Friday, November 8, 2013

የቅዱሳን አማላጅነት በአፀደ ነፍስ




የቅዱሳን አማላጅነት በአፀደ ነፍስ
ባለፈው ጽሑፋችን አማላጅነት ከመቼ ጀምሮ እንደነበረ የአማላጅነት ትርጉም ቅዱሳን በአፀደ ስጋ እንደሚያማልዱ እግዚአብሔር የወዳጆቹን ጸሎት እንደሚስማና የለመኑትን ሁሉ እንደሚፈጽሙላቸው አይተናል በዚህ ክፍል ደግሞ ቅዱሳን በአፀደ ነፍስ ማማለድ ይችላሉን? ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመስጠት እንሞክራለን፤ ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ያስችለን ዘንድ አስቀድመን የሰውን ተፈጥሮና ከሞት በኋላ የሚገጥመውን ሁኔታ ምን እንደሚመስል በመግቢያት እናያለን፡፡
የሰው ልጅ በአርአያ ስላሴ የተፈጠረ ክቡር ፍጡር ነው (ዘፍ 1፡26) ሰው ሥጋው ከምድር አፈር የተሠራ ቢሆንም ሥጋ ብቻ አይደለም ከሥጋ ጋር የተዋሃደች ነፍስ ደግሞ አለችው ፡፡ ስለዚህ ሰው በሥጋው የሚራብ የሚጠማ የሚበላ የሚጠጣ የሚደክም የሚታመም የሚዋለድና የሚሞት ሲሆን በነፍሱ ደግሞ የማይሞት የማይራብ የማይፈርስ የማይበሰብስ አሳቢ አዋቂ ተናጋሪ ሕያው ነው፡፡ ሰው ሲሞት ሥጋው ወደ ተፈጠረበት አፈርነቱ ይመለሳል ይፈርሳል ይበሰብሳል ነፍሱ ግን ሕያው ስለሆነች እንደ ስራዋ ወደ ገነት ወይም ወደ ሲዖል ትሄዳለች፡፡ በዚህ መሠረት ቅዱሳን ሥጋቸው በምድር እግዚአብሔር ከፈቀደላቸው ሥፍራ ሲቀበር ነፍሳቸው ደግሞ በገነት ውስጥ እንደመላእክት በደስታ ይኖራሉ፡፡




ይህ ከሆነ ዘንዳ ጻድቃን በአፀደ ነፍስ ሆነው መለመን ይችላሉን? በምድር የሚደረገውንስ ያውቃሉ? የሚሉትንና ሌሎችንም ጥያቄዎች ለመመለስ እንሞክር፡-
1.   ከሞት በኋላ ነፍስ የማትሞት ህያው እንደሆነች ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል ‹‹ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ›› (ማቴ 10፡28) ትንሳኤና ሕይወት እኔ ነኝ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፡፡ ሕያው የሆነው የሚያምንብኝም ለዘላለም አይሞትም፡፡ (ዮሐ 11፡26-26) ‹‹እኔ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ የሚል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ እናንተ የተባለውን አላነበባችሁምን የሕያዋን አምላክ እንጂ የሙታን አምላክ አይደለሁም›› (ማቴ 22፡23-33) በማለት የሞቱ ቅዱሳን በነፍስ ሕያዋን እንደሆኑ አስረድቶናል ከዚህም ሌላ ቅ/እስጢፋኖስ ‹‹ጌታ ኢየሱስ ሆይ ነፍሴን ተቀበል›› (ሐዋ 7፡59) ሲል ቅ/ጳውሎስ ደግሞ በአፀደ ሥጋ ከመኖር በአፀደ ነፍስ መኖር የበለጠ እንደሆነ ሲያስረዳ ‹‹በእነዚህ በሁለቱ እጨነቃለሁ ልሔድ ከክርስቶስ ጋር ልኖር እናፍቃለሁ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና›› (ፊሊጵ 1፡22-23) በማለት ጽፏል፡፡
2.   ሰው ከሞተ በኋላ በአፀደ ነፍስ እያለ በምድር የሚደረገውን ያውቃል ወይ? ለሚለውና ጥያቄ መልስ የሚሰጥ ቃል አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሮናል፡፡ (በሉቃስ 16፡19-31) ያለውን ጌታችን የተናገረውን ታሪክ ልብ በለው ያንብቡት በወንጌሉ መሠረት አብርሃምና አልዓዛር በገነት በደስታ ባለጸጋው ነዌ ደግሞ በሲዖል በአፀደ ነፍስ እንዳሉ እንረዳለን፡፡
ሀ) ባለፀጋው ከሥቃይ የተነሣ አባቴ አብርሃም ሆይ አልዓዛርን ላከውና አንድ ጠብታ ውሃ ይስጠኝ ሲለው አብርሃም ግን በአፀደ ስጋ ስላችሁ አንተ መልካም እንደተቀበልህ አልዓዛር ደግሞ ክፉ እንደተቀበለ አስብ አሁንም አንተ ብድርህን ሥቃይ አልዓዛር ዋጋውን ተቀብላችኋል በማለት ነግሮታል፡፡
አብርሃም ከሞተ የቆየ ቢሆንም አልዓዛርና ነዌ በምድር ሳሉ በምን ዓይነት ሁኔታ ይኖሩ እንደነበር አውቆ እንደተናገሩ አስተውሉ፡፡
ለ) ባለፀጋው ነዌ ሥቃይ ቢበዛበት በሲኦል ሆኖ ወደ አብርሃም ጮሆ እንደለመነና ልመናው ተቀባይነት እንዳላገኘ ከተረዳ በኋላ ተስፋ ቆርጦ ዝም አላለም በምድር ያሉትን ወንድሞቹን አስቦ አባቴ አብርሃም በምድር አምስት ወንድሞች አሉኝና አልዓዛርን ወደ እነርሱ ልከህ ወደ እዚህ ስቃይ እንዳይመጡ ይንገራቸው በማለት ስለወንድሞቹ እንደለመነ እንደማለደ እናያለን ባለፀጋው በአፀደ ነፍስ ሆኖ በምድር ስላሉት ወንድሞቹ ማሰቡ ኃጢዓተኛም ቢሆን ነፍሱ አዋቂ ስለሆነች ወንድሞቹ በንስሐ እንዳልተመለሱ በቀዱሞ ኑሯቸው ያሉ መሆኑን ስላወቀ አይደለም? ኃጢዓተኛው ባለፀጋ ለወንድሞቹ አዝኖ ወደ መከራ እንዳይገቡ ካለመነላቸው ቅዱሳን በገነት እያሉ በምድር የሚኖሩ ምዕመናን በፀሎትና በትሕትና በፍቅር በአክብሮት ስማቸውን ጠርተን መታሰቢያቸውን በማድረግ ቢለምኗቸው አይረዷቸውም ጨርሶም አይሰሟቸውም ተብሎ እንዴት ይታሰባል?
ሐ) ባለፀጋው ለለመነው ልመና አብርሃም ኦሪትና ነቢያት አሉላቸው ማለትም መፃሕፍት ተጽፎላቸዋል ሕግ ተሰርቶላቸዋል ብሎ መለሰለት፡፡ ባለፀጋው ከሙታን አንዱ ቢሄዱ ያምናሉ ቢለው ኦሪትና ነቢያትን የማይሰሙ ከሆነ ከሙታን አንዱ ቢሄድላቸው አያምኑም ማለቱ እስከመጨረሻው ድረስ የሚሠሩትን ቢያውቅ አይደለምን?
3.    (በሉቃ 9፡28-31) በተጻፈው ቃል ጌታችን በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን በገለፀ ጊዜ ‹‹ሙሴና ኤልያስ ከጌታ ጋር ይነጋገሩ ነበር በኢየሩሳሌም ይፈፀም ስላለው ስለመውጣቱ ይናገር ነበር›› ማለት ያልሞተው ኤልያስና በአፀደ ነፍስ ያለው ሙሴ ጌታ በኢየሩሳሌም ስለሚቀበለው ሕማማተ መስቀል አስቀድመው እንደተናገሩ እናያለን ሙሴ በአካለ ነፍስ በክብር ተገልጾ ወደፊት የሚሆነውን መናገሩ ሀብተ ትንቢት እንዳልተነሣውና አዋቂነቱን ያሳያል፡፡
4.   ቃየል በቅንዓት ምክንያት አቤልን ቢገድለው እግዚአብሔር ቃየልን ‹‹የወንድምህ የደሙ ድምፅ ከምድር ወደ እኔ ይጮሃል›› በማለት እንደመለሰለት እናያለን (ዘፍጥ 4፡9-10) ቅዱስ ጳውሎስም (በዕብ 11፡4-5) ላይ አቤል ከቃየል ይልቅ የሚበልጥ መስዋዕት ለእግዚአብሔር በእምነት አቀረበ በዚህም እግዚአብሔር ስለ ስጦታው ሲመሰክር እርሱ ፃድቅ እንደሆነ ተመሠከረለት ሞቶም ሳለ እስካሁን ይናገራል በማለት አቤል በነፍሱ እንደሚናገር ገልéEል፡፡ ጌታችንም በወንጌል ‹‹ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በቤተመቅደስና በመሠዊያው መካከል እስከገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም በምድር ላይ የፈሰሰው የጻድቅ ደም ሁሉ ይደርስባችሁ ዘንድ እውነት እላችኋለሁ፡፡›› (ማቴ 23፡35) በማለት የቅዱሳን ደም በከንቱ ፈሶ እንደማይቀር ከሞቱ በኋላ እንደሚያስፈርዱ ገልéEል ለዚህም የአቤልና የሌሎች ቅዱሳን ነፍስ ጠላቶቻቸውን እንዴት እንደተፋረዱ እንመለከታለን፤ በመጽሐፈ ሔኖክ እንደተፃፈው መልአኩ ቅ/ሩፋኤል ለነቢዩ ሄኖክ ነፍሳት ያሉበትን ቦታ እየዞረ ሲያሳየው እንዲህ ብሏል ‹‹የደጋግ ሰዎች ልጆች ነፍሳትንም አየሁ እነሱ ሞተው ሳሉ ቃላቸው እስከሰማይ ይደርሳል ወንድሞቻቸውንም ይከሳሉ ያንጊዜም ከኔ ጋር ያለ ሩፋኤል ቃሉ እስከ ሰማይ ድረስ የሚደርስ የሚከስ ይህ ነፍስ የማን ነው? ብዬ ጠየቅሁት እሱም ይህ ነፍስ ወንድሙ ቃየል በግፍ ከገደለው ከአቤል የተለየ ነፍስ ነው ልጆቹ ከዚህ ዓለም እስኪጠፋ ድረስ የልጅ ልጁም ከሰው ተለይቶ እስኪጠፋ ቃየልን ይከሳል ብሎ መለሰልኝ ›› በማለት ያየውን ጽፎልናል (ሄኖክ 6፡26-28) የአቤልና የሌሎቹም ነፍሳት በምድር የሚገኙትን ጠላቶቻቸውን ለመበቀል የሚከሱ ከሆነ ይልቁንም ለማዳን ወደ ፈጣሪያቸው ሊለምኑ አይችሉም ማለት ምክንያታዊ አይሆንም፡፡
5.   በሐዲስ ኪዳን ውስጥ ከላይ የተጠቀሰውን የመሰለ ጽሑፍ እናገኛለን ‹‹አምስተኛውን ማኅተም በፈታ ጊዜ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለጠበቁት ምስክር የታረዱትን የሰዎች ነፍሳት ከመሰዊያው በታች አየሁ በታላቅ ድምጽም እየጮኹ ቅዱስና እውንተኛ ጌታ ሆይ እስከመቼ ድረስ አትፈርድም ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም? አሉ ለእያንዳንዳቸውም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው እንደነርሱም ደግሞ ይገደሉ ዘንድ ያላቸው የባሪያዎች ባልንጀራዎቻቸውና ወንድሞቻቸው ቁጥር እስኪፈፀም ድረስ ገና ጥቂት ዘመን እንዲያርፍ ተባለላቸው›› (ራዕ 6፡9-11) በማለት ቅዱስ ዮሐንስ በራዕይ ያየውን ጽፎልናል፡፡

ከነዚህ ጥቅሶችም የምንረዳው፡
ሀ) ቅዱሳን በአፀደ ነፍስ ሆነው ፈጣሪያቸውን መጸለይ (መለመን) እንደሚችሉ የአቤልም ሆነ የሌሎች ሰማዕታት ነፍሶች በታላቅ ድምፅ እየጮሁ እንደለሙ ያሳያል
ለ) ቅዱሳን በአፀደ ነፍስ ሆነው በምድር የሚደረገውን እንደሚያውቁ የአቤልም ሆነ የሌሎች ቅዱሳን ነፍሶች ጠላቶቻቸው ጨርሰው እንዳልተፈረደባቸው አሁንም በምድር እንዳሉ አውቀው ፈጣሪያቸው እንዲበቀልላቸው እንደለሙ ለመረዳት ይቻላል፡፡
ሐ) ቅዱሳን በአፀደ ነፍስ ሆነው የሚለምኑት ልመናቸው ተሰሚ ጸሎታቸው ግዳጅ ፈጻሚ እንደሆኑ የአቤል ነፍስ ተካሰ የቃየልን ልጆች በጥፋት ውሃ አስጠፍታለች ዮሐንስም ያያቸው የቅዱሳን ነፍስ የለመኑት ልመና ተቀባይነት ያገኘ ሲሆን እንደነሱ አክሊለ ሰማዕት የሚቀበሉ ወንድሞቻቸው ሰማእታት እስከሚገደሉ ብቻ እንዲታገሱ ከዚያ እንደሚፈረድላቸው ተነግሯቸዋል የንጽሕና ምልክት የሆነ ነጭ ልብስም አጎናጽፏቸዋል እንግዲህ እነዚህ ቅዱሳን ጠላቶቻቸውን ለመበቀል ከጸለዩ የእነሱን ሰማዕትነት ለሚቀበሉ በእነሱ ሃይማኖት ለሚያምኑ በጸሎቻቸውም ለሚማጸኑ መታሰቢያቸውን ለሚያደርጉ ለሚያከብሯቸው ምእመናን ወዳጆቻቸው ወደ እግዚአብሔር ‹‹ማርልን›› ይቅር በልልን ከጠላታቸው ከሰይጣን ጠብቅልን ለመንግስተ ሰማያት አብቃልን……›› ብለው ለመለመን አይችሉም፤ እግዚአብሔር አይሰማቸውም አይባልም፡፡ (ማቴ 23፡35) ላይ ጌታችን እንዳስተማረን ከአቤል ጀምሮ እስከ ዘካሪያስ ድረስ የፈሰሰው የቅዱሳን ደም በዚህ ትውልድ ይፈለጋል ያለው በአፀደ ነፍስ እነዚህ ቅዱሳን ራሱን ጌታችንን አቤቱ እስከመቼ ደማችንን በምድር በሚኖሩት ላይ አትፈርዱም ብለው እንደጠየቁትና እርሱም ልመናቸውን ሰምቶ ፈታሂ በጽድቅ ኩናኒ በርትዕ ነውና እንደሚፈርድ የገለፀው በዚህ ምክንያት ነው (ኤር 26፡15፣ ሄኖ 39፡40)
6.   ቅዱሳን በአፀደ ነፍስ ሆነው በምድር ያሉ ኃጢዓተኞችን እንደሚገዙ ጥበበኛው ሰሎሞን በመጽሀፍ ጥበብ ‹‹የደጋግ ሰዎች ነፍስ ግን በእግዚአብሔር እጅ ናት የኃጢዓተኞች መከራ አላገኛቸውም ለአላዋቂዎች ግን የሞቱ መስሎ ሞታቸው ጥፋት መሠለ እነርሱ ግር በተድላ በደስታ አሉ በሰው ፊት ሞቱ ቢባል አለኝታቸው ግን በእግዚአብሔር ዘንድ ሞት የሌለበት ፍጽምት ሕይወት ናት›› (ጥበብ 3፡1-4) ብሎ ከጻፈ በኋላ በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ‹‹ደግ ሰው ግን ከሞተ በኋላ በደኅንነት ሳሉ እግዚአብሔር የዘነጉ ሰዎችን ይገዛል›› (ጥበብ 4፡16) በማለት ለቅዱሳን የተሠጣቸውን ክብር ጽፎልናል ነቢዩ ዳዊት ቅዱሳን በአፀደ ሥጋ ሳሉ ኃጢዓተኞችን እንደሚገዙ ሲናገር ‹‹ቅዱሳን በክብር ይመካሉ በምንጣፋቸውም ላይ ሐሴትን ያደርጋሉ የእግዚአብሔርም ምስጋና በጉሮሮአቸው ነው ሁለት አፍ ያለው ሰይፍ በእጃቸው ነው በአሕዛብ ላይ በቀልን በሰዎችም መካከል ቅጣትን ያደርጉ ዘንድ ንጉሦቻቸውንም በሰንሰለት አለቆቻቸውንም በእግር ብረት ያስሩ ዘንድ የተጻፈውንም ፍርድ ያደርጉባቸው ዘንድ ለቅዱሳን ሁሉ ይህች ክብር ናት፤ ሃሌ ሉያ›› ብሏል (መዝ 149፡5-9) በምድር እያሉ የተሰጣቸው ጸጋና ክብር በሰማይ በአፀደ ነፍስ ፈተና በሌለበት ድል ካደረጉ በኋላ ክብራቸው የሚጨምር (የሚበዛ) እንጅ የሚቀንስ አይደለም በምድር ሳሉ በእግዚአብሔር ኃይል ወደሱ ጸልየው አመፀኞችን የሚቀጡ ትሑታን ምዕመናንን የሚረዱ ከሆነ ይህን በአፀደ ነፍስ የማይፈጽሙበት አንዳችም ምክንያት የለም (ራዕይ 6፡9-11)
7.   እግዚአብሔር ለወዳጆቹ ለቅዱሳን ሙታነ ሥጋን በተአምራት ሙታነ ነፍስን በትምህርት እንዲያስነሱ ‹‹ድውያችን ፈውሱ ሙታንን አስነሱ ለምጻሞችን አንጹ አጋንንትን አውጡ (ማቴ 10፡8)›› በማለት ጽኑ ሥልጣን ሰጥቷቸዋል በዚህ መሠረት በነቢዩ ኤልሳዕ በአፀደ ስጋ ሳለ አንድ ሙት አስነስቷል (2ነገ 4፡32-37) ኤልሳዕ ስለሞተው ሕፃን ወደ ፈጣሪው አማልዶ (ለምኖ) የህፃኑን ነፍስ ከአፀደ ነፍስ አምጥቶ በአፀደ ሥጋ ከሚገኘው አስከሬን ጋር በማዋሐድ አስነስቶታል ይኸው ነቢይ ኤልሳዕ ከሞተም በኋላ በአፀደ ነፍስ ሆኖ ተመሳሳይ ሥራ ሠርቷል፡፡ ‹‹ኤልሳዕ ሞተም ቀበሩትም ከሞዓብም አደጋ ጣዮች በየዓመቱ ወደ አገሩ ይገቡ ነበር ሰዎችም አንድ ሰው ሲቀብሩ አደጋ ጣዮችን አዩ ሬሳውንም በኤልሳዕ መቃብር ላይ ጣሉት የኤልሳዕንም አጥንት በነካ ጊዜ ሰውየው ድኖ በእግሩ ቆመ›› (2ነገ 13፡20-21) ኤልሳዕ በኤልያስ ያደረው ሀብተ መንፈስ ቅዱስ እጥፍ ድርብ ሆኖ እንደተሰጠው ለማጠየቅ ኤልያስ አንድ ሙት ሲያስነሣ ኤልሳዕ ግን ሁለት ሙት አስነስቷል፡፡ አንዱን በአፀደ ሥጋ ሳለ ሁለተኛውን ግን በአፀደ ነፍስ እያለ አስነስቷል ውጤቱ ማለትም የሞቱት ሰዎች መነሣት አንድ፤ ሲሆን ኤልሳዕ በአፀደ ሥጋ ሆኖ የሰራውን ከሞተ በኋላም ያንኑ ተመሳሳይ ስራ መሥራቱ ቅዱሳን ከሞቱ በኋላ ቢለምኗቸው አይረዱም የሚለውን ሐሳብ ውድቅ ያደርገዋል፡፡
8.   (በ1ነገስ 13፡1-32) በተጻፈው ታሪክ መሠረት በቤቴል መሠዊያ ላይ ትንቢት የተናገረው ነቢይ በሐሰት ያሳሳተውና ያስቀሰፈው ሽማግሌው ነቢይ የነቢዩን አስከሬን ወደ ገዛ ከተማው አምጥቶ በራሱ መቃብር ቀበረው አለቀሰለትም በመጨረሻም ሽማግሌው ነቢይ ልጆቹን ሰብስቦ ‹‹በሞትህ ጊዜ የእግዚአብሔር ሰው በቤቴል ትንቢት የተናገረው ነቢይ በተቀበረበት መቃብር ቅበሩኝ አጥንቶቼንም በአጥንቶቹ አጠገብ አኑሩ በቤቴል ባለው መሠዊያ ላይ በእግዚአብሔር ቃል የጮኸው ነገር በእውነት ይደርሳልና›› በማለት ተናዘዘ ይህ ሽማግሌ ነቢይ ይህንን መናዘዙ በሐሰት ያሳሳተው ነቢይ እውነተኛ መሆኑን አውቆ በፈጸመው ኃጢዓት በአካለ ነፍስ እንዲረዳው አይደለምን? ቅዱሳን ከተቀበሩበት ቦታ የሚቀበር ከቅዱሳን ረድኤት በረከት እንደሚሳተፍ የኤልሳዕና የዚህ ነቢይ ታሪክ አስረጅ ነው፡፡ ስለ ቅዱሳን ሰዎች መቃብር በተመለከተ ነቢዩ ዳዊት ‹‹የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው እግዚአብሔርም ከሁሉ ያድናቸዋል እግዚአብሔር አጥንቶቻቸውን ሁሉ ይጠብቃል ከእነርሱም አንዱ አይሰበርም›› (መዝ 33፡19-20) በማለት እግዚአብሔር ከቅዱሳን መቃብር እንኳ እንደማይለይ ተናግሯል፡፡ ስለዚህ ቅዱሳን በተቀበሩበት ቦታ መቀበር ሳይቀር ጥቅም እንዳለው ይህ ጉልህ ማስረጃ ነው ዛሬም ቅዱሳን ከተቀበሩበት ቦታ ለምሳሌ ደብረ ሊባኖስ ወስዳችሁ ቅበሩኝ በማለት ብዙ ሰዎች የሚናዘዙትና በኑዛዜው መሠረት የሚቀበሩት ከላይ በተጠቀሱት የቅዱሳት መጻሕፍት ማስረጃዎች ላይ በመመሥረት እንጂ ልማድ አይደለም ደግሞም የፃድቃነ ብሉይ መቃብር ይህን ያህል ከጠቀመ የፃድቃነ ሐዲስ መቃብርማ አብልጦ እንዴት አይጠቅም፡፡
9.   በ (ኤር 15፡1) ላይ እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ ‹‹ሙሴና ሳሙኤል በፊቴ ቢቆሙም ልቤ ወደ እዚህ ሕዝብ አያዘነብልም ከፊቴ ጠላቸው ይውጡ›› በማለት ጽፏል ሙሴና ሳሙኤል በአፀደ ሥጋ ሳሉ ለወገኖቻቸው ያማልዱ እንደነበር ታሪካቸው ያስረዳል እስራኤላውያን በኃጢዓታቸው ሰለጸኑ ኤርሚያስም ቢጸልይላቸው እግዚአብሐየር ‹‹አልሰማህምና አትጸልይላቸው!›› እንዳለው ተጽፏል (ኤር 7፡16-20) ኤርሚያስ በአፀደ ሥጋ ስለወገኖቹ ሊፀልይ ሙሴና ሳሙኤል በአፀደ ነፍስ ሆነው እንደሚጸልዩ ጥቅሱ ያስረዳል ‹‹በፊቴ ቢቆሙም›› የሚለው አባባል ቢፀልዩም፣ ቢለምኑም ፣ ቢያማልዱም ማለት እንደሆነ ዳዊት በመዝሙሩ ‹‹ያዳናቸውንም እግዚአብሔርን ረሱ እንዳያጠፋቸውም ቁጣውን ይመልስ ዘንድ የተመረጠው ሙሴ በመቅሰፍት ጊዜ በፊቱ ባይቆም ኖሮ ያጠፋቸው ዘንድ ተናገረ›› (መዝ 105፡19-23) በማለት ሙሴ በኦሪት ዘጽዓት 32፡1-14 ላይ ያለውን እስራኤላውያንን በጸሎቱ ከመቅሠፍት ያዳነበትን ታሪክ ገልጾታል በዚህ መሠረት ሙሴ በአፀደ ነፍስ ከሳሙኤል ጋር እንደለመደው እግዚአብሔር ሕዝቡን እንዳይቀስፍ በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ ይጸልይ ነበር ማለት ነው፡፡
10. የእስራኤል ንጉሥ ሳዖል ፍልስጤማውያን ከበውት በተጨነቀ ጊዜ ወደ ፈጣሪው ጸለየ እግዚአብሔርም በሕልምም በነቢይም አልመለሰለትም፡፡ ስለዚህ በተጨነቀ ጊዜ በዓይንዶር ወዳለች አንዲት ሴት ሄዶ የነቢዩ የሳሙኤልን ነፍስ እንድትጠራለት ጠየቃት (1ሳሙ 28፡1-25) እሷም በተባለችው መሠረት ሳሙኤልን ጠርታ ባየችው ጊዜ ደነገጠች ‹‹አንድ ሽማግሌ ሰው ወጣ መጎናፀፊያም ተጎናጽፏል›› አለች ሳኦልም ሳሙኤል እንደሆነ አውቆ በምድር ላይ ተጎንብሶ እጅ ነሣው ሳሙኤልም ሳኦልን ‹‹ለምን አወከኝ ለምንስ አስነሳኸኝ አለው›› ሳኦልም ‹‹እነሆ ፍልስጤማውያን ከበውኛል እጅግ ተጨንቄአለሁ እግዚአብሄርም አልመለሰልኝም ከእኔ ርቋል አለው›› ‹‹ሳሙኤልም እግዚአብሔር በቃሌ እንደተናገረ እንዲሁ መንግስትህ ከአንተ ወስዶ ለዳዊት ሰጥቶታል በአማሌቅ ላይ ያለው ታላቅ ቁጣውን አላደረግህምና እስራኤላውያንን ከአንተ ጋር አሳልፎ ይሰጣል አንተና ልጆችህ ነገ ከእኔ ጋር ትሆናላችሁ›› በማለት ወደፊት የሚደርስበትን ሁሉ ነገረው ከዚህ የምንረዳው በዘመነ ኦሪት በዓመተ ፍዳ በዓመተ ኩነኔ የነበረ ሳሙኤል በአካለ ነፍስ ተገኝቶ ካነጋገረውና የሚደርስበትን ነገር አስቀድሞ ካሳወቀው ከተፈፀመ በዘመነ ሐዲስ በዓመተ ምህረት በገነት ያሉ ቅዱሳን ነፍሳት በተጨነቅን ጊዜ በጸሎታቸው አምነን በቃል ኪዳናቸው ተማጽነን ብንጠራቸው በአካለ ነፍስ በረድኤት እንደሚጎበኙንና ከችግራችን እንደሚታደጉን ለእኛ ለኦርቶዶክሳውያን ጥርጥር የሌለበት በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ሁል ጊዜ የምናረጋግጠው እውነተኛ ቃል ነው፡፡
11. በማቴ 19፡27-30 ላይ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹እነሆ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ እንግዲህ ምን እናገኝ ይሆን?›› ብሎ ጌታን ጠየቀው ጌታችንም ‹‹እውነት እላችኋለሁ እናንተስ የተከተላችሁኝ በዳግመኛ ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ እናንተ ደግሞ በአስራሁለቱ የእስራኤል ነገድ ልትፈርዱ በአስራ ሁለቱ ዙፋን ትቀመጣላችሁ›› በማለት በአፀደ ሥጋና በአፀደ ነፍስ የሚያገኙትን ክብር ገልጾላቸዋል እንግዲህ በአስራ ሁለቱ ወንበር ተቀምጠው እንዲፈርዱ ስልጣን ከሰጣቸው ለምኖ ማስታረቅን ይቅርታን ማሰጠትን ይነፍጋቸዋል ተብሎ አይታሰብም ከማማለድ ይልቅ መፍረድ ይበልጣልና፡፡

No comments:

Post a Comment