Monday, March 24, 2014

‹‹የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱ ምንድን ነው?›› (ማቴ 24፡3)




ይህንን ጥያቄ የጠየቁት ለጊዜው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዋለበት የዋሉት ካደረበት ያደሩት የእጁን ታምራት ያዩት የቃሉን ትምህርት የሰሙት ቅዱሳን ሐዋርያት ሲሆኑ ከደብረዘይት አቀበት ቁልቁል በማለዳ ፀሐይ የሚያብረቀርቀውን የኢየሩሳሌምን ከተማና በውበቱ እጅግ ያማረውን የዘሩባቤልን ሕንፃ ቤተመቅደሱን በመልካም ድንጋይና በተሰጠው ሽልማት እንዳጌጠ ሲነጋገሩ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህ የምታዩት ሁሉ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ የማይቀርበት ዘመን ይመጣል ባላቸው ጊዜ ነበር ‹‹መምህር ሆይ ይህ ሁሉ መቼ ይሆናል?›› ይህስ ይሆን ዘንድ እንዳለው ምልክቱ ምንድን ነው? ያሉት፡፡ (ማር 13፡3)




ለጊዜው በውበቱ እጅግ ያማረውን የዘሩባቤልን ሕንፃ ሲያደንቁ በዘሩባቤል የተሰራው በጥጦስ ይፈርሳልና ፡፡ ይህም እንዴት ሆነ ቢሉ ከጥጦስ ሠራዊት አንዱ ድንጋይ ቢፈነቅል ድስት ሙሉ ወርቅ አገኘ ከዚያ በኋላ የበለጠ እናገኝ ሲሉ ቤተመቅደሱን ሲያፈርሱ ኖረዋል፡፡ አንድም ‹‹ብልጥግናቸው ለምርኮ ይሆናል ቤቶቻቸውም ይፈርሳሉ፣ ቤቶችንም ይሠራሉ ነገር ግን አይቀመጡባቸውም ተብሎ እንደተፃፈ (ሶፎ 1፡13) ይህስ ድንጋይ ግዑዝ ነው፡፡ ነገር ግን ንስሐ ያልገባው በርኩሰት በኃጢዓት የፈዘዘው የደነዘዘው ሕንፃ እግዚአብሔር የሆነው የሰው ሕይወት በአመጻ ብዛት ይፈርሳል ሲል ነው፡፡
በሌላው ‹‹ድንጋይ በድንጋይ ላይ ተቀምጧል›› የተባለው ትንቢት የደረሰበት ይሁዳና አይሁድ የክርስቶስን ደም አፍሰው ጌታቸውን አምላካቸውን ገርፈውና ሰቅለው ገደሉት የእነርሱም ደም በግፍ ፈሰሰ፡፡ ጥጦስ ተነስቶ የእነርሱን ደም አፈሰሰ ሽማግሌዎቻቸውን አዋረደ ሕፃናቶቻቸውን ሴቶቻቸውን አዋረደ፣ ሮማውያንም በአይሁድ ላይ በግፍ ተነስተው አጥፍተዋቸዋል::
እንዲሁም እኛም የሰው ልጆች በዳግም ምጽዓት ሞተን ትንሣኤ ዘለክብር እንነሳለን ‹‹ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግስት ሊወርሱ አይችሉም የሚበሰብሰውም የማይበሰብሰውን አይወርስም›› 1ቆሮ 15፡50 ተብሎ ተጽፏልና፡፡ ጌታችን ይህንን የነገረ ምጽዓት ትምህርት ያስተማረው በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሲሆን (ማቴ 24፡3) ቅድስት ቤተክርስቲያንም ጌታችን በደብረ ዘይት ዓለምን ሊያሳልፍ እንደሚመጣ ተስፋ ታደርጋለች ታስተምራለች፡፡ ይህም የነቢዩ የዘካርያስን ትንቢት መሠረት በማድረግ ነው፡፡
‹‹በዚያም ቀን እግሮቹ በኢየሩሳሌም ትይዩ በምሥራቅ በኩል ባለው በደብረዘይት ላይ ይቆማሉ ደብረዘይትም በመካከል ወደ ምሥራቅና ወደ ምዕራብ ይሰነጠቃል›› (ዘካ 14፡4)
ደብረ ዘይት ማለት የቃሉ ትርጉም የዘይት ተራራ ማለት ሲሆን ተራራው የወይራ ዛፎች በብዛት ስላሉበት ይህንን ስያሜ አግኝቷል፡፡ ይህ ተራራ ከባሕር በላይ 800 ሜትር ያህል ከፍታ ያለው ሲሆን ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ በቅርብ የሚገኝ ተራራ ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ቀን በኢየሩሳሌም ከተማዎች እየተዘዋወረ ሲያስተምር ይውላል ማታ ሲመሽ በደብረ ዘይት ተራራ ከሚገኘው የኤሊዎን ዋሻ ገብቶ ያድር ነበር፡፡ (ሉቃ 21፡37-38)
ከዚህም የተነሣ ነበረ ክርስቶስ የምጽዓትን ዋዜማ ፣ የዓለምን መጨረሻ ምልክትንና ለፍርድ ተመልሶ የመምጣቱን ምስጢር በደብረ ዘይት አቀበት እንዲህ ሲል በዝርዝር ያስተማረው:-
1.  ብዙ ሐሰተኞች ነቢያቶች ይነሳሉ
በመቅደሱም ትይዩ በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ ጴጥሮስና ያዕቆብ ዮሐንስም እንድርያስም ንገረን ይህ መቼ ይሆናል? ይህስ ሁሉ ይፈጸም ዘንድ እንዳለው ምልክቱ ምንድን ነው? ብለው ለብቻቸው ጠየቁት ኢየሱስም መልሶ እንዲህ ይላቸው ጀመር ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ›› (ማር 13፡6) ብዙዎች ስተው የሚያስቱ መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኀይል የማያውቁ በንባብ የሞቱ ግብዞች መምህራን ይነሳሉ፡፡ (ማቴ 22፡29) መጻሕፍትን ያጣምማሉ ሳይላኩ ተላክን ፣ ሳይማሩ ተማርን ማስተዋላቸው የተወሰደ ዝናብ የሌለባቸው ደመናዎች ናቸው ‹‹በእነዚያ ዘንድ ለማስተዋል የሚያስቸግር ነገር አለ ያልተማሩትና የማይጸኑትም ሰዎች ሌሎችን መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ እነዚህ ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ›› (2ጴጥ 3፡16) ለማሳሳትና ወደ ጥፋት ለመውሰድ ቀንና ሌት በክፋት ይሰራሉ፣ መማለጃንና ጉቦን በመስጠት በጭብጥ ገብስና በቁራሽ እንጀራ በተገኘው ደካማ ጎን ሁሉ በመግባት የስህተት ትምህርታቸውን ለማሰራጨት ይተጋሉ፡፡ ከዚህም የተነሣ በትጋት ሐዋርያትን ለመምሰል ይሰራሉ ‹‹እንደዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸውን እየለወጡ ውሸተኞች ሐዋርያትና ተንኮለኞች ሠራተኞች ናቸው›› (2ቆሮ 11፡13) ጌታችንም ብዙዎች እኔ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና ብዙዎችንም ያስታሉ (ማር 13፡7) እንዳለ በተለያየ ዘመን እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ የተነሱ አሉ ከነዚህም መካከል ለአብነት በ1978 እ.ኤ.አ ዲቪድ ኮርሽ የሚባል እኔ ክርስቶስ ነኝ ብሎ ተነስቶ ብዙዎችን አስቷል፣ እንዲሁም በአሜሪካን ሀገር በፍሎሪዳ ግዛት የሚኖረው ጆን የተባለው ‹‹የ666›› ተከታይ ሁለተኛ የሚመጣው ክርስቶስ እኔ ነኝ ብሎ እያስተማረ ነው በሚሊዮን የሚቆጠሩትንም አሳስቶ ተከታዮቹ አድርጓል፡፡
አምላካችን ክርስቶስ ቢቻላቸው የተመረጡትን እንኳ ያስታሉ (ማቴ 24፡23) ይላልና ፣ ጳጳሳት ፣ ካህናት መምህራን ሊስቱ ይችላሉና መጽናት ይገባል፡፡ ‹‹በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን ትጠብቋት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመበት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ›› (ሐዋ 20፡28) ተብሏልና ተግተን እንጸልይ፡፡
ብዙዎች በከንቱ ልፍለፋ ዕውቀት አለን በማለት የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ ሐይማኖትን ይክዳሉና ሐዋርያት ከዚህ ጠማማ ትውልድ ዳኑ ብለው ከማስተማራቸውም ባሻገር ልዩ ልዩ በሆነ እንግዳ ትምህርት አትውሰዱ ኢየሱስ ክርስቶስ ትላንትና ዛሬ እስከዘላላም ያው ነው (ዕብ 13፡7 ፣ ሐዋ 2፡40 ፣ 1ጢሞ 4፡1) እንደ ስህተት ሽንገላ ባለ ተንኮል በሰዎች ማታለል ምክንያት በትምህርት ነፍስ እየተፍገመገምን ሕፃን መሆን አይገባንም ይልቁንም ጸንተን ሃይማኖታችንን መጠበቅ ይገባናል፡፡ (ኤፌ 4፡14 ፣ ዕብ 4፡14)




2.   ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ
‹‹ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጨረሻውን ዘመን ዋዜማ ምልክት በመቀጠል ሕዝብ በሕዝብ ላይ ይነሳልና›› (ማቴ 24፡6) ሀገር በሀገር ላይ ፣ ብሔር በብሔር ላይ ፣ ወገን በወገን ላይ በተለያየ ምክንያት በክፋት ይነሳል ጦርንም ያውጃል፡፡ ስለዚህም ጌታችን ‹‹ጦርንም የጦርንም ወሬ በሰማችሁ ጊዜ አትደንግጡ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ነገር ግን መጨረሻው ገና ነው›› (ማር 13፡7) በማለት አስተምሯል፡፡ ለጊዜው ሮማውያን በሮማውያን አይሁድ በአይሁድ ላይ ተነስተዋልና ፍጻሜው ግን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በነገድ፣ በጎሳ፣ በቆዳ ቀለም የሚሆነውን ጸብና ክርክር፣ አምባጓሮና ጦርነት ሲገልጽ ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ ነቢዩ እንዳለው ‹‹ጥፋት መጥቷል ሰላምንም ይሻሉ እርሱም አይገኝም ድንጋጤ በድንጋጤ ላይ ይመጣል ወሬም ወሬውን ይከተላል ከነቢይም ዘንድ ራዕይን ይሻሉ ከካህኑም ዘንድ ትምህርት ከሽማግሌዎችም ዘንድ ምክር ይጠፋል›› (ሕዝ 7፡25) ይህንንም በዕለት ተዕለት ኑሮአችን እየተመለከትን ነው፣ የመገናኛ ብዙኀን የሚያወሩት ሁሉ የሚያስደነግጥ የሚያሸብር ነው ራዕይን ፈላጊዎች ብዙ ናቸው፣ ምክርን የሚሹ በርካታ ናቸው ነገር ግን መጨረሻው ዘመን የሚያስጨንቅ ይሆናል ሰዎች ራስ ወዳድ፣ ትዕቢተኞች፣ ቅድስና የሌላቸው ስለሚሆኑ በጎ ነገር አይገኝባቸውም፡፡
ራዕይ ከሌለ ፣ መካሪ ሽማግሌ ከሌለ ሕዝብ መረን ከመሆኑም ባሻገር ሕዝብ በሕዝብ ላይ ሲነሳ ሰላም ሲጠፋ ሠርቶ መብላት ወልዶ መሳም ወጥቶ መግባትም የለም (ምሳ 29፡18) ሥርዓት አልበኝነት፣ ሥር አጥነት፣ ድኅነትና ረኃብ በሀገርና በወገን ላይ ይጸናል፡፡ በመሆኑም ከክፉው ዘመን ማምለጫው መርከብ ጾምና ጸሎት ነውና ተግተን እንጸልይ፡፡   
3.   በክርስቲያኖች ላይ ፈተና ይመጣል
በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል ይገድሏችሁማል ስለስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ (ማቴ 24፡9) ለጊዜው ደቀመዛሙርቱ በስሙ ስላስተማሩ ተአምራቱን ስላደረጉ ዕውራን ስላበሩ ለምጻም ስላነጹ መከራ ይመጣባችኋል ፈተና ይመጣባችኋል ሲላቸው ነው ፍጻሜው ግን እኛም ከዚያ በኋላ እስከዘመኑ ፍጻሜ ለምንነሳ ክርስቲያኖች በስሜ ስለምታምኑ ፣ ስለምታስተምሩ ፣ ስለምትማሩ መከራ አለባችሁ፡፡ ‹‹እንዳትሰናከሉ ይህን ተናግሬአችኋለሁ ከምኩራባቸው ያወጧችኋል ከዚህ በላይ ደግሞ የሚገድላችሁ ሁሉ እግዚአብሔርን እንደሚያገለግል የሚመስልበት ጊዜ ይመጣል›› (ዮሐ 16፡2)
ቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ ወንጌል ስለሰበከ ስለክርስቶስ ስለመሰከረ በድንጋይ ወግረው ገድለውታል፣ ሐዋርያትንም ያዕቆብን ጳውሎስን፣ ቶማስን፣ ታዲዎስን ፣ ጴጥሮስን መከራ አጽንተው ገድለዋቸዋል የተቀሩትንም አሳደዋቸዋል፡፡
ዛሬስ በቤተክርስቲያን ላይ የጥፋት ዘመን አልሆነም እንዴ ከዘመነ ሐዋርያት እስከ አራተኛው ክፈለ ዘመን ዋዜማ ቤተ ክርስቲያን በብዙ መከራ አልፋ በሰማዕታት ደም አንዳሸበረቀች ዛሬም ተቃዋሚዎች አሕዛብ በቤተክርስቲያን ላይ ፈተናውን በማጽናት በግብፅ፣ በየመን፣ በሦሪያ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች አቢያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል፣ ንዋያተ ቅዱሳት ተመዝብረዋል ይህም የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡
በግብፅ ብቻ ከ20 በላይ ታሪካዊ ጥንታዊ አብያተክርስቲያናት ሲቃጠሉ አይተናል በሀገራችንም በኢትዮጵያ ከዮዲት ጉዲት እስከ ግራኝ መሐመድ እንዲሁም ላለፉት አስርት ዓመታት አቢያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል ቅርሶች ተመዝብረዋል ክርስቲያኖች በግፍ ታርደዋል ካህናት ሳይቀር በመቅደስ ውስጥ የዘካርያስ ዕጣ ፈንታ ደርሷቸዋል አሁንም የጥፋት ዘመን ሆኗል፡፡ ሕንጻ እግዚአብሔር በርኩሰት በግብረሰዶም በዝሙት እየተቃጠሉም ነው ነገር ግን ሐዋርያው ጳውሎስ አትፍሩ ይለናል ‹‹በአንድ ነገር እንኳ በተቃዋሚዎች አትደንግጡ ይህ ለእነሱ የጥፋት ለእናንተ ግን የመዳን ምልክት ነው ይህም ከእግዚአብሔር ነው ይህ ስለክርስቶስ ተሰጥቷችኋልና ስለ እርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም›› (ፊልጵ 1፡28) በማለት እንዳስተማረ ፈተና መከራ ይመጣ ዘንድ ግድ ስለሆነ ጽናቱን ብርታቱን ማለፊያውን መንገዱን ይሰጠን ዘንድ ተግተን እንጸልይ፡፡
4.  ከዓመፃ ብዛት የተነሳ ፍቅር ትቀዘቅዛለች
‹‹በዚያን ጊዜም ብዙዎች ይሰናከላሉ እርስ በእርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ፣ እርስ በእርሳቸውም ይጣላሉ ከዓመፃም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች›› (ማቴ 24፡10) መጻሕፍት ከሚያስረዱት ሰባኪ ከሚናገረው በላይ ፍቅር ከመቀዝቀዝ አልፎ በረዶ ሆኖአል ማለት ይቻላል፣ ዓለማውያኑን ያለመኑትን ሳይሆን ክርስቲያን ነን አምነናል አውቀናል በምልነው መካከል መለያችን መታወቂያችን እርስ በእርስ መበላላት ጸብ ክርክር መፈራረድ እየሆነ ነው፡፡
የቀደሙት ክርስቲያኖች እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው እንደኖሩ በመጽሐፍ ተጽፎ እናነባለን ‹‹ያመኑትም ሕዝብ አንድ ልብ አንዲትም ነፍስ ነበሩአቸው ገንዘባቸውም ሁሉ በአንድነት ነበረ እንጂ ካለው አንድ ነገርስንኳ የራሱ እንደሆነ ማንም አልተናገረም›› (ሐዋ 4፡32) ዛሬ ግን ቤተክርስቲያናችን በሁለት ሲኖዶስ ከሆነች ዓመታትን አስቆጠረች በውስጥ ያለነውም ፍቅር አጥተን አንዱ አንዱን እየተቸ እርስ በእርስ እየተናቆርን የጠላት መሳለቂያ ከሆን የጋዜጣና የመጽሔት ማሻሻጫ ከሆን ሰንብተናል፡፡
አሁንም ትንቢቱ ሳይፈጸምብን ጊዜ ሳይመሽብን የዋዜማው ምልክት ሳንሆን በንስሐ ተመልሰን የፈረሰውን እንስራ በሌላው ‹‹ወንድምም ወንድሙን አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፣ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ ይነሳሉ ይገድሏቸውማል›› (ማር 13፡12) ወንድሙን የሚጠላ ነፍሰ ገዳይ ከመሆኑም ባሻገር ፍቅር የሌለው እግዚአብሔር የለውም በመጽሐፍ ቢቻላችሁስ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነው ይለናልና እርስ በእርሳችን በፍቅር እንሁን፡፡
5.  የመንግስቱ ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል
ለጊዜው ደቀመዛሙርቱ ወንጌልን ከዓለም ጫፍ እስከ ዓለም ጫፍ ይሰብካሉና ከዚህም በኋላ ኢየሱስ ራሱ ለዘላለም ደኅንነት የሆነውን የማይለወጠውን ቅዱስ ወንጌል ከፀሐይ መውጫ እስከ ፀሐይ መጥለቂያ ድረስ በእጃቸው ላከው›› (ማር 16፡8)
ፍጻሜው ግን ከዘያ በኋላ የተነሱት ፈለገ ሐዋርያትን የተከተሉ ሊቃውንት ክርስቲያኖች ወንጌልን በዓለም ሁሉ ይሰብካሉና፣ ወንጌል በአሕዛብም ሳይቀር በአንድም ሆነ በሌላ ይሰበካል፡፡
ከዚህ በኋላ አንባቢው ያሰተውል አለ ጌታ በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋትን ርኩሰት በተቀደሰችው ሥፍራ ቆሞ ስታዩ የጊዜውን መድረስ አስተውሉ ‹‹ከእርሱ ጋር ይቆማሉ መቅደሱንም ግንቡንም ያረክሳሉ የዘወትሩንም መስዋዕት ያስቀራሉ የጥፋትንም ርኩሰት ያቆማሉ›› (ማቴ 24፡15 ፣ ዳን 11፡31) ያችን ቀን ግን ከአባት በቀር ማንም አያውቃትም ‹‹የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምጽ ያልፋሉ የሰማይ ፍጥረት በትልቅ ትኩሳት ይቀልጣል ምድርም በእርሷ ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል›› (2ጴጥ 3፡10)
ይህ ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ የመምጣቱ ዋዜማ ምልክቶች ናቸውና ማንም በማናቸውም መንገድ አያስታችሁ ክህደቱ አስቀድሞ ሳይመጣና የአመጽ ሰው እርሱም የጥፋት ልጅ ሳይገለጥ አይደርስምና በመሆኑም ጌታችን ክርስቶስም እንዲህ ሲል አሳሰበን ‹‹በዚያም ቀን በሰገነት ያለ በቤቱ ያለውን ዕቃ ሊወስድ አይውረድ እንዲሁም በእርሻ ያለው ወደ ኋላው አይመለስ ያን ግን ዕወቁ ባለቤት ከሌሊቱ በየትኛው ክፍል ሌባ እንደሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ በነቃ ቤቱም ሊቆፈር ባልተወም ነበር ስለዚህ እናንተም ተዘጋጅታችሁ ኑሩ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና›› (2ተሰ 2፡3 ፣ ሉቃ 17፡31 ፣ ማቴ 24፡43)
ንስሐ ገብታችሁ ተዘጋጅታችሁ ምግባርን ከሃይማኖት አስተባብራችሁ ያዙ በመጽሐፍ ወገባችሁ የታጠቀ መብራታችሁም የበራ ይሁን እንዲል ነቅታችሁ ጠብቁ፣ ለክፉዎች ለአመጸኞች ቀኖቹ ክፉዎች አስፈሪዎች ናቸውና፡፡
‹‹ጌታስ ወራቶቹን ስለተመረጡት ባያሳጥር ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነገር ግን ቀኖቹ ስለተመረጡት ያጥራሉ›› (ማር 13፡20)
ከዚህም በላይ ምሳሌውን ከበለስ ተማሩ ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቆጠቁጥ ያን ጊዜ በጋ እንደቀረበ ታውቃላችሁ እንዲህ እናንተ ደግሞ ይህን ሁሉ ስታዩ በደጅ እንደቀረበ እወቁ እውነት እላችኋለሁ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም ሰማይና ምድር ያልፋል ቃሌ ግን አያልፍም›› (ማቴ 24፡32)
ከዚህ በኋላ ‹‹ከክብሩ ውበት ከጽዮን እግዚአብሔር ግልጥ ሆኖ ይመጣል አምላካችን ይመጣል ዝምም አይልም እሳት በፊቱ ይነዳል›› በኀጥአን ይፈርዳል ለጻድቃን ይፈረዳል፣ የዚያን ጊዜ ሁሉ በፊቱ የተራቀተ ይሆናል በምድር ዋይታ ይበዛል የወጉትም ሁሉ ያዩታል፡፡ (መዝ 49፡2-9 ፣ ራዕ 7፡1)
‹‹ጌታ ሆይ በመጣህ ጊዜ በመንግስትህ አስበን››
አሜን

No comments:

Post a Comment