Thursday, February 27, 2014

‹‹ዓብይ ጾም›› ክፍል ሁለት (2)






የዓብይ ጾም ስያሜዎችና ለምን 55 ቀን እንደሚጾም
ባለፈው ጽሑፋችን ለማየት እንደጀመርነው የዓቢይ ጾም ከሕግ-አጽዋማት መካከል አንዱ ሲሆን ይህንን ጾም የምንጾመውም ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስን አርአያ፣ አብነት አድርገን ነው፡፡
ነገር ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው 40 ቀንና 40 ሌሊት ብቻ ነው፤ በቤተክርስቲያናችን ግን አበው ቀኖና ሰርተው እንድንጾም የወሰኑት 55 ቀን ነው፡፡ ይህ እንደምን ነው ቢሉ ስለ ሁለት ነገር ነው፡፡





1.  አንድም ክርስቶስ 40 ቀናት የጾመው ከቆመ ሳይቀመጥ፣ ከዘረጋ ሳያጥፍ ፣ እህል ውሃ ሳይቀምስ በመሆኑ እኛም እህል ውሃ የሚበላባቸውን በ55ቱ ቀን ያሉትን ቅዳሜና እሁድን ብንቀንሳቸው 40 ቀናት ከእህል ከውሃ፣ ከጥሉላት የሚጾምባቸው ፍጹም ሱባዔ ይሆናልና ነው፡፡
2.  በሌላው ከ40ኛው ቀናት ፊትና ኋላ ያሉትን ሁለቱን ሳምንታት ከፍ ሲል አበው ሐዋርያት ዝቅ ሲል ሃይማኖታቸው የቀና፣ ርቱዓነ ሃይማኖት 318ቱ ሊቃውንት ከዚያም በኋላ የተነሱ አበው ሊቃውንት ከ40ው ጾም ጋር አብሮ እንዲጾም ሕግ ስለሰሩ ነው፡፡
ሀ/ የመጀመሪያው ሳምንት (ከ40ው ቀን በፊት) ያለው እንዲጾም የተወሰነበት ወይም የሚጾምበት ምክንያት ‹‹ፎቃ የተባለ ንጉሥ አገዛዝ አጽንቶባቸው በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ምዕመናን ህርቃል እንዲረዳቸው በጠየቁት ጊዜ ለመርዳት ፈቃደኛ ቢሆንም ሐዋርያት ሰው የገደለ ሰው ዕድሜውን ሙሉ እንዲጾም ስለወሰኑ በጉዳዩ የሚቸገርበት መሆኑን ገለጸላቸው ሕዝቡም የአንድ ሰው ዕድሜ ሰባ፣ ሰማንያ ነው እኛ እንጾምልሀለን ዘምተህ ጠላቶቻችንን አስወግድልን ስላሉት ቃላቸውን ተቀብሎ ችግራቸውን አስወግዶላቸዋል እነርሱም አምስት አምስቱን ቀን ተካፍለው ጾመውለታል›› ያላወቁት ምዕመናኑ ወይም ሕዝበ ክርስቲያኑ አንድ ጊዜ፣ ያወቁት የተረዱት ከምስጢር ባለጸጋ የሆኑት አበው ሐዋርያት ጹሙ ብለው ሥርዓት አድርገው በየዓመቱ የሚጾሙት ሆነዋል፡፡ አበው ሐዋርያት ከትምህርተ ወንጌል ሥምሪት አስቀድሞ አምስት አምስት ቀን የመጾም ልማድ እንደነበራቸውም ታውቋል፡፡
ለ/ ሌላው ከ40ው ቀን በኋላ ከሆሣእና እስከ ትንሣኤ ያለው ሳምንት ሰሞነ ሕማማት ነው፡፡ በሕማማት ሰሞን የዓለም መድኅን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ደኅንነት ሕማም መከራ የተቀበለበት በመስቀልም የሞትን ጽዋ ተቀብሎ ለሞት ኃጢዓት ከመገዛት ነጻ ያደረገን ስለሆነ ህማሙን፣ ምክረ ሞቱን ለኛ ሲል የተቀበለውን ፀዋትወ መከራ በጾም በፀሎት በሰጊድ በኀዘን ለማሰብ በቤተክርስቲያን አበው የተወሰነ በመሆኑ ማንኛውም ክርስቲያን ‹‹ጾም በእናንተ ዘንድ የከበረ ይሁን›› ብለው የዓለም ብርሃናት ብፁዓን ሐዋርያት በዲድስቅልያቸው (አንቀጽ 29) በወሰኑት መሠረት ከጥሉላት መባልዕት ሥጋ፣ ቅቤ፣ ወተት፣ ዓሣ ተከልክሎ ከ40ው ቀን ጋር አንድ ላይ ይህን ጾምም ሆነ ሌሎች አጽዋማትን እንዲከታተል ግዴታ አለበት፡፡
የዓቢይ ጾም ስያሜዎች
የተቆጠረው ሱባዔ የተነገረው ትንቢት ሲፈጸም በዘመን ፍጻሜ ወልደ እግዚአብሔር ከሰማየ ሰማያት ወረደ፣ ቃል ሥጋ ሆነ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወሰነ በግዕዘ-ሕፃናት ተመላልሶ በየጥቂቱ አደገ፣ የሕግ ባለቤት ሆኖ ከሕግ በታች ሆኖ ተመላለሰ እርሱ በእሳትና በውሃ የሚያጠምቅ መለኮት ሆኖ ሳለ በፍጡሩ በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ፣ ሳያውል ሳያድር ወደ ገዳመ ቆሮንጦስ በመሄድ (በመግባት) ከዘረጋ ሳያጥፍ ከቆመ ሳይቀመጥ እህል ውሃ ሳይቀምስ 40 ቀንና 40 ሌሊት ጾመ ከዚህም የተነሣ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን የዓቢይ ጾምን በተለያየ ስያሜ ይጠሩታል፡-
1.  የአስተምህሮ ጾም
ቀድሞ በነቢዩ በኢሳይያስ ‹‹ታዳጊህ የእስራኤል ቅዱስ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል እኔ የሚረባህን ነገር የማስተምርህ በምትሄድባትም መንገድ የምመራህ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ›› (ኢሳ 48፡17) ተብሎ እንደተጻፈ እንደ እግዚአብሔር ያለ ግሩም መምህር የለምና አምላችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው አስተምሯል ይህንን ሲያደርግ ግን ጌታችን እርሱ ሳይሰራ ሥሩ አላለም፡፡ አበው በምሳሌ ‹‹ባልዋጁበት ጣት የዘንዶ ጉርጋድ ይለኩበት›› እንዲሉ እርሱ በቃል ያስተማረውን በተግባር ፈጽሟል፡-
ሀ/ ጥምቀትን በዮሐንስ እጅ ራሱን ዝቅ አድርጎ በትህትና ተጠምቋል
ለ/ ከማያምኑ ከኀጥአን ጋር አንድ ሆኖ ተቆጥሯል
ሐ/ ከጲላጦስ ፊት ቆሞ እውነትን መስክሯል
መ/ 40 ቀንና 40 ሌሊት ከቆመ ሳይቀመጥ ፣ ከዘረጋ ሳያጥፍ ጾመ ጸለየ
ሠ/ በብሕትውና በድንግልና ኖረ (ለመነኮሳት ለባሕታውያን አብነት ይሆን ዘንድ)
በሌላው፡- 1/ ምጡቅ ረቂቅ እንደሆነ ለማጠየቅም በኀቱም ድንግልና ተፀንሶ በኀቱም ድንግልና ተወለደ
  2/ ረኀብን የማይራብ እንደሆነ ለማጠየቅ 40 መዓልት 40 ሌሊት ጾመ (ማቴ 4)
  3/ የማይደፈር የማይገሠሥ እንደሆነ ለማጠየቅ በባሕር ላይ ተጓዘ
  4/ የብርሃናት ብርሃን እንደሆነ ለማጠየቅ ብርሃነ መለኮትን በደብረ ታቦር ገለጸ (ማቴ 17፡1)
  5/ የሕያዋን ሁሉ ሕይወት እንደሆነ ለማጠየቅ የአራት ቀን ሬሳ አልዓዛርን አስነሣ (ዮሐ 11፡43)
‹‹አቤቱ አንተ የገሰጽኸው ሕግህንም ያስተማርከው ሰው ምስጉን ነው›› (መዝ 94፡13) እንዲል ልበ አምላክ ዳዊት እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ያስተምረን፡፡
2. የሥራ መጀመሪያ ጾም
ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችንና አምላካችን መድኀኒታችንም ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉን ነገር ከማድረጉ በፊት ለማስተማርም ከመጀመሩ በፊት፣ ለሥራ ከመነሣቱ በፊት፣ ተአምራትንም ከማድረጉ በፊት አርባ መዓልት እና አርባ ሌሊት ጾሞ እናንተም የሥራችሁ መጀመሪያ ጾም ጸሎት ይሁን ሲል አብነት አርአያ በመሆኑ ከዚያ በኋላ ቅዱሳን ሐዋርያትም የሥራቸው መጀመሪያ ያደረጉት ጾም ጸሎትን ነበረ (ሐዋ 13፡1) ከዚህም የተነሣ ይህ ጾም የሥራ መጀመሪያ ጾም ተብላል፡፡
3.  የካሣ ጾም






ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኃጢዓት ምክንያት በአዳም ላይ የተፈረደበትን ሞት ለማስቀረት በነፍሱ ተወራርዶ ለአዳም ፍጹም ካሣን ከፈለ ነገር ግን ካሣ ከፋዩ ነፍሱን ሰጥቶ ካሣ ከፍሎ አዳምን ለመታደግ የተወሰኑ ነገሮችን ማሟላት ነበረበት፣ እነዚህን መስፈርቶች ደግሞ አሟልቶ የተገኘው የድንግል ማርያም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነበረ፡፡
ሀ/ ካሣ ከፋዩ ሰውን የሚወክል ሰው መሆን ነበረበት በመሆኑም ቃል ጸጋንና እውነትን ተመልቶ በእኛ አደረ መለኮት ከሥጋ በተዋህዶ ከበረ፡፡
ለ/ ‹‹የኀጢዓት ደመወዝ ሞት ነው›› (ሮሜ 6፡23) ተብሎ እንደተጻፈ ካሣ ከፋዩ መሞት ነበረበት በመሆኑም ‹‹መጽሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ስለ ኀጢዓተኞች ሞተ፣ ተቀበረም በሦስተኛም ቀን ተነስቷል›› 1ቆሮ 15፡3
ሐ/ ነውር ያለበት፣ እንከን የተገኘበት ሌላውን መታደግ አይችልምና ካሣ ከፋዩ ኀጢዓት የሌለበት ንጹሐ ባሕርይ መሆን አለበት አለበለዚያ ግን ኀጢዓት ያለበት ለራሱም መድኀኒትን ይሻልና፡፡
‹‹እርሱም ኀጢዓትን ሊያስወግድ እንደተገለጠ ታውቃላችሁ በእርሱም ኀጢዓት የለም›› (1ዮሐ 3፡5)
መ/ ካሣ ከፋዩ አምላክ መሆን አለበት ለምን ኀጥአንን ከሲኦል ማውጣት ብቻ ሳይሆን የረከሰውን የሰውን ልጅ ሥጋ መቀደስ ነበረበትና››
ሠ/ ኀጢዓት በመብል ምክንያት ወደ ዓለም ስለገባ ካሣ ከፋዩ (ኢየሱስ ክርስቶስ) ካሣን ይከፍል ዘነድ ስለ አዳምና ስለ ሔዋን ተገብቶ 40 ቀንና 40 ሌሊት መጾም ነበረበት (ዘፍ 2፡16)
ከዚህም የተነሣ ይህ ጾም የካሣ ጾም ተብሏል
4. የመሸጋገሪያ ጾም
አስቀድሞ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ሕዝቡን ከሕገ-ልቡና ወደ ሕገ-ኦሪት ለመመለስ ፣ ለማሸጋገር አስርቱ ትዕዛዛት የተጻፈበትን ጸላት ከመቀበሉ በፊት አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ጾሞ ነበር፡፡
‹‹በዚያም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ እንጀራም አልበላ ውሃም አልጠጣም›› ዘጻ 34፡28 ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እኛን ከሕገ-ኦሪት ወደ ሕገ-ወንጌል ከጨለማ ወደ ብርሃን ፣ ከሞት ወደ ሕይወት ያሸጋግረን ዘንድ 40 ቀንና 40 ሌሊት የጾመው ጾም በመሆኑ የመሸጋገሪያ ጾም ተብሏል፡፡


5. የቀድስተ ገዳም ጾም
የቀደሙት አበው እነ መልከጼዴቅ ሔኖክ በብሕትውና የኖሩትን ኑሮ ጌታችንና አምላካችን ክርስቶስ ቀድሶታል ባርኮታል እንዴት ቢሉ በዮሐንስ እጅ ከተጠመቀ በኋላ ሳይውል ሳያድር ወደ ገዳመ ቆሮንጦስ ሄዶ 40 ቀንና 40 ሌሊት ጾመ፣ ይህንም የአደረገው ከዚያም በኋላ የሚነሱ አበው በብሕትውና ተወስነው በምንኩስና ጸንተው በገዳም ቢጾሙ ቢጸልዩ ብዙ በረከት እንዳለውና ከራስ አልፎ ለሀገር ለወገን እንደሚተርፉ ለማስተማር አብነት አርአያ ለመሆን፣
‹‹እነርሱ ግን ዓለምን ንቀው በእግዚአብሔር ፍቅር ተሸንፈው ግርማ ሌሊቱን ድምፀ-አራዊቱን ታግሰው በዱር በገደል በዋሻ ተንከራተቱ›› (ዕብ 11፡33-38) እንዲል የጽድቅ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ በጾሙ ገዳማትን የባረከበት የቀደሰበት በመሆኑ ይህ ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡



6. የድል ጾም
የዓለም መድኅን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቆሮንቶስ ገዳም ጾሞ የዓለምን ተፈታታኝ ክፉ መንፈስ ከነፈተናው ድል ነስቶታል በዚህ ጾም ሶስት ታላላቅ የኅጢዓት አበጋዞች (አርእስተ ኃጣውዕ) ስስት፣ ትዕቢት ፍቅረ ንዋይ ድል ተነስተውበታል፡፡
ሀ/ ስስት
‹‹ከዚህ በኋላ ተራበ ‹‹የሁሉ ዓይን አንተን ተስፋ ያደርጋል አንተም ምግባቸውን ትሰጣቸዋለህ›› (መዝ 144፡15) ተብሎ የተጻፈለት የእግዚአብሔር ልጅ እግዚአብሔር በፈቃዱ ተራበ፣ በለበሰው ሥጋ ተራበ እንጂ መለኮትስ አይራብም፣ በኀጢዓት የጎሰቆለውን ሰው ልጆችን ሥጋ ያጸድቅ ዘንድ ተራበ፣ በዚህን ጊዜ የሚፈታተነው ዲያብሎስ ሩቅ ብዕሲ መስሎት ወደ እሱ ቀረበ ‹‹አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ ይህን ድንጋይ ዳቦ አድርገው›› ብሎ ፈተነው (ማቴ 4፡4)
ጌታችን ኢየሱስ ግን ‹‹ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም›› ተብሎ ተጽፏል በማለት ቀድሞ በሙሴ በኩል በ (ዘዳ 8፡3) ላይ ለእስራኤል ልጆች የተሰጠውን ትምህርት አስተማረው (ማቴ 4፡4) በስስት ሲመጣበት በትዕግስትም መለሰው ድልም አደረገው፡፡
ለ/ ትዕቢት
እንደገናም በትዕቢት ይፈትነው ዘንድ ወደ ቅድስት ሀገር ወደ ኢየሩሳሌም ወስደው፡ ካህናትን ድል ነስቼ በት በማላውቀው በገዳም ቢሆን ነው እንጂ ያላሸነፍኩት ብሎ፣ ካህናትን ድል በምነሳበት በቤተመቅደስ ቢሆን መች ድል ይነሳኝ ነበር ብሎ ለፈተና ተዘጋጀ ጌታም እንጂ በፈቃዱ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ፣ ዲያብሎስም አምሞ ጠምጥሞ በአምሳለ ሊቀ ካህናት መነሳንስ ይዞ ቀረበውና ‹‹በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ መላዕክቱን ስለአንተ ያዝዝልሃልና እግርህንም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሱሃል ተብሎ ተጽፏልና ወደ ታች ራስህን ወርውር ከዚህ ዘለህ ውረድ›› ብሎ ፈተነው ተፈታተነው ጌታችን ክርስቶስም ‹‹ጌታ አምላክህን አትፈታተነው ተብሎ ተጽፏል›› ብሎ ቀድሞ በሙሴ በኩል በ (ዘዳ 6፡16) ላይ የተሰጠውን ትምህርት አስተማረው በትዕቢት ሲመጣበትም በትህትና መለሰው ድልም አደረገው፡፡
ሐ/ ፍቅረ ንዋይ
ከዚህ በኋላ በፍቅረ ንዋይ ይፈትነው ዘንድ ወደ ረጅም ተራራ አወጣው፣ ነገስታትን ድል በማልነሳበት በቤተመቅደስ ቢሆን ድል ነሳኝ እንጂ ነገስታትን ድል በምነሳበት በተራራ ቢሆን መች ድል ይነሳኝ ነበር ብሎ በማሰብ ወደ ተራራ ይዞት ወጣ፣ የዓለምን መንግስት ሁሉ አሳየው፣ ጠጠሩን ወርቅ ብር፣ ቅጠሉን ደግሞ ግምጃ አስመስሎ አሳየው (ሉቃ 4፡5) ዲያብሎስ ይህን ሁሉ ካሳየው በኋላ ደፋር ነውና ‹‹ብትሰግድልኝ እጅ ብትነሳኝ ይህን ሁሉ እሰጥሀለሁ አለው›› (ማቴ 4፡9) ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ‹‹ሂድ አንተ ሰይጣን ለጌታ ለአምላክህ ስገድ እርሱን ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፏል በማለት በሊቀነቢያት በሙሴ የተጻፈውን ቃል ጠቅሶ አስተማረው፡፡ (ዘዳ 5፡7-10፣ ዘዳ 7) በፍቅረ ንዋይ ይፈትነው ዘንድ ቢመጣበት በጸሊዓ ንዋይ መለሰው ድልም ነሳው፡፡
ከዚህም የተነሳ ይህ ጾም የድል ጾም ተብሏል፡፡
7. ጾመ ሁዳዴ
ሁዳዴ ሁዳድ ከሚለው ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም ሰፊ የእርሻ መሬት፣ ወይም ሰፊ ርስት ማለት ነው፡፡ በመሆኑም በጥንት ጊዜ ገባሮች ለባለርስቶች የማያገቡት የሚያርሱት መሬት ሁዳድ ተብሎ ይጠራ ነበር፡፡ የርስቱ ባለቤት የሁላችን ባለቤትና ጌታ የሁላችን ሰሪ እግዚአብሔር ነው እኛም ደግሞ ለእግዚአብሔር በፍርሃት እየተገዛን በትህትና በትጋት የምንጾመው ጾም በመሆኑ ጾመ ሁዳዴ ተብሏል፡፡
በሌላው ይህ ጾም ካህን ምዕመን፣ ባለጠጋ ደሃ፣ ነጭ ጥቁር፣ ታላቅ ታናሽ ሳይል ሁሉ ይጸመዋል፤ ሁሉ የእርሱ ፍጥረት ነውና፡፡
‹‹እጆችህ ሰሩኝ አበጃጁኝ እንዳስተውል አድርገኝ›› እንዲል ቅድስ ዳዊት (መዝ 118፡73) ሁላችን የፈጠረን በእጆቹ ያበጃጀን በመዳፉ የቀረፀን እርሱ ነውና ለእግዚአብሔር በፍርሃት እንገዛ፣ በቅድስና ሆነንም ይህን ጾም እንጹም፡፡
‹‹ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ በረዓድም ደስ ይበላችሁ›› (መዝ 2፡11)
8. ዓቢይ ጾም
ዓቢይ ማለት የቃሉ ትርጉም ዋና፣ ትልቅ፣ የሚበልጥ ማለት ነው ሌሎችን ሁሉ አጽዋማት የምንጾመው ከቅዱሳን አበው፣ ነቢያት፣ ሐዋርያት በትውፉት በወረስነው የኑሮአቸው ፍሬ ነው ፡፡ በ ዕብ 13፡7-8 ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ ‹‹የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነት ምሰሉአቸው›› እንዲል ዋኖች የተባሉ አበው ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ ሊቃውንት እምነታቸውን በሥራ የገለፁት ኢየሱስ ክርስቶስ ጻድቅ እንደሆነ እነሱም ጽድቅን በእምነት ያደረጉት ቅዱሳን ጻድቃንን አርአያ አብነት አድርገን የምንጾማቸው ናቸው፡፡ (ያዕ 2፡17 ፣ 1ዮሐ 3፡7)
የዓብይ ጾም ግን ዓብይ ወይም ታላቅ ያሰኘው አንድም በመጾም ቀን ብዛት 55 ቀኖችን በመያዙ፣ እንዲሁም የቅዱሳን ፈጣሪ፣ የሁላችን አባት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነውራችንን ሊያንከባልልን ፣ ኀጢዓታችንን ሊያስወግድ፣ መርገማችንን ሊሽር፣ ከእስራት ሊፈታን፣ አርአያ ምሳሌ ሊሆነን፣ ጸጋችንን መልሶ ሊያለብሰን ፣ የፍቅር ረሃባችንን ሊያጠግብ ከዘረጋ ሳያጥፍ ከቆመ ሳይቀመጥ እህል ውሃ ሳይቀምስ የጾመው ጾም በመሆኑ ነው ፡፡
9. ጾመ አርባ
ምንም እንኳን የቀኖቹ ብዛት 55 ቀን ቢሆኑም ሰባቱ ቅዳሜና ስምንቱ እሁድ አስራ አምሰቱ ቀን ከጥሉላት ብንጾመውም እህል ውሃ ግን ይቀመሳልና፣ ፍጹም የሱባዔ ቀናት 40ው ቀናት ናቸው፡፡ አንድም ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው 40 ቀንና 40 ሌሊት በመሆኑ ጾመ አርባ እየተባለ ይጠራል፡፡
በሌላው የመጀመሪያውና የመጨረሻው ሳምንት በአበው ውሳኔ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን አብሮ እንዲጾም የተወሰነ በመሆኑና የጾሙን ይዘት የማይቀይረው ስለሆነ ጾመ አርባ እየተባለ ይጠራል፡፡
10. የመዘጋጃ ጾም
ቀድሞ እስራኤል በግብፅ ምድር በባርነት በነበሩበት ጊዜ እግዚአብሔር ፈርኦንን በነፃነት ይገዛልኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ ቢለው ፈርኦን ልቡን አደነደነ አሻፈረኝም በማለቱ የእግዚአብሔር እጅ በዘጠኝ ጽኑ ተአምራት በግብፅ ላይ ተገለጠ ፈርኦን ግን አልተመለሰም እግዚአብሔርም እንደገና ሌላ መቅሠፍትን አመጣ ሞተ በኩርን ከፈርኦን ቤት እስከ ተራው ሰው ቤት ድረስ አዘዘ እንዲህም አለ፡-
‹‹እስራኤል የበኩር ልጅ ነው ይገዛልኝ ዘንድ ልጄን ልቀቅ እልሁ አንተም ትለቀው ዘንድ እምቢ አልህ እነሆ እኔ የበኩር ልጅህን እገላለሁ›› (ዘጻ 4፡22) ሙሴ ግን ‹‹እንዲህ ከሆነ የእስራኤልን በኩር ሊሞት አይደለምን?›› ቢለው እግዚአብሔር ‹‹እንዲህስ እንዳይሆን ስለ እስራኤል የበኩር ልጆች ምትክ በእያንዳንዱ ቤት አንድ ጠቦት (በግ) ይሠዋ ሥጋውንም ብሉት ደሙን ግን በመቃኑና በጉበኑ ላይ ይርጩት ይቀቡት ደሙንም ባየሁ ጊዜ ከእናንተ አልፋለሁ እኔም የግብጽን ሀገር በመታሁ ጊዜ መቅሠፍት ለጥፋት አይመጣባችሁም›› (ዘዳ 12፡13)
በመሆኑም እስራኤል ከሞተ በኩር ይድኑ ዘንድ ነውር የሌለባትን ጥፍሩ ያልዘረዘረውን፣ ቀንዱ ያልከረከረውን፣ ጠጉሩ ያላረረውን፣ የፋሲካ ጠቦት በግ አዘጋጅተዋል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ‹‹አጥፊው የበኩሮች ልጆችን እንዳይነካ ፋሲካንና ደም መርጨትን በእምነት አደረገ›› (ዕብ 11፡28) በማለት ይህን ግልጽ አድርጎታል፡፡
በሌላው ሕዝበ እስራኤል ይህን የፋሲካውን በግ ከመመገባቸው በፊት ዝግጅት አድርገዋል ‹‹ወገባችሁን ታጥቃችሁ፣ ጫማችሁን በእግራችሁ፣ በትራችሁንም በእጃችሁ አድርጋችሁ ፈጥናችሁ ትበሉታላችሁ እርሱም የእግዚአብሔር ፋሲካ ነው›› (ዘጸ 12፡11) ተብለው ታዝዘው ነበርና፡፡
እኛም የአዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች ነውራችን የተንከባለለበት፣ መርገማችን የተሻረበት ለ5500 ዘመን በሥጋችንም በነፍሳችንም ላይ ሰልጥኖ የነበረው የሞትን አበጋዝ ድል የነሳንበት የቀራኒዮው በግ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡
ነውር ነቀፋ የሌለበት ጠቦት ወይም በግ ነገር ግን ኀጢዓትን ያስወግድ ዘንድ መርገምን ይሽር ዘንድ የተገለጠ በግ የድንግል ማርያም ልጅ ክርስቶስ ነው እርሱ በሃሣብ በቃል በሥራ ንጹሐ ባሕርይ ነው፣ ኀጢዓት ለባሕርይው የማይስማማው እንከን የማይወጣለት ነቀፋ ያልተገኘበት ቅዱስ ነው:: የአዲስ ኪዳኑ በግ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ነቢያት በትንቢታቸው ሐዋርያትም በስብከታቸው ‹‹ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት በሸላቾቹ ፊት ዝም እንደሚል በግ እንዲህ አፉን አልከፈተም›› ኢሳ 53፡7 ‹‹እነሆ የዓለምን ኀጢዓት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ›› (ዮሐ 1፡29) ‹‹የታረደው በግ ኃይልና ባለጠግነት ጥበብም ብርታትም ክብርም ምስጋናም በረከትም ሊቀበል ይገባዋል›› (ራዕ 5፡12) በማለት ግልጽ አድርገው አስተምረዋል፡፡
እስራኤል ከሞተ በኩር ይድኑ ዘንድ የፋሲካውን በግ እንዳዘጋጁ እኛም ፍጹም ድኅነትን እናገኝ ዘንድ ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዷል (ተሰውቷል) (1ቆሮ 5፡7) በደሙም ነጽተናል ‹‹ነውርና ዕድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክብር የክርስቶስ ደም ታዋጅታችኋል›› (1ጴጥ 1፡19)
እነሱ የፋሲካውን በግ በሰው ጊዜ ከባርነት ወደ ነፃነት እንደተሻገሩ እኛም በፋሲካችን በክርስቶስ ከድካም ወደ ኃይል ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከመከራ ወደ ዕረፍት፣ ከውርደት ወደ ክብር አልፈናል ከሲኦል ወደ ገነት ተሻግረናል፡፡
በመሆኑም ይህንን የእግዚአብሔር ፋሲካ የቀራኒዮ በግ ቅዱስ ሥጋውን ለመብላት ቅዱስ ደሙን ለመጠጣት መዘጋጀት ያስፈልገናል፡፡ ወገባችንን በንስሐ በንጽሕና ታጥቀን፣ የወንጌልን ጫማ ተጫምተን፣ ምግባርን ከሃይማኖት አስተባብረን ይዘን፣ ነገረ መስቀሉን እያሰብን ሥጋውን ደሙን ለመብላት ለመጠጣት ይህ የጾም ጊዜ የመዘጋጃ ጊዜ በመሆኑ የመዘጋጃ ጾም ተብሏል፡፡





No comments:

Post a Comment