Monday, December 15, 2014

የአባታችን የጻድቁ ተክለ ሃይማኖታ የህይወት ታሪክ ስለ ክርስቶስ ያደረጉት መንፈሳዊ ተጋድሎ

 ክፍል ሁለት፡-

እግዚአብሔር ያከበረውን ክቡር ብትለው ከንቱ ነገር ከመናገር ተከልክለህ ብታከብረው ያን ጊዜ በእግዚአብሔር ደስ ይልሃል በምድር ከፍታዎች ላይ አወጣሃለሁ፡፡ ኢሳ 58÷13-14


አባታችን ተክለ ሃይማኖት ወደ አንዲት ገዳም ገብተው ፆምን ይጾማሉ ከአንዲት የሰንበት ቀን ውጪ አንዳች በአፋቸው እህል አይገባም ከጾም ውጪ ለህዝበ ክርስቲያኑ ትምህርትን የእግዚዓብሔርን ቃል ያስተምራሉ ከትምህርት ቡኋላ በጾም ስጋቸውን ይቀጣሉ አጋንንትን ይዋጋሉ ስለ ህዝቡ ይጸልያሉ በድካምም በጥረትም እንቅልፍም በማጣት ይተጋሉ፡፡ (2ኛ ቆሮ 11÷27) ከሶስት አመት ቡሃላ ከሰማይ ተክለ ሃይማኖት ተክለ ሃይማኖት ተክለ ሃይማኖት ብሎ ሲጣራ ሰሙ የእግዚዓብሄር ድምፅ ነበረ ቀጥሎም ብዙዎችን ወደ ክርስትና ታመጣለህና ተነስተህ ወደ ዳሞት ሂድ አላቸው፡፡ አባታችን ጻድቁ ተክለ ሃይማኖት የዛሬዋ ወላይታ የቀድሞዋ ዳሞት ወደምትባል ስፍራ በደስታ የእግዚዓብሄርን ትዕዛዝ ለመፈጸም ለእጃቸው በትር ለእግራቸው ጫማ ሳይዙ በብርሃን ሰረገላ ሄዱ የደቡብ ሸዋን ሃገራት እንዳለ እየዞረ ወንጌልን እያስተማሩ የእግዚዓብሄርን ቃል እየተናገሩ ዞሩ ወደነ ስድስቴ ወደምትባል ስፍራ ወርደው ሁፋት ተብሎ ወደሚጠራው ታላቅ ተራራ ሲቀርቡ አጋንንት ሲደነፉ አገኟቸው እንደ ውሻ እንደ ቀበሮ ይጯጯሃሉ በምሽት ያሃገሩ ህዝብ ሁሉ ያመልኳቸዋል፡፡ ጻድቁም ወደ እነሱ ቀርበው በትምህርተ መስቀል አማተቡባቸው፡፡ በዚህ ግዜ አጋንንቶች በንፋስ ላይ እንዳለ ጭስ ብን ብለው ጠፉ፡፡ አባታችን በዚሁ ታራራ ላይ ጸሎት በማድረግ ለሊቱን ሙሉ ተጉ ሲነጋ ለአጋንንቶች የሚሆን ግብር ምግብና መጠጥ የሚሰዋም ከብት ይዘው ህዝቡ ተሸክመው ወደ ተራራው መጡ ህዝቡ በተራራው ላይ ያገኙት አጋንንቶችን ሳይሆን አባታችንን ነበር ህዝቡም አልፈው ተራራው ላይ ወጥተው ለአጋንንቶች ይሰግዳሉ ጻድቁ ተክለ ሃይማኖት ግን ህዝቡን ስለምን ለአጋንንቱ ትሰግዳላችሁ በንሳሃ ተመለሱና እኔ ለምሰግድለትና ለማመልከው አምላክ ብቻ ስገዱ እርሱንም ብቻ አምልኩ እርሱ በተናገራት ወንጌል ብቻ እመኑ ብለው ተናገሩ፡፡ ህዝቦችም የመለሱት ‹‹ካልሰገድንና ካልሰዋንለት ልጆቻችንን ያጠፋብናል›› ብለው ፍራሃታቸውን ገልጸው መለሱ፡፡ አባታችንም እኔ አየው ዘንድ ወዴት አለ ብለው ጠየቁ እነርሱም በማታ/በለሊት እንጂ በቀን አይታዩም ግን በዚህ ተራራ ላይ ይኖራሉ እሳት ለብሶ በጅብ ተቀምጦ ድምጽ እያሰማ እያገሳ ይመጣል፡፡ በጅብ የተቀመጡ ብዙ ሰዎች በግራና በቀኝ ይከቡታል ሁሉም በአፋቸው እሳት ይተፋሉ ብለው መለሱ አባታችን ተክለ ሃይማኖትም በእውነት ይህ እርኩስ ነው ከፈረሶቹም እርሱ ይረክሳል ብለው ሲቀጥሉ እስኪመሽ ድረስ እንጠብቀው እኔ ካሸነፍኩት ለእኔ አምላክ ለእየሱስ ክርስቶስ ብቻ ትሰግዳላችሁ እርሱንም ብቻ ታመልካላችሁ አጋንንቱ ካሸነፈኝ እኔም እሰግድለታለሁ አሉ፡፡ አምላካቸውንና አምላካችንን በልባቸው ዙፋን ሹመዋልና በእርሱም ተልከዋልና ህዝቡ ሁሉ ተስማማ፡፡
ሲመሽ በጅብ ተቀምጦ እሳት እየተፋ እንደ ክረምት ነጎድጓድ እያጋሳ ህዝቡ የሚያመልኩት ጋኒዬን መጣ፡፡ አባታችንም ተነስተው በጋኒዬኑ ላይ መስቀል አማተቡበት ጋኒዬኑ ከተቀመጠበት ጅብ ላይ ወደቀ እያጓራም ብን ብሎ ከአከባቢው ጠፋ፡፡ አብረውትም ያሉ አጋንንቶች ከቦታችን መጥቶ የሚያሳድደን ይህ ማን ነው? እያሉ እየጮሁ አብረው ጠፉ፡፡ ህዝቡም አምላክህ ሁሉን የሚያሸንፍ ሃያል አምላክ ነው ከዚህ ቡኋላ ያንተን አምላክ እንከተላለን በእርሱም እንታመናለን ብለው ከእግራቸው ስር ወደቁ፡፡ በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን ተብሎ ጳውሎስ በመልዕክቱ እንደተናገረ፡፡ አባታችንም በከበረ አንደበታቸው ለህዝቡ ወንጌልን አስተማሩ ለአጋንንቱ የምታረጉትን ሁሉ አምላካችን አይፈልግም በመገዛት ስገዱ በጽኑ እምነት አምልኩት እርሱ ብቻ የሁላችን ፈጣሪ ነው ከእርሱም ሌላ አምላክ የለንም እርሱ ይገድላል እርሱም ያድናል እያሉ ስለ አንዱ አምላካችን ስለ እየሱስ ክርስቶ መሰከሩ፡፡ ከዚህም ቡኋላ ህዝቡን ሁሉ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቁ (እግዚአብሔር በቅዱሳኑ ላይ ድንቅ ነው ተብሎ እንደተጻፈ) አምላካችን በጻዱቁ አማካኝነት ሃይልን አደረገ፡፡ ዘጠኝ ወር ከህዝቡ ጋር ቆይተው ወደ እናዕርታ አውራጃ አመሩ በዚያም ወንጌልን አስተማሩ የጣዖታትን ቤት አፈራረሱ ይህንንም ሃገር አልፈው በጉራጌ አቋርጠው ቢላል ወደሚባል አውራጃ ደረሱ፡፡
አከባቢው በጠንቋይ ንጉስ የሚመራ ነው አባታችንም ወንጌልን እየመሰከሩ ያለ ፍርሃት ህዝቡን ይገስጻሉ በዚህ አከባቢ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጠማቸው ብሎም በአካላቸው ላይ ደም በአፋቸውና በአፍንጫቸው እስከሚወጣ ድረስ ደበደቧቸው ከዚህም የተነሳ የሞቱ ስለ መሰላቸው ከተራራው ስር ጣሏቸው ቅዱስ ሚካዔል ግን አጽንቶ አስነሳቸው፡፡ ብጹዕ አባታችን ዳግም ሄደው የወንጌልን ቃል ተናገሩ የአካባቢውን ንጉስ ጭምር እየገሰጹ የእግዚአብሄርን ቃል መሰከሩ አሽከሮች ዳግም መከራን አበዙባቸው ቡኋላ ግን አልመለስ ያሉትን ሁሉ ለእግዚአብሄር አልገዛም ያሉትን ሁሉ መሬት አፏን ከፍታ እንድትውጣቸው ጸለዩ ‹‹አንቺ ምድር እነዚህን የማይገዙትን ሁሉ አፍሽን ከፍተሸ ትውጪያቸው ዘንድ በእኔ ቃል አይደለ በእግዚአብሄር ቃል አዝሻለሁ እያሉ ጸለዩ ወዲያውም መሬት ተከፍታ የአከባቢውን ንጉስና ጠንቋዮችን ሁሉ ዋጠቻቸው፡፡
ንጉስ ሞቶሎኒ እግዚአርያን አገባለሁ ብሎ ባሰበ በሰርጉ እለት ሚካዔል በብርሃንና በመብረቅ ሲሰነጥቀው ስላየ ንጉስ ሞቶሎኒ ጭንክላቱ ታውኮ ይኖር ነበርና የቢላቱ መስፍን ንጉሱን እንዲፈውሱ መልዕክት ለአባታችን ላከ ወደ ዳሞት ተመልሰውም ከመስፍን ጋር አብረው ሄዱ መቶሎኒ አባታችንን በቅርጫት ከቶ ወደ በጦም ግራርያ ገደል ውስጥ እንዲጥላቸው አሽከሮቹን ላከ በገደሉም ሲጣሉ ሚካዔል በክንፎቹ ደግፎ አዳናቸው ምንም ሳይሆኑ ወጡ አባታችንም በቶሎኒ ፊት ቆመው የእግዚኣብሄርን ክብር ይመሰክራሉ፡፡ ሞቶሎኒ የላካቸውን ሰዎች አላምናቸው ብሎ ከብዙ የአይን ምስክሮች ጋር አርጎ በድጋሚ እንዲጣሉ አዘዘ አሁንም ጉዳት ሳይደርስባቸው በሰላም ወጡ፡፡ ይህንን የተመለከቱ ሁሉ አስሩ የአይን ምስክሮች ሳይቀሩ በተክለ ሃይማኖት አምላክ በአምላካችን አመኑ ክርስትናን ተቀበሉ አምልኮተ ጣዖትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተዉ፡፡ አባታችንም ከጠንቋዮች ጋር ተከራክረው አሸነፉ ንጉሱን ሞቶሎኒን ክርስቲያን አርገው አጠመቁ ከዚህ ሁሉ ቡኋላ ንጉሱ ለቤተ-ክርስቲያን የሚሆን ገንዘብና ርስት ሰጠ፡፡ አባታችን በዳሞት ለአስራ ሁለት አመት እያገለገሉ ኖሩ ፡፡ ከግብጽ መጥተው በጳጳስነት ሲያገለግሉ የነበሩት ጳጳስ ለአባታችን ድቁናንና የቅስናን ማዕረግ የሰጡ አቡበ ጌርሎስ ከዚህ አለም በስጋ ከመለየታቸው የተነሳ ለብዙ ጊዜ ከግብጽ ጳጳስ ማስመጣት ቆሞ ስለ ነበር አፄ ይኩኑ አምላክ ከግብጽ ጳጳሥ ለማስመጣት በየመኑ ስልጣን በኩል ይጻጻፉ ነበር ነገር ግን የግብጽ ባለስልጣን ሙስሊም በመሆኑና በወቅታዊ ምክኒያት ኢትዮጵያ ጳጳስ አልነበራትም ነበር፡፡ በሸዋ አከባቢ በስብከተ ወንጌል ላይ ተሰማርተው የነበሩት አባታችን የምዕመናኑን ችግር ቤተ-ክርስቲያኗ ያለ መሪ መሆኑን እንደ ሰሙ ወደ አምላካችን ችግሩን ይፈታላቸው ዘንድ ፀለዩ እግዚኣብሄርም ጳጳስ በሊቃነ ጳጳሳት እንደሚሾም ሁሉ እኔ ግን አንተን ሾምሁህ በማለት እግዚአብሔር አምላክ ሾማቸው ለዚህ ስራ ከእኚህ ከሃዋርያው መነኩሴ የኢትዮጵያ ብርሃን ከሆኑ አባታችን ተክለ ሃይማኖት ውጪ ሌላ የለምና እግዚአብሔር መረጣቸው፡፡
በዚህ ሰማያዊ ስልጣናቸው ብዙ ስራዎችን ሰለቸኝ ደከመኝ ሳይሉ በመበርታትና በመጠንከር ሰሩ ህዝቡ ሁሉ በአመራራቸው የሚረኩ ለዚህ ስራ በእግዚአብሔር አብ የተመረጡ አባታችን ብጹዕ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከዚህ ቡኋላ ወደ አማራ ክልል ተጓዙ በክልሉ የአባታችንን ስለ ክርስቶስ የሚረጉት ተዓምር ተሰማ በተለያየ ደዌ የተያዙትንና በአልጋ ቁራኝነት ላይ ያሉትን ሁሉ እጃቸውን አሳርፈው እየጸለዩ ይፈውሱ ነበር፡፡ የደብር መነኮሳትም ይህንን ያደረገ እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር፡፡ ቅዱስ ሚካዔል ለአባታችን ተገልፆ አሁን ካለህበት ተነስተህ ሃይቅ ወደ ምትባል ስፍራ ሂድ ከእዛም ስትደርስ እየሱስ ኖሃ የሚባል ደግ ሰው ታገኛለህ እርሱም የምንኩስናን ቀንበር ያሸክምሃል ተከተለኝ እመራሃለሁም አላቸው፡፡ አባታችን ብፅዕ አቡነ ተክለ ሃይማኖትም ወደ ሃይቅ አመሩ ወደቡን የሚሻገሩበት አልቸገራቸውም የእግዚአብሄር መላዕክ ከእነርሱ ጋር ነውና ከሃይቁም ደረሱ ሃይቁን እንደመሬት እየረገጡ በሚካዔል መሪነት አባ እየሱስ ኖኃ ስር ደረሱ አባ እየሱስ ኖሃም ከተቀመጡበት ተነስተው በእንግድነት ተቀበሏቸው የቅድስናቸው ምሳሌ የሚሆነውን የምንኩስናን ልብስ አባታችን ለበሱ በዚሁ ሃይቅም ኖሩ በየሳምቱም ያከፍላሉ ከሰንበት ቀኖች ውጪ እህል አይቀምሱም ስጋቸውን በጾም በስግደት ያደክሙታል፡፡
ቀሪውን በቀጣዩ ክፍል እናቀርባለን የአባታችን የጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በረከትና ምልጃ አይለየን፡፡ ብቻውን ለሆነውና አለምን ሁሉ ላዳነው አምላክና መድሃኒታችን ከዘመን ሁሉ በፊት አሁንም እስከ ዘላለም ድረስ ለጌታችን ለመዳህኒታችን ለእየሱስ ክረስቶስ ክብርም ስልጣንም ሃይልና ግርማ ለእርሱ ይሁን የእናቱ የእመቤታችን የቅድስተ ቅዱሳን የድንግል ማርያም ጸጋዋና ምልጃዋ አይለየን፡፡ አሜን

No comments:

Post a Comment