Thursday, March 13, 2014

የኋላውን እየተውን ወደፊት መጓዝ



በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
 


ልጄ ሆይ እነሆ በመንፈሳዊ ሕይወትህ ወደ ፊት እንዳትጓዝ ተብትቦ የያዘህ ብዙ ያለፈ የትዝታ ገመዶች ይኖራሉ፡፡ እነዚህም በጎም ሆነ ክፉ ትዝታዎች ሊሆኑ ይችላሉ አስተውል ተደርገው ወይም ሆነው ያለፉ ናቸው፡፡ ነገር ግን በልብህ ውስጥ ስላሉ ስትተኛ ስትነሳም ስትቀመጥም ስትሄድም ከአንተ ጋር ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ዘወትርም ይታሰቡሃል ታዲያ ያለፈውን በጎም ይሁን ክፉ ስራህን እያሰብክ ባለፈው ታሪክህ ተዘፍቀህ የምትኖር ከሆነ ወደ ፊት እንዴት መጓዝ ይሆንልሃል?



ልጄ ሆይ የሰራኸውን በጎ ስራ የምታሰብ ከሆነ ያን እያሰብህ በትዕቢት ትወድቃለህ፡፡ ለዛሬ አዲስ የሆነ በጎ ነገር ለመስራት ጊዜው አይኖርምህም ያለፈውን በማሰብና በማውራት ብቻ የታሪክ ሰው ሆነህ ትቀራለህ፡፡ ለዚህ አይደለም አንዴ በሕይወቱ ጌታን የመሰለው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹አንድ ነገር አደርጋለሁ በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ አዘረጋለሁ›› ብሎ የተናገረው ፊል 3፡13 ፡፡ እሱ በኋላው ያለውን መልካም ስራውን የተጋደለውን ገድል እየረሳ ምንም እንዳልሰራ ሰው በጎ ምግባር ለመስራት በየዕለቱ ይሮጥ ከነበረ አንተማ ምን ያህል ለወደፊቱ መታገል ይገባህ ይሆን? ምናልባት መልካም ሰርተህ እንደሆነ በፍጹም አታስበው፡፡ አንተ መልካሙን ስራህን ስትረሳው ጌታ በምጽዓት ዋጋህን ይሰጥሃልና፡፡
ልጄ ሆይ ያለፈ መልካም ስራህን ማሰብ እንደማይገባህ ሁሉ ያለፈውን ስህተት ያለ አግባብ እያሰብክ መኖር የለብህም፡፡ ምክንያቱም ያለፈውን የስህተት ሕይወት ሁል ጊዜ የምታስብ ከሆነ ዘወትር ልብህ ስለሚቆሽሽ በጎ ለመስራት መነሳሳትን ታጣለህ፡፡ ዲያብሎስም በሕይወትህ አንድ ቀን የፈጽምሃትን ስህተት እያሳሰበ ምህረት እንደማታገኝ በመንገር ተስፋ እንድትቆርጥ ይገፋሃል፡፡ ልታገለግል ስትነሳ ደግሞ አንተ ማነህና? ይልሃል ልትዘምር ስትዘጋጅ አሁን አታፍርም ዪኒፎርምህን አስቀምጠህ ሂድ ውጣ ይልሃል፡፡ ብቻ ዋናው አላማው ያለፈውን በማስታወስ ዛሬን ማበላሸት ነው፡፡ ሀሳቡ ከንስሐ ሊያደርስህ ሳይሆን የይሁዳን ታሪክ ሊደግምብህ ነው የሚያሳዝነው ግን አንተም ለእርሱ ተመችተህ ያለፈውን ስህተትህን እያሰብህ መመላለስህ ነው፡፡ ሰው ግን የኋላውን እያየ ወደ ፊት መሄድ አይችልም ቢሄድም አጨራረሱ ጥፋት ነው በእርግጥ በጣም አስፈላጊ ሲሆን በሌሎች እንዳትፈርድ በትዕቢት አንዳትወድቅ ካለፈው ስህተት ትማር ዘንድ አልፎ አልፎ ልታስተውላቸው የሚገቡ ነገሮች ይኖራሉ ነገር ግን ለሁሉ ገደብ ያስፈልገዋል ፡፡ ልጄ ሆይ አንድ ምሣሌ እንይ መኪና የሚነዳ ሰው ወደ ፊት እና ወደኋላ የሚያይበት መስታወት አለው፡፡ ይሁን እንጂ በጣም አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር ወደ ኋላ የሚያሳየውን መስታወት ማየት አያስፈልገውም ወደ ኋላ የሚያሳየውን መስታወት እያየ ቢነዳ ግን መጨረሻው ምን እንደሚሆን ካንተ የሚሰወር አይደለም፡፡ ለዚህ እኮ ነው ወደ ኋላ የሚያሳየው መስታወት በጣም ትንሽ ተደርጋ የተሰራው እንደዚህም ሁሉ ያለፈውን ሕይወት እያሰብህ ስላለፈው ማዘንም ሆነ መቆጨት ዛሬን እንዳትኖር ያደርግኻል፡፡ አንዳንዴ ሕይወትህን ስመለከተው ያለው ውድቀትህን የምታይበት መስታወት በጣም ገዝፎ ከፊትህ ያለውን የምታይበት ግን እጅግ ያነሰ ይመስላል፡፡
ልጄ ሆይ ብትቀይራቸው የምትሻውና የምትወደው ነገር ግን ልትቀይራቸው የማትችላቸው ብዙ ነገሮች በሕይወትህ ተከስተው ይሆናል፡፡ ምን ማድረግ ትችላለህ? አንዴ ሆኗል ፡፡ ከሆነ እውን ላንተ የሚበጀው የታሰርህበትን ያለፈውን የትውስታ ገመድ ፈትተህ ዛሬን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መኖር ነው ወይስ ያለፈው ትዝታ ላይ ሙጢኝ ብለህ ዛሬን ማበላሸት ነገንም ማጨለምን ባለፈ ክረምት የሚያርስ ማንም የለምና ከእጅህ ስላመለጠው ትላንት ማሰብን ትተህ ዛሬን ከአምላክህ ጋር በንስሐ ኑር፡፡ ምናልባትም ያ የሚረብሽ ትውስታ ኃጢዓት ከሆነ እንዲህ እያልህና እየተናዘዝህ አዲስ ሕይወት ጀምር፡፡
‹‹የልጅነቴን ኃጢዓትና መተላለፍ አታስብብኝ አቤቱ ስለ ቸርነትህ ብዛት እንደ ምሕረትህ አስበኝ›› መዝ 23፡6

No comments:

Post a Comment