Tuesday, February 11, 2014

‹‹መዳን በሌላ በማንም የለም›› (ሐዋ 4፡12)






‹‹የሉተራውያን ስህተት በሊቃውንት አስተምህሮ ሲገለጥ ሲጋለጥ›› ክልፍ 3

ይህንን ኃይለ ቃል የተናገረው በዕድሜ በጸጋና በመንፈሳዊ አገልግሎት በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ የሸመገለው ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ሲሆን መጽንኢ (አጽናኝ)፣ መስተፈስሒ (አስደሳች)፣ መንጽሒ (የሚያነፃ)፣ መስተሰርይ (የሚያስተሰርይ)፣ እና ከሳቲ (ገላጭ) የሆነውን መንፈስ ቅዱስን ከተቀበለ በኋላ በዕለቱ በዙሪያው ተሰብስበው ለነበሩት ለቤተ አይሁድ በ72 ቋንቋ ወንጌልን በመስበክ 3000 ነፍሳትን አሳመነ፡፡ በዘጠኝ ሰዓትም ከሐዋርያው ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ወደ ቤተመቅደስ ሲሄዱ በቤተመቅደስ በር ላይ ተቀምጦ ሲለምን የነበረውን አንድ አንካሳ ሰው ወደ እኛ ትኩር ብለህ ተመልከት ብሎ በናዝሬት በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሣና ተመላለስ በማለት ፈወሰው፡


ነገር ግን በነጋው ሰዱቃውያንና ፈሪሳውያን የካህናት አለቆች (ሐናና ቀያፋ) ና የመቅደስ አዘዦች በምን ኃይል ወይም በማን ስም ይህን አደረጋችሁ? ባሉት ጊዜ ነበር ‹‹እናንተ በሰቀላችሁት እግዚአብሔርም ከሙታን ባስነሣው በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው ግንበኞች የናቁት የማዕዘን ራስ የሆነው ይህ ድንጋይ ነው መዳንም በሌላ በማንም የለም እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና›› (ሐዋ 4፡6-12) በማለት የመለሰላቸው፡፡
በመሆኑም የዚህ ጽሁፍ መሠረታዊ ዓላማ ሉተራውያን ፕሮቴስታንትና ተረፈ አርዮሳውያን ‹‹መዳን በሌላ በማንም የለም›› የሚለውን ጥቅስ እንደ መፈክር በመያዝ ዝም ብለን ‹‹ኢየሱስ›› በማለት ብቻ እንድናለን ፕሮሰስ አያስፈልግም በማለት የመዳንን ትርጉም ባለመረዳት የቅዱሳንን፣ የመላዕክትን የመስቀልን፣ የዕምነትን፣ የፀበልንና ሌሎችን የመዳን መንገዶችን በመቃወም የስህተት ትምህርት ሲያስተምሩ ይስተዋላሉና፣ ይህ የመናፍቃን ስህተት በሊቃውንት አስተምህሮ ሲመረመር ምን እንደሚመስል ለተዋህዶ ክርስቲያኖች ማስተማርና በቂ ግንዛቤ በማስጨበጥ ትውልዱን ከስህተት ትምህርት ከጥርጥር መታደግ ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ በተለያየ ቦታ መዳንን በተመለከተ ያስተምረናል ነገር ግን መዳንን በተመለከተ የእኛ የአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ ለሁሉም አንድ ዓይነት ቃል ነው የሚጠቀመው ከዚህም የተነሣ ምስጢርን የማያስተውሉ ሰዎች መጻሕፍትን በትርጉም ሳይሆን በጥሬ ንባብ ለመረዳት የሚሞክሩ ወገኖች በሁለት መልኩ ሲስቱ እናስተውላለን፡፡
ሀ/ የመጀመሪያዎች መዳንን ጠቅልለው ቅዱሳንንም፣ መላዕክትንም ኢየሱስ ክርስቶስንም በተመለከተ የተናገረው ቃል አንድ ዓይነት ትርጉም ያለው የሚመስላቸው ናቸው፡፡
ለ/ በሌላው መልኩ ደግሞ መላዕክት ቅዱሳን ያድናሉ ብለን ስንል ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚያድነው ዓይነት ማዳን ያለ የሚመስላቸው ወገኖችም አሉ፡፡
መዳን የሚለው ቃል ከመጽሐፍ ቅዱስ አንፃር በሦስት ዓይነት ፍቺ ወይም ትርጉም አመስጥረን እናየዋለን:-




፩ኛ. የዓለም መድኃኒት  የባሕርይ አምላክ ኢየሱስ  ክርስቶስ 
                     የመጀመሪያውና ዋንኛው እግዚአብሔር አዳምንና ልጆቹን ከወደቁበት ውድቀት አንስቶ ከጠፉበት ከባዘኑበት መልሶ ወደ ነበሩበት ክብር መመለስ ወይም ለመመለስ ያደረገው ጉዞ ማዳን ይባላል፡፡ አዳም በዕለተ አርብ ወደ ተፈጠረበት ክብር መመለስ ከባርነት ታድጎ ከሲኦል ነፃ አውጥቶ አዲስ አድርጎ መሥራቱ ማዳን ነው (2ቆሮ 5፡15)
ከዚህም የተነሣ ነው እግዚአብሔር አዳነን ኢየሱስ ክርስቶስ አዳነን የባርነታችን ቀንበር ሰበረ ከእስራታችን ፈታን የምንለው ‹‹ፊል 2፡8-11 በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማዳን ይገልፅልናል የዘመኑ ፍፃሜ በደረሰ ጊዜ ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያም ተወልዶ የውርደት ሞት (የመስቀል ሞት) ሞቶ እኛን አዳምና ልጆቹን እንዴት እንደ አዳነን ነው የሚያስተምረው›› ‹‹በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው›› (ፊልጵ 2፡8-11)
ኢየሱስ ክርስቶስ የሚለው ስም ከስም ሁሉ የከበረ ስም መሆኑን ሐዋርያው ያስተምረናል እንዲሁም ፍጥረት ሁሉ ይድንበት ዘንድ የተሰጠው ስም ይህ ስም እንደሆነም አስረግጦ ይነግረናል፡፡
ሐዋርያው ይህን ያለበት ምክንያት እግዚአብሔር ኤልሻዳይ አዶናይ ኤል፣ አልፋና ኦሜጋ ፣ ፊተኛውና ኋለኛው ፣ ያህዌ የሚለው ስም አያድንም ማለቱ ነው? ይህ አይደለም የቅዱስ ጳውሎስም ሆነ የሐዋርያት ሃሣብ::
እግዚአብሔር የሚለው ስም የእግዚአብሔርነቱ የአንድነቱ የሦስትነቱ ኅቡዕ ስም ነው አዶናይ ፣ ኤል ፣ ያህዌ የሚሉት ስሞች ከሥጋዌ በፊት የተሰጡ ስሞች ናቸው ኤልሻዳይ፣ ፊተኛውና ኋለኛው፣ አልፋና ኦሜጋ የሚሉት ስሞች ከሀሊነቱን ሁሉንቻይነቱን ያለ የነበረ ወደ ፊትም የሚኖር መሆኑን የሚገልጹ ከሥጋዌ በፊት የተሰጡ ስሞች ናቸው፡፡
እግዚአብሔር ሰው ሆነ በተዋህዶ ከበረ ለማለት የተሰጠው ስም ኢየሱስ የሚለው ነው፣ ከስም ሁሉ በላይ የሆነ ስም ያስባለውም ይህ የተዋህዶ ምስጢር ነው፡፡ኢየሱስ ክርስቶስ የሚለው ስም ከስም ሁሉ የተለየ ስም ነው፡፡
ሚካኤል ገብርኤል ዑራኤል ብንል የፍጡር ስም ነው ምንም እንኳን የቅዱሳን መልዕክት ስም ቢሆንም ሌሎችም አበበ፣ ተስፋዬ፣ አልማዝ ….. የተጻውአ መጠሪያ ስም ነው እግዚአብሔር ስንል የፈጣሪ ብቻ ስም ነው፡፡
ኢየሱስ ስንል ግን ፍጡርና ፈጣሪ በተዋህዶ ያገኙት ስም ነው የፍጡር ስም ለብቻ ነበረ የፈጣሪም ስም ለብቻ ነበረ ፈጣሪ ከፍጡር ጋር በተዋህዶ በመክበር ከድንግል ማርያም ከሥጋዋ ስጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሲወለድ ግን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚለው ስም ተሰጠው ይህም በመሆኑ ይህ ስም የማይደገም ልዩ ስም ነው እንደፍጡራን ስም በተለያየ ጊዜ የሚደገም አይደለም፡፡
ኢየሱስ የሚለው ስም ግን ምስጢረ ሥጋዌ ስለማይደገም ሌላ ጊዜ የሚደገም ስም አይደለም አንዱና ዋንኛውም ምክንያት ይህ ነው ኢየሱስ የሚለው ከስም ሁሉ በላይ የሆነ ስም ያሰኘው፡፡
ሌላው ምክንያት ሌሎችን ስሞች ግብሩን ተመልክተው የእግዚአብሔርን ድንቅ ስራ ተመልክተው ሰዎች በዚያ ስም ሲጠሩት በሌላ መልኩ ስምህ ማን ነው ብለው እነአብርሃም እነሙሴ ‹‹ማን ብየ ልንገራቸው ቢለው ሙሴ›› ፊተኛውና መጨረሻው ሁሉን ቻይ (ኤልሻዳይ) የሆነው ብለህ ንገራቸው ነው ያለው፡፡
ኢየሱስ የሚለው ስም ግን በመላዕክት ተነግሮ በእናቱ በኩል የወጣ ‹‹ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅ ትወልጃለሽ አሕዛብን በባርነት በትር ይገዛል ድንቅ መካር ኃያል አምላክ ይባላል ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ›› (ሉቃ1 ፣ ኢሳ 9፡6)
እግዚአብሔር የተባለው በዚህ ዘመን ነው በዚህ ሰዓት ነው ልንለው አንችልም ኢየሱስ ክርስቶስ የተባለበትን ዘመን የተባለበትን ሰዓትና ቦታ እናውቀዋለን በመሆኑም ኅቡዕ የነበረው ዘመንና ጊዜያት ዕለትና ቀናት የማይቆጠሩለት ፣ በቦታና በጊዜ የማይወሰን ተወስኖ ተወልዶ ኢየሱስ ስለተባለ ይህ ስም ልዩ ስም ነው እንድንበት ዘንድ የተሰጠ ስም ሲልም ቃላቶቹን ኢየሱስ የሚለውን ብቻ ሳይሆን ይህንን የማዳንን ምስጢር የሚወክል ስም የዳንበት ስም የተፈወስንበት ስም ስለሆነ ነው በመጽሐፍ ቅዱስ ስም አንድን ግብር ይወክላልና ኢየሱስ ክርስቶስ ተብሎ ስም ሲወጣለት ምስጢረ ሥጋዌን ምስጢረ ተዋህዶን፣ ሥጋዌን ለመግለጽ ነው፣ ስለዚህም ለመዳን የተሰጠን ምስጢር ምስጢረ ተዋህዶ ነው፣ ምስጢረ ተዋህዶ ባይፈጸም ድህነት የለም፣ ለዚህ ነው ስሙ ልዩ ስም ነው፣ አጋንንት ሲሰሙት የሚንቀጠቀጡለት ስም የሆነው አጋንንት የሚፈሯት ተዋሕዶን ነው፣ ዲያብሎስ ድል የተነሣው በምስጢረ ተዋህዶ በምስጢረ ሥጋዌ ነውና፡፡
ምስጢረ ስላሴ ለእኛ ሳይገለጥ ኅቡዕ ይሁን እንጂ በፊትም ነበረ፣ ሌሎችም ምስጢራት ከምስጢረ ሥጋዌ በኋላ የመጡ ናቸው ከምስጢር ሁሉ የሚበልጠው አስደናቂው ምስጢር ምስጢረ ሥጋዌ ነው፣ ለምን ቢባል አምላክ ሰው የሆነበት ልዩና ረቂቅ ምስጢር ስለሆነ ነው ለዚህም ነው ሊቃውንት እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ሰው የሆነበት በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ የተወለደበት ምስጢር ይበልጣል ያሉት፡፡
‹‹መቼም እግዚአብሔርን ያየው አንድስኳ የለም በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ ተረከው እንጂ›› ዩሐ 1፡18 እንዳለ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ እግዚአብሔርን አየነው ዳሰስነው ነካነው ብለን የምንናገርበት ምስጢር ይህ የሥጋዌ ምስጢር ነው፡፡ እግዚአብሔርን ማንም አላየውም ነገር ግን በምስጢረ ስጋዌ የእኛን ሥጋ ለብሶ በማርያም ሥጋ ተዳሰሰ ታየ ሲናገር ተሰማ አፉን ከፍቶ ሲያስተምር ታየ ይህንን ነው ማዳን የሚሉት ቅዱሳት መጻሕፍት ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝ ነው፣ አዳነን፣ እግዚአብሔር አዳነን ማለት ይህ ነው  ይህ የእግዚአብሔር ማዳን የሚተካ ነገር አይደለም ሌላ ፍጡር የሚጋራው ማዳን አይደለም እግዚአብሔር በከሐሊነቱ በእግዚአብሔርነቱ የሚያደርገው ብቻ ነው ለምን አዳምን ከሲኦል ግዛት ነፃ ማውጣት እንደገና በአዲስ ተፈጥሮ በሥጋ ተፈጥሮ መስራት የእግዚአብሔር ብቻ ገንዘብ ስለሆነ፣ የተዘጋውን ገነት መክፈት የእግዚአብሔር ብቻ ገንዘቡ ስለሆነ ይህ ማዳን የማይተካ ነው በቅዱሳን መላዕክት በቅዱሳን ጻድቃን በድንግል ማርያም ሊደረግ የማይቻል ማዳን ነው ይህ ማዳን ደግሞ በዓለም ላይ በዘመናት መካከል የተደረገ ማዳን ነው በቀራኒዮ አደባባይ ስጋውን ቆርሶ ደሙን አፍሶ ያደረገው ማዳን ነው፡፡
ሌላው ማዳን ሁሉ ከዚህ የሚገኝ በረከት ነው፣ ይህ የመጀመሪያው ማዳን ነው የቅዱሳን ማዳን፣ በጸበል መዳን በእምነት መዳን፣ በቅዱሳት መጻሕፍት ተሻሽቶ ተሳልሞ መዳን፣ በመስቀል መዳን የምንላቸው ሁሉ በዚህ መዳን ምክነያት የተገኙ ናቸው ይህን ማዳን ኢየሱስ ክርስቶስ ያድናል ብለን ቅዱሳን መላዕክት ያድናሉ ስንል ልዩነት አለው ይህንን አውቀን ነው እኛ ኦርቶዶክሳውያን የምንናገረው ሉተራውያን ወይም መናፍቃኑ እንደሚሉት ጠቅልለን አይደለም የምንናገረው፣ ምን ማለታችን እንደሆነ አውቀን ተረድተን ነው የምንመሰክረው፡፡
ለምሣሌ (በመዝ 33፡7) ላይ ‹‹የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ዙሪያ ይሰፍራል ያድናቸውማል›› የኢየሱስ ክርስቶስን ያድናል ያለው መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ሥፍራ ደግሞ ቅዱሳን መላዕክት ያድናሉ ይላል፣ ይህ ማለት መላዕክት አዳምን ከሲኦል አውጥተው ወደ ገነት ይመልሱታል ማለት አይደለም ይህን ማድረግ ለፍጥረታት ስላልተቻለ ነቢዩ ዳዊትም ሆነ ነቢዩ ኢሳይያስ እጅህን፣ ቀኝህን ከአርያም ላክ አድነንም ሰማዮችን ቀደህ ውረድ (መዝ 143፡5-7 ፣ ኢሳ 64፡1) በማለት ተናግረዋል፡፡
አዳምን ከወደቀበት የሚያነሣ ወደ ጥንት ክብሩ የሚመልስ አልተገኘም ነበርና እግዚአብሔር ቀኙን ማዳኑን ጥበቡን አንድያ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ላከው አዳምን ለማዳን አበው የእንሰሳት በመስዋዕት፣ ነቢያት በጽድቃቸውና በለቅሶ በጸሎት እንዲያውም ደማቸውን በማፍሰስ አጥንታቸውን በመከስከስ ሞክረዋል ግን ስላልቻሉ እንዲህ ነው ያሉት ‹‹ጽድቃችን እንደ መርገም ጨርቅ ነው፣ በደላችን እንደ ነፋስ አፍገምግሞ ወስዶናል›› ኢሳ 64፡5 ምክንያቱም የሰው ልጅ መዳን ወደ ጥንተ ተፈጥሮ መመለስ በእነዚህ ቅዱሳን በአብርሃም፣ በይስሐቅ፣ በያዕቆብ በሰሎሞን በዳዊት በነቢያቱ የሚሆን አልነበረም የሚከፈል ካሣ ይጠይቅ ነበረ ስለዚህም ነው ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ መጥቶ ራሱ ሊቀ ካህን፣ ራሱ በግ፣ ራሱ እግዚአብሔር ሆኖ፣ በአንድ ጊዜ ሦስቱንም ሆኖ መስዋዕት ሰውቶ፣ መስዋዕት ተቀብሎ፣ ራሱ ደግሞ መስዋዕት ሆኖ ድኅነትን ፈጸመልን፡፡ ይህንን ማዳን ማንም ሊያደርገው አይችልም፡፡
የኢየሱስ ክርስቶስ ማዳን የተለየ ማዳን ነው የኦሪቱም ሊቀ ካህናት የሐዲሱም ሊቀ ካህናት ሦስት ነገር ይፈልጋሉ ክህነት ይፈልጋሉ፣ መስዋዕት ይፈልጋሉ፣ መስዋዕትን የሚቀበላቸውም ይፈልጋሉ፡፡ በሐዲስ ኪዳን በቤተመቅደስ ካህኑ በክህነቱ፣ መስዋዕቱን ኅብስቱንና ወይኑን ያቀርባል፣ መስዋዕቱን የሚቀበል እግዚአብሔር ነው እርሱ ካህን ነው፣ መስዋዕቱ በግ ነው መስዋዕቱን የሚቀበል እግዚአብሔር ነው፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው ልዩ ካህን ነው (ዕብ 8፡2) ምክንያቱም ሊቀ ካህናቱ ሁሉ ሦስት ነገሮች (መስዋዕት፣ ክህነት፣ መስዋዕት ተቀባይ) ሲፈልጉ እርሱ ግን አላስፈለገውም፡፡
መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ እንደመሰከረ ‹‹ነዋ በግዑ ለእግዚአብሔር›› የእግዚአብሔር በግ የተባለ መስዋዕቱ ራሱ ነው ፣ ሊቀ ካህን ነው መስዋዕቱን አቀረበ፣ እግዚአብሔር ነው መስዋዕቱን ተቀበለ (2ቆሮ 5፡16-21) ይህንን ነው የኢየሱስ ክርስቶስ ማዳን በፍጡር ሊደረግ የማይችል ድህነት የምንለው ነገር ግን አይሁድ ፈሪሳውያን ሰዱቃውያን በኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት፣ የአብ የባሕርይ ልጁ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ መድኅኒት (አዳኝ) እንደሆነ አያምኑም ነበረና ይሰናከሉበት ነበረና የኢየሱስ ክርስቶስን ስም ደጋግመው በመጥራት ከማስተማራቸው ባሻገር ‹‹መዳን በሌላ በማንም የለም›› በማለት የተናገሩት፡፡ ‹‹ሰው ደግሞ የሰውን ልጅ የእግዚአብሔርን ልጅ የአብ የባሕርይ ልጅ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የተካከለ ወልደ አብ ወልደ ማርያም በተዋሕዶ የከበረ እንደሆነ ካላመነ አይድንምና››
‹‹ዮሐ 20፡31 ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ታምኑ ዘንድ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ ይህ ተጽፏል››
መጥምቀ ዮሐንስም ‹‹እኔም አይቻለሁ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ መስክሬአለሁ›› ዮሐ 1፡34 ነው ያለው ይህ ነው ምስክርነቱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መድኀኒት አዳኝ ፈዋሽ እንደሆነ የአብ የባሕርይ ልጅ እንደሆነ መመስከር፣ ምክንያቱም አይሁድ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካከለ ብለው ሊገድሉት ይፈልጉት ነበረና (ዮሐ 5፡18) ስለዚህም መዳን በሌላ በማንም የለም በደላችን የተደመሰሰው፣ መርገማችን የተሻረው ፣ አዳምና ልጆቹ ወደ ቀደመ ክብራችን የተመለስነው በኢየሱስ ክርስቶስ ማዳን ነው፡፡                  
    ፪ኛ. የመላዕክት ማዳን፣ የቅዱሳን ማዳን፣ የመስቀል ማዳን የፀበል ማዳን ፣ በመስቀልና በእምነት በቅዱሳት መጻሕፍት በመተሻሸት መዳን የምንለው ነው::
                                                         ሀ/ የመላዕክት ማዳን
ከላይ ከፍ ብለን እንደጠቀስነው የመላዕክትን ማዳን በተመለከተ ቅዱስ ዳዊት ‹‹የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል ያድናቸውማል›› (መዝ 33፡7) ይላል መላዕክት ያድናሉ ብለን ስንል ምን ማለታችን ነው ብለን ብንጠይቅና ብንጠየቅ የመላዕክት ማዳን የጸጋ ነው፡፡
በአጠቃላይ የመላዕክት ማዳን የምንለው ሦስት ነገሮችን ነው፡-
1.   ጥበቃቸውን (መላዕክት በመጠበቅ ያድናሉ ይታደጋሉ)
‹‹በመንገድህ ሁሉ ይጠብቅህ ዘንድ መላዕክቱን ስለ አንተ ታዟል›› መዝ 90፡11 ‹‹ከክፉ ነገር ሁሉ ያዳነኝ እርሱ እንዚህን ብላቴናዎች ይባርክ›› (ዘፍ 48፡16) ሰዎች ክፉ ነገር እንዳይደርስባቸው ክፉም ነገር እንዳያደርጉ ከዲያብሎስ ተንኮልና ፍላéE መጠበቅ ነው የመላዕክት ማዳን የተባለው (ዘፍ 19፡15 ፣ ዳን 3፡23-30)  






2.   ሁለተኛው ማዳን ደግሞ በምልጃቸው በጸሎታቸው የሰው ልጆች ከወደቁበት የኃጢዓት ውድቀት እንዲነሱ ማድረግ ወደ እግዚአብሔር ምልጃን በማቅረብ መታደግ ማዳን ‹‹ዘካ 1-12 አቤቱ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሆይ እነዚህ ሰባ ዓመት የተቆጣሃቸውን ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች የማትምራቸው እስከመቼ ነው?›› በማለት ወደ እግዚአብሔር ምልጃን ሲያቀርብ ‹‹እግዚአብሔርም ወደ ኢየሩሳሌም በምህረት ተመልሻለሁ በኢየሩሳሌም ላይ ቤቴ ይሠራባታል ገመድም ይዘረጋባታል›› ‹‹ገብርኤል እየበረረ መጣ፣ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ …..›› (ዳን 4፡21 ፣ ዳን 10፡13)



ይህንን ለማብራራት በሚገባን ምሳሌ ብንገልጸው አንድ ሰው በደዌ ታሞ ወደ ሐኪም ቤት ቢሄድና በጤና ጣቢያው ያለው ሐኪም ምርመራ አድርጎ የተለያዩ መድኅኒቶችን ሰጥቶ ቢመልሰውና ይህ ታማሚ ቢድን ሐኪሙ ራሱ መድኅኒት ሆኖ አዳነው ማለት አይደለም፣ የመረመረው ምርመራ፣ የታዘዘለት መድኅኒትና ሙያዊ ምክር ባንድ ላይ ሆነው ነው ይህ ሰው የዳነው እንደዚሁ ሁሉ ቅዱሳን መላዕክት ከእግዚአብሔር በተሰጣቸው ጻጋ ሲያድኑ እግዚአብሔር ሆኑ ማለት አይደለም፣ በምልጃቸው በጸሎታቸው በተሰጣቸው ጸጋ ይታደጋሉ ያድናሉ ማለት ነው ‹‹ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን?››

3.   ሦስተኛው መላዕክት በሚፈሯቸው ዙሪያ ይሰፍራሉ ያድናሉ (ይመራሉ) ማለት ነው፡፡ እስራኤል ከግብፅ ምድር ከባርነት ነፃ ከወጡ በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ መጋቤብሉይ ቅዱስ ሚካኤል ከፊት ከፊታቸው ይመራቸው ነበር (ዘጻ 23፡20)
በመሆኑም የእግዚአብሔር መላዕክ መምራቱ ማዳን ይባላል ለምን ሕዝቡ ወደ ክፉ ነገር ከመግባታቸው በማይሆን አቅጣጫ ከመሄዳቸው በፊት መንገዱን ማሳየቱ ማዳን ነው ይህንን ማማለዳቸውን፣ መጠበቃቸውን መምራታቸውን ነው ማዳን ያለው ዳዊት በመዝሙሩ ‹‹የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ዙሪያ ይሰፍራል ያድናቸውማል›› መዝ 33፡7 ሲል እንጂ አዳምን በጥንተ ተፈጥሮ በሥጋ ተፈጥሮ ወይም በአዲስ ተፈጥሮ ወደ ቀደመ ክብሩ ይመለሳል ማለት አይደለም፣ ያን ያደረገው ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡
                                              ለ/ የቅዱሳን ጻድቃን የቅዱሳን ሰማዕታት ማዳን
ስለ ቅዱሳን አዳኝነትም ስንናገር ልክ እንደመላዕክት ሁሉ በጸሎታቸው በምልጃቸው በተሰጣቸው ቃል ኪዳን ያድናሉ ይራዳሉ ከክፉ ይታደጋሉ ማለት ነው እግዚአብሔር ለቅዱሳኑ በተለያየ ዘመን ቃል ኪዳን ሰጥቷል፣ ወደፊትም ይሰጣል ደግሞም እግዚአብሔር ለቅዱሳኑ በገባው ቃል ኪዳን መሠረት ይታደጋል ያድናል

 


‹‹ከመረጥኳቸው ጋራ ቃል ኪዳኔን አደረግሁ›› መዝ 88፡3 ብሎ እንደተናገረ ቅዱስ ዳዊት፣ ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ቃል ኪዳን ስለተገባላቸው ስለተመረጡት ስለቅዱሳት የመከራው ቀን ፊተናው እንደሚቀንስ ጊዜው እንደሚያጥር እንዲህ በማለት አስተምሯል ‹‹እውነት እላችኋለሁ እነዚያ ቀኖችስ ባያጥሩ ኖሮ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር ነገር ግን እነዚያ ቀኖች ስለ ተመረጡት (ስለ ቅዱሳኑ) ሰዎች ያጥራሉ›› (ማቴ 24፡22) በዚያ ቃል ኪዳን ለሚታመኑት ሁሉ ከሲኦል ግዛት ከዲያብሎስ ግርፋት ያድናል ይታደጋል ይሁን ይደረግልን አሜን ቅዱሳን በተሰጣቸው ጻጋ በነፍሳቸው ተወራርደው እባክህ ማርልኝ ብለው ይለምናሉና ይጸልያሉና ‹‹ሊቀነቢያት ሙሴ ሕዝቡ በበደለ ጊዜ እግዚአብሔር ሊያጠፋ ሲነሣ ይህን ሕዝብ ከምታጠፋ እኔን ከሕይወት መዝገብ ደምስሰኝ በማለት እንደጸለየ›› (መዝ 105፡23)
ማዳን የባሕርይ ገንዘቡ የሆነ እግዚአብሔር ብቻ ነው ቅዱሳን ግን ይህንን በጸጋ ከአምላካቸው ከእግዚአብሔር ተቀብለዋል፣ በመሆኑም የጻጋ አምላክ እስከመባል የደረሱ ቅዱሳን ወገኖቻቸውን ወንድሞቻቸውን የመርዳት ጻጋ ተቀብለዋል (ዘጻ 7፡1)
ነገር ግን በቅዱሳን አማላጅነት ለመጠቀም የመጀመሪያው ማዳን አምኖ መቀበል ግድ ይላል ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያም ተወልዶ በገዳመ ቆሮንጦስ ጾሞ ጸልዬ ከዲያብሎስ ተፈትኖ በ30 ዘመኑ በባሕረ ዮርዳኖስ ተጠምቆ በዕለተ አርብ ተሰቅሎ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍሶ ማዳኑን ማመን አለበት፡፡ ምክንያቱም ቅዱሳኑ የሚያማልዱት በዚህ መንገድ ሲጓዙ የደከሙትን ነው ሐዋርያው በዕብራውያን መልዕክቱ ይህንን ግልጽ አድርጎ ጽፎታል (ዕብ 1፡14) ‹‹ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ሰላላቸው ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን?›› ይህ ማለት በኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት አምነው ሥጋውና ደሙን ተቀብለው ተጠምቀው ወደ እግዚአብሔር መንገድ ሲሄዱ የሚድሙትን የሚሰናከሉትን ወደ ኋላ የሚቀሩትን የሚወድቁትን እነዚህን በጸሎታቸው በምልጃቸው ያግዛሉ ይራዳሉ ያለው ይህን ነው ምክንያቱም መራዳት መተካት ማለት አይደለምና አንድን ሰው ተክተን ከሰራን ረዳን አይባልም፣ ቅዱሳን መላዕክት ፣ ጻድቃን ይራዱናል፣ ያግዙናል መቼ ነው የሚራዱን የሚያግዙን ቢባል ንስሐ ለመግባት ሥጋ ወደሙን ለመቀበል ፈልጎ ነገር ግን ካልቻለ ከአቅሙ በላይ ከሆነ ሰይጣን ማህበራዊ ችግር ቤተሰባዊ ችግር የትዳር ችግር የንግድ ችግር የትምህርት ችግር የጤና ችግር እያመጣ ካሰናከለው ነገር ግን ቅዱሳን መላዕክት ቅዱሳን ጻድቃን በጸሎታቸው በምልጃቸው ይራዱንና ከዚህ ወጥመድ እንድንወጣ ያደርጉናል ይህ ማዳን ይባላል ‹‹በዳን 3 ላይ ቅዱስ ገብርኤል ሰልስቱ ደቂቅን አዳነ›› የጻድቃን የሰማዕታትም ማዳን ይህ ነው፣ እኛ በምናደርገው ተጋድሎ እንደክማለን፣ ያቅተናል ከአቅማችን በላይ ሲሆን በምልጃቸው በጸሎታቸው አምነን ተማምነን ተማጸን ይረዱናል ያግዙናል፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንኳን አገልግሎቱ የተሳካ እንዲሆንና እንዲሰፋ እግዚአብሔር ከክፉ ሰዎችም ያድነው ዘንድ ጸልዩልኝ ይል ነበር (1ኛ ተሰ 5፡25) ‹‹በቀረውስ ወንድሞች ሆይ የጌታ ቃል እንዲሮጥ በእናንተም ዘንድ ደግሞ እንደሚሆን እንዲከበር እምነትም ለሁሉ ስለማይሆን ከአመጸኞችና ከክፊዎች ሰዎች እንድንድን ስለ እኛ ጸልዩ›› (2ኛ ተሰ 3፡1) ቅዱስ ጳውሎስ የማይጸልይ ሆኖ ሳይሆን ጸልዩልኝ ያለው ሥጋን የለበሰ ሁሉ ድካም አለበትና ሊቅ እስከ ደቂቅ ጸሎት የማያስፈልገው እርዳታ የማያስፈልገው የለምና፡፡




ጸሎተኛ የሚባለው እንኳ በጸሎት እንዳይደክም ጸሎት እርዳታ ያስፈልገዋል በክርስትና አንዱ አንዱን መርዳት ያለ የነበረ የሚኖር ነው ይህንን ቅዱስ ያዕቆብ ‹‹እያንዳንዱ ስለሌላው ይጸልይ፣ የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች›› (ያዕ 5፡16)
አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም ‹‹የሚያጭድ ደመወዝን ይቀበላል የሚዘራና የሚያጭድም አብረው ደስ እንዲላቸው ለዘላለም ሕይወት ፍሬን ይሰበስባል አንዱ ይዘራል አንዱም ያጭዳል የሚለው ቃል በዚህ እውነት ሆኗልና፡፡ እኔም እናንተ ያልደከማችሁበትን ታጭዱ ዘንድ ሰደድኳችሁ ሌሎች ደከሙ እናንተም በድካማቸው ገባችሁ›› (ዮሐ 4፡36-38) ይህ ማለት ከእኛም በፊት ሆነ ከእኛ ጎን የበረቱ ብዙ ብርቱዎች አሉ፣ በእነሱ ድካም እኛ እንገባለን ይህ የክርስትና ሕይወት ነው ብርቱዎች ይደክማሉ ሰነፎች ደግሞ በብርቱዎች ድካም ይገባሉ፡፡ ሰነፎች ማለት ሲጸልዩ ሲጾሙ ሲሰግዱ አቅም ያነሳቸው ማለት ነው እንጂ ምንም ሳይሰሩ ሳይንቀሳቀሱ የተቀመጡትን አይደለም ክርስትና እንቅስቃሴ ነው የሩጫ ሕይወት ነው ቁጭ ብሎ ክርስትና የለም ሰው መጸለይ ሊያቅተው ይችላል መጾም ሊያቅተው ይችላል፣ በጤናና በተለያየ ምክንያት መስገድ ሊያቅተው ይችላል፣ እነዚህ በብርቱዎች ምልጃ እርዳታና ጸሎት ይገባሉ፡፡
መጸለይ አለመቻልና መጸለይ አለመፈለግ የተለያዩ ናቸው መጸለይ ያልቻለ ሰው ጌታ ሆይ መጸለይ እፈልግ ነበር ነገር ግን አልቻልኩም ማለት ይኖርበታል ቅዱሳንም የሚራዱት እየሞከሩ አቅም ያጡትን የደከሙትን ነው ስለዚህም መንን ይወርሱ ዘንድ ያላቸውን የሚራዱ ያለው ሐዋርያው ይህንን ነው ፡፡
ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ አንዱ አንዱን ያድናል እርስ በእርስ በወንጌል ስንማማር ወንድማችንን ከክፉ ስንመልሰው ከኃጢዓት መክረን ስናመጣው ተስፋ ከመቁረጥ ስንመልሰው ማዳን ይባላል ይሄ ማዳን ማለት ደግሞ በድኅነቱ መንገድ ማሳየታችን ነው ማዳን የተባለው ወዳጄ ከክፉ ነገር አወጣኝ ከጸጸት አትረፈኝ ተስፋ ከመቁረጥ አዳነኝ ብለን የምንናገረው ማለት ነው ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ በመልዕክቱ ይህን አይነቱን ማዳን እንዲህ ጽፎታል ‹‹ወንድሞች ሆይ ከእናንተ ማንም በእውነት ቢስት አንዱም ቢመልሰው ኃጢዓተኛን ከተሳሳተበት መንገድ የሚመልሰው ነፍሱን ከሞት እንዲያድን የኃጢዓትንም ብዛት እንዲሸፍን ይወቅ›› (ያዕ 5፡20)
ይሄ ማዳን ግን እንደ ቅዱሳኑ ያለ ማዳንም አይደለም፣ እንደ ጸበሉና እምነቱ ያለም ማዳን አይደለም ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳዳነውም ያለ አይደለም፣ መምከር ማስተማር መመለስ ሲሆን ይህ ማዳን ይባላል፡፡
በመሆኑም ማዳን ብለን ስንል ኢየሱስ ክርስቶስ ያድናል፣ መስቀል ያድናል፣ ቅዱሳን ያድናሉ፣ መላዕክት ያድናሉ፣ ስንል ዓይነቱንና ልዩነቱን ተረድተን ነው፣ መጻሕፍትም ይህን ቀላቅሎ አይደለም የጻፈው ሁሉን በምስጢር በዓይነትና በልዩነት ነው በአጠቃላይ የሁሉም ማዳን ከእግዚአብሔር ማዳን የሚመነጭ ነው እግዚአብሔር በባሕርይው ያለውን ለቅዱሳን በጸጋው ስለሰጠ አምላክ ነው በባሕርይው አማልክት ዘበጸጋ ይባሉ ዘንድ ሰጥቷል፣ ሕያው ነው በባሕርይው ሕያዋን እንሆን ዘንድ ሰጥቷል፡፡ ዘላለማዊ ነው በባሕርይው ዘላለማዊውን ሕይወት እንድንወርስ ፈቅዷል ሰማያዊ ነው ሰማያውያን እንድንሆንም ፈቅዷል ያልፈቀደውና ያልተሰጠን ጸጋ የለም ነገር ግን በትዕቢት በኩራት በኑፋቄ ወይም በጥርጥር አናገኘውም እንጂ በጽድቅ በትህትና የማናገኘው ምንም ነገር የለም በመሆኑም ማዳን የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ቢሆንም እንኳን ቅዱሳን በጸሎታቸውና በምልጃቸው መላዕክት በተራዳኢነታቸው መምህራን በትምህርታቸው ባልንጀሮች በምክራቸው በተግሳጻቸው እንዲያድኑ ፈቅዷል ጸጋውንም ሰጥቷል፡፡ መዳን ስንል ይህን ማለታችን ነው በተለያየ ጊዜ መጻሕፍትን ስናነብ ወይም የተለያየ ነገር ስናይ ስለ ቅዱሳን ማዳን፣ ስለ መላዕክት ማዳን ስለጸበሉ ማዳን ሲነገር ሌላ ነገር የሚመስላቸው ወገኖች አሉ ‹‹ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አባቴ ገበሬ ነው እኔም እውነተኛ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ ነው ያለው›› (ዮሐ 14፡1-5) በመሆኑም ስለ ዛፉ በአጠቃላይ መናገር ስለ ቅርንጫፍ መናገር ነው፣ ስለግንዱም መናገር ነው ቅርንጫፍ ደረቀ ስንል ዛፉ ደረቀ ማለታችን ነው ወይም ቅርንጫፍ ለመለመ ስንል ዛፉ ለመለመ ማለታችን ነው፡፡
እንደዚሁ ሁሉ ስለ ተክለሃይማኖት ቅርንጫፍ ስለሆኑት፣ ስለ ገብረመንፈስ ቅዱስ ስለ ሌሎችም ቅዱሳን መናገር ስለ ክርስቶስ የወይን ግንድ (የወይን ዛፍ) ስለሆነው መናገር ነው ወይም ደግሞ በሌላ ምሳሌ እርሱ አካል ነው እኛም ብልቶች ነን ተብሏል፡፡ እናም አንድ እጅ ቢታመም፣ እግሩ ቢታመም እጅና እግሩን አይደለም ሐኪም ቤት የሚልከው አንድ ብልት ቢታመም መላ አካል ነው ወደ ሐኪም ቤት የሚሄድ ይህም የሆነበት ስለ ብልቱ ሕመም ማውራት ስለ ሰውየው አካል ማውራትና መናገር ስለሆነ ነው፡፡
ለዚህም ነው በአንድ ኃጢዓተኛ ንስሐ መግባት በሰማይ መላዕክት ዘንድ ታላቅ ደስታ ይሆናል የተባለው (ሉቃ 15፡10) በእኛና በመላዕክት መካከል ያለው ግንኙነት አንድ አካል ብልቶች ስለሆን ነው ሚካኤል አዳነን ስንል እግዚአብሔር አዳነን ማለታችን ነው ለቅዱስ ሚካኤል ጸጋውን ባይሰጠው ፈቃዱን ባይሰጠው አያደርገውምና፡፡ ተክለሃይማኖት አዳነን፣ አቡየ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አዳነን፣ ቅድስት አርሴማ አዳነችን ስንል እግዚአብሔር አዳነን ማለታችን ነው ምክንያቱም እግዚአብሔር በተክለሃይማኖት ላይ አድሮ ስራውን ሰራ አዳነን ማለታችን ነው እኛ ድንግል ማርያም ታድነናለች ስንል እግዚአብሔር በሰጣት ቃል ኪዳን የማማለድ ጸጋ ሞገስ ታድነናለች የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው ማለታችን ነው፡፡ ይህንንም ስንናገር የማዳንን ልዩነት ከላይ በተገለጸው መሠረት ተረድተንና አውቀን ነው፡፡
ይቀጥላል…






4 comments:

  1. Hello I am so delighted I found your weblog, I really found you by error, while I was browsing on Askjeeve for something else, Anyhow I am here now and would just like to say cheers for a remarkable post and a all round interesting blog (I also love the theme/design), I don_t have time to read it all at the minute but I have book-marked it and also added in your RSS feeds, so when I have time I will be back to read more, Please do keep up the superb b.
    ranjang pasien murah

    ReplyDelete
  2. I am very educated and I am grateful if I get the amount of grace I earned part from 1st and 2nd, and if I got the next one, I was lucky.

    ReplyDelete
  3. I am very educated and I am grateful if I get the amount of grace I earned part from 1st and 2nd, and if I got the next one, I was lucky.

    ReplyDelete