Monday, September 21, 2015

“አዎ ድንግል ማርያም ተነሥታለች ፤ ዐርጋለች!”

                    
          
 “አዎ ድንግል ማርያም ተነሥታለች ፤ ዐርጋለች!”
‹‹በቅድሚያ በመላው ዓለም ለምትገኙ ኦርቶዶክሳውያን ሁሉ እንኳን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም በዓለ ትንሣዔ ወዕርገት አደረሳችሁ››
በቀጥታ ወደ መነሻ ርዕሴ ከመግባቴ በፊት ጌታችን በወንጌሉ ‹‹አፌን በምሣሌ እከፍታለሁ………ያለ ምሳሌም አልተናገራቸውም››(ማቴ 13፡34-35) እንዳለ ፤ አበውም ‹‹ነገር በምሳሌ›› እንዳሉት ነውና እርሱን ላስቀድም፡- ‹‹አንድ ሕጻን የድንግል ማርያም ፍቅር በልቡናው ሰርጾበት “አሟሟትሽ በጥር ነሐሴ መቃብር” ፣ “ዐርጋለች ድንግል ተነሥታለች” እያለ ይዘምራል፡፡ ይህን የሰማ አንድ መናፍቅ ሕጻንነቱን አይቶ ለማሳት “ድንግል ማርያም ዐርጋለች ተነሥታለች እያልህ የምትዘምር መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲህ የሚል ነገር እኮ አልተጻፈም” ይለዋል፡፡ ሕጻኑ ግን የተቀደሰ ነበርና “ ተጽፏል እንጅ እንዴት አልተጻፈም ትላለህ?” ብሎ ይመልስለታል፡፡ መናፍቁም መግቢያ ቀዳዳ ያገኘ ስለመሰለው “አቡሽዬ መጽሐፍ ቅዱስ ይኼውልህ እስኪ ተነሥታለች የሚል አሳየኝ?” ይለዋል፡፡ አቡሽዬ ግን መጽሐፉን ሳይቀበል “ከመሞትና ከመነሣት የቱ ይቀድማል?” በማለት መናፍቁን የሚያስደነግጥ ጥያቄ ጠየቀ፡፡ መናፍቁም “እንዴ መሞት ነዋ!” ብሎ መለሰለት፡፡ አቡሽዬም “እንግዲያውስ መሞቷን ከያዝከው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አሳየኝ ፤ አንተ መሞቷን ስትነግረኝ ያን ጊዜ እኔ ደግሞ መነሣቷን እነግርሃለሁ” አለው፡፡ መናፍቁም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ማግኘት ስላልቻለ አፍሮ በአቡሽ ተሸንፎ ሔዷል›› መናፍቃን ድንግል ማርያም መሞቷን ያምናሉ ትንሣዔዋን ግን አያምኑም !!! ሞታለች የሚለው ሳይጻፍ ካመኑ ተነሥታለች ብሎ ማመን ለምን ተሳናቸው??? አንድም አልተነሣችምን ያምናሉ ተነሥታለችን ግን ይክዳሉ! አልተነሣችምን ያመነ ሕሊናቸው ተነሥታለችን ማመን ለምን ተሳናቸው???ክፋት እንጂ!!! እኛስ መጽሐፍ ቅዱስን እና አዋልድ መጻሕፍትን ተጠቅመን ፅንሰቷን ነሐሴ 7፣ ልደቷን ግንቦት 1፣ እረፍቷን ጥር 21፣ ትንሣኤዋንና ዕርገቷን ነሐሴ 16 ቀን ነው እንላለን፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በልጇ ዓርአያነት በሦስተኛው ቀን (እሑድ ተቀብራ ማክሰኞ)ተነሥታ ወደ ሰማይ ዐርጋለች፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በራዕዩ ላይ እንዳሰፈረው “ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ ፀሐይን ተጐናፅፋ ጨረቃ ከእግሮቿ በታች ያሏት አሥራ ሁለት ከዋክብት የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች” ራዕይ 12÷1 ፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያረፈችው በ49 ዓ.ም ሲሆን ቅዱስ ዮሐንስ ደግሞ ይህንን ራዕይ የተመለከተው እርሷ ካረፈች ከብዙ ዓመታት በኋላ ነው፡፡ ምን አልባትም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንደ አርዮሳውያን(መናፍቃን) አባባል ሞታ ቀርታ ቢሆን ኖሮ ቅዱስ ዮሐንስ በሥላሴ ዙፋን እንዴት ተመለከታት??? ያስተውሉ “ታላቅ ምልክት በሰማይ ታየ ” ነው ያለው :: በሰማይ ማለቱ እመቤታችን ሞትን ድል አድርጋ መነሣቷንና በሠማያት በክብር ዙፋን መቀመጧን ለመግለፅ ነው፡፡ ደግሞም ከርሷ ውጪ በእንዲህ ባለ ልዩ ክብር ያጌጠች ሴት በሠማያት የለችም !!! ምንም በማያሻማ መልኩ ቅዱስ ዮሐንስ በራዕዩ ድንግል ማርያምን ተመልክቷታል፡፡በተጨማሪም “በወርቅ ልብስ ተሸፋፍናና ተጐናፅፋ ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች” መዝ 44(45)÷9 :: በማለት የመንፈስ አባቷ ቅዱስ ዳዊት አስቀድሞ እንደተነበየ በክብር ተነሥታ በልጇ ቀኝ መቀመጧን ተናግሯል ፡፡ እኛም እንናገራለን ፤ እንመሰክርማለን !

እንደገናም ‹‹ተንሥእ እግዚኦ ውስተ ዕረፍትከ፤ አንተ ወታቦተ መቅደስከ›› “አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ አንተና የመቅደስህ ታቦት ” መዝ 131(132)÷8 ይላል:: የዚህ የመዝሙረ ዳዊት አንድምታም ይህን ቃል እንዲህ ይተረጉመዋል፡- ‹‹አንተ›› ሲል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሲሆን ‹‹የመቅደስህ ታቦት›› ማለቱ ደግሞ አማናዊት ማደሪያውን ድንግል ማርያምን ነው ፡፡ ‹‹ወደ ዕረፍትህ ተነስ›› ሲል ደግሞ አማናዊት ማደሪያህ ከሆነችው ከእናትህ ከድንግል ማርያም ጋር‹‹ ከሞት ››ተነሥ ማለቱ ነው፡፡ ምን አልባትም ይህንን ቃል ለታቦት እንጂ ለድንግል ማርያም አይደለም የሚሉ ወገኖች(መናፍቃን) ይኖራሉና ጥቂት ማስረዳቱ ተገቢ ነው፡፡ በእርግጥ ቤተ ክርስቲያናችን እንዲህ ዓይነት ምስጢር አዘል ቃላቶችን በመመርመር ለጊዜው እና ለፍጻሜው ለተለያዩ አካላት መነገሩን ታምናለች ፣ ትመሰጥርማለች፡፡ በመሰረቱ ሁለቱም(ታቦትና ድንግል ማርያም) የእግዚአብሔር ማደሪያዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን በታቦትና በድንግል ማርያም መካከል የማይተመን(የማይለካ ፣ የማይወሰን ፣ የማይወዳደር)ልዩነት አለ፡፡ እግዚአብሔር በታቦት ላይ ቢያድር በመንፈስ ብቻ ነው!!! በድንግል ማርያም ላይ ያደረው ግን ‹‹በመንፈስም በሥጋም ››ነው!!! ይሄ ልዩነት ከገባን ይሄ ቃል ለጊዜው ለታቦት ፤ ለፍጻሜው ግን ለድንግል ማርያም መነገሩን ልብ ይሏል፡፡ እንደገናም የዳዊት ልጅ ሰሎሞን ትንሳዔዋን በገሃድ ሲመሰክር ‹‹ወዳጄ ሆይ፥ ተነሺ ውበቴ ሆይ፥ ነዪ›› በማለት በግልጽ ተናግሯል፡፡
‹‹ የድንግል ማርያም ትንሳዔ እና ዕርገት ማረጋገጫዎች ››
1ኛ)ጌቴ ሴማኒ (የእመቤታች መካነ መቃብር) ባዶ መሆን ፡፡ ለምሳሌ ከጌታችን ትንሳዔ ማረጋገጫዎች መካከል አንዱ የጎሎጎታ(የጌታችን መካነ መቃብር) ባዶ መሆን ሲሆን የእመቤታችን መካነ መቃብር ጌቴሴማኒም ባዶ ነው፡፡ ቅዱስ ሥጋዋ በቦታው የለም!!! ዛሬም ድረስ ከተለያዩ ዓለማት የሚመጡ ብዙ ምእመናን በቦታው እየተገኙ የድንግልን ትንሳዔ እየመሰከሩና እየተባረኩ ይገኛሉ፡፡ ቦታውንም በዶክመንተሪ ፊልም ለማየት እንደቻልኩት ብዙዎች እመቤታችን ተቀብራ በነበረበት ቦታ ላይ ስለት እየተሳሉ ላደረገችላቸው ተአምር ለክብሯ መግለጫ የሚሆኑ የተለያዩ ስጦታዎችን እና የብር ኖቶችን በመካነ መቃብሯ እያስቀመጡ ይሄዳሉ፡፡
2ኛ)በተለያዩ ጊዜአት እና ቦታዎች የድንግል ማርያም በአካል መገለጥ፡፡ ለምሳሌ በግብጽ ደብረ ቁስቋም ፣ ዘይቱን ማርያም እንዲሁም በኢንዶኔዢያ ፣ በኮትዲቯር ፣ በኢራቅ እና በሌሎች አገራት ላይ ዛሬም ድረስ እየተገለጠች ለሕዝብ እና ለአሕዛብ በገሃድ ትታያለች ፡፡
+++ በዚህች ዕለት ይህ የእመቤታችን የቅድስት ድንግለ ማርያም ትንሳዔ የሚታሰበው(የሚከበረው) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን በሌሎቹም እህት አቢያተ ክርስቲያናት(oriental church's) ጭምር ነው፡፡ ከዚህ ባለፈም የካቶሊክ ቤተ እምነትን ጨምሮ በሌሎቹም ‹‹ኦርቶዶክስ መለካውያን›› ተከታዮችም ዕርገቷን በማመን ይህችን ቀን ያከብሯታል፡፡(ኦርቶዶክስ መለካውያን የሚባሉት እንደ ግሪክ እና ሩሲያ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ናቸው)፡፡
+++ እውነት ለመናገር በዛሬው ዕለት ይህን የድንግል እናታችንን ዕርገት ከዲያቢሎስ እና ከመናፍቃን በቀር የማያከብራት የለም! ይህች ቀን በምድራውያን ፍጥረታት እና በሰማያውያን መላእክት ሁሉ እጅግ ከብራ ትውላለች፡፡ በመሠረቱ የድንግል ማርያም ትንሳዔ እና ዕርገት የሚያስደንቅ ነገር አይደለም! እንኳን የአምላክ እናት ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ይቅርና ነቢየ እግዚአብሔር ኤልያስ እንኳ በእሳት ሠረገላ ወደ ሰማይ ዐርጐ የለም እንዴ? ጸሐፍተ ትዕዛዛት ሔኖክስ በሃይለ ነፋሳት ወደ ብሔረ ሕያዋን ተሰውሮ አይደል እንዴ? ኧረ እንደውም በሐዲስ ኪዳን ወንጌላዊው ዮሐንስ ፣ ጃንደረባው አቤላክ ባኮስ ፣ ቅዱስ ያሬድ እና ጻድቁ አቡነ አረጋዊ ዘደብረ ዳሞ ሞትን ሳይቀምሱ ተሰውረው አይደል እንዴ? ታዲያ የድንግል ማርያም ትንሳዔ የሚያስደንቀው ምኑ ላይ ነው? ሞትን የሻረ ልጅ እያላት ሞት እርሷ ላይ ይሰለጥን ይሆን? ለነገሩ ክፋተኛና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይሻል!(ማቴ 12፥38) አንድም ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ›› ብሎ እንደተናገረ የዛሬዎቹም መናፍቃን እንዲሁ በምልክት የታጠሩ ናቸው(1ኛ ቆሮ1፥22) ፡፡ የእመቤታችን ትንሣኤና ዕርገት ትውፊት ወይም የቤተ ክርስቲያንን ትውፊት የማትቀበሉ ከሆነ ለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስን ከየት አገኛችሁት? ማን ሰጣችሁ? ምዕራፍና ቁጥሩንስ ከየት ተቀበላችሁት? ነቢያት ሐዋርያት እንደጻፉትስ በምን ታረጋግጣላችሁ? በእነማንስ በኩል ተጠብቆ ደረሳችሁ? ለመሆኑ ተነሣች ዐረገችን ለመቀበል ከቸገራችሁ አልተነሣችም አላረገችምን ለምን አመናችሁት? የተነገረውንና ሲተላለፍ የኖረውን ለማመን የምትቸገሩ እናንተ ልብወላዳችሁን ለማመን የሚያፋጥናችሁ ማን ነው? መቼና እንዴት እንደተፈጸመ ወይም የዕረፍቷንና የአቀባበሯ ሌላ ትውፊት እንኳ ሳትይዙ የነበረውን ለማቃለል ብቻ የሚያጣድፋችሁ እንዴት ያለ ክፉ መንፈስ ነው? እናንተ የተረጋገጠ ጽሑፍ ብቻ ነው የምንቀበልስ ካላችሁ ትንሣኤና ዕርገቷ የተመለከተውን ጽሑፍ ማን እንደጀመረው፣ እንዴት እንደተሸጋገረና እንዴት ስሕተት እንደሆነስ ለምን አልመረመራችሁም? ጥላቻ ጊዜ አይሰጥማ፤ ክህደት የእውነተኛ ዐውቀት ጭላንጭል የለውማ፡፡ እንግዲህ እናነተን በምን መርዳት ይቻል ይሆን?ትንሣኤዋና ዕርገቷ ለክርስቲያኖች ሊቀበሉት የማያስቸገረው ግን የተረጋገጠ ትውፊት በመኖሩ ብቻም አይደለም፡፡ ትልቁና ዋናው ምሥጢር ያለው ደግሞ እመቤታችን ‹‹ልዩ›› መሆኗ ላይ ነው፡፡ ዕድገቷና ሕይወቷ ልዩ ነበር፡፡ በእርሷ የተደረገው የአካላዊ ቃል ጽንስና ወሊድም እስካሁን ሊገልጹት ቀርቶ ሲያስቡትም ይከብዳል፡፡ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው ‹‹ ይህንም ባሰብኩ ጊዜ ኅሊናዬ የልጅሽን የባሕሩን ጥልቅነት ሊዋኝ ይወዳል፤ የወዳጅሽ የመሰወሪያው ማዕበልም ያማታዋል፡፡ ... አሁንም ገናንቱን አንመርምር፤ ጥልቅነቱንም አንጠናቀቅ፤ የገናንቱን መጠን ለማመስገን የነቢያትና የሐዋርያት አንደበት የማይቻለው ነው›› እንዳለው ለማንም የሚቻል አይደለም፡፡ ለዚህ የታደለችው ነገሩን ሁሉ በልቧ ትጠብቀው የነበረችው እራሷ ድንግል እመቤታችን ብቻ ናት፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ገብርኤልም ቅድስት ኤልሳቤጥም ‹‹ ልዩ›› መሆኗን አስቀድመው ምስጋናቸውን ያስከትሉላት፡፡ ታዲያ እመቤታችን ልዩ በሆነ መንገድ ከጸነሰችና ከወለደች ልዩ በሆነ መንገድስ የማትነሣው የማታርገው ለምንድን ነው? መነሣቷና ማረጓ አድሎ ያስመስላል የሚባለው በድንግልና ጸንሳ በድንግልና መውለዷንስ ለምን አድሎ ነው አይባልም? ጽንሱ ልደቱ ሰለ እርሱ ነው የምትሉ ከሆነስ ትንሣኤውና ዕርገቷ ምን የሚያረጋግጥ ይመስላችኋል? የእርሱን ትንሣኤና ዕርገት ተሰርቆ ነው ሲሉ የነበሩ አይሁድ በእርሷ ትንሣኤና ዕርገት ሲያፍሩ ብዙዎቹም ከእነርሱ ወደ ክርስትና ሲመለሱ እናንተ ይህን ከማለት የማትመለሱ የክርስቶስን ትንሣኤም ሳታውቁ ታቃልላላችሁን? የእናንተ ክሳደ ልቡና በእውነቱ እንደምን ከዚያ ዘመን አይሁድ ይልቅ ጸና? በውኑ አድሎን ለእመቤታችን ትንሣኤና ዕርገት የምትጠቅሱት በደብረታቦር በዓል ሙሴን ከሙታን ኤልያስን ከብሔረ ሕያዋን አምጥቶ ከደቀ መዛሙርቱ ሦስቱን ብቻ ይዞ መውጣቱንስ አድሎ ትሉታላችሁን? በእውነቱ ስንቱን ተመሳሳይ ታሪክ ልንጠቅስ ስንቱንስ ልናስታውሳችሁ እንችላለን? በእውነት የቀደሙትን አበው ትምህርትና ትውፊት እንዳትቀበሉ የእግዚአብሔርንስ የማይታወቅ መንገድ የደረሳችሁበት አስመስሎ ያሞኛችሁ ወይንም ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው? የእመቤታችን ልዩ መሆን ካልገባችሁ በትንሣኤዋና በዕርገቷም ልዩ መሆኗን እንዴት ልትረዱ ትችላላችሁ? ማስተዋላችሁን የጋረደውን የስድብና የስም ማጥፋት ግብር ያሰደረባችሁን ከፉን መንፈስ ትቃወሙትና ከዚህም ነጻ ትወጡ ዘንድ በእውነት እግዚአብሔር ይርዳችሁ ከማለት በቀር ምን ልንል እንችላለን፡፡ድንግልማ በእውነት ተነሥታለች ዐርጋለችም፤ ክብር ምስጋና ለተወደደ ልጇ ይሁን፤ አሜን፤ በረከቷም ይደረብን፡፡(ክፍል-2 ይቀጥላል)
አርምሞትኪ ማርያም ኃለፈ እም አንክሮ፤
እስከ ንሬኢ ሕዝብኪ ለተአምርኪ ግብሮ፤
ገነትኪ ትጽጊ ሰላመ ወተፋቅሮ፤
እለያማስኑ ለዓጸደ ወይንነ ወፍሮ፤
ቆናጽለ ንዑሳነ አፍጥኒ አሥግሮ፡፡
(ቢኒ ዘልደታ ነሐሴ 15/2007 ዓ/ም)

No comments:

Post a Comment