾኑ “የአቡኑ” ደቀ መዛሙርት ጉዳዩን ወደ ቤተ ክርስቲያን አሾልከው ለማስገባት ምእመናንም ሀሳባቸውን እንዲቀበሏቸው በብዙ በመጣር ላይ ይገኛሉ።“አቡነ” መልከጼዴቅ ሃሳባቸው ተቀባይነት እንዲያገኝ ርእሰ ጉዳዩን ከሁለት የቅርብ ጊዜ ታሪካዊ ሁኔታ ጋር ለማቆራኘት ሞክረዋል። አንደኛው በአፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት የተተረጎመው መጽሐፍ ቅዱስ ኦርጋን ወይም አርጋኖን የሚለውን ቃል መጠቀሙን፣ ሁለተኛም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ዘመነ ፕትርክና ዘመን ኦርጋን በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ላይ መዋሉን በአጽንኦት ገልጠዋል። ሁለቱንም ሃሳበቸውን በማስተዋል ስንመለከተው ሚዛን የማይደፉ ሆነው እናገኛቸዋለን።

1. ተተረጎመ ስለ ተባለው መጽሐፍ ቅዱስ
የመጽሐፍ ቅዱስ ሁለቱ ታላላቅ ክፍሎች ማለት ብሉይ ኪዳንና ሐዲስ ኪዳን በተለያዩ ቋንቋዎች መጻፋቸው ይታወቃል። ብሉይ ኪዳን በዕብራይስጥ ሐዲስ ኪዳን ደግሞ በግሪክ ቋንቋ ተጽፈዋል። በመዝሙረ ዳዊት ላይ የተጠቀሱትን የዜማ መሣርያዎች ለማወቅ መዝሙረ ዳዊት የተጻፈበት የዕብራይስጥ ቋንቋ ምን ብሎ እንደ ገለጣቸው በጥሞና መመርመሩ ሁላችንንም ከስሕተት ያድነናል። ይኽን ደግሞ ራሳቸው “አቡነ” መልከጼዴቅ አሳምረው ያውቁታል። አኮርድዮን የሚባለው የሙዚቃ መሣርያ ክሪስቲያን ፍሬድሪክ ቡሽማን (1775-1832) በተባለ ጀርመናዊ ለመጀመርያ ጊዜ እ.ኤ.አ በ1822 በዓለማችን ብቅ ማለቱን ታሪክ ይመሠክራል። ኦርጋን የሚባለው የሙዚቃ መሣርያ ጽንሰ ሃሳቡ ለመጀመርያ ጊዜ የተገለጠው ቅድመ ልደተ ከርስቶስ 246 ዓመት ግድም ነው። ይኽን ሃሳብ ያመነጨው ሰውም ሲቴሲቢየስ ዘእስክንድርያ በተባለ ሰው ነው። ይኽ ማለት ደግሞ መዝሙረ ዳዊት ተጽፎ ብሉይ ኪዳንም በሰባው ሊቃናት ወደ ግሪክ ከተተረጎመ በኋላ መሆኑ ነው። ስለዚህ በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን በተተረጎመው መጽሐፍ ቅዱስ ኦርጋን ወይም አኮርዲዮን የተባለው የሙዚቃ መሣርያ ተጠቅሷል የተባለው አባባል መጽሐፍ ቅዱስ ከተጻፈበት ዘመንና የሙዚቃ መሣርያዎቹ ኅልውናቸውን ካገኙበት ዘመን አንጻር ስንስተውለው ተቀባይነት የለውም። ምክንያቱም አንድ መሣርያ ኅልውና ሳያገኝ አገልግሎት ላይ ዋለ ያሰኛል፤ ወይም ትንቢት ተነግሮለት ነበር ብለን ለመሣርያዎቹ ነቢያት መሆን ካላማረን በስተቀር።
ኦርጋን በመጽሐፍ ቅዱስ ይቅርና በምዕራባውያን አብያተ ክርስቲያናት እንኳን ዕውቅና አግኝቶ ወደ ቤተ ክርስቲያናቸው የገባው እ.ኤ.አ 900 ዓ.ም አካባቢ ሲሆን ለተለያዩ ዝግጅቶች ብቻ አገልግሎት ላይ ይውል ነበር። በሂደትም ወደ ቤተ ክርስቲያናቸው ገብቶ የመዝሙራቸው ማጀቢያ ሊሆን ችሏል። ይኽም በቀደምት የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በምዕራቡም ሆነ በምስራቁ አብያተ ክርስቲያናት ኦርጋን ቦታ ያልነበረው በሂደት ሰዎች ያስገቡት መሆኑን እንረዳለን።
2. በብፁዕ ወቅዱስ ሰማዕቱ አቡነ ቴዎፍሎስ ዘመነ ፕትርክና ሥራ ላይ ውሏል ስለ ተባለው
ቅዱስነታቸው ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንደ ሰበካ ጉባኤ፣ እንደ ሰንበት ትምህርት ቤት የመሳሰሉ እጅግ ጠቃሚና ቋሚ አሠራሮችን ማስተዋወቃቸው ታሪክ የሚዘክረው አሁንም ቤተ ክርስቲያናችንን ኅልውናዋን እየጠበቁ ያሉ ናቸው። አዎ በቅዱስነታቸው ዘመነ ፕትርክናም ሆነ ከዚያን በኋላ አንዳንድ ሰዎች በኦርጋን ዘምረዋል። ግን ቅዱስነታቸው ኦርጋንን የቤተ ክርስቲያናችን የማመስገኛ መሣርያ ሆኖ እንዲያገለግል በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃ አስወስነው ነበርን? ለመሆኑ በርሳቸው ዘመነ ፕትርክናም ሆነ ቀደም ሲል ኦርጋንን ወደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያስገቡት ማን ናቸው? ጉዳዩ ዝርዝር ጥናት ቢጠይቅም አንዳንድ የቃል አስረጂዎች ሊቀ ሥልጣናት ሀብተ ማርያም ወርቅነህ የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አስተዳዳሪ በነበሩበት ዘመን በካቴድራሉ እውቅና አግኝተው በነበሩ የሠራዊተ ክርስቶስ ማኅበር፣ በሃይማኖተ አበው ማኅበር አባላት ወደ ውጪ አገር ለነገረ መለኮት ትምህርት ተልከው በተመለሱ አንዳንድ ግለሰቦች መጠቀም እንደ ተጀመረ ያስረዳሉ። እንግዲህ ራሳቸው በኀላፊነት በነበሩበት ካቴድራል የተጀመረውን ፓትርያርኩም በቅዱስ ሲኖዶስ ዕውቅና ያላሰጡትን የኦርጋን አገልግሎት “አቡነ” መልከጼዴቅ ከሰማዕቱ ፓትርያርክ ጋር ማገናኘታቸው ፈጽሞ አያስኬድም። ለመሆኑ በመጽሐፋቸው ያብጠለጠሏቸውን ሰማዕቱ ቅዱስ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን በዘመናቸው ሲቃወሟቸው የነበሩት “አቡነ” መልከጼዴቅ ኦርጋንን ወደ ቤተ መቅደስ ለማስገባት ነው እንዴ ምስክር አድርገው የሚያነሷቸው?
በመሠረቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የ”አቡነ”መልከጼዴቅ ዓይነት ሰዎች በሂደት በመዝሙርና በመዝሙር መሣርያዎች የተነሣ በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚያደርሱት ፈተና ከወዲሁ ስለ ገባው በ1986 ዓ.ም በየትኞቹ የዜማ መሣርያዎች መዘመር እንዳለበት ውሳኔ አስተላልፏል። “አቡነ”መልከጼዴቅ እንደሚሉት ሳይሆን ቅዱስ ሲኖዶሳችን በመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ላይ ተመርኩዞ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዋቢ ባላቸው የዜማ መዋርያዎች፡ በከበሮ፣ በጸናጽል፣ በበገና፣ በመሰንቆ፣ በእንቢልታና በመሳሰሉት ብቻ ዝማሬ እንዲቀርብ ወስኗል። ይኽን የቤተ ክርስቲያናችን ቅዱስ ሲኖዶስ ተወያይቶበት ያስተላለፈውን ውሳኔ የአንድ ማኅበር ውሳኔ አስመስሎ ማቅረብ “አቡነ” መልከጼዴቅንም ሆነ ደቀ መዛሙርቶቻቸውን ትዝብት ላይ ይጥላል። በሌላ መልኩም ይኽ ድርጊታቸው በቅዱስ ሲኖዶሱ ላይ ያላቸውን ንቀት እንዲሁም ጠጠር በተወረወረ ቁጥር ማኅበረ ቅዱሳንን ተጠያቂ የማድረግ መጥፎ ልማድ እንዳለባቸው ያሳያል። ከላይ እንደ ተገለጠው ስለ መዝሙር መሣርያዎች ቅዱስ ሲኖዶሱ መመርያ ያውጣው በ1986 ዓ.ም ነው። ያ ማለት ደግሞ ማኅበረ ቅዱሳን ገና የተመሠረተበት ወቅት ነበር። በመሆኑም ያኔ በአበው ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ዘንድ አገልግሎቱ ገና በተግባር ያልተፈተሸበት ወቅት ነበር። ስለዚህ ቅዱስ ሲኖዶስ በ1986 ዓ.ም የመዝሙር መሣርያዎችን አስመልክቶ ያወጣው መመርያ አንዳንድ የዋሃን እንደሚመስላቸው የማኅበረ ቅዱሳን አጀንዳ ሳይሆን የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ለቤተ ክርስቲያን ሥርዓትና ለመጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ መጠበቅ ያላቸው አርቆ አስተዋይነት ውጤት ነው።
በመሠረቱ “አቡነ” መልከጼዴቅ ከአፄ ኀይለ ሥላሴ ዘመን ጀምሮ በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከግብፅ ቤተ ክርስቲያን ተለይታ ራሷን ችላ በራሷ ሲኖዶስ እንድትመራ ሰማዕቱ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስና ሌሎች በከፍተኛ ሁኔታ እየተጉ በነበሩበት ዘመን ከተወሰኑ የዚህ ቅዱስ ጥረት ተቃዋሚዎች ጋር ሲያደርጉት የነበረውን ደባ ታሪክ ዘግቦታል።(ተኮናኙ ኮናኝ፡ በዓለማየሁ ዓለምነህ ተመልከት)።
“አቡነ”መልከጼዴቅ እርግናዎን እናከብራለን። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን መላ ዘመንዎን መቃወምዎትን ደግሞ እንኮንናለን። ከግብፃውያንም ሆነ ለኦርጋን ታሪካዊነት ይረዱኛል ብለው ካነሧቸው ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ እርስዎም ሆኑ በእርስዎ ደረጃ ያላችሁት የተቀበላችሁት አንዲትና ያልተከፋፈለች ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ነበር። አሁን ግን አንዲቷን የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ያለ ትምህርቷ በሥጋዊ ፍላጎታችሁ ተነሣሥታችሁ ከፋፈላችኋት። ምነው ለኦርጋን ዋቢ አድርገው እንዳነሧቸው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን ሰማዕትነትን እስከ ሞት በመቀበል መታመንን ለምን አላሳዩንም?
እንደ እውነቱ ከሆነ በኦርጋን እንዘምር ብለው ዋቢ ሊያቆሙለት ሲጥሩ በመስማቴ ብዙም አልተገረምኩም። ምክንያቱም ከዚህን በፊት ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር በተባለው መጻፋቸው ላይ “ለስለስ ያለ ሙዚቃ” መስማት ደስታን እንደሚሰጥ አድርገው የጻፉትን ስላነበብኩ ከዚህም የበለጠ ሊሉ እንደሚችሉ እገምት ነበር። የሆነው ሆኖ ለእኛ ችግራችን ኦርጋን አይደለም። መች መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ባላቸው የዜማ መሣርያዎች እግዚአብሔርን በፍቅር፣ በሰላም፣ በንጽሕና አመሰገነውና? እኛ መች የዜማ መሣርያው ጠፋብን? በቤተ ክርስቲያናችን ሐዋርያዊ ትውፊት ለሌለው ለኦርጋን እንደ ተቆረቆሩ እስቲ ክርስቶስ በውሂዘ ደሙ የመሠረታት ቤተ ክርስቲያንን አንድ ለማድረግ ራስዎን እንደ ሰማዕቱ ቴዎፍሎስ አሳልፈው በመስጠት ያሳዩን? እስቲ በጎጥ የተከፋፈለውን የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ካሉበት አጥቢያ ጀምረው ዓለሙ አንድ በሆነበት በክርስቶስ መስቀል አንድ ለማድረግ ይታገሉ? እስቲ እርስዎ ባሉበት ቤተ ክርስቲያን በርስዎ ዘንድም ተቀባይነት ለማግኘት መስፈርቱ የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓትና ቀኖና መሻርና የእርስዎ የጎጥ ሰው መሆኑ ቀርቶ የቤተ ክርስቲያኒቱ እውነተኛ አስተምህሮ ይኹን።
ይኽ የ”አቡነ” መልከጼዴቅ የሰሞኑ ንግግር በርካታ የተሐድሶ ኑፋቄ አራማጆች ራሳቸውን ቀብረው ከሰነበቱበት ቦታ ወጥተው አለን እንዲሉና አቡኑን የውዳሴ ቃል እንዲያዘንቡላቸው አድርጓል። አሁንም አንድ ነገር ግን በጥልቀት ማየትና ማስተዋል እንዳለብን ይሰማኛል። አሜሪካም ሆነች ሌሎች ምዕራባውያን ሀገሮች በአሁኑ ወቅት የሕዝባቸው የመንፈሳዊ ሞራል ልዕልና ምን ይመስላል? በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የተጻፈው መጽሐፍ ቅዱስ የሚያወግዘውን ግብረ ሰዶማዊነትና የተመሳሳይ ጾታን ጋብቻ አሜሪካ በቅርቡ አጽድቃ ተቀብላዋለች። ሌሎችም የእርሷን ፈለግ በመከተል ላይ ይገኛሉ። በሚገርም ሁኔታ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ በአሜሪካ ሕግ ተቀባይነት እንዲያገኝ በግንባር ቀደምትነት ሲታገሉና ሲደግፉ የነበሩት የምዕራባውያኑ የተሐድሶ እንቅስቃሴ ውጤት የሆኑት ፕሮቴስታንት ፓስተሮችና ምእመናኑ ናቸው።
የምዕራባውያኑ የተሐድሶ እንቅስቃሴ የአበውን ትርጓሜ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት፣ ነገረ ቅዱሳንን፣ ጾምን፣ ስግደትን፣ ክህነትን፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ባላቸው የመዝሙር መሣርያዎች ማመስገንን አስጣለ። ከፍ ብሎም መጽሐፍ ቅዱስ የሚተችበት (ክሪቲሳይስ የሚደረግበት) ኮሌጅ አስከፈተ። የመሰብሰቢያና የጸሎት ቤታቸውን ያለ ሰው አስቀረ። ሕንፃዎቻቸው ለመዝናኛና ለመስጊድነት እንዲሸጡ አደረገ። በስተ መጨረሻም ግብረ ሰዶማዊነትን በመጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ ያለው ለማስመሰል በብዙ አተጋቸው። እንግዲህ ይኽ ሩጫቸው የት እንደሚያደርስ ለመገመት እምብዛም አይከብድም።
“አቡነ” መልከጼዴቅና ደቀ መዛሙርቶቻቸው ይኽን እጅጉን እየተጋደላችሁለት ያላችሁት ቤተ ክርስቲያናችንን በምዕራባውያን ቅኝት የማዘመን አንቅስቃሴያችሁ ወደ ፊት በትውልዱ ላይ የሚያስከትለውን የማይጠፋ ጠባሳ አስተውላችሁ ይሆን? አሁን ምዕራባውያኑ በኦርጋን ሲዘምሩ እኛም እንዘምር ያለ ኅሊና ወደ ፊት እኛም ግብረ ሰዶማዊነትን እንቀበል ላለማለቱ ምን ማረጋጋጫ አለን? ሥልጣኔ እኮ የራስን መተው ሳይሆን የራስን አጥብቆ ይዞ ከሌላው ደግሞ ከራስ ጋር የማይጣረሰውን መውሰድ ነበር። እግዚአብሔር ማስተዋሉን ይስጠን።
የሰሞኑን የሚዲያዎችን ግርግር ካጠበቡት ክርክሮች መካከል አንዱ “አቡነ መልከጼዴቅ የግል አስተሳሰባቸውን ነው የሰጡት። ይኽ አባባላቸው በስደት ያለውን ሲኖዶስ አይወክልም” የሚል ነው። ግን ግን ማን ነው ስደተኛ የሚባለውን ሲኖዶስ እንደ ፈለገ የሚያሽከረክር? “አቡነ” መልከጼዴቅ አይደሉምን? አስተያየት ሰጪው እንደ ተናገሩት ከሆነም እስቲ ሌሎቹ ስደተኛ ሲኖዶስ የሚባለው አካል አባላት የ”አቡነ” መልከጼዴቅ ሃሳብ እኛን አይወክለንም ብለው መግለጫ ይስጡ?
አንድ ነገር ግን በስፋት፣ በጥልቀትና በማስተዋል ማየት ያለብን ነገር አለ። አንዳንድ ግለሰቦች የ”አቡነ”መልከጼዴቅንና የሌሎቹን የሰሞኑን ወዝግብ የማኅበር፣ የፖለቲካ ወይም ተራ ጉዳይ አድርገው ሊወስዱት ይችላሉ። ነገር ግን ጉዳዩ በቤተ ክርስቲያናችን አንድነት ላይ ታላቅ ዕንቅፋት እንደሚፈጥር ከወዲሁ እናስብ። የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባላት ከ70 ዓመታት የመለያየት ሂደት አኳያ ተመልሰው ታርቀዋል። በዘመናችን ግጭት የፈጠሩ ቤተ ክርስቲያኒቷንም የከፋፈሉ ሰዎችም ሆነ ለክፍፍሉ ምክንያት የሆነው ሥርዓትም በጊዜው ያልፋሉ። እስከዚያው ግን በግል ስሜትና አመለካከት ላይ ተንተርሶ ወደ ቤተ ክርስቲያኒቱ ሾልከው የሚገቡ ጤናማ ያልሆኑ አዳዲስ አሠራሮችና ሥርዓቶች ሰዎቹ ቢያልፉም ለምንናፍቀው የቤተ ክርስቲያናችን አንድነት ታላቅ እንቅፋት ይሆናሉ። እነ “አቡነ” መልከጼዴቅና በዙርያቸው ያሉ የቤተ ክርስቲያኒቱን መዳከም ዘወትር የሚያልሙ አካላትና ግለሰቦች በአሜሪካን ሀገር በኦርጋን “መዝሙር” ቀርጸው የሚያሳድጓቸው ተረካቢዎች ሀገር ቤት ያለችው ቤተ ክርስቲያን አገልግሎቷ እንግዳ ስለሚሆንባቸው ለአንድነት የመነሣሳት መንፈሳቸውን እጅጉን ይፈታተነዋል። ስለዚህ ርእሰ ጉዳዩን ከአንድ ማኅበር ጋር ያለ ግጭት አስመስለን ከማየት ያለውን መለያየት የሚያባብስ መሆኑን ተረድተን ለቤተ ክርስቲያን ልንቆምላት ይገባናል። በያለንበት ሆነን አበው ያስረከቡንን ኦርቶዶክሳዊ እምነትና ሥርዓት እየጠበቅን ቤተ ክርስቲያናችን ወደ አንድነቷ ከነ ሙሉ ክብሯ የምትመለስበትን ጊዜ እግዚአብሔር እንዲቀርብልን ልንጸልይ ይገባናል። ለዚሁም የእግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን አማላጅነት አይለየን።

(source: Sitotaw Tilahun)

No comments:

Post a Comment