Tuesday, March 18, 2014

የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላ ሀሳቦችን ማን ያስተውላል?




ዲያብሎስ የብርሃን መልአክ መስሎ በመቅረብ ሰውን ማሰናከልና ሰውን መጣል ትልቁ ሰውን የሚዋጋበት መንገድ ነው፡፡ ወንጌልም ይህን ያረጋግጥልናል 2 ቆሮ 1114 ይሁን እንጂ ብርሃንን የተጎናጸፈ ጨለማ መንፈሳዊነትን የተላበሰ ስጋዊ ሀሳብና ምክርን ጠላት በሕይወታችን ምን ያህል ጊዜ አቅርቦልናል? እንደነዚህ ያሉ ሀሳቦች የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላ ሀሳቦች ሊባሉ ይችላሉ፡፡

ልክ ጌታ ስለ ሐሰተኛ ነቢያት በተናገረበት አንቀጽ ‹‹የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውሥጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኩላዎች ከሆኑ… ተጠንቀቁ›› እነዳለው ያሉ ናቸው ማቴ 715፡፡ ልዩነቱ እነዚህ ሰዎች ሳይሆኑ ከራሳችን ልብ የሚፈልቁ ወይም ሌሎች የሚያቀርቡልን ሀሳቦች ናቸው፡፡ ዛሬ ከሰዎች በላይ ከራሳችን ወይም ከሌሎች ከሚቀርቡልን ተኩላ ሀሳቦች ልንጠነቀቅ አይገባን ይሆን? ከላይ በጎና መንፈሳዊ የሚመስሉ ውስጣቸው ወይም ፍሬያቸው ግን ስጋዊና መራራ የሆኑ ናቸው፡፡ አንዳንዴ በቀናነትና በበጎነት የሚታሰቡ ቢሆኑም ፍጻሜያቸው ግን ምንም ቀናነት ሆነ በጎነት የለበትም፡፡
በወንጌል ጌታ እሰቀላለሁ እሞታለሁ ሲል ጴጥሮስ ‹‹አይሁንብህ›› እንዳለው ወይም ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ጌታው ለመታሰር ብቻ አይደለም ለመሞት ተዘጋጅቶ ሳለ ሌሎች ከዚያ እንዲርቅ እያለቀሱ ጭምር እንደለመኑት ያሉ ሀሳቦች ናቸው ማቴ 1622 ሐዋ 2113፡፡ ነገር ግን ጌታም ሆነ ጳውሎስ ምንም እንኳ ሌሎች ለበጎ አስበው ቢናገሩትም የሀሳባቸውን ምንጭና ለምድ ለባሽነት ስለተረዱ ሀሳባቸውን አልተቀበሏቸውም፡፡ ጌታ መከራን ስለ እኛ ተቀብሎ ሞቶ አዳነን ጳውሎስም ስለ አምላኩና ስለወንጌል መከራን ተቀበለ፡፡ በክርስቲያናዊ ሕይወትም ሁኔታው ይለያይ እንጂ በየዕለቱ ምርጫ ልናደርግባቸው የሚገቡ ሁለት ሀሳቦች ፈጽሞ አይጠፉም ክርስቲያን ሁለት ነገሮች እንዲመርጥ ሳይቀርብለት የሚያሳልፈው ቀን አለ ብሎ ለማሰብ ይከብዳል፡፡ ትልቁ ነገር ግን በግ የሆነውን ሀሳብና የበግ ለምድ ለብሶ የመጣውን ሀሳብ ከመለየት ላይ ነው፡፡ ምክንያቱም ለብዙዎች በመንፋሳዊ ሕይወት እንደሚገባ ካለማደግ የተነሳ ከሀሳቦች ውስጥ እውነተኛና መንፈሳዊውን ለመለየት አስቸጋሪ የሚሆንበት ጊዜ አለና ነው፡፡
ታዲያ ባለንበት የሕይወት ደረጃ እንዴት ልንለያቸው እንችላለን? የሚለው ጥያቄ ተገቢ ነው በተለይ ፍሬ ከማፍራታቸው በሥራ ከመዋላቸው በፊት ገና በሀሳብ ደረጃ ላይ ሳሉ ማወቅና ከነዚህ ሀሳቦች መሸሽ መራራ ፍሬ ከመብላት ያድናል፡፡ እኛ የዛሬ ብቻ ነንና አባቶቻችንን ተጠግተን ብንጠይቅ ካሳለፉት መንፈሳዊ ልምድ ብዙ ሊረዱን ይችላሉ፡፡ ለአሁኑ ግን ከጌታና ከጳውሎስ የምንማረውን አንድ እውነት እንያዝ፡፡
እርሱም ጌታችንም ሆነ ጳውሎስ ለራሳቸው የሚሆነውን ሀሳብ አልመረጡም፡፡ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጆች መዳን ራሱን ለሞት አሳልፎ በመስጠት ሰዎችን አዳነ፡፡ ጳውሎስም ለሥጋው እረፍትን መምረጥ ሲችል መከራ እየተቀበለ ምዕመናንን ለማገልገልና አምላኩ የሚከብርበትን ሀሳብ ያዘ፡፡ በስጋው መከራን በመቀበል ነፍሱን ጠቀመ እንደ ጳውሎስ ያለ እንኳ ባይሆን እኛም ያቅማችን ሲገጥመን እግዚአብሔር የሚከብርበትን ከእኛ ይልቅ ሌሎች የሚጠቀሙበትን ሥጋችን ተጎድታ ነፍሳችን የምትድንበትን መርምረን እንምረጥ፡፡ እንዲህ ሲባል እርሱንስ ቢሆን እንዴት እንለየዋለን? የሚል ጥያቄ አይጠፋም፡፡ መልሱ ይህን ከሚጽፉት በላይ ቢሆንም በቃለ እግዚአብሔር እየመዘንን ከልባችን የጌታ የሆነውን ስንሻና ሕይወታችን ሲለወጥ… ልንለየው እንደሚቻለን የታመነ ነው፡፡ ‹‹እናንተ ትሹኛላችሁ በፍጹም ልባችሁም ካሻችሁኝ ታገኙኛላችሁ›› ብሏልና ኤር 2913 እንግዲህ የበግ ለምድ የለበሰውን ሀሳብ ሰይጣን ባቀረበልን ጊዜ ከጌታ ጋር ሆነን ‹‹ወደ ኋላዬ ሂድ አንተ ሰይጣን የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና›› እንበለው፡፡
ከእኛ በላይ ከሆነና ማስተዋል ካቃተን ከተሰወረብን ግን ከዳዊት ጋር በጌታ ፊት ተንበርክከን እጆቻችንን ዘርግተን በዕንባ እየታጠብን እንዲህ እንበለው፡-
‹‹ስሕተትን ማን ያስተውላታል ከተሰወረ ኃጢዓት አንጻኝ›› መዝ 1812
ከምንለምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ ይልቅ እጅግ አብልጦ ሊያደርግ የሚቻለው እግዚአብሔር ይመስገን፡፡ አሜን!!

No comments:

Post a Comment