ይህንን ቃል የተናገረ ልበአምላክ ቅዱስ
ዳዊት ሲሆን ለጊዜው የሕዝበ እስራኤልን ከግብፅ ምድር መውጣት አስመልክቶ ተናግሮታል፡፡ እስራኤል ከ430 ዓመት የግብፅ ስደትና
የባርነት ኑሮ ቢከብዳቸው መከራው ቢበዛባቸው ወደ አምላካቸው ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፡፡ በተለይ የልጆቻቸው ሐዘን ልባቸውን
የሰበረው ራሔልና መሰሎቿ የእስራኤል እናቶች እንባቸውን አፍስሰው ወደ መንበረ ፀባኦት ወደ እውነተኛው ዳኛ ወደ እግዚአብሔር
ጮኹ "የአምብርሃምና የይስሐቅ የያዕቆብም አምላክ ሆይ ወዴት
አለህ? አብርሃምን ዘሩን ያበዛህ በዘርህ ምድር ይባረካል ብለህ ተስፋ የሰጠህ ይስሐቅንም የታደግህ ያዕቆብንም እንደ መንጋ
የምትጠብቅ እረኛችን እግዚአብሔር ሆይ እስከመቼ ፈጽመህ ትረሳናለህ? እያሉ አብዝተው ተማጸኑ፡፡
ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር የሕዝቤን
ጩኸት ሰምቻለሁ መቃተታቸውንም አይቼ ላድናቸው ወርጃለሁ በማለት በሙሴና በአሮን አማካኝነት ሕዝበ እስራኤልን ከግብፅ ምድር
ከፈረኦን አገዛዝ በዘጠኝ ጽኑ ተአምራት በአስረኛ ሞተ በኩር ባሕረ-ኤርትራን ከፍሎ ውሃውን እንደ ሳር ክምር እንደ ግርግዳ
አቁሞ በደረቅ መሬት አሻገራቸው ከፈርኦንና ከሠራዊቱ ከግብፅ ባርነትም ነፃ አወጣቸው ከዚያም ነቢዩ ቅዱስ ዳዊት በእሳትና በውሃ
መካከል አሳለፍከን እንዲል እሳት የተባለውን የቃዴስን በረሃ ቀን በደመና ሌሊትም በብርሃን አምድ እየመራ ውሃን ከጭንጫ
እያፈለቀ መናንም ከሰማይ እያወረደ በመጋቢ ብሉይ በተራዳኢው መላዕክ በቅዱስ ሚካኤል አማካኝነት መርቶ ማርና ወተት ወደ
ሚፈስበት ምድረ-ርስት ከነዓን አስገባቸው፡፡
እነሱ ግን የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራና
ውለታውንም ዘንግተው እግዚአብሔርን አሳዘኑ፡፡ "ትውልድ ሁሉ ወደ አባቶቻው ተከማቹ እግዚአብሔርም ለእስራኤል
ያደረገውን ቸርነትና ውለታ የዘነጋ ትውልድ ተነሣ" (መሳ 2÷10) እንዲል መጽሐፍ እግዚአብሔርን በደሉ
ካህናቱና መምህራኑ ዕለት ዕለት ስለ ሕዝቡና ስለማደሪያው ስላዘኑ አብዝተው አሳሰቡ እነሱ ግን አልሰማ አሉ በቃለ እግዚአብሔርም
አፌዙ ነቢያቱንም አሳደዱ፡፡ (2ዜና 36÷15) ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ጨካኞችንና ክፍዎችን አሕዛብ ከለዳውያንን አስነሳባቸው
አሮጊቶችንና ሽማግሌዎችን ሴቶችንና ህፃናትን ወጣቶችን ሁሉ ገደሉ የእግዚአብሔርን ቤት ሳይቀር አፈረሱ በእሳትም አቃጠሉ ንዋያተ
ቅድሳቱንም መዘበሩ የኢየሩሳሌምን ቅጥር አፍርሰው ባድማ አድርገው ለአራዊት መፈንጫ አድርገው ተሳለቁበት፣ የተረፈውን ሕዝብም
ማርከው ወደ ባቢሎን ምድር በባርነት ወሰዱ፡፡ እግዚአብሔር ግን አሁንም ለሕዝቡ ይራራልና ነቢያቱንና መምህራኑን ያጽናኗቸውና
ያበረቷቸው ዘንድ አብሮ ወደ በባቢሎን አወረደ፡፡ ከነዚህም መካከል ሶስቱ የእምነት አርበኞች አርአያና ምሳሌ ሆነው የሚጠቀሱ
ናቸው፡፡
ኢዮአቄም ከተባለ የይሁዳ ንጉሥ አባታቸው
ጋር ተማርከው ወደ ባቢሎን የተወሰዱት አናንያ አዛርያና ሚሳኤል በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነጾር ቤት ውስጥ ያሳደጋቸውና በባቢሎን
አገሮች ውስጥ የሾማቸው ናቸው፡፡ በባቢሎን አውራጃ በከፍተኛ የመንግስት የኃላፊነት ሥራ የተመደቡት እነዚህ ወጣቶች ግን ምንም
እንኳን በባዕድ ሀገር በምቾት ወንበር ቢቀመጡም ኢየሩሳሌምና ሕዝቦቿን አልዘነጉም አምላካቸውንም አልረሱም ይልቁንም ዕለት ዕለት
የሚያሳስባቸው የኢየሩሳሌም ቅጥር መፍረስና የሕዝቡ በባዕድ ሀገር መማረክ ነበረ፡፡ በመሆኑም በባቢሎን አውራጃዎች በኃላፊነት
ሳሉ ንጉሥ ናቡከደነጾር ቁመቱ ስድሳ ክንድ ወርዱም ስድስት ክንድ የሆነ የወርቅ ምስል አሠርቶ በዱራ ሜዳ አቆመው ለህዝቡም
አዋጅ አስነግሮ ለዚህ ምስል ይሰግዱ ዘንድ አዘዘ ይህንን የማያደርግ በግንባሩ ተደፍቶ የማይሰግድ ወደ እቶን እሳት ይጣላል
በማለት አሳወጀ፡፡ ሲድራቅ ሚሳቅ አብደናጎ ግን እግዚአብሔር አምላክ ነውና የልዕልናና የአምልኮት ስግደት ለእርሱ ብቻ ይገባል
እንጁ ንጉሡ ላቆመው ምስል ወይም ጣዖት አይገባም በማለት አንሰግድም ብለው ቆሙ፡፡ አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
ሥጋን የሚገድሉትን አትፍሩ ብሎ እንዳስተማረ (ማቴ 10÷28) አሕዛብ ሰይፍና ጦር ይዘው ከእምነት ሊያናውጹ መፍራት እንዳይገባ
በርትተው ሕዝቡን አበረቱ፡፡ ከለዳውያን ግን ከንጉሱ ዘንድ ቀርበው አዋጅ ሲነገር መለከት ሲነፋ ሕዝቡ ሁሉ ላቆምከው ምስል
እንዲሰግዱ የማይሰግድ ካለ ግን ወደ እቶን እሳት ውስጥ ይጣላል ብለህ አዘዝህ፡፡ በባቢሎን አውራጃ ሥራ ላይ የሾምሃቸው
ሲድራቅና ሚሳቅ አብድናጎም የሚባ አይሁድ አሉ፤ ንጉሥ ሆይ፤ እነዚህ ሰዎች ትእዛዝህን እንቢ ብለዋል አማልክትህን አያመልኩም
ላቆምከውም ለወርቁ ምስል አይሰግዱም፡፡
ናቡከደነጾርም በብስጭትና በቁጣ
ሲድራቅንና ሚሳቅን አብድናጎንም ያመጡ ዘንድ አዘዘ፤ እነዚህንም ሰዎች ወደ ንጉሡ ፊት አመጡአቸው፡፡ ናቡከደነጾርም ሲድራቅና
ሚሳቅ አብድናጎም ሆይ አምላኬን አለማምለካችሁ ላቆምሁትም ለወርቁ ምስል አለመስገዳችሁ እውነት ነውን? አሁንም… ተደፍታችሁ
ላሠራሁት ምስል ብትሰግዱ መልካም ነው፤ ባትሰግዱ ግን በዚያ ጊዜ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ትጣላላችሁ፤ ከእጄስ የሚያድናችሁ
አምላክ ማነው? ብሎ ተናገራቸው፡፡ ሲድራቅና ሚሳቅ አብድናጎም መለሱ ንጉሡንም፡- ናቡከደነጾር ሆይ በዚህ ነገር እንመልስልህ
ዘንድ አስፈላጊያችን አይደለም፡፡ የምናመልከው አምላካችን ከሚነድደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይቻላል፤ ከእጅህም ያድነናል፤
ንጉሥ ሆይ! ነገር ግን ንጉስ ሆይ እርሱ ባያድነን አማልክትህን እንዳናመልክ ላቆምከውም ለወርቁ ምስል እንዳንሰግድለት ዕወቅ
አሉት፡፡"
በሃይማኖታቸው ሕፀፅ ያልተገኘባቸውና
እስከ ሞት ድረስ የታመኑ የሠለስቱ ደቀቅ በረከታቸው ይደርብንና አምላካችን ለእኛም እስከ ሞት ድረስ በአሚነ ሥላሴ ጸንተን
ለመኖር ያብቃን፡፡
ምንም በሥልጣን ከፍ ከፍ ቢያደርጋቸውና
በከበሬታ ወንበር እንዲቀመጡ (ሰው ሰውኛውን) የፈቀደላቸው ቢሆንም ነገር ግን ያደረገላቸውን እንደውለታ ቆጥረው ላቆመው ምስል
አልተንበረከኩም አምልኮ ሥርዓትን አልፈጸሙም፡፡ ውለታህን ቆጥረን በዚህ እንድንመልስልህ ዘንድ አስፈላጊያችን አይደለም" ብለውታል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ
ወንጌል ላይ "ማንም ወደ እኔ የሚመጣ ቢኖር አባቱንና እናቱን ሚስቱንም
ልጆቹንም ወንድሞቹንም አኅቶቹንም የራሱን ሕይወት ስንኳ ሳይቀር ባይጠላ ደቀመዝሙሬ ሊሆን አይችልም፡፡… "(ሉቃ 19÷26) ብሎ መናገሩ ክብሩን እንዳንወርስ እንቅፋት
የሚሆኑብን የገዛ ቤተሰቦቻችንን እንኳን መለየት እንደሚገባን ሲያሳስበን ነው፡፡ (ዘፍ 12÷1-2)፡፡
ስለሆነም ሶስቱ ወጣቶች በዚህ ጊዜ
ከናቡከደነፆርና ከከለዳውያን ተለይተው ለብቻቸው ቀሩ፡፡ ነገር ግን ለብቻቸው አልቀሩም፤ በረድኤት የማይለያቸው ጠባቂ መልአካቸው
ቅዱስ ገብርኤል ከእነርሱ ጋር ነበር፡፡ ክብሩ እንደተነካ የተሰማው ይልቁንም አምልኮ ባዕድ እንዲፈጽም ያነሳሳው ሰይጣን
የናቡከደነፆርን ልቡና በጭከና መልቶ ሶስቱ ወጣቶች እጅና እግራቸው ታስሮ ወደ እቶን እሳት እንዲጣሉ አዘዘ፡፡ እነሆም የንጉሡን
ትዕዛዝ ለመፈጸም ወታደሮቹ እጅና እግራቸውን አስረው ከእሳት ጣሏቸው፡፡
ኃያል መልአክ ቅዱስ ገብርኤልም ከእነርሱ
ጋር ወደተጣሉበት እሳት ገባ፡፡ በነቢዩ ኢሳይያስ መጽሐፍ አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር "ተቤዥቼሃለሁና አትፍራ፤ በስምህም ጠርቼሃለሁ አንተ የእኔ
ነህ፡፡ በውኃ ውስጥ ባለፍህ ጊዜ ከአንተ ጋር እሆናለሁ በወንዞችም ውስጥ ባለፍህ ጊዜ አያሰጥሙህም በእሳትም ውስጥ በሄድህ ጊዜ
አትቃጠልም ነበልባሉ አይፈጅህም፡፡… " (ኢሳ 43÷1-2) ብሎ በተናገረው ቃል መሠረት ቅዱስ
ገብርኤልን ልጆ የእሳቱ ዋዕይ እንዳይፈጃቸው አብርዶላቸዋል፡፡ ይህም የቅዱስ ገብርኤል መውረድ ለንጉሡ እንደታየ መጽሐፍ እንዲህ
ያስነብበናል፡፡
"የዚያን ጊዜም ንጉሡ ናቡከደነፆር ተደነቀ ፈጥኖም ተነሣ፤
አማካሪዎቹንም ሶስት ሰዎች አስረን በእሳት ውስጥ ጥለን አልነበረምን? ብሎ ተናገራቸው፡፡ እነርሱም፡- ንጉሥ ሆይ እውነት ነው
ብለው ለንጉሴ መለሱለት፡፡ እርሱም እነሆ እኔ የተፈቱ በእሳቱም መካከል የሚመላለሱ አራት ሰዎች አያለሁ፤ ምንም አላቆሰላቸውም፤
የአራተኛውም መልክ የአማልክትን ልጅ ይመስላል ብሎ መለሰ፡፡ የዚያን ጊዜም ናቡከደነፆር ወደሚነድደው ወደ እሳቱ እቶን በር
ቀርቦ፡- እናንተ የልዑል አምላክ ባሪያዎች ሲድራቅና ሚሳቅ አብድናጎም ኑ ውጡ ብሎ ተናገራቸው፡፡ ሲድራቅና ሚሳ አብድናጎም
ከእሳቱ መካከል ወጡ፡፡ መሣፍንቱና ሹማምንቶቹም አዛዡቹና የንጉሡ አማካሪዎች ተሰብስበው እሳቱ በእነዚያ ሰዎች አካል ላይ ኃያል
እንዳልነበረው የራሳቸውም ጠጉር እንዳልተቃጠለች ሰናፊላቸውም እንዳልተለወጠ የእሳቱም ሽታ እንዳልደረሰባቸው አዩ፡፡
ናቡከደነፆርም መልሶ፡- መልአኩን የላከ ከአምላካቸውም በቀር ማንንም አምላክ እንዳያመልኩ ለእርሱም እንዳይሰግዱ ሰውነታቸውን
አሳልፈው የሰጡትን የንጉሡንም ቃል የተላለፉትን በእርሱ የታመኑትን ባሪያዎችን ያዳነ የሲድራቅና የሚሳቅ የአብድናጎም አምላክ ይባረክ፡፡
እኔም እንደዚህ የሚያድን ሌላ አምላክ የለምና በሲድራቅና በሚሳቅ በአብድናጎም አምላክ ላይ የስድብ ነገር የሚናገር ወገንና
ሕዝብ በልዩ ልዩም ቋንቋ የሚናገሩ ይቆረጣሉ ቤቶቻቸውም የጉድፍ መጣያ ያደርጋሉ ብዬ አዝዣለሁ አለ፡፡ የዚያን ጊዜም ንጉሡ
ሲድራቅና ሚሳቅና አብድናጎንም በባቢሎን አውራጃ ከፍ ከፍ አደረጋቸው፡፡
የተከበራችሁ ምእመናን የቅዱስ ገብርኤልን
ትድግናና ጥበቃ ስናስታውስ በዚያው አንጻርም የሶስቱን ወጣቶች ጽናት ልብ ማለት ያስፈልገናል፡፡ በሃይማኖታቸው ጽናት የተነሣ
የእሳቱን ኃይል ማጥፋት ብቻ ሳይሆን (ዕብ 11÷33-38) መከራውን በጸጋ በመቀበላቸው ምክንያት አምላካቸው እግዚአብሔር
በአሕዛብ ዘንድ እንዲታወቅ አድርገዋል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል ላይ "መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን
እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ" (ማቴ 5÷16) በማለት መናገሩ ክርስቲያናዊ ሥነ
ምግባራችን በኢአማንያን ዘንድ ጎልቶ መታየት እንደሚያሻው ያስረዳናል፡፡
እንግዲህ እንደ ሶስቱ ወጣቶች በሃይማኖት
ጸንተን በምግባር ቀንተን መንግስቱን ለመውረስ ያብቃን! የሊቀ መላእክት የቅዱስ ገብርኤል ፈጣን ተራዳኢነቱ የቅዱሳኑ የአናንያ
የአዛርያና የሚሳኤል በረከታቸው ይደርብን፡፡ አሜን፡፡
ወስብሐት
ለእግዚአብሔር
No comments:
Post a Comment