Saturday, November 2, 2013

ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕሪ አምላክ ነው





ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕሪ አምላክ ነው
የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክረስቶስን የባሕሪ አምላክነት ሐዋርያት በሰፊው አስተምረውናል፡፡ በየዘመኑ የተነሱ ሊቃውንትም አሟልተውና አስፍተው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል ነገር ግን ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆርንቶስ ክርስቲያኖች እንደፃፈው (1ቆሮ 1፡24) የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ጥበብ በመሆኑ ለሰነፎች ሊረዳቸው አልቻለም፡፡ ጥበብን የሚረዳ ልባሞች እንጂ ሰነፎች አይደሉምና፡፡ በተለይም የሰው ጥበብ የእግዚአብሔርን ጥበብ ሊመረምር አይችልም ከሰው ጥበብ ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ስለሚጠበብ በእምነት ልባሞች የሆኑ እንጂ በሥጋዊ ጥበብ ልባሞች የሆኑ የዋጃቸውን አምላክ ማወቅ አልቻሉም የፍጡራን ጥበብ ፍጥረታትን እንጂ ፈጣሪን መርምሮ መረዳት አልቻሉም፡፡ በቀደሙት ዘመናት አይሁድ ቀጥሎም ክርስትናን ከተቀበሉት ወገን አርዮስና ተከታዮቹ ከ325 ዓ.ም ቀደም ብለው ጀምረው በሥጋዊ ጥበብ ሊያውቁት በመሞከራቸው በእምነት ያውቁት የነበረውን የባሕሪይ አምላክ ክርስቶስን አጥተውታል፡፡ አሁንም በዚህ ዘመን ክርስቶስን በሥጋዊ ጥበብ ለማግኘት በሚደረግ ጥረት ሰለባ የሆኑ ጥቂቶች አይደሉም፡፡

በመጀመሪያ አርዮስ የወደቀው በመጽሐፈ ምሳሌ ምዕራፍ ስምንት ቁጥርም ሃያሁለት ላይ ባለው ኃይለቃል ሲሆን ዛሬም ያሉት ተከታዮቹ ይህንኑ ጥቅስ ጨምረው ራሳቸውን በስንቱ ጠልፈው የሚጥሉበት ጥቅስ አላጡም በሥጋዊ አመለካከታቸው ብቻ ስለሚረዱ ጠቅላላው መጽሐፍ ቅዱስ ለእነርሱ ስጋዊ እንጂ መንፈሳዊ ትርጉም የለውም፣ ይነገራቸው ዘንድ አይሹም በመጽሐፈ ምሳሌ 8፡22 የተነገረው ለጥበብ ሆኖ ሳለ በ1ኛ ቆሮ 1፡24-25 መሠረት ለክርስቶስ ተጠቅሷል ጥበብ ማለት ክርስቶስ ነው ይላሉ ሆኖም በቆላ 2፡3 ላይ የጥበብና የዕውቀት መዝገብ ሁሉ በእርሱ ነው ይላሉ፡፡ ይህ ጥቅስ አዋቂነቱን ጥበቡን ይገልጣል እንጂ ጥበብ የተባለ አካላዊ ክርስቶስ ነው አይልም፣ እንደተባለውም ቢሆን እንኳን የእግዚአብሔር ጥበብ ዘላለም ከእርሱ ጋር ስለሚኖር የተፈጠረ ሊሆን አይችልም፡፡ ስለ ጥበብም መፍጠር አይታሰብም፣ ጥቅሱም ‹‹የመንገድ መጀመሪያ አደረገኝ›› ይላል እንጂ ‹‹ፈጠረኝ›› አይልም በተለይም ወልድ አባቴ ወለደኝ ከአብ ወጥቼ ወደ ዓለም መጥቻለሁ (ዮሐ 16፡28 ፣ መዝ 110፡3) ከማለት በስተቀር በአንድም ቦታ ፈጠረኝ አላለም አብም ቢሆን ወለድሁህ አለ እንጂ ፈጠርሁህ አላለም፡፡
መውለድና መፍጠር ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው እንደ አርዮስና ተከታዮቹ መውለድና መፍጠር አንድ ሊሆኑ አይችሉም ማንም የሚወልደውን አይፈጥረውም የሚፈጥረውንም አይወልደውም ሆኖም የአብ መውለድ የወልድ መወለድ በስጋ ለባሽ ሥርዓት በሥጋ ፍጥረት ሕግ የሚተረጎም አይደለም፣ ሰው ሕልውናውን የሚጀምረው በዘመን ነው በአንድ ወቅት ልጅ ይባል የነበረው በሌላ ጊዜ አባት ይባላል፡፡ ወልድ ግን ዘላለም ወልድ ነው ‹ቃል› በመባሉም ሆሄያት ተገጣጥመው ድምፅ   እንደሚሰጡ በላንቃ በትናጋ እንደሚነገሩ ዝርዋን ቃላት አይደለም አካላዊ ቃል ነው እንጂ የሰው ቃል የመስራት ኃይል የለውም፡፡ የእግዚአብሔር ‹‹ቃል›› ግን ከፍጹም አምላክ የተገኘ ፍፁም አምላክ ስለሆነ ፈጣሪ ‹‹ቃል›› ነው፡፡ (ዮሐ 1፡3)
መውለድንና መፍጠርን አንድ የሚያደርጉ ወገኖች ለሃሣባቸው ድጋፍ (መዝ 89፡2) ያለውን ተራሮች ሳይወለዱ የሚለውን ጥቅስ በመጥቀስ በተራሮች መፈጠር አንጂ መወለድ ስለማይስማማቸው ተወለዱ ሲል ተፈጠሩ ማለቱ ስለሆነ ለክርስቶስም ተወለደ ማለት ተፈጠረ ማለት ነው ይላሉ፣ ነገር ግን የመውለድንና የመወለድን ፅንስሰ ሃሣብ ስለማወቅ የመነጨ ነው፡፡
ተወለደ ማለት ከነበረው ተገኘ ከአንድ ባሕሪይ ተከፈለ መስሎና አክሎ ወጣ፣ ካለው ተገኝቶ ታየ ማለት ነው፡፡ እንደምናውቀው ሁሉ አስመስሎ አሳክሎ የራሱን ልጅ የሚፈጥር እስካሁን የለም ወደፊትም አይኖርም፣ የፈጠረውን የፀጋ ልጅ ማድረግም ቢሆን የእግዚአብሔር ብቻ ነው ተራሮች ሳይወለዱ ማለቱ ሳይፈጠሩ ማለቱ ካልሆነ ታዲያ ምን ማለቱ ነው? የሚል ጥያቄ ይነሣ ይሆናል መልሱ እንዲህ ነው የተራሮች መፈጠር ከመሬት ጋር እንጂ ከመሬት ተለይቶ አይደለም፡፡ ተራራ ከመሬት አካል መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ እግዚአብሔር አንዱን ምድር ተራራና መሬት ብሎ በሁለት ከፍሎ ሁለት ጊዜ አልፈጠረም፡፡ በሥነ ፍጥረት መጽሐፍም ‹‹ምድር ባዶ ነበረች›› (ዘፍ 1፡2) ቅርፅም አልነበራትም ባለው መሠረት እንዲሁም (ዘፍ 1፡6-9) ላይ እንደተገለፀም ውሃ ቦታ ቦታውን ሲይዝ ከመሬት የተወለደ መጀመሪያ ከተፈጠረው መሬት የተገኘ ነው እስከዛሬም ድረስ በሳተ ገሞራ ፍንዳታና፣ በጎርፍና በመሳሰሉት ሜዳ ከነበረው መሬት ላይ ተራራ ሲወጣ ሲወለድ ይታያል፣ ተራራ በየምክንያቱ በወጣ ቁጥር በልማድ ካልሆነ በስተቀር ተፈጠረ አይባልም አንድ ጊዜ ከተፈጠረው የመሬት አካል ከመገኘቱም ሌላ እግዚአብሔር ሥነፍጥረቱን በስድስት ቀን ፈጥሮ በሰባተኛው ቀን አርፎአል ተራራዎችን ለመፍጠር በየጊዜው አይደክምም፡፡ (ዘፍ 2፡1-3) ስለዚህ ተራራ መጀመሪያ ከተፈጠረው መሬት የወጣ፣ የተገኘ የተወለደ እንጂ የተፈጠረ አዲስ ፍጥረት አይደለም፣ በ(መዝ 89፡2) ላይ ያለው ሃሣብ ውሃና የብስ ከመለያየታቸው አስቀድሞ ተራሮች በየምክንያቱ ከመውጣታቸው በፊት ማለት ነው፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ፍጹም የባሕሪይ አምላክ እንጂ ተቃዋሚዎች እንደሚሉት በአብ የተዘጋጀ ትንሽ አምላክ አይደለም፣ የባሕሪይ አምላክ የኢየሱስ ክርስቶስን ታላቅ አምላክነት ቅዱሳት መጻሕፍት በእርግጠኝነት ይገልጻሉ፡፡
‹‹አንቺም ቤተልሔም ኤፍራታ ሆይ አንቺ በይሁዳ አዕላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ እሰከ ከዘላለም በእስራኤል ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል›› (ሚክ 5፡2)
‹‹ከዚችም ዓለም ገዥዎች አንዱ እንኳን ይህንን ጥበብ አላወቀም፣ አውቀውስ ቢሆን የክብርን ጌታ ባልሰቀሉትም ነበር›› (1ኛ ቆሮ 2፡8) ‹‹በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና፣ አለቅነትና ለስልጣንም ሁሉ ራስ በሆነ በእርሱ ሆናችሁ ተሞልታችኃል›› (ቆላ 2፡9)
‹‹ከእነርሱም ክርስቶስ በሥጋ መጣ እርሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው አሜን›› (ሮሜ 9፡5)
‹‹አምላካችንና አባታችን ራሱ ጌታችንም ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እናንተ መንገዳችንን ያቅና›› (1ኛ ተሰ 3፡11)
‹‹የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን አምላካችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ክብር መገለጥ እየጠበቅን ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንኑር›› (ቲቶ 2፡13-14)
‹‹እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለማዊ ሕይወት፣ ልጆች ሆይ ከጣዖታት ራሳችሁን ጠብቁ›› (1ኛ ዮሐ 5፡20-21)
‹‹በክርስቶስም ትምህርት ለማይኖር ሰው አምላክ የለውም በክርስቶስ ትምህርት ለሚኖር አብና ወልድ አሉት ማንም ወደ እናንተ ቢመጣ ይህንን ትምህርት ባያመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት ሰላምም አትበሉት ሰላምም የሚለው ሰው በክፉ ሥራው ይካፈላልና›› (2ኛ ዮሐ 1-9)
‹‹ነውር የሌላችሁ አድርጎ እንዲያቆማችሁ ለሚችለው ብቻውን ለሆነ አምላክና መድኀኒታችን ከዘመን ሁሉ በፊት አሁንም እስከ ዘላለም ድረስ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ግርማ ኃይልም ስልጣንም ይሁን አሜን›› (ይሁዳ 1፡24-25) በተጨማሪም ከዚህ በታች ያሉት ጥቅሶች የክርስቶስን የባሕሪ አምላክነት ያስረዳሉ (መዝ 2፡12፣ መክ 12፡14፣ ማቴ 11፡27፣ ማር 1፡2 ፣ ሐዋ 10፡36 ፊልጵ 3፡18-19፣ ምሳ 30፡4 ፣ ማቴ 3፡3 ፣ ማቴ 12፡8 ሐዋ 7፡57፣ ሮሜ 6፡11)
የክርስቶስን ታላቅ አምላክነት የሚገልጹ እጅግ ብዙ ማስረጃዎች እያሉ ክርስቶስን ትንሽ አምላክ የሚሉበት ምክንያት ‹‹የምትወዱኝ ብትሆኑ ከእኔ አብ ይበልጣልና ወደ አብ በመሄዴ ደስ ባላችሁ ነበር›› (ዮሐ 14፡28) የሚለውን የፍቅር አጽናኝ ቃል በመያዝ ነው በመሠረቱ ስለ ክርስቶስ ታላቅነትና የባሕሪ አምላክነት የሚያስረዳ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እያሉ ይህን አንድ ጥቅስ ይዞ መደናገርና ማደናገር ሆን ተብሎ የተደረገ እንጂ የመሳሳት አይመስልም ዳሩ ‹‹መጽሐፍን ለገዛ ጥቅማቸው ያጣምማሉ›› አይደለም ያለው ሐዋርያው ትንቢቱ ይፈፀም ዘንድ ግድ ነው፡፡
መናፍቃን (ተቃዋሚዎቸ) እውነተኛ ቢሆኑ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙር 8፡5 የጻፈውንና ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን መልክቱ ምዕራፍ ሁለት ላይ ጠቅሶ የተረጎመውን አንብበው በትክክል በተረዱ ነበር ‹‹ስለ ሰው ሁሉ ሞትን ይቀምስ ዘንድ ከመላዕክት ይልቅ በጥቂቱ አንሶ የነበረውን ኢየሱስን ከሞት መከራ የተነሣ የክብርና የምስጋና ዘውድ ተጭኖ እናየዋለን ይላል፡፡››
ይህንን ኃይለ ቃል ቀደም ብሎ ክቡር ዳዊት የፃፈውና የተናገረው ሲሆን ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ ከመላዕክት ያነሰበት ምክንያት ሞትን በመቅመሱ መሆኑን መልአክ ካለመሆኑ ጋር በጉልህ ይነግረናል፡፡ መላዕክት  በባሕሪያቸው ሞት የለባቸውም፣ በባሕሪው ሞት የሌለበት ወልድ የሚሞተውን የሰውን ሥጋ ገንዘቡ በማድረጉና ከአብርሃም ዘር በመምጣቱ የማይሞተው ሞተ ሞት ግን አላሸነፈውም፡፡

ነገር ግን ሞትን በመቅመሱ እንኳን ከአብ ከእጁ ሥራዎች ከመላዕክት አንሶአል ተብሎ የለምን? መጽሐፍ ‹‹ንባብ ይገድላል ትርጉም ያድናል›› ይላልና እባካችሁ እናስተውል፡፡
ቅዱስ ዳዊት ትንቢት በሚናገርበት ዘመን ‹‹ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ›› (መዝ 117፡22) በማለት ትንቢት የተናገረው ለጊዜው ለቤተ አይሁድ ሲሆን የባሕሪ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ የአዳምን ዘር ከጠፋበት ለመመለስ፣ ለ5500 ዘመን ገዥ ሆኖ የሰው ልጆችን በመርገም እየተቆራኘ ሥጋቸውን በመቃብር ነፍሳቸውን በሲኦል ስያግዝ የነበረውን ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስን ድል በማድረግ ካሣ ይከፍል ዘንድ ከሰማያት ወርዶ ከድንግል ተፀንሶ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ በምድር ላይ ቢመላለስ አይሁድ ‹‹የዮሴፍ ልጅ ፍጡር›› ብለው አቃለውታልና፣ ፍፃሜው ግን ግንቦች ያላቸው የዛሬዎቹን ከሃዲያንና መናፍቃንን የባሕሪ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስን ‹‹የሺህ ዓመት ገዥ፣ አማላጅ፣ ከአብ ያነሰ፣ ፍጡር›› እያሉ የሚያቃልሉትን ስተው የሚያስቱትን ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ እያሉ ኃይሉን ግን በመካድ የተሳሳተ ትምህርትን ለሚያስተምሩ የተነገረ የትንቢት ቃለ ነው በወንጌል አርጋዊውና ካህኑ ሰምዖን እንዲህ በማለት ተናግሯል፡፡
‹‹እነሆ የብዙዎች ልብ ሃሣብ ይገለጥ ዘንድ ይህ በእስራኤል ላሉት ለብዙዎች ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው ለሚቃወሙትም ምልክት ተሾሟል›› ለቃ 2፡34
በመሆኑም ብዙዎች አናጺዎች የተሰኙ ቤተ አይሁድ ፃሕፍት ፈሪሳውያን ቃሉ ሞልቶናል እናውቃለን የሚሉ የቃሉ ባለሙያዎች በክርስቶስ በተሰናከሉ ጊዜ በፊሊጶስ ቂሣሪያ ደቀመዛሙርቱን ጥያቄ ጠየቀ በምድር ላይ ሰው ሆኜ መገለፄን የእጄን ተአምራት የሚያዩ የቃሌን ትምህርት የሚሰሙ ሰዎች እኔን ማን ይሉኛል? ምክንያቱም የተወደደውን የተከበረውን ድንጋይ ፍጡር የዮሴፍ ልጅ በአጋንንት አለቃ አጋንንት የሚያወጣ ብለው አይሁድ እንደሚያስወሩበት አምተው እንደሚያሳሙት በአምላክነቱ ያውቃልና ‹‹ነገር ግን የሰራዊትን ጌታ እግዚአብሔር ቀድሱ የሚያስፈራችሁና የሚያስደነግጣችሁ እርሱ ይሁን እርሱም ለመቅደስ ይሆናል ነገር ግን ለሁለቱ የእስራኤል ቤቶች ለዕንቅፋት ድንጋይና ለማሰናከያ ዓለት በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ለወጥመድና ለአሸክላ ይሆናል ብዙዎችም በእርሱ ይሰነካከላሉ ይወድቃሉም ይሰበሩማል ይያዝማል›› ኢሳ 8፡13-14
በቅዱሳት መጻሕፍት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአብ የባሕሪ ልጅ መሆኑ ተገልል፡፡ ክብር ምስጋና ይግባውና አማኑኤል ፈጣሪያችን በባሕረ ዮርዳኖስ በፍጡሩ በዮሐንስ እጅ ሲጠመቅ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በጌታችን ራስ ላይ ተቀምጧል፡፡ እግዚአብሔር አብም በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው በማለት ድምጹን አሰምቷል፡፡ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል መውረዱ አብ ድምጽ ማሰማቱ ጌታችን መጠመቁ ምስጢረ ስላሴን ያመለክታል ከእመቤታችን ስጋንና ነፍስን ነስቶ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት የተገለጠው መድኃኔዓለም እንደ አብና መንፈስ ቅዱስ የሚሰግዱለት አምላክ መሆኑን እንማራለን፡፡
መናፍቃን መድኃኒታችን በዮርዳኖስ መንፈስ ቅዱስን ባይሞላ ኖሮ ሰይጣንን ድል ለመንሳት ባልቻለ ነበር ይላሉ ይህ ግን ፍጹም ከእውነት የራቀ ስህተት ከመሆኑም ባሻገር ክህደት ነው ፣ ጌታችን በዮርዳኖስ የተጠመቀበት ዓላማ ምስጢሩ ሰፊ ቢሆንም ዋናው ግን ዲያብሎስ አስቀምጦት የነበረውን የዕዳ ደብዳቤ ለመደምሰስ፣ በጥምቀቱ ጥምቀታችን ሊባርክልንና ለጥምቀታችን ኃይል ሊሰጥ ነው፡፡
በመንፈስ ቅዱስ ከብሯል ከተባለ ግን ጌታችን የፀጋ አምላክ ነው ማለት ነው፣ ይህ ደግሞ ምንፍቅናና ክህደት ነው፡፡
ከእናታቸው ማህፀን የተመረጡ እነ ኤርሚያስና መጥምቀ መለኮት ዮሐንስም ዓለምን ለማዳን አልቻሉም፡፡ ነቢያትም ሁሉ ጽድቃችን እንደ መርገም ጨርቅ ሆነ ሲሉ ነው የተናገሩት ደግሞስ ስለቅዱስ ዮሐንስ ልደት ለማብሰር የተላከው መላዕክ ቅዱስ ገብርኤል ገና በእናቱ ማህፀን ሳለ መንፈስ ቅዱስ ይሞላበታል ብሏል፡፡ (ሉቃ 1፡15) ታዲያ ዮሐንስ ስለምን ጌታችንን ከማጥመቁ በፊት እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል አንተም ወደ እኔ ትመጣለህን? (ማቴ 3፡2) በማለት ስለምን ተናገረ? ፈጣሪው መሆኑን ስለተረዳ አይደለም? ነው፡፡ በቀደሙት በአበው ሊቃውንት ቃል አማኑኤል በጥምቀት ከብሯል የሚሉ ከቅድስት ቤተክርስቲያን የተለዩ ናቸው ተስፋ ገነትና መንግስተ ሰማያትም የላቸውም፣ ፈጣሪያቸውን ፍጡር ብለውታልና፡፡
እግዚአብሔር አብ የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት ሲል ስለጌታችን መናገሩ የአማኑኤልን ባሕሪ አምላክነት ያረጋግጣል ጌታችን የፀጋ ልጅ ቢሆንም ድምጹ ዮሐንስንም ጨምሮ የምወዳቸውን ልጆቼን ስሟቸው የሚል ይሆን እንደነበር አያከራክርም በነገው ዮሐንስ ጌታ ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ ‹‹እነሆ የዓለምን ኃጢዓት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ›› (ዮሐ 1፡29) ለመሆኑ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የፀጋ ልጅ ወይስ የባሕሪ ልጅ? መድኃኒዓለም ክርስቶስ በእውነት የባሕሪ አምላክ መሆኑን እንመን፡፡
ቅዱስ ቄርሎስ ዕልው ንስጥሮስን ከገሰጸበት በ 5ኛው አንቀጽ ‹‹አለቆች በጉባኤያችን መካከል መሪር ነገርን ልንናገር አይገባም የልቡና ድንቁርና እግዚአብሔር ቃል በሕማም በሞት እንደተያዘ፣ በመለኮቱ መከራን እንደታገሰ እንደታመመ የሚናገር፣ ባማረ በቀና ትምህርት ጸንተን መልኮቱ እንዳልታመመ በሥጋ እንደታመመ እናውቃለን ሰማዕታት ፍጹማን ሆነው መከራን በተቀበሉ ጊዜ፣ ሃይማኖትን በጠበቁ ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ደስ የሚያሰኘውን ክብር ባገኙ ጊዜ በክብር ፍጹማን እንደሆኑ እንናገራለን፡፡ ዛሬም ከእኛ ጋራ አንድ ሰው መከራከርን ቢጀምር የቅዱሳን ሥጋቸው በሰይፍ በተቆረጠ ጊዜ በእሳት ባቃጠሏቸው ጊዜ ይዘው በሰንሰለት ባሠሯቸው ጊዜ በእውኑ የነሱ ነፍሳት ከሥጋ ጋር ይህን መከራ ይቀበላሉ? ዳግመኛም ነፍሳትም በእሳት ተቃጠሉ፣ በሰይፍ ተቆረጡ ብሎ ቢከራከረን፣ እኛ ግን የነሱን ነገር እንናገራለን ከሥጋ ሕማም እንደማይወጡ ይህን ሁሉ መከራ ገንዘብ እንዲያደርጉ እንናገራለን ዳግመኛም እንዲህ ብሎ ቢመልስልን በባሕሪያቸው መከራን ካልተቀበሉ የስጋን መከራ ስላልተቀበሉ ክብር አያገኙም ብሎ ቢከራከረን፣ እኛም እውነት ነገርን እንናገራለን፣ ከታመመ ከሥጋ ሕመም እናውጣቸው? ብለን እንመለስለታለን ሥጋ የሌላ አካል አይደለም የነሱ አካል ነው እንጂ›› የፀጋ ልጆች የሚባሉት አማላጆች ናቸው፡፡ እነርሱም የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ልጆች ፍጡራን ናቸው፡፡
ክቡር የሚሆን ዮሐንስ አፈወርቅ ዳግመኛ በድርሳኑ እንዲህ አለ ለኛ የተደረገውን ክብር አይተው ለራሳቸው እንደተደረገ አድርገው ደስ እንዳላቸው አወቅህን ወደ ሰማይ ሲያርግ ባዩትም ጊዜ ፈጽሞ ደስ እንዳላቸው፣ አመሰገኑም አብረውትም ወደ ሰማይ አረጉ ስለዚህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካረገበት ቀን ጀምሮ ያዕቆብ ያየው ራዕይ እውነት ሆነ መላዕክት ወደ አብ ሲወጡ ሲወርዱ ያየው ከዛሬ አስቀድሞ መላዕክት ያዩት ዘንድ ይመኙት የነበረ እንግዳ ራዕይ ይህ ነው፡፡
እነሆ ዛሬ አዩት እንደኛ ያለ ሩቅ ብዕሲ አይደለም  ከሰው ባሕሪ የራቀ ነው እንጂ ስለዚህ አካላዊ ቃል ነፍስና ሥጋን ነስቶ እንደተዋሐደ እናምናለን አንደኛ ሰው ሆነ በመለኮት ሞትን ድል የነሣ እሱ ነው እንደተፃፈ ዳግመኛ በሰውነቱ ሊቀካህናት ሆነ በተዋሐደው በሥጋ መስዋዕት እሱ ነው በአምላክነቱ መስዋዕትን ያቀርቡለታል እንደ ጌትነቱ ሥልጣን ኃጢዓትን የሚያስተሰርይ እሱ ነው እንኪያስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ አካል አንድ ባሕሪ ነው ሥጋን ስለተዋሃደ በሊቀ ካህናትነቱ ለአብ ሰገደም ብንል፣ ወዲህም በአምላክነቱ ፍጥረት ሁሉ ይሰግዱለታል በጌትነቱ ዙፋን ይኖራል፡፡ መላዕክትም በዙሪያው ይቆማሉ በጊዜው ሁሉ ኃይላት ሊቃናት ያመሰግኑታል መኳንንትም እግዚእ ይሉታል፡፡
ስለዚህ ሰማዕታትና መላዕክት ቅዱሳን የሚገዙለትን አማላጅ ማለት ታላቅ ክህደት መሆኑን እንገነዘባለን ጌታችን ለቤዛ ዓለም ሲል በመሞቱ እንኳን ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ከመላዕክትም አንሷል ተብሎ ተጽፋል ምክንያቱም መላዕክት አይሞቱምና ‹‹ከመላዕክት ይልቅ ጥቂት አንሶ የነበረውን ኢየሱስን ከሞት መከራ የተነሣ የክብርና የምስጋና ዘውድ ተጭኖ እናየዋለን›› ዕብ 2፡9
ቅዱሳን መላዕክትን የፈጠራቸው አማኑኤል አምላካችን ነው፡፡ እንግዲህ መላዕክት አይበሉም አይጠጡም፣ አይታመሙም፣ አይሞቱም፣ ድካምን አያውቁም ጌታችን ግን እኛን ለማዳን ሲል ሥጋን ተዋህዶ ተገልጦአልና በህማሙ ኃጢዓታችንን ሊያስወግድልን ታመመ፣ ከሞት ሊያድነነን ሞተልን፡፡ እንግዲህ ከዚህ በላይ በገለጥነው አገልግሎቱ በመሞቱም ጭምር ከመላዕክት አንሶአልና ፍጡር ነው ካልነው እንሳሳታለን፡፡
‹‹ተቀዳሚና ተከታይ ቀኝና ግራ የለብንም፣ ጠፈር የለብንም መሠረትም የለብንም ጠፈርም መሠረትም እኛው ነን እንግዲህ የቃል ሥጋ መሆን ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ አያሳንሰውም፡፡ ምሳሌውም ቃል ከልብ ተገኝቶ በልብ ህልው ሆኖ ሲኖር ልገለጽ ባለ ጊዜ ባንደበት እንዲገለጽ ቃለ እግዚአብሔርም በዓመተ ምህረት ስለ ቤዛ ዓለም በሥጋ ተገልጦ ታይቷል››
ቅዱሳን ሐዋርያትም ስለ አካላዊ ቃል ሲገልጡ የማያከራክር ምስክርነት ሰጥተዋል እግዚአብሔርን የመምሰል ምስጢር ያለጥርጥር ታላቅ ነው፡፡ በሥጋ የተገለጠ ፣ በመንፈስ የጸደቀ ፣ ለመላዕክት የታየ ፣ በአሕዛብ የተሰበከ በዓለም የታመነ ፣ በክብር ያረገ በማለት ጽፈዋል፡፡ 1ጢሞ 3፡16
እንግዲህ ከእመቤታችን የተወለደ አካላዊ ቃል አንድ እግዚአብሔር በማለት ከምንጠራቸው ከሦስቱ አካላት አንዱ መሆኑን በጉልህ እንረዳለን፡፡ ከደቀመዛሙርት አንዱ የሆነው ፊሊጶስም ጌታ ሆይ አብን አሳየንና ይበቃናል ‹‹በማለት መድኃኒዓለምን ቢጠይቀው እጅግ አስደናቂ ምላሽ ተሰጠው›› አንተ ፊሊጶስ ይህን ያህል ዘመን ከአንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አየ ብሎታል፡፡ (ዮሐ 14፡8-10)
ስለዚህ ወልድ አብን በመልክ ይመስለዋል በባሕሪይም ይስተካከለዋል ‹‹እኔና አብ አንድ ነን›› ብሏልና :ከአብ ጋር አንድ ከሆነ የባሕሪ አምላክ ነውና የፀጋ አምላክ አማላጅ የሚሉት ምላሽ የላቸውምና ይፈሩ፣ ቅዱስ ጳውሎስም የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በአባታዊ ምዕዳኑ ሲሰናበት አማኑኤል እንደ አብና መንፈስ ቅዱስ አምላክ መሆኑን ገልጧል፡፡ የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ህብረት ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን (2ቆሮ 13፡14)
በመሆኑም ስለ ቤዛዓለም በቀራኒዮ ኮረብታ የተሰዋው ከሦስቱ አካላት አንዱ የሆነው አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ አይደለምን? ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስም የሐዋርያትን ሥራ በጻፈበት (ሐዋ 20፡28) ላይ ‹‹እግዚአብሔር በገዛ ደሙ የዋጃትን ቤተክርስቲያን…›› በማለት ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር መሆኑን መስክሯል፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔርነት የባሕሪ ገንዘቡ የሆነውን ጌታ ክርስቶስ የጸጋ ልጅ አማላጅ የሚሉት ምን ያህል እንደተሳሳቱ በአንክሮ እንመለከታለን፡፡
ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊትም ስለእርገተ ክርስቶስ ሲመሰክር ‹‹እግዚአብሔር በመለከት ድምጽ አረገ›› (መዝ 46(47) ፡5) ነው ያለው ፡፡ እግዚአብሔር ያለው ከሶስቱ ቅዱስ አንዱን አካላዊ ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስን ነው ቅዱስ ኤጴፍንዮስ በሃይማኖተ አበው የባሕሪ አምላክ አብን በተለየ አካሉ አንድ እንደሆነ እናውቃለን የባሕሪ አምላክ ወልድን በተለየ አካሉ አንድ እንደሆነ እናውቃለን የባሕሪ አማላክ መንፈስ ቅዱስንም በተለየ አካሉ አንድ እንደሆነ እናውቃለን እንኚ ሦስቱ አካላት የተፈጠሩ አይደሉም፣ በዚህ ጊዜ ተገኙ በዚህ ጊዜ ያልፋሉ መባል የለባቸውም፣ አይለወጡም አይናወጡም፡፡ ቅዱስ ጎርጎርዮስም ከቅ/ኤጱፍንዮስ ጋር ይተባበራል፡፡ ‹‹ሳናቋርጥ የሦስቱን ምስጋና አንድነት እንናገራለን ፍጹም አሸናፊ አንድ አምላክ እግዚአብሔር አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ሆይ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ ተብለህ የምትመሰገነው ምስጋናህ በሰማይ በምድር ምሉዕ ነው›› በማለት ሃይማኖታዊ ምስክርነቱ ይገለጻል፡፡
እንግዲህ ምን እንላለን ሁሉን እንዳንተርክ ጊዜ ያጥርብናል ‹‹ነገር ግን አናፂዎች የናቁት እርሱ ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ›› ዮሐ 6፡51 በማለት እየነገረን፣ የዛሬዎች አናጺዎች የመናፍቃን መምህራን ነን ባዮች የጸጋ አምላክ አማላጅ ቢሉት ትልቅ ስህተትና ክህደት እየፈጸሙ ነውና በኋላ በግርማ መንግስቱ በአሰፈሪ ሁኔታ ከዕልፍ አዕላፍ ቅዱሳት ጋር ሲመጣ ማጣፍያው ያጥርባቸዋል መግቢያ ቀዳዳው ይጠፋቸዋል ምክንያቱም ራሱ ባለቤቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹በዚህ ድንጋይ (ዓለት) ላይ የሚወድቅ ሁሉ ይቀጠቀጣል፣ ድንጋዩ ግን የሚወድቅበትን ሁሉ ይፈጨዋል፡፡›› (ማቴ 21፡44) ከላይም ሆነ ከታች ድንጋይ ሁል ጊዜ ሰባሪ ነውና፣ ለጊዜው ይሁዳ በዕለተ አርብ በዚህ ዓለት በክርስቶስ ላይ በጠላትነት ቢነሣበት ይቀጠቀጣል ይጠፋል፣ በሌላው ጻሕፍት ፈሪሳውያን አይሁድ የክርስቶስን ደም እንዳፈሰሱ የእነርሱም ደም በጥጦስ ዘመን ፈስሶ ብዙዎች ተቀጥቅጠዋል፣ እንዲሁም በመጨረሻው ዕለት በምጽዓት ጊዜ በመለኮታዊ ክብሩ በማርያም ስጋ (በክበበ ትሰብዕት) ፣ በይባቤ መላእክት በግርማ መለኮት ሲገለጽ የዮሴፍ ልጅ፣ የጸጋ አምላክ አማላጅ በማለት የተሰናከሉበት በዚህ ዓለት ላይ የወደቁ ሁሉ ይቀጠቀጣሉ፡፡ ‹‹እጅም ሳይነካው ድንጋይ ከተራራው ተፈንቅሎ ከብረትና ከሸክላ የሆነውን የምስሉን እግሮች ሲመታና ሲፈጭ አየሁ›› (ዳን 2፡34) እንዲል ነቢዩ ዳንኤል ይህ ዓለት (ድንጋይ) ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ቅዱስ አባ ኤፍሬም በማክሰኞ ውዳሴ ማርያም ቁጥር 12 ላይ ‹‹ነቢዩ ዳንኤል ያየው ያለ እጅ ከረዥም ተራራ የተፈነቀለው ያ ድንጋይ ከአብ ዘንድ የወጣው አካላዊ ቃል ነውና መጥቶ ያለ ወንድ ዘር ከድንግል ተወልዶ አዳነን›› በማለት አመስግኖታል እጅ ሳይነካው ማለቱ ማንም ሳያስገድደው በአባቱ ፈቃድ በራሱ ፈቃድ በመንፈስ ቅዱስም ፈቃድ ከሰማየ ሰማያት የወረደው እግዚአብሔር ቃል ወልድ ነው፡፡ ከብረትና ከሸክላ የሆነውን ምስሉን ቀጠቀጠው፡፡
ዛሬም እያዩ የማያዩ የማያስተውሉ ብዙ ናቸው አማላጅ የሚሉ ለማኝ የሚሉ ከአብ ሥር እየወደቀ እየተነሣ ይቃትታል የሚሉ፣ እነዚህን ‹‹የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል›› 2ኛ ጢሞ 3፡5 እናም ‹‹በመጨረሻቸው ጥፋት ሆዳቸው አምላካቸው ክብራቸው በነውራቸው አሳባቸው ምድራዊ ነው›› (ፈሊጵ 3፡19) እናንተ ግን ልዩ ልዩ በሆነ እንግዳ ትምህርት አትወሰዱ ኢየሱስ ክርስቶስ ትላንትና ዛሬ እስከዘላለሙ ያው ነውና ዕብ 13፡8 ‹‹እርሱም እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው›› (1ኛ ዮሐ 5፡20-21)
ወደዚህ ደግሞ ወደ እውነተኛው አምላክ ወደ ልጁ ወደ ጌታችን ወደ ኢየሰሱ ክርስቶስ ኅብረት የጠራን እግዚአብሔር ያታመነ ነው (1ኛ ቆሮ 1፡9)
እግዚአብሔር እንዳይጠማ እንዳይራብ እንዳይታመም እንዳይሞት እናውቃለን ነገር ግን ስለ እኛ ብሎ በገዛ ፈቃዱ መከራ መስቀልን ተቀብሎ ነፍሱን ከሥጋው በመለየት በከበረ ደሙ ፈሳሽነት ከአስፈሪው የሲኦል መከራ አዳነን፡፡
ስለዚህ የባሕሪ አምላክ እያልን እንመንበት

No comments:

Post a Comment