Saturday, October 26, 2013

‹‹ናሁ እግዚአብሔር ይነብር ዲበ ደመና ቀሊል ወይመጽዕ ውስተ ግብፅ›› ኢሳ 19÷1

 
 

 
ሰማይና ምድር በጉምና በጭጋግ ተሸፍነው ከላይ ዝናም እየመታን ከታች ጎርፍ እየጠለፈን በብርድ እየተንቀጠቀጥን ወርኃ ክረምት አልፎ ፀሐይ ከምስራቅ የብርሀን ጨረሯን ፈንጥቃ ጋራ ሸንተረሩ በአደይ አበባ ደምቆ አፍላጋት ከየቦታው እየተፍለቀለቁ የአዲስ ዘመን ሀሴት በልባችን በፈነደቀበት የመፀው ወራት ልዑለ ቃል ኢሳይያስ ‹‹እንሆ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና እየበረረ ወደ ግብፅ ይመጣል›› ይለናል፡፡ በመሠረቱ ነቢዩ ስለክረምቱ ደመና ሳይሆን ይህንን ኃይለ ቃል የተናገረው ሕዝብ አዳምን የሕይወት ውሃ ያጠጣ እውነተኛ ዝናብ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ስላስገኘች አማናዊት ደመና ቅድስት ድንግል ማርያም ስደት በሚስጢር ለመናገር ፈልጎ ነው፡፡




ለጊዜው ግን ነብየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ ይህንን ቃል የተናገረው ለግብፃውያን ሲሆን የጥጃና የላም ምስልን ሠርተው  ፈጣሪያቸውን ረስተው ጣዖትን እያመለኩ እግዚአብሔርን አስቆጡ ንጉስ በመንግስቱ ጎልማሳ በሚስቱ እንዲቀና ከኔ በቀር ሌላ አማልክትን አታምልኩ ያለ እግዚአብሔርም በአምላክነቱ ቀናተኛ ነውና (ዘፅ 20÷3-6) በነብዩ በኤርሚያስ ላይ አድሮ ይገስፃቸው ዘንድ ይመጣል፡፡ ኤርሚያስ የአህዛብ ነብይ ከመሆኑም በላይ ብርቱና ሀያል የእግዚአብሔር መንፈስ በኃይል ያለበት በመሆኑ ፈጣን ደመና ተብሏል፡፡ የእግዚአብሔር ገጸ መአት በኤርሚያስ ላይ አድሮ ከመገለፁ የተነሳ የግብፃውያን የእጃቸው ሥራ ጣዎት ይጠፋል፣ እንዲሁም በጣዖት አምልኮ የግብፃውያን ልቦና ይርዳል ይንቀጠቀጣል፡፡ አንድም እግዚአብሔር በኤርሚያስ ላይ አድሮ በመገለጡ ከኤርሚያስ ተግሳፀ ትምህርት የተነሳ ለእግዚአብሔር አምልኮ ቀናተኛ የሆኑት የግብፃውያን ልቦናቸው በፍቅር ይቃጠላል ለማለት ነው፡፡
ፍፃሜው ግን በእግዚአብሔር በፈጣን ደመና ወደ ግብፅ እየበረረ ይመጣል የተባለው ለአምላካችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስና እርሱንም በድንግልና ወልዳ ስለሰጠችን ስለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የተነገረ ትንቢት ነው፡፡ በኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቶያናችን እመቤታችን በደመና ትመሰላለችና፡፡ ይህም ከልቦናችን አንቅቶን ከአእምሮዎችን ፈጥረን ያወጣነው ሳይሆን ነቢያት በመንፈስ ቅዱስ አስተማሪነት የተናገሩት በቅዱሳት መፃህፍት ያሰፈሩትና የተረጎሙት በመሆኑ ነው፡፡
በባህሪው ሕልፈት በመንግስቱ ሽረት የሌለበት አልፋና ኦሜጋ እግዚአብሔር አምላካችን በክብሩ ላይ የሚጨምረው ወይም የሚቀንሰው ነገር ባይኖርም ስሙን ጠርተው ፈጣሪነቱን አምነው የመንግስቱ ወራሽ እንዲሆኑ በመፈለጉ የሰውን ልጆች ፈጠረ፡፡ ነገር ግን የሰጠውን ትቶ ያልሰጠውን ፣ ያለውን ንቆ የሌለውን የሚመኝ የሰው ልጅ አምላክነትን በመፈለጉና ፈጣሪነትን በመሻቱ ከክብር ተዋርዶ ከገነት ተሰደደ (ዘፍ 3÷22-24) ያም ሆኖ በከሀሊነቱ ላይ ቸርነት የባህሪው የሆነ አምላካችን ለፍጥሩ ያለው ፍቅር አገብሮት ይቅርታውን ለግሶ በሞቱ ሞትን ደምስሶ ሊያድነው ወደደ፡፡ ‹‹ፍቅር ሳሀቦ ለወልድ ሀይል እመመንበሩ ወአብድሖ እስከለሞት›› እንዲል ቅዳሴ ማርያም፡፡ ሰማይና ምድር የማይችሉት በሥጋ ድንግል ማርያም ሥጋዋ ሆኖ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ ሆነ ነባቤ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ እንደመሰከረ ‹‹ቃልም ሥጋ ሆነ ፀጋንና እውትንም ተመልቶ በእኛ አደረ አንድ ልጁም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነውን ክብሩን አየን›› (ዮሐ 1÷14)
በቤተልሔም ኤፍራታ በእኩለ ሌሊት የብርሀን አምድ ተተከለ የዓለምንም ሀጢያት የሚያስወግደው የሞትን አከርካሪ የሰበረው የጨለማውን አበጋዝ ያሳፈረው መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ተወለደ ድንግልም ፈጣሪዋንና የበኩር ልጅዋን ወለደችው እረኞችና መላዕክትም በቅዱስ ገብርኤል ብስራት በአንድ ላይ ዘመሩ፣ የጥበብ ሰዎችም የተወለደው የአይሁድ ንጉስ ወዴት አለ እያሉ ወርቅ ፣ እጣን ፣ ከርቤን አምጥተው ሰጥተው ይሰግዱለት ዘንድ ከሩቅ ምስራቅ መጡ፣ ሔሮድስ ግን የመንግሥቱ ተቀናቃኝ የመጣ መስሎት በቅናት ተነሳ ህፃኑን ይገድለውም ዘንድ አሳደደው፡፡ የጌታ መላዕክ ግን በሕልም ለዮሴፍ ተገልጾ ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልን ተነሣ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ አለው፡፡
ይቀጥላል!   

No comments:

Post a Comment