‹‹ስለ መተላለፋችን ቆሰለ
ስለ በደላችንም ደቀቀ›› ኢሳ 53፡6
ባለፈው ጊዜ
የነቢዩ የኢሳይያስን መጽሐፍ መሠረት አድርገን የጌታችንን የመድኀኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ሕማም መከራ መስቀል ለማየት ጀምረን
ነበር፡፡ እሱ ጥልቅ በሆነ ፍቅሩ ስለወደደን መተኪያ በሌላት ነፍሱ ተወራርዶ አዳነን፣ ነቢያት በትንቢት መጽሐፋቸው፣ ሐዋርያት በስብከታቸው
ስለ ፍቅር አስተምረዋል እሱ ግን ፍቅርን በተግባር ገለጠው፣ እጆቹንና እግሮቹን በመስቀል አስቸነከረ ይህን ያህልም እወዳችኋለሁ
ብሎ ነፍሱን ሰጠ፣ ፍቅርንም በተግባር ሰበከ እኛም አርአያውንና ፈለጉን እንከተል ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነውና፡፡ በፍቅር እንሁን…..ብለን
ነበር ክፍል አንድን የፈጸምን ቀጣዩን ክፍል ደግሞ ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ አድርገን ጀመርን፡፡
ከትንሳኤ በፊት
ያለው ሳምንት በቤተ ክርስቲያናችን ሰሙነ ሕማማት በመባል ይታወቃል፡፡ ይኸውም በነቢዩ በኢሳይያስ ‹‹ነስአ ደዌነ ወፆረ ሕማምነ››
‹‹በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸከመ እኛ ግን እንደተመታ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሰፈ እንደተቸገረም ቆጠርነው
እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቆሰለ ስለበደላችንም ደቀቀ፣ የደኅንነታችንም ተግሳጽ በእሱ ላይ ነበረ በእሱም ቁስል እኛ ተፈወስን፡፡››
(ኢሳ 53፡4-6) ተብሎ የተጻፈው ትንቢት ተፈጽሞ፣ ጌታችን በስሞነ ሕማማት ውስጥ ለድኅነተ ዓለም ሲል ከሰማያዊ ዙፋኑ ዝቅ ብሎ
፣ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ የተቀበለውን ጻዋትወ መከራ ለማዘከር የወጣ ስያሜ ነው፡፡ በስሞነ ሕማማት ውስጥ ካህናትና
ምዕመናን በአጸደ ቤተክርስቲያን ተሰብስበው ከእህል ከውኃ ተከልክለው እንዲሁም ከነገርና ከኅጢዓት ርቀው፣ የሕማሙን ነገር የሚያወሳውን
ዜማ ሲያዜሙ፣ ግብረ ሕማም በመባል የሚታወቀውን መጽሐፍ ሲያነቡ፣ ሲሰግዱና ሲጸልዩ ይሰነብታሉ፡፡ ይህም ከላይ እንደተመለከትነው
ጌታችን ስለ እኛ ሲል ቆሰለ፣ በእርሱም ቁስል እኛ ተፈወስን ሲሉ ነው፡፡
የድኅነታችን
ነገር የተረጋገጠው በዚህ ሳምንት ነውና፡፡ በስሙነ ሕማማት መስቀል መሳለም (መሳም)፣ እርስ በእርስ መሳሳም የለም ይህም ይሁዳ
ጌታን በመሳም አሳልፎ እንደሰጠው ለማሰብ ነው፡፡
በስሙነ ሕማማት
ውስጥ ያሉትን ዕለታት ሊቃውንት ከጌታ መከራ ጋር በማመሳጠር ስያሜና ትርጓሜ ሰጥተዋቸዋል፡-
1. ሰኞ
ይህ ዕለት አንጽሆተ
ቤተመቅደስና መርገመ በለስ የተፈጸመበት ዕለት ነው፡፡ የሆሳዕና ዕለት ቢታኒያ ያድራል በማግስቱም ከቢታኒያ ሲመጣ ተራበ (ማር
11፡11-12) ቅጠል ያላት በለስ ከሩቅ አይቶ ወደ በለሲቱ ቀረበ ነገር ግን ከቅጠል በቀር አንዳች ፍሬ አላገኘባትም ከአሁን ጀምሮ
ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ ብሎ ረገማት፣
በለስ የተባለች
ቤተ እስራኤል ናት፣
ፍሬ የተባለች ሃይማኖትና ምግባር ናት ጌታ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከእስራኤል ተወለደ ሰው ሆኖ መጥቷልና፣ ቀድሞ የበኩር ልጄቼ ካላቸው ከእስራኤል ፍቅርን ሃይማኖትን ምግባርን ፈለገ አላገኘም፤ እስራኤል (ሕዝበ እግዚአብሔር መባልን እንጂ ደግ ሰው አይገኝብሽ ብሎ ረገማት በመርገሙ ምክንያት እርሱ ከለያቸውና ከመረጣቸው በስተቀር ደግ ሰው ጠፋበት)
ፍሬ የተባለች ሃይማኖትና ምግባር ናት ጌታ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከእስራኤል ተወለደ ሰው ሆኖ መጥቷልና፣ ቀድሞ የበኩር ልጄቼ ካላቸው ከእስራኤል ፍቅርን ሃይማኖትን ምግባርን ፈለገ አላገኘም፤ እስራኤል (ሕዝበ እግዚአብሔር መባልን እንጂ ደግ ሰው አይገኝብሽ ብሎ ረገማት በመርገሙ ምክንያት እርሱ ከለያቸውና ከመረጣቸው በስተቀር ደግ ሰው ጠፋበት)
በለስ ኦሪት ናት
እሱ ከልዕልና
ወደ ትህትና ሥጋ ለብሶ ሰው ሆኖ ሲመጣ ኦሪትን በዚህ ዓለም ሰፍና ቢያገኛት፤ ኦሪትና ነቢያትን ልሽር አልመጣሁም ልፈጽም እንጂ…(ማቴ
5፡17) በማለት ፈጸማት ሕገ ኦሪትን ከመፈጸም በቀር በእርሷ ድኅነት አላደረገባትምና ፍሬ ባንቺ አይሁን አላት፣ ድኅነት በአንቺ
አይደረግብሽ ብሏታልና እንደመድረቅ ፈጥና አለፈች፡፡
በለስ ኃጢዓት ናት
ጌታችን የባሕርይ
ክብሩን ትቶ ነውር ነቀፋ ሳይኖርበት፣ ኃጢዓት በደል ሳይገኝበት ወደ ውርደት ሞት (የመስቀል ሞት) ሲመጣ የበለስ ቅጠል ሰፊ አንደሆነች
ሁሉ ኃጢዓት በዚህ ዓለም ሰፍታ ሰፍና አገኛት፡፡ በለስ ሲበሉት ይጣፍጣል ቆይቶ ግን ይመራል፤ ኃጢዓትም ሲሰሩት ደስ ደስ ያሰኛል
ኋላ ግን ያሳዝናል፤ ወደ እርሷም ሄደ (ከኃጥአን ጋር ዋለ) ነገር ግን ኀጥእ ከመባል በቀር በመዋሉ ኃጢዓት አለመስራቱን ለማመልከት
ፍሬ አላገኘባትም አለ፤ በአንቺ ፍሬ አይገኝ የሚለውም፣ በኀጢዓት ፍዳ ተይዞ የሚቀር አይኑር ለማለት ነው፡፡ ስትረገም ፈጥና መድረቋም፤
በአዳም ምክንያት ያገኘችን ዕዳ በደል በእርሱ እንደጠፋችልን ለመግለጽ ነው፡፡
ከዚህ ቀጥሎ
ወደ ቤተ መቅደስ ሄደ፤ ቤተ መቅደስ ቤተ ጸሎት፤ ቤተመስዋዕት መሆኑ ቀርቶ ቤተምስያጥ (የንግድ ቤት) ሆኖ ቢያገኘው፤ ቤቴ የጸሎት
ቤት ትባላለች እናንተ ግን የወንበዶዎች ዋሻ አደረጋችኋት ብሎ የሚሸጡበትን ሁሉ ገለበጠባቸው ገርፎም አስወጣቸው ይህም የሚያሳየው
ማደሪያው ቤቱ የነበርነው የአዳም ልጆች ኃጢዓት ሰፍኖብን ስንኖር ቢያገኘን ኃጢዓታችንን ሁሉ እንዳራቀልን የሚገልጽ ነው፡፡
በዚህ በስሙነ
ሕማማት ካህናትና ምዕመናን በቤተ ክርስቲያን ተገኝተው ወዛቸው ጠብ እስኪል ድረስ በነግህ፣ በስልስት፣ በስድስቱ ሰዓትና፣ በተሰዓቱ
ሰዓት መላልሰው ሲሰግዱና ሲጸልዩ ይሰነብታሉ፣ በተለይም ካህናት በማንኛውም አገልግሎት ጥቁር ልብስ ይለብሳሉ ምክንያቱም የደረሰበትን
መከራ ሐዘኑንና ፭ሺህ ፭ መቶ ዘመን የሰው ልጅ በጨለማ ሕይወት ውስጥ ይኖር እንደነበር ለማዘከዘር ይህን ያደርጋሉ፡፡
2. ማክሰኞ (የጥያቄ ቀን በመባል ይታወቃል)
ይኸውም የሆነበት
ምክንያት ሹመትን ወይም ስልጣንን ለሰው ልጅ ሰጠ ጌታችን ፣ ሰኞ ባደረገው አንጽሐተ ቤተመቅደስ ምክንያት በዚህ ዕለት ስለ ሥልጣኑ
በጻሐፍት ፈሪሳውያን ተጠይቋል ነው፡፡
ጥያቄውም ከምድራውያን
ነገስታት ከሌዋውያን ካህናት ያይደለህ ትምህርት ማስተማር፣ ተአምራት ማድረግ፣ ገበያ መፍታትን በማን ሥልጣን ታደርጋለህ? ይህንስ ስልጣን
ማን ሰጠህ? የሚል ነበር፡፡
(ማቴ 21፡23-27 ፣ ማር 11፡27-33 ፣ ሉቃ 20፡1-8) ጌታም መልሶ እኔም አንድ ነገር እጠይቃችኋለሁ እናንተም ብትነግሩኝ
በማን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ እነግራችኋለሁ፣ የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነበረች ከሰማይ? ወይስ ከሰው? አላቸው፤ እነሱም
ከሰማይ ብንል ለምን አልተቀበላችሁትም ይለናል፣ ከሰው ብንል ሕዝብ ሁሉ ዮሐንስን እንደ አባት ያከብሩታል፣ እንደ መምህርነቱ ይፈሩታልና
ሕዝቡን እንፈራለን ተባብለው ከወዴት እነደሆነ አናውቅም ብለው መለሱለት፣ እርሱም እኔም በማን ሥልጣን እነዚህን እንደማደርግ አልነግራችሁም
አላቸው ይህንንም መጠየቃቸው እርሱ የሚያደርጋቸውን ሁሉ በራሱ ስልጣን እንደሚያደርግ አጥተውት አልነበረም፣ ልቡናቸው በክፋትና በጥርጥር
ስለተሞላ ነው እንጂ፡፡
ጌታ ከፈሪሳውያን
እርሾ ተጠበቁ እንዲል (ማቴ 16፡7) እንደ ፈሪሳውያን ከክፋት ከጥርጥር መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡
በዚህ ዕለት
በቤተመቅደስ ረጅም ትምህርት ስላስተማረ የትምህርት ቀንም ይባላል፡፡ ይኸውም ከሃይማኖት የራቁትን ከፍቅረ እግዚአብሔር የተለዩትን
አስተምሮ ማቅረብ መክሮ መመለስ እንደሚገባን ሲገልጽልን ነው፡፡ (ማቴ 21፡28 ፣ ማቴ 25፡46 ፣ ማር 12፡2 ፣ ማር 13፡37
ሉቃ 20፡9 ፣ ሉቃ 21፡38) በዚህ ሳምንት ክርስቲያን የሆነ ሁሉ ከሥጋዊ ነገር ርቆ የሃይማኖት ትምህርት ሲማር ሲጠይቅ መሰንበት
ይገባዋል፡፡
3. ረቡዕ (የምክር ቀን)
ይህ ዕለት የምክር
ቀን ይባላል፣ ምክንያቱም የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጻሕፋት ጌታን እንዴት መያዝ እንደሚገባቸው ምክር የጀመሩበት ወይም የያዙበት
ቀን ስለሆነ ነው፡፡ ወቅቱ አይሁድ የፋሲካ በዓላቸውን የሚያከብሩበት በመሆኑና ብዙ ሕዝብም በጌታችን ትምህርት የተማረከ ተአምራቱንም
የሚያደንቁ ስለነበር ምናልባት ሁከት ይፈጠራል ብለው በክፉ ምክራቸው እጅግ ተጨንቀው ሳለ ከደቀመዛሙርቱ መካከል አንዱ የሆነው የአስቆሮቱ
ይሁዳ በክፉ ምክራቸው በመሳተፍ ጌታን በመሳም አሳልፎ እንደሚሰጣቸው ቃል ስለገባላቸው ጭንቀታቸው ተወገደ ለወረታውም ሰላሣ ብር
መዘኑለት (ማቴ 26፡1-5 ፣ ማቴ26፡14-15 ፣ ማር 14፡1-2፣ ሉቃ 22፡1-6)
የሐዲስ ኪዳን
ካህናትና ምዕመናን በዚህ ዕለት በቤተክርስቲያን ተሰብስበው ከእህል ከውሃ ተለይተው መላ ሰውነታቸውን ለእግዚአብሔር አስገዝተው የሞት
ፍርዱን በማሰብና በማልቀስ፣ ስለዚህ የሚያወሳውን ሁሉ በመዘመርና በማንበብ እንዲሁም እስከ ስርቀተ ኮከብ (እስከ ኮከብ መውጫ)
በመጾም በጸሎትና በስግደት ተወስነው ይሰነብታሉ፡፡
መልካም መዓዛ ያለው ቀን
ይህ ዕለት
(ረቡዕ) መልካም መዓዛ ያለው ቀንም ይባላል፣ ምክንያቱም ጌታችን
በዚህ ዕለት በቤተ ስምዖን ዘለምጽ ተቀምጦ ሳለ መላ ሕይወቷን ለዝሙት አስገዝታ ትኖር የነበረችው ማርያም እንተ እፍረት ከእንግዲህ
ወዲህ በኅጢዓት ተበላሽቶ ይኖር የነበረውን ሕይወቴን እንደዚህ መልካም ሽቱ የሚያጣፍጥ፣ ኀጢዓትን ይቅር የሚል አምላክ መጣ ስትል
ዋጋው እጅግ በጣም ውድ የሆነ ከሦስት መቶ ዲናር በላይ የሚያወጣ፣ በአልባሲጥሮስ ብልቃጥ የሞላ ሽቱ ይዛ በመሄድ በጠጉሩ (በራሱ)
ላይ በማርከፍከፍ ስለቀባቸው ነው፡፡
የእንባ ቀን ይባላል
ይህም ስያሜ
የተሰጠበት ምክንያት ይህችው ማርያም እንተእፍረት በጌታችን እግር ላይ ተደፍታ መላ ኃጢዓቷን ይቅር እንዲልላት በእንባዋ እግሩን
አጥባዋለችና፣ በጠጉሯም በእንባዋ ያጠበችውን እግሩን አብሳዋለችና፡፡ (ማቴ 26፡6-13 ፣ ሉቃ 7፡36 ፣ ማር 14፡3-9 ፣ ዮሐ
12፡1-8)
የማርያም እንተእፍረትን
ኃጢዓት ይቅር ብሎ መባዋን የተቀበለ አምላክ ዛሬ በመካከላችን አለና በማንኛውም ጊዜና ሰዓት የራሳችንን ኃጢዓት በማሰብ በማልቀስና
የተወደደ መስዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር በማቅረብ በመልካም ሥራዋ ልንመስላት ይገባል፡፡
4. ሐሙስ
በሰሞነ ሕማማት
ከስቅለትና ከትንሣኤ በፊት ያለው ሐሙስ በቤተክርስቲያን የተለያዩ ስያሜዎች አሉት፡፡
·
ጸሎተ ሐሙስ
ይባላል
በፍጥረታት የሚለመንና
የሚመሰገን አምላክ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚለምንና አላዋቂ የሆነውን ሥጋ የተዋሐደ አምላክ፣ ፍጹም ሰውም መሆኑን ለመግለጥና
ለአርያነት ጠላቶቹ መጥተው እስኪይዙት ድረስ በጌተሰማኒ በአታክልቱ ሥፍራ ሦስቱን የምስጢር ሐዋርያት ይዞ ሲጸልይ በማደሩ ምክንያት
ይህ ዕለት ጸሎተ ሐሙስ ተብሏል፡፡ (ማቴ 26፡36-46 ፣ ዮሐ 17)
·
ሕፅበተ ሐሙስ
ይባላል
የነገስታት ንጉሥ
አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም ፣ መጥቶ ሲያስተምር መምህርነቱን ልዩ ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል ከቃል ይልቅ ተግባር
ይሰብካልና የተግባር መምህር በመሆን አርአያ መሆኑ ነው፡፡ በዚህ ዕለት መምህራቸው ሆኖ ሳለ ክርስቶስ በአጭር ታጥቆ አደግድጓ ወገቡን
አስሮ የደቀመዛሙርቱን እግር ያጥብ ዘንድ በትህትና ዝቅ አለ፡፡
ይህም የሚያሳየው
ከትህትናው ባሸገር የዓለምን ኃጢዓት ለማጠብ የመጣ መሆኑን ነው ‹‹ነዋ በግዑ ለእግዚአብሔር ዘያአትት ኃጢዓተ ዓለም›› ተብሎ እንደተጻፈ፡፡
ይህንን ለማስታወስ ዛሬም ካህናት በተለይም ሊቃነ ጳጳሳትና የደብር አስተዳዳሪዎች በመካከላችን ተገኝተህ የእኛንና የሕዝብህን ኃጢዓት
እጠብ ሲሉ በዕለቱ በአጸደ ቤተክርስቲያን የተገኙትን ምዕመናንን እግር በወይንና በወይራ ቅጠል ሲያጥቡ ያረፍዳሉ፡፡
·
የምስጢር ቀን
ይባላል
ከሰባቱ ምስጢራተ
ቤተከርስቲያነ አንዱ በዚህ ቀን ተመስርቷል፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምሲተ ሐሙስ ከደቀመዛሙርቱ ጋር ለእራት ተቀመጠ
ህብስቱንም አንስቶ ባርኮ ከቆረሰ በኋላ ‹‹ይህ ስለ እናንተ በመስቀል ላይ ሚቆረሰው ሥጋዬ ነው እንካችሁ ብሉ››፣ የወይኑንም ጽዋ
አንስቶ ‹‹ይህም ስለ እናንተ በመስቀል ላይ የሚፈሰው ደሜ ነው ከእርሱም ጠጡ›› በማለት እኛ ከእርሱ ጋር፣ እርሱ ከእኛ ጋር አንድ
የምንሆንበትን ምስጢረ ቁርባን ከጠላት ዲያብሎስ ሰውሮ ለደቀመዛሙርቱ የገለጠበት ዕለት በመሆኑ የምስጢር ቀን ተብሏል፡፡ በዚህ ዕለት
ቅዳሴ ይቀደሳል የሚቀደሰውም በለሆሳስ ሲሆን እንደቃጭል ሆኖ የሚያገለግለውም ጸናጽል ነው፡፡ ይህም አይሁድ ጌታችንን ለመያዝ ሲመጡ
ድምጻቸውን ዝግ አድርገው፣ በለሆሰስ እየተነጋገሩ መምጣታቸውን ለማሰብ ነው፣ በቅዳሴውም ጸሎተ ተአምሆ፣ ኑዛዜ አይደረግም ሥረዓተ
ቁርባን ግን ይፈጸምበታል፣ ይህም የሆነው ጌታችን የሰጠውን ዘላለማዊ ቃል ኪዳን ለማሰብ ነው በዚዘህ ዕለት ክርስቲያን የሆነ ሁሉ
በንስሐ ታጥቦ ተዘጋጅቶ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን መቀበል ይኖርበታል፡፡
·
የሐዲስ ኪዳን
ሐሙስ ይባላል
ይህንን ስያሜ
ያገኘበት ምክንያት በእንሰሳት ደም የሚቀርበው የኦሪት መስዋዕት ማብቃቱን ገልጦ ለድኅነተ ዓለም ራሱን የተወደደ መስዋዕት አድርጎ
የአቀረበበት ዕለት በመሆኑ ነው፡፡ ‹‹ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው ከእርሱም ጠጡ›› በማለት አዲስ
ኪዳንን መሥርቷል፡፡ (ሉቃ 22፡20)
ኪዳን ማለት
በሁለት ወገን መካከል የሚደረግ ውል፣ ስምምነት መሐላ ማለት ነው በዚህ መሰረት ጌታችን ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ዘላለማዊ ቃል ኪዳን
በራሱ ደም የፈጸመበት ዕለት መሆኑን በማሰብ የቃል ኪዳኑ ፈጻሚዎች ጠባቂዎች መሆን እንደሚገባን እንማራለን፡፡
·
የነፃነት ሐሙስ
ይባላል
በአዳምና በሔዋን
አለመታዘዝ ምክንያት ልጆቻቸው ሁሉ ለ፭ሺህ ፭ መቶ ዘመን የኃጢዓትና የዲያብሎስ ባሪያ ሆነው ይኖሩ ነበረ፡፡ ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ
ክርስቶስ ለኃጢዓትና ለዲያብሎስ ባሪያ ሆኖ መኖር ማብቃት፣ የሰው ልጅ ያጣውን ክብር መልሶ ማግኘቱ የተረጋገጠበት ቀን ስለሆነ የነፃነት
ሐሙስ ተብሏል፡:
ራሱ ጌታችን
ስለሰው ልጅ ነፃነት ሲናገር ‹‹ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም ባሪያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ››
በማለቱ ይህ ዕለት ከባርነት ነጻ የወጣንበት መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስረዳናል፡፡ (ዮሐ 15፡15) ስለዚህም እያንዳንዱ
ክርስቲያን ከኃጢዓት ባርነት ርቆ፣ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያወዳጁትን መልካም ሥራ በመሥራት ሕይወቱን መምራት ይኖርበታል፡፡ እርሱ
ጠላቶቹ ሳለን ወዳጆች አድርጓናልና፡፡
በዚህ ዕለት
ሦስት ዓበይት ነገሮች መከናወናቸውን መጽሐፍ ቅዱስ መዝግቦልናል፡-
-
አይሁድ የፋሲካን ዝግጅት ያደረጉበት ዕለት ነው ፋሲካ ማለት የቃሉ ትርጉም ማለፍ መሻገር ማለት
ሲሆን ይኸውም እስራኤላውያን ከግብፅ የባርነት ቀንበር ተላቀው ወደ ከነዓን ምድር ጉዞ ከመጀመራቸው በፊት በእያንዳንዳቸው ቤት የበግ
ጠቦት እንዲያርዱ ደሙን በመቃናቸው ላይ እንዲቀቡ ሥጋውንም ጠብሰው ወገባቸውን ታጥቀው፣ በትራቸውን ይዘው ፈጥነው እንዲበሉ በታዘዙት
መሠረት ፋሲካንና ደም መርጨትን በእምነት አደረጉ (ማቴ 26፡17-19 ፣ ማር 14፡12-16 ፣ ዘፀ 12፡1-52)
ይህንንም ያደረጉት
ስለ ሁለት ምክንያቶች ነበረ መጀመሪያ አጥፊው የፈርኦናውያንን ግብጻውያንን የበኩር ልጆች ሲያጠፉ የእነሱን እንዳያጠፋ የበጉን ደም
በመቃናቸው ቀብተው ፋሲካን በዕምነት አድርገዋል፣ ሌላው ማርና ወተት የምታፈሰውን ምድረ ርስት ከነዓንን ለመውረስ የበጉን ሥጋ ተዘጋጅተው
በልተው ፋሲካን ማድረግ ነበረባቸውና ነው፡፡
በዚህ መነሻነት
በየዓመቱ እስራኤላውያን በመጀመሪያ ወራቸው በ 14 ኛው ቀን በግ እያረዱ የፋሲካን በዓል ያከብራሉ፡፡ ሀገራችንም አስቀድማ ብሉይ
ኪዳንን የተቀበለች ሀገር እንደመሆኗ ይህ ድርጊት ይፈጸምባት ነበር፡፡
በሐዲስ ኪዳን
ግን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ነው መርገማችን የሻረልን ሞታችንን የሻረልን በመሆኑም ራሱን የተወደደ መስዋዕት አድርጎ ያቀረበ የዋህ በግ ነው፡፡ ሐዋርያው
‹‹ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዷል እንዲል›› 1ቆሮ 5፡6 የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ፋሲካችን ነው፡፡ (1ጴጥ 1፡18)
-
ጌታ ረዥም ትምህርት
አስተምሯል
በዚህ ዕለት
እንደ ማክሰኞ ለደቀመዛሙርቱ ረዥም ትምህርትን አስተምሯል (በዮሐ 14፡17) የትምህርቱም ዋና ዋና ክፍሎች ምስጢረ ሥላሴ (የሦስትነት
ትምህርትና ምስጢረ ሥጋዌ (የአምላክ ሰው መሆን፣ ምስጢረ ትንሣኤ ሙታንና የዳግም ምጽዓት ትምህርት ነው) እነዚህን ትምህርቶች በጥልቀት
መማር እንደሚገባ ሲያስረዳን በተአምራት ሊገለጥላቸው ሲችል በረጅም ትምህርት እንዲረዱት አድርጓል፡፡ ተማሪዎቹም እሱ እያስተማራቸው
ሳለ ያልገባቸውን እየጠየቁ ተረድተዋል፣ እኛም በቤተክርስቲያን ተገኝተን መማርና ያልገባንን ጠይቀን መረዳት እንደሚገባን እንማራለን፡፡
-
ይሁዳ ጌታን
በመሳም አሳልፎ ሰጥቶታል
በዚህ ዕለት
‹‹እንጀራዬን የበላ እሱ ተረከዙን በእኔ አነሳ›› (መዝ 40፡9) ተብሎ እንደተጻፈ የቃሉን ትምህርት ከሰሙና የእጁን ተአምራት
ካዩት ከደቀመዛሙርት መካከል አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ የተባለው ‹‹ጌታ ሆይ መምህር ሆይ›› ብሎ በሽንገላ ጌታውን አሳልፎ የሰጠበት
ዕለት ነው፡፡
ጭፍሮችም በዚህ
ዕለት ሌሊት የክብር ባለቤት የሆነውን ጌታችንን ይዘው ወደ ፊት፣ ወደ ኋላ እየጎተቱ እያዳፉ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ወስደውታል፡፡
(ማቴ 26፡47-58)
5. ዓርብ
የስሞነ ሕማማት
ዕለተ ዓርብ በቤተክርስቲያናችን ልዩ ቀን ነው፡፡ ይህ ቀን ልዩ ነው፣ የማይታመመው ታሞ የዋለበት፣ የወደቁትን ከተረሱበት ከትቢያ
የሚያነሳ እሱ ሲወድቅ ሲነሣ የዋለበት፣ ሕመምተኞችን የሚፈውስ እሱ ሲያቃስት የዋለበት፣ ከሲኦል የዲያብሎስ ግርፋት ነፃ የሚያወጣ
ሲገረፍ የዋለበት ወልደ እግዚአብሔር ለወዳጆቹ ድኅነት በመስዋዕትነት ሙሽራ የሆነበት የደስታ ቀን የዓመፃ መዝገባችን መገልበጡ እርግጥ
የሆነበት ፣ አሳዳጃችን አሳሪያችን ዲያብሎስ ከነወጥመዱ ድል የተነሳበት ቀን ነውና፣ ከዚህም የተነሳ በቤተክርስቲያን የተለያየ ምስጢራዊ
ስያሜዎች ተሰጥቶታል፡፡
የዓለም ሁሉ
መድኀኒት የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ቤዛ ሆኖ በመልዕልተ መስቀል ላይ ተሰቅሎ ለዓለም ድኅነት መስዋዕት
ሆኖ የዋለበት ዕለት በመሆኑ የስቅለት ዓርብ ተብሏል (ማቴ 27፡35)
·
መልካሙ ዓርብ
(GOOD FRIDAY) ይባላል
ይህም የሚያስገነዝበን
ከስቅለተ ክርስቶስ በፊት ማንም ሰው ስያጠፋ በመስቀል ተሰቅሎ እንዲሞት ይደረግ ነበር፡፡ በተለይ በሮማውያንና በፈሪሳውያን ሕግ
መስቀል የወንጀለኞች መቅጫ ነበረ፣ በዚህ ዕለት ግን ታሪክን የሚቀይረው፣ ነገርን የሚገለብጠው አምላክ የወንጀለኞች መቅጫ ምልክት
የነበረውን መስቀል በደሙ ቀድሶ የምህረት ምልክት፣ የሕይወት አርማ፣ የዲያብሎስ ድል መንሻ ፣ የቤተክርስቲያን ጌጥ፣ የገዳማት ዘውድ፣
ስለአደረገውና በዕለተ ዓርብም በሞቱ ሕይወትን ስለአገኘን መልካሙ ዓርብ ተብሏል፡፡
-
በዚህ ዕለት በቤተክርስቲያን በርካታ ሥርዓቶች የሚፈጸሙ ሲሆን ለአብነትም ያህል ሥዕለ ሥነ-ስቅለትና
ልዩ ልዩ የቤተ መቅደስ ንዋያተ ቅድሳት ከቤተ መቅደስ ወጥተው ከመቅደሱ በር ላይ ይደረደራሉ፣ ካህናትና ምዕመናንም ወዛቸው ጠብ
እስኪል ድረስ በነግህ፣ በሠለስት፣ በስድስቱ ሠዓትና በተሰዓቱ ሰዓት መላልሰው ሲሰግዱ ይውላሉ፡፡ ይኸውም ጌታችን እርጥቡን ግንደመስቀል
ተሸክሞ ወደ መሬት ሦስት ጊዜ ወድቆ መነሣቱን ለማሰብ ነው ስለመተላለፋችን መከራን የተቀበልክ አምላክ ይቅር በለን፣ ታረቀን ሰላምን
ስጠን ስድባችንን አርቅልን፣ መርገማችንን ሻርልን በምህረትህ እየን ለማለት መከራውን ለማሰብ ነው፡፡
-
በዘጠኝ ሰዓትም ካህናት በጥቁር ካባ ተሸፍነው ቁጭ ይሉና በሚያሳዝን ዜማ ደጋግመው አቤቱ ይቅር
በለን ይላሉ፣ ሕዝቡንም እንደ እነሱ ያዜማል፣ ይኸውም ነፍሳት በጨለማ ሲዖል ሆነው ለ፭ሺህ ፭ መቶ ዘመን ያሰሙትን ጩኸት ለማዘከር
ነው፡፡
-
በሰሞነ ሕማማት ውስጥ በማሰብ፣ በማየት ፣ በመናገር፣ በገቢር የተፈጸመ ኃጢዓት ቢኖር ምዕመናን
ካህኑ ፊት ቀርበው ይናዘዛሉ ይህም ኃጢዓትን ሁሉ የሚያስተሰርይ ኢየሱስ ክርስቶስ በመልዕልተ መስቀል ላይ ሆኖ የምህረት አዋጁን
ለሰው ልጅ ሁሉ ማሰማቱን ለመግለጥ ነው፡፡
-
እንደዚሁም ከኑዛዜው ጋር ተያይዞ የሚፈጸም ሥርዓት አለ እርሱም ጥብጣቤ ይባላል፡፡ ስንብት ከመደረጉ
በፊት ካህናት የወይራ ዝንጣፊ ይዘው በፊታቸው ቀርቦ የሚናዘዘውን ምዕመን ጀርባ እየጠበጠቡ ይህን ያህል ስገድ እያሉ ያውጃሉ፡፡
ሁሉም የታዘዘውን ይሰግዳል የስግደቱ ትርጉም እንደላይኛው ሲሆን የጥብጣቤው ትርጉም አይሁድ ከሕጋቸው ውጪ እየተፈራረቁ ስድስት ሺ
ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ጊዜ እንደገረፉት ለማሰብ ነው፡፡
በዚህ ዕለት
ጌታችን በመልዕልተ መስቀል ላይ ተሰቅሎ መስዋዕት ሆኖ የዋለበት ስለሆነ ሥርዓተ ቅዳሴ አይፈጸምም፡፡
-
በ 11 ሰዓት ደግሞ ሊቃውንት መቋሚያ ላይ ጧፍ አብርተው ዙሪያውን በመክበብ ከመዝሙረ ዳዊት
የተለያየ ክፍል ያስተዛዝሉና በመጨረሻም ‹‹ለይሁዳ ወልዱ ወለውሉደ ወልዱ ይደምሰስ›› ይሁዳ ልጁም የልጅ ልጁም ይደምሰስ ብለው
በርቶ የነበረውን ጧፍ ቀጥቅጠው ያጠፉታል ጧፍ ሰይጣን በልቡ የገባ የይሁዳ ምሳሌ ሲሆን፣ መቋሚያ ላይ መታሰሩ በክርስቶስ መሠረትነት
ላይ ለሐዋርያነት ለዓለም ብርሃንነት መመረጡን (መቋሚያ የጌታ ምሳሌ ነው)፡፡ ነገር ግን ይህን ክብሩን በማቃለሉ መውደቁን፣ ቀጥቅጠው
ማጥፋታቸው ሰውን ያሳተው ዲያብሎስ በመስቀል ኃይል መመታቱን፣ ድል መነሳቱን ለማዘከር ነው፡፡
-
በቀጠልም ሊቃውንት ‹‹ንሴብሆ ለእግዚአብሔር ስቡሐ ዘተሰብሐ›› የተመሰገነ እግዚአብሔርን እናመሰግናለን
በማለት ይዘምራሉ፣ ይኸም በሞትህ ሞትን ሻርህ ጠላትን ደምስሰህ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከሞት ወደ ሕይወት ከሲዖል ወደ ገነት አገባኸን
ሲሉ ነው፡፡
-
በመጨረሻም ቄጠማውን በመጎናጸፊያ ጠቅልለው ይሸከሙና እግዚኦታ ያደርሳሉ፡፡ ይኸውም ዮሴፍና ኒቆዲሞስ
እንዲህ አድርገው ገንዘው ቀበሩህ ለማለት ነው፡፡ እርጥብ ቄጠማ መሆኑ በኃጢዓት የደረቀውን የሰው ልጅ በሞቱ ያለመለመ ንጹሐ-ባሕርይ
ጌታ ነው ሲሉ አንድም ጌታ ራሱ ‹‹በእርጥብ እንዲህ ያደረቁ በደረቁማ የቱን ያህል?›› እንዲል
በወንጌል ሰላም፣ ዕረፍት፣ ደኅንነት የሆንክ ጌታ ሞትክልን ሲሉ ዮሴፍና ኒቆድሞስ ቅዱስ፣ ቅዱስ እያሉ እንደገነዙት ሊቃውንትም ይህን
ለማዘከር ቄጠማውን በመጎናጸፊያ ይጠቀልሉታል፡፡
የትንሣኤን በዓል
ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም የሚሔዱ ምዕመናን ሁሉ በዕለተ ዓርብ መከራውን ለማሰብ ከቤተ ጴላጦስ እስከ ጎልጎታ መቃብረ ክርስቶስ ድረስ
መስቀሉን ተሸክመው ጎዙ ያደርጋሉ ጉዞ የሚደረግባቸውም 13ቱ ሕማማተ መስቀል የተፈጸመባቸው ቦታዎች ናቸው፡፡
-
በዚህ ዕለት በቤተክርስቲያን ተገኝተው መከራውን በማሰብ ሲሰግዱ የሚውሉ እንዳሉ ሁሉ በአንጻሩ
ደግሞ በስም ክርስቲያን ተብለው ከምንጠራው መካከል፣ ተድላ ደስታ በሚፈጸምባቸው ስፍራዎች ክፉ ሥራ ስንፈጽም የምንውል አንጠፋም፤
እንዲህ የምናደርግ ሁሉ በአለፈው ልንጸጸትና በቀሪ ዘመናችን ልንታረም ይገባል፡፡ በዓመት አንድ ጊዜ የምናገኘው ይህ ዕለት ቀራንዮን
የምናስብበት ነገረ መስቀሉን የምናስተውልበት እንጂ ስለምድራዊ ኑሮአችን ስንባክን ኃጢዓት ስንሰራ የምንውልበት ሊሆን አይገባም፡፡
6. ቅዳሜ
የሰሞነ ሕማማት
ቅዳሜ በዝምታ ድባብ የተዋጠች ሐዋርያት አዝነውና ተጨንቀው እንዳይወጡ የጌታ ወዳጅ ብለው አይሁድ እንዳይወግሯቸው ፈርተው በራቸውን
ዘግተው ግራ ተጋብተው የዋሉበት ዕለት ከመሆኑም በሻገር ሊቃውንት በተለያየ ስያሜ ይጠሯታል፣
·
ቅዳም ሥዑር
ይህ የተባለበት
በሰንበት ከእህል ከውሃ መጾም አይፈቀድም ፡፡ ነገር ግን በዚህ ዕለት ጌታ በመቃብር ውስጥ በመሆኑ ሐዋርያት ትንሣኤውን ሳናይ አንበላም
አንጠጣም ብለው በማክፈል ስለጾሙትና ሰንበተ አይሁድነቱ በመሻሩ ነው፡፡ ይህም ይታወቅ ዘንድ ከሰዓት በፊት ቄጤማ እስኪዞር ሥራ
ይሠራል፡፡
·
ለምለም ቅዳሜም
ይባላል
ምክንያቱም በዚህ
ዕለት ለምለም ቄጤማ ስለሚታደልበት ነው፡፡ ቄጤማ የሚታደልበት ምክንያት ምሳሌያዊና ምስጢራዊ ትርጉም ስላለው ነው ምሳሌያዊ ትርጉም
በኖኅ ዘመን የዘነበው ማየ አይኀ መድረቁን ለማረጋገጥ፣ ኖኅ ርግብን በመስኮት አውጥቶ ላከ በመጀመሪያው ዝም ብላ ተመልሳለች በሁለተኛው
ስትላክ ‹‹ነትገ ማየ አይኀ ሐፀ ማየ ኃጢዓት›› እያለች ቄጤማ በአፏ ይዛ ስትመለስ ኖኅ እጁን ዘርግቶ ተቀብሏታል፡፡ የርግቢቱ
ድርጊት የጥፋት ውሃ ደረቀ፣ የኃጢዓት ውሃ ደረቀ የሚል የምስራች አጉልቶ የሚያሳይ ነው፡፡ (ዘፍ 8፡6-11)
ምስጢራዊ ትርጉሙ
ደግሞ ርግብ የተባለችው አማናዊት ርግብ እመቤታችን ድንግል ማርያም ናት፣ ለምለም ቄጠማ በአፏ ይዛ እንደመታየት፣ አምላክ ወልደ
አምላክን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና መውለዷን የሚያመለክት ነው፡፡ ከእርሷ የተወለደው ክርስቶስ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ በሞቱ
ሞትን እንዳጠፋልን "ማየ አይኀ" የተባለ ሞተ ነፍስን እንዳስቀረልን ለማመልከት የምስራች ሲሉ ካህናት ቄጤማ ያድላሉ፣ ምዕመናንም እስከ
ትንሳኤ ሌሊት በራሳቸው ላይ ያሥሩታል፡፡
·
ቅዱስ ቅዳሜ
ይባላል
ቅዱስ ቅዳሜ
መባሉ ቅዱስ የሆነ እግዚአብሔር በጥንተ ተፈጥሮ ፍጥረታትን አከናውኖ ከፈጠረ በኋላ በዚህ ቀን ከሥራው ሁሉ ያረፈበት ሲሆን፣ በዘመነ
ሐዲስ ደግሞ የማዳን ሥራውን ሁሉ ፈጽሞ በሥጋው መቃብር ሲያርፍ በነፍሱ ሲዖልን በርብሮ ባዶዋን አስቀርቷታል፡፡ በዚያ ለነበሩት
ነፍሳትም የዘላለም ዕረፍትን ያወረሰበት ዕለት ስለሆነ ከሌሎች ዕለታት የተለየ ዕለት ለማለት ቅዱስ ቅዳሜ ተብሏል፡፡
በዚህ ዕለት በቤተክርስቲያን የሚፈጸሙ ሥርዓቶች
1. መኀልየ መኅልየ
ይነበባል ምክንያቱም ተስፋ ትንሳኤ አለባትና
2. እስካሁን በሌሎች
ዕለታት ሳይደርስ የሰነበተው እግዚአ ሕያዋን (የሕያዋን ጌታ) ፣ ፍትሐተ ዘወልድ፣ ጸሎተ ዕጣን "ዘእንበለ ስኢም" ይደረሳል፣ ያለመሳሳም
ወይም ያለ ሰላምታ ማለት ነው፡፡
3. ገብረ ሰላመ
በመስቀሉ (በመስቀሉ ሰላምን አደረገ የሚለው መዝሙር ይዘመራል ምክንያቱም በሲኦል ያሉትን ነፍሳት በርብሮ በገነት ዕረፍተ ነፍስን
(ሰላምን) ለሰው ልጅ የሰጠው በመስቀል ላይ ከተሰቀለ በኋላ ስለሆነ ነው፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ከላይ እንዳየነው ጌታ በዕፀ መስቀል
ከመሰቀሉ በፊት መስቀል የሰላም ምልክት አልነበረም፡፡ እርሱ ከተሰቀለበት በኋላ ግን የሰላም ምልክት ሆኗልና ከፊተኛው ለመለየት
ነው፡፡
4. ከዚህ ሁሉ በኋላ
በረከተ ቄጤማ ይዞራል
5. አክፍሎት፡-
ዓርብና ቅዳሜ ይሆናል፣ ያልቻለ አንድ ቅዳሜን ያከፍላል የዚህ አክፍሎት ጦም የተጀመረው በሐዋርያት ነው፡፡ ጌታ በመዋዕለ ትምህርቱ
ሳለ ፈሪሳውያን እኛና የዮሐንስ ደቀመዛሙርት እንጦማለን አንተ ደቀመዛሙርት የማይጦሙት ለምንድን ነው? ብለው ጠይቀውት
ነበር እርሱም ሙሽራ ከነሱ ጋር ስለ ሚዜዎች ሊጦሙ አይገባም ነገር ግን ሙሽራው ከነሱ የሚወስድበት ጊዜ ይመጣልና ያን ጊዜ ይጦማሉ
ብሎ መለሰላቸው በዚህ መሠረት ሐዋርያት ሙሽራው ክርስቶስ ከነሱ ከተለየበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ትንሣኤው ድረስ ከሰው ርቀው፣ ከእህል
ከውሃ ተለይተው፣ በዝግ ቤት ተወስነው ጹመዋል ካህናትና ምዕመናን የሐዋርያትን ፈለግ በመከተል ሐሙስ ማታ ከበሉ እስከ ትንሣኤ ሌሊት
ይቆያሉ ሁለቱን ቀን ያልቻሉ ግን ቅዳሜን ብቻ ያከፍላሉ፡፡
6. በሌላ መልኩ
አክፍሎት ማለት ማካፈል ማለት ነው በዚህ ዕለት ካህናት ምዕመናን ካመጡላቸው የትንሣኤ መዋያ በረከት ለድሆች ያካፍላሉና፡፡
ከሰሙነ ሕማማትና ከትንሣኤው በረከት ለመሳተፍ ያብቃን አሜን
No comments:
Post a Comment