Monday, October 28, 2013

‹‹ናሁ እግዚአብሔር ይነብር ዲበ ደመና ቀሊል ወይመጽዕ ውስተ ግብፅ›› ኢሳ 19÷1

ክፍል ሁለት

 

                                                                   
ባለራእዩ ቅዱስ ዮሐንስ ‹‹ሴቱትም ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን በዚያ እንዲመግቡአት በእግዚአብሔር ተዘጋጅቶላት ወደ ነበረው ሥፍራ ወደ በረሃ ሸሸች›› (ራዕ 12፡6) እንዲል አዛኝት እናት ድንግል ማርያም ልጇን ወዳጇን ይዛ ስደት ተነሣች፣ የስደተኞችን መፅናኛ (ምስካዬ ኅዙናን) ይዛ ተሠደደች ዓላማትን የፈጠረውን ጌታ ታቅፋ አሽዋ ለአሽዋ ተንከራተተች፣ ፍጥረታትን በየሥፍራቸው የወሰነውን እርሱ ግን ቦታና ጊዜ የማይወስነውን የእግዚአብሔር ልጅ እግዚአብሔር የተባለው ልጇን ለተወሠኑ ጊዜያት በተወሠነ ስፍራ ታቆየው ዘንድ አዝላው ተሰደደች ለሰው ልጆች ክፉ ቀንን የሚያሳልፈውን አምላክ አዝላ ክፉ ቀን እስከሚያልፍ ተሰደደች ‹‹ዘንዶውም ወደ ምድር እንደተጣለ ባየ ጊዜ ወንድ ልጅ የወለደችውን ሴት አሰደዷት ከእባቡም ፊት ርቃ አንድ ዘመን ዘመናትም የዘመን እኩሌታ ወደ ምትመገብበት ወደ ሥፍራዋ ወደ በረሃ እንድትበር ለሴቲቱ ሁለት የታላቅ ንስር ክንፎች ተሰጣት›› (ራዕ 12፡13-15) ተብሎ እንደተፃፈ ፈጣን ደመና ናትና በተሰጣት ክንፍ እየበረረች ቀድሞ በነቢዩ በኢሳይያስ እንደተፃፈ ‹‹ሰማይ ዙፋኔ ምድር የእግሬ መረገጫ ነው›› (ኢሳ 66፡1) ያለ አምላክን ሥጋና ደምን ተዋህዶ ሕፃን ሆኖ ከማህፀኗ በመወለዱ አንድ ጊዜ በእቅፏ አንድ ጊዜ በጀርባዋ እያዘለች የግብፅን በረሃ አቋርጣ ወደ ኢትዮጵያና ወደ ግብፅ ተሰደደች ኢትዮጵያም ተባረከች ኢትዮጵያንም ተደሰቱ እግዚአብሄርንም አመስግኑ ይህንንም በትንቢት መነጽር ተመልክቶ የእግዚአብሔር ነቢይ እንባቆም ‹‹የኢትዮጵያ ድንኳኖች ሲጨነቁ አየሁ የምድያም ሀገር መጋረጃዎችም ተንቀጠቀጡ›› (ዕንባ 3፡7) በማለት ሕፃኑንና እናቱን ለመቀበል በትህትናና በፍቅር መቅደሱን ሞልተው የነበሩትን ኢትዮጵያውያንን ጠቅሶ መዝግቦልናል፡፡











ደመና የእግዚአብሔር የክብሩ መገለጫ ነው በዘመነ ኦሪት እግዚአብሔር በመገናኛው ድንኳን በደመና አምድ ይገለፅ ነበር ‹‹ሙሴም ወደ መገናኛው ድንኳን በገባ ጊዜ የደመናው አምድ ይወርድ ነበር በድንኳኑም ደጃፍ ይቆም ነበር እግዚአብሄርም ሙሴን ይናገረው ነበር›› (ዘጻ 33፡8-9) ንጉሥ ሰሎሞንም የመጀመሪያውንና ትልቁን ቤተመቅደስ ሰርቶ በጨረሰ ጊዜ ደመናው የእግዚአብሔርን ቤት ሞላው ‹‹ደመናው እግዚአብሔርን ቤት ሞላው የእግዚአብሔር ክብር ቤቱን ሞልቶት ነበርና ከደመናው የተነሣ ካህናት መቆም አልተቻላቸውም›› (1ኛ ነገ 8፡10)
በአዲስ ኪዳንም በደብረ ታቦር ተራራ ላይ አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሦስቱ የምሥጢር ሐዋርያት ብርሃነ መለኮቱን በገለፀላቸው ጊዜ ብሩህ ደመና ጋርዷቸው ነበር (ማቴ17፡1-5) ሞትን ድል አድርጎ ከተነሣ በኋላ በአርባኛው ቀን ከደብረ ዘይት ተራራ ሲያርግም ወደ ላይ ከፍ ከፍ ሲል ሲመለከቱት ከነበሩት ሐዋርያት ደመና ከዓይናችን ሰውራ ተቀበለችው (ሐዋ 1፡9)
ዳግመኛ ዓለምን ለማሳለፍ በሚመጣበት ጊዜ ከደመና ጋር መሆኑን ሲናገር ባለራዕዩ ቅዱስ ዮሐንስ ‹‹እነሆ ከደመና ጋር ይመጣል ዓይንም ሁሉ የወጉትም ያዩታል›› (ራዕ 1፡7) በማለት ጽፎአል፡፡ በሌላው ደመና የተባሉት እግዚአብሔር በተለያዩ ዘመናት ክብሩን የሚገልጽባቸው ቅዱሳን ናቸው፡፡ ‹‹እንግዲህ እንዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎ የሚከበንንም ኃጢዓት አስወግደን እምነታችን ራስና ፈፃሚ የሆነውን ኢየሱስን ተመልክተን በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግስት እንሩጥ›› (ዕብ 12፡2-4) ቅዱሳን ለምን በደመና ተመሰሉ ስንል ደመና ጥላ ነው ደመና ካለ የፀሐይ ሐሩር አያቃጥልም፣ እንደዚሁ ደመና የተባሉ ቅዱሳን ካሉ ቁጣው መቅሠፍቱ በመጣ ጊዜ መዓቱን በምህረት ቁጣውን በትዕግስት እንዲያሳልፍ ከእግዚአብሔር ዘንድ ምህረት ምልጃ ያቀርባሉ፡፡ በመሆኑም ደመና ካለ ዝናም ቅዱሳን ካለ ዝናመ ምህረት ይኖራል፡፡
እግዚአብሔር ክብሩን ከገለፀባቸው ቅዱሳን ሁሉ በላቀ ደረጃ ግን መትሐተ ፈጣሪ መልዕልተ ፍጡራን የሆነችው ድንግል ማርያም በተዋህዶ በረቀቀ መልኩ ክብሩን አብዝቶ የገለፀበት ደመና እርሷ ስለመሆኗ ሙሴም በህግ መፀሐፍ ነቢያትም በትንቢታቸው ፅፈውልናል ለዘጠኝ ወራት ማህፀኗን ዙፋን አድርጎ ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ነስቶ ጡትዋን ጠብቶ ክብሩን ገልጦበታልና፡፡ የእመቤታችንን በደመና መመሰል ከመጽሀፍ ቅዱስ ምሳሌዎችን ጠቅሷል እንመለከታለን፡፡
1. ደመና ኖህ
የጥፋት ውሃ ከደረቀ በኋላ ኖህና ልጆቹ ከመርከቧ ወጡ መሰዊያውንም ሰርቶ ንጹህ ከሆኑት እንሰሳት መርጦ መስዋዕት አቀረበ እግዚአብሔርም ‹‹ብዙኃ ወተባዝኁ ዳግመ ወሞልዋ ለምድር›› ዳግመኛም ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሉአት በማለት ባረካቸው ኖህ ግን ‹‹ጌታን ከእኔ ልጆች ስህተት ኃጢአት አይቀር አንተ መፍረድህን አትተው ፈርደህ ልታጠፋቸው ነውን?›› በማለት ተቃወመ እግዚአብሔርም ምድርን ዳግመኛ በውሃ እንደማያጠፋት ‹‹እሠይም ቀስትየ በውስተ ደመናት ከመ ኢያማስና ለምድር ዳግመ በማይ አይኃ›› ምድርን በውሃ እንዳላጠፋት ቀስቴን በደመና አደርጋለሁ በማለት ቃል ኪዳን አደረገ ‹‹ኪዳነ ኖህ›› (ዘፍ 9፡12-15) ዛሬ በደመና ላይ ተሰሎ የምናየው ቀስት ባለ አራት ኅብር ነው ከአራቱ ባሕርያት ሥጋ የተፈጠረ ሰውን አላጠፋውም ሲል አንድም ደመናው የእመቤታችን አራቱ ኅብር የጌታ ምሣሌ ነው አራቱን ባሕርያት ከእመቤታችን በመንሳት ሰው ሆኗልና እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ደግሞ የቃል ኪዳን እናታችን ናት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመልዕልተ መስቀል ላይ ሳለ ለቁርጥ ቀን ሐዋርያ ለቅዱስ ዮሐንስ ‹‹እናትህ እነኋት›› እርሷንም እንሆ ልጅሽ በማለት አስረክቦናል (ዮሐ 19፡26-27)

2. ደመና ሙሴ
ሊቀ ነቢያት ሙሴ እስራኤልን ከግብፅ ባርነት አውጥቶ በምድረ በዳ እየመራ ወደ ከነዓን በሚወስዳቸው ጊዜ በልዩ ልዩ ምክንያት እያንጎራጎሩ በማስቸገራቸው የአርባ ቀኑ ጉዞ አርባ ዓመት ፈጅቶባቸዋል፡፡ ከዚህም መካከል ዳታን ፣ አቤሮንና ቆሬ የተባሉት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች በሙሴና በአሮን ላይ በተቃዋሚነት በተነሱባቸው ጊዜ ምድር ተከፍታ ዋጠቻቸው ዘመዶቻቸውንም ይህ ሁሉ መከራ የሚመጣብን በእነዚህ ሰዎች ምክንያት አይደለምን ኑ በድንጋይ ወግረን በእሳት አቃጥለን እንግደላቸው ብለው መጡባቸው ሙሴና አሮን ሸሽተው ከደብተራ ኦሪት ገቡ ‹‹እንዲህም ሆነ ማኅበሩ በሙሴና በአሮን ላይ በተሰበሰቡ ጊዜ ወደ መገናኛው ድንኳን እዩ እነሆም ደመናው ሸፈነው እግዚአብሔርም ክብር ተገለጠ›› እግዚአብሔር በድንኳን አስገብቶ በደመና ጋርዶ ከተነሳባቸው ሰዎች አዳናቸው ያቺ ደመና የእመቤታችን ምሳሌ ናት በእርሷ ታምነው ስሟን ጠርተው ውዳሴዋን አድርሰው ጠዋት ማታ ለሚማፀኗት ከተወረወረ ጦር ከተሰነቀረ ሰይፍ ጋሻ መከታ ሆና ትሰውራለችና፡፡
3. ደመና ኤልያስ
በንጉሱ በአክአብ ዘመን የነበረው ነቢየ እግዚአብሔር ኤልያስ ለሦስት ዓመት ከመንፈቅ ሰማይን ለጉም ዝናምን ለዘር ጠልን ለመከር እንዳይሰጥ ከለከለ፡፡ ይህም የሆነው ንጉሡና ንግስቲቱ ኤልዛቤል ካህናተ እግዚአብሔርን አሰፈጅተው ለየራሳቸው ከአራት መቶ በላይ ነቢያተ ሐሰት ካህናተ ጣዖት አዘጋጅተው በአምልኮተ ባዕድ በመጽናታቸው ነበር ኤልያስ ንጉሡና ንግስቲቱን ገስጾ ሊሳካለት ባለመቻሉ ወደ እግዚአብሔር በመፀለይ ዝናሙን አቆመ፡፡ ከሦስት ዓመት በኋላ በሀገሪቱ በሰማርያ ረሃብ ፀንቶ ሳለ በእግዚአብሔር ትዕዛዝ ኤልያስ ለአክዓብ ተገለጠ ሕዝቡንም እስከመቼ ድረስ በሁለት ሃሣብ ታነክሳላችሁ? እግዚአብሔር አምላክ ቢሆን እርሱን ተከተሉ በአል ግን አምላክ ቢሆን እርሱን ተከተሉ በማለት ተናግሮ እሱና የጣዖት ካህናት ለየራሳቸው መስዋዕት ሰውተው መስዋዕቱን የተቀበለለት አምላክ እንዲሆን ተስማሙ፡፡ እግዚአብሔርም የኤልያስን መስዋዕት ተቀበለ (1ኛ ነገ 17 እና 18) ከዚህ በኋላ ኤልያስ ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ወጣ ፊቱንም በጉልበቱ መካከል አድርጎ በግንባር ተደፋ ብላቴናውንም ወጥተህ ተመልከት አለው ወጥቶ ተመልክቶም ምንም የለም አለ ሰባት ጊዜ ተመላለስ አለው ብላቴናውም ሰባተ ጊዜ ተመላለሰ በሰባተኛው ጊዜ እነሆ የሰው እጅ የምታህል ታናሽ ደመና ከባሕር ወጣች አለው እርሱም ወጥተህ አክአብን ዝናም እንዳይከለክልህ ሰረገላህን ጭነህ ውረድ በለው አለ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሰማዩ ከደመናውና ከነፋሱ የተነሣ ጨለመ ብዙም ዝናብ ሆነ የእግዚአብሔር እጅ በኤልያስ ላይ ነበረች ይላል (1ኛነገ 18፡41-45)
ደመናዋ የሰው እጅ የምታህል ትንሽ ስትሆን ከእርሷ የተገኘው ዝናም ግን ብዙ ነበረ የደረቀውን ምድር አራሰ የጠወለገውንም አለመለመ ድርቅንም አጠፋ ምድሪቱም ፍሬዋን አበቀለች ደመና የእመቤታችን ዝናም የጌታ ምድር የሰው ልጆች ምሳሌ ነው ትንሽ ንጽሕት ነጭ ደመና ምድርን ያረካ ዝናም እንደተገኘባት ሁሉ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ከሰው ወገን የተመረጠች ታናሽ ብላቴና ሳለች የባሕርይ አምላክ ዝናመ ምህረት ኢየሱስ ክርስቶስን በመውለድ ሰላምን ተርቦ ምህረትን ተጠምቶ የነበረውን የሰው ልጅ በማጥገቡና በማርካቱ በኤልያስ ደመና ተመስላለች ፡፡ የቅዳሴ ማርያም ትርጓሜና/ ቅዱስ ኤፍሬም በረቡዕ ውዳሴው ‹‹አንቲ ዘበአማን ደመና እንተ አስተራይኪ ለነ ማየ ዝናም›› የዝናም ውሃ የታየብሽ እውነተኛ ደመና አንቺ ነሽ በማለት አመስግኗታል፡፡  
4.  ደመና ኢሳይያስ
ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ሰባት መቶ ዓመታት በፊት የነበረውና ደረቅ ሐዲስ እየተባለ የሚጠራው ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ ‹‹ወይወርድ እግዚእነ ውስተ ምድረ ግብፅ ተጽኢኖ ዲበ ደመና ቀሊል›› እግዚአብሔር በፈጣን ደመና እየበረረ ወደ ግብፅ ይመጣል በማለት ተናግሮ ነበር (ኢሳ 19፡1) ፈጣን ደመና ያላት እመቤታችንን ሲሆን ትንቢቱም ጌታ ወደ ምድረ ግብፅ በተሰደደበት ጊዜ ተፈፃሚነትን አግኝቷል፡፡

No comments:

Post a Comment