Thursday, October 31, 2013

ባልንጀራዬ ማነው? ሉቃ 10፡29



 


ባልንጀራዬ ማነው? ሉቃ 10፡29
ምንም እንኳን ሁሉም ሰው ከአንድ የአዳም ዘር የተገኘ ቢሆንም ሲወርድ ሲዋረድ በመጣው የሰው ልጆች በአከባቢ በቋንቋ ፣ በአኗኗር ፣ በባሕል ወዘተ መለያየት እንዲሁም የቁጥር መብዛት የተነሣ፤ እስከተወሰነ የዘር ግንድ ድረስ ያለውን የሥጋ ዘመዴ ብሎ ሲጠራ ሌላውን ደግሞ ባዕድ ይለዋል፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው ብቻውን ወይም የሥጋ ዘመዴ ካላቸው ጋር ብቻ ስለማይኖር በአጠቃላይ በማኅበራዊ ሕይወቱ፣ በሥራው ፣ በትምህርቱ ከብዙ ዓይነት ሰዎች ጋር ይገናኛል አብሮም ይኖራል፡፡ በእነዚህ አጋጣሚዎችም በሃሳብ፣ በዓላማ ከሚመስሉት ጋር ባልጀርነትን (ጓደኝነትን) ይመሠርታ፡፡ በብዙ አጋጣሚ እንደሚታየውና በጽኑ ፍቅር ላይ የተመሠረተ ጓደኝነት ከሆነ ከሥጋ ዝምድና ቢበልጥ እንጂ የማያንስ ችግርን ደስታን ምስጢርን በጋራ የሚካፈሉበት፣ ለአንተ ለአንቺ የሚባባሉበት ትልቅ የሕይወት ክፍል ነው፡፡


በአንፃሩ ደግሞ የሔዋንና የእባብ ጓደኝነትን ይመስል፣ አንዱ ሌላውን ለማጥፋት የሚሯሯጥበት ፣ መተማመን የሌለበት፣ ጥላቻና ቅንዓት የሰፈነበት ይሆናል ለጉዳት ሲዳርግ እንመለከታለን፡፡ ይህም የሚያመለክተው አንድ ሰው በሰፈሩ በት/ቤቱ በመሥሪያ ቤቱ ወዘተ የሚያውቀውን ወይም አብሮ የሚውለውን ሁሉ ጓደኛ ሊያደርግ እንደማይችልና ለባልንጀራነት የራሱ የሆነ መቀራረብ፣ የፍቅርና የውህደት ደረጃ እንዳለው ነው፡፡
በርካታ ሰዎች ጓደኛዬ ባሉት ሰው ክህደት ደርሶባቸው ወንጀል ተፈጽሞባቸውና ታማኝነት ጎድሎባቸው ሰውን ሁሉ የሚጠራጠሩ አንዳንዴም ብቻቸውን ለመኖር የወሰኑ ያህል ከሰዎች ተገልለው የሚታዩ አሉ፡፡ መልካም ጓደኝነትን በዕጣ ወይም በሒሳብ ቀመር ተጠቅመን የምናገኘው ነገር ባይሆንም የራሱ የሆኑ መመዘኛዎች ግን ይኖሩታል፡፡ እውነተኛ ጓደኞች ውድና ብቅር እንደሆነ አልማዝ ናቸው የችግር ተካፋይ፣ የሐዘን አጋሮች፣ ተስፋ የቆረጠውን ተስፋውን የሚያለመልሙ ፣ የወደቀውን የሚያነሡ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሞት ወደ ሕይወት የሚመልሱ በአጠቃላይ ከጎናችን ሆነው የሕይወት ስንክሣራችንን የሚጋሩ ጓደኞች ዋጋቸው ከወርቅም ከዕንቁም የበለጠ ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ በጎ ስጦታ መልካምም ነገር ሁሉ ከላይ ነው አንዲል (ያዕ 1፡17) መልካም ጓደኛ ባልንጀራ ከፈጣሪ ነው የሚቸረው፡፡
አብሮን የዋለ አብሮን ያደረ በተለያየ እንቅስቃሴአችን ውስጥ የምናገኘው ሰው ሁሉ የልብ ጓደኛችን ሊሆን አይችልም ነገር ግን ከእነዚህ ሰዎች መሀል ሃሣቡ ከሃሣባችን፣ ዓላማው ከዓላማችን ሕይወቱ ከሕይወታችን የሚገጣጠመው ብቻ ባልንጀራችን ይሆናል፡፡ ለዚህም ነው ጓደኝነት ምርጫን የሚጠይቅ ተግባር የሚሆነው፡፡
ብዙ ሰዎች በጓደኝነት ጉዳይ ብቻም ሳይሆን በሌሎች ነገሮች ላይም እነርሱ ያልሆኑትን ከሌላው የመመኘት ባሕርይ አለ ነገር ግን ሰዎች እንዲታመኑልን ከፈለግን እኛ ታማኝ፣ ሰዎች እንዲያፈቅሩን ከፈለግን እኛ የፍቅር ሰዎች መሆን፣ ሰዎች ይቅር እንዲሉን ከፈለግን እኛ ዘወትር የይቅርታ ልብ ሊኖረን ይገባል፡፡ በአጠቃላይ እኛ የማንፈልገውን የማንወደውን ነገር በእኛ ሊደረግ የማንፈልገውን ክፋት፣ ተንኮል፣ ምቀኝነት፣ ክደት፣ ጭካኔ፣ ቂም በሌላው ላይ አለማድረግ፡፡ ‹‹መጽሐፍም በአንተ ላይ ሊደረግ የማትፈልገውን በሌላው አታድርግ ይላል›› ማቴ 7
በአጠቃላይ መልካም ጓደኛ ለማግኘት ከፈለግን እኛም ለሌሎች ጥሩ ጓደኞች መሆን ይጠበቅብናል፡፡ እንዲያውም ጓደኝነት መወደድን ሳይሆን መውደድን ፣ መፈቀርን ሳይሆን ማፍቀርን፣ መከበርን ሳይሆን ማክበርን፣ ጥቅም ማግኘትን ሳይሆን ማስገኘትን የሚጠይቅ ሥነምግባር ነው፡፡
አንዳንድ ሰዎች ጓደኝነትን የሚመሠርቱት ጥቅም ለማግኘት ሆን ብለው አስበው፣ በሽንገላ ከንፈር አንደበታቸውን በማጣፈጥ፣ ንብረት ለመውረስ ፣ ገንዘብ ለመዝረፍ ይሞክራሉ ከተሳካላቸውም ያደርጉታል ፡፡ ጓደኛዬ ባሉት ሰው ትከሻ ተረማምደው ከሀብት ርካብ ከሥልጣን ኮርቻ ላይ ከተፈናጠጡ በኋላ ያንን ሰው ከነመፈጠሩ ይረሱታል፡፡ ቅዱስ ዳዊት ‹‹አቤቱ ደግ ሰው አልቋልና አድነኝ ከሰው ልጆችም መተማመን ጎድሏልና›› (መዝ 111 (112)፡1) በማለት የተናገረው ለእንደዚህ ዓይነት ከዳተኛ ባልንጀራዎች ሳይሆን ይቀራል?
እግዚአብሔር ክፉ መንፈስንና ክፉ ኃሣብ ያላቸውን ሁሉ በመልካም ጎዳና ይምራልን፡፡
መፅሐፍ ቅዱስ ስለ ክፉ ባልንጀርነት ምን ይላል?
በመጽሐፍ ቅዱስ ለመልካምና ለክፉ ባልንጀርነት ጥሩ ምሣሌዎች የሚሆኑ ሁለት ታሪኮች አሉ፡፡ እግዚአብሔር ከእረኝነት አንስቶ የቀባው ብላቴናው ዳዊት በንጉሥ ሳኦል ቤት ሳለ ክብርና ሞገስን በማግኘቱ ንጉሡ ቀናበት ሊያጠፋውም እጅግ ጣረ ፡፡ የሳዖል ልጅ ዮናታን ግን የዳዊት የልብ ጓደኛው ነበርና ከአባቱ ሰይፍና ጦር እንዲሸሽ እያደረገ ይረዳው ነበር፡፡
ስለፍቅራቸውም ‹‹የዮናታን ነፍስ በዳዊት ነፍስ ታሠረች፣ ዮናታንም እንደነፍሱ ወደደው፣ ስለወደደውም ከዳዊት ጋር ቃል ኪዳን አደረገ›› በማለት ይገልፃል፡፡ (1ሳሙ 18፡10-15) እና (1ሳሙ 19፡1-5) ጓደኝነት ከሆነ አይቀር እንደዚህ ነፍስ ለነፍስ የሚዋሀዱበት ሊሆን ይገባዋል፡፡
የክፉ ባልንጀርነት ምሣሌ ደግሞ ኢዮናዳብ ነው፡፡ የዳዊት ልጅ አምኖን በአባቱ በኩል እህቱ የምትሆን ትዕማር የተባለችውን ልጃገረድ በልቡ ተመኝቷት ሳለ፣ ምን እንደሚያደርግ ቢቸግረው ጓደኛው ኢዮናዳብን አማከረው፡፡ ኢዮናዳብ አይሆንም ከማለት ይልቅ በክፉ ምክሩ ትዕማርን እንድትደፈር አደረገ አምኖንም በዚህ ተግባሩ በወንደሙ አቤሴሎም ሠይፍ ጠፋ (2ሳሙ 13፡1-39) እንዲህ ዓይነት ባልንጀሮች የዲያብሎስ ጋሻ አጃግሬዎች የሞት አበጋዞች ናቸው፡፡
ወጣትነት ስሜታዊነት እሳትነት ፈጣንነት ነው፡፡ በቃለ እግዚአብሔር ልጓምነት ካልታገታም ጎትቶ ከገደል ሊጥል ከባሕር ሊከት ይችላል፡፡ በዚህ ላይ የጓደኛ ተፅዕኖ ከታከለበት ደግሞ ምን ያል አስቸጋሪ እንደሚሆን መገመት አያዳግትም፡፡
ወጣቶች እንኳንስ የልብ ጓደኛቸውን አዘውትረው አብረው የሚውሏቸውን ሰዎች ሳይቀር በጥንቃቄ መምረጥ መቻል አለባቸው፡፡ ነቢዩ ‹‹ከቸር ሰው ጋር ቸር ሆነህ ትገኛለህ ከጠማማ ጋር ጠማማ ሆነህ ትገኛለህ›› በማለት ሲፅፍ ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ ‹‹ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል ይለናል›› (መዝ 17፡18) እና (1ቆሮ 15፡33)
ስለዚህ በዘመነ ውርዝና (ወጣትነት) ለጓደኝነት ያለን ስሜት የማንነታችንና የወደፊት የሕይወት አቅጣጫችን ላይ የሚኖረው ድርሻ የጎላ ነው፡፡ጠቢቡ ሰለሞን ‹‹ብረት ብረት ይስለዋል ሰውም ባልንጀራውን ይስላል›› እንዲል (ምሣ 27፡17) በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የባልንጀሮቻችን ባሕሪ የእኛም ባሕሪ ፣ ጠባያቸው ጠባያችን ፣ ግብራቸው ግብራችን ስለሚሆን የልብ ጓደኛን በመምረጡ በኩል ትኩረት ያስፈልገዋል፡፡
የመልካም ባልንጀርነት ባሕርያት ምን ይመስላሉ?
ጤናማ ጓደኝነት የራሱ የሆኑ መገለጫዎች አሉት እንደማለዳ ጤዛ ታይቶ የሚጠፋ፣ በሐሜትና በተንኮል የሚፈታ ለታይታ የሚፈረግና ጊዜያዊ ስሜት የሚንፀባረቅበት በጥቅም ፍለጋ ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡
የልብ ጓደኝነት በዘር በቋንቋ በአንድ አካባቢ ተወላጅነት ወዘተ ላይ በመመስረት ሊመጣ የሚችል አይደለም፡፡ ከጠባያዊ ግንኙነትም ፍጹም የራቀ ነው በሀገራችን ላይ መጽሐፍ ባልንጀራ የሚለው የሰው ዘርን ሁሉ ቢሆንም እኔ ግን በዚህ ጽሑፍ ባልንጀራ የምለው የልብ ጓደኛን (የፍቅር ጓደኛ፣ የዓላማ ጓደኛ የስራ ጓደኛን አለበለዚያም የምስጢር ጓደኛን ነው)
የመልካም ጓደኝነት ዋና ዋና ባሕርያት እነሆ፡-
1.   ፍቅር
‹‹መጽሐፍ ቅዱስ ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ›› ዘሌ 19፡18 ይላል ይህ ቃል እግዚአብሔር አምላካችን ለሙሴ በጽላቱ ላይ ቀርጾ ከሰጣቸው ከአስርቱ ትዕዛዛት አንዱ ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በመዋዕለ ሥጋዌው ከትዕዛዛቲቱ ሁሉ የትኛው እንደሚበልጠ በተጠየቀ ጊዜ ‹‹ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍፁም ነፍስህ በፍጹም ሃሣብህ ውደድ ታላቂቱና ፊተኛይቱ ይህች ናት ሁለተኛይቱም ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ የምትለው ናት›› በማለት ተናግሯል፡፡ (ማቴ 22፡35-40)
ባልንጀርነት በፍፁም ፍቅር ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት፡፡ ለእኔ ከማለት ለወንደሜ (እህቴ) ፣ ፍቅረኛዬ፣ ባልደረባዬ የሚያስብል ተለያይተው እስከሚገናኙ የሚያነፋፍቅ ከውስጥ ዘልቆ የሚሰማ እውነተኛ ፍቅር አንዱ የጓደኝነት ባሕሪይ ነው ፍቅር ካለ ስህተት ጥፋት ቢኖር እንኳ ፍቅር የስህተትን ብዛት ይሸፍናል፡፡
2.   ታማኝነት
የልብ ጓደኝነት በመተማመን መሠረት ላይ የታነፀ መሆን ይገባዋል፡፡ አንዱ ከሌላው የወሰደውን የማይመልስ ምስጢሩ የሚያባክን፣ ለክፉ አደጋ አጋላጦ የሚሰጥ ወዘተ ከሆነ ጠላትነት እንጂ ጓደኝነት ሊባል አይችልም፡፡ ከላይ እንደጠቀስናቸው ዳዊትና ዮናታን እስከሞት ድረስ የታመኑ ነበሩ ‹‹ዮናታን ዳዊትን እነሆ እኛ ሁለታችን በእኔና በአንተ በዘሬ በዘርህ መካከል ለዘላለም እግዚአብሔር ይሁን ብለን በእግዚአብሄር ስም ተማምለናል አለው፡፡ (1ሳሙ 20፡42) ዮናታን ለአባቱ አድልቶ ክፉ ሥራውን ደግፎ ታማኝነቱን አላጎደለም ዳዊትነም አልካደውም፡፡
3.   መረዳዳት (መተባበር)
ሰሎሞን ‹‹የቀረበ ወዳጅ ከራቀ ወንድም ይሻላል›› እንዳለ (ምሣ 27፡10) መልካም ጓደኛ ለችግር ጊዜ ደራሽ ፣ በመከራ ፣ በሐዘን፣ በደስታ ተካፋይ፣ መልካም አማካሪና፣ ገመናን ሸፋኝ ነው፡፡ ክርስቶስ ማስተማር በጀመረ ጊዜ ፊሊጶስን ይከተለው ዘንድ ሲጠራው ብቻውን አልሄደም፡፡
ይልቁንም ጓደኛውን ናትናኤልን በመጥራት ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አገናኝቶታል አብረውም ሐዋርያ ሆነዋል፡፡ (ዮሐ 1፡46) ይህ የሚያሳየው በመልካም ጓደኝነት ውስጥ አንዱ ያገኘውን ለሌላው ለማካፈል የሚጓጓበት ብቻውን የመጠቀም ፍላጎት የሌለበትና ከራስ አስበልጦ ለጓደኛ የሚታሰብበት ግንኙነት መሆኑን ነው፡፡
4.   ቤተሰባዊነት
እውነተኛ ባልንጀርነት በሁለቱ ሰዎች ብቻ ተወስኖና ከቤት ውጪ የሚደረግ ሆኖ አይቀርም፡፡ አንዱ በሌላው ቤተሰብ ታውቆና ተወዳጅቶ ዝምድናን ይፈጥራል በጓደኛው ቤተሰብ ውስጥ በሚፈጠር ሐዘንም ሆነ ደስታ ተካፋይ ይሆናል፡፡ በባልንጀራ ምርጫ ላይ ቤተሰብ የተወሠነ አስተዋጽዖ ሊያበረክት ይችላል ለምሣሌ ጓደኛ ያልነው ሠው እኛ ሳናውቅ የተለየ መጥፎ ባሕሪይ ያለውና፣ ለጥፋት ሊዳርገን፣ ከዓላማ ሊያስተን፣ ሃይማኖት ሊያስለውጠን፣ በጎውን ምግባራችንን ሊያስተወን፣ እንደቤታችንና እንደ አቅማችን እንዳንኖር መስመር ሊያስተን ፣ ከሚጨፍሩት ዳንኪራ ከሚረግጡት ፣ አስረሽ ምቺውን ከሚያበዙት፣ ከዘማውያን ከሰካራም ጋር ተወዳጅተን ሊሆን ይችላልና፡፡ በሌላው ግን ቤተሠብ በተዋደዱ ባልንጀራሞች በተማመኑ ጓደኛሞች መካከል ጣልቃ በመግባት ውሣኔን የሚወስን፣ ፍቅርን የሚያሻክር፣ መተማመንን የሚያጎድል ከሆነ አይሆንም ማለት ይገባል፡፡
5.   ይቅር ባይነት መቻቻል
ባልንጀርነት ዘወትር ፍጹምነት ሊኖረው አይችልም አልፎ አልፎ አንዳንድ ልዩነቶች እና አንደኛውን ወገን የሚያሳዝኑ ነገሮች በማወቅም ባለማወቅም ሊከሠቱ ይችላሉ፡፡ ኢዮብ በመከራው ሠዓት ሊያጽናኑትና አይዞህ ሊሉት የመጡት ሰሶት ጓደኞቹ ከፍኖተ እግዚአብሔር የሚያወጣው ነገር ቢናገሩትም እስከ መጨረሻው ድረስ ታገሣቸው ከዚያም አልፎ ከእግዚአብሔር ጋር አስታረቃቸው እንጂ ቂም አልያዘባቸውም በብዙ ፍቅር መካከል ቃለ ጥቂት ልዩነት ወይም ድንገተኛ መኳረፍ ለጥላቻ ሊያበቃን አይገባም፡፡
እንዲህ አይነት ጥቃቅን ነገሮች በመቻቻል ማሳለፍ ከእውነተኛ ጓደኝነት ባሕርያት አንዱ ነው፡፡ ‹‹በአቡነ ዘበሠማያት›› አባታችን ሆይ በሚለው ጸሎታችን ላይ ‹‹በደላችንን ይቅ በለን እኛም የበደሉንን ይቅር እንደምንል›› እንላለን ይህ እንኳንስ የልብ ጓደኛችን ቀርቶ ማንኛውም ሰው ቢበድለን ይቅርታ ማድረግ እንደሚገባ ያሳያል፡፡ በመሆኑም በመልካም ጓደኝነት ውስጥ ይቅር ባይነትና መቻቻልን እንደ ንጹህ ሸማ (ነጠላ) ለብሰን ልንደምቅባቸው ይገባል፡፡
6.   አብሮነት
መልካም ጓደኝነት በቦታ ርቀት፣ በሥራ ብዛትና በመሣሠሉት ምክንያቶች ተለያይቶ የሚቀሩበት ሕይወት አይደለም፡፡ እንኳንስ ዛሬ ሳይንስና ቴክኖሎጂ በተቀቀበትና የመረጃ የመገናኛ ዘዴዎች በተስፋፋበት ዘመን ቀርቶ በድሮው ዓለም እንኳ ሰዎች በደብዳቤ ግንኙነት ያደርጉ ነበር ቅዱስ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስና ቴቶ የላካቸው መልዕክታት ምሣሌዎች ናቸው፡፡ ልክ ከጎናችን እንደሆነ ያህል እየመከረ እያስተማረ እያበረታታ ይጽፍላቸው ነበር፡፡ አብሮነት ስንል ሁለትና ከዚያ በላይ የሆነ ባልንጀሮች የሚገናኙት ለተለየ ጥቅም ለመዝናናት ለመጫወት ወዘተ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ጊዜ በሐዘንና በደስታ፣ በማጣትና በማግኘት ሁሉ አይለያዩም ለማለት ጭምር ነው፡፡
ባልንጀራዬ (ወዳጄ) አጣ፣ ነጣ፣ ከሣ፣ ጠቆረ ብሎ ለመለየት የሚያስ ካለ ተሣሥቷል በተለይም በአሁኑ ጊዜ በዘመናችን በሽታዎች በበዙበት ዘመን ወላጅ ልጁን፣ ልጅ ወላጁን በሚሸሽበት ክፉ ዘመን ከመልካም ጓደኛ ብዙ ይጠበቃል በማጽናናት፣ በማስተማር፣ አይዞህ በማት፣ በማስታመም ባልንጀርነትን ማሣየት ይገባል
7.   ተግባራዊነት
የመልካም ጓደኝነት ባሕርያት ብለን ከላይ የተወያየንባቸው ሁሉ በዚህ ማጠቃለል ይቻላል፡፡ ፍቅርም ታማኝነትም መረዳዳትም ቤተሰባዊነትም ሆነ ይቅር ባይነት የሚታዩ የሚጨበጡ የሚዳሰሱ በመሆናቸው ጥሩ ባልንጀርነት በተግባር የሚገለጽ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሲለያዩ የሚረሣሡ በአጋጣሚ ካልሆነ በምክንያት የማይገናኙ የልባቸውን የማይተዋወቁ የዓላማ አንድነት የባሕርይ ተመሳሳይነት የሌላቸው ነገር ግን ጓደኛሞች ነን የሚሉ ካሉ ተሳስተዋል፣ ባልንጀርነታቸው ከዕለታዊ ወይም ከወቅታዊ ግንኙነት የተሻለ አይደለምና፡፡ በመንፈሳዊ ጎዳና ለምንጓዘው ለእኛ ደግሞ ከዚህ የበለጠ ትልቅ ነገር አለው፣ እስከመስዋዕትነት የሚያደርስ ገንዘብንና ቁሳቁስን ብቻ ሳይሆን ነፍስን እስከመስጠት ሊያደርስ ይችላል፡፡
እንግዲህ ጥሩ ጓደኛ እንደምንፈልግ ሁሉ እኛም ለሌላው ጥሩ ጓደኛ ለመሆን መዘጋጀት ይኖርብናል ጠቢቡ ሰለሞን ‹‹ብዙ ሰዎች መልካምነታቸውን ያወራሉ መልካም የሆነውን ግን ማን ያገኘዋል›› ይለናልና፣ ጌታችንም በመዋዕለ ስብከቱ ‹‹ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ሁሉ እናንተም አድርጉላቸው›› ይለናል፡፡ ለመሆኑ ለእውነተኛ ጓደኝነት የሚያበቁ መመዘኛዎች ምንድን ናቸው? የተለያዩ ሰዎች ለባልንጀርነት የተለያየ መስፈርት ቢኖራቸውም ቅሉ ክርስቲያኖች ግን ግልፅና የተወሰኑ ነጥቦት ሊኖረን ይገባል፡፡
1.   የዓላማ አንድነት
በተቃራኒ የሕይወት ጎዳናዎች የሚጓዙ ሰዎች በጊዜያዊ ጥቅም ታስረውና በውለታ ተይዘው ካልሆነ በቀር ዘላቂነት ያለው መልካም ጓደኝነትን ለመመስረት አይችሉም፡፡ እንመሰርታለን ቢሉም እንኳ አንዱ የሌላውን ዓላማ አስለውጦ በራሱ ጎዳና ላይ ይወስደዋል እንጂ ልዩነታቸውን እንደያዙ ለመዝለቅ ያዳግታቸዋል፡፡
የመንፈሳዊ ሰዎች (የክርስቲያኖች) ዓላማ ደግሞ አንድና አንድ ነው በክርስቲያናዊ ሕይወት ፀንቶ የመንግስተ ሰማያት ወራሽ መሆን ነው፡፡ እስራኤል በባቢሎን ምርኮ በነበሩበት ጊዜ ናቡከደነፆር ለሠራው ጣዖት አንሰግድም በማለት ወደ እሳት የተጣሉትን ሦስቱን ደቂቅ በአንድ ቃል ‹‹የምናመልከው አምላካችን ከእቶን እሣቱ ያድነን ዘንድ ይችላል›› በማለት የተናገሩት ዓላማቨው አንድና አንድ በመሆኑ ነበር ክርስቲያን የትም ይሁን የት፣ በምንም ዓይነት ነገር ውስጥ ይሁን፣ ባለጸጋም ይሁን ደሃ ሁል ጊዜ ዓላማው እግዚአብሔር ነው፡፡ ‹‹ሙሴም ታላቁ ነቢይ መሠዊያን ሠርቶ ከጨረሰ በኋላ›› ‹‹ያህዌ ንሲ›› አለው እግዚአብሔር ዓላማዬ ነው ማለት ነው፡፡
በአንፃሩ ደግሞ መንፈሳዊ ጉዞ ጀምሮ የነበረው ዴማስ ዓላማው በመቀየሩ ከመምህሩ ከባልንጀራው ከአስተማሪው ከቅዱስ ጳውሎስና ከሌሎቹም ክርስቲያኖች ለመለየት ተገዷል፡፡ (2ጢሞ 4-9) ዓላማው ምድራዊ የሆነ ሰው ለዓለማዊ ነገር ያስባልና እንብላ እንጠጣ ደረታችን ይቅላ፣ ሆዳችን ይሙላ፣ ኃጢዓትም ቢሆን እኛን ከተስማማን ደስታ ከሰጠን እናደርገዋለን ነው የሚለው፡፡
መንፈሳዊ ዓላማ ያለው ሰው ደግሞ አንጹም፣ እንፀልይ የተቸገሩትን እንርዳ፣ የታመሙትን እንጠይቅ፣ ያዘኑትን እናጽናና ተስፋ የቆረጡትን ተስፋቸውን እንቀጥል፣ የወደቁትን እናንሣ፣ የተንገዳገዱትን ደግፈን እናቁም ነው የሚለው፡፡
2.   የባሕሪይ ተመሳሳይነት
ባሕሪይ የአንድ ሰው ውስጣዊ ነፀብራቅ የሚታይበት መስታወት ነው ስሜትን ፣ ምኞትን ፣ ዝንባሌን ጠባይን ያጠቃልላል፡፡ ሰው የሚለው ቃል ራሱ የጠባይ ስም ነው፡፡ ‹‹ስብእሰ በእንተ ፍጥረት ጠባይዒሁ›› ‹ሰው ስለ ባሕሪው መገኘት ሰው ይባላል እንዳለ ገበሬ መንክራት ጎርጎርዮስ በሃይማኖት አበው ባሕርው የማይታወቅን ሰው ጓደኛ ማድረግ ቀርቶ ቀርቦ ለማነጋገርም ሊከብድ ይችላል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙ ሰዎችም ብዙ ለመነጋገር የሚፈሩትም ለዚህ ነው ‹‹የምናገረው ነገር ያስከፋው ወይስ ያስደስተው ይሆን?›› ያሰኛልና፡፡ በዓለም ላይ መቶ በመቶ ተመሳሳይ የሆነ ባሕሪይ ላቸው ሰዎች ሊገኙ አይችሉም ነገር ግን በተወሰነ ደረጃ የሚቀራረቡ ሞልተዋል፡፡
የአንድ ሰው ባሕሪይ ዝምተኛነት ቢሆን በአንድ ሊወደድ በሌላው ሊጠላ ይችላል፡፡ ይህን ባሕሪውን የወደደው ጓደኛ ሲያደርገው ያልወደደው ላያደርግ ይችላል፡፡
በአጠቃላይ ወጣትነት የእሳትነት ባሕሪይ የሚንፀባረቅበዘት ጊዜ ነው፡፡ እሳት ያገኘውን ነገር ሁሉ ላጥፋ እንደሚል ወጣትነትም በኃይል በጉልበት በፍጥነት ሁሉን ላድርግ የሚያሰኝ በመሆኑ ባልንጀራ ምርጫ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያደርጋል፡፡ በሌላው በወጣትነት የባሕሪይ ተለዋዋጭነትም በሰፊው ይታያል ዛሬ የተናገሩትን ነገ አለመድገም አንዴ መደሰት አንዴ መከፋት የሚያዩትና የሚሰሙት ሁሉ መልካምና የሚያጓጓ መስሎ መታየት ሁሉ የወጣትነቱ ባሕሪይ በመሆኑ በጓደኝነት ላይ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡

3.   በእምነትና በምግባር መመሳሰል
ዛሬ ዛሬ እምነት (ኃይማኖት) እንደ ሁለተኛ መሥፈርት ተቆጥሮ በባልንጀርነት ሕይወት ውስጥ ትኩረት አይሰጠውም ሌላው ቀርቶ ትዳርን (ጋብቻን) ያህል ቁም ነገር እንኳ ሲመሠረት አንተም በኃይማኖትህ አንቺም በኃይማኖትሽ በማለት ብዙዎች በሕይወታቸው ይቀልዳሉ፡፡ ነገር ግን በሃይማኖት መለያየት እንኳንስ ለትዳር ለልባዊ ጓደኝነት እንደማያበቃ ማወቅ ብቻ ሳይሆን አምኖ መቀበል ያስፈልጋል ከማያምኑ ወይም ከመናፍቃን ጋራ አብሮ መሥራትና በማኅበራዊ ሕይወት መረዳዳት የልብ ጓደኝነት አለመሆኑን ልብ ልንል ይገባል፡፡
በኃይማኖት ተመሳስሎ በምግባር ተለያይቶ ባልንጀርነት መመሥረት ተገቢ አይደለም፡፡ ማኅቶተ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹አትሳቱ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል›› (1ቆሮ 15፡33) እንዳለ መልካም ምግባር የሌላቸው ሰዎች አርአያነታቸው በዘክፉ አንጂ በጥሩ ሊሆን አይችልም፡፡ ስማቸው ኦርቶዶክስ ግብራቸው ግን የዓለማውያን የሆኑ በርካታዎች ናቸው፡፡ ኃይማኖት ደግሞ በሥራ እንጂ በስም አይገለጽም እንዲህ ዓይነቶቹ ሆዳቸው አምላካቸው ክብራቸው በነውራቸው ፣ ሃሣባቸው ምድራዊ ፣ መጨረሻቸው ጥፋት ነውና፣ ቢቻል መምከርና መዘከር ካልሆነ ግን መለየት ያስፈልጋል፡፡
በኃይማኖትም በምግባርም ፍፁም የተለያዩ ሰዎች ባልንጀራ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ሃይማኖት ፍኖተ (መንገድ) እግዚአብሔር ነው በመሆኑም ብዙ የእምነት ድርጅቶች ቢኖሩም እውነተኛዋ መንገድ ግን አንዲት ናት (ኤፌ 4፡4) ከመናፍቃን ጋር ያለን ግንኙነት ልክ ያለውና በጥንቃቄ ሊሆን ይገባል፡፡ ‹‹ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ ጽድቅ አመጽ ጋር ምን ተካፋይነት አለው ይለናል›› ብርሃን ከጨለማ ጋር ፣ ክርስቶስ ከሠይጣን ፣ የሚያምነስ ከማያምን ምን ክፍል አለው? በመሆኑም ምግባር ከኃይማኖት ከሌለው ባልንጀርነት አይገባም ለመጀመር ያነሳሳን ለመፈፀም ያበረታን መድሀኒተ ዓለም ክርስቶስ ይመስገን፡፡
ወስብሀት ለእግዚአብሔር

No comments:

Post a Comment