Friday, March 28, 2014

‹‹በእርሱቁስልእኛተፈወስን››




ክፍል 
‹‹ነስአ ደዌነ ወረ ሕማምነ›› (ኢሳ 53፡4)
‹‹ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንን ተሸከመ››
          ልዑለ ቃል ኢሳይያስ በትንቢት መጽሐፉ ደረቅ ሐዲስ እየተባለ በሚጠራው ክፍል ውስጥ እግዚአብሔር የራቀውን አቅርቦ የረቀቀውን አጉልቶ ምስጢሩን ስለገለጸለት የኢየሱስ ክርስቶስን መከራ መስቀል በትህትና መንፈስ በመሆን መዝግቦልናል፡፡
ሙሴ በምድረበዳ እባብን እንደሰቀለ እንዲሁ በእሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ሊሰቀል ይገባዋል፡፡ (ሐዋ 3፡14) ተብሎ እንደተፃፈ የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ በዘመኑ ፍጻሜ የእግዚአብሔር ልጅ እግዚአብሔር ከሰማየ ሰማያት ወርዶ መለኮታዊ ክብሩን ዝቅ አድርጎ ሥጋ በመልበስ ፍጹም ሰው በመሆን በተዋሕዶ ከበረ፡፡
ከዚህም የተነሳ የማይራበው ተራበ፣ የማይጠማው ተጠማ ኅይለኛው ደከመ፣ የወደቁትን የሚያነሳ እሱ ወደቀ፣ እውነተኛ ዳኛ ፈታሒ በርትዕ ሆኖ ሳለ በአይሁድ ተከሶ እንደ ወንጀለኛ በፍርድ አደባባይ ቆመ፡፡





መከሰሱም በሰውነቱ ክፋት በአንደበቱ ሐሰት ነውር ነቀፋ ኀጢዓት ኖሮበት ሳይሆን በሰንበት በሽተኞችን ይፈውሳል (ዮሐ7፡23)፣ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር ያስተካክላል (ዮሐ 6፡14) ፣ ለቄሳር ግብር እንዳይሰጥ ይከለክላል (ዮሐ 13፡7) ፣ ራሱን የእግዚአብሔር ልጅ ያደርጋል (ሉቃ 22፡69) ቤተ መቅደስን አፍርሼ በሦስት ቀን እሠራለሁ ይላል (ዮሐ 12፡3) ሕዝብ ሁሉ ይከተሉታል (ዮሐ 12፡19) በሚል የሐሰት ውንጀላ ፍርድ ተጣሞበት ነው እንጂ፡፡





አይሁድ እነዚህንና ሌሎችን የማከሰሻ ምክንያቶች ይዘው የሐሰት ምስክር ቆጥረው ምቹ ጊዜን ጠብቀው ይፈርዱበት ዘንድ ይሁዳን በሰላሳ ብር ሸንግለው ንጹሕ ደምን አሳልፎ እንዲሰጣቸው ዶለቱ፣ ክፉ ምክርንም ተማከሩ በእርግጥ የስደት፣ የመከራና የሞት ወጥመድ የተጀመረው በቤተልሔም ከተማ በእንሰሳት በረት ከተወለደበት ጊዜ ገና በግዕዘ ሕጻናት ሳለ ነበር፡፡
ሰባ ሰገል የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ የታለ ብለው በሞት መንደር የባለመድኀኒቱን ዜና ሲያወሩ ሄሮድስ በቅናት ተነሣ ልቡ በክፋት ተምልቶ አሳደደው ከዚያም በኋላ ተረፈ ሄሮድስ አይሁድ የዲያብሎስ የግብር ልጆች ምድራዊ ስልጣናቸውን የሚሻማቸው የሚሰበስቡትን ግብር ቀረጥ የሚካፈልባቸው እየመሰላቸው እነሱ ተሸብረው ሽብርን ነዙ ትምህርትና ተአምራቱን ያለ አቅጣጫው እየተረጎሙ ምክንያትና መክሰሻ እየፈለጉ ሲያሳድዱትና ሲያጠምዱት ቆይተዋል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ጊዜው ሳይደርስ ራሱን ሊገልጥ ባለመፈለጉ በተንኮል ሊያጠምዱት ባሴሩበት ሰዎች መካከል በተአምራት አልፎ እየሄደ አይሁድ ያሰቡትን ሳያሳኩ ቆይተዋል፡፡ ነገር ግን የመጨረሻ ምክረ ሞቱ እየተጠናከረ የመጣው የ38 ዓመቱን በሽተኛ ካዳነበት እለተ ሰንበትና አልዓዛርን ከሞት ካስነሳበት ድንቅ ተአምራት በኋላ ነበር፡፡ ነቢዩ ዳዊት በትንቢት መጽሐፍ ‹‹ፊደዩኒ እኪተ ህየንተ ሠናይት (ስለ በጎ ፈንታ ክፉ ብድራት መለሱልኝ)›› (መዝ 34፡12) እንዲል ዕውራንን ባበራ ለምጻሞችን ባነጻ፣ ደካሞችን በበረታ፣ አነካሶችን ባቆመ ሙታንን ባስነሳ አሳደዱት፡፡ ዳሩ ግን የእሱ ስደትና መከራ አላወቁትም እንጂ የሰውን   ክብርና ነፃነት ያሳጣውን ሐሳዊ ዲያብሎስን የሚያሳድድና የጠፋውን አዳምን የሚፈልግ ሕይወት ነበር፡፡
ለቤዛዓለም ተላልፎ የሚሰጥበት ጊዜው ደርሶ አይሁድ ኅይለኛውን ኅይል አግኝተው በያዙት ጊዜ፣ ጊዜ የማይቆጠርለትን ጊዜ አግኝተው በያዙት ጊዜ የሞትን መድኀኒት የሞት ፍርድ ሊወስኑበት የፈራጆች ክፍል ስልጣን አስከባሪዎችና ጠባቂ ጭፍሮች መከራን ያጸኑበት ጀመር፡፡
·         ጸጋን የሚያለብሰውን የጸጋውን ባለቤት እሱን ልብሱን ገፈው ቀይ ከለሜዳ አልብሰው በራሱ ላይ የእሾህ ጉንጉን በመጫን የሸንበቆ ምርኩዝ በማስጨበጥ ‹‹አነገስንህ›› እያሉ ከፊቱ እየሰገዱ በፌዝ ተሳልቆ (በማሳለቅ) ንጉሱን ዘበቱበት
·         በብሉይ ኪዳን ሕግና በአይሁድ ማህበረሰብ ባህል እጅግ የተጠላና የተወገዘውን ርኩስ ምራቅ በንቀት በፊቱ ላይ ተፉበት (ዘኃ 12፡14 ፣ ዘዳ 25፡7 ፣ ኢዮ 30፡10)
·         ኪሩቤል ከግርማው የተነሣ መንበሩን ተሸክመው ከፊቱ በቆሙ ጊዜ በፊትህ ጸንተን መቆም አንችልም ፣ ከአንተ የሚሰወር ምንም ነገር የለም፣ ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣኸን፣ ካለመታየት ወደ መታየት ያመጣኸን አንተ ነህ ሲሉ በሁለት ክንፋቸው እግራቸውን በሁለት ክንፋቸው ዓይናቸውን ሸፍነው ቅዱስ (3) እያሉ የሚያመሰግኑትን ፊቱን በጨርቅ ሸፍነው በጥፊ እየመቱ ‹‹ነቢይ ኢየሱስ ሆይ የመታህ ማነው?›› እስኪ ንገረን እያሉ ተሳለቁበት (ኢሳ 6፡3)
·         እጃቹን የኋሊት (የፊጥኝ) አስሪው ወደፊትና ወደ ኋላ እየጎተቱ ከገበያ ለእርድ እንደሚጎተት ጠቦት አንገላቱት
·         ጭፍራዎች እየተሳለቁና ቁማር እየተጫወቱ ‹‹ቁጥር ተሳሳተብን›› በማለት መቶ ፮፮ጊዜ ሥጋው ከሰውነቱ አልቆ አጥንቱ ሊቆጠር እስከሚችል በጅራፍ ገረፉት
·         በመጨረሻም በአምስቱ ቅንዋተ (ችንካር) ሳዶር፣ አላዶር፣ ዳናት፣ ሮዳስ፣ አዴራት በእንጨት ላይ ቸንክረው ከሰቀሉት በኋላ ተጠማሁ ባለ ጊዜ ከሐሞትና ከርቤ (ድኝ) የተበጠበጠ ዮምጣጤ አጠጡት
·         በዕለተ አርብ ከሌሊቱ 3 ሰዓት ጀምሮ ነፍሱ ከሥጋው እስከተለየችበት 9 ሰዓት ድረስ 18 ሰዓት ሙሉ የሰው አቅምና ሕይወት ሊቀበለው የማይችለውን እሱ ግን በአምላክነቱ የቻለውን ልዩ ልዩ ፀዋትወ መከራ አደረሱበት
·         ከዚህ ሁሉ በኋላ የአይሁድ ጭፍራ አለቃ የነበረው ሌንጊኖስ ነፍሱ ከሥጋው መለየቷን ለማረጋገጥ ቀኝ ጎኑን በጦር ወጋው፣ ከጎኑም ለኛ ደህንነት ሕይወት የጥምቀታችን ምንጭ ሆኖ የተሰጠን የልጅነትን ክብር ያደለንና የኃጢዓታችንን ሥርየት የሆነው ክቡርና አማናዊ ደሙና ውሃ በ‹ለ› ቅርጽ ፈሰሰልን





ይህ ሁሉ የመከራ ማዕበል በለበሰው ሥጋ ሲፈራረቅበት በአንደበቱ ሐሰት ሁሉ በደልና ስህተት ያልተገኘበት ጻድቅ የዋህና ሐዳጌ በቀል አምላክ ነው፡፡ ልብሱን ተገፎ ከለሜዳ መልበሱም ከክብሩና ከጸጋው የተራቆተውን የሰውን ልጅ እርቃን ሐፍረት በልጅነት ጸጋ ለማጎናጸፍ ነበር በሐሰት ምስክርና ግብዝ ፍርድ እንደ በደለኛ ተቆጥሮ በበደለኖቹ መካከል ቢሰቀልም ስለኃጢዓት ጠላቶቹም ቢሆኑ አንዳችስንኳ የሚወቅሱበት አልነበራቸውም፡፡
‹‹ስለ ኀጢዓት የሚወቅሰኝ ማን ነው?›› (ዮሐ 8፡46) ‹‹ስቀለው ስቀለው›› የሚለውን የክፋተኞችን ጉባዔ ጩኸት ለማብረድና ስልጣኑን ለመከላከል ሲል አሳልፎ የሰጠው ጲላጦስ ‹‹እኔስ በዚህ ሰው አንዲት በደልስኳ አላገኘሁበትም ፣ እኔ ከዚህ ጻድቅ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ›› በማለት ያለ አበሳው መገፋቱን ከመመስከሩም ባሻገር ሚስቱም ‹‹በሕልም እጅግ መከራ ተቀብያለሁ በዚያ ጻድቅ ሰው አንዳች እንዳታደርግ›› በማለት ነውር ነቀፋ የሌለበትን ንጹሐ ባሕርይ ጌታ መከራ እንዳጸኑበት መስክራለች፡፡ (ማቴ 27፡19 ፣ ማቴ 27፡24 ፣ ማቴ 27፡38)
ነገር ግን ‹‹እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ›› የተባለው ይፈጸም ዘንድ ጌታ በዕለተ አርብ የመስቀልን ሞት ተቀበለ (ዮሐ 10፡10) በወቅቱ የነበሩት የአይሁድ የክፋት ጉባኤተኞች የአመጽ ባልደረባቸው አሸባሪውና ወንበዴው በርባን እንዲፈታላቸው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የስቅላት ሞት ቢፈርዱም ፍርዱን በማጣመማቸው የታሪክ ትዝብትን አተረፉ እንጂ የጌታችን ሞት ግን አለም የሚድንበት ከቁስለ ኀጢዓትም የሚፈወስበት የማይቀር መስዋዕትነት ነበር ‹‹ደም ሳይፈስ ሥርየት የለም›› (ዕብ 9፡23) ተብሎ ተጽፏልና፡፡
ጌታችን ለሞትና ለመከራ ተላልፎ ሊሰጥ በሾተልና በገመድ ተከቦ በጭፍሮች በሚዋከብበት ጊዜ በጠላቶቹ ላይ ሠይፍ አንስተው የበቀል እርምጃ ሊወስዱ ለሞከሩት ለነቅዱስ ጴጥሮስ ጌታ የሰጠው ምላሽ እጅግ የሚገርምና የትዕግስቱን ብዛት የሚያሳይ ከመሆኑም ባሻገር በጉልበታቸውና በሠራዊታቸው ብዛት ለሚመኩት ለዓለማችን ጦረኞችና ሠይፈኞች ትልቅ ትምህርት ነው ‹‹ሠይፍህን ወደ አፎት መልስ እኔ ይህን ጦር መቋቋም ብፈልግ ከአስራ ሁለቱ ጭፍሮች የሚበዙ ብዙ ሠራዊቶች ነበሩኝ፣ ሠይፍን የሚያነሱ ሁሉ በሰይፍ ይሞታሉና›› የሚል ነበር (ማቴ 26፡52)
በእኛ ላይ ያለው ዓላማው ፍቅር ነውና፣ ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲቀርቡ ወዶ ይታገሳል ተብሎ ተጽፏልና (መኀ 2፡1 ፣ 2ጴጥ 3፡10) በመስቀል ላይ ሆኖ እየቆሰለና እየደማ ለበደለኞች ለኀጢዓተኞች መከራን አጽንተው ለሰቀሉት ‹‹የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው ብሎ ማለደ›› ከራሱና ከመንፈስ ቅዱስ እንዲሁም ከባሕርይ አባቱ ከአብ ጋር አስታረቀ፡፡ (2ቆሮ 5፡16-21)
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበለው ጻዋትወ መከራ ሁሉ ‹‹የድኅነታችን ተግሣጽ በእሱ ላይ ወደቀ›› (ኢሳ 53፡5) ተብሎ እንደተጻፈ ለድኀነታችን ቤዛ ነው፡፡
ስለ ህመማችን እሱ ታመመ ስለ ተሸከምነው የኀጢዓት ደዌ እሱ ደዌያችንን ተሸከመ ‹‹ነስአ ደዌነ ወጾረ ሕማምነ›› ይህንን ውለታውን በሰው ድካምና ጥረት መመለስ ባይቻልም ነገር ግን አበው ይህንን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ያዳነበት ጥበቡን በአርምሞ ሆነን ዕፁብ እያልን መከራውን እንድናስብ ከሆሣዕና እስከ ቀዳም ሥዑር ያለውን ሳምንት የጌታ ሕማማት መታሰቢያ ሆኖ በጾም በፀሎት በሐዘን እንዲታሰብ በወሰኑት መሠረት ሳምንቱን ስሞነ ሕማማት ወይም ልዩ ሳምንት ብለው ሰይመውታል፡፡
አርባው(40ው) ቀን የጌታ (ዓቢይ) ጾም በኒቆድሞስ ዕለተ አርብ ይጠናቀቃል፡፡ ከዚህ በኋላ እስከ ቅዳሜ ስዑር ያለው የሕማምት ሰሞን ነው ቅዳሜ በጥንተ ፍጥረት ጌታ ከሥጋው ሁሉ ስላረፈበት ከእህል ከውሃ አይጾምም በዓብይ ጾም መግቢያ መጀመሪያው ሳምንት ከሚጾምባቸው ምክንያቶች አንዱ በ40 ጾም (በሁዳዴው) ውስጥ ከጥሉላት ምግቦች በቀር የማይጾምባቸውን የቅዳሜን ዕለታት ለመተካት እንደሆነ ተገልጾአል ቅዳሜ ስዑር ግን የፍጥረታት ፈጣሪ ጌታ በመቃብር ስላደረባት ይጾማል፡፡
የአጽዋማትን ሰዓት ልክና መጠን በተመለከተ ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ባስልዮስና ሌሎች ሊቃውንት በዐቢይ ጾም የመጀመሪያው ሱባዔ ሣምንት እስከ ፍፃሜ መዓልት፣ (12 ሰዓት) ስድስቱ ሱባዔ (40ው ቀን) ምሽቱ 1 ሰዓት፣ ሰሞነ ሕማማት የምሽት ኮከብ ደምቆ እስከሚታይ ድረስ እንዲጾም ሲወስኑ፣ የኋላ ሊቃውንት ጌታ ነፍሱን ከሥጋው የለየው በ9 ሰዓት ነው እሱ ነፍሱን ከሥጋው በፍቃዱ ለይቶ አይሁድ ካመጡበት መከራ እንዳረፈ እናንተም ከድካምና መከራ እረፉባት ሲለን ነው ብለው ጾም እስከ 9 ሰዓት ይሁን ብለው ወስነዋል በቀኖና ቤተ ክርስቲያን የተወሰኑት አጽዋማትም ሰባት ሲሆኑ እስከ 9 ሰዓት ጹሟቸው ብለዋል፡፡ ከዓብይ ጾም መጀመሪያ ሳምንትና ከሕማማት በስተቀር በሌሎች አጽዋማት ሁሉ ሰዓቱ ይኸው ነው፡፡
ነገር ግን ለቱሩፋት ሥራ ቀናዒ የሆነ ሁሉ ለጾም ብልጫ ቢሰጥ የበለጠ ዋጋ ክብር ያገኝበታል እንጂ አይጎዳበትም የአክፋሎትም ታሪክ አመጣጥ ከሐዋርያት ጀምሮ ከሰሞነ ሕማማት ጋር የተያያዘ ነው፡ እረኛቸው ክርስቶስ ‹‹ሙሽራው ከነእሱ ጋር ሳለ ሚዜዋች ሊጦሙ አይገባም ነገር ግን ሙሽራው ከነሱ በሚወሰድበት ጊዜ ይጦማሉ›› ብሎ በተናገረው መሠረት ሚዜዎች የተባሉት ሐዋርያት ጾም የጀመሩት በሙሽራው በጌታ ዕለተ ስቅለት ነው፡፡
ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን የዕለተ ዓርብ ሙሽራ ያሉት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተያዘበት፣ መከራ በተቀበለበትና በመልዕልተ መስቀል በተሰቀለበት ስሙነ ሕማማት በሐዋርያት ዘንድ ብዙ መደናገጥ ሽብርና ሐዘን ገብቷቸው ነበር፡፡ ‹‹እረኛውን እመታለሁ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ›› (ማቴ 26፡32) ተብሎ በተጻፈው መሠረት እረኛ ሲያዝ የመንጋው መበተን አይቀሬ ነውና፣ የጌታ መከራ መቀበል አስቀድሞ በሰፊው የተነገረና የታወቀ ቢሆንም በተግባር በተፈጸመ ጊዜ ግን እንኳንስ የእጁን ተአምራት ያዩ የቃሉን ትምህርት የሰሙ ያበረከተውን የበሉ ለፍቅሩ የሚሳሱለት ደቀመዛሙርቱ ቀርቶ ተመልካችን ሁሉ የሚያሳዝን የሚያስፈራና የሚያስደነግጥ ነበር፡፡




ሐዋርያት ጌታችን በፈቃዱ ነፍሱን ከሥጋው ለይቶ ከተቀበረ በኋላ እህል እንቅመስ ብለው ነበር፡፡ የጌታችን ወዳጅና ወንድም እየተባለ የሚታወቀው ሐዋርያው ያዕቆብ ግን ትንሣኤውን ሳላይ አይሆንም ስላላቸው ሐዋርያት እሱን ተከትለው አክፍለዋል በዚህ ሥርዓት ብዙ አበው ካህናትና ምዕመናን ከሐሙስ  ማታ እስከ ትንሣኤው ሌሊት እህል ውሃ ሳይቀምሱ ያከፍላሉ፡፡ ብዙዎች ደግሞ ዓርብ ማታ ተመግበው ቀሪውን እስከ ትንሣኤ ሌሊት ይጾማሉ፡፡
በሰሞነ ሕማማት ማጥመቅ ፣ ሥልጣነ ክህነት መስጠት፣ ጸሎተ ፍትሐት ማድረግ ክልክል ነው፡፡ ምክንያቱም ነፍሳት ከሲኦል አልወጡምና ለሙታን አጠቃላይ ጸሎተ ፍትሐት የሚደረገው፣ መስቀል መሳለምና ኑዛዜ የሚሰጠው የሆሳዕና እሁድ ነው ጸሎተ ፍትሐቱ ከሕማማት በፊት ያለፉትንና በሕማማት ቀኖች የሚሞቱትን ሁሉ ያጠቃልላል:: መስቀል መሳለምና ቡራኬ የማይደረገው ልጅነት አልተሰጠምና :በተቀደሰ አሳሳም የሰላምታ ልውውጥ የማይደረገው የሰላምታ ጸሎት የማይጸለየውም ነፍስና ሥጋ ተዋህደው ስላልተነሱ ሰላምታውም የይሁዳ መሳሳም እንዳይሆን ነው ‹‹ይሁዳ፡- የምስመው እሱ ነው ያዙት›› ብሎ ጌታን በመሳም አሳልፎ ሰጥቷልና ነው፡፡
በሰሞነ ሕማማት ሁላችን እንድንጾም እንድንሰግድና ግብረ ሕማማት ሲነበብ እንድንሰማ ቤተ ክርስቲያን ታዝዛለች፡፡ ነገር ግን ይህን ሳያደርግ የቀረ በዓለ ሐምሳ እንዲጾምና እንዲሰግድ ተወስኗል፡፡ይህን ሁሉ እንድንፈጽም አበው የወሰኑትና ያዘዙት የዓለም መድኀኒት ኢየሱስ ክርስቶስ በፍቅሩ ጽናት ያደረገውን የቸርነቱን ውለታ ለማሰብና ለማመስገን ነው፡፡
‹‹ፍቅር ከሞት የበረታች ናት›› (መኀ 8፡7) እንዲል መጽሐፍ እግዚአብሔር በእኛ ላይ ያለው ዓላማው ፍቅር ስለሆነ ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ አንድያ ልጁን ሰጠን እሱም መተኪያ በሌላት ነፍሱ ተወራርዶ አዳነን፡፡ ሊቁ አባ ሕርያቆስ ‹‹ፍቅር ሰሐቦ ለወልድ ኃያል እመንበሩ ወአብጽሖ እስከለሞት›› ፍቅር ኃያል ወልድን ከመንበሩ ሳበው እስከ ሞት አደረሰው በማለት የክርስቶስን ጥልቅ ፍቅር ገልጾታል፡፡










ሰው ሰውን ቢወድ ድቃቂ ሳንቲም፣ አላቂ ልብስ ወይም የሚሻግተውን የሚበሰብሰውን እንጀራ ሊሰጥ ይችል ይሆናል፣ ሕይወቱን የሚሰጥ እስከሞት የሚወድ ግን አይኖርም እግዚአብሔር ለፍጥረቱ ያለው ፍቅር ግን ከሞት አድማስ ባሻገር ከመቃብርም ማዶ ሞትና በሕይወት እስከመለወጥ ከሞት አስነስቶ ከመቃብር አውጥቶ የዘላለም ሕይወትን እስከመስጠት፣ ሥጋውን ምግብ ፣ ደሙን መጠጥ አድርጎ እስከማቅረብና መንግስቱንና ርስቱን እስከማውረስ ነው፡፡ ይህንን ፍቅር የሚመስለውና የሚስተካከለው ፍቅር እስካሁን በዓለም ላይ አልነበረም ወደፊትም አይኖርም ለዚህም ነው ሊቃውንት ‹‹እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ሰው ሆኖ ተወልዶ፣ ተጠምቆ ፣ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ፣ ሞቶ ተነስቶ ያዳነበት ጥበቡ ይበልጣል›› ያሉት ማን ያርዳ የቀበረ እንዲሉ በቁርጥ ቀን በመስቀል ሥር በመገኘት ፍቅሩን ያጣጣመ ውለታውን ያየ ሐዋርያው ዮሐንስ ‹‹በእሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷል፣ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም›› (ዮሐ 3፡16 ፣ 15፡13)
ሰው ላም አርብቶ ወተቱን እህል ዘርቶ እሸቱን ምርቱን፣ በግ ጠብቆ ሥጋውን ለምግቡ ጸጉሩንና ልብሱን ጥቅም ያውላል፡፡ በዚህ መካከል እንሰሳው ቢሞት ለአራዊት እህሉ ቢነቅዝ ለእንሰሳት ይሰጠዋል እግዚአብሔር ግን ከእምነትና ከምስጋና በቀር ከፍጥረቱ የሚሻው ምንም የሌለ ከመሆኑም ሌላ ሰው በምኞቱ ፀንሶ በኃጢዓቱ ስቦ ባመጣው ሞት በሞተ ጊዜ ከክብሩ እንደተዋረደ ከፀጋው እንደተራቆተ ልጅነቱን እንዳጣ ከተድላው እንደተባረረ ከጽድቅ ገነት እንደወጣ በሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ እንደተፈረደበት ፈጣሬ ፍጥረታት እግዚአብሔር በቸርነቱ ተመልክቶ ሕይወትን ለመመለስ ሕይወቱን ሰጠለት ተላልፎ ሞተለት ሰው ሁሉ የጌታችንን ቸርነት የማዳኑን ጥበብ የፍቅሩን ጽናት ጣዕም ቢቀምስ አይደለም ጊዜውንና ጉልበቱን ነፍሱንም ቢሆን ለመስጠት ወደ ኋላ ባላላ ነበር ምክንያቱም ነፍሱን ስለወዳጆቹ ከመስጠት የሚበልጥ ምንም ፍቅር የለምና፡፡
ሰው ሰውን ሲወደው ለሰላምታ ለውለታ ነው እጅግ ይቀርበኛል የሚለውን የቤቱን ሰው እንኳ ቢወድ ከልጆቹ እኩል አይመለከተውም ሀብቱን አያካፍለውም፣ ርስቱን ጉልቱን አያወርሰውም ጌታ ግን ልጅነትን ሰማያዊ ሀብትንና ዘላለማዊ ሕይወትን የሰጠ ለሁሉ ነው ፡፡ ላመነበት ከቤተሰቡ፣ ምድራዊ ሀብቱ ይልቅ የጌታን ፍቅር በማስበለጥ መስቀሉን ተሸክሞ የሚከተለውን ሁሉ የጸጋውና የክብሩ ወራሽ ይሆናል፡፡
ወንጌላዊውም ‹‹ለተቀበሉትና በስሙ ለሚያምኑት ለነሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው›› (ዮሐ 1፡12) በማለት አስረግጦ አስተምሮናል፡፡
ከጌታችን ከመድኀኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ሕማምና መከራ ሞትና ትንሣኤ በፊት በተኖረው ሕይወት ሁላችን በኀጢዓት በር ወደ ዓለም የገባው የሞት ባሮችና ተገዥዎች ነበርን፡፡ አሁን ግን ነጻ ነን ክርስቶስ ነፃ አወጣን ስለ እኛ ታስሮ ኃይለኛውን ዲያብሎስን አሰረው እኛንም ከእስራታችን ፈታን፣ ስለ እኛ ተገርፎ ቆስሎ ከቁስላችን ፈወሰን ፣ በመስቀል ላይ ተቸንክሮ ከችንካር አላቀቀን፣ በሚጮሁትና በሚያስደነግጡት መካከል አንበሳ ሆኖ ያለ ነውርና ነቀፋ በመሄድ ፍርሃትና ድንጋጤያችንን አስወገደልን፣ እርቃኑን ውሎ አበሳችንን ከደነልን የተራቆተውን ስብዕናችንን በጸጋው አለበሰ፣ ከእንግዲህ ወዲህ የእግዚአብሔር ልጆችና ወዳጆች እንጂ ባሮችና አገልጋዮች ተብለን አንጠራም፡፡ (ዮሐ 15፡15) ከእግዚአብሔር ለመወለድና የክብሩ ወራሽ ለመሆን ግን በግብር እርሱን መከተል እሱን የሚያስመስል መልካም ሥራ መሥራት ያሻል፡፡ (1ቆሮ 4፡15)

ዋቢ፡- መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ ዱ)
      ሕማማተ መስቀል
      ግብረ ሕማማት    




No comments:

Post a Comment