Tuesday, September 29, 2015

ተዋሕዶ

አዲስ መጽሐፍ በገበያ ላይ



(ከመጽሐፋ  ደ)

     ትንቢቶች ሁሉ መፈጸማቸዉ ግድ ነዉ፡፡ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናንተ ጋር ሳለሁ በሙሴ ህግና በነቢያት በመዝሙራትም ስለእኔ የተጻፈዉ ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል (ሉቃ24፤44) እንዳለ ስለርሱ የተነገሩ ትንቢቶችን በሙሉ እርሱ ፈጽሟቸዋል፤ ነቢያትና ሐዋርያት ስለመጪዉ ጊዜ  የተናገሩትም ትንቢት ቅንጣት ታክል እንኳን ሳትፈጸም አትቀርም፡፡ ስለ ሰዎች እምነትና ክህደት የተነገሩ ትንቢቶች ተፈጽመዋል፡፡እየተፈጸሙም ነዉ ገና ወደ ፊትም ይፈጸማሉ፡፡
ሐዋርያት “በግልጽ በለኞች ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና በዉሸተኞች  ግብዝነት የተሰጠዉን የ አጋንንትን ትምህርት እያደመጡ ሃይማኖትን ይክዳሉ”  (1ጢሞ4፡1) <<በቅዱሳን ነቢያትም ቀድሞ የተባለዉን ቃል በሐዋርያቶቻችሁም ያገኛችሁትን የጌታንና  የመድሃኒታችንን ትዕዛዝ እንድታስቡ በሁለቱ  እያሳሰብኳችሁ ቅን ልቡናችሁን አነቃለሁ፡፡በመጨረሻዉ ዘመን እንደራሳቸዉ ምኞት የሚመላለሱ ዘባቾች በመዘበት እንዲመጡ ይህን በፊት እወቁ>>(2ጴጥ3፤2) የሚሉት ትንቢቶች ሁሉ የግድ መፈጸም አለባቸዉ፡፡<<ክህደት  ትጠፋለች ሃይማኖት ግን ለዘላዓለሙ ትጸናለች>>ሲራ40፤12






ይህቺ ሃይማኖት ደግሞ ሌላ አይደለችም ነቢያት<< በመንገድ ላይ ቁሙ ተመልከቱም የቀደመችዉን መንገድ ጠይቁ መልካሚቱ መንገድ ወዴት እንደሆነች እወቁ በእርሷም ላይ ሂዱ ለነፍሳችሁም እረፍት ታገኛላችሁ  እነርሱ ግን አንሄድባትም አሉ>>(ኤር6፤16) እያሉ የተነበዩላት ሐዋርያት << ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኳችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ>>( ይሁ1፡3) <<አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት >>ኤፌ4፤5  እያሉ የሰበኳት ተዋሕዶ ሃይማኖት ናት፡፡ እነዚህ ጥቅሶች እነ መሀመድ እስልምናን በ622ዓ.ም  እነ  ሉተር ፕሮቴሰታንተኒዚም በ16ኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን ለመሰረቱት የእምነት ድርጂት ሊነገር አይችልም፡፡ አመተ ምህረት አንድ ተብሎ መጠር ሲጀምር ወይም ከዛሬ 2000 ዘመናት በፊት የአዲሰ ኪዳን ክርስትና በክርስቶስ እንደተመሰረተ ሁሉ በ 570 ዓ.ም የተወለደዉ መሐመድም እስልምናን በ622ዓ.ም ነዉ የመሰረተዉ፡፡ ከዚያም ከመካ ወደ መዲና ተሰዶ ብዙ ተከታዮችን ካፍራ በዋላ ነዉ ሃይማኖቱን በሃይልና በሰይፍ ያስፋፋዉ፡፡(ዘ ዎርልድ ቡክ ኦፍ ኢንሳይክሎፒዲያ ቮሉዩም 13 ገጽ 533) እንዲሁም በቀለሙም የታሪክ ተምህርት የተማርነዉና የምናነበዉ ይህንኑ ነዉ፡፡ እስልምናን የመሰረተዉ መሀመድ መሆኑን ራሱ ቁራኑም ይነግረናል ፡፡ በሱረቱ አል አንዓም 6፤163 ላይ “ እኔም የሙስሊሞች የመጀመሪያ ነኝ “”እንዲሁም በሱረቱ አልዙመር 39፤12 ላይ “” የሙስሊሞችም መጀመሪያ እነድሆን ታዘዝሁ”” ብሎ መሐመድ ስለራሱ እንደተናገረ ቁራኑ በግልጽ ያስቀምጠዋል፡፡






    እናም ትንቢቶቹ በመሀመድ ወይም በሉተር አልያም ከእነርሱ ወዲህ ለተመሰረተ ሃይማኖት የተነገሩ ናቸዉ ተብሎ እንኳን ቢታሰብ ፍጹም የማይመስል ነገር ነዉ፡፡ምክንያቱም መስራቾቹ እነርሱ እስከሆኑ ድረስ ከመሀመድ ወይም ከሉተር በፊት ሃይማኖት አልነበረም እንዴ ? ተብሎ ቢጠየቅ መልስ አይኖርም፤ምናልባት ላለማመን ተብሎ ሌላ ነገር ካልተነገረ በቀር ማለት ነዉ ወይም በሌላ በኩል ከእነ መሀመድ እና ሉተር በፊት የነበሩ ሐዋያት ቅዱሳን ጻድቃን ሰማእታት በሙሉ እነ ሉተር ዘመን ላይ ስላልደረሱ እነዚህ ሁሉ ሃይማኖት አልነበራቸዉም ማለት ነዉ? ሰዉነታቸዉ እንደ ሽንኩርት በሰይፍ የተቀረደደዉ ፤ በእሳት የተቃጠለዉ ፤ አጥንታቸዉ  እየተፈጨ በንፋስ የተበተነዉ ፤ ቆዳቸዉ ተገፎ አቅማዳ እስኪሆን ድረስ ያደረሳቸዉና ያን ሁሉ ሰማእትነት ይከፍሉ የነበረዉ ገና ወደፊት ፍር ለሚመሰርተዉ ሃይማኖት ነበር ማለት ነዉ?






በጭራሽ እረ እነርሱስ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለተሰጠችዉ ለቀደመችዉ መንገድ አንዲት ብቻ ለሆነችዉ ለተዋህዶ ሃይማኖታቸዉ ለአምላካቸዉ ለኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ሲሉ ነዉ ያን ሁሉ ሰማእትነት ሲቀበሉ የነበረዉ፡፡ቅዱስ ጴጥሮስ ወልድ ዋሕድ ሁለት ልደት ብሎ በመሰከረ ጊዜ በእርሱ አለትነት ለተመሰረተችዉ ቤተክርስቲያን ሲሉ ነዉ ያን ሁሉ መከራ የተቀበሉት እንጂ ከተመሰረተዉ መሰረት ዉጪ ሌላ መሰረት እንደማይመሰረት ያዉቁታል፡፡ማቴ16፡18  እንዲሁም “ በነቢያትና በሐዋርያት መሰረት ላይ ታንጻችሀዋል”ፊሊ2፤20 “ከተመሰረተዉ በቀር ማንም ሌላ መሰረት ሊመሰርት አይችልምና እርሱም ክርስቶስ ነዉ”1ኛ ቆሮ3፤11  ማለት ምን ማለት እንደሆነ ጠንቅቀዉ ስለሚያዉቁ ነዉ እስከሞት ድረስ ታምነዉ  የሕይዎትን አክሊል የተቀዳጁት።
እነርሱ በዚህ መልኩ ያጸኗትን ሃይማኖት ነዉ ለተረካቢዉ ትዉልድ በክርስቶስ ክርስቲያን ተብለን ለተጠራን ለእኛ ያስረከቡን፡፡ የእነርሱን  ሃይማኖት እስካልተከተልን ድረስ ክርስቲያን ነኝ ማለት አይቻልም፡፡እናም ሐዋርያቱ ወልድ ዋሕድ  ብለዉ ያጸኗትን ሃይማኖት የእነ ቅዱስ አትናቴዎስን ፤የእነ ቅዱስ ዲዮስቆሮስን፤ የእነቅዱስ ዮሐንስ አፈዎርቅን ፤ የእነ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን …….ሃይማኖት ያልተከተል ለአፉ ካልሆነ በቀር ክርስቲያን ነኝ ማለት አይችልም፡፡ ቅዱስ ጳዉሎስ  “ የመጀመሪያ እምነታችን እስከመጨረሻዉ አጽንተን  ብንጠብቅ የክርስቶስ ተካፋዮች ሆነናል “  ዕብ3፤4 በማለት  ከማሳሰቡ ባሻገር አሁንም በክርስቶስ ክርስቲያን ለመሰኘት እነዚህ የቀደሙ አባቶቻችን የነገሩንን እንድናስብ  በሃይማኖትም እንድንመስላቸዉ  አዟል  “ የእግዚአብሔርን  ቃል የተናገሯችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፤ የኑሮአቸዉንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በሃይማኖት ምሰሉአቸዉ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ትላንትና ዛሬ እስክ ዘላለም ያዉ ነዉ፡፡ ዕብ13፤7 እናም ዛሬ በዚህ ዘመን ያለን ክርስቲያኖች የቅዱስ ጳዉሎስን ትዕዛዙን ፈጽመንለት እርሱ ያሰተላለፈላቸዉን የአባቶቻችንን ሃይማኖት ተከትለን በእምነት መስለናቸዉ ብንገኝ ደግሞ በጣም ይደሰትብናል፡፡ ስለዚህም ነዉ ለደቀመዝሙሩ ለጢሞቲዎስ “ በእናትህ በኤዎንቄ ፤ በአያትህም በሎይድ ጸንታ ያለች መጠርጠር የሌለባትን ሃይማኖትህን አይቼ ደስ አለኝ ፡፡ባንተ ጸንታ እንዳለች አምኘ ፈጽሞ ደስ ይለኛል፡፡” 2ኛ ጢሞ1፤5 በማለት የጻፈለት፡፡ታዲያ እኛስ እናትና አባቶቻችን ያጸኗትን ሃይማኖት አጽንተን ይሆን? መጠርጠር የሌለባትን ሃይማኖትህን አይቼ ደስ አለኝ ፤ እዉነትም ቅድስትና ጥርጥር የሌለባት  አንዲት ሃይማኖት፡፡
ከሊቢያ የተወለደዉ አርዮስ “”ወልድ ፍጡር ነዉ”” በማለቱ በ325ዓ.ም 318ቱ ጳጳሳት አባቶች በኒቂያ ተሰብስበዉ ለዩትና ከቅዱሳን ሓዋርያት በአደራ የተረከባትን አንዲት ሃይማኖት ኦርቶዶክስ የሚል ስያሜ ሰጡት፡፡ቀጥተኛ መንገድ ማለት ነዉ ፡፡እንደገና ከግሪኮች ዘር በሮም የተወለደዉ መቅዶኒዮስ ”እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ ያንሳል “ብሎ በሐሰት በመነሳቱ በ381ዓ.ም 150 ቅዱሳን አባቶች በ ቁስጥንጥንያ ተሰብስበዉ አወገዙት፡፡ሊቃዉንቱም አምላክ ሰዉ ፤ ሰዉ አምላክ ሆነዋል ሥጋና መለኮት በተዋሕዶ አንድ ሆነዋል ሲሉ ኦርቶዶክስ በሚለዉ ስያሜ ላይ “ተዋሕዶ” የሚል ስያሜ ጨመሩለት፡፡ እንደዚሁም ከሮማዉያን ዘር የተወለደዉ  ንስጥሮስ “” እግዚአብሔር ወልድ ሁለት አካል ሁለት ባሕሪይ ነዉ ፤ ድንግል ወላዲተ አምላክ አትባልም “ በማለቱ በ431ዓ.ም 200 ቅዱሳን አባቶች በ ኤፌሶን ተሰብስበዉ አወገዙት፡፡ “እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሁለት አካል አንድ አካልን ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይን ገንዘብ ያደረገ አምላክ ነዉ፤ቅድስት እናቱም ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ ናት” በማለት ኦርቶዶክስ ሃይማኖትን አጸኗት፡፡ ከ 451ዓ.ም በሀላ ግን ሁለት ባሕርይ ባዮች ተገንጥለዉ ምዕራባዊ ፡ካቶሊካዊ እምነትን አቐቐሙ፡፡
በመሆኑም ቅድስት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በመጀመሪያ በጌታችን ደም የተመሰረተችዉ በ 12ቱ ሐዋርያትና በ72ቱ አርድዕት በአለም ላይ የተስፋፋች  በ318፤ በ150፤እና በ200 ቅዱሳን አባቶች የጸናች በቅዱሳን ጻድቃን ጽኑ ተጋድሎ ና            በሰማእታት ደም ያሸበረቀች ናት፡፡በመሆኑም መጠርጠር የሌለባት ሃይማኖት ማለት   ይህቺ ናት ቅድስት ተዋሕዶ፡፡


No comments:

Post a Comment