Monday, March 10, 2014

‹‹ዓይኖችህ ከሚያዩት የተነሣ ዕብድ ትሆናለህ›› (ዘዳ 28፡34)






‹‹ዓይኖችህ ከሚያዩት የተነሣ ዕብድ ትሆናለህ›› (ዘዳ 28፡34)
እግዚአብሔር በሊቀ ነቢያት በሙሴ በኩል ለርስቱ ለተጠሩ ለበኩር ልጆቹ ለእስራኤል ትዕዛዙን ይጠብቁ ዘንድ ሥርዓቱን ያደርጉ ዘንድ ሰው ሆነው ለተፈጠሩበት ዓላማ ይኖሩ ዘንድ በግልጽ ተነግሯል፡፡
‹‹እስራኤል ሆይ ዝም ብለህ አድምጥ ዛሬ የአምላክህ የእግዚአብሔር ሕዝብ ሆነሃል ለአምላክህም ለእግዚአብሔር ቃል ታዘዝ ዛሬም የማዝዝህን ትዕዛዙን ሥርዓቱን አድርግ›› (ዘዳ 27፡10-26)





ለሕጉ ከተገዙ በሥርዓቱ ከሄዱ ትዕዛዙንም ካከበሩ ከምድር አሕዛብ ሁሉ ከፍ እንደሚያደርጋቸው ከምድርም በረከት ሁሉ እንደሚያጠግባቸው፣ ሁል ጊዜ ራስ እንደሚያደርጋቸውና በአንፃሩ ደግሞ ትዕዛዙን ባይጠብቁ መርገም ሁሉ እንደሚመጣባቸው ሁል ጊዜ የተጨነቁ የተገፉ እንደሚሆኑና ከሚያዩት ነገር የተነሣ እንደሚያብዱ አስጠንቅቋቸዋል፡፡ (ዘዳ 8፡1-14) (ዘዳ 28፡15-68)
ዕብደት ማለት አዕምሮን መሣት፣ ህሊናን መጣል፣ ከተፈጥሮ ሕግ ውጪ መሆን ማለት ነው:: ሰው በተለያዩ ምክንያቶች አውቆም ይሁን ሳያውቅ ሊያብድ ይችላል በዓለማችን ላይ በተለያዩ ሀገራት አእምሮአቸውን ስተው ዕርቃናቸውን የሚሄዱ ህሊናቸውን ጥለው የሚጮሁ፣ የሚሳደቡ፣ አረፋ እያደፈቁ የሚወድቁ የሚነሱ የሚዘረሩ፣ ከተፈጥሮ ሕግ ውጪ በመሆን ነውርን ንቀው እግዚአብሔርን ሳይፈሩ ሰውንም ሳያፍሩ ርኩሰትን የሚሰሩ ከእንሰሳት ያነሱ ዕብዶች በብዛት ይስተዋላሉ፡፡ ይህም የሆነው አስቀድሞ በመጽሐፍ እንደተነገረው የሰው ልጅ የእግዚአብሔርን ቃል መስማት ትቶ በፈቃዱ መኖር ሲጀምር እምነት ሲያጎድል፣ ትዕዛዛትን ሲሽር ህጉን ሲጥስ ጣዖት ሲያመልክ የሚመጣ መቅሠፍት ነው፡፡
ሰው በተለያዩ ነገሮች ሊያብድ ይችላል ከእነዚህም መካከል የተወሰኑትን እንመልከት፡-
1. ከጭንቀትና ከክፉ አሠራር የተነሣ
ሀ/ በቅናት በምቀኝነት በተንኮል
ሰው ከተንኮልና ከምቀኝነት የተነሣ ዕብድ ይሆናል ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ ዛሬም በሰዎች ልቡና እያደረ በክፋት በማነሣሣት በምቀኝነት፣ ከእኔ ለምን ተሻለ፣ ለምን ነግዶ አተረፈ፣ ለምን ተምሮ ሰው ሆነ፣ ለምን ሕይወቱ ተስተካከለለት ወዘተ በሚል በቅናት ተነሳስተው ከአስማተኛ ፣ ከሟርተኛ፣ ከደጋሚ ከሥር በጣሽ ጠንቋዮች ዘንድ በመሄድ ፣ መርዝ በመበጥበጥ ወንድማቸውን፣ እህታቸውን የሚያሳብዱ የሥላሴን ሕንፃ የሚያፈርሱ ክፉዎች አሉ ጥበበኛው ሰሎሞን ‹‹የእናቴ ልጆች ተጣሉኝ›› (መኅ 1፡6) እንዲል በዮሴፍ ላይ የአጥንቱ ፍላጭ የሥጋው ቁራጭ የሆኑ ወንድሞቹ እንደተነሱበት በወገኖቻቸው ላይ በቅናት ተነስተው የሚያሳብዱ አእምሮ የጎደላቸው ብዙ ናቸው፡፡
ለ/ ከክፉ መናፍስት ከአጋንንት አሰራር የተነሣ
በርካታ ወገኖች ከአጋንንት አሠራር የተነሣ በልክፍት፣ በቡዳ፣ በዛር፣ በመሳሰሉት የክፉ መናፍስት አእምሮአቸውን ስተው ርቃናቸውን የሚሄዱ፣ ከሰው የተለዩ ፣ አካላቸውን የሚጎዱ፣ በየፀበሉና በየሆስፒታሉ የሚንከራተቱ ዕብዶች አሉ አጋንንት ክፉ ከመሆናቸው የተነሣ በሰው ልጆች ሕይወት ጣልቃ በመግባት ስብዕናቸውን ከመጉዳታቸው ባሻገር ትዳርን፣ ማህበራዊ ሕይወትን በመበጥበጥ፣ ሀብት ንብረትን በማራቆት ሰዎችን ያሳብዳሉ፡፡ (ማር 5፡1-13)
ሐ/ ከጭንቀት የተነሣ
አንዳንዶች ከመጠን በላይ ከማሰብና ከጭንቀት የተነሣ ያብዳሉ ያሰቡት ስላልተሳካ ያቀዱት ግቡን ስላልመታ፣ ነግጄ አተርፋለሁ ተምሬ ሥራ እይዛለሁ፣ እወልዳለሁ እከብዳለሁ ብለው አስበው ነገር ግን እንደጠበቁት ስላላገኙት እንዳሰቡት ስላልሆነ አእምሮአቸውን የሚስቱ ከጭንቀት የተነሣ የሚያብዱ ጨርቃቸውን የሚጥሉ ህልውናቸውን የሚያጠፉ አልባሌ ቦታ የሚገኙ ዕብዶች አሉ፣ እነዚህ በመጽሐፍ ‹‹ትካዜህን በእግዚአብሔር ላይ ጣል እርሱም ያሳርፍሃል›› (መዝ 54፡22) ‹‹የሚያስጨንቃችሁን በእግዚአብሔር ላይ ጣሉት›› (1ጴጥ 9፡7) ተብሎ ሳለ ባለማስተዋል፣ ያላቸውን ባለማወቅ፣ አቅምን ባለማወቅ፣ ነገር ሁሉ ለበጎ ነው ተመስገን ባለማለት የሚያብዱ ናቸው፡፡
እንዲህ ዓይነት ዕብደት በመንፈሳዊ አሰራር በጸበልና በእምነት ይፈወሳል እግዚአብሔር ከአጋንንት አሰራር ከጭንቀት የተነሳ አእምሮአቸውን የሳቱትን በብዙ ተአምራቱ በቸርነቱ ፈውሷል፣ ቀንበራቸውን ሰብሯል፣ ወጥመዳቸውንም በጣጥሷል (ማቴ 15፡21-28 ፣ ማቴ 15፡29-31)‹‹አሁንም ቀንበሩን ከአንተ እሰብራለሁ እስራትህንም እበጣጥሳለሁ››(ናሆ 1፡13) 
2.   በሐሰት መንፈስ ያበዱ
እነዚህ በምድራዊ ሐኪም ዕብደታቸው ያልተረጋገጠ ከእኛ ወገን የነበሩ ነገር ግን ከእኛ ጋር ስላልሆኑ ከእውነት ስተው የወጡ በእግዚአብሔርና በቅዱስ ቃሉ በመንፈሳዊ ዓይን ሲመዘኑ ግን ያበዱ ኅሊናቸውንም የጣሉ፣ አብደው የሚያሳብዱ ከሚሰሩትና ከሚናገሩት ነገር የተነሣ ዕብድ በሚለይባቸው ባሕርያት የሚለዩ የክፉ መናፍስት እስረኞች ናቸው፡፡
1.  ዕብድ ሳይነኩት ይነካል፣ የሚያውቀውንም የማያውቀውንም ይጎነትላል፣ መግቢያ መውጫ ያሳጣል ያሳድዳል
እነዚህም በየአውቶቢሱና ታክሲው፣ በመዝናኛ ሥፍራ፣ በመንገድ ላይ፣ በየፌርማታው ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የሚያውቁትንም የማያውቁትንም ‹‹ጌታን ተቀበሉ›› በማለት አምላክነቱን የካዱትንና የማያምኑበትን ‹‹ኢየሱስን›› ለአማንያኑ የዋህ ክርስቲያን ሊያስተዋውቁ የሚሞክሩ ዕብዶች ናቸው፡፡ አበው ‹‹ራሷ ክርስትና አልተነሳች ልታቋቁም ሄደች›› እንዲሉ ሳያውቁ ለማሳወቅ ፣ ሳይማሩ ለማስተማር የሚጨቃጨቁ ዕብዶች አላወቁም እንጂ እነርሱ ክርስቶስን ሳይቀበሉ እኛ በቤተልሔም ተገኝተን ‹ወርቅ፣ ዕጣን፣ ከርቤን› ገብረን ነበርን በኋላም ጌታ ባረገ በ9ኛው ወር ከሁሉ ቀድመን ተጠምቀን ክርስትናን ተቀብለን በክርስቶስ ክርስቲያን ሆነናል፡፡ (ሐዋ 8፡26-36)
ዛሬም ቅድስት ቤተክርስቲያን ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ ጥዑመ ዜማ ዘትጸውኦ›› እያለች በፈራጅነቱ በአምላክነቱ አምና ታስተምረዋለች ስለዚህም ነቢዩ እንዳለው ‹‹እያንዳንዱ ሰው ባልንጀራውን፣ ወንድሙን እግዚአብሔርን እወቅ ብሎ አያስተምርም ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛል ይላል እግዚአብሔር›› (ኤር 31፡34)
ቅዱስ ጳውሎስም ይህንን የነቢዩን ኅይለ ቃል ጠቅሶ አጽንቶ አስተምሮናል (ዕብ 8፡11) ማንም በእነዚህ ዕብዶች ተታሎ ከጽናቱ እንዳይናወጥ
2.  ዕብድ ትንሹንም ትልቁንም ይሳደባል፣ ያዋርዳል
‹‹እነዚህ ሰዎች እያለሙ ሥጋቸውን ያረክሳሉ ጌትነትንም ይጥላሉ ሥልጣን ያላቸውንም ይሳደባሉ›› (ይሁ 1፡8) ተብሎ እንደተፃፈ በክፉ መንፈስ ተለክፈው አእምሯቸውን የጣሉ በመሆናቸው ቅዱሳንን ጻድቃንን እግዚአብሔር ያከበራቸውን የአምላክን እናት ድንግል ማርያምን ሳይቀር ይሰድባሉ፡፡
‹‹የማያውቁትን ሁሉ ይሳደባሉ›› (ይሁ 1፡10) ክብራቸውን የተሰጣቸውን ማዕረግ ባለመረዳት ‹‹እኔም ሰው እነሱም ሰው›› ብለው በድፍረት ይናገራሉ፣ ነገር ግን በመጽሐፍ ‹‹የአንዱ ኮከብ ክብር ከአንዱ ይበልጣል›› እንዲል ሰው ቅዱስ መሆን ቢችልም ቅሉ ‹‹ድንግል ማርያምን›› መሆን አይችልም፣ ሌሎችንም ቅዱሳን መሆን አይችልም፡፡
ዳሩ ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ የአውሬው መንፈስ ያደረባቸው ሁሉ ይሳደቡ ዘንድ ግድ ነው (ራዕ 13፡5-7) ቅዱስ ዳዊት ‹‹በድፍረትና በትዕቢት በመናቅም በጻድቅ ላይ የሚናገሩ ድዳ ይሁኑ›› (መዝ 30(31)፡18) እንዲል እግዚአብሔር ያከበራቸውን የሚንቁትን የሚሳደቡትን መከራ የሚያሳዩትን ሳይበቀል አይቀርም (ራዕ 6፡7-11)
3.  ዕብድ አእምሮውን ስለጣለ አያስተውልም
 እነዚህ ክፉ መንፈስ አእምሯቸውን ስለሰወረው መጻሕፍትን አያስተውሉም፣ ምስጢርን አይረዱም፡፡ ‹‹ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኀይል አታውቁምና ትስታላችሁ›› (ማቴ 22፡29) እንዲል ባለማስተዋልም ኃይማኖት ይክዳሉ፣ በሐሰት መንፈስም ይመራሉ ‹‹በኋለኞች ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጠውን የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ ኃይማኖትን ይክዳሉ›› (1ጢሞ 4፡1)
ትርጉሙን ባለመረዳት ከምስጢር ይራቆታሉ፣ ከንቱ መለፍለፍና የክፉ መንፈስ ተገዥ ይሆናሉ፡፡ ‹‹ንባብ ይገድላል መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል›› (2ቆሮ 3፡6) እንዲል ሐዋርያው በንባብ ብቻ የጠፉ ያበዱ በርካታ ናቸው፡፡ (1ጢሞ 6፡21)
መንፈስ ተሞላን በማለት በርኩስ መንፈስ ይዘረራሉ ይንከባለላሉ፣ ይጮኀሉ፣ ሣር ይግጣሉ፣ ዕርቃናቸውን ይሆናሉ፡፡ ነገር ግን መፈራገጥ መዘረር የእግዚአብሔር መንፈስ ሳይሆን የሰይጣን መንፈስ ነው ‹‹የእግዚአብሔር መንፈስ የመላባቸው ካህኑ ዘካርያስ ፣ ቅድስት ኤልሳቤጥ ፣ ሐዋርያት በትህትና ሆነው በማስተዋል ቃሉን ተናገሩ አመሰገኑ ተብሎ ተጻፈ እንጂ ተዘረሩ፣ ወደቁ፣ ተፈራገጡ አልተባለም›› (ሉቃ 1፡67፣ ሉቃ 1፡42 ፣ ሐዋ 2፡1-13)
በቅዱስ ወንጌል ተጽፎ እንደምናነበው ‹‹አንድ ሰው በርኩስ መንፈስ የተያዘ ልጁን ይዞ መጣ ይህ መንፈስ ያፈራግጠዋል አረፋ ያስደፍቀዋል፣ በየሥፍራው ይጥለዋል (ይዘርረዋል)፣ ጥርሱን ያፋጨዋል ብሎ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ነገረው›› (ማር 9፡18-29) ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሚያስረዳን የሚያፈራግጥ ፣ የሚዘርር አእምሮን የሚያስት፣ አረፋ የሚያስደፍቅ ርኩስ መንፈስ እንጂ መንፈስ ቅዱስ አለመሆኑን ነው፡፡
ይህ የመንፈስ ዕብደት ነው በመናፍቃን (ገላ 5፡23) ዘንድ በመንፈስ ዕብደት እየተከሰቱ ካሉ የአጋንንት አሰራሮች የተወሰኑትን እንጥቀስ፡፡
ሀ/ በቅርብ ጊዜ የመገናኛ ብዙኀን ሽፋን አጨናንቆ የነበረው አንድ በደቡብ አፍሪካ (ፕሪቶሪያ) ግዛት የሚኖር ፓስተር በአዳራሹ የነበሩትን የጉባዔውን ተከታዮች እንደ ፍየሎች እያስጮኸ ሣር እንዲግጡ ማድረጉ ርኩስ መንፈስ ምን ያህል የሰውን አእምሮ እየተቆጣጠረ እያሳበደው እንዳለ ማስተዋል ግድ ይለናል፡፡ በመሠረቱ በመጽሐፍ ተጽፎ እንደምናነበው ሰዎች ባሕርያቸውን ቀይረው እንደ እንሰሳም ሆነው ሳር የጋጡት በትዕቢትና በኃጢዓት ምክንያት እንደሆነ ከናቡከደነፆርና ከኮቲባ ሕይወት መማር ይጠቅማል፡፡ (ዳን 4፡25 :ተአምረ ማርያም)
http://www.patheos.com/blogs/friendlyatheist/2014/01/11/south-african-pastor-orders-his-congregation-to-eat-grass-terminates-demonic-pregnancy/
ለ/ ሌላውና የመረጃ መረቦች መነጋገሪያ ርዕስ ሆኖ የከረመው የናይጄሪያው ፓስተር ፍራንክ ካቤሌ (FRANEK KABELE) በያስተምራቸው ተከታዮቹ ፊት ልክ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ በውኃ ላይ እራመዳለሁ ብሎ በትዕቢትና በዕብደት በመነሳት እዚያው ውሃ ውስጥ ሰጥሞ ሕይወቱ አልፏል፡፡
ይህ ዓይነቱ የመናፍቃኑ ትዕቢትና ዕብደት አዲስ አይደለም በተመሳሳይ መልኩ በደቡብ ምዕራብ ናይጄሪያ ራሱን ከነቢዩ ከዳንኤል ጋር በትዕቢት ያስተካከለ አንድ ፓስተር ኢባደን በሚባል የዱር አራዊት ማዕከል (IBADON ZOO) ውስጥ ባሉ አንበሶች መካከል እንደ ነቢዩ ዳንኤል መሄድ እችላለሁ ብሎ አንበሶች መሀል ገብቶ በጥቂት ሴኮንድ ውስጥ ቀረጣጥፈው በልተውታል፡፡
በቅድስና በንጽሕና የብቃት ደረጃ የደረሱት ቅዱሳን አበው ሐዋርያትን ጨምሮ ደመና ጠቅሰው የተጓዙት፣ እንደነ አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ ደግሞ አንበሳን እንደ ፈረስ ለትራንስፖርት የተጠቀሙበት፣ እነ አቡነ አረጋዊ በዘንዶ ጀርባ የተጓዙት በእግዚአብሔር መንፈስ በመሞላት በብዙ ተጋድሎ ኃይማኖትን ከምግባር አስተባብረው ይዘው በእውነተኛዋ ጎዳና በተዋሕዶ በመጓዛቸው ነው እንጂ፣ እንደ ዘመናችን ዕብዶች በባዶ ጩኸት በርኩስ መንፈስ አይደለም፡፡ (ያዕ 2፡14-18 ፣ ሐዋ 14፡21)http://www.alan.com/2014/02/05/nigerian-pastor-tries-walking-on-water-like-jesus-and-drowns/
ሐ/ የክርስቲያን ደሴት በሆነችው በሀገራችን በኢትዮጵያም ብሉይን ከሐዲስ አመስጥረው የሚያስተምሩ ሊቃውንት ባሉባት ምድር ነቢዩ ኤልያስ በአራት ኪሎ መጣ ብለው በሐሰት መንፈስ ያበዱ ቢጽ ሐሳውያን ተነስተው እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ክፉዎች ሰራተኞች ይላቸዋል ‹‹ከውሾች ተጠበቁ ከክፉዎችም ሠራተኞች ተጠበቁ›› (ፊልጵ 3፡2)
መ/ ሰሞኑን ደግሞ የመጨረሻው ዋዜማ መቅረቡን የሚያበስር ክስተት ተስተዋለ፣ እነዚህ ደግሞ ከምድረ አሜሪካ የተነሱ ዕርቃናቸውን የጣሉ ያበዱ መናፍቃን ናቸው፡፡ በቨርጂኒያ ሳውዝሀምፕተን የሚገኝ አለን ፓርከር (Allen Parker) የተባለ ፓስተርና ተከታዮቹ ሴቶች ሳይቀር ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለው ራቁቱን ስለሆነ እኛም እርቃናችን ሆነን ማምለክ አለብን በሚል የተሳሳተ ፈሊጥ ሰው በጥበብና በምርምር በተራቀቀበት በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመንና በሰለጠነው ዓለም እርቃናቸውን ሆነው በእግዚአብሔር ሲዘብቱ መታየታቸው ዕብደቱ መጠኑን እያለፈ መሆኑን ያሳያል፡፡
በመሠረቱ የክብር ክብር ምስጋና ይግባውና የኛ ጌታ መድኀኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ዕርቃኑን የዋለው እኛን ከጸጋ ተራቁተን የነበርነውን አዳማውያንን ጸጋ ሊያለብስ ነበረ ግን አላስተዋሉም ፣ ደግሞስ ዕርቃኑን የሰቀሉት እንደ እነሱ ዓይነቶች ምስጢርን ያልተረዱ ጌትነቱን የካዱ አይሁድ አይደሉም እንዴ ምን ያስገርማል ዳሩ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹በእነዚያ ዘንድ ለማስተዋል የሚያስቸግር ነገር አለ ያልተማሩትና የማይጸኑትም ሰዎች ሌሎችን መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ እነዚህን ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ እንግዲህ እናንተ ይህን አስቀድማችሁ ስለምታውቁ በዓመፀኞች ስህተት ተስባችሁ ከራሳችሁ ጽናት እንዳትወድቁ ተጠንቀቁ›› (2ጴጥ 3፡16) ነውና ያለን እግዚአብሔር ይጠብቀን፡፡
በምንፍቅና በክህደት በአጋንንት ትምህርት ያበዱ ለመፈወስ በእግዚአብሔር ቃል ተዋጅተው እውነትን መረዳት አለባቸው፣ ከዚያ በኋላ በእግዚአብሔር ቃል ተፈውሰው እውነትን ተረድተው ከመጡ በጸበልና በእምነት እብደታቸው ይለቃቸዋል፡፡ ነገር ግን እነዚህን መመለስ ከባድ ነው፣ ባለማወቅና ባለማስተዋል የጠፉ ናቸው ብኩርናቸውንም አቃለዋልና ከፍርድ አያመልጡም፡፡ (1ኛ ጢሞ5፡12) 
  http://www.huffingtonpost.com/2014/02/10/nude-church-white-tail-virginia_n_4763199.html
3. የምግባር እብዶች
እነዚህ ደግሞ ኃይማኖት አላቸው፣ ኦርቶዶክሳዊ ነኝ ብለው መስቀል በአንገታቸው አድርገው ይመላለሳሉ፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔርን አያውቁትም አንዳንዶች በደባል ቤት ያኖሩታል፣ ሌሎችም ዳንኪራ ይረግጣሉ፣ ይጨፍራሉ፣ ጠጥተው ይሰክራሉ ፣ በጫት በሲጋራ፣ በሀሺሽና በሁካ ሱስ ይናውዛሉ፣ ያመነዝራሉ ሐዋርያው ‹‹የአይሁዳዊ ብልጫው ምንድን ነው?››እንዲል (ሮሜ 4፡4) በአሕዛብ ባሕርይ ሆነው የአሕዛብን ግብር ስለሚያደርጉ ከአሕዛብ በምንም አይሻሉም (1ጴጥ 4፡3)
መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹ዝሙት ፣ ርኩሰት ፣ መዳራት ፣ ጣዖትን ማምለክ ፣ ምዋርት፣ ጥል፣ ክርክር፣ ቅንዓት፣ ቁጣ ፣ አድመኝነት ፣ መለያየት መናፍቅነት፣ ምቀኝነት፣ መግደል ፣ስካርና ዘፋኝነት የሥጋ ሥራ መሆናቸው ከመገለጹም ባሻገር የጨለማ ኑሮ የፈቃድ ዕብደቶች ይላቸዋል፡፡›› (ገላ 5፡20-21 ፣ ሮሜ 13፡12) በርካታ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በዚህ የዕብደት ሰንሰለት ታስረው ባሪያዎች የሆኑ ከመሆናቸው ባሻገር ድሮ ድሮ ወንዶች ነበሩ የዚህ ዕብደት ሰለባዎች አሁን ግን በሚያስገርም ሁኔታ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪው ሀገር ሀሺሽና ሲጋራ የሚያጨሱ፣ ጠጥተው የሚንዘላዘሉ አዕምሯቸውን ጥለው ዕርቃናቸውን የሚሄዱ፣ በሁካ ምድጃ ተጥደው የሚውሉ በርካታ ሴት ኢትዮጵያውያንን እያየን በመሆኑ በእውነት የዘመኑ ፍፃሜ ቀረበ እንዴ ያሰኛል ሥጋችን ከእግዚአብሔር የተቀበልነው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንጂ የሱስ ማከማቻ አይደለም፡፡
‹‹ሰውነታችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተመቅደስ እንደሆነ አታውቁምን?›› በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፡፡ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩት›› (1ጴሮ 6፡20) ደግሞም እምነት አለኝ የሚል እምነቱን ግን በሥራ የማይገልጥ ምግባርን ከኃይማኖት አስተባብሮ የማይዝ በፈቃዱ የሚያብድ እምነቱ ለድኅነት አያበቃውም፡፡
‹‹ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደሆነ ሁሉ ከሥራ የተለየ እምነትም የሞተ ነው›› (ያዕ 2፡26) እንግዲህ በፈቃድ አብደን በባርነት የተያዝን ሁሉ እግዚአብሔር ‹‹ተመለሱና በሕይወት ኑሩ›› (ሕዝ 18፡32) ይላልና ጊዜው አሁን ነው ‹‹የመዳን ቀን ዛሬ ነው›› ያለበለዚያ ግን በክፉ አድራጊዎች ይፈርዳል ምስር በዛፍ መካከል ተቀምጧል ‹‹መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል ወደ እሳትም ይጣላል›› (ማቴ 3፡10) ተብሎ እንደተጻፈ ምግባርን ከኃይማኖት አስተባብሮ ያልያዘ ከመንግስቱ ዕጣ ፈንታ አይኖረውም ኦርቶዶክሳዊ ነኝ ካሉ ኦርቶዶክሳዊ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እምነት አለን እያሉ ምግባር ግን ያልነበራቸውን አይሁድ ጻሕፍት ፈሪሳውያን ‹‹የአብርሃም ልጆች ነን›› በማለት ይመጻደቁ ለነበሩት ‹‹የአብርሃም ልጆችስ በሆናችሁ የአብርሃምን ሥራ በሠራችሁ ነበር›› (ዮሐ 8፡39)
እምነት ለድኅነት መሠረት ቢሆንም ከፀሐይ ሐሩር ከዝናብና ከሚነፍሰው ነፋስ ለመዳን ግን እንደ ጣራና ግርግዳ የሚከላከለውን ምግባርን መያዝ ግድ ይላል፡፡
ለዚህም ነበር መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ መንግስተ ሰማያት የሚገባ አይደለም፡፡ በዚያን ቀን ብዙዎች በስምህ አልነበርንም ይሉኛል እኔም ከቶ አላውቃችሁም እናንተ አመፀኞች ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ›› በማለት ያስተማረው ፡፡ (ማቴ 7፡23)
ሐዋርያው ጳውሎስም ምግባር የጎደላቸውን የፈቃድ እብዶች አመፀኖች መንግስቱን አይወርሱም ይላል፡፡ ‹‹ይህን እወቁ አመንዝራም ቢሆን ወይም ርኩስ ወይም የሚመኝ፣ ሰካራም፣ ጣዖትን የሚያመልክ በክርስትና በእግዚአብሔር መንግስት ርስት የለውም ወይስ አመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግስት እንዳይወርሱ አታውቁምን?›› (ኤፌ 5፡5-6) (ራዕ 22፡15)  
4.  ግብረ ሰዶም
ሰዶማዊነት ዕብደት ነው ሰው አእምሮውን ሲጥል ክብሩን ሲዘነጋ ማስተዋሉ ሲወሰድ ከእንሰሳትም ያንሳል ‹‹ሰው ክቡር ሆኖ ሳለ አላስተዋለም በልባብና በልጓም እንደሚለጉሟቸው እንደሚጠፉት እንሰሶች እንደ ፈረስና በቅሎ መሰለ›› (መዝ 48፡12 ና 20) ሰዶማዊነት በሽተኛነት ፣ ዕብደት ከመሆኑም ባሻገር የልብ ክፋት ተንኮልም ነው፡፡
የተፈጠሩበትን ዓላማ መዘንጋት በእግዚአብሔር ላይ ማመፅ ዕምነት ማጉደል ነው፡፡ ‹‹የሰዶም ሰዎችም እጅግ ክፍዎችና በእግዚአብሔር ፊት ኃጢዓተኞች ነበሩ›› (ዘፍ 13፡13)
ሰዶማዊነት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በብሉይም በሐዲስ ኪዳንም የተከለከለ ፣ በቀኖና ቤተክርስቲያን በጥብቅ የተወገዘ በሕገ ተፈጥሮ ያልተፈቀደ እንሰሳት እንኳን የማይፈጽሙት አስጸያፊ ኢ-ሰብአዊና: ኢ-ግብረገባዊ ተግባር፣ ቀደም ሲል የሰው ልጅ በአጠቃላይ ዕልቂት የተቀጣበት ለሞት የሚያበቃ ኃጢዓት ከመሆኑም ባሻገር በአሁኑ ጊዜ ይህ ድርጊት ፈውስ ለሌለው በሽታ የሚዳርግ እኩይ ተግባር ነው፡፡
በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰውን ወንድና ሴት አድርጎ ስለፈጠረ ጋብቻ ወይም የግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈጸም የሚገባው በአንድ ወንድና በአንድ ሴት መካከል በቅዱስ ጋብቻ ነው (ዘፍ 1፡27)
ከዚህ ውጪ በተመሳሳይ ጾታ መካከል የግብረ ሥጋ ግንኙነት እንዳይፈጸም ቅዱስ መጽሐፍ እንዲህ ሲል ይደነግጋል ‹‹ከሴት ጋር እንደምትተኛ ከወንድ ጋር አትተኛ ይህ ጸያፍ ነገር ነውና›› ዘሌዋ 18፡22 ‹‹ማንኛውም ሰው ከሴት ጋር እንደሚተኛ ከወንድ ጋር ቢተኛ ሁለቱም ጸያፍ ነገር አድርገዋል ፈጽመው ይገደሉ፣ ደማቸው በላያቸው ነው›› (ዘሌዋ 20፡13)
በሐዲስ ኪዳንም ይህ ድርጊት ፈጽሞ የተወገዘ ድርጊት ነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን እኩይ ተግባር የሚፈጽሙ እንደሚጠፉ ሲናገር ‹‹አስቀድሞ ግን ብዙ መከራ እንዲቀበል ከዚህም ትውልድ እንዲጣል ይገባዋል፣ በኖህ ዘመንም እንደ ሆነ በሰው ልጅ ዘመን ደግሞ እንዲህ ይሆናል፣ ኖህ ወደ መርከብ እስከገባበት ቀን ድረስ ይበሉና ይጠጡ ያገቡና ይጋቡም ነበር የጥፋት ውኃም መጣ ሁሉንም አጠፋ እንዲህ በሎጥ ዘመን እንደሆነ ይበሉ ይጠጡም ይገዙም ይሸጡም ይተክሉም ቤትም ይሰሩ ነበር ፣ ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ቀን ግን ከሰማይ እሳትና ዲን ዘነበ ሁሉንም አጠፋ›› (ሉቃ 17፡25-29) ቅዱሳን ሐዋርያትም በተለያየ ሥፍራ ይህ ድርጊት እንደሚያስቀጣ ከዕብደት የተነሣ የሚመጣ እንደሆነ አስተምረዋል ‹‹ሴቶቻቸው ለባሕርያቸው የሚገባውን ሥራ ለባሕርያቸው በማይገባው ለወጡ፣ እንዲህም ወንዶች ደግሞ ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን መገናኘት ትተው እርስ በእርሳቸው በፍትወታቸው ተቃጠሉ፣ ወንዶችም በወንዶች ነውር አድርገው በስህተታቸው የሚገባቸውን ብድራት በራሳቸው ተቀበሉ›› (ሮሜ 1፡27) ‹‹በመሆኑም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሰሩ ቀላጮችም እግዚአብሔርን መንግስት አይወርሱም›› (1ቆሮ 6፡9-10) ቅዱስ ጴጥሮስም ክፉዎችንና አመፀኞችን አእምሯቸውን የሳቱትን ሰዶማውያንን እግዚአብሔር በተለያየ ዘመን ተበቅሎ እንዳጠፋቸው ወደፊትም በዚህ ግብር ያሉ እንደሚጠፉ አስገንዝቧል፡፡ (2ጴጥ 2፡4-10)
ሐዋርያዊትና ቅድስት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን በጥብቅ ትቃወማለች ታወግዛለችም የምትቃወመውም ድርጊቱ
1.  ኢ-ክርስቲያናዊ ብቻ ሳይሆን ኢ-ሰብሰዊ በመሆኑ
2.  የቤተክርስቲያን ትምህርትን የሚጻረር በመሆኑ
3.  በሕገ-ተፈጥሮ በሕገ- መጻሐፋዊ የተፈቀደውን በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል የሚፈጸመውን ቅዱስ ጋብቻ የሚያስቀር በመሆኑ
4.  እንደ ሰዶምና ገሞራ ሰዎች ታላቅ ጥፋትን መቅሠፍትን የሚያመጣ በመሆኑ
5.  ለደዌ ሥጋና ለደዌ ነፍስ የሚዳረግ ስለሆነ ነው፡፡
በድፍረትም ይሁን ባለማወቅ በዚህ ጸያፍ ሕይወት ያሉትን ቅድስት ቤተክርስቲያን በ314 ዓ.ም የተደረገውን የአብያተ ክርስቲያናት ጉባዔ የ16ኛው ቀኖና መሠረት በማድረግ ሰዶማውያንና ሰዶማውያቱ የመጸጸታቸውና የቀና ኅሊናቸው ንጽሕና እስኪታወቅ ድረስ መላ ዘመናቸውን በንስሐ እንዲኖሩ፣ ከንዑሰ ክርስቲያኖች ጋርም እንዲጸልዩ ታዝዛለች፡፡ የዕድሜ ልክ ንስሐው የበደሉን ክብደት እንደሚያሳይም ታብራራለች፡፡  


No comments:

Post a Comment