Tuesday, October 29, 2013

‹‹እነሆ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና ተጭኖ ወደ ግብፅ ይመጣል›› (ኢሳ 19-1)

ክፍል ሦስት     

ሰባዓ ሰገል ከሩቅ ምስራቅ ተነስተው ‹‹የተወለደው የአይሁድ ንጉስ ወዴት ነው?›› እያሉ በመጡ ጊዜ ሄሮድስ ደነገጠ ‹‹ንጉስማ ከሆነ ንጉሥ ሳይገድል ይነግሳልን?›› ብሎ የካህናትንም አለቆች ሰበሰበ ክርስቶስ ወዴት እንዲወለድ ጠየቃቸው በቤተልሔም መሆኑን ነገሩት ከዚያ በኋላ ሰብአ ሰገልን ጠርቶ ከአገኙት ተመልሰው እንዲነግሩትና ሄዶ እንደሚሰግድለት መክሮ ላካቸው፡፡ እነርሱ ግን ወደ ሄሮድስ እንዳይመጡ በሕልም ተረድተው በሌላ መንገድ ወደ አገራቸው ሄዱ፡፡ ለዮሴፍም መልአክ በሕልም ታይቶ ሕፃኑንና እናቱን ይዞ ወደ ግብፅ እንዲሸሽ አደረገው (ማቴ 2፡15) እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ጌታችንን አዝላ ፀሐይና ብርድ እየተፈራረቀባት የአሸዋው ግለት የመንገዱ ርዝመት ሳይበግራት ከእየሩሳሌም ተነስታ እስከ ግብፅና ኢትዮጵያ ድረስ ለሦስት ዓመታት ያህል በመንከራተትና ልጇን ከሚፈታተኑ ጠላቶች ሁሉ አቅፋ ሸፍና በመከለሏ ደመና ተብላለች፡፡ ከዚህም የተነሣ አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን ወደ ግብፅና ኢትዮጵያ ተሰደደ ለሚለው ጥያቄ ይህ የኢሳይያስ የትንቢት ቃል ‹‹እነሆ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና ተጭኖ ወደ ግብፅ ይመጣል›› (ኢሳ 19-1) የሚለው አንዱና የመጀመሪያው ምክንያት ነው፡፡




·         ምሳሌው ይደርስ ዘንድ

ግብፅ ታቀርበዋለችና ግብፃውያንና ኢትዮጵያውያን ይሹታልና ለፍቅሩም ይሳሳሉና፡፡ አምልኮ ጣዖትና ክህደትም በግብፃውያን ፀንቶ ነበርና ወደ ፀናበት መሄዱም ልማድ ነውና በነቢዩ በኤርሚያስ ላይ አድሮ ጣዖታትን ያጠፋ ዘንድ ወደ ግብፅ እንደወረደ ሁሉ እናንተም የአዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች በፍቅር ከፈለጋችሁኝ በእምነት ከጠራችሁኝ በተሰበረ ልብ ከቀረባችሁኝ በሕይወታችሁ ጣዖት ሆኖ ያስቸገራችሁን ነገር ሁሉ አጠፋለሁ ሲል ነው፡፡ ‹‹እሹ ታገኛላችሁ ለምኑ ይሰጣችኋል›› (ማቴ 7፡7) እንዲል ወንጌሉ እንዲሁም እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፡፡ ‹‹የእግዚአብሔር መስዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነውና የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም›› መዝ 33፡18 ፣ 50፡17



·         ኪዳነ ልከ ጼዴቅ ይፈፀም ዘንድ

ክህነቱ ዘላለማዊ የተባለው የሳሌም ንጉሥ መልከ ጼዴቅ በሴዊ ሸለቆ ሆኖ ግብፃውያንን እንዲምርለት አጥብቆ ቢለምነው ፣ ቢማፀነው የነገሩትን የማይረሣ የለመኑትን የማይነሣ እግዚአብሔር ‹‹ኪዳንዬ ተካየድኩ ምስለ ኁሩያንየ›› ከመረጥኳቸው ጋራ ቃል ኪዳኔን አደረግሁ ተብሎ እንደተፃፈ ልጄን በስጋ ሰድጄ እምርልሃለሁ ብሎ ቃል ገብቶለት ነበርና፡፡ የዘመኑ ፍፃሜ ሲደርስ ከድንግል ማርያም ተወለደ ቃል ኪዳኑን ያፀና ዘንድ ወደ ግብፅ ተሠደደ፡፡

·         አንድም በመጨረሻው ዘመን ሃሣውያን ሲነሱ ምድርን ሁሉ በክህደታቸውና በሐሰት ትምህርታቸው ሲያጥለቀልቁ የጥፋትን ርኩሰት በተቀደሰው ሥፍራ ሲቆም ክህደት ሲይስፋፋ ኃይማኖት ከምድር አይጠፋም ወልድ ዋህድ እያሉ እስከ ምጽዓት ድረስ እግዚአብሔርን እያመለኩ ይገኛሉና ትውልዱን ይባርክ ዘንድ ተሰደደ፡፡

  •  የመጀመሪያው ሠው አዳም እግዚአብሔር በአምሳሉና በአርያው ግሩምና ድንቅ አድርጎ ፈጥሮ በገነት ካስቀመጠው በኋላ ዕፀ በለሰን እንዳይበላ ከበላ ግን የሞት ሞትን እንደሚሞት አስጠንቅቆ ትዕዛዝን ቢሰጠው ፣ አዳም ግን ቅጠልን ቀጥፎ በመብላት ትዕዛዝን ሻረ እምነት አጎደለ ህግንም ተላለፈ፡፡ እግዚአብሔርም በአዳም ተቆጥቶ ከገነት አሰድዶ አስወጣው አባረረው ነገር ግን ከዘመናት በኋላ (5500) ከልጅ ልጁ ተወልዶ ፍጹም ካሣን ክሶ ስደትን ተሰዶ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍሶ እንደሚያድነው ቃል ገብቶለት ነበርና የአዳምን ስደት ይሰደድ ዘንድ ወደ ግብፅና ኢትዮጵያ በፈጣን ደመና መጣ፡፡

  •  ለ5500 ዘመን በሰዎች ልቡና ነግሦ ስጋን በመቃብር ነፍስን በሲኦል እተቆራኘ ገዥ ሆኖ የኖረውን ዲያብሎስንና ሠራዊቱን ከሰዎች ልቡና አስወጥቶ ያሰድድ ዘንድ የነገስታት ንጉሥ የገዥዎች ገዥ ኢየሱስ ክርስቶስ የደካሞች ብርታት ሆኖ ሳለ እንደ መፃተኛ ተሰደደ፡፡

  •  ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ንዑዳን ናቸውና (ማቴ 5፡5) ነቢያት ስለአምላካቸው ስለእውነት ተሰደዋል፡፡ ከዚያም በኋላ ሐዋርያትና ተከታዮቻቸው እስከዓለም ፍፃሜም የሚነሱት እውነተኞች ክርስቲያኖች ሁሉ ስለአምላካችን ስለመድኃኒታችን ስለኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ‹‹ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ በዋሻና በምድር ጉርጓድ ተቅበዘበዙ›› (ዕብ 11፡37) ይላልና፡፡ የነቢያቱን ፣ የሐዋርያቱንና የቅዱሳኑን ሁሉ ስደት በእርሱ ስደት ይባረክ ዘንድ በፈጣን ደመና ተጭኖ ተሰደደ፡፡
  • በክርስትና ሕይወታቸው አርአያና ምሳሌ የሚሆኑ ቃልኪዳናቸውና ተጋድሎቸው ለብዙሀን የሚተርፍ ታላላቅ ቅዱሳን የሚወጡባቸው የግብፅ ገዳማት አስቄጥስና ሲዓት የኢትዮጵያው ዋልድባ ፣ብርብር ማርያምና ጣና ቂርቆስን ይባርክና ያፀና ዘንድ ተሰደደ

  •  በዚያውስ ላይ መሰደዱ ስለምን ነው ቢሉ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ የዓለምን ኃጢዓት የሚያስወግድበት ዕለተ አርብ ቀኑ ገና አልደረሰም ነበርና ፣ ጸጋና እውነትን ተመልቶ በእኛ አድሯልና ሄሮድስ አስራ አራት ዕልፍ ህፃናት ሲያስፈጅ እርሱ ግን በፈጣን ደመና በእመቤታችን ጀርባ ታዝሎ ወደ ግብፅና ኢትዮጵያ ሸሸ፡፡

ዛሬ በዓለማችን የተለያዩ ቦታዎች ድርቅ ርሃብና ቸነፈር እየተፈራረቁ የሰውን ልጅ ሕይወት ይፈታተናሉ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ በእምነት ድርቅ በሥነምግባር ቸነፈር ተመቶ የሚታየው ህዝብ ያሳዝናል፡፡ ምክንያቱም አፍአዊ ድርቅን ረሃብ ሥጋን ቢገድሉ እንጂ በነፍስ ላይ ሥልጣን የላቸውም፣ የእምነት ድርቅ ግን ነፍስን ወደ ሲኦል ያግዛልና፡፡

ምድር በእጽዋት በአዝርዕት ተሸፍና ፍሬ ልምላሜ ልታሳይ የምትችለው ዝናም ስታገኝ ነው፡፡ ‹‹ምድር ነህና ወደ ምድር ትመለሳለህ›› እንዲል ምድር የተባለ ሰውነታችንም የመንፈሳዊነት ፍሬ የምግባር ልምላሜ ሊያሳይ የሚችለው በቃለ እግዚአብሔር ዝናምነት ሲረሰርስ ነው፡፡

በመሆኑም ደመናውን ሳያዩ ዝናሙን ማግኘት እንደማይቻል ሁሉ እመቤታችንን ሳያውቁ ጌታን አምናለሁ ማለትም ማየትም አይሞከርም፡፡ ብዙዎች ይህንን ባለመረዳት የጌታን አምላክነት እንደሚያምኑ የእመቤታችንን አማላጅነት ግን እንደማይቀበሉ ይናገራሉ ይህም ዝናሙን እየፈለጉ ደመናውን እንደመጥላት ይቆጠራል፡፡ ነገር ግን አንዱ ከአንዱ ተለያይተው እንደማይኖሩ ጌታችንም ፍፁም ሰው ተብሎ ከአብርሃምና ከዳዊት ዘር ሀረግ ሊቆጠር የቻለው የእመቤታችንን ስጋ በመዋሀዱ ነው፡፡ ስለዚህ ጌታችንን ሲያነሱ እመቤታችንን ፣ እመቤታችንን ሲያነሱ ደግሞ  ጌታችንን መጥራት ይገባል፡፡ እርሷ እናትም ድንግልም መሆን የቻለች የድህነታችን ምንጭ የነፍሳችን ቤዛ ከፈጣሪ በታች ከፍጡራን በላይ የተባለች ናትና፡፡ ደመና ዝናምን ቋጥሮ ለዘር ለመከር የሚሆን ውሃ ይሰጣል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ወንዙን ሐይቁን ያለልክ ሞልቶ ጥፋትን ያደርሳል ደመና ከተባለች እመቤት የተወለደ ጌታችንም ሕገ ወንጌልን ጠብቀው በስሙ አምነው ንስሐ ገብተው ሥጋ ወደሙን ተቀብለው የሚኖሩትን ሲያድን፣ በኃጢያት ጎዳና የሚጓዙትን ደግሞ ተበቅሎ ያጣፋቸዋል፡፡

አንድም ደመና አትክልት እጽዋትን በፀሐይ ቃጠሎ እንዳይደርቁ ከለላ ይሆናቸዋል፡፡ እስራኤል ዘስጋ በሲና ምድረበዳ ሲጓዙ በሙቀቱ እንዳይዝሉ ቀን ቀን በደመና ይጋርዳቸው እንደነበር እመቤታችን ‹ሰዓሊለነ› እያሉ ጠዋት ማታ የሚማፀኗትን በእናትነቷ ተማምነው ውዳሴዋን ቅዳሴዋን የሚያደርሱትን ከተለያየ ችግርና መከራ ትጠብቃቸዋለች፡፡

አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም ‹‹ምሥጋናን የተመላሽ ድንግል ሆይ በማንና በምንስ ምሳሌ እንመስልሻለን›› በማለት እንደተናገረው ስለእመቤታችን ተናግሮ አመስጥሮ መፈፀም አይቻልም፡፡ በዚህ ጽሑፍም በደመና የመመሰሏን ነገር አጠቃሎ መጨረስ ስለማይቻል ‹‹ሰላም ለኪ ማርያም ርግብ ሰማያዊት ሰላም ለኪ ወንሰር መንፈሳዊት ሰላም ለኪ ስምረተ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ሰላምለኪ እምትካት ዘኀረየኪ ሰላም ለኪ›› ‹‹አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ከጥንት የመረጠሽና የወደደሽ መንፈሳዊት ንስርና ሰማያዊት ርግብ ድንግል ማርያም ሆይ ሰላምታ ይገባሻል›› በማለት አባጊዮርጊስ ዘጋስጫ በሰባቱ ጊዜያት ጸሎቱ እንዳመሰገኗት እኛም ፍቅሯን በልባችን ጣዕሟን በአንደበታችን አኑራ በሕይወታችን ነግሣ ትኑር በማለት እናበቃለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

No comments:

Post a Comment