Monday, March 3, 2014

በሰውም በእግዚአብሔርም ፊት መልካሙን አስብ



በሰውም በእግዚአብሔርም ፊት መልካሙን አስብ
ለልቤ ከልቤ

ልቤ ሆይ ሃላፊ አለም ሩጫው እሰኪ ይብቃህና ጥቂት አረፍ ብለን የውስጣችንን እንነጋገር፡፡ ልቤ ሆይ አንደው ጾምን የምትጾምበትን እውነተኛ ምክንያት ንገረኝ? በአካባቢህ ያሉት ሰዎች ስለሚጾሙ? ስርዓተ ቤተክርስቲያን ስለሆነ ብቻ ነው? ጽዋሚ ለመባል? ቁመናህንስ ለመጠበቅ ይሆን? እሺ ደግሞስ መጣብኝ ወይስ መጣልኝ ነው የምትለው? በቅበላ ጊዜስ በጾም ውስጥ ሥጋ እንዳያምርህ ጥሩ አድርገህ ነው አምሮትህን የምታወጣው? ገና ሳይገባ የሚፈታበትን ቀን ቆጥረኸው ይሆን? እንጃ! ብቻ መልሱን አንተው ታውቀዋለህ፡፡ የምወድህ ልቤ ሆይ እንዲያው እውነተኛውን ጾም ከማየታችን በፊት ዳግም እስኪ ጥቂት ልጠይቅህ? ሰው የደሃውን ጩኸት እንዳይሰማ ጆሮውን ደፍኖ ቁርሱን መብላት ቢተው ምን ይረባዋል? ከልቡ መዝገብ ክፉን ሳያወጣ ወደ ውስጡ ምግብን ማስገባት ቢያቆም ለሰው ምን ይበጀዋል? በአይኑ ከንቱን እያሳደደና እያየ ጾምሁ ቢል እንዲህ ያለውን ሰው ከሰማያውያን ማን ያምነዋል? ይህ ሁሉ ለታይታ የሚሆን የውጭ ብቻ አይደለምን?





ልቤ ሆይ ይህን የምለው አይሁድን እንዳትመስልብኝ በጣም ስለምፈራ ስለማስብልህ ነው፡፡ አይሁድ በውጭ በሰዎች በሚታየው ነገር ሁሉ የሚያህላቸው አልነበረም፡፡ ውስጣቸው ግን ብዙ አመጽና ግብዝነት ነበረበት እጃቸውን እንጂ ልባቸውን አይታጠቡም ይጾማሉ ቃሉን በልብሳቸው ጭምር ይጽፋሉ ግን ሰዎች እንዲያዩዋቸው ብቻ ነበር፡፡ ጌታ በምን እንደመሰላቸው ታውቃለህ? ይኸውልህ ሕይወታቸውን በመቃብር እስከ መመሰል ድረስ ገስጽዋቸዋል፡፡ መቃብር ከላይ ሲያዩት መልካም ሕንፃ ቢመስልም ውስጡ ግን ለአይን የሚከፋ ለአፍንጫ የሚከረፋ ነው አይሁድ ምንም እንኳ በሰዎች ፊት ሕይወታቸውን መልካም ለማስመሰል ቢሞክሩም የውስጣቸው የልብ መዓዛ ግን በእግዚአብሔር ፊት የሚከረፋ ነበር፡፡ ‹‹በሰው ዘንድ የከበረ በእግዚአብሔር ፊት ርኩሰት ነውና›› ሉቃ16፡13 ፡፡ እነሱ የጽዋውን ውጭውን ያጠራሉ ውስጡ ግን ቅሚያና ክፋት ሞልቶበት ነበር ልቤ ሆይ አንተስ የውስጡን እያጠብክ ነው? አይሁድ የሕግ ዋና የሆኑትን ምሕረትና ፍቅርን ታማኝነትን ትተው ጥቃቅን ስርዓታቸውን ብቻ ሲጠብቁ ጌታ እንዲህ አላቸው
‹‹ከአዝሙድና ከእንስላል ከከሙንም አስራት ስለምታወጡ ፍርድንና ምሕረትን ታማኝነትንም በሕግ ያለውን ዋና ነገር ስለምትተው ወዮላችሁ ሌላውን ሳትተው ይህን ልታደርጉት ይገባችሁ ነበር››  ማቴ 23፡23
ልቤ ሆይ ጌታ ለአይሁድ ምን እንዳዘዛቸው አስተውል የሕግ ዋና የሆነውን ፍቅር ትተው ሌላውን ስርዓታቸውን ብቻ ይከታተሉ ነበርና ‹‹ሌላውን ሳትተው›› በማለቱ ሰዎች የሚያዩትንም በጎውን ሥርዓት ሳይተው በእግዚአብሔር ፊት በንጽሕና በፍቅር እንዲመላለሱ ነገራቸው፡፡ እነሱ የጎደላቸው የውስጡ ነበርና ‹‹የውስጡን ምጽዋት አድርጉ›› አላቸው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እኔ ደግሞ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ሁልጊዜ ነውር የሌለባት ሕሊና ትኖረኝ ዘንድ እተጋለሁ›› ያለው በውጭም በውስጥም ያለነውር መመላለስ ይገባልና ነው፡፡ ሐዋ 24፡16
ልቤ ሆይ እንግዲህ ጾምህ ሌላውም ሥራህ በሰው ፊት እንዳይሆንብህ ተጠንቀቅ፡፡ ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነውን ጾም ጹም፡፡ ምክንያቱም ‹‹ጾም ከእህልና ከውሃ መከልከል አይደለም ከእግዚአብሔር ፊት የሚደርስ ጾምስ የልብ ንጽሕና ነው፡፡ ሥጋ ቢራብ ቢጠማ ነፍስ ግን ፈቃዷን ብትፈጽም ልብም ከጣዕሙ የተነሣ ደስ ቢለው የጾምህ ጥቅሙ ምንድን ነው?›› ብለው አባቶችህ ያስተማሩህን መዘንጋት የለብህም (ፍት ነገ አንቀጽ 13) ደግሞ ‹‹ጾምን አንጹም ወንድማችንን እንውደድ›› ብለውሃል፡፡
ካለህ ላይ ለተራበው ቁረስለት የታረዘውን አልብስበት ስደተኛውን ከቤትህ ተቀበልበት ኢሳ 58 አልያ ግን አንተም በከንቱ ደክመህ እኔንም አክስተህ ረሃብ እንጂ ጾም አይሆንም፡፡ መቼም ቅር እንዳላሰኘሁም ተስፋ አለኝ ምነው ‹‹እውነቱን ስለነገርሁህ ጠላት ሆንሁብህን?›› ገላ 9፡16 ደግሞ ቅር ቢልህስ ‹‹ምላሱን ከሚያጠፍጥ ይልቅ ሰውን የሚገስጽ ሞገስን ያገኛል›› እንደተባለ አታውቅም? ምሳ 28፡23 ለማንኛውም ልቤ ሆይ እንደዚህ እየተገናኘን በየጊዜው ሕይወታችንን መመርመር አለብን፡፡ አሁንም ብዙ አልያዝህ ግን በዚህን አለም የሚታየውን ነገር ብቻ ስታስብ የዘላለሙን እንዳታጣ እጅግ ያስፈራል፡፡ ምክንያቱም፡-
‹‹የሚታየው የጊዜው ነውና የማይታየው ግን የዘላለሙ ነው›› 2ቆሮ 9፡18

No comments:

Post a Comment