Friday, March 28, 2014

አንተ ካልፈረድህባት እኔ ማነኝ?




 


ጌታ ሆይ አንተ ብቻ እውነተኛ ዳኛ ነህ፡፡ ሰው ውጪን ይመለከታል አንተ ግን ውስጥን ትመረምራለህ፡፡ ልብ የመከረውን ህሊና የወጠነውን ታውቃለህ ሰው ላይ ላዩን አይቶ ይፈርዳል፡፡ አንተ ግን የልቦናን ጥልቀት አይተህ ትፈርዳለህ እንደ ሰው ቢሆን አይሁድ ወደ አንተ እያዳፉ ያመጧት ሴት ተወግራ ትሞት ነበር፡፡ ኸረ እንደ ሰውማ ቢሆን ማን ይቆም ነበር? ሕግን የምትሰጥም የምትፈርድም አንድ አንተ ነህ ልታጠፋም ልታድንም የምትችል አንድ አንተ ነህ ታዲያ እንዲህ ከሆነ እንደ እኔ ላለው ሰው በሌላው ይፈርድ ዘንድ ማን ሰጠው?


ጌታ ሆይ የተፈጠርኩበት ዓላማ ለመፍረድ እስኪመስል ድረስ እራሴን በራሴ የሾምኩ ዳኛ ሆኛለሁ፡፡ በትንሹም በትልቁም ነገር ከመፍረድ አልመለስም፡፡ የምፈርድበት ምክንያት ለራሴ ግራ እስኪሆንብኝ እፈርዳለሁ ባየሁት ብቻ አይደለም ባልተጣራው ወሬ በመስማትም እንጂ ክፉ ባደረጉት ብቻ አይደለም መልካምም ባደረጉት እንጂ ምን አልባት እኔ ብቻ ትክክለኛ ነኝ ብዬ ስለማስብ ይሆን? በፊቴ ባየሁት ነገር ሁሉ ላይ አስተያየት እንደሚሰጥ ሰው እፈርዳለሁና፡፡ እኔ ካልፈረድኩበት የሚስተካከል ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ ሌላው ቀርቶ በአንተ የመንፈስ አሰራር ውስጥ ገብቼ የፈረድሁባቸው ጊዜያት የሚዘነጉ አይደሉም፡፡

 


ጌታ ሆይ በዚህ ምድር ሳለህ አይሁድ እየከሰሱ ወደ አንተ ያመጧትን ሴት ባየህ ጊዜ ከእናንተ ኃጢዓት የሌለባት አስቀድሞ ይውገራት ነበር ያልካቸው፡፡ እነርሱም ሰምቷቸው ህሊናቸው ሲወቅሳቸው ሳይወግሯት ሸሽተዋል እኔ ግን ከእነርሱ ብሻለሁ፡፡ ስንቱን በፊትህ እየገፋው ለፍርድ እንዳቀረብሁ አንተ ታውቃለህ፡፡ አንድ ጊዜ አይደለም ብዙ ጊዜ እንጂ ፈጽሞ ግን ስህተቴ ተሰምኝ አልተመለስሁም፡፡ ታዲያ ከአይሁድ በምን እሻላለሁ? እኔ ራሴ የምሰራውን ስህተት በሚሰራ ሰው ላይ ልፈርድ ይገባልን? እኔስ በሌላው የምፈርድ ከአንተ ፍርድ እንዴት አመልጣለሁ? በምፈርድበት ነገር በራሴ እፈርዳለሁና፡፡ በራሴ ላይ ብፈርድ ኖሮ ባልተፈረደብኝ ነበር ፡፡ ነገር ግን በሰዎች ላይ ፈርጄ ለመጨረስ ጊዜው ስላጠረኝ በራሴ ላይ ለመፍረድ አልቻልኩም፡፡
ጌታ ሆይ ሁሉን የምታውቅ እውነተኛ ፈራጅ ስትሆን እኔ አልፈርድብሽም ብለህ ነበር ያችን ምስኪን ሴት በነጻነትና በፍቅር የተውሃት፡፡ ፍቅራዊ አባት ነህና ዛሬስ አንተ አልፈርድባችሁም ያልካቸውን ሰዎች እስከመቼ ስፈርድባቸው እኖራለሁ? እውነት ለአንተ ተቆርቁራ ነውን? ልብን ታውቃለህ፡፡ አሁንም ጌታ ሆይ አይኔን ከሰዎች ጉድፍ ላይ አንስቼ በእኔ ስላለው ተራራ ስለሚያህለው ኃጢዓቴ እጮህ ዘንድ ስጠኝ፡፡ አንተ አልፈርድባችሁም ያልሃቸውን እኔ እፈርድባቸው ዘንድ በእውነት ማነኝ?
‹‹አንተም በወንድምህ ላይ ስለ ምን ትፈርዳለህ? ወይስ አንተ ደግሞ ወንድምህን ስለ ምን ትንቃለህ? ሁላችን በክርስቶስ ፍርድ ወንበር ፊት እንቆማለንና››







No comments:

Post a Comment