Tuesday, October 14, 2014

ማዕተብ የክርስቲያን ዓርማ


"ማህተብህን በአንገትህ እሰረው ስትሔድ ይመራሃል

ስትተኛ ይጠብቅሃል" ምሳ 6÷21
 

 

የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስቲያኖች በአንገታቸው ላይ ክር ያስራሉ ለሕፃናቶቻቸውም ክርስትና ሲነሱ ክር ያስሩላቸዋል በሕፃናቱም ሆነ በአዋቂዎቹ ክርስቲያኖች የሚታሰረው ክር በግዕዝ ማዕተብ በአማርኛ ማተብ ይባላል፡፡ ቃሉ የወጣው ዐተበ ካለው ግዕዛዊ ግሥ ሲሆን ዐተበ ፍቺው አመለከተ ባረከ ማለት ነው፣ ማዕተብ ከዚህ ይወጣል ምልክት ማለት ነው፡፡ ለተጠመቁ ክርስቲያኖች የክር ማዕተብ ለሃይማኖት ምልክትነት ወይም መታወቂያ ከመሆኑ በፊት በብሉይ ኪዳን ዘመን የሃይማኖት አባቶች ከጣዖት አምላኪዎች ተለይተው የሚታወቁበት ምልክት ነበራቸው፡፡




ስለ ታላቁ የሃይማኖት አባት ስለ ፃድቁ አብርሃም የሃይማኖት ማኅተም (ምልክት) ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል ሳይገረዝም በነበረው እምነት ያገኘው የፃድቅ ማኅተም የሆነ የመገረዝን ምልክት ተቀበለ" (ሮሜ ፬÷11 ፣ ዘፍ ፲፯÷፱-፲፬)

በሥርዓተ ኦሪት ብኩርና ከጥንት ጀምሮ ለእግዚአብሔር የተለየ ገንዘብ ሆኖ ስለሚቆጠር ብኩርና ላለው ሁሉ የአባት በረከት ከሌሎች ይልቅ በይበልጥና ምርቃት ዕጥፍ ድርብ ሆኖ ስለሚሰጠው ብኩርና ይወደዳል ይፈቀራል ብኩርናን ማቃለል ዋጋ የሌለው ፀፀትን ያስከትል ነበር፡፡ ብኩርና ለዘመነ ሐዲስ ክርስትና ምሳሌ እንደሆነ ይታመናል፡፡

ክርስትናውን ንቆ አቃሎ አለምን መስሎ የሚኖር ሰው በኩርነቱን ለሆዱ ጊዜያዊ ፍላጎት በሸጠው በያዕቆብ ወንድም በኤሳው ተመስሏል፡፡ "ስለ አንድ መብል በኩርነቱን እንደሸጠው እንደ፣ ኤሳው ለዚህ ዓለም የሚመች ሰው እንዳይሆን ተጠንቀቁ ከዚህ በኋላ እንኳ በረከቱን ሊወርስ በወደደ ጊዜ እንደ ተጣለ ታውቃላችሁና በእንባ ተግቶ ምንም ቢፈልገው ለንስሐ ሥፍራ አላገኘምና" (ዕብ ፲፪÷፲፮-፲፯ ዘፍ ፳፭÷፴፬ ፣ ዘፍ ፳÷፵) ብኩርና ለክርስትና ምሳሌ መሆኑ ከላይ ተገልጿል፡፡

ከይሁዳ ትዕማር መንትያ ልጆችን ፀንሳ በምትወልድበት ጊዜ በኩር እጆቹን ሲያወጣ አዋላጅቱ ቀይ ፈትል ለምልክት አስራበታለች፡፡ ይህ ምሳሌያዊ ድርጊት በሐዲስ ኪዳን ሲተረጎም ከትዕማር የተወለደው በኩሩ ዛራ ለክርስቲያን ምሳሌ ሲሆን ቀዩ ፈትል ለክርስትናው ምልክት ለማዕተብ ምሳሌ ሆኗል፡፡

አዋላጂቱ ለአጥማቂው ቄስ ምሳሌ ናት ትዕማር የቤተክርስቲያን ምሳሌ ስትሆን በኋላ የወጣው ፍሬስ በኩሩን ጥሶ ቀድሞ መወለዱና ከቀይ ፈትል አልባ መሆኑ በምሳሌያዊ ትንቢትነት ከቤተክርስቲያን ከጥምቀት የፀጋ ልጅነትን አግኝተው ከተወለዱ በኋላ ክርስትናቸውንና ጥምቀታቸውን ክደው የእውነተኞቹ ክርስቲያኖች ተቃዋሚዎች በመሆን ፊት ከተፈጠረ ጆሮ እንደ ቀንድ ብቅ ያሉ የመናፍቃን ወይም የኢጥሙቃን ኢ-አማንያን ምሳሌ እንደሆኑ ሊቃውንት በትርጓሜ ያስተምራሉ፡፡ (ማቴ ፩÷፫ ዘፍ ፴፭÷፳፮-፴) በዛራ ልማድ ጌታችን ከድንግል ማርያም በተወለደ ጊዜ እመቤታችን አውራ ጣቱን በክር አስራዋለች፡፡ ቅ/ገብርኤል ለእረኞች ተገልጦ ምልክቱን እንዲህ ሲል ነግሯቸዋል "ወከመዝ ትእምርቱ ለክሙ ትረክቡ ሕፃነ እሱረ መንኮብያቲሁ…" ምልክቱ ይህ ነው ሕፃኑ አውራ ጣቱ ታስኖ ታገኙታላችሁ፡፡" ሉቃ ፪÷፲፪ ማስረጃው "ወወለደት ወልደ ዘበኩራ ወአሠርቶ መንኮብያቲሁ የበኩር ልጅዋን ወለደች አውራ ጣቱን አሰረችው ሉቃ ፪÷፯

በመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር የታተመው የአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ የተወሰነውን ገድፎታል፡፡ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የታተመውን ግዕዝና አማርኛ ነጠላ ትርጉም ሐዲስ ኪዳን ብንመለከት እናገኘዋለን፡፡ ድንግል ማርያም አውራ ጣት ማሰሯ ለክርስቲያኖ ማዕተብ ማሠር አብነት ሆኗል፡፡ ጣቱን ማሠሯ ያለምክንያት አልነበረም፡፡ ፩ኛ/ ሕፃን ስለሆነ እንዲያፀናው ፪ኛ/ ጣቱ ባይታሠር ምትሐት ነው ሰው አልሆነም ለሚሉ መናፍቃን ለክህደታቸው ምክንያት ባገኙ ነበርና ምክንያት ለማሳጣት ፫ኛ/ ቀደም ብለን እንደገለጽነው ልማዳችንን አስቀረብን እንዳይሉ በዛራ ልማድ ፬ኛ/ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ በዕለተ ዓርብ ከመስቀል አውርደው እንዲህ አድርገው ይገንዙሃል ለሰው ቤዛ ለመሆን ልትታሠር መጣህን? ስትል ነው፡፡ በማለት መምህራነ ቤተክርስቲያን (ሊቃውንት) በአንድምታ ትርጓሜያቸው ያትታሉ፡፡

በኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ዘንድ ክርስቲያን የሆነ ሁሉ ማተብ የማሠር ልምድ የጀመረው በሃይማኖት አበው በድርሳነ ያዕቆብ መረጃው እንደሚያስረዳው ከልደተ ክርስቶስ በኋላ በእስክንድርያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በአምስተኛው ምዕተ ዓመት ያስተምር በነበረው በሊቀ ጳጳሱ በያዕቆብ ዘእልበረዳኢ ዘመነ ስብከት ነበር፡፡

በኢትዮጵያ ክርስትና የገባው በዘመነ ሐዋርያት መሆኑ ቢታወቅም የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በመንበረ ጵጵስና ከሌሎች ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ጋር የእኩልነት ማዕረግ ያገኘችው በ፬ኛው ምዕተ ዓመት በቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን እንደሆነ ተረጋግጧል፡፡ በዚህ ዘመን አቡነ ሰላማ በሰሜን ያሉትን አጥምቀው ወደ ክርስትና ሲያስገቡ ለክርስትናቸው ምልክት ከግንባራቸው ላይ እየበጡ መስቀለኛ ምልክት ያደርጉላቸው እንደነበር ይተርካል እስከአሁንም አልፎ አልፎ በሰሜናውያን ዘንድ በመብጣትም ሆን በንቅሳት ለክርስትናቸው ምልክት መስቀል ከግንባራቸው ይታያል፡፡ የማዕተብ ማሠር ልምድ ከግብጽ ቤተክርስቲያን ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ ይሠራበት ጀመር በ፱ኙ ቅዱሳን ዘመንም እየተስፋፋ ሔዶ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በቤተክርስቲያን ክርስትና ለሚነሱ ሁሉ ማዕተብ ማሠር ትውፊት ሥርዓት ሆኖ ቆይቷል፡፡

ቀደም ብለን እንደገለጽነት የማዕተብ ማሰር ልምድ በግብጽ ቤተክርስቲያን ያዕቆብ ዘእልበረዳኢ ሲያስተምር እንደጀመረው ጠቅሰናል ያዕቆብ ዘእልበረዳኢ የሶርያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አባት ነው፡፡ መምህሩ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ የእስክንድርያው ሊቀጳጳሳት ስለ ተዋሕዶ ሃይማኖት ሲመሰክር በግድ በቁስጥንጥንያው ንጉስ በመርቅያን ተፅዕኖ በንግስት ብርክልያ በመለካውያን (ልዮናውያንና ንስጥሮሳውያን) ግፊትና ተቃውሞ መከራ ሲቀበል ሳለ በብርክልያ ደንገጡሮች ጽሕሙ ተነጭቶ ጥርሶቹ ረግፈው ስለነበር የተነጨ ጽሕሙን የረገፉ ጥርሶቹን በመሐረም ቋጥሮ "ዝንቱ ፍሬ ሃይማኖቱ ለእግዚአብሔር ለእግዚአብሔር የማናቀርብለት የሃይማኖት ፍሬ ይህ ነው" በማለት ለእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን በያዕቆብ ዘእንበረዳኢ እጅ ልኮለታል፡፡ እሱም ስለ ሃይማኖት በደሴተ ጋግራ ታሥሮ ሙቷል፡፡

ደቀመዝሙሩ ቅዱስ ያዕቆብ አልባሌ መስሎ በሶርያ ብቻ ሳይሆን በእስክንድርያም የሴት ቀሚስ ሳይቀር ለብሶ ሲያስተምር ንስጥሮሳውያን ከጉባኤው እየገቡ ስላስቸገሩት ኦርቶዶክሳውያንን ከመናፍቃን ለመለየት ከእግዚአብሔር ባገኘው ምልክት ጥቁር ቀይ ብጫ ክሮች አንድ ላይ ፈትሎ በአንገታቸው ላይ ያስርላቸው ጀመር ሌሊት ሌሊት ሲያስተምርና ሲፀልይ የቅዱስ ዲዮስቆሮስ ጥርሶቹ እንደ ፋና ያበሩለት ነበር፡፡ ይህም በተአምራት የተፈፀመ ነው ሶስት ቀለማት ያላቸው ክሮች የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ሲሆኑ አንድ ላይ መፈተላቸው ወይም አንድ መሆናቸው ቅድስት ሥላሴ ማለት አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በመለኮት በህልውና አንድ አምላክ መሆናቸውን ያመለክታል፡፡ ጥቁሩ ክርስቲያን ስለሃይማኖት የሚቀበለው መከራ የሚሸከመው መስቀል ሲሆን ቀጡ በሰማዕትነት ደም የማፍሰስ ብጫው የክርስቲያን ተስፋ የሃይማኖት ምልክት ነው፡፡

በኋላ ግን ቆይቶ ቀይ ነጭ ሰማያዊ ፈትሎች በአንድ ላይ ተገምደው በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ሕፃናት ክርስትና ሲነሱ ኢ-አማንያን አምነው ሲጠመቁ መታሰር ጀመረ፡፡ ትርጓሜውም የሶስቱ አንድ ላይ መገመድ ሥላሴን አንድነት ሶስትነት የሚያመለክት ምሳሌ ሲሆን ቀለሞቹ ደግሞ ቀይ ክርስቶስ ደሙን አፍሶ አድኖናል ስለስሙ በሰማዕትነት ደማችንን ማፍሰስ ይገባናል የማለት ሲሆን ነጩ የጥምቀት በጥምቀትም የሚገኝ ሥርየተ ኃጢያት (ከኃጢአት ምንጻት) ሰማያዊ አባት አለኝ (በፀጋ ልጅነት አግኝቻለሁ) ሰማያዊ ርስት መንግስተ ሰማይ ይቆየኛል ስለዚህም በሰማያዊ ግብር ጸንቼ መኖር በሰማያዊ ሕግ ሕገ ክርስቶስ ወንጌል ተመርቼ መኖር ይገባኛል እንደ ማለት ነው፡፡

ይኸንንም ጠቅለል ባለ መልኩ ኢትዮጵያዊው ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ሲያስረዱ ሥላሴ ማዕተበ ብርሃን ኃይል ሃይማኖቶሙ ለክርስቲያን÷ ሥላሴ ለክርስቲያን ሁሉ የሃይማኖታቸው ጉልበት መታወቂያ የብርሃን ማዕተብ (ምልክት) ናቸው ብለዋል፡፡
 

 

 
 

ማዕተብ ያላሠረ ኦርቶዶክሳዊ በውግዘት ከቤተክርስቲያኒቱ እንደ መናፍቅ ተቆጥሮ ባይለይም ማዕተብ አለማሠሩ ግን የአባቶቹ ትውፊት እንዳልተቀበለ ያስቆጥረዋል፡፡ በምሳሌያዊ አነጋገርም ሃይማኖት አልባውን ማለትም ክርስቲያን ያልሆነውን ማተብ የለሽ ያልተጠመቀ አረሚ ይሉታል ክርስቲያን በማተቡ መነኩሴ በቆቡ እንዲታወቅ ማተብ አልባ መሆን ደግሞ ክርስቲያን ይሁን ያልተጠመቀ መሆኑ ለማወቅ ያስቸግራል፡፡ በመለዮዋቸው ሌሎች እንዲታወቁ ክርስቲያን በማተቡ ክርስትናውን ሲያሳውቅ ኖሯል፡፡

በተለመደው አነጋገር እገሌ ማተብ አለው ባለማተብ ነው ሲባል እገሌ ታማኝ ክርስቲያን ነው እውነተኛ ሐቀኛ ነው የማለት ትርጉምን ይሰጣል "ባለማተቢቱ" ሲባል ከአሚን ባሏ የረጋች ከባሏ ሌላ የማታውቅ እውነተኛ ታማኝ ክርስቲያን የማለት ፍች አለው፡፡

በዚህ ምክንያት በክርስቲያኑ ኅብረተሰብ የማተብ ትርጉም ከፍተኛ ቁም ነገርን አዝሎ ይገኛል፡፡ አንዲት ሀገር ነፃ መሆኗ የሚታወቀው ወይም ራሷን የቻለች የራሷ መንግስት ያላት ከባዕድ ቀንበር ቅኝ ግዛት ነፃ የወጣች መሆኗ የሚታወቀው በባንዲራዋ ምልክትነት እንደሆነ እንደዚሁም አንድ ክርስቲያን በክርስቶስ አምኖ በጥምቀት ከዲያብሎስ ቁራኝነት ነፃ መውጣቱ ነፃነት ያለው አማኝ መሆኑ የሚታወቀው በማተቡ ምልክት ነው፡፡ ለደብዳቤ ለጽሑፍ ዓርማ ማኅተም ፊርማ እንደሚያስፈልገው ያም ለመተማመኛ እንደሚያገለግል ጥቅሙ ታውቆ ይሠራበታል፡፡

የክርስቲያን ማዕተብም በዚሁ አንፃር ብዙ ኃይማኖታዊ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ መጀመሪያ በልቡ የሚያምነው ሃይማኖት ክርስትናን ሳያፍርበት በአንገቱ ባለው ማተብ መግለጹ በክርስትናው አለማፈሩን ክርስትናህን ካድ ማተብህን በጥስ የሚል ዐላዊ ቢመጣና ያንን ምልክት ዓይቶ ቢሰዋው የሰማዕትነትን ክብር ያገኝበታል፡፡ ያም ባይሆን በማተቡ ምልክትነት በመናፍቃንና በኢአማንያን የሚቀበለው ዘለፋ ስለ ክርስቶስ መስቀል እንደተሸከመ ያስቆጥረዋል፡፡

ሁለተኛው ከክርስቲያን ወገኖች ጋር ያለ ጥርጥር ማለትም ክርስቲያን መሆኑ ታውቆለት በቀላሉ ክርስቲያናዊ ተሳትፎውን ማከናወን ይችላል፡፡ ማተብ ከሌለው ግን ክርስቲያን ይሁን ያልተጠመቀ ስለማይታወቅ በሃይማኖት ዜጎች ዘንድ በቀላሉ ተቀባይነት ማግኘት አይችልም ሶስተኛ ከማይታወቅበት አገር በአደጋም ይሁን በበሽታ እንደወጣ ሞት ቢደርስበት በማተቡ መታወቂያነት የክርስቲያን ሥርዓት ተፈጽሞለት አስክሬኑ ተፈርቶ በቤተክርስቲያን ሊቀበር ይችላል፡፡ ማተብ ከሌለው ግን ለክርስቲያንነቱ ማረጋገጫ የሰው ምስከር በአካባቢው ያውም በሰበካው ቤተክርስቲያን የሚታመን ክርስቲያን ከሌለ እንደ አልተጠመቀ ተቆጥሮ እንደ አሕዛብ ሥጋው ዱር ከበረሐ ወድቆ ይቀራል፡፡

አራተኛ ማተብና መስቀል ያለው ክርስቲያን በውሃ ዋና ወይም በበረሐ ጎዳና በውሃ የሚኖሩ ወይም በበረያ ያሉ አጋንንት በቀላሉ ሊለክፉት አይችሉም፡፡ ይህም በየጠበሉ ሥፍራ በተአምራት ተረጋግጧል፡፡ አጋንንት የለከፋቸው ሰዎች ማተብና መስቀል አይወዱም፡፡ የሠፈረባቸው ርኩስ መንፈስ ማተብ እንዲበጥሱ መስቀል እንዲጥሉ ያደርጋቸዋል፡፡ ማተብ በሰይጣን ዘንድ ከተጠላ በአጋንንት ላለመለከፍ የማተቡ መኖር ይጠቅማል ማለት ነው፡፡

አንዳንድ ሰዎች የማዕተብ ሥርዓትን ለመቃወምና ዘመናውያን መስለው ለመታየት "ሃይማኖት በልብ ነው" ይላሉ ተሳስተዋል፡፡ ሃይማኖት የልብ ብቻ አይደለም የጠቅላላው ሕዋሳት ሁሉ ናት እግዚአብሔርን ስንወደውና ስናመልከው በልባችን ብቻ ሳይሆን በአፋችንም በአንገታችንም በጠቅላላው ሰብአዊ ተፈጥሮአችን ሁሉ መሆን ይገባዋል፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር የጠቅላላው ሰውነታችን አምላክና ፈጣሪ ስለሆነ ነው፡፡ "ስለዚህ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ በሰው ፊትም የሚክደኝን ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እክደዋለሁ፡፡" ማቴ ፲፤ ፴፪-፴፫

በዚህ ቃል መሠረት በኢአማንያን ዘንድ ክርስቲያን መሆናችንን የምንገልፀው በልባችን ብቻ ሳይሆን በቃላችንና በሥራችንም ጭምር ነው፡፡ በአንገታችንስ እንዳንመሰክርለት ማን ያግደናል? በአንገታችን ባለው ማዕተብም ለእግዚአብሔር እንመሰክራለን የስሙን ምልክት በአንገታችን እናኖራለን አናፍርበትም፡፡ የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ በጥምቀታችን እንደምንመሰክር የጥምቀታችንንም አርማ በማተባችን እናረጋግጣለን፡፡ /ሮሜ ፲፤፮-፲፫፡፡ ኢዮኤ ፪፤፴፪፡፡ ሮሜ ፮÷፩-፭ ፣ ማቴ ፭÷፲፩-፲፪፡፡ ፩ጴጥ ፫÷፳፩-፳፪ ፩ጴጥ ፬÷፲፪-፲፮/ ተመልከት፡፡

ሌሎችም ማተብ መሠርን ብቻ ሳይሆን ጥምቀተ ክርስትናንም ለመቃወም ከሚሰነዝሯቸው ትችቶች አንዱ ሰው ሁሉ ሲወለድ ክርስቲያን ሳይሆን ይወለዳል፡፡ እናንተ ክርስቲያኖች ግን በውሃ ነክራችሁ እንደ ውሻ በአንገቱ ላይ ክር ታሥሩለታላችሁ ስለዚህም ማተብ አልባነት ከማኅፀን ጀምሮ የተፈጥሮ ሲሆን ክርስትና ግን ሰው ሠራሽ በኋላ የመጣ ነው ይላሉ፡፡ ከአምላክ ሕግ ከወንጌል ይልቅ በሌላ ሥርዓት የሚሄዱ ከክርስትና በኋላ የመጡ ስለሆነ ባለማወቃቸው ቢተቹ አንደነቅም፡፡

ከወንጌል የተለየች ትምህርት እንዳንቀበል ሐዋርያት አስጠንቅቀውናል፡፡ መላእክት በራእይ ገልጸውልናል ከእግዚአብሔር አግኝቻለሁ እያሉ የሚመጡትን መናፍስት እንድንበረምራቸው ከወንገል ትምህርት የሚቃረን ትምህርት ካላቸው እንዳንቀበል ቅዱሳት መጻህፍት ያስጠንቅቁናል ቅዱ ዮሐንስ ፍቁረ እግዚእ እንዲህ ይላል "ወዳጆች ሆይ መንፈስን ሁሉ አትመኑ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደሆነ መርምሩ ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና የእግዚአብሔርን መንፈስ በዚህ ታውቃላችሁ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደመጣ የሚታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው፡፡

 

ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ እንደመጣ የማይታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፡፡ ይህም የክርስቶስ ተቃዋሚው መንፈስ ነው፡፡ ይህም እንዲመጣ ሰምታችኋል አሁንም እንኳ በዓለም አለ፡፡" ፩ኛ ዮሐ ፬÷፩-፫/

ቅዱስ ጳውሎም "ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን አስቀድመን እንዳልን እንዲሁ አሁን ሁለተኛ እላለሁ ከተቀበላችሁት የተለየውን ማንም ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን … ይህም ድንቅ አይደለም ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና እንዲህ አገልጋዮቹ ደግሞ የጽድቅን አገልጋዮች እንዲመስሉ ራሳቸውን ቢልጡ ታላቅ ነገር አይደለም፡፡ ፍጻሜአቸውም እንደ ሥራቸው ይሆናል፡፡" /ገላ ፩÷፰-፱ ፪ቆሮ ፲፩÷፩፬-፲፭፡፡/

አንዳንድ ተቃዋሚዎች የክርስቲያን ማተብ ማሰር ልምድ ከአረማውያን የተሰወረ ነው ይላሉ፡፡ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ የማያምኑ የተረፈ አይሁድ አባባል ስለሆነ ተቃውሞውን ዋጋ ሳንሰጠው በትዕግስት እናልፈዋለን፡፡ ስለ እኛ ሞቶ የተነሳውን ጌታ ባለማመናቸው የሚናገሩት ስለሆነ ቅዱስ ጳውሎስ የነገረንን ምክር በማስታወስ ማተባችንን እናጠብቃለን፤ "ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል መከራ ወይስ ጭንቀት፤ ወይስ ስደት ወይስ ረሃብ ወይስ ራቁትነት ወይስ ፍርሃት ወይስ ሰይፍ ነውን? ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን ተብሎ እንደተጻፈ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን፡፡

ከዚህችም ዓለም ገዦች አንዱ እንኳ ይህን አላወቁም አውቀውስ ቢሆን የክብርን ጌታ ባልሰቀሉት ነበር፡፡ ይህ የክብር ንጉስ ማነው? የጭፍሮች አምላክ እግዚአብሔር እርሱ የክብር ንጉሥ ነው፡፡" ሮሜ ፰÷፴፭-፴፯ ፤ ፩ቆሮ ፪÷፰ ፤ መዝ ፳፫÷፲

እንደ ውሻ በአንገታችሁ ማዕተብ ማሰራችሁ ተብለን በመነቀፋችንም እንደሰትበታለን እንጂ አንከፋም፡፡ ምክንያቱም ውሻ ለጌታው ታማኝ ነው፡፡ ሌሎች የተለከፉ ያበዱ ዘላን ውሾች እንዳይለክፉትና ከሞት እንዳያደርሱት ወይም ወንበዴዎች በሥጋ መርዝ ቀብተው ለሥጋው ሲሳሳ እንዳይገድሉት ትንሽ ጎጆ ሠርቶለት ቢያስረው ለውሻው ሕይወት አስፈላጊ እንደሆነ በሁሉም ያታወቀ ነው፡፡ ቀበሮ ወይም ተኩላ ከሆነ ግን አውሬ ስለሆነ ለማዳ ካልሆነ በስተቀር ማንም አያስረውም ለበጎችም ፀር ስለሆነ ከተገኘ የሚምረው የለም፡፡

በዚሁ አንፃር ክርስቲያን ለክርስቶስ ታማኝ በመሆኑ በነፍሱ ሞግዚት፣ በቄሱ እጅ ከሕፃንነቱ ጀምሮ የድኅነቱ ምልክት በሚሆን አንገቱ በማዕተብ ክርስትና ይታሠራል፡፡ ጌታ ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ በብረት ሐብል በብረት ገመድ ስለ እኛ ቤዛ ለመሆን አይሁድ በአንገቱ ታሥሮ መጎተቱን ስለሚያስታውሰን ለታማኝነታችንና ለክርስቲያንነታችን ምልክትነቱ ማረጋገጫ ስለሆነ አናፍርበትም፡፡ በድርሳነ ሰንበት ቅዱስ ያዕቆብ ዘሰሩግ ስለውሻ ታማኝነት ለክርስቲያን ታማኝነት ምሳሌ አድርጎ ገልጾታል "ከልብሰ የአምር እግዚኡ" ውሻ ጌታውን ያውቃል ጌታችንም በቅዱስ ወንጌል ያችን ከነናዊት በውሻ የተመሰለችውን ሴት ስለታማኝነቷ አድንቋታል ልጅዋንም ፈውሶላታል /ማቴ ፲፭÷፳፩-፳፰/

ማዕተብን የሚቃወሙ ሌሎች ጽዳት ያጎድላል በማለት ያመካኛሉ፡፡ የጠንቋይ ክታብ የቃልቻ ግሥንግሥ መሰብሰቢያ ካደረጉት የሥጋ ንጽሕናን ብቻ ሳይሆን የሚያጎድለው የነፍስንም ጽዳት የሚያጎድል መሆኑ እውቅ ነው፡፡ ማተብና መስቀሉ ግን ጽዳት ያጎደለበት ጊዜ ስለሌለ ሰበብ አያዋጣም፤ ስለዚህ የክርስትናችንን ዓርማ የነፍሳችንን ሰንደቅ ዓላማ በነፃነት ስናውለበልብ ለመኖር ያብቃን አሜን፡፡

2 comments:

  1. እግዚአብሄር ይስጥልን ቃለ ህይወት ያሠማልን.

    ReplyDelete
  2. አሜን ቃለሕይወትያሰማልን

    ReplyDelete