Monday, February 1, 2016

የእመቤታችን ክብር

                                                      
                                                                           የእመቤታችን  ክብር
በቀሲስ ደረጀ ሥዩም

“ማርያም ንጽሕት፣ ድንግል፣ ወላዲተ አምላክ፣ ማእምንት፣ ሰኣሊተ ምሕረት፣ ለውሉደ ሰብእ” ትርጉም “ንጽሕት፣ ድንግል ማርያም የታመነች፣ የአምላክን የወለደች ናት፡፡ ለሰዎች ልጆችም ምሕረትን ትለምናለች፡፡” (ውዳሴ ማርያም ዘዓርብ አንቀጽ 6 ቁ. 15)

የቀደሙት አባቶቻችን የቤተክርስቲያን ሊቃውንት የቤተክርስቲያኒቱን የቅዳሴና የውዳሴ መጻሕፍት ሲያዘጋጁ አብዛኛዎቹ ከጸሎት መጽሐፍትነታቸው ባሻገር ሃይማኖታዊ ትምህርታቸውም እንዲጎላና ክርስቲያኑ በየዕለቱ በጸሎት መልኩ ሲያዘወትራቸው ሃይማኖቱንም እንዲያጠና በጥበብ አዘጋጅተውታል። እንደምሳሌ የሃይማኖት ጸሎትንና ውዳሴ ማርያምን መጥቀስ ይቻላል።
በተለይ ውዳሴ ማርያምን የደረሰው ቅዱሱ አባታችን ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ አካላዊው ቃል ወልደ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋን ተዋሕዶ እንደሚወለድ የተነገሩትን የብሉይ ኪዳንን የትንቢት ቃሎችና ምሳሌዎች እያመሳጠረ በአዲስ ኪዳን የወንጌል ቃል እየፈታና የእመቤታችንን ክብር እያብራራ ውዳሴ ማርያምን ከጸሎትነቱ ባሻገር ምስጢረ ሥጋዌን የምናጠናበት እንዲሆን አድርጎ አዘጋጅቶታል።

ከየዕለቱ ውዳሴ ማርያም ውስጥ ከላይ በመነሻችን የጠቀስነው የዓርብ ውዳሴ ማርያም አንቀጽ 6 ቁ.15 በብዙ ሃይማኖታዊ እውነት የተሞላ በመሆኑና በተለይም የሰባቱንም ቀን ውዳሴ ማርያም የሚወክል ሙሉ የሆነ ሃይማኖታዊ ቃል ስላለው ከያዘው ሃይማኖታዊ ምስጢር የተነሳ የቤተክርስቲያን አባቶች ከቤተክርስቲያኒቱ የአገልግሎት ስፋት ምክንያት የዕለቱን ውዳሴ ማርያም ሙሉውን ማድረስ ጊዜ ሲያጥራቸው ውዳሴ ማርያም ዘዓረብ አንቀጽ 6 ቁጥር 15ን በመጸልይ የየዕለቱን ውዳሴ ማርያም ይወክሉበታል።
አባታችን ቅዱስ ኤፍሬም የእመቤታችንን ክብር በገለጠበት ውዳሴ ማርያም ዘዓርብ አንቀጽ 6 ቁጥር 15 ክፍል ውስጥ አምስት መሠረታዊ የሆኑ ሃይማኖታዊ ምስጢራትን እናገኛለን፤
1. ማርያም ንጽሕት፤
2. ማርያም ድንግል፤
3. ማርያም ወላዲተ አምላክ፤
4. ማርያም የታመነች፡ (ማእምንት)
5. ማርያም የምሕረት አማላጅ፤ (ሰዓሊተ ምሕረት ለውሉደ ሰብእ) የሚሉት ናቸው።
1. ማርያም ንጽሕት “ንጽሕተ ንጹሐን”
በመጀመሪያ ደረጃ ቅድስና የባሕርይ ገንዘቡ የሆነ እግዚአብሔር ብቻ ነው። ከአምላካችን ከእግዚአብሔር ስሞች አንዱ ቅዱስ ይባላል። ቅድስና ለእግዚአብሔር የባሕርይው መገለጫም ነው፡፡ እግዚአብሔር እንደስሙ ቅዱስ ነው፡፡ ዘጸ.15፥11 “11 አቤቱ፥ በአማልክት መካከል እንደ አንተ ያለ ማን ነው? በምስጋና የተፈራህ፥ ድንቅንም የምታደርግ፥ በቅድስና የከበረ እንደ አንተ ያለ ማን ነው?” እንዲል። ይህ ቅዱስና በቅድስናው ትወዳዳሪ የሌለው አምላክ ከሰዎች መካከል መርጦ ሰዎችን፣ ክብሩ የተገለጠባቸውን ሥፍራዎችንና ቀናትን ይቀድሳል።
በመጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ሰዎችን ለእግዚአብሔር ሥራ ሲለያቸው እንደሚቀድሳቸው ይናገራል። ለምሳሌ ዘጸ. 28፥41 “41 ይህንም ሁሉ ወንድምህን አሮንን ከእርሱም ጋር ልጆቹን ታለብሳቸዋለህ፤ በክህነት እንዲያገለግሉኝ ትቀባቸዋለህ፥ ትክናቸዋለህ፥ ትቀድሳቸውማለህ” ይላል።
እንዲሁም ቅዱሳን መካናት በእግዚአብሔር ይቀደሳሉ። ለምሳሌ በመጽ. ነገሥት ቀዳ. 9፥2-3 ሰሎሞን የመጀመሪያውን ቤተመቅደስ ሠርቶ ከጨረሰ በኋላ እግዚአብሔር እንዲቀድስለት በለመነ ጊዜ እግዚአብሔር ቤቱን እንዲህ በማለት ቀድሶታል፡- “2 እግዚአብሔር በገባዖን ለሰሎሞን እንደ ተገለጠለት ዳግመኛ ተገለጠለት። 3 እግዚአብሔርም አለው። በፊቴ የጸለይኸውን ጸሎትህንና ልመናህን ሰምቻለሁ፤ ለዘላለምም ስሜ በዚያ ያድር ዘንድ ይህን የሠራኸውን ቤት ቀድሻለሁ፤ ዓይኖቼና ልቤም በዘመኑ ሁሉ በዚያ ይሆናሉ” ይላል። እንዲሁም በዘጸ. 3÷5 ላይ ለሙሴ በሲና ተራራ በተገለጠለት ጊዜ “ወደዚህ አትቅረብ አንተ የቆምክባት ሥፍራ የተቀደሰች መሬት ናትና ጫማህን ከእግርህ አውጣ” ብሎታል።
ከቀናትም ለይቶ እግዚአብሔር ቀኖችን ይቀድሳል። ለምሳሌ ዘፍ. 2፥2-3 “2 እግዚአብሔርም የሠራውን ሥራ በሰባተኛው ቀን ፈጸመ፤ በሰባተኛውም ቀን ከሠራው ሥራ ሁሉ አረፈ። 3 እግዚአብሔርም ሰባተኛውን ቀን ባረከው ቀደሰውም፤ እግዚአብሔር ሊያደርገው ከፈጠረው ሥራ ሁሉ በእርሱ አርፎአልና” እንዲል።
ወደ አዲስ ኪዳን ስንመጣ መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖችን ቅዱሳን ይላቸዋል፡፡ (በመጠመቅ ያገኙትን ክብር ያመለክታል)፡፡ 1ኛ ቆሮ. 1÷2 “2 በቆሮንቶስ ላለች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፥ በክርስቶስ ኢየሱስ ለተቀደሱት፥ የእነርሱና የእኛ ጌታ የሆነውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በየሥፍራው ከሚጠሩት ሁሉ ጋር ቅዱሳን ለመሆን ለተጠሩት፤” ይላል።
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ንጽሕት ስንል ግን ከላይ ለምሳሌ ከጠቀስናቸው ሁሉ የተለየ ንጽሕና ነው። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ መልዕልተ ፍጡራን መትህተ ፈጣሪ (ከፍጡራን በላይ ከፈጣሪ በታች) በመሆኗ ክብሯ ይነገራል። ይህም ማለት የእመቤታችን ክብር ከመላዕክትና ከቅዱሳን ክብር ሁሉ ይበልጣል ማለት ነው።
ጠቢቡ ሰሎሞን መኃልዬ ማኀልይ ዘሰሎሞን (ከመዝሙራት ሁሉ የሚበልጥ የሰሎሞን መዝሙር) በተባለው ድርሳኑ ክፍል ስለ ብዙ የእግዚአብሔር ዓላማዎች ተናግሮአል። የመጽሐፉ ዓቢይ ክፍል ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተክርስቲያን የተናገረበት ክፍል ነው። መርዓዊሃ ለቤተክርስቲያን (የቤተክርስቲያን ሙሽራ) የተባለው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን፤ መርዓት (ሙሽሪት) የተባለችው ደግሞ ቅድስት ቤተክርስቲያን ናት። እንዲሁም ጠቢቡ ሰሎሞን በዚሁ የድርሳኑ ክፍል ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሰፊ የሆነ ምስጢራዊ ቁምነገሮችን መዝግቦልናል። ከዚሁም ውስጥ አንዱ በራዕይ ያያውን የድንግል ማርያምን ንጽህና ሲገልጥ በመኃል 4፥7 ላይ “አልባኪ ነውር ወኢምንትኒ ላእሌኪ፤ ሁለንተናሽ ውብ ነው ምንም እንከን የለብሽም” በማለት እመቤታችን በውስጥ በአፍአ ንጽሐ ሥጋ ንጽሐ ነፍስ እንዳላት ተናግሯል። ይህ ጸጋዋ ነው መልእልተ ፍጡራን (ከፍጡራን በላይ) የሚያሰኛት።
በዚህ ዓለም ከሚኖሩ ሴቶች የልማደ አንስት ኃጢአት ሰውነታቸውን ያላጎደፋቸው ወይም ያላረከሰቸው በሥጋ ንጽሕናቸውን እንደጠበቁ የኖሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ ከአዳምና ከሄዋን ጀምሮ የነበሩ ብዙ ሴቶች ስለ ድንግልናቸው ቢነገር ለጊዜው ሲሆን ቆይቶ ግን ተፈትሖ አለባቸው። እመቤታችን ግን ፍጽምት ናት። እንዲሁም ቅዱሳን አንስት ብለን ክብር የምንሰጣቸውም ቢሆኑ ከገቢረ ኃጢአት በመንፈሳዊ ተጋድሎ ባገኙት ጸጋ ንጹሐን ይሁኑ እንጂ በነፍስ ከነበረው ጥንተ አብሶ (ኃጢያት) ከመሠረታቸው ንጹሐን አልነበሩም።
ልበ አምላክ የተሰኘው ዳዊት አባቷ ስለ ድንግል ማርያም ለእግዚአብሔር ማደሪያነት መመረጥ በመንፈስ ሲረዳ እንዲህ አለ። “እስመ ኃረያ እግዚአብሔር ለጽዮን ወአብደራ ከመትኩና ማህደሮ ዛቲ ይእቲ መዕራፍየ ለዓለም፤ እግዚአብሔር ጽዮንን መረጣት። ማደሪያውም ትሆን ዘንድ አዘጋጃት። ይህች የዘላለም ማደሪያዬ ናት።” መዝ. 132፥13
ከላይ እንደጠቀስነው ሁሉ የእመቤታችን ክብር ከቅዱሳን ሁሉ ከብር እንደሚበልጥ የተረዳ ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴዋ ድርሰቱ እንዲህ አላት፤ “የአቢ ክብራ ለማርያም እምኩሎሙ ቅድሳን እስመ ደልወ ኮነት ለተወክፎ ቃለ አብ፤ ከቅዱሳን ክብር የማርያም ክብር ይበልጣል የአብን ቃል ለመቀበል በተገባ ተገኝታለችና፡፡” /ውዳሴ ዘረቡዕ/
የአዳም ዘር ሆና ሳለ ለእርሷ ይህ እንዴት ሆነላት?
ማኃልየ ማኃልይ ዘሰሎሞን 3፥6 ላይ “6 መዓዛም እንደ ከርቤና እንደ ዕጣን የሆነችው፥ ከልዩ ከነጋዴ ቅመም ሁሉ የሆነችው፥ ይህች ከምድረ በዳ እንደ ጢስ ምስሶ የወጣችው ማን ናት?” የሚል አስገራሚ ቃል ተቀምጦአል። ጠቢቡ ሰሎሞን የሰው ሕይወት በአዳም በደልና በኃጢያት ምክንያት መንፈሳዊ ምድረበዳ በነበረበት ዘመን፣ ሰው ከመንፈሳዊ ጸጋ ጎድሎ ተስፋ በጠፋበት የመንፈሳዊ ድርቀት ዘመን ከደረቀው የሰው ሕይወት ውስጥ ስትወጣ ያያትን ዘር “ከምድረበዳ ውስጥ እንደ ጢስ ዓምድ ሆና ስትወጣ አየሁ” ብሎ በግራሞት ይገልጣታል። ከሰው ሁሉ ተለይታ የተባረከች ከመድረበዳው የሰው ሕይወት ውስጥ በቅድስና ስትወጣ የሚያሳይ ምስጢር አይቶ “ይህች ማነች?” ብሎ በመገረም ይጠይቃል። ይህ ቃል ኢሳይያስ በትንቢቱ 1፥8-9 “የጽዮንም ሴት ልጅ በወይን ቦታ እንዳለ ዳስ፣ በድባም አትክልትም ውስጥ እንዳለ ጎጆ፣ እንደተከበበችም ከተማ ሆና ቀረች፡፡ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ እንደሰዶም በሆንን እንደገሞራም በመሰልን ነበር፡፡” ካለው ቃል ጋር ተመሳሳይ ነው።
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምንም እንኳን የሰው ዘር ብትሆንም ወደ ሕልውና ከመጣችበት ማለትም በእናቷ ማኅጸን ከተጸነሰችባት ቅጽበት ጀምሮ ለይውጣ ነገር ለሰከንድ ክፍልፋይ ጊዜ እንኳን ያለ ንጽሕና የኖረችበት ጊዜ የለም ማለት ነው። ምክንያቱም ዳዊት “እስመ ኃረያ እግዚአብሔር ለጽዮን” (እግዚአብሔር የዘላለም ማደርያው እንድትሆን ጽዮንን መርጦአታል) እንዳለ መዝ. 132፥13 እንዲሁም ልጁ ሰሎሞን በመኃ. 4፥14 “አልብኪ ነውር፤ ምንም ነውር የለብሽም” ብሎ እንዳረጋገጠው።
ለእመቤታችን ንጽሕና ዓብይ የሆነው ማስረጃ ግን የመልአኩ ቅዱስ ገብረኤል ብሥራት ነው። መልአኩ ቅዱስ ገብረኤል ከግዚአብሔር ተልኮ የመፅነሷን ነገር ባበሠራት ጊዜ ስለ ንጽሕናዋ የተናገረው ገና እንደምትቀደስ ሳይሆን አስቀድማ ቅድስት እንደሆነች ሲያስረግጥ የተናገረው በኃላፊ ግስ ነበር። እንዲህ አላት ሉቃ. 1÷28 “መልአኩ ወደ እርሷ ገብቶ ደስ ይበልሽ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ ጌታ ከአነቺ ጋር ነው፡፡ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ አላት፡፡” ቅድስት ቤተክርስቲያን ይህንን መሠረት አድርጋ እግዚአብሔር ድንግል ማርያምን ከእናቷ ማኅጸን ጀምሮ ከውርስ ኃጢያት ጠብቋታል ሲሉ “ዐቀባ እምከርሠ እማ” በማለት ትናገራለች።
ከሴቶች ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ። ይህንን የመልአኩን ቃል በመንፈስ የተረዳ አባታችን አባ ሕርያቆስ “ኦ ድንግል አኮ ዘተአምሪ ርስሐተ ከመ አንስት እለ እምቅድሜኪ ወእምድህሬኪ አላ በቅድስና ወለ ንጽሕት ሥርጉት አንቲ” ትርጉም “ድንግል ሆይ ከአንቺ አስቀድመው፣ ከአንቺም በኋላ እንደነበሩ ሴቶች እድፍ ጉድፍ የምታውቂ አይደለሽም። ይልቁንም በቅድስና በንጽህና ፀንተሽ ኖርሽ እንጂ።” በማለት ተናግሮአል።
ከላይ እንደተገለጠው በዚህ ዓለም ምልልሳቸው በመልካምነታቸው የተመሰከረላቸው አያሌ ቅዱሳን አንስት ኖረው አልፈዋል። ነገር ግን ለአንዳቸውም እንኳን “ከሴቶች ተይተሽ የተባረክሽ ነሽ” የተባለላቸው የሉም፤ አይገኙምም። ለምሳሌ አቢግያ፣ ሳራ፣ ማርያም እኅተ አልዓዛርን መጥቀስ ይቻላል። እንዲሁም በመልአክ ብሥራት የመፅነሳቸውን ነገር የሰሙ አሉ። ለምሳሌ በመጽ. መሳ. 13፥3-18 ላይ መልአኩ ለማኑሄ ሚስት ሶምሶንን እንደምትወልድ አብሥሯታል። ነገር ግን ከበፅነሷ በፊትና ከወለደችም በኋል ማድረግ ስለሚገባት ጥንቃቄ በአፅንኦት ነገራት እንጂ እንደ ድንግል ማርያም ከሴቶች ተለየሽ የተባረክሽ ነሽ አላልትም።
አንዳዶች ከእኛው ዘንድ የሆኑት ጭምር የድንግል ማርያም ንጽሕና ከመልአኩ ብሥራት በኋላ ነው ብለው ይናገራሉ፤ ለዚህም የሚያቀርቡት ማስረጃ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ “አንጺሖ ሥጋሃ ቀዲሶ ኪያሃ ኀደረ ላዕሌሃ" ያለውን ቃል በመጥቀስ ይሞግታሉ። በመሠረቱ ቃሉን እንዳለ ሳይሆን በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ስንመረምረው ቃሉ የጥንት በደልን አያሳይም። እንደ ቅዱስ ያሬድ ነገረ መለኮትን ለተረዳ ሰው ቃሉ የሚያረጋግጠው ድንግል ማርያምን ለእናትነት፣ ባሕርይዋን ለተዋሕዶ መርጦ ማክበሩን ነው።
ንጹሕ የሚለው ቃል ሁሉ ርኩሰት ይቀድመዋል ማለት አይደለም። ለምሳሌ መላእክት “ንጹሐን መላእክት” ይባላሉ። ለመላእክት ንጹሐን የሚለው ሲቀጸልላቸው ተፈጥሮአቸውን ለመግለጥ እንጂ ቀድሞ በደል የነበረባቸውና በኋላ የተቀደሱ ለማለት አይደለም። እመቤታችንም ምንም የሰው ዘር ብትሆንም ለሰው ሁሉ የደረሰው ጥንተ አብሶ ለእርሷ እንዳይደርስባት እግዚአብሔር ከእናቷ ከማኅጸን ጀምሮ ጠበቃት።
እመቤታችን በአምላክ ሕሊና ታስባ ትኖር ነበር፣
ይህንን ሐሳብ አንዳንዶች እመቤታችን ከአርያም ናት ወደ ማለት ያደርሱታል። ከእኛው ወገን የሆኑ አንዳንዶች ደግሞ በአምላክ ህሊና ታስባ ትኖር ነበር ከተባለ የሰው ዘር ሆና ሳለ ከአዳም ጀምሮ የአዳም ኃጢያት ሳይነካት እንዴት እየሾለከች መጣች? የሚል ጥያቄ ያነሳሉ። “እመቤታችን በአምላክ ሕሊና ታስባ ትኖር ነበር” ማለት ግን ከአርያም ናት ማለትም አይደለም። እመቤታችን የታወቁ እናትና አባት ያላት የሰው ዘር ናት። እንዲሁም በሰው ዘር ውስጥ እየሾለከች የመጣችም አይደለችም። “በአምላክ ሕሊና ታስባ ትኖር ነበር” የሚለው አባባል የሚያመለክተው እግዚአብሔር ከዘላለም ዘመናት በፊት ሰውን ከመፍጠሩም አስቀድሞ በአዋቂ ባሕርይው ተረድቶ ሰው ከተፈጠረ በኋላ እንደሚበድል ሲያውቅ ስለ ድኅነቱም አቅዶ ነበር ማለት ነው።
ለምሳሌ ቤተክርስቲያን የተመሠረተችው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ባፈሰሰው ደሙ በቆረሰው ሥጋው አማካኝነት እንደሆነ ሁላችንም እናምናለን። ክርስቶስ በሥጋው ከተቀበለው መከራ ውጪ ቤተክርስቲያን የሚባል ነገር አይኖርም። የቤተክርስቲያን መሥራች የሆነው ጌታ ከተዋሕዶ በፊት በባሕርይው ሥጋና ደም አልነበርውም። ጌታ ሥጋውና ደሙን የነሳው ከእመቤታችን መሆኑን ሳንዘነጋ ይህንን በሚከተለው የእግዚአብሔር ቃል እናብራራው፤
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያኑን እንደሚሠራ መቼ እንደታሰበ ቲቶ 1፥1-2 “የእግዚአብሔር ባሪያና የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፥ በእግዚአብሔር ለተመረጡት እምነት እንዲሆንላቸው በዘላለምም ሕይወት ተስፋ እንደ አምልኮት ያለውን እውነት እንዲያውቁ የተላከ፤ ይልና ስለዚህም ሕይወት የማይዋሽ እግዚአብሔር ከዘላለም ዘመናት በፊት ተስፋ ሰጠ፥” ብሎ ቤተክርስቲያን ከዘላለም ዘመናት በፊት በእግዚአብሔር እንደታቀደች ይናገራል።
ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ ቃል የሚነግረን “የወንጌል አገልግሎት፣ የቤተክርስቲያን ህልውና በእግዚአብሔር ቃል የተገባ ነበር” ይልና መቼ? ለሚለው ሲመልስም (ይህን ሰሙ) “ከዘላለም ዘመናት በፊት” ብሎ ይደመደመዋል። የተስፋ ቃል ያለተስፋ ተቀባይ ሊኖር አይችልም። ተስፋ ሲሰጥ ተስፋ ተቀባይ መኖር ይገባዋል። ጥያቄው ዘመን ከመቆጠሩ በፊት (ከዘላለም ዘመናት በፊት) እግዚአብሔር ይህን ቃል ኪዳን ለማን ሰጠ? ምክንያቱም ከዘላለም ዘመናት በፊት ምንም ፍጥረት የለም፡፡ ሰውና ፍጥረታት በሙሉ የተፈጠሩት ጊዜ ከተቆጠረ በኋላ ነው፤ የመጀመሪያ ፍጥረት የሚባሉት መላእክት እንኳን በጊዜ ውስጥ ተፈጥረዋል፡፡ ስለዚህ ከዘላለሙ ዘመናት በፊት የነበረው በሥልጣን በአገዛዝ በአኗኗር የሚተካከለው አንድያ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔር ከዘላለም ዘመናት በፊት ቤተክርስቲያኑንን በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚመሠርት ኪዳን ከሰጠ ልጁ ደግሞ ቤተክርስቲያንን የሚመሠርተው ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ ስለሆነ የሚዋሐደው የድንግል ማርያም ሥጋ በአምላክ ሕሊና ታስቦ ነበር ማለት ነው።

ቃሉ የሚያስረዳን ቤተክርስቲያንን ወልድ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚመሠርታት ከዘላለሙ ዘመናት በፊት እግዚአብሔር (ሥላሴ) ቃል ገባ። ይህ እርግጥ እንደሆነ ቅዱስ ጳውሎስ በሌላ ሥፍራ ሲያረጋግጥ እንዲህ ይለዋል 2ኛ ጢሞ. 1÷9 “ያዳነን በቅዱስም አጠራር የጠራን እግዚአብሔር ነውና፥ ይህም እንደ ራሱ አሳብና ጸጋ መጠን ነው እንጂ እንደ ሥራችን መጠን አይደለም፤ ይህም ጸጋ ከዘላለም ዘመናት በፊት በክርስቶስ ኢየሱስ ተሰጠን፥” ይላል፡፡ በዚህ ቃል መሠረት ቤተክርስቲያን ከዘላለም ዘመናት በፊት በእርሱ ታቅዳ የተስፋው ቀን ሲደርስ በእርሱ የደም ዋጋ የተሠራች ስለሆነ የተዋሐደው ሥጋም ከእቅዱ ጋር ከዘላለም ዘመናት በፊት ታስቦ ይኖር እንደነበር ያስረዳል። ኤፌሶን 1፥11 “11 እንደ ፈቃዱ ምክር ሁሉን የሚሠራ እንደ እርሱ አሳብ፥ አስቀድመን የተወሰንን በክርስቶስ ደግሞ ርስትን ተቀበልን” እንዳለ።
ከዘላለም ዘመናት በኋላም አዳም በወደቀበት ዕለት ከዘላለም ዘመናት በፊት ያሰበውን እቅዱን በሥጋ ከይሲ ተሸሽጎ ሰውን ላሳተው ዲያቢሎስ ሲገልጥ በዘፍ. 3፥15 ላይ “15በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፥ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ” ብሎታል።
ከዘላለም ዘመናት በፊት የታሰበው የእግዚአብሔር እቅድ ከድንግል ማርያም ሥጋን ተዋሕዶ በተገለጠው ወልደ አምላክ እንደተፈጸመ ሲያረጋግጥ ቅዱስ ጳውሎስ በገላ. 4፥3-4 “3 እንዲሁ እኛ ደግሞ ሕፃናት ሆነን ሳለን ከዓለም መጀመሪያ ትምህርት በታች ተገዝተን ባሪያዎች ነበርን፤ 4 ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤” በማለት ከዘለዓለም ዘመናት መፊት የነበረውን የእግዚአብሔርን ተስፋና የተስፋውን ፍጻሜ ያረጋግጥልናል።
በእነዚህ ሁለት የምጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ በተስፋው ኪዳን እና በተስፋው ዘመን ፍጻሜ የተነገረችው ድንግል ማርያም ናት ብለን የምናምን ከሆነ (በዚህ እንደምንስማማ ተስፋ አደርጋለሁ) "እመቤታችን በአምላክ ሕሊና ታስባ ትኖር ነበር" የሚለውን ለመረዳት አዳጋች ይሆናል ብዬ አላስብም። ከዚህም የተነሳ ነው እመቤታችን ከኢያቄምና ከሃና ከመወለዷ በፊት በብዙ ቅዱሳን ሕይወት ውስጥ እንደነበረች እየመሰልን የምንናገረው። "ከገነት በተሰደደ ጊዜ የአዳም ተስፋው አንቺ ነበርሽ፣ በግፍ የተገደለ የአቤል የዋሃቱ አንቺ ነሽ፣ የሴት ቸርነት አንቺ ነሽ። የሄኖክም ሥራዎቹ፣ ከክፉ ጥፋት የዳነባት የኖህ መርከብ የሴም ቡራኬውና ዕድል ፈንታው አንቺ ነሽ። የአብርሃም እንግድነት የይስሐቅ መዓዛ፣ የያዕቆብ መሰላል አንቺ ነሽ፣ ዮሴፍን የምታረጋጊው አንቺ ነሽ። የሙሴ ጽላት የተባልሽ የሲና ዕፅ፤ በካህኑ አሮን ልብስ ላይ የነበርሽ ጸናጽል፤ ዳግመኛ የበቀለችና ያበበች ያፈራች የአሮን በትር አንቺ ነሽ። የኢያሱ የምስክሩ ሐውልት፤ የጌዲዮን ጸምር፣ የሳሙኤል የሽቱ ሙዳይና የዘይት ቀንድ አንቺ ነሽ። የኤልያስ የወርቅ መሶብ፣ የኤልያስ ጋን አንቺ ነሽ። ኢሳይያስ ፅንስን ከድንግልና ጋር የተናገረልሽ ዳንኤልም ያለ ሩካቤ መውለውድሽን የተናገረልሽ አንቺ ነሽ። እየተባለ በቤተክርስቲያን የሚነገረው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከመኖርዋ በፊት በአምላክ ሕሊና ታሰባ ትኖር እንደነበርና በብሉይ ኪዳን በቅዱሳን ሕይወት ውስጥ ስትግገለጥ እንደመጣች የሚያረጋግጥልን ነው። ስለዚህ ከላይ እንደተገለጠው እግዚአብሔር በአንድያ ልጁ ቤተክርስቲያንን እንደሚሠራት ሲያቅድ ልጁ የሚዋሐደውንም ሥጋ በሕሊናው አስቦታል ማለት ነው።
ከላይ በተገለጠው ሐሳብ ድንግል ማርያም በዘመን በማይገናኟት ቅዱስን ሕይወት ውስጥ ስትነገር መጥታለች። የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት በዘመን የማይገናኙትን ሰዎች በአንድ ዘመን እንደኖሩ አድርገው በሕብር (በምስጢር) ሲያቀራርቧቸው የመንረዳባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች አሉ። ለምሳሌ በዕብራውያን 7፥10 አብርሃም ለመልከጼዴቅ አሥራት ሲከፍል በአብርሃም ዘመን ያልነበረው ሌዊ በአብርሃም ጉልበት ሆኖ አሥራት እንዳወጣ ይናገራል። ዕብ. 7፥9-10 ".... አሥራትን የሚያስወጣ ሌዊ እንኳ በአብርሃም እጅ አሥራትን ሰጥቶአል፤ 10 “መልከ ጼዴቅ በተገናኘው ጊዜ ገና በአባቱ ወገብ ነበረና" እንዲል።
ይህ ማለት ግን ከላይ እንደተገለጠው ድንግል ማርያም ሰው ሆና በእናቷ ማኅፀን ከመፀነሷ በፊት በአርያም ነበረች ማለት ሳይሆን እግዚአብሔር ከዘላለም ዘመናት በፊት የሰጠው ተስፋ የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ ልጁ የሚዋሐደውን የእመቤታችንን ሥጋ ለሰው ሁሉ ከሚደርሰው ጥንተ አብሶ እንዳይደርስባት ከመኖር ሕልውናዋ በእናቷ ማኅፀን መኖር በጀመረችበት ቅጽበት ጀምሮ ጠበቃት፣ ቅድስት ሆነች። ለሰው የሚደርሰው የሰው ልማድ ሳይደርስባት በቅድስና ተወለደች። ለዚህ ነው ቅዱስ ያሬድ “አንጺሖ ሥጋሃ ቀዲሶ ኪያሃ ኀደረ ላዕሌሃ" ያለው። እንዲሁም “ይህች ከምድረ በዳ እንደ ጢስ ምስሶ የወጣችው ማን ናት?” ብሎ ሶሎሞን የጠየቀው ጥያቄ የሚመለሰውም በዚሁ ነው።
ይህንን ለማድረግ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም። እግዚአብሔር ከሕግ በላይ የሚሠራ አምላክ ነው፡፡
1. የኤልያስ ታሪክ 1ኛ ነገሥ. 17 እሳት ከሰማይ ወርዳ በሕግ የማይነዱ ድንጋይና ውሃ በዚያን ቀን ነደዱ።
2. ለሦስት ቀናት ቀኑ ጨለማ የሆነበት የእስራኤል ታሪክ ዘፀ. 1ዐ ላይ እናነባለን። በሕግ ቀንም ቀን ነው ጨለማም ጨለማ ነው። በዘጸዓት 10 ላይ በምንመለከተው ታሪክ ግን በአንድ ከተማ የሚኖሩ በእግዚአብሔር ለሚያምኑ ፀሐይ ስትወጣላቸው እግዚአብሔርን ለተገዳደሩ ግብጻውያን ግን ቀኑ ጨለማ ሆነ።
3. በገባኦን ፀሐይ ከመጥለቅ ዘገየች ኢያሱ 10፤ በነዚህ ሁሉ የምንመለከተው አምላካችን የተፈጥሮን ሕግ የሠራ እንጂ ሕግ እርሱን አይይዘውም፤ ከሕግ በላይ የሚሠራ አምላክ ነውና። ለዚህ ነው እመቤታችንም የአዳም ዘር ሆና ሳለ የአዳም መርግም ሳይደርስባት እግዚአብሔር በእናቷ ማኅጸን መኖር በጀመረችበት ቅጽበት ከሕግ በላይ በሆነ ችሎታው አብሮ ቅድስናን ሰጣት/አጐናጸፋት/።
2. ማርያም ድንግል “ወተረ ድንግል” (ዘላለማዊ ድንግልና)
እመቤታችንን ከፍጡራን ሁሉ በላይ ናት የሚያሰኛት አንዱ ከፍጥት ሥርዓት ውጪ ያለ ወንድ ዘር ሊያውም በድንግልና ፀንሳ በድንግልና የመውለዷ ነገር ነው። መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል የመፅነሷን ነገር ሊያበሥራት በመጣ ጊዜ "እነሆ ትፀንሻለሽ" ቢላት ያለወንድ ዘር በድንግልና መፅነስ ያልተለመደና ከተፈጥሮ ሥርዓት ውጪ በመሆኑ እመቤታችን በብሥራቱ በመገረም "ወንድ ሳላውቅ እንዴት ይሆንላኛል?" ብላ ጠይቃአለች። ነገር ግን ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር ስለሌለ ዓለም ከተፈጠረ ዘመን ከተቆጠረ ጀምሮ ሆኖ የመያውቅ፤ ወደፊትም በሌላ በማንም የማይፈጸም ነገር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በድንግልና ፀንሳ በድንግልና በመውለድ የእግዚአብሔር ድንቅ በእርሷ ተፈጽሞ አይተናል።
ስምዖን አረጋዊ በወጣትነቱ ዘመን እግዚአብሔር በትንቢተ ኢሳይያስ 7፥14 "14 ....ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች።" የሚለውን ትንቢታዊ ቃል እንዴት ድንግል ትፀንሳለች ብሎ ተጠራጠረ? እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም ድንግል በድንግልና ፀንሳ በድንግልና ስትወልድ በዓይኖችህ እስክታይ አትሞትም" ብሎት ስለነበር የተነገረው የእግዚአብሔር ተስፋ በተፈጸመ ጊዜ ድንግል ማርያም በድንግልና ፀንሳ በድንግልና የወለደችውን ጌታ በእናቱ እቅፍ አይቶ የሰጠው ምስክርነት በሉቃስ 2፥25-31 ተመዝግቦ እናገኘዋለን "25 እነሆም፥ በኢየሩሳሌም ስምዖን የሚባል ሰው ነበረ፥ ይህም ሰው የእስራኤልን መጽናናት ይጠባበቅ ነበር፤ ጻድቅና ትጉህም ነበረ፥ መንፈስ ቅዱስም በእርሱ ላይ ነበረ። 26 በጌታም የተቀባውን ሳያይ ሞትን እንዳያይ በመንፈስ ቅዱስ ተረድቶ ነበር። 27 በመንፈስም ወደ መቅደስ ወጣ፤ ወላጆቹም እንደ ሕጉ ልማድ ያደርጉለት ዘንድ ሕፃኑን ኢየሱስን በአስገቡት ጊዜ፥ 28 እርሱ ደግሞ ተቀብሎ አቀፈው እግዚአብሔርንም እየባረከ እንዲህ አለ። 29 ጌታ ሆይ፥ አሁን እንደ ቃልህ ባሪያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ፤ 30-31 ዓይኖቼ በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን ማዳንህን አይተዋልና፤" በማለት።
ቅድስተ ቅዱሳን ወላዲተ አምላክ ማርያም ጌታን ከመፅነሷ በፊት፣ በፀነሰች ጊዜ፣ ከፀነሰችም በኋላ፤ ጌታን ከመውለዷ በፊት፣ በወለደች ጊዜም፣ ከወለደችውም በኋላ፤ ድንግል ናት። የእመቤታችንን ዘላለማዊ ድንግልና አምኖ መቀበል የጌታችን የአምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስን መለኮታዋ ክብር መረዳት ነው፡፡ የልጇን አምላክነት አምናለሁ እያሉ “ጌታ ባደረበት ዙፋን ፍጡር አድሯል” ማለት በእግዚአብሔር ላይ የድፍረት ቃል እንደመሰንዘር ነው።
የእመቤታችን ድንግል በክልኤ (በሁለት ወገን ድንግል ናት) በሥጋዋ ድንግል እንደሆነች ሁሉ በሕሊናዋም ድንግል ናት። ሁለቱን አስተባብሮ የተገኘ ከሰው ወገን አንድስ እንኳ የለም። ሰለዚህም ዘላለማዊት ድንግል እንላታለን፡፡ ይህንን ከእግዚአብሔር የተረዳ ክህነትን ከነቢይነት ጋር አስተባብሮ የያዘ ሕዝቅኤል በኖረበት ዘመን እንዲህ አለ፡፡ ሕዝ. 44፥1-2 “ወደ ምሥራቅም ወደሚመለከተው በስተውጭ ወዳለው ወደ መቅደሱ በር አመጣኝ ተዘግቶም ነበር፡፡ እግዚአብሔር ይህ በር ተዘግቶ ይኖራል፡፡ እንጂ አይከፈትም ሰውም አይገባበትም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶብታልና ተዘግቶ ይኖራል አለኝ፡፡” በማለት የእመቤታችንን ድንግልና ግልጽ በሆነ ትንቢታዊ ቃል አስቀምጦታል። የነቢዩ ትንቢት ሲተረጎም፡-
- ምሥራቅ የተባለችው እመቤታችን ምሳሌ፤ 
- የመቅደስ የማኅጸኗ ምሳሌ፤
- “ተዘግቶ ነበር” የተባለው ቅድመ ፀኒስ፣ ቅድመ ወሊድ፣ ስለ ማኅተመ ድንግልናዋ የሚናገር፡ ምሳሌ ነው። ማቴ. 1፥18 “በመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች” በማለት ያረጋግጥልናል።

- “አምላክ ገብቶበታይልና ተዘግቶ ይኖራል፤” የተባለው ድኅረ ወሊድ ዘላለማዊ ድንግልናዋን የሚያረጋግጥ ምሳሌ ነው።
ይህንን የነቢዩን ትንቢት በውል የተረዱ የቤተክርስቲያን አባቶች በስፋትና በምላት አብራርተው ተጉመውታል። ከነዚህም ውስጥ ነባቤ መለኮት ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ በሃይማኖተ አበው ም.8 ክፍል 1 ከቁጥር 12-14 እንደተመዘግበው እንዲህ ብሏል፤ "የሚወለድበት ጊዜ በደረሰ ጊዜ በማይመረመር ግብር በህቱም ድንግልና ተወለደ። ማህተመ ድንግልናዋም አልተለወጠም። ማህተመ ድንግልናዋ ሳይለውጥ ተወለደ እንጂ ከእስራኤል ፈጣሪ በቀር ሰው እንዳልገባባት ነቢዩ ሕዝቅኤል እንዳያት የመቅደስ በር ማህተመ ድንግልናዋ ሳይለወጥ በህቱም ድንግልና ተፀንሶ በህቱም ድንግልና ተወለደ።"
እንዲሁም ሳዊሮስ ዘአንፆኪያ በሌላ ምስጢር የመቤታችንን ዘላለማዊ ድንግልና ሲግልጥ በሃይማኖተ አበው 87 ክፍል 9 ቁጥር 10 ላይ "በእውነት ሰው የሆነ በሥራው ሁሉ የመሰለን ከእሴይ ሥር የተገኘ በትር ሆኖ ተገለጠልን። በዘመኑ ሁሉ ሁል ጊዜ ድንግል ሆና ከምትኖር የባሕርይ አምላክን ከወለደች ከድንግል ማርያም ያለ ዘራዐ ብእሲ የተወለደውን ልደት ይህ በትር ያስረዳናል" ይላላል። መዝ. 78፥69 “መቅደሱን እንደ አርያም ሠራ፥ ለዘላለምም በምድር ውስጥ መሠረታት” እንዳለ ዳዊት፡፡
ሉቃስ 1፥34 “ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል? አለችው። 35 መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት። መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፥ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል፡፡”
ጠቢቡ ሰሎሞን በመኃል 4፥12 "ገነት ዕፁት አዘቅት ኅትምት" (12 እኅቴ ሙሽራ የተቈለፈ ገነት፥ የተዘጋ ምንጭ የታተመም ፈሳሽ ናት።) እንዳለ፤ እመቤታችን ድንግል ወእም ትባላለች፤ እናትም ድንግልም ማለት ነው፡፡ እናትነትን ከድንግልና ጋር አስተባብሮ መገኘት ለፍጥረታዊ ሰው የማይቻል ቢሆንም ለድንግል ማርያም ግን ተችሏል። ሌሎች ሴቶች ድንግል ቢሆኑ እናት መሆን አይችሉም፡፡ እናት ከሆኑ ደግሞ ድንግል አይባሉ፡፡ “ልጅዋ አምላከ ወሰብ” እንደሆነ እርሷም “ድንግል ወእም” ትባላለች፡፡ ድንግል በክልኤ (በሁለት ወገን ድንግል፤) በሥጋዋ ድንግል እንደሆነች ሁሉ ከሃልዩና ከነቢብ ኃጢአት ንጽህት ናት፡፡
እመቤታችን ድንግል ማርያምና አረጋዊው ቅዱስ ዮሴፍ፤
ሉቃ. 1፥26-27 “መልአኩ ገብርኤል ናዝሬት ወደምትባል ወደ ገሊላ ከተማ፥ 27 ከዳዊት ወገን ለሆነው ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨች ወደ አንዲት ድንግል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ፥ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ።" መልአኩ ለብሥራት የመጣው ለዮሴፍ ወደታጨች ድንግል እንደሆነ ከላይ ያለው የእግዚአብሔር ቃል ይናገራል። የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እንደ ቃሉ አግባብ ለተነገረለት ዓላማ ተለይቶ ካልተተሮጎመ የመጽሐፍ ቅዱስን ቃላት እርስ በርሳቸው አጋጭተን የምናደባድባቸው እንሆናለን።
እጮኛ ማለት ምን ማለት ነው? ወንድ ሚስት የምትሆነውን ያጫል። እንዲሁም ሰዎች ከሰዎች መካከል ተመርጠው ለሐኃላፊነት፣ ለሹመት፣ ለአገልግሎት ይታጫሉ። አረጋዊው ቅዱስ ዮሴፍም በመንፈሳዊነቱና በአረጋዊነቱ ተመርጦ በመቅደሱ እንድትኖር ብጽአት የተሰጠችውን እመቤታችንን ሲያገለግልና ሲንከባከብ የኖረ ቅዱስ አባት ነው። መታጨት ለባልና ለሚስትነት (ለሥጋ) ብቻ እንዳልሆነ የመጽሐፍ ቃል ሲያስረዳ በ1ኛ ቆሮ. 11፥2 ላይ " 2 በእግዚአብሔር ቅንዓት እቀናላችኋለሁና፥ እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና፤" ይላል። የዚህ ዓይነቱ መታጨት የሚያመለክተው የእግዚአብሔር ልጅነት የማግኘት ሹመትንና ይህንን የመጠበቅ ኃላፊነትን የምያስገነዝብ ቃል ነው።
ደንግል ማርያምን እንዲንከባከብ እንዲጠብቅ የታጨው ዮሴፍ በመንፈስ ቅዱስ ግብር ፀንሳ በተገኘች ጊዜ ድንግል ማርያም በመንፈስ ቅዱስ መፅነሷን ስላላወቀ ከሰው የፀነሰች መስሎት በሰው ፊት ገበናዋን ላለመግለጥ ተጠንቅቋል። ማቴ. 1፥18-19 "ከመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች። 19 እጮኛዋ ዮሴፍም ጻድቅ ሆኖ ሊገልጣት ስላልወደደ በስውር ሊተዋት አሰበ።" ይላል ። ነገር ግን የድንግል ማርያም በመንፈስ ቅዱስ ግብር አምላክን መጽነስ በአክራሪዎቹ የአይሁድ ማኅበረ ሰብ ዘንድ ቢሰማ ዮሴፍ ለታጨበት ድንግል ማሪያምን የመጠበቅ ኃላፊነት እምነት ማጉደል ወንጀል በመሆኑ የሚያስከትለውን ቅጣት ሲያስብ ዮሴፍ ፈራ። በዚህ ጊዜ "20 እርሱ ግን ይህን ሲያስብ፥ እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ታየው፥ እንዲህም አለ። የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ፥ ከእርስዋ የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ። 21 ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ። 22 በነቢይ 'ከጌታ ዘንድ። 23 እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል' የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኖአል፥ ትርጓሜውም። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው። 24 ዮሴፍም ከእንቅልፉ ነቅቶ የጌታ መልአክ እንዳዘዘው አደረገ፤ እጮኛውንም ወሰደ፤" (ማቴ. 1፥20-24)
ቅዱስ ዮሴፍ ከላይ የጠቀስናቸው ሁኔታዎች ሁሉ ውስጥ የገባው በጊዜው የድንግል ማርያም ክብር የአምላክ እናትነቷ ስላልተገለጠለት ማንነቷን ስላላወቀው ነበር፤ ለዚህ ነው በማቴ. 1፥25 "25የበኩር ልጅዋንም እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም፤" የተባለው። ቅዱስ ዮሴፍ የእመቤታችንን ክብር ያወቀው መቼ ነው? ከተባለ፡-
ሀ. ቅዳሴ መላዕክት ሲሰማ ሉቃ. 2፥13-14 "13 ድንገትም ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ። እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ።14 ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ።"
ለ. ሥርቀተ ስብሐት እግዚአብሔር ዐቢይ (የጌታ ክብር መታየት ጊዜ) ሉቃ. 2፥8-9 "8 በዚያም ምድር መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ በሜዳ ያደሩ እረኞች ነበሩ። 9 እነሆም፥ የጌታ መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አበራ፥ ታላቅ ፍርሃትም ፈሩ።"
ሐ. ሑሩተ ኮከብ በካለፍና (የኮከቡ መንገደኞችን መምራት) ማቴ. 2፥9-10 እነሆም፥ በምሥራቅ ያዩት ኮከብ ሕፃኑ ባለበት ላይ መጥቶ እስኪቆም ድረስ ይመራቸው ነበር። 10 ኮከቡንም ባዩ ጊዜ በታላቅ ደስታ እጅግ ደስ አላቸው።
መ. ምጻተ ሰብአ ሰግል ዘምስለ አምሃ (የጥበብ ሰዎች ለመንግሥቱ ወርቅ፣ ልክህነቱ እጣን፣ ለሞቱ ከርቤ ይዘው ከእጅ መንሻ ጋር በምጡ ጊዜ) ማቴ. 1፥11-1211 ወደ ቤትም ገብተው ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፥ ወድቀውም ሰገዱለት፥ ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን ከርቤም አቀረቡለት።" እነዚህ ሁሉ እስኪፈጸሙ ድረስ ቅዱስ ዮሴፍ የድንግል ማርያምን እመ አምላክ መሆኗን አላወቃትም ነበር። ለዚህ ነው “መጽሐፍ ቅዱስ የበኩር ልጅዋን እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም ነበር” የሚለው።
በኩር እንዴት ይተረጎማል? በኩር ማለት ከሰውም ይሁን ከእንስሳ የእናቱን ማኅጸን ከፍቶ የሚወጣ ማለት ሲሆን በኩር የሆነ ሁሉ የግዴታ ተከታይ አለው ማለት አይደለም። ዘጸአት 12፥29 "29 እንዲህም ሆነ፤ እኩለ ሌሊት በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር፥ በዙፋን ከተቀመጠው ከፈርዖን በኵር ጀምሮ በግዞት እስካሉት እስከ ምርኮኞቹ በኵር ድረስ፥ የግብፃውያንን በግብፅ ምድር የተገኘውን በኵር ሁሉ፥ የእንስሳውንም በኵሮች ሁሉ መታ።"
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ ዓለም ከአብ፤ ድኅረ ዓለም ከድንግል ማርያም ተወልዶ ለቀዳማይ ልደቱ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው በኩር ነው። መዝ. 109(110)፥3 "3 ከአንተ ጋር ቀድሞ በኃይልህ ቀን፥ በቅዱሳን ብርሃን፥ ከአጥቢያ ኮከብ አስቀድሞ ከሆድ ወለድሁህ። እንዳለና እንዲሁም ቅዱስ ጳውሎስ በቆላይሲስ 1፥15-16 ላይ "15-16 እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው። የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው። ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል።" በማለት የወልድን ቀዳማይ ልደት አረጋግጦልናል። እንዲሁም ከቅድስት ድንግል ማርያም በተወለደው ደኀራዊ ልደቱ ተቀዳሚ ተከታይ እንደሌለው ዮሐንስ ወንጌላዊ በዮሐ.3፥16 ላይ "16 በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።" በሚለው ቃል ውስጥ አንድያ ልጅ የተባለው በዚህ የወንጌል ኃሳብ ወስጥ በሥጋ ማርያም ተግልጦ ዓለምን ያዳነው ክርስቶስ በመሆኑ በደኀርዊ ልደቱም ተቀደሚ ተከታይ የሌለው አንድያ መሆኑንን አረጋግጦልናል።
ጌታ በሞቱ ዓለምን ላማዳን በመስቀል ላይ ነፍሱን ስለ እኛ አሳልፎ ሊሰጥ በቀረበበት ደቂቃ እናቱን ድንግል ማርያምን የሚያስጠጋበት የሥጋ ዘመድ ተቀዳሚም ተከታይም ስላልነበረው የጌታው ፍቅር አገብሮት በመጨረሻዋ የጭንቅ ሰዓት በመስቀሉ ሥር ለተገኘው ተወዳጁ ሐዋርያ ለወንጌላዊው ዮሐንስ አደራ ሰጠ። የዮሐንስ ወንጌል 19፥26-27 "26 ኢየሱስም እናቱን ይወደው የነበረውንም ደቀ መዝሙር በአጠገቡ ቆሞ ባየ ጊዜ እናቱን አንቺ ሴት፥ እነሆ ልጅሽ አላት። 27 ከዚህ በኋላ ደቀ መዝሙሩን እናትህ እነኋት አለው። ከዚህም ሰዓት ጀምሮ ደቀ መዝሙሩ ወደ ቤቱ ወሰዳት። ወንጌላዊው ዮሐንስ ምስጢረ ሥጋዌን ከሌሎቹ ወንጌላውያን በበለጠ አስፍቶና አምልቶ የጻፈው ከእመቤታችን ባገኘው መረዳት እንደሆነ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ይናገራሉ። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የእመቤታችን ኑሮ ከዮሐንስ ጋር፣ ውሎዋ ደግሞ ከሐዋርያት ጋር ነበር።
3. ማርያም ወላዲተ አምላክ (አምላክን የወለደች)
ድንግል ማርያም “ወላዲተ አምላክ (አምላክን የወለደች) ተብላ እንድትጠራ የተወሰነው በ431 ዓ.ም በኤፌሶን ከተማ 200 የቤተክርስቲያን ሊቃውንት የንስጥሮስን ኑፋቄ በቅዱስ ቄርሎስ አፈ ጉባኤነት ባወገዙበት ጊዜ ነበር፡፡ ንስጥሮስ “ማርያም ወላዲተ ሰብ እንጂ ወላዲ አምላክ አትባልም ሰውን ወልዳ በዮርዳኖስ በተጠመቀ ጊዜ አምላክ አደረበት” በማለቱ የተወገዘ መናፍቅ ነው፡፡
መላኩ ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔ ዘንድ ተልኮ "ትፀንሻለሽ" ባላት ጊዜ እመቤታችን "ወንድ ሳላውቅ እንደምን ይሆኛል?" ብላ ከመላኩ ጋር ተከራክራለች። "እስመ አልቦ ነገር ዘይሰአኖ ለእግዚአብሔር፤ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም” ባላት ጊዜ “ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ፤ እንደቃልህ ይደረግልኝ” ብላ በእምነት ስትቀበል ሰማይና ምድር የማይወስኑት አካላዊው ቃል ከሥጋ ጋር፤ ሥጋም ከቃል ጋር በፍጹም ተዋሕዶ ተዋሐደ። ፈጣሬ ዓለማት ቃል ሰማያዊነቱን ሳይለቅ በድንግል ማርያም ማኅጸን ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ተፀነሰ። ቀዳማዊው ቃል ዳኃራዊ ሥጋን ስለተዋሐደ ተፀነሰ ተባለ። በቀዳማዊ ልደቱ ጊዜ እናት ያላስፈለገው ቃል፤ ከባሕርይ አባቱ ከአብ አካል ዘእምአካል ባሕርይ ዘእምባሕርይ የተወለደ ወልድ፤ በዳኃራዊ ልደቱ ደግሞ እንበለ ዘር ያለ አባትም ምንም ምክንያት ሳያስፈልገው ከድንግል ማርያም ተፀንሶ ተወለደ። ስለዚህ ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ መሆኗ የተረጋገጠ እውነት ነው።
በመጽሐፍ ቅዱስ ሰለ ጌታችን የባሕርይ አምላክነትና የእመቤታችንን ወላዲተ አምላክነት ከሚያሳረዱት ውስጥ ጥቂቶቹ፡-
(ሉቃ. 1፥35) “ከአንቺ የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል፡፡” በማለት እንዳበሠራት ቅዱስ ገብርኤል። ከድንግል ማርያም ያለ ዘርዐ ብእሲ ፀንሳ የወለደችው የእግዚአብሔር ልጅ ስለሆነ ወላዲተ አምላክ ናት።
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በመላኩ ብሥራት ወልድ አምላክን ከፀነሰች በኋላ በዚያው ወራት በተራራማው አገር ወደምትኖረው ወደ እመ ዮሐንስ መጥምቅ ኤልሳቤት እንደሄደች በጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ኤልሳቤትም የድንግል ማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ በማኅጸኗ የነበረው ፅንስ ሲሰግድ ተሰማት። በልዩ ሁኔታ መንፈስ ቅዱስ አደረባት ኤልሳቤት ድንግል ማርያም የፀነሰችው ጌታ ጸባኦት መሆኑን ያደረባት መንፈስ ቅዱስ ሲገልጥላት በታላቅ ድምፅ ጮኻ “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፥ የማኅጸንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል?” በማለት ወላዲተ አምላክ መሆኗን በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝታ መስክራለች።
ሉቃ. 1፥33-44 “39 ማርያምም በዚያ ወራት ተነሥታ ወደ ተራራማው አገር ወደ ይሁዳ ከተማ ፈጥና ወጣች፥ 40 ወደ ዘካርያስም ቤት ገብታ ኤልሳቤጥን ተሳለመቻት። 41 ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ፅንሱ በማኅጸንዋ ውስጥ ዘለለ፤ በኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ ሞላባት፥ 42 በታላቅ ድምፅም ጮኻ እንዲህ አለች። አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፥ የማኅጸንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። 43 የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል? 44 እነሆ፥ የሰላምታሽ ድምፅ በጆሮዬ በመጣ ጊዜ ፅንሱ በማኅጸኔ በደስታ ዘሎአልና። 45 ከጌታ፤ የተነገረላት ቃል ይፈጸማልና ያመነች ብፅዕት ናት።”
ቅዱስ ጳውሎስም በሚከተሉት ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በሥጋ ማርያም የተገለጠው ጌታ በሥጋው የመለኮት ምላት እንዳለ ይናገራል። "በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና። የተባለለትን ጌታ የወለደችው ድንግል ማርያም ስለሆነች ወላዲተ አምላክ ለማለት አናፍርባትም። ቆላ. 2፥6-10 6 እንግዲህ ጌታን ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ተቀበላችሁት በእርሱ ተመላለሱ። 7 ሥር ሰዳችሁ በእርሱ ታነጹ፥ እንደ ተማራችሁም በሃይማኖት ጽኑ፥ ምስጋናም ይብዛላችሁ። 8 እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፥ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ። 9 በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና። 10 ለአለቅነትና ለሥልጣንም ሁሉ ራስ በሆነ በእርሱ ሆናችሁ ተሞልታችኋል።
1ኛ ጢሞ. 3፥14-16 “ 14 ፈጥኜ ወደ አንተ እንድመጣ ተስፋ አድርጌ ይህን እጽፍልሃለሁ። 15 ብዘገይ ግን፥ በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት መኖር እንዴት እንደሚገባ ታውቅ ዘንድ እጽፍልሃለሁ፤ ቤቱም የእውነት ዓምድና መሠረት፥ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ነው። 16 እግዚአብሔርንም የመምሰል ምሥጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው፤ በሥጋ የተገለጠ፥ በመንፈስ የጸደቀ፥ ለመላእክት የታየ፥ በአሕዛብ የተሰበከ፥ በዓለም የታመነ፥ በክብር ያረገ።” እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ።
አባታችን አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ የመለኮትን ስፋቱ፣ ርቀቱንና ታላቅነቱን ካብራራ በኋላ ሥፍራ የማይዘው መወሰን ለባሕርይው የመይስማማው አምላክ በድንግል ማርያም ማኅጸን ያደረበት ምስጢሩ አዕምሮን የሚያልፍ ስልሆነበት እንዲህ በማለት ይጠይቃል፤ "ቅድስት ድንግልም ለሁሉ የሚሆን የፅንሷን ነገር እንዲህ እያልን እንመርምር፤ ድንግል ሆይ እሳተ መልኮት በሆድሽ ባደረ ጊዜ ፊቱ እሳት፤ ልብሱ እሳት ቀሚሱ እሳት ነው፤ እንደምን አላቃጠለሽ? ሰባት የእሳት ነበልባል መጋረጃ በሆድሽ ውስጥ ወዴት ተዘጋጀ? ወዴትስ ተጋረደ? በጎንሽ በቀኝ ነውን? ወይስ በጎንሽ በግራ ነውን? ትንሽ አካል ስትሆኝ የሚያንጸባርቅ ነደ እሳት የሚከበው ኪሩቤል የሚሸከሙት ዙፋን በሆድሽ ውስጥ ወዴት ተዘጋጀ? ወዴትስ ተተከለ?" ብሎ የተገረመበትን የድንግል ማርያምን ወላዲተ አምላክነት ከገለጠ በኋላ ይህንን በሰብዓዊ ሕሊና ተመራምሮ መድረስ የማይቻል ረቂቅ የእግዚአብሐር ምስጢር መሆኑን ሲያስረዳ “ይህንን ባሰብኩ ጊዜ ሕሊናዬ ተሰውሮ ወደ ላይ ወጥቶ የሕያው መሰወሪያ የሆነውን ሊገልጥ ይወዳል፤ ከነደ እሳቱ የተነሳ ይፈራል ከአየራት ከእርቦአቸው እርቦ አይደርስም፤ ይህንንም ባሰብኩ ጊዜ ሕሊናዬ በንፋስ ትከሻ ተጭኖ በምሥራቅና በምዕራብ በሰሜንና በደቡብ በዳርቻውም ሁሉ ሊበር ይወዳል። ....አቅቶት ወደ ቀደመ አኗኗሩ ይመለሳል።" በማለት የድንግል ማርያምን ወላዲተ አምላክነት በገናንነቱ የማይደረስበት፣ ከጥልቅ ምስጢርነቱ የተነሳ የማይመረመር ድንቅ ነው በማለት መስክሯል።
ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊም ከሌሎቹ ሐዋርያት በተለየ ሁኔታ ምስጢረ ተዋሕዶን አብራርቶና አስፋፍቶ በገለጠበት ወንጌሉ በዮሐ. 1፥1 ላይ ከድንግል ማርያም የተወለደው “በመጀመሪያ ቃል ነበረ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፡፡ ቃልም እግዚአብሔር ነው፡፡” ካለ በኋላ ቁ. 14 “ቃልም ሥጋ ሆነ ጸጋና እውነትን ተመልቶ በእኛ አደረ አንድ ልጅም በአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነውን ክብሩን አየን፡፡” ይላል። ቃል ሥጋን በመዋሐዱ በቀዳማዊ ልደቱ ከነበረው ክብሩ አንዳች ሳይጎድልበት በዳኃራዊ ልደቱ ከድንግል ማርያም ሥጋን ነስቶ ተወለደ። ስለዚህ ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ ናት።

4. ድንግል ማርያም የታመነች፤ 
መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ባበሠራት ጊዜ የደረሳት ዜና አስደንጋጭ ነበር እየተደሰቱ የሚቀበሉት አልነበረም ምክንያቱም አክራሪ በሆነው የአይሁድ ማኅበረሰብ መካከል ያላገባች ልጃገረድ ያለ ባል ልጅ መውለድ በድንጋይ ያስወግራል። ስንቱ ጥርሱን ሊነክስባት ነው። በማኅበረሰቡ አይንሽ ላፈር ልትሰኝ ነው። ስለዚህ እንደዚህ አይነቱን መሥዋዕትነት የሚያስከፍል ዜና ዕልል እያሉ የሚያደምጡት አይደለም። ድንግል ማርያም ዜናው ዋጋ የሚያስከፍላት መሆኑን ብታውቅም በእግዚአብሔር በመታመን “ይሁንልኝ” ብላ ተቀበለች። ይህንን አስፈሪ ዜና እግዚአብሔርን ለማገልገል ስትል ዋጋ ለመክፈል ፍርሃቷን በእምነት አርቃ ታመነች።
ሉቃስ 1፥28-38 “28 መልአኩም ወደ እርስዋ ገብቶ ደስ ይበልሽ፥ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፥ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ አላት። 29 እርስዋም ባየችው ጊዜ ከንግግሩ በጣም ደነገጠችና። ይህ እንዴት ያለ ሰላምታ ነው? ብላ አሰበች። 30 መልአኩም እንዲህ አላት። ማርያም ሆይ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ አግኝተሻልና አትፍሪ። 31 እነሆም፥ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፥ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። 32 እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፥ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ 33 በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለላም ይነግሣል፥ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም። 34 ማርያምም መልአኩን ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል? አለችው። 35 መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት። መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፥ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል። 36 እነሆም ዘመድሽ ኤልሳቤጥ፥ እርስዋ ደግሞ በእርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች፥ ለእርስዋም መካን ትባል ለነበረችው ይህ ስድስተኛ ወር ነው፤ 37 ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና። 38 ማርያምም እነሆኝ የጌታ ባሪያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ አለች።
5. ማርያም ሰዓሊተ ምሕረት ለውሉደ ሰብ (ለትውልድ ሁሉ ምሕረትን የምትለምን)
ሉቃ. 1፥30 “በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ አግኝተሻል፡፡” ከቅዱስ ገብርኤል ብሥራት እንደምንረዳው ድንግል ማርያም በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን ያገኘች እመቤት ናት፡፡ ቃል ኪዳንዋ ከዚህ የተነሳ በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት አለው፡፡
በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን ያገኙ ቅዱሳን ምሕረትን ቸርነትን ለምነው አግኝተዋል፡፡ አብርሃም በዘፍ. 18፥3 “አቤቱ በፊትህ ሞገስን አግኝቼ ከሆነ አትለፈኝ አለ፡፡” ከቁ. 23-32 አብርሃም ስለ ሰዶም ለመነ፡፡ ሙሴ ዘጸ. 32፥9-14 9 እግዚአብሔርም ሙሴን። እኔ ይህን ሕዝብ አየሁት፥ እነሆም አንገተ ደንዳና ሕዝብ ነው። 10 አሁንም ቍጣዬ እንዲቃጠልባቸው እንዳጠፋቸውም ተወኝ፤ አንተንም ለታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ አለው። 11 ሙሴም በእግዚአብሔር በአምላኩ ፊት ጸለየ፥ አለም። አቤቱ፥ ቍጣህ በታላቅ ኃይልና በጽኑ እጅ ከግብፅ ምድር ባወጣኸው በሕዝብህ ላይ ስለ ምን ተቃጠለ? 12 ግብጻውያንስ። በተራራ መካከል ሊገድላቸው፥ ከምድርም ፊት ሊያጠፋቸው ለክፋት አወጣቸው ብለው ስለ ምን ይናገራሉ? ከመዓትህ ተመለስ፥ ለሕዝብህም በክፋታቸው ላይ ራራ። 13 ዘራችሁን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛለሁ፥ ይህችንም የተናገርኋትን ምድር ሁሉ ለዘራችሁ እሰጣታለሁ፥ ለዘላለምም ይወርሱአታል ብለህ በራስህ የማልህላቸውን ባሪያዎችህን አብርሃምንና ይስሐቅን እስራኤልንም አስብ። 14 እግዚአብሔርም በሕዝቡ ላይ ሊያደርግ ስላሰበው ክፋት ራራ።
የእመቤታችን ሞገስ ከቅዱሳን ሁሉ ሞገስ የበለጠ የአምላክ እናት የሆነችበት ሞግስ ስለሆነ በዘመን የማይገደብ እስከ ምጽዓት የሚዘልቅ ለትውልድ ሁሉ የምሕረት ቃል ኪዳን አላት። ለዚህ ነው ድንግል ማርያም በሉቃስ 1፥47-48 "47 ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፥ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፤ 48 የባሪያይቱን ውርደት ተመልክቶአልና። እነሆም፥ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል፤" ያለችው።
እግዚአብሔር በቃልኪዳን ሥርዓት ሕዝቡንና ዓለምን ያስተዳድራል። “ኪዳነ ተካየድኩ ምስለ ኅሩያንየ፤ከመረጥኳቸው ሰዎች ጋር ቃልኪዳኔን አደረግሁ” ይላል መዝሙር 88(89)፥2፡፡ እግዚአብሔር ሰው የመረጠው ንጉሥና ሹም አይደለም፤ ሰው ግን እግዚአብሔር የመረጠውና የሾመው ክቡር ፍጥረት መሆኑን መምህራችን ኢየሱስ ክርስቶስ “አኮ አንትሙ ኅሩይክሙኒ አላ አነኅሩይኩክሙ፤ እኔ እናንተን መረጥኳችሁ እንጂ እናንተ እኔን አልመረጣችሁኝም” በማለት በዮሐንስ 15፥16 ደቀ መዛሙርቱን አስተምሯል። ስለዚህ ነው የኃይላን ኃያል ጌታ እግዚአብሔር በልበ አምላክ ዳዊት አንደበት “ከመረጥኳቸው ጋራ ቃልኪዳኔን አደረግሁ” ያለው።
ይህንን መሰረት በማደረግ ሰፊ የሆነ የቤተክርስቲያን ትምህርት መኖሩን የቅድስት ቤተክርስቲያን ልጆች የሚረዱት ሲሆን እነዚህን ለማብራራት ከስፋቱ የተነሳ በዚህ መልክት ሁሉን ማጠቃለል ባይቻልም ለእመቤታችን በወላዲተ አምላክነቷ፣ ለመላዕክት በንጽህናቸውና በትጋታቸው፣ ለጻድቃን በትጋታቸው፣ ለማዕታት በተጋድሎቸው ለሰው ልጆች በረከትና ከድኅነት ብኋላ ለደከሙበት የክርስትና ሕይወት በስማቸው ብንማጸን ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረትን የሚያስገኝ ቃል ኪዳን እንዳላቸው የእግዚአብሔር ቃል ያረጋግጣል።
በትንቢት ኢሳያስ 56፥4-6 "እግዚአብሔር ሰንበቴን ስለሚጠብቁ ደስ የሚያሰኘኝንም ነገር ስለሚመርጡ ቃል ኪዳኔንም ስለሚይዙ ጃንደረቦች እንዲህ ይላልና። ‘በቤቴና በቅጥሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ መታሰቢያና ስም እሰጣቸዋለሁ፤ የማይጠፋም የዘላለም ስም እሰጣቸዋለሁ" ይላል።
ከዚህ ቃል ስንነሳ ጃንደረባ የተባሉት በዚህ ዓለም ሁሉንም ማድረግ እየቻሉ እግዚአብሔርን ለማግልግል ሲሉ ሁሉን ትተው እግዚአብሔርን ማገልገል ሕይዎታቸው ያደረጉ ቅዱሳንን ማለት መሆኑን ልንረዳ ይገባል። ሰው ለስሙ መጠሪያ ልጅ ይወልዳል፤ ወይንም ምድራዊ ሀብትና ክብር ሥልጣን ያጠራቅማል፤ እነዚህ ቅዱሳን ግን እግዚአብሔርን ማገልገል ሀብታችው፣ በመንፈስና በትምህርት የወለዷቸውን ልጆቻቸውን ልጆቻቸው በማድርግ በፍጹም በመስጠት እግዚአብሔር በማቴ. 19፥29 ላይ “ስለ ስሜም ቤቶችን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ ሁሉ መቶ እጥፍ ይቀበላል የዘላለምንም ሕይወት ይወርሳል።” ያለውንና በማርቆስ ወንጌል 10፥29-30 "....እውነት እላችኋለሁ፥ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ፥ አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን ወንድሞችንና እኅቶችንም እናቶችንም ልጆችንም እርሻንም መቶ እጥፍ፥ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም።" በማለት የሰጠውን ቃልኪዳን በማመን በክርስቶስ ስም የመጣባቸውን ጸዋትዎ መከራ ሁሉ ሳይሰቀቁ በሕይዎት ዘመናቸው ሁሉ አክብረውትና አስከብረውት አልፈዋል። ከዚህ የተነሳ “በቤቴና በቅጥሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ መታሰቢያና ስም እሰጣቸዋለሁ፤” እንዳለ የእግዚአብሔር ቤት በተባለችው ቤተክርስቲያን ቢታሰቡ፣ ቢከበሩ፣ በስማቸው የመታሰቢያ ሕንፃ ቢታነፅ፣ በሥጋቸው የሚፈተኑ ክርስቲያኖች ቃልኪዳን ስለ ሰጠሃቸው፤ ስለ “ቅዱሳን” ስትል ማረን ቢሉ (ብንል) መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ነው። በእመቤታችንም ሆነ በቅዱሳን ቃል ኪዳን ላይ መደገፍ በፍጹም ከአምልኮ ጋር የተያዘ ነገር የለውም።
ይህ በኢሳያስ የተነገረው ቃል በብሉይ ኪዳን የተነገረና ያለፈ ቃል ነው ብለን እንዳንል እግዚአብሔር “የማይጠፋም የዘላለም ስም እሰጣቸዋለሁ።” ብሏል ዘላለማዊነት የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ሲሆን ዘላለም ነዋሪ፣ ዘመን የማይዘው፣ ከዘመን በላይ የሚኖር እንደሆነ የምናምን ከሆነ ቅድስት ድንግል ማርያምንም ሆነ ቅዱሳንና ጻድቃን ሰማዕታት በሥጋ በሕይወት እየኖሩም ሆነ በዓጸደ ነፍስ ቢሆኑ በቃልኪዳንቸው ተማምኖ ስማቸውን የጠራ ሁሉ እንደሚጠቀም ዘላለማዊ ቃል ኪዳን እንዳላቸው ማመን አስቸጋሪ ነገር አይደለም።
ጌታችን በማቴዎስ 10፥39 ላይ "ነፍሱን የሚያገኝ ያጠፋታል፥ ነፍሱንም ስለ እኔ የሚያጠፋ ያገኛታል።" እንዳለ ይህንን ዋጋ ለከፈሉት የዘላለም ከብር ሲሰጥ በማቴዎስ 10፥40-42 “እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል። ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፥ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል። ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋው አይጠፋበትም።” የተባለውን የእግዚአብሔር ቃል ማክበር ወንጌላዊነት ነው። ይቆየን

No comments:

Post a Comment