Monday, September 21, 2015

ዕረፍቱ ለሊቀ ነቢያት ሙሴ


አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን
መስከረም 8-የሊቀ ነቢያት ሙሴ ዕረፍቱ ነው፡፡ ይኸውም 40 ዓመት በሆነው ጊዜ አንዱ ግብጻዊ ዕብራዊውን ሲገድለው አይቶት ለወገኑ ተበቅሎ ግብጻዊውን ገድሎ ወደ ምድያም አገር ማለትም ወደ ኢት...ዮጵያ መጥቶ የካህኑን የዮቶርን ልጅ አግብቶ ሁለት ልጆችን ወለዶ በኢትዮጵያ 40 ዓመት ከኖረ በኃላ የዮቶርን በጎች እየተበቀ ሳለ እግዚአብሔር በቁጥቋጦ ውስጥ በታላቅ ራእይ ተገልጦለት እስራኤልን ከግብጽ እንዲያወጣ ነግሮት ሄዶ በተአምራት 10 መቅሰፍታት አምጥቶ ነጻ ያወጣቸው ነው፡፡
ዳግመኛም ዛሬ የመጥምቁ ዮሐንስ አባት የበራክዩ ልጅ ካህኑ ዘካርያስ በሰማዕትነት ያረፈበት ዕለት ነው፡፡
"ክርስቶስን አምላክ አትበል" በማለት አንድ ከሃዲ መኮንን በእጅጉ ካሠቃየው በኋላ አንገቱን በሰይፍ የቆረጠው የሰማዕቱ የቅዱስ ሉክዮስም ዕረፍቱ መስከረም 8 ነው፡፡

ዳግመኛም ዛሬ የሰማዕቱ ቅዱስ ዲማድዮስ ዕረፍቱ ነው፡፡ ይኸውም በሃይማኖትና በምግባር ያጌጠ ስለነበር ጌታችን ተገልጦለት ሄዶ በስሙ ሰማዕት ይሆን ዘንድ አዘዘው፡፡ ከደቡባዊ ግብጽ ተነሥቶ እናት አባቱን ትቶ ወጥቶ ወደ አትሪብ በመሄድ በከሃዲው መኮንን ፊት ስለ ጌታችን መሰከረ፡፡ ከሃዲውም ገዥ ጽኑ ሥቃይ ካደረሰበት በኋላ ወደ እስክንድርያ ላከው፡፡ የእስክንድርያም መኮንን
ሉክያኖስ በተራው አሠቃየው፡፡ ነገር ግን ጌታችን  ዲማድዮስ ተገልጦለት አረጋጋው፡፡ በኋላም መኮንኑ ዲማድዮስን ማሠቃየት በሰለቸው ጊዜ ራሱን በሰይፍ አስቆረጠውና የሰማዕትነቱ ፍጻሜ ሆነ፡፡ 
ሊቀ ነቢያት ሙሴ፡- የፈርዖን ሴት ልጅ ‹‹ከውኃ አውጥቼዋለሁና›› ስትል ሕፃኑን ሙሴ ብላ ጠርታዋለች፡፡ ዘጸ 2፡10፡፡
እስራኤላውን በግብፅ ባርነት እየተገዙ ባለበት ወቅት ፈርዖን እስራኤላውያን ወንድ ልጅ ሲወልዱ እንዲገደል በአዋጅ አስነገረ፡፡ የሙሴም እናት ልጇ በፈርዖን ትእዛዝ መሠረት እንዳይገደልባት ስለ ፈርዖን ትእዛዝ ፍራቻ ልጇን በቅርጫት አድርጋ ወንዝ ውስጥ ጣለችው፡፡ ተርሙት የምትባለው የፈርዖን ሴት ልጅ በወንዝ ገላዋን ልትታጠብ ወርዳ ሳለ በዚያ ቅርጫት አግኝታ ብትከፍተው የሚያሳሳ ውብ ልጅ አገኘት፡፡ ‹‹ይህንንስ አሳድገዋለሁ›› ብላ ወደ ቤቷ ወሰደችውና ሙሴ በንጉሡ በፈርዖን ቤት አደገ፡፡ የሙሴም እናት ተንከባካቢ ሞግዚቱ ሆና ተጥሎ የተገኘውን ልጇን እንድታሳድግ ከፈርዖን ሴት ልጅ ጋር በድብቅ ተስማምታ በንጉሡ ቤት ገባች፡፡ እናቱም ልጇን ሙሴ የፈርዖን ልጅ እንዳይባል ሃይማኖቱን፣ ማንነቱን፣ ታሪኩን፣ ባሕሉን ጠንቅቃ እያስተማረች አሳደገችው፡፡
ሙሴ 40 ዓመት በሆነው ጊዜ አንዱ ግብፃዊ ዕብራዊውን ሲገድለው አይቶት ለወገኑ ተበቅሎ ግብፃዊውን ገደለው፡፡ በማግስቱ ደግሞ ሁለት ዕብራውያን እርስ በእርሳቸው ሲጣሉ አያቸው፡፡ ሊያስታርቃቸው ፈልጎ ወደ እነርሱ ጠጋ ቢል አንደኛው ዐመፀኛ ዕብራዊ ‹‹ትናንት ግብፃዊውን እንደገደልከው ልትገድለን ትሻለህን?›› አለው፡፡ ሙሴም ‹‹በድብቅ አደረኩት ያልኩት ለካ ታውቆብኛል›› ብሎ ፈርዖንን ፈርቶ ወደ ምድያም አገር ሸሽቶ ሄደ፡፡
የምድያም አገር ካህን የሆነውን የዮቶርን (በሌላ ስሙ ራጉኤል ይባላል) ሴት ልጁን ሲፓራን አግብቶ 40 ዓመት በምድያም ተቀምጦ ሁለት ልጆችንም ወለደ፡፡ ይህችውም ምድያም የተባለች አገር ቅድስት ኢትዮጵያ ናት፡፡ ስለዚህም ጉዳይ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡- ‹‹ፈርዖንም ሙሴ ግብፃዊውን እንደገደለው በሰማ ጊዜ ሙሴን ሊገድለው ፈለገ፡፡ ሙሴ ግን ከፈርዖን ፊት ኰበለለ፣ በምድያምም ምድር ተቀመጠ፤ በውኃም ጕድጓድ አጠገብ ዐረፈ፡፡ ለምድያምም ካህን ሰባት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም መጥተው ውኃ ቀዱ፣ የአባታቸውንም በጎች ሊያጠጡ የውኃውን ገንዳ ሞሉ፡፡ እረኞችም መጥተው ገፏቸው፤ ሙሴ ግን ተነሥቶ ረዳቸው፣ በጎቻቸውንም አጠጣላቸው፡፡ ወደ አባታቸው ወደ ራጉኤልም በመጡ ጊዜ ‹ስለ ምን ዛሬ ፈጥናችሁ መጣችሁ?› አላቸው፡፡ እነርሱም ‹አንድ የግብፅ ሰው ከእረኞች እጅ አዳነን፣ ደግሞም ቀዳልን፣ በጎቻችንንም አጠጣ› አሉ፡፡ ልጆቹንም ‹እርሱ ወዴት ነው? ለምንስ ያንን ሰው ተዋችሁት? ጥሩት እንጀራም ይብላ› አላቸው፡፡ ሙሴም ከዚያ ሰው ጋር ሊቀመጥ ወደደ፤ ልጁንም ሲፓራን ለሙሴ ሚስት ትሆነው ዘንድ ሰጠው፡፡›› ዘጸ 2፡1-25፡፡
‹‹ሙሴም ኢትዮጵያይቱን አግብቶአልና ባገባት በኢትዮጵያይቱ ምክንያት ማርያምና አሮን በእርሱ ላይ ተናገሩ፡፡ እነርሱም ‹በውኑ እግዚአብሔር በሙሴ ብቻ ተናግሮአልን? በእኛስ ደግሞ የተናገረ አይደለምን? አሉ፣ እግዚአብሔርም ሰማ፡፡ ሙሴም በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ሰው ነበረ፡፡ እግዚአብሔርም ወዲያው ሙሴንና አሮንን ማርያምንም ‹ሦስታችሁ ወደ መገናኛው ድንኳን ውጡ› ብሎ ተናገረ፤ ሦስቱም ወጡ፡፡ እግዚአብሔርም በደመና ዓምድ ወረደ፣ በድንኳኑም ደጃፍ ቆመ፤ አሮንንና ማርያምን ጠራ፣ ሁለቱም ወጡ፡፡ እርሱም ‹ቃሌን ስሙ በመካከላችሁ ነቢይ ቢኖር፣ እኔ እግዚአብሔር በራእይ እገለጥለታለሁ፣ ወይም በሕልም እናገረዋለሁ፡፡ ባሪያዬ ሙሴ ግን እንዲህ አይደለም፤ እርሱ በቤቴ ሁሉ የታመነ ነው፡፡ እኔ አፍ ለአፍ በግልጥ እናገረዋለሁ፣ በምሳሌ አይደለም፤ የእግዚአብሔርንም መልክ ያያል፤ በባሪያዬ በሙሴ ላይ ትናገሩ ዘንድ ስለ ምን አልፈራችሁም?› አለ፡፡ እግዚአብሔርም ተቈጥቶባቸው ሄደ፡፡ ደመናውም ከድንኳኑ ተነሣ፤ እነሆም ማርያም ለምጻም ሆነች፣ እንደ አመዳይም ነጭ ሆነች፤ አሮንም ማርያምን ተመለከተ፥ እነሆም፥ ለምጻም ሆና ነበር፡፡ አሮንም ሙሴን ‹ጌታዬ ሆይ፥ ስንፍና አድርገናልና፥ በድለንማልና እባክህ፥ ኃጢአት አታድርግብን››› አለው፡፡ ኦሪት ዘኁልቅ 12፡1-12፡፡ እንግዲህ ሕዝበ እስራኤል ከግብፅ ሳይወጡ በኋለኛውም ዘመን ጌታችን ከመወለዱም ከብዙ ዘመን በፊት በቅድስት አገር ኢትዮጵያ ውስጥ እግዚአብሔርን የሚያገለግል ካህን እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ የሚመሰክረው ሐቅ መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት የሚባለው ከበቂ በላይ ብዙ ምክንያትና ማስረጃ ኖሮ ነው እንጂ እንዲሁ አይደለም፡፡
ወደ ሙሴ ታሪክ እንመለስና ሙሴ በምድያም አገር በዱር ሆኖ የካሁኑን የዮቶርን በጎች እየጠበቀ ሳለ በቁጥቋጦ ውስጥ ታላቅ ራእይ አየ፡፡ ነበልባል ከሐመልማል ጋር ሐመልማልም ከነበልባል ጋር ተዋሕዶ ነበልባሉ ሐመልማሉን ሳያቃጥለው፣ ሐመልማሉም ነበልባሉን ሳያጠፋው ተመልክቷል፡፡ ይህንንም ምሥጢር ለመረዳት ጠጋ ሲል ከቁጥቋጦው ውስጥ እግዚአብሔር ድምፅ አውጥቶ ጠራው፡፡ የቆመባት ስፍራ የተቀደሰች ስለሆነች ጫማውንም ከእግሩ እንዲያወልቅ ነገረው፡፡ ዘጸ 3፡5፣ ሐዋ 7፡30-34፡፡ ለጊዜው ሐመልማል የእስራኤል፣ ነበልባሉ ደግሞ የመከራቸው ምሳሌ ነው፡፡ ሐመልማሉ ነበልባሉን ያለመጥፋቱ እስራኤልም መከራውን ግብር ገብተን ቀኖና ይዘን እናርቀው ያለማለታቸው ምሳሌ ሲሆን ነበልባሉ ሐመልማሉን ሳያቃጥል ማየቱ የግብጽ መከራ እስራኤልን ጨርሶ ያለማጥፋቱ ምሳሌ ነው፡፡ ፍጻሜው ግን ሙሴ ያየው የነበልባልና የሐመልማል ተዋሕዶ የመለኮትና የትስብእት ተዋሕዶ ምሳሌ ነው፡፡ ነበልባሉ ሐመልማሉን እንዳላቃጠለው ሁሉ ሐመልማሉም ነበልባሉን እንዳላጠፋው ሁሉ መለኮት ምልአቱን ስፋቱን ርቀቱን ሳይተው ሥጋም ግዙፍነቱን ሳይተው የመዋሐዳቸው አንድ አካል አንድ ባሕርይ የመሆናቸው ምሳሌ ነው፡፡
እንዲሁም ነበልባሉ የጌታችን ምሳሌ ሲሆን ሐመልማሉ ደግሞ የእመቤታችን ምሳሌ ነው፡፡ ይኸውም ነበልባሉ ሐመልማሉን እንዳላቃጠለው ሁሉ እሳተ መለኮት ጌታችንም 9 ወር ከ5 ቀን በማኅፀኗ ባደረ ጊዜ እመቤታችንን ባሕርየ መለኮቱ አላቃጠላትም፤ ሐመልማሉም ነበልባሉን እንዳላጠፋው ሁሉ ጌታችንም ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ሰው ቢሆንም ባሕርየ መለኮቱ አልተለወጠም፡፡ ይህንንም ቅዱስ ኤፍሬም በሐሙስ ምስጋናው ላይ እንዲህ ሲል ገልጾታል፡- ‹‹መለወጥ የሌለባት ድንግል ማርያም ሙሴ በበረሐ በነደ እሳት ጫፎቿ ሳይቃጠሉ ያያት ዕፅን ትመስላለች፣ የአብ ቃል በእርሷ ሰው ሆኗልና እሳተ መለኮቱ አላቃጠላትምና፤ ከወለደችው በኋላ ድንግልንናዋ አልተለወጠምና፤ ሰውም ቢሆን መለኮቱ አልተለወጠም በእውነት አምላክ ነውና፣ በእውነት አምላክ የሆነ እርሱ መጥቶ አዳነን፡፡›› የደማስቆው ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስም ‹‹ዕፀ ጳጦስ የአምላክ እናት አምሳል ነበረች፤ ሙሴ ወደ እርሷ በተጠጋ ጊዜ እግዚአብሔር ‹አንተ የቆምክባት ስፍራ የተቀደሰች መሬት ናትና ጫማህን ከእግርህ አውልቅ› አለው፡፡ እንግዲህ ሙሴ የወላዲተ አምላክን ምሳሌ ያየባት መሬት የተቀደሰች ከሆነች ምሳሌዋ ራሷ ምን ያህል የተቀደሰች ትሆን? እርሷ ቅድስት ብቻ ሳትሆን ቅድስተ ቅዱሳን ናት›› በማለት ስለ እመቤታችን አስተምሯል፡፡
ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን ሕዝበ እስራኤልን ከግብፅ ባርነት እንዲያወጣቸው ላከው፡፡ ሙሴም ወደ ግብፅ አገር ሄዶ 10 የተለያዩ መቅሰፍቶች አመጣ፡፡ መጀመሪያ ውኃውን ወደ ደምንት ለወጠው፡ 10ኛው የበኩር ልጆቻቸው ሞቱ፡፡ በተአምራቱም ሕዝቡን ይዞ ከግብፅ ወጣ፡፡ የኤርትራን ባሕር በበትሩ ለሁለት ከፍሎ አሻገራቸው፡፡ ከዚህም በኋላ ሕዝበ እስራኤልን በምድረ በዳ 40 ዓመት ሙሉ መና ከሰማይ እያወረደ መገባቸው፣ ከአለትም ላይ ውኃ እያፈለቀ አጠጣቸው፡፡ እራኤል ግን እጅግ ክፉዎች ነበሩና በክፋ ይነሱበት ነበር፡፡ በድንጋይ ሊወግሩት ያሉበት ጊዜም ነበር፡፡ እርሱ ግን ፍጹም በመታገስ በኃጢአታቸው እንዳይሞቱ ወደ እግዚአብሔር ይማልድላቸው ነበር፡፡ ሙሴ ሰው ከወዳጁ ጋር እንደሚነጋገር ከእግዚአብሐር ጋር 570 ጊዜ ቃል በቃል ተነጋግሯል፡፡ 40 ቀን 40 ሌሊት ከጾመ በኋላ ዓሥሩን ትእዛዛት የተጻፉባቸውን ጽላት ተቀበለ፡፡ እስራኤላውያን ባዩት ጊዜ እንዳይሞቱ ፊቱን እስኪሸፍንላቸው ድረስ ፊቱ እንደ ፀሐይ የሚያበራበት ጊዜም ነበር፡፡
ሊቀ ነቢያት ሙሴ 120 ዓመት በሆነው ጊዜ እግዚአብሔር ሕዝቡን ለአገልጋዩ ለነዌ ልጅ ለኢያሱ እንዲያስረክበው ስላዘዘው ለኢያሱ አስረክቦታል፡፡ ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው በምስክሩ ድንኳን ውስጥ የሚሠራውን ሁሉ ሠርቶ ካዘጋጀ በኋላ በተራራ ውስጥ ዐረፈ፡፡ በዚያም በመልእክት እጅ በሥውር ተቀበረ፡፡ የእስራኤል ልጆችም ወስደው እንዳያመልኩት እግዚአብሔር የሙሴን ሥጋ ሰወረ፡፡ ሰይጣንም የሙሴን ሥጋ ለእስራኤል ሊገልጥላቸው በወደደ ጊዜ ሐዋርያው ይሁዳ በጻፈው መጽሐፉ ላይ እንደመሰከረ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ገሠጸው፣ ከዚህም ሥራ ከለከለው፡፡ የእስራኤልም ልጆች ለሙሴ 40 ቀን አልቅሰውለታል፡፡ ጌታችን ስለ ሙሴ ሲናገር ከእስራኤል ልጆች ውስጥ እንደ ሙሴ ያለ ደግ የዋህ ቅን ነቢይ እንደማይነሣ መስክሮለታል፡፡ ዕረፍቱም መስከረም 8 ነው፡፡
የመጥምቁ ዮሐንስ አባት የበራክዩ ልጅ ካህኑ ዘካርያስ፡- የበራክዩ ልጅ ካህኑና ነቢዩ ዘካርያስ- ይህም ነቢይ ዘካርያስ በንጉሥ ሄሮድስ እጅ መስከረም 8 ቀን በሰማዕትነት ያረፈ ሲሆን የመጥምቁ ዮሐንስ አባት ነው፡፡ ስለ ልጁ ዮሐንስ መወለድ ቅዱስ ገብርኤል ባበሰረው ጊዜ አምኖ ባለመቀበሉ ልጁ ዮሐንስ እስኪወለድ ድረስ ዲዳ ሆኗል፡፡ ልጁ በተወለደም ጊዜ ‹‹ስሙን ዮሐንስ በሉት›› ብሎ በእጁ ሲጽፍ አንደበቱ ተከፍቶለታል፡፡ እርሱና ሚስቱ በእግዚአብሔር ሕግ ያለነቀፋ የጸኑ ደጎች እንደሆኑ ቅዱስ ወንጌል ይመሰክርላቸዋል፡፡ ‹‹በጌታ ትእዛዝና ሕግጋት ሁሉ ያለ ነቀፋ እየሄዱ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ›› ተብሎ ነው በወንጌል ጽድቃቸው የተነገረላቸው፡፡ ሉቃ 1፡5-6፡፡
ንጉሥ ሄሮድስ ጌታችንን የሚያገኝ መስሎት 144 ሺህ ቤቴልሔም ሕፃናትን ሲጨፈጭፍ እመቤታችን ጌታችንን ይዛ ወደ ግብጽ ስትሸሽ ዮሐንስንም እናቱ ቅድስት አልሳቤጥ ይዛው ወደ ሲና በረሃ ገባች፡፡ ኤልሳቤጥ ከመሄዷ በፊት ግን ከባሏ ከዘካርያስ ጋር ሲሰነባበቱ የሚሆነውንም ሁሉ እርሱ ቀድሞ ያውቅ ነበርና ‹‹ሕፃኑን ልጄን ሲያጡ እኔን ይገድሉኛል፣ አንቺ ግን ወደ በረሃው ይዘሽው ሂጂና በዚያ ሸሽጊው›› ብሎ መክሯታል፡፡ ከሄደች በኋላ የርጉም ሄሮድስ ጭፍሮች ዮሐንስን ባጡት ጊዜ ወደ ዘካርያስ መጥተው ‹‹ልጅህን ወዴት አድርሰኸው ነው? ወዴትስ ደበቅኸው? አሁን ከደበቅህበት አምጥተህ ፈጥነህ አስረክበን›› በማለት የፍጥኝ አስረው አሠቃዩት፡፡ ሄሮድስም ዘካርያስ ዘንድ ሄዶ ሕፃኑን ልጅ ዮሐንስን ካልሰጠው እንደሚገድለው ነገረው፡፡ ካህኑ ዘካርያስም የንጉሡን ዛቻ ባለመፍራት አገልግሎቱን ቀጠለ፡፡ ንጉሡም ወታደሮቹን ልኮ በቤተ መቅደሱና በመሠዊያው መካከል አስገደለው፡፡
ነገር ግን እግዚአብሔር የቅዱስ ዘካርያስን ሥጋውን ሰወረው፣ ደሙ ግን እንደ ድንጋይ ሆነች፡፡ ሕዝቡም እንደ ልማዳቸው ለጸሎት በመጡ ጊዜ ከካህናት አንዱ ወደ ቤተ መቅደስ ሲገባ የረጋ የዘካርያስን ደም አገኘ፡፡ ከመሠዊያውም እንዲህ የሚል ድምፅ ተሰማ፡- ‹‹እነሆ የበራክዩ ልጅ ዘካርያስ ተገደለ፣ የሚበቀልም እስኪመጣ ድረስ ደሙ ስትጮህ ትኖራለች›› የሚል ድምፅ ተሰማ፡፡ ይህንንም አንዳንዶች በማሳሳት ከ12ቱ ደቂቀ ነቢያት አንዱ ስለሆነው ስለ በራክዩ ልጅ ነቢዩ ዘካርያስ የተነገረ ነው ይላሉ ግን አይደለም፡፡ ከ12ቱ ደቂቀ ነቢያት አንዱ የሆነው የበራክዩ ልጅ ነቢዩ ዘካርያስ የእርጅና ዘመኑ ደርሶ ኡረት በሚባል አገር ሞተ፡፡ ሥጋውም ያለጥፋት በዚያ ተገኝቶ ቤተ ክርስቲያን ሠርተውለታል፡፡ የዚህኛው የካህኑና የመጥምቁ አባት ዘካርያስ ግን ሥጋው አልተገኘም፡፡ ስለመገደሉ የደሙ ድምፅ ምስክር ሆነ እንጂ፡፡ ጌታችንም ለተረገሙ አይሁድ ስለእርሱ ሲናገር ‹‹የገደላችሁት የዘካርያስ ደም በላያችሁ ይደርሳል›› ብሏቸዋል፡፡ የዘካርያስም ደም እስከ ሰባት ዓመት ድረስ እየፈላ ደሙ ሲካሰሳቸው ከኖረ ገዥው ጥጦስ ገዳዮቹን በሰይፍ ሲገድላቸው ደሙ መፍላቱን አቁሟል፡፡
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን! እኛንም በአማላጅነታቸው የምንታመን የተዋሕዶ ልጆች የሆንን ሁላችንን ዛሬ መስከረም 8 ቀን በዓመታዊ በዓላቸው አስበናቸው የምንውለውን የሊቀ ነቢያት ሙሴን፣ የካህኑ ዘካርያስን፣ የሰማዕታቱን የቅዱስ ሉክዮስንና የቅዱስ ዲማድዮስን ረድኤት በረከታቸውን ያሳድርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን፡፡
(የመስከረም ወር ስንክሳር፣ ኦሪት ዘፍጥረት አንድምታ ትርጓሜ)

No comments:

Post a Comment