Tuesday, November 18, 2014

ለሚያምን ሁሉ ይቻላል(ማር9:23)



እነሆ፥ የመዳን ቀን አሁን ነው

… የአምስት ገበያ ያህል ሕዝብ ይከተለው ነበር በርካታ ሴቶችና ሕፃናት አረጋውያንና ወጣቶች፤ ከዚህ ሁሉ ሕዝብ መካከል እኩሉ ድውያንን ሲፈውስ እውራንን ሲያበራ በሚያደርገው ድንቅ የሆነ ተአምር ተከቦ እኩሉ መሲህ ይመጣል የተባለውን የሰማ እኩሉም በሚያስተምረው ትምህርት የተመሰጠ እኩሉም መልኩና ቁመናው የክርስቶስ ደም ግባቱ አስገርሟቸው ለማየት የሚከተሉ ነበሩ…


ይህቺ ዓለም ተሸብራ የሰው ልጆች በኃጢዓት ደዌ  ተበክለው ባለበት ወቅት ፍቅር አስገድዶት መሲህ ክርስቶስ መጣ ሲባል አይደለም የአምስት ገበያ ሕዝብ የአለም ሕዝብ ከዳር እስከዳር ሊከተለው በተገባ ነበር ግን ምን ዋጋ አለው የተወደደው ሰዓት አሁን መሆኑን ማንም አልተረዳም ነበር ከኃጢዓት ደዌውም ለመፈወስ የሚሻ ከእስራት ለመፈታት የሚፈልግ ወደ ሕይወት መሸጋገርን የሚያልም ማንም አልነበረም….. "እነሆ፥ የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤ እነሆ፥ የመዳን ቀን አሁን ነው።"(2ኛ ቆሮ6:2)

ከዚህ የአምስት ገበያ ያህል ሕዝብ መካከል መሲህ ክርስቶስን ለማየትና የረገጠውን ምድር ትቢያ የሚሹ የመዳን ቀናቸውም አሁን መሆኑን ያወቁና በእምነት ሆነው ክርስቶስን ሲከተሉ የነበሩ ተነሳሂ ክርስቲያኖች ነበሩ… ስንት ሺህ ሕዝብ እየተተራማመሰ በሚተምበት ወቅት ማን ማንን እንደገፈተረው….ማን ማንን እንደነካው ማን ማንን እንደረገጠው ማን ያውቅና….. ብቻ መትመም ነው መሲሁንም መከተል ነው…… ከትርምሱ መካከል ግን ለረዥም አስራ አመታት በደዌ ስትሰቃይ የኖረች ዛሬ ግን ከዚህ ሁሉ በርካታ ሕዝብ ጋር በፍፁም እምነት ሆና የመሲሁን አዳኝነት ተረድታ ከዘመናት ደዌዋ ለመፈወስ በእርግጠኛነት ከቤቷ ወጥታ ከበርካታው ሕዝብ ጋር ትተማለች "የሰናፍጭ ቅንጣት ታህል እምነት ቢኖራችሁ አይደል ያለው ክርስቶስ…" ዛሬ እኮ እኛ የተቸገርነው ትንሽና የጸናች እምነት ልቦናችን ውስጥ ባለመኖሩ ነው፡፡….

በርካታውን ትርምስ ካለፈች በኋላ ክርስቶስ ያለበት ሥፍራ ከኋላ በኩል ደረሰች…  የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤ በጣም የሚገርመው ነገር ግን በርካታ ክርስቲያኖች ንስሐ ሊገቡ ኃጢዓታቸውንም ሊናዘዙ ይፈልጉና ነገር ግን ለምን እንደሆነ አይገባኝም ለነገ ቀጠሮ ይይዛሉ በትርምሱ መካከል ማለፍ አቅቷቸው ይሆን?..... እንደ እኔ ከሆነ ግን እነዚህ ክርስቲያኖች አንድም የያዛቸው ደዌ እንደዚች ሴት አላሰቃያቸውም አለበለዚያም ዛሬውኑ መዳን አይፈልጉም አለያም ደግሞ እንደዚች ብፅዕት ሴት የሰናፍጭ ቅንጣት ታህል እምነት የላቸውም…. እንዴት የሚገርም ነገር ነው እጅግ ያማረ ነጭ ልብስ እያለ አሮጌውንና የቆሸሸውን ልብስ ለብሶ መቆየት የሚሻ ልቦና ምንኛ የደነደነ ይሆን?....



…. ታዲያ ከዚህ ከሚተራመስ ሕዝብ መካከል የድህነት ቀኗ አሁን መሆኑን ያወቀች ለመዳን ቆርጣ የተነሳች ነፍስ በእውነት ብፅዕት ናት፡፡ እነሆ ይህቺ ሴትም ከሐዋርያት መካከል ሆና የሰማያዊውን ሙሽራ የክርስቶስን ቀሚስ ለመንካት ተዘጋጀች በፍጹም ትህትና ነበርና የቀረበችው ኃጢዓተኛነቷ ቢያስፈራትም ከያዛት ደዌ ግን ዛሬውኑ መፈወስ እንዳለባት ወሰነች እንደምንም ብላ ከትርምሱ መሐል አልፋ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን የቀሚሱን ጫፍ ነካችው … ልቧ በሐሴት ተሞላ ከእግር ጥፍሯ እስከ ራስ ፀጉሯ ሰውነቷን ውርር አደረጋት ለካንስ በእምነት ሆኖ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መኖር እንዲህ ያስደስታል፡፡ ለአንድ አስርትና ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት ሲፈስ የነበረው ደሟ ቀጥ አለላት  " ፤ በነቢዩ በኢሳይያስ: እርሱ ድካማችንን ተቀበለ ደዌያችንንም ተሸከመ የተባለው ይፈጸም ዘንድ፥ መናፍስትን በቃሉ አወጣ፥ የታመሙትንም ሁሉ ፈወሰ።"ማቴ(8:16)   ክብር ምስጋና ይግባውና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድህነት ወደ ተፈፀመበት አቅጣጫ ዘወር አለና ወደ ሐዋርያቱና ወደ በርካታው ሕዝብ ሴቲቱን ጨምሮ "ማነው ቀሚሴን የነካ" አለ ሐዋርያት ግን ምስጢሩ አልገባቸውም ነበርና ጥያቄው አስገረማቸው ምን ያድርጉ ከዚህ ሁሉ ትርምስ መሐል እንዲህ ያለ ተአምር ይፈፀማል ብሎ ማን አሰበ…. እንዲህ ያለስ የእምነት ጀግና ይኖራል ብሎ ማን ገመተ…… ለአምላክነቱ ክብር ምስጋና ይግባውና ክርስቶስ ግን "ኃይል ከእኔ ወጥቷል…" ነበረ ያላቸው በድጋሚ ማነው ቀሚሴን የነካ ብሎ ጠየቀ ይህቺም ሴት ልቧ በሐሴት ተሞልቷልና የስቃይ ዘመኗም አክትሟልና በእምነቷ ንስሐ ታጥባለችና ከሰማያዊው ንጉስም ጋር ለመነጋገር በቅታለችና "ጌታ ሆይ እነሆኝ እኔ ነኝ" በማለት መለሰች ጌታም መለሰና ከእስራኤል መካከል እንዲያ ያለ እምነት አላገኘሁም "አንቺ ሴት እምነትሽ አድኖሻል አላት ታዲያስ አሁንም ንስሐን ለነገ እንቀጥር ይሆን የመዳን ቀን ዛሬ ነውና ተነስተን ትርምሱን እንለፍ የቀሚሱንም ጫፍ እንንካ….፡፡ ማቴ 9÷20

No comments:

Post a Comment