ነገረ ማርያም


"ለእኛስ ልዩ ናት"

ኢትዮጵያውያን በተለይም ኦርቶዶክሳውያን የተዋህዶ ልጆች የእመቤታችን የድንግል ማርያም ነገር አይሆንልንም፣ የዛሬን አያድርገውና ነገስታቱ ሳይቀር የኢትዮጵያን ሕዝብ ከወላዲተ አምላክ ጋር ያላቸውን ቁርኝት በውል ያውቁ ስለነበረ "ማርያምን አማላጅ ብትልክ ምህረት አላደርግልህም" በማለት እነርሱም ለእርሷ ያላቸውን ፍቅር ከመግለፃቸው ባሻገር የህዝቡን የልብ ትርታ ያዳምጡባት ነበር፡፡ ምክንያቱም ልመናዋ፣ ምልጃዋ ፊት የማያስመልስ አንገት የማያስቀልስ ልዩ ነውና፡፡

ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ስሟን ሳይጠራ ምስጋናዋን ሳያደርስ በተሰጣትም ቃል ኪዳን ከልጇ እንድታስታርቀው ሳይማፀን የሚውል ኦርቶዶክሳዊ የለም ማለት ይቻላል፡፡ በጸሎትና በምልጃዋ የሚታመኑ ወገኖች ከሰይጣን ተንኮል የሚያመልጡ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ከሞት ባሻገርም በገነት የመኖር ተስፋ አላቸው የጣዖታት አዳራሽ እንዲጠፋ ዲያብሎስና ሠራዊቱ መርዛቸው እንዲፈርስና ፈታኙ እንዲፈረድበት ወደ ልጇና ወዳጇ መድኃኔዓለም ክርስቶስ አቅርባ የነበረውን ጸሎት በአድናቆት እናስታውሰዋለን፡፡

በአጠቃላይ ድንግል ማርያም በእኛ በኦርቶዶክሳውያን ልቡና ልዩ ሥፍራ ያላት ከመሆኑም ባሻገር ለእኛ ልዩ ናት ይህም የሆነበት ምክንያት፡-

፩ኛ) በድንግልና የታተመች በመሆኗ

እመቤታችን ጌታን ከመውለዷ በፊት፣ በወለደችም ጊዜ፣ ከወለደችም በኋላ በድንግልና የታተመች በመሆኗ ልዩ ናት፡፡ ነቢዩ ሕዝቅኤል ዘላለማዊ ድንግልናዋን ሲያረጋግጥልን "ወደ ምስራቅም ወደ ሚመለከተው በስተውጪ ወዳለው ወደ መቅደሱ በር አመጣኝ ተዘግቶም ነበር እግዚአብሔርም ይህ በር ተዘግቶ ይኖራል እንጂ አይከፈትም፡፡ ሰውም አይገባበትም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል" አለ፡፡ (ሕዝ 44÷1-2)



ፀሐይ ከምስራቅ ወጥቶ ጨለማውን ዓለም እንዲያበራ ምስራቅ ያላት የፀሐየ ጽድቅ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ እናት እመቤታችንን ነው፡፡ ምክንያቱም ፀሐይ ኢየሱስ ክርስቶስ ከምስራቅ ከእመቤታችን በህቱም ድንግልና ተወለዶ ለጨለማው ዓለም ብርሃን ሆኗልና፡፡ መቅደስም ያለው ማህፀኗን ሲሆን ተዘግቶም ነበር ማለቱ ጌታችንን ከመፀነስዋ በፊት፣ በፀነሰች ጊዜ እና ከፀነሰች በኋላ ድንግል መሆኗን ነው፡፡ ይህንንም ነቢዩ ኢሳይያስ በበለጠ ሲመሰክር "ድንግል ትፀንሳለች ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች፡፡" (ኢሳ 7÷14) በማለት በፀነሰች ጊዜ ድንግል መሆኗን ገልጿል፡፡ ይህ በር ተዘግቶ ይኖራል እንጂ አይከፈትም ማለቱ እመቤታችን ጌታን ከወለደችም በኋላ ድንግል ሆና እንደምትኖር ያረጋግጥልናል፡፡ እርሱንም ከወለደች በኋላ በማህፀኗ ፍጡር ሊቀመጥ ሊወለድ እንደማይችል ሲናገር ሰውም (ሩቅብዕሲ) አይገባበትም ምክንያቱም የእስራኤል አምላክ መድኃኔዓለም ተፀንሶበታልና፡፡ በሰማይ በጽርሐ አርያም በኪሩቤል ዙፋን ላይ ፍጡር እንደማይቀመጥበት ሁሉ ማለት ነው፡፡ ዘላለማዊት ድንግል "እህቴ ሙሽራ የተቆለፈ ገነት የተዘጋ ምንጭ የታተመም ፈሳሽ ናት" (መኃ 4÷12) ብሎ ንጉስ ሰሎሞን ከመዝሙር ሁሉ በሚበልጥ መዝሙሩ እንዳመሰገናት በመሆኑም እመቤታችንን ልዩ የሚያደርጋት ድንግል ወእም መሆኗ ነው፡፡ ድንግልናዋንም ከፍጡራን ሁሉ ልዩ የሚያደርገው ፍጡራን ድንግል ቢባሉ በሥጋ ብቻ ነው፡፡ ማንም በሃሳብ ሊነጻ አይችልምና፡፡ እመቤታችን ግን በሃሳብም በግብርም በመናገርም ድንግል ናት፡፡ ስለዚህም ነው ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ በወንጌል "በስድስተኛውም ወር መልአኩ ገብርኤል ናዝሬት ወደምትባል ወደ ገሊላ ከተማ ከዳዊት ወገን ለሆነው ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨች ወደ አንዲት ድንግል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ" በማለት የጻፈው (ሉቃ 1÷26) ጠቢቡ ሰሎሞን "ርግቤ መደምደሚያዬም አንዲት ናት" መኃ 6÷9 እንዳለ እመቤታችን "አንዲት" ብቸኛና ተወዳዳሪ ተነፃፃሪ የሌላት ከፍጡራን ወገን ተመሳሳይ የሌላት መልዕልተ ፍጡራን መትህተ ፈጣሪ በመሆኗ የተለየች ናት፡፡

፪ኛ) የተመሰገነች በመሆኗ ልዩ ናት

ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት "ለቅኖች ምስጋና ይገባል" እንዳለ በዝማሬው (መዝ 32÷1) የእግዚአብሔር ሰዎች ለተባሉ ለቅኖች ለቅዱሳን የፀጋ ምስጋና እንደሚገባ ያስረዳናል፡፡ ስለዚህም ለቅዱሳን አምላክ እናት ለሆነችው ለእመቤታችንማ እንደምን ምስጋና አይገባት? ከእርሷስ በላይ ከፍጡራን ወገን በርህራሄ በቅንነት ማን ይወዳደራል? ጻድቅ ሰው ለእንስሳው ነፍስ ይራራል ባለው መሠረት ለተጠማ ውሻ ውሃን ያጠጣች ለተጨነቁ ለተቸገሩ ለምና የምታሰጥ ናት፡፡ (ምሳ 12÷10፣ ዮሐ 2÷1)

ስለዚህም ቅዱሳን መጻህፍት ለእመቤታችን የምስጋና ሲሶ እንዳላት ይመሰክራሉ፡፡ በሰማያውያን ብርሃናውያን ቅዱሳን መላዕክት እንደምትመሰገን ሲያጠይቅ ቅዱስ ገብርኤልን እግዚአብሔር ላከው "ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ" ይለናል፡፡ ይህ መልአክ በእግዚአብሔር ፊት የሚቆም በስሩም ብዙ መላዕክትን የሚመራና በትጋት ቀንና ሌሊት እግዚአብሔርን የሚያመሰግን ብርሃናዊ መልአክ ነው፡፡ ታዲያ በእግዚአብሔር ዘንድ የከበረው መልአክ ያመሰገናት እኛማ እንደምን እናመሰግናት? አምላካችን እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባውና ክፉና በጎ በሚናገረው አንደበታችን እንደ ቅዱስ ገብርኤል እንድናመሰግናት ፈቀደልን በመሆኑም ተመስገን ብሎ ማመስገን ነው፣ አለቃው ካመሰገነ ሠራዊቱም ያመሰግናሉና እመቤታችን በሰማይ በመላዕክት ዘንድ የተመሰገነች ናት ስለዚህም ልዩ ናት፡፡

በምድራውያን ፍጥረታትም እንደምትመሰገን የቅድስት ኤልሳቤጥ ምስክርነት አብነት ይሆነናል፡፡ እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባውና ለመላዕክት የሰጠውን ሃይማኖት ሕጉን ትዕዛዙን ለሚፈፅሙ ሰዎችም በልባቸው አሳድሮባቸዋል (ይሁ 1÷3) ቅዱስ ገብርኤል ገንዘብ ያደረጋት ኃይማኖት በቅድስት ኤልሳቤጥ ውስጥ አለና፣ እንደ ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችንን አመሰገነቻት፡፡

ቃሉም እንዲህ ይላል "ማርያምም በዚህ ወራት ተነስታ ወደ ተራራማው ሀገር ወደ ይሁዳ ከተማ ፈጥና ወጣች ወደ ካህኑ ዘካርያስም ቤት ገብታ ኤልሳቤጥን ተሳለመቻት ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ፅንሱ በማህፀኗ ውስጥ ዘለለ፡፡ በኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ ሞላባት በታላቅ ድምፅም ጮኻ እንዲህ አለች፡፡ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ የማህፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው የጌታዬ እናት እመቤቴ ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል? እነሆነ የሰላምታሽ ድምፅ በጆሮዬ በመጣ ጊዜ ፅንሱ በማህፀኔ በደስታ ዘሎአልና ከጌታ የተነገረላት ቃል ይፈፀማልና ያመነች ብፅዕት ናት" (ሉቃ 1÷39-45)

ቅድስት ኤልሳቤጥ አካሄዷን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገች ጻድቅ ሴት ናት፡፡ ጻድቅነቷም በእግዚአብሔር ዘንድ የተመሰከረላት ናት "ሁለቱም ካህኑ ዘካርያስና ኤልሳቤጥ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ" (ሉቃ   ) እንዲሁም የታላቁ ነቢይ የመጥምቀ መለኮት የቅዱስ ዮሐንስ እናት ናት፡፡



ሌላው ልጅን እንደምትወልድ ብስራተ መልአክን የሰማች ቅድስት እናት ናት፣ ታዲያ በዚች ታላቅ እናት እመቤታችን ተመሰገነች እጅግ የሚገርመው ከማህፀኗ ፍሬ በፊት እሷን ማመስገኗ ነው፡፡ "ከሴቶች መካከል ተለይተሸ አንቺ የተባረክሽ ነሽ" ካለች በኋላ "የማህፀንሽም ፍቴ የተባረከ ነው" አለች፡፡ እንዲህ ያናገራት መንፈስ ቅዱስ በቅድሚያ ማንን ማመስገን እንዳለባት ያውቃልና፡፡ ነገር ግን ለምስጢረ ስጋዌ ለአምላክ ሰው የመሆን ምክንያት መሠረት እርሷ መሆኗን ሲያጠይቅ፣ እንዲሁም ለእርሷ ምስጋና ገደብ እንዳንሰጥ፣ የጌታን ልደት ስናከብር ቅድሚያ ልደታ ለማርያም ማለት እንደሚገባን ሲያስተምረን ነው፡፡ ለዚህም ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከተአምረ ኢየሱስ በፊት ተአምረ ማርያም እንዲነበብ ማድረጓ የቅድስት ኤልሳቤጥን የመስጋና አካሄድን አብነት በማድረግ ነው፡፡ የድልን ክብር የተረዳች ይህች ቅድስት እናት በፍጹም ትህትና "የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል?" አለች፡፡

ዛሬም የአምላክን እናት ክብር የተረዱ የተዋህዶ ልጆች ሁል ጊዜ እንዲህ ይላሉ፡፡ "በቅዱስ ገብርኤልና በቅዱሳን መላዕክት በቅድስት ኤልሳቤጥና በብሩካን ጻድቃን የምትመሰገን እመቤት እኛ እንዴት እናመሰግንሽ?" እያሉ ልክ እንደ ቅድስት ኤልሳቤጥ በትህትና ራሳቸውን ዝቅ እያደረጉ ይማጸኗታል፡፡ ይህች ቅድስት እናት ስትናገርም "የሰላምታሽ ድምጽ ወደ እኔ ሲመጣ ጽንሱ በማህፀኔ በደስታ ዘሎአልና" አለች፡፡ ድምጿ ደስታን እንደሚሰጥ መሰከረች፡፡ ዛሬም ድምጿን ምስጋናዋን፣ ቅዳሴዋን፣ ውዳሴዋን የሚሰሙ የተዋህዶ ልጆች ደስ ይላቸዋል ሕዋሳቶቻቸው ሐሴትን ይሞላሉ የእርሷን ምስጋና የጠሉ ለእነሱ ባይታወቃቸው እንጂ ምንኛ የተጎዱ ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ከዚህ ነጻ ያውጣቸው በማለት እንጸልያለን፡፡

መች በዚህ አበቃና ገና ለመናገር ያልደረሰው የስድስት ወሩ ሕፃን የቅድስት ኤልሳቤጥና የቅዱስ ዘካርያስ ፍሬ መጥምቀ መለኮት ዮሐንስ እግዚአብሔር ባወቀ ምስጋናን አቀረበ፡፡ ለጌታችን የባህርይ የአምልኮት ስግደት ለእመቤታችን የጸጋ ስግደት ሰገደ፡፡ በመጨረሻም ቅድስት ኤልሳቤጥ ከጌታ የተነገረለት ቃል ይፈጸማልና ያመነች ብፅዕት ናት አለች፡፡

የእመቤታችን እምነት ፍጹም ስለነበር፤ በዚህ የተመሰገነች የተለየች እንደሆነች እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በኤልሳቤጥ ላይ አድሮ መሰከረላት፡፡ እስኪ እምነቷ ከፍጡራን ወገን የተለየ ለመሆኑ እያነጻጸርን እንመልከት፡፡ ለአብነት የሚሆነን የዘካርያስ ታሪክ ይሆናል ካህኑ ዘካርያስ መልአኩ ልጅ እንደሚወልድ ሲያበስረው "እንዴት ይሆናል ከባለቤቴ ሙቀት ልምላሜ ተለይቷል እኔም አርጅቻለሁ አለ" እርሱ የሚወልደው ከህጋዊ ሚስቱ ሲሆን የእመቤታችንን ልዩ የሚያደርገው መፅነሷና መውለዷ በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከመሆኑም ባሻገር በድንግልና በመሆኑ እጅግ በጣም ልዩ ናት፡፡ ካህኑ ዘካርያስ ቢወልድ እርሱን የሚመስል ሰው ነው፣ ምንም እንኳን በማዕረጉና በቅድስና ከሴቶች ከተወለዱት የሚተካከለው ባይኖርም፡፡ (    )

እመቤታችን ግን የምትወልደው የሰማይና የምድርን ፈጣሪ እግዚአብሔር ወልድን ነው፡፡ እርሷ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም ብላ ስታምን ካህኑ ዘካርያስ ግን ተጠራጥሮ ነበር ስለዚህም በእምነቷ የተመሰከረላት ብፅዕት እየተባለች ትመሰገናለች፡፡ እርሷም ሲሶ እንደሚገባት የበለጠ ስትናገር "ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል፡፡" አለች (ሉቃ 1÷49) ይህም ኃይለ ቃል እርሷን የማያመሰግኑ ከትውልድ ማለትም ለመንግስተ ሰማያት ከታጩት እንደማይቆጠሩ ያስገነዝበናል፡፡

በብሉይ ኪዳን እስራኤላውያን ከፍልስጤማውያን ጋር ሲጋጠሙ ጎልያድን የሚገዳደር ሰው ጠፋ፡፡ በዚህ ምክንያት ተጨንቀውና ፈርተው ሳለ የእሴይ ልጅ ዳዊት በእግዚአብሔር ኃይል ታምኖ አምስት ድንጋዮችን ሰብስቦ ሄደ፡፡ አንዱን ወርውሮ ሥጋዊ ጠላታቸውን ድል አድርጎ ሲመለስ እስራኤል እየዘመሩ እልል እያሉ እየተቀኙ "ዳዊት እልፍ ገደለ" እያሉ አሞገሱት ይህ ምሳሌ ለሐዲስ ኪዳን ምሳሌ ነበር በጎልያድ የተመሰለ የአዳምን ልጆች ሁሉ የተገዳደረ ዲያቢሎስ ድል የሆነው በድንግል የማህፀን ፍሬ ነው፡፡ ስለዚህም እመቤታችን አስቀድሞም አባቷ ዳዊት ያመሰገናት (መዝ 44(45)÷9-17) የሥጋና የነፍስ ጠላቶቻችን የሆኑ አጋንንትን በማህፀን ፍሬ ድል ያደረገችልን ስለሆነች ከዳዊት ይበልጥ ልትመሰገን ይገባታል፡፡ እግዚአብሔር በአንተና በሴቲቱ መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፡፡ አንተ ሰኮናውን ትቀጠቅጣለህ የሴቲቱም ዘርም ራስ ራስህን ይቀጠቅጥሃል" (ዘፍ 3÷15) የተባለው ትንቢት ለመፈጸሙ ምክንያት የሆነችውን እመቤት እንደምን እንቀኝላት? እንደምንስ እናመስግናት? አዳም እንኳ የአጥንቱን ፍላጭ ሔዋንን ሕይወቴ ነሽ ብሎ አመሰገናት ፍጻሜው ግን ተስፋ የሆነችው የሕይወትን ራስ ወልዳ ሰላምን የሰጠችው የሕያዋን ሁሉ እናት ድንግል ማርያም ናት፡፡

እመቤታችን ለእኛም የድኅነታችን ምክንያት ሆናለችና እናመስግናት እግዚአብሔር "እንደ ልቤ" ብሎ የመሰከረላት ዳዊት ንግስናውን ትቶ ከክብሩ ከልዕልናው ዝቅ ብሎ "ታቦተ ጽዮንን" አመሰግኗል፡፡ ታቦተ ጽዮን ደግሞ የአማናዊት ታቦት የድንግል ማርያም ምሳሌ ናት በዚህ ምስጋና የተሳለቀችው ሜልኮል ግን መሃን ሆና ቀረች (2ሳሙ 6÷23)



ዛሬም በአማናዊቷ ጽዮን በድንግል ማርያም ፊት እንዘምራለን፡፡ እናመሰግናታለን እናወድሳታለን ከዚህ ጸጋ የሚርቁና የሚንቁ ግን በመንፈሳቸው ይመክናሉ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ከማፍራት ይከለከላሉ፡፡ ስለዚህም እመቤታችን በሰማያውያንም በመድራውያንም በመመስገኗ ልዩ ናት፡፡

፫ኛ) ትንሳኤን ያየች በመሆኗ ልዩ ናት

ከ22ቱ ስነ ፍጥረት መካከል መላዕክትና የሰው ልጆች ህያዋን ሆነው ተፈጥረዋል፡፡ ስለዚህ የሰው ልጅ ምንም እንኳ በሥጋ በጊዜው በሞት ቢያንቀላፋም የትንሳኤ በኩር የሆነው ጌታችንን አብነት አድርጎ በእግዚአብሔር ኃይል ለፍርድ ይነሳል፡፡

(ዮሐ 5÷25) ከሰው ልጆች ትንሳኤ ዘጉባኤን የማትጠብቅ እመቤታችን ብቻ ናት፡፡ ለዚህም ቅዱስ ዳዊት እንዲህ እያለ ዘምሯል፡፡ "በወርቅ ልብስ ተጎናጽፋና ተሸፋፍና ንግስቲቱ በቀኝህ ትቆማለች" ትርጉሙም ንጽሐ ሥጋን ንጽሐ ነፍስን እና ንጽሐ ልቡናን አንድ አድርጋ በተሰጣት ክብር ጸንታ ትኖራለች በቀኝህ ትቆማለች ማለቱም ቀኝ ክብር ነውና፡፡

ጌታችን ይህንን ዓለም ለማሳለፍ ሲመጣ በትንሳኤ ዘጉባኤ ጻድቃንን በቀኝ ኃጥአንን በግራ ያቆማቸዋል፡፡ እመቤታችን ግን ይህንን እንደማትጠብቅ ሲናገር በቀኝህ ትቆማለች ብሎ እርገቷን ተናገረ (መዝ 44÷9-11)

እንዲሁም በሌላ የዝማቴ ክፍል ቅዱስ ዳዊት "ተንሥአ እግዚኦ ውስተ እረፍትከ እንተ ወታቦተ መቅደስከ" አቤቱ ወደ እረፍትህ ተነስ አንተና የመቅደስህ ታቦትም ይላል (መዝ 131÷8-10) አቤቱ ብሎ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መቅደስም ያለው ሰውነቱን ነው፡፡ (ዮሐ 2÷19) ታቦት ያላት እመቤታችንን ነው እረፍት ያለውም መንግስተ ሰማይን ነው፡፡ ስለዚህም አቤቱ ሙስና መቃብርን ድል አድርገህ በኃይል በሥልጣንህ ተነሳ በአንተም ኃይልና ሥልጣን እንደ አንተ ማደሪያህ ድንግል ማርያም ወደ ዕረፍትህ ቦታ ትነሳ በማለት ወደ መንግስተ ሰማይ መግባቷን ይገልጻል፡፡ መንግስተ ሰማይ በቅድምና የገባች ትንሳኤን የማትጠብቅ እርሷ ናት፡፡ ስለዚህም መርህ ለመንግስተ ሰማይ ትባላለች መንግስተ ሰማይ በአማላጅነቷ በቃል ኪዳኗ የምታስገባ ማለት ነው፡፡ ለዚህም ቅዱስ ዳዊት (መዝ 44÷15) "ባልንጀሮቿንም ወደ አንተ ያቀርባሉ በደስታና በሐሴት ይወስዱአቸዋል፣ ወደ ንጉስ እልፍኝም ያስገቡአቸዋል፡፡ በአባቶችሽ ፈንታ ልጆች ተወለዱልሽ በምድርም ላይ ገዥዎች አድርገሽ ትሾሚያቸዋለሽ"””



እንግዲህ ምን እንላለን? የቃል ኪዳን ልጆቿን ቅዱሳን መላዕክት የደስታ ዕልፍኝ ወደ ተባለች መንግስተ ሰማይ ያስገቧቸዋል፡፡ እርሷም አስቀድማ በዚች ምድር የሾመቻቸውን ነፍሳቸውን በሥጋቸው ላይ እንድትገዛ ስልጣን የሰጠቻቸውን ኃላም ይህች ምድር አልፋ የምትተካውን መንግስተ ሰማያትን እንዲወርሱ ስልጣን ትሰጣቸዋለች አለን፡፡ ስለዚህም መርህ ለመንግስተ ሰማይ ትባላለች፡፡ እስራኤል ዘሥጋ በሲና ሳሉ የመሩበትና የተዳደሩበት ዘንድ ጽላትን ሰጥታቸው ነበር ታላቁ ሙሴ ያንን ጽላት ተቀብሎ ከተራራ ላይ ሲወርድ ሕዝቡ የወርቅ ጥጃን አስቀርጸው ያመልኩ ነበር ታዲያ ለእግዚአብሔር አምልኮት የሚቀናውም ሙሴ ያንን እነሱ ሲያመልኩ የነበረውን ጣኦት በጽላቱ ወርውሮ ሰበረው፡፡ እግዚአብሔርም ድጋሚ ጠርበህ አምጣ እኔም እጽፍበታለሁ አለው፡፡ ይህቺም ጽላት በበረሃ ጠላቶቻቸውን ድል እያረገች የኢያሪኮን ግንብ እያፈረሰች የዮርዳኖስን ባሕር እየከፈለችላቸው ከፊት ከፊት እየመራች ከነዓን አባቶቻቸው ከተማ እንዲገቡ አደረገች ይህም ምሳሌነቱ አስቀድመው የተሰሩት ሁለቱ ጽላት የአዳምና የሔዋን ምሳሌ፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ጽላቶቹ መዘጋጀታቸው አዳምና ሔዋን የመጀመሪያው የእግዚአብሔር ልጆቹ ፍጡራን መሆናቸውን ያመለክታል የመጀመሪያው ጽላት በእስራኤል ጣኦት ማምለክ ምክንያት እንደተሰበረም አዳምና ሔዋን አምላክነቱን ሽተው ከእግዚአብሔር ጸጋ ተራቁተው ከገነት የመባረራቸው ምሳሌ ነው፡፡

ሁለተኛይቱ ጽላት የእመቤታችን ምሳሌ ናት በሙሴ እጅ መዘጋጀቷ ድንግል ማርያም አዳማዊት መሆኗ ከተቀደሰ ጋብቻ ከሰው ወገን ከሆኑት ከቅዱስ ኢያቄምና ከቅድስት ሀና በዘር በርካቤ የመገኘቷ ምሳሌ ነው ኃይል አርያማዊት አለመሆኗን ሲያጠይቅ ነው፡፡

በታቦቱ ላይ የእግዚአብሔር ሕጉ፣ ቃሉ መዳፉ፣ በእመቤታችን ማህፀንም አካላዊ ቃል በከዊን መጸነሱና ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን መንሳቱ ሲሆን፤ በዚች ጽላት እስራኤል እንደተጠቀሙበት የገነት በር ባስከፈተችልን በአማናዊቷ ታቦት በድንግል ማርያም ጸጋ እየተጠቆምን ሠራዊተ አጋንንትን እንቀበላቸዋለን፡፡ በኢያሪኮ ግንብ የተመሰለ ኃጢዓት መከራን በእርሷ ጸሎት እንጥለዋለን፡፡ በባሕር የተመሰለውን ይህንን ክ ዓለምና አስቸጋሪ ዘመን በእመቤታችን ጸሎት ተከልለን እናልፈዋለን፡፡ ያቺ ጽላት እየመራቻቸው ርስት ከነዓን እንደገቡ ለእኛ ለሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች አማናዊቷ ታቦት ድንግል ማርያም እየመራች መንግስተ ሰማይ ታስገባናለች ስለዚህም ነው መርህ ለመንግስተ ሰማይ እየተባለች የምትጠራም የምትመሰገንም፡፡

፬ኛ) የእግዚአብሔር የክብሩ መገለጫ በመሆኗ ልዩ ናት

እግዚአብሔር በባሕርይው ክቡር ነው፡፡ ለክብሩም ተወዳዳሪ ተነጻጻሪ በአጠቃላይ የሚመስለውም የለም፡፡ ይህ ክብሩን በሥራው ይገለጣል (መዝ 18÷1 ፣ ኢሳ 6÷3) ይህ የከበረ ገናና አምላክ በመለኮታዊ ባሕርይው ማንም ሊቀርበው የማይችል ሊያየው የሚበቃ አይኖርምና ዓለምን ለማዳን በወደደና በፈቀደ ጊዜ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በፍጹም ተዋህዶ ሰው ሆኖ ተወለደ፡፡ ይህንን ነገር አስቀድሞ ነቢዩ ኢሳይያስ በትንቢት መነጽር አይቶ "ብርሃንሽ መጥቷልና የእግዚአብሔርም ክብር ወጥቶልሻልና ተነሽ አብሪ፡፡ እነሆ ጨለማ ምድረ ድቅድቅ ጨለማም አሕዛብን ይሸፍናልና ነገር ግን በአንቺ ላይ እግዚአብሔር ይወጣል ክብሩም በአንቺ ላይ ይታያል፡፡ አሕዛብም ወደ ብርሃንሽ ነገስታትም ወደ መውጫሽ ጸዳል ይመጣሉ፡፡ (ኢሳ 60÷1-3) ለጊዜው ስለቤተክርስቲያን ቢናገርም ፍጻሜው ግን ስለ እመቤታችን ስለድንግል ማርያም የብርሃን መገለጫ፣ የክብሩ መገለጫ መሆኗን የሚገልጽ ትንቢት ነው፡፡



"በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃንን አየ በሞት ጥላ ውስጥም ላሉ (ለአሕዛብ) ብርሃን ወጣላቸው" (ኢሳ 9÷6) ተብሏልና ከማህፀን ጀምሮ ይቆራኙ የነበሩ አጋንንት ድል ስለተመቱ ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም ከፀነሱ በፊት ደስ ይበላችሁ አለ በአንቺ ላይ እግዚአብሔር ይወጣል ማለቱም ከድንግል ማርያም የተወለደው ብርሃን እግዚአብሔር ነውና ነው (ኢሳ 9÷6 .ዮሐ 1÷1-14) ክብሩም በአንቺ ላይ ይታያል ማለቱ እመቤታችን በድንግልና ፀንሳ ከድንግልና ጡቷ ወተትን ማስገኘቱ፣ ይህም ለጌታችን ክብሩ የሚነገርበት ታላቅ ተአምር ነው፡፡
አንድም ከእርሷ በነሳው ሥጋ ለዓለም ተገልጾ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን አድርጓልና፣ በአማላጅነቷ ጌትነቱን ገልጧልና ነው ይኽም ትንቢት በዶኪማስ ቤት ተፈጽሟል፡፡

ጌታ ኢየሱስ ይህንን የተአምራት መጀመሪያ በገሊላ ቃና አደረገ ክብሩንም ገለጠ ደቀመዛሙርቱም በእርሱ አመኑ፡፡ የጌትነቱን የአምላክነቱን መታወቂያ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ የገለጠው የአምላክ ልጅ አምላክ መሆኑን ለፍጥረቱ በግልፅ ያሳየባት ስለሆነ የተአምራት መጀመሪያ አለው፡፡ ይህም በድንግል ማርያም አማላጅነት ተፈፀመ፡፡ እመቤታችን አስቀድሞም በነቢያት የጌትነቱ መገለጫ ምልክት እንደምትሆን አናግሮ ነበር (ኢሳ 7÷14) በድንግልና ጸንሳ በድንግልና መውለዷ፣ በተወለደው ለአማኑኤል የጌትነቱ መታወቂያ ነበርና ነው፡፡ (ኢሳ 9÷6) አሁንም በሰዎች መካከል ሁሉን ቻይነቱን የሚሳነው የሌለው መሆኑ ለተከተሉት ይገልጽ ዘንድ ተአምራቱን በድንግል አማላጅነት አደረገው ውሃውንም ወደ ወይንጠጅ በመለወጡ ክብሩን ገለጠ፣ ደቀመዛሙርቱም በእርሱ አመኑ ይላል፡፡ (ዮሐ 2÷1-11)

እንግዲህ ለሐዋርያት ሃይማኖታቸው ፍጹም እንደሆነ በጌታችን የባሕርይ አምላክነት እንዲያምኑ፣ የተደረገበት ድንቅ ተአምራት የተፈፀመው በእመቤታችን አማላጅነት ነው፡፡ ጌታችንም ይህን በማድረጉ ክብሩ ተገለጠ ተባለ፡፡ እንግዲህ ምን እንላለን እርሱ በባሕርይው ክብር ሆኖ ሳለ በእርሷ አማላጅነት ክብሩ እንዲገለፅ አደረገ፡፡ አንድም የማይታየው ባሕርይ ከእርሷ ሥጋንና ነፍስን ነስቶ በመወለዱ ክብሩን ገለጠ በመሆኑም እርሱ ከእርሷ ተወልዶ እንዲህ በማድረጉ ትህትናው ሲደነቅ እመቤታችን ደግሞ ልዕልናዋ ይነገርላታል፡፡ ስለዚህም የጌታችንን የክብር መገለጫ ማመን የእርሷን አማላጅነት ማመንና መቀበል ማክበር ነው፡፡ ይኽንን ደግሞ አለማመን የጌታችንን ክብር ማቃለል ነው፡፡

በባሕርይው ክብር የሆነ አምላክ ለክብሩ መገለጫ ምክንያት ካደረጋት ለእኛማ እንዴት ክብራችን ሞገሳችን አትሆንም? በመጽሐፍ ቅዱስ (ዘጸ 4÷16) ሙሴና አሮንን ወደ ፈረኦን ቤተ መንግስት ሊልካቸው በወደደ ጊዜ ጠርቶ እንዲህ ነበር ያላቸው "አሮን ስለ አንተ ከሕዝቡ ጋር ይናገራል እንዲህም ይሆናል እርሱ አፍ ይሆንልሃል አንተም በእግዚአብሔር ፈንታ ትሆንለታለህ" በፈረኦን ላይ አምላክ (ፈራጅ) አድርጌሃለሁ" (ዘጸ 7÷1)

ይህንን የተናገረው ሁሉን የሚያውቅ እግዚአብሔር ነው ለቅዱሳኑ የተሰጣቸውን ጸጋ (በእኛ አዕምሮ) ገደብ እንዳንሰጠው ይህንን ተናገረ፡፡ "ስለ እኔ ፈንታ በፈረኦን ቤት ሙሴ ይቁምልህ" አለው ለአሮን ስለ እግዚአብሔር ፈንታ ማለቱ በፍጹም ምስጋና ክብር ስለ ሰዎች የሚቆሙ መሆናቸውን ለቅዱሳን የሰጠው ጸጋ ሲሆን፣ እመቤታችን ደግሞ ከቅዱሳን ሁሉ ትለያለች ትበልጣለች የእርሷ ሞገስነት እንደ አምላክ እናትነቷ ነውና በምንሄድበት፣ በምንሰራበት በማንኛውም ቦታ ሞገስ ትሆነናለች ሙሴ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን በማግኘቱ ስለ እስራኤል ዘወትር ይማልድ ይለምን ነበር እግዚአብሔርም የጸሎቱን ዋጋ ምህረትን ያደርግ ነበር (ዘጸ 32÷11፣ ዘጸ 33÷10፣ ዘኁ 14÷20)

በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን ያገኘው አብርሃም ስለ ሰዶም ያቀረበውን ልመና እግዚአብሔር ተቀብሎታል (ዘፍ 18÷3-32) እግዚአብሔር በእርሱ ፊት ሞገስን ባለሟልን ወዳገኙት ቅዱሳን፣ ሰዎችን ለሥርየተ ኃጢዓት ጸሎትን እንዲያደርጉላቸው ይልካል፡፡ ለዚህም አቤሚሊክን ወደ አብርሃም፣ ኤልፋዝን ወደ ኢዮብ መላኩን መጻሕፍት ይናገራሉ (ዘፍ 20÷7፣ ኢዮ 42÷7)



የእነ አብርሃምንና የእነ ኢዮብን ፈጣሪ የወለደች እመቤት በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን እንዳገኘች ቅዱስ ሉቃስ እንዲህ መዝግቦልናል፡፡ "ማርያም ሆይ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን አግኝተሸልና አትፍሪ" (ሉቃ 1÷30) ስለዚህም የማማለድ ሞገስ ተሰጥቷታል ንጉሱ አቤሜሊክን ወደ አብርሃም፣ ቴማናዊውን ኤልፋዝንም ወደ ኢዮብ እንደ ላከ እኛንም ወደ እርሷ ይልከናል፡፡ በጸሎቷና በአማላጅነቷ እንድንጠለል ይመራናል፡፡ ሙሴ ለአሮን ስለ እግዚአብሔር ፈንታ ሞገስ ከሆነው እግዚአብሔርም ከፈቀደለት ለእኛም እመቤታችንን ፈቅዶ ሰጥቶናልና ሞገሳችን ክብራችን እንላታለን፡፡

በጸሎቷም ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ እንጠበቃለን ይህንን የተሰጣትን ክብር የምንገልጸው በጸሎቷ በመጠቀም በቃል ኪዳኗ በመታመንና በመለመን የጸጋ ስግደት ለእርሷ በማቅረብ ነው፡፡ (ሮሜ 13÷7፣ ኢሳ 49÷22፣ መዝ 131÷13)

በመሆኑም ከዚህ ሁሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነታ በመነሳት ድንግል ማርያም ለእኛ ልዩ ናት፡፡

10 comments:

  1. dingil hoy yebezaw hatiaten bemiljash atefilegn

    ReplyDelete
  2. ራዕይ ማርያመን ከዚህ ድህረ ገጽ ብትለጥፉልን/በብታስቀምጡል ጥሩ ነው ።

    ReplyDelete
  3. ቃለሂወት ያሰማልን የአገልግሎት ዘመንዎንም ይባርክልን

    ReplyDelete
  4. ቃለሂወት ያሰማልን የአገልግሎት ዘመንዎንም ይባርክልን

    ReplyDelete
  5. ቃለህይዎት ያሰማልን

    ReplyDelete
  6. ቃለ ሂወት ያሰማልን ጸጋ እመቤታችን ከናንተጋ ይሁን

    ReplyDelete
  7. ቃለ ህይወት ያሰማልን መንግስተ ሰማያትን ያዋርስልን!

    ReplyDelete
  8. እግዚአብሔር ይክብርልን

    ReplyDelete