Monday, February 10, 2014

‹‹የክርስቶስ የማስታረቅ አገልግሎት በሞቱ ተፈጽሟል››




‹‹የሉተራውያን ስህተት በሊቃውንት አስተምህሮ ሲገለጥ ሲጋለጥ ››
(ክፍል ሦስት)  
‹‹የክርስቶስ የማስታረቅ አገልግሎት በሞቱ ተፈጽሟል››

ቅዱሳን ሐዋርያት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክነት በስፋት አስተምረዋል መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር መሆኑን በሚገባ ይነግረናል ቅዱሳን አባቶቻችን ሊቃውንትና ቅዱሳት መጻሕፍትም ክርስቶስ ፈራጅ ጌታ እውነተኛ አምላክ መሆኑን አመስጥረው ይነግሩናል፡፡ ታድያ ጌታ መድኅኒዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ ፈጣሬ ዓለማት ፈራጅ ሕያው አምላክ ቅዱስ እግዚአብሔር ሆኖ ሳለ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እርሱን በሚመለከት ለምን የምልጃ ቃላት ሊነገሩለት ቻሉ? ይህን መሠረታዊ ጥያቄ በዚህ ጽሑፍ አጠር አድርገን እንመልሳለን፡፡




ጌታችን ዓለምን ያዳነበት መንገድ የማስታረቅ አገልግሎት ይባላል የባሕርይ አምላክ ሲሆን በለበሰው ሥጋ ስለ እኛ ለምኗል፣ አማልዷል፣ አስታርቆናል እርቅ ጥል ባላቸው በሁለት አካት መካከል አስፈላጊው ድርድር ከተከናወነ በኋላ ነው የሚፈጸመው አማላጅ ደግሞ በሁለት አካት መካከል ገብቶ አንዱን ከሌላው የሚለምን ሦስተኛ አካል ማለት ነው፡፡
አስታራቂው ወይም አማላጅ አካል የጥሉን ጉዳይ በጥልቀት የሚያውቅና መፍትሔም የሚያመጣ መሆን አለበት አማላጅነት ደግሞ ምንም እንኳን በአምላክ ፊት ክብርና ሞገስን ያስገኘ ቃልኪዳን የተገባለት ቅዱስ ቢሆንም ስለወቅታዊ ችግር ፈጣሪውን መለመን ይችላል እንጂ ትውልዱን ለተቆራኘው አዳማዊ በደል ስርየት መስጠትም ሆነ ማሰጠት አይቻለውም (አልተቻለውም)፡፡ የጥሉን ግርግዳ ለማስወገድ የሚቻለው እርሱ ራሱ እግዚአብሔር ካልሆነ በቀር ፍጹምነት ያለው እርቅ የለም ነበር በመሆኑም በአምላክነቱ አምላክ እንደ ሰውነቱ ደግሞ ፍጹም ሰው የሆነው ክርስቶስ የማስታረቅ ሥራውን ሠርቷል ስለዚህ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ እግዚአብሔር ልጅነቱ የተበደለውን አምላክ ወክሎ እንደ ሰውነቱ ደግሞ በደለኞች የሆንን እኛን ወክሎ ራሱ መስዋዕት አቅራቢ፣ ራሱ መስዋዕት ተቀባይ ፣ ራሱ መስዋዕት ሆኖ በመስቀል ላይ ውሎ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስና ራሱ ጋር አስታረቀን፡፡ (ነገረ ሥጋዌ) ለዚህም ነው ሐዋርያው ‹‹በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድር ወይም በሰማያት ያሉትን ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዷል›› ያለው፡፡ (ቆላ 1፡19) ይህ ነው እንግዲህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በ1ጢሞ 2፡5 ላይ እና በዕብ 12፡24 ላይ የሐዲስ ኪዳን መካከለኛ ያስባለው፡፡
ይህንኑ የማስታረቅ አገልግሎት ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው መልዕክቱ ላይ እንዲህ ይገልጸዋል ‹‹እንደሠራነው ዋጋችንን እንቀበል ዘንድ ሁላችን በክርስቶስ የፍርድ ዙፋን ፊት እንቆማለን… አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ…. የሆነው ሁሉ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሠጠን ከእግዚአብሔር ነው እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር በእኛም የማስታረቅን ቃል አኖረ እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማለድ ስለ ክርስቶስ መልዕክተኞች ነን›› (2ቆሮ 5፡10-21)
በዕብ 7፡25 ላይ ‹‹ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራል›› ተብሎም ተጽፏልና ይህንንም ማየቱ አስፈላጊ ነው በመሠረቱ ይህንን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከላይ ከዕብ 7፡11 ጀምሮ በደንብ ላስተዋለው ሰው አነጋገሩ በጣም ግልጽ ነው፡፡ ሐዋርያው የኦሪትና የሐዲስ ኪዳኑን ክህነት እያነጻጸረ ነው የጻፈው፣ በሌዊ ክህነት ፍጹምነት እንዳልተገኘ የእነ አሮንም ሹመት እንዳለፈችና እንደ ምልከጼዴቅ ሌላ ካህን ማስፈለጉን በዚህም ምክንያት በመልከጼዴቅ አምሳል ሌላ ካህን ከነገደ ይሁዳ መውጣቱንና ይህም በሊቀ ካህናችን በኢየሱስ ክርስቶስ መፈጸሙን ይናገራል፡፡
ቁጥር 17 ላይም ‹‹እንደ መልከጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን አንተ ነህ›› ሲል ያስቀምጠዋል ኦሪት ደካማ ሥርዓት ስለነበረች ግዳጇን አልፈጸመችም፣ ፍጹም የሰው ልጅ ድኅነት አልተገኘባትም ነበር ካህኑ ለኃጢዓት ማስተሰርያ እንሰሳትን መስዋዕት አድርጎ የሚረጨው ደም የአዳምን የውርስ ኃጢዓት ሊያነፃ በፍጹም አልቻለም ነበርና በእሷ በኦሪት ፈንታ ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት ተስፋ ገብቷል እያለ ነው ቅዱስ ጳውሎስ የሚያብራራው ከታች ዝቅ ብሎ ከቁጥር 24 ጀምሮ ‹‹እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው ስለ እነርሱም ሊማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል እንደ እዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ይገባልና እርሱም እንደነዚያ (እንደኦሪቶቹ) ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ ስለራሱ ኃጢዓት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢዓት ዕለት ዕለት መስዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጓልና›› (ዕብ 7፡27) ለነገሩ ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል መናፍቃኑ ለምንፍቅና ትምህርታቸው እንዲመቻቸው ‹‹ስለ እነርሱ ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራል›› ብለው ያጣሙት እንጂ ቆየት ብሎ በታተመው መጽሐፍ ቅዱስ (1960) ላይ ግን እንደዚህ አይደለም የተቀመጠው ትክክለኛው ቃል ‹‹ክህነቱ አይሻርምና ዘወትር በእርሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡትን ሊያድናቸው ይቻለዋል ለዘላለም ሕያው ነውና ያስታርቃቸዋል›› ነው የሚለው (ዕብ 7፡24-25) ይህስ ቢሆን ምን ማለት ነው?
ጌታችን ራሱ መስዋዕት አቅራቢ ራሱ መስዋዕት ፣ ራሱ መስዋዕት ተቀባይ ሆኖ አንድ ጊዜ ብቻ ራሱን ባቀረበው መስዋዕት ለዘላለም ኃጢዓታችንን ያስተሰርይልናል፡፡
አንድ ጊዜ በመስቀል ላይ ያፈሰሰው ደም ያለፈውንም ሆነ የሚመጣውን ትውልድ ለዘላለም ያስታርቀዋል እንጂ እንደ ኦሪቱ ሥርዓት ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው ‹‹ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም›› ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጓልና ስለዚህ እኛም ፍጹም ድኅነትን ያገኘነው አንድ ጊዜ በሠራልን የክህነት ስራ ነው በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድራዊ ወይም በሰማያት ያሉትን ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዷል (ቆላ 1፡19) ተብሎ እንደተጻፈ ይህ የሠራልን የክህነቱ ሥራው ነው ዘወትር ሲያስታርቀን የሚኖረው አሁንም ያማልደናል ካልን ግን ክርስቶስ ዕለት ዕለት ኃጢዓት በሠራን ቁጥር መሞት አለበት ማለት ነው፡፡
ምክንያቱም ዓለም ፍጹም ድኅነት ያገኘችው በእርሱ ሞት ብቻ ነውና እግዚአብሔር ለቃየል ‹‹የወንድምህ የደሙ ድምጽ ከምድር ወደ እኔ ይጮሀል›› ሲል ተናግሮታል (ዘፍ 4፡10) ታዲያ የአቤል ደም ጩኸት እግዚአብሔር ጋር መድረሱን ከነገረን እርሱ ራሱ ለእኛ ሲል ያፈሰሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ደምማ ምን ያህል ስለእኛ የጩኸት ድምፁን ሲያሰማ ይኖር ይሆን!! ወይም በሌላ አገላለጽ እንዲህ ማለት ለምሳሌ ቅዱስ ጴጥሮስ አንካሳውን ሰውዬ ‹‹በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሣና ተመላለስ›› ሲለው ተነሥቶ ተመላልሷል ጴጥሮስ ‹‹ተነሣና ተመላለስ›› ብሎ ሲናገር አንድ አንካሳ ብቻ ዳነ እንጂ ለዚህ አንከሳ የተነገረው ቃል በጴጥሮስ እጅ ሊተፈወሱ ሌሎች ብዙ አንካሶች አልሠራም ማለትም ለሁሉም አንካሶች እንደገና ለእያንዳንዳቸው ‹‹ተነሣና ተመላለስ›› ተብሎ መነገር አለበት፡፡ ይህ የሚያሳየው በፍጡራን አንድ ጊዜ የተነገረው ቃል ሥራ የሚሰራው አንድ ጊዜ ብቻ ነው ማለት ነው፡፡
የፈጣሪ ቃል ግን እንዲህ አይደለም ፈጣሪ አንድ ጊዜ የተናገረው ቃል ለዘላለም ጸንቶ ነው የሚኖረው ለምሳሌ እግዚአብሔር ዓለሙን ሲፈጥር ‹‹ይሁን ይሁን›› እያለ የፈጠረው ፍጥረት ሁሉ ይኸው አንድ ጊዜ በተናገረው ቃል እስከ ዕለተ ምጽዓት ‹‹ሁኑ›› እንዳላቸው ሆነው ተገኝተዋል ‹‹ቀንና ሌሊት ይለዩ›› (ዘፍ 1፡14) ብሎ አንድ ጊዜ ብቻ በተናገረው ቃሉ ይኸው ቀንና ሌሊት እየተፈራረቁ ነው ይህም በፈጣሪ አንድ ጊዜ የተነገረው ቃል ዘላለማዊ ሥራ እንደሚሠራ ነው የሚያሳየን <<< (1) እናም ‹‹ለዘላለም ሕያው ነውና ያስታርቃቸዋል›› ወይም መናፍቃኑ እንደሚሉት ‹‹ሲያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራል›› ተብሎ ቢነገረም እንኳን ትርጉሙ ከዚዘሀ ከላይ ካየነው የተለየ አይደለም ‹‹ራሱን መስዋዕት አድርጎ ባቀረበ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎልናልና›› እንደተባለው ጌታችንም ‹‹የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው›› ብሎ ማስታረቅን ያጠቃለለበት ያው አንዴ የተናገረው የምልጃ ቃል ክርስቶስ ደጋግሞ ሳያማልድ የሚመጣውንም ሁሉንም ትውልድ የሚያስታርቅ ነው፡፡
‹‹ተፈጸመ›› ያለውም ይህንኑ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታረቀበትን ሥራ ነው ያው አንድ ጊዜ በመስቀል ላይ የተነገረ ቃል የአምላክ ቃል ነውና ለዘወትር ይጸናል፡፡ ልክ እግዚአብሔር ‹‹ቀንና ሌሊት ይለዩ›› ብሎ አንዴ በተናገረው ቃል መሠረት ቀንና ሌሊት እየተፈራረቁ እስከ ዕለተ ምጽዓት ድረስ እንደሚቆዩት ማለት ነው ከዚህ ውጪ ግን ክርስቶስ ያን በሞቱ አንድ ጊዜ የፈጸመውን የማዳን የማስታረቅ ሥራ አሁንም ይሠራል ብሎ ማመን ከኑፋቄም በላይ ክህደት ነው የእግዚአብሔርንም ፍቅሩን አለማወቅም እኛም አልዳንም ክርስቶስም እንደገና መጥቶ መሞት አለበት ማለት ነው፡፡
በአጠቃላይ ሐዋርያት የክርስቶስን ስም ከምልጃ ጋር ቢጠቅሱም እንኳን እስካሁን ባየነው መልኩ ነው መታየት ያለበት ከዚህ ውጪ ግን ራሱ ጌታችን ለሐዋርያት በዚያች ቀን (ከትንሣኤ በኋላ) በስሜ ትለምናላችሁ እኔም ስለ እናንተ አብን አለምንም (ዮሐ 16፡26) ብሏቸው እያለ ‹‹አይ አንተ ከትንሣኤህ በኋላ ታማልዳለህ›› ብለው አይቃወሙትም ‹‹ብትወዱኝስ ትዕዛዜን ጠብቁ›› ያላቸውን አምላክ ጠንቅቀው ያውቁታል ደግሞስ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ክርስቶስ ከትንሣኤው በኋላ በሥጋው ወራት እንደምናውቀው ከእንግዲህ ወዲያ እኛም ሐዋርያቱ ብንሆን በሥጋ እንዳወቅነው አናውቀውም›› በማለት ነው የጻፈው (2ቆሮ 5፡16-18) ይህ ማለት በአጭሩ ያማለደን በሥጋው ወራት ብቻ ነው፣ ከሞተ በኋላ ግን አያማልደንም ማለት ነው እንዲያውም እዚያው ላይ ቁጥር 19 ጀምሮ ‹‹በእኛም የማስታረቅን ቃል አኖረ፣ የማስታረቅን ሥልጣን ለእኛ ሰጠን እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማለድ ዕወቁ›› ነው ያለው፡፡
ሉተራውያን (መናፍቃን) ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ለራሳቸው የስህተት ትምህርት እንዲመች እንደሚማለድ የሚለውን ‹ለ› ን ‹ል› ቀይረው እንደሚማልድ ብለው አጣመውታል ነገር ግን የአማርኛው የአነባበብ ዘይቤ ከዋናው ሐሳብ ጋር እነሱ ባጠመሙት መንገድ ትርጉም አይሰጥም፡፡
በመሆኑም የክርስቶስ የማስታረቅ ሥራ የማማለድ አገልግሎት በመስቀል ላይ በፈሰሰው ደሙ በመስዋዕትነት ተፈጽሟል፡፡
‹‹ነገር ግን የሆነው ሁሉ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን (ከባሕርይ አባቱ ከአብ፣ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ) ጋር በሥልጣን፣ በአገዛዝ፣ በሕልውና አንድ ስለሆኑ) የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን ከእግዚአብሔር (የሦስትነትና የአንድነት ስማቸው) ነው አንድም ኢየሱስ ራሱ እግዚአብሔር ነው፣) እግዚአብሔር ‹‹በክርስቶስ ሆኖ›› (ሥጋን ለብሶ ሰው ሆኖ) ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበር›› (ኀላፊ ቃል) በደላቸውንም አይቆጥርባቸውም ነበር በእኛም የማስታረቅን ቃል አኖረ እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማለድ ስለ ክርስቶስ መልዕክተኞች ነን ከእግዚአብሔር ጋር ታረቀ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን እናማልዳለን›› (2ቆሮ 5፡18-21)
ይቀጥላል
  
   


No comments:

Post a Comment