Tuesday, December 9, 2014

መንገደኛዋ ታዛቢ

 
መንገደኛዋ ታዛቢ
ወቅቱ ክረምት ነው የአየሩ ሁኔታ  የቅዝቃዜው ነገር አያድርስ ነው በረዶው መኪናም አያስነዳም በእግርም አያስጉዝም ባጠቃላይ ምን አለፋችሁ የዚህ ዓለም ጣጣ ባይኖር ኖሮ ከቤት መውጣት አያስመኝም ነበር በማግስቱ ታህሳስ 19 ቀን የመላዕኩ የቅዱስ ገብርኤል ክብርና ልዕልና የሚነገርበት የእነዚያ ሶስት የእምነት ጀግኖች የሲድራቅ የሚሳቅና የአሚዲናጎም የእምነት ምስክርነት የሚወሳበት ታላቅ ክብረበዓል ነበር፡፡ እኔም የዚህን ብስራታዊ መልዓክ ተ ለመስመትና የእነዚህን ሶስት ቅዱሳን ወጣቶችንም የእምነት ምስክርነት ከምንም በላይ ደግሞ የእግዚአብሔርን ድንቅ ተአምር ለማየት ፈለግሁና በመላዕኩ በቅዱስ ገብርኤል ስም የታነፀውና በአካባቢው ምዕመናን አማካኝነት ወደ ተሠራው በዋሽንግተን ሲያትል ወደ ሚገኘው ቤተክርስቲያን ተጉዤ ነበር በአካባቢው በርካታ ኢትዮጵያውያን ማህበረሰቦች የሚገኙ ሲሆን ከምንም በላይ ግን ፈሪሃ እግዚአብሔር ያላቸው እግዚአብሔር ለራሱ የመረጣቸው የቤተክርስቲያን ማህበረሰቦችም አሉ፡፡

እኔ ከምኖርበት የዋሽንግተን ዲሲ እስከ ዋሽንግተን ሲያትል የ6 ሰዓት የአውሮፕላን ጉዞ ሲሆን ከምሽቱ 5፡00 ሰዓት ተነስቼ ጠዋት ረፋዱ ላይ ነበር የደረስኩት፤ ምንም እንኳን ቤተክርስቲያኑ ግቢ ባይኖረውም ፀጋ እግዚአብሔር ስላለ የፀጥታው ድባብ ለነፍስ ደስታን ይሰጣል፡፡ እንደ ሀገራችን ከቤተክርስቲያን ውጪ ቆሞ ማስቀደስ ባለመቻሉ አብዛኛውን ጊዜ ምዕመናኑ በውስጥ ሆነው ነው የቅዳሴውን ሥርዓት የሚከታተሉት፡፡ በአካባቢው ምዕመናን አማካኝነት የተሠራውና በመላኩ ቅዱስ ገብርኤል ስም በታነፀው የሲያትል ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን በርካታ ባይሆኑም እንኳ በአሜሪካ የሰዓት ውድነት ይህ ሁሉ ሕዝብ በዚህ ቅዱስ ሥፍራ ተሰባስቦ መገኘቱ በእውኑ አስገረመኝ "ኢትዮጵታ ታበጽህ እደዊሃ ሃበ እግዚአብሔር" (መዝ68:31) ተብሎ የተፃፈው አምላካዊ ትንቢት ትዝ አለኝ፡፡
በስፍራው ስደርስ የቅዳሴው ሥርዓት ወደመጠናቀቁ ተዳርሷል፣ ወደ ውስጥ ስዘልቅ ካህናተ እግዚአብሔር ታቦታቱን ለዑደት ይዘው ለመውጣት እየተዘጋጁ ነበር፡፡
በአጋጣሚ ግን ቀልቤን የሳበኝ ከሀገሩ ባህል አስቸጋሪነት የተነሣ   ምዕመናን  ትውፊቱን እየለቀቁ መሆን ሳይ በጣም አዘንኩኝ :: በእርግጥ እኔ ከሀገረ-እግዚአብሔር ኢትዮጵያ ከወጣሁ ሶስትና አራት ወራት ስለሆነኝ እንጂ በዚያ ለኖሩት ምዕመናን እንደ ልምድ ቆጥረውታል ለእነርሱ ምንም አይታያቸውም ግን እኮ ትውፊት ለቤተክርስቲያናችን መሠረት ነው፣ እኛ ክርስትናን ፈፃሚዎች እንጂ ጀማሪዎች አይደለንም አባቶቻችንን ያቆዩልንን ትውፊት ለቀሪው ትውልድ ሳይለወጥ ሳይሸረፍ ማስረከብ ይጠበቅብናል ግን እንዴትና? ለምን? ብዬ ራሴን በራሴ ጠየቅሁ ፊቴን ጭፍግግ ፈታ እያደረግሁ ከራሴ ጋር አወጣ አወርድ ጀመርኩ ለወጣት ምዕመናን  ሽማግሌዎች አርአያና ምሳሌ ይሆኑ ዘንድ ግድ ይላችዋል::  እግዚአብሔር የማይለወጥ አምላክ ነው ከዘላለም እስከዘላለም ያው ነው ታዲያ እኛ የተነገረልንን ትንቢት ረስተን ለምን ማንነታችን እንቀይራለን፣ መለወጥ በመንፈሳዊ ሕይወት እንጂ ትውፊትን በማዛባት አይደለም እኮ ምናልባት "እትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊነቱን ነብር ዝንጉርጉርነቱን ሊቀይር (ሊለውጥ) ይችላልን?" ተብሎ የተነገረልንን ትንቢት ዘንግተን ይሆን በእርግጥ ክርስቲያኖች እንደ እባብ ብልህ እንደ ርግብ የዋህ መሆን ያስፈልጋቸዋል ቢሆንም ግን እዚህ ላይ መዘንጋት የሌለብን እኛ ክርስቲያኖች ምንም እንኳ ለሰለጠነው ዓለም ላለንበት አካባቢ ልዩ ሆነን ብንታይም ይገባናል ምክንያቱም ክርስትናችን በአሕዛብ ዘንድ፤ መንፈሳዊነታችንም በአላማውያን ዘንድ ሞኝቢያስመስለንም የክርስትና ባህሪ የዋህነት ጭምትነት ነውና አያስደንቅም ጥንቱንም ስንፈጠር እኛ ክርስቲያኖች ከዓለም በጣም የተለየን መሆኑን መዘንጋት የለብንም በብልጭልጩ ዓለምም ልንደነቅና ልንጎመጅ አይገባም፡፡ ሀገራችን ምድራዊ ሳይሆን ሰማያዊ ነውና በይሉኝታ ተይዘንም ወደ ዓለም ባህር በፍራቻ ልንሰምጥ አይገባም አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም "በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ ነገር ግን እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁና አይዟችሁ አትፍሩ ብሎናልና" ከሐሳቤ ጋር እየተሟገት ሳለ "ገብርኤል አማልደን ከአምላካችን እንዳንጠፋ እንዳንሞት በነፍሳችን አደራ ቁምልን ከጎናችን" የሚለው መንፈሳዊ ዜማ ከሐሳቤ ቀሰቀሰኝ ሥርዓተ ዑደቱም አበቃና ታቦታቱ በአውደ ምህረቱ ፊትለፊት ላይ ቆም አሉና፤ የዕለቱን በዓል በማስመልከትም በተጋባዥ መምህራን ስለነዚያ የዘመኑ የእምነት ጀግኖች አናኒያ አዛርያና ሚሳኤልም የእምነት ምስክርነት ተነገረ እኔም "አምላካችን እግዚአብሔር ቢያድነንም ባያድነንም እኛ አንተ ላቆምከው ምስል አንሰግድም" ብለው የመሠከሩት አስደነቀኝ እኛ የዘመኑ ትውልዶች እንኳንስ "ቢያድነንም ባያድነንም" አንድ ቀን ሄደን ተስለን ስዕለታችን በእምነታችን ደካማነት ባይደርስልን እንኳ ሁለተኛ ቤተክርስቲያን አንሄድም ብለን ስንል እንቀር ይሆን? መምህሩ የብስራታዊ መልዓክ የቅዱስ ገብርኤልን ተአምር አብራርተው ለምዕመናኑ ከአስተማሩ በኋላ የማሳረጊያ ጸሎት በሊቀ ጳጳሱ ተሰጠና በዕልልታና በጭብጨባ ታቦታቱ ወደ መቅደሱ ተመለሱ፡፡
ምዕመናኑ መበታተን ሲጀምሩ እኔም የደብሩ ሰንበት ትምህርት ቤት ወደ አዘጋጀው ዝግጅት አመራሁ ወደ አዳራሹ ሳመራ አዳራሹ ውስጥ በርካታ እንግዶች ገብተው ነበረ የሰንበት ትምህርት ቤቱ አዘጋጅ ኮሚቴ አስቀድሞ በማስታወቂያ ዝግጁነት አሳውቆ ስለነበረ የተዘጋጀውን ዝግጅትና "ሲድራቅ ሚሳቅ አብደናጎ ኑ ውጡ" በሚል ርዕስ ስም የተዘጋጀውን መንፈሳዊ ድራማ ለመከታተል ተጋባዥ ምዕመናን በጉጉት ይጠብቃሉ ከአዳራሹ በኋ በኩል አመራሁና የመጨረሻው ወንበር ጠርዝ ላይ አረፍ ብዬ ፕሮግራሙ እስከሚጀመር የሚገቡትን ተጋባዥ እንግዶች ማስተዋል ጀመርኩኝ በመገረምና በመደነቅ አይኖቼ በሚያዩት ነገር በእጅጉ አዘንኩኝ ወደ አዳራሹ የሚገቡት አብዛኛወች አረጋውያን እናቶችና አባቶች  ነበሩ፣ ወጣቶች፣ የቤተክርስቲያን የነገ አደራ ተረካቢዎች ወዴት አሉ፣ ነው ወይስ አዋጅ እነርሱን አይመለከት ይሆን "እንደዚያ እንዳንል ደግሞ በወጣትነት ዘመንህ በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ" ተብሎ ተጽፏል፣ ታላላቅ የቤተክርስቲያን አባቶችም ገድልን የፈጸሙት ለቤተክርስቲያን የተፋለሙት ለእምነታቸው የተሰዉት በዱር በገደል በግበበምድር፣ በዋሻ የተሰደዱት በወጣትነታቸው ፍቅረ እግዚአብሔር አስገድዷቸው ነበረ፡፡
ዳሩ ውሃው ነው መሰለኝ ወጣቶችን የባዕዱን ሀገር ምድር ሲረግጡ እንዲለወጡ የሚያደርጋቸው ምክንያቱም እንደመጡ ምስክር ሆኖ አርአያ የሚሆናቸው ባለማግኘታቸው ወዲያው እንደመጡ ክርስቲያናዊ ውበታቸውን እንዲቀይሩ የሚያስገድዳቸው፣ ግን ማን ይሆን የዘመኑን ማንነት የተረዳ እርሱ የእምነት ጀግና ሆኖ የተሸበሩትን የሚያረጋጋ በአሉበት በክርስትናቸው ጸንተው እንዲቆዩ እንደ ቅዱስ ገብርኤል "ንቁም በበኅላዌነ እስከንረክቦ ለአምላክነ" በማለት አርአያ ሆኖ የሚያረጋጋ፣ አሊያም የመድኃኔዓለም የኢየሱስ ክርስቶስን ሐዋርያትን ያረጋጋበትን መንፈስ ቅዱስንም እስከሚቀበሉ በሀገረ ኢየሩሳሌም ጸንተው እንዲቆዩ እንዳደረገ ሁሉ ወደ ባዕድ ሀገር የሚመጡ እህቶችና ወንድሞች በኢየሩሳሌም ምሳሌ በቤተክርስቲያን ጸንተው እንዲቆዩና አክሊላቸውንም እንዳይነጠቁ ምሳሌ ሆኖ የሚገኝ ማን ይሆን?
ራሴን በሐሳብ አስጨንቄ እኔም ነገ ከነገወዲያ የዚሁ ዕጣ ተካፋይ መሆኔን ሳስበው "እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ እባክህን ልቦና ስጠኝ ቀሪውንም ዘመኔን ባርክልኝ ምክንያቱም ምናልባት ይህ ነገር እኔን ያስገረመኝ ገና ለሀገሩ  እንግዳ ለባህር ማዶውም ሰው ባዳ ስለሆንኩ ይሆናል ገና አሜሪካ ምድር ገባሁ እንጂ መቼ መኖር ጀመርኩና የዚያን ጊዜማ እንኳንስ ታዛቢ ልሆን እኔንም የሚታዘበኝ ሳያሻኝ ይቀራል ብላችሁ ነው "እውነቴን ነው የምላችሁ በጎችን የሚያሰማራ በመልካም ቦታ የሚመራ እረኛ እንደሚያስፈልግ ሁሉ ምዕመናንንም እርሱ ፍጹም መንፈሳዊና ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን የተላበሰ አርአያ የሚሆን ሰው ከሌለ ክርስቲያን እህቶቻችንና ወንድሞቻችን በባሕር ማዶው አስቸጋሪ ወግና ባሕል ተጠልፈው ክርስትናቸውን ትውፊታቸውን ይረሳሉ ማንነታቸውን ይዘነጋሉ? አክሊላቸውንም ይነጠቃሉ ለክፉ ፈተናም ይጋለጣሉ የአልባሌ ሱሶችም ተገዥ ሆነው ለሀገር ለወገን የማያስቡ ግዴለሽ ዜጎች ይሆናሉ፡፡
"ሁላችንንም ለፀሎት እንነሣ!" የሚለው የጉባኤው መሪ ድምፅ ከሐሳቤ አነቃኝ፡፡ ፀሎቱ አብቅቶ መዝሙር ተዘመረና የጉባኤው መሪ ስለዕለቱ በዓል ትንሽ ከአወሳ በኋላ በሰንበት ት/ቤቱ መዘምራን አጠር ያለና የዕለቱን በዓል ያስመለከተ ወረብ ቀረበ እግዚአብሔር ዕድሜ ይስጣቸውና የዘማሪያኑ ጥንግ ድርብ ሥርዓተ ሽብሸባቸውና የከበሮ ምታቸው የቅዱስ ላሊበላን የቤዛ ኩሉ ሥርዓት በአርምሞ ተደሞ በትዝታ ባሕር ወደ ኋላ ተጉዤ እንዳስታውስ አደረገኝ ልቦናዬንም ደስ አሰኘኝ በሃይማኖቴና በኢትዮጵያዊነት የአለባበስ ወግ ማዕረግም ኮራሁኝ የዕለቱን በዓል በተመለከተ የተዘጋጀው ድራማም ቀረበ ተጋባዥ እንግዶችን ያስደሰተና መንፈሳቸውንም ያረካ ነበረ፡፡ በእውነቱ ይበሉ ያሰኝ ነበረ ምክንያቱም ከሰዓት አለመኖር የተነሣ ውድ የሆነ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን መስዋዕት አድርገው ይህን የመሰለ ዝግጅትም በማቅረባቸው ልንኮራባቸው ይገባል፡፡ ድራማውም ተጠናቀቀና መዝሙር ከተዘመረ በኋላ ጉባኤው በፀሎት ተዘጋ መንገደኛዋም ታዛቢ እግዚአብሔር አምላክ ከፈተና ይሰውረን ብላ ተሰናብታ ጉዞዋን ቀጠለች፡፡


No comments:

Post a Comment