Saturday, January 2, 2021

የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በቤተ ክርስቲያን አንደበት

 




ታኅሣሥ ፳፰ እና ፳፱ ልደቱ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ

‹‹ሰው ሆይ! ፈጽመህ ደስ ይበልህ፣ እግዚአብሔር ዓለሙን ወዶታልና አንድ ልጁንም የሚያምንበት ሁሉ እስከ ዘለዓለም ፈጽሞ ይድን ዘንድ አሳልፎ ሰጥቷልና ልዑል ክንዱን ሰደደልን፡፡››
‹‹በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ታላቅ ብርሃን ወጣላቸው፤ በቅዱሳን ላይ የሚያድር እግዚአብሔር እኛን ለማዳን ልዩ ከሆነች ድንግል ሰው ሆኗልና ኑ ይህን ድንቅ እዩ፤ ስለተገለጠልን ምሥጢር ምስጋና አቅርቡ፤ ሰው የማይሆን ሰው ሆኗልና ቃል ተዋሕዷልና ጥንት የሌለው ሥጋ ጥንታዊ ቀዳማዊሆነ፣ ዘመን የማይቆጠርለት መለኮት ዘመን ተቆጠረለት፡፡ የማይታወቅ ተገለጠ፣ የማይታይ ታየ፣ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ በእርግጥ ሰው ሆነ፡፡››
‹‹ከቅድስት ሥለሴ አንዱ ወልድ መዋረዳችንን አይቶ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ባሕርዩን ዝቅ አደረገና መጥቶ በድንግል ማኅፀን አደረ፤ ከብቻዋ ከኃጢአት በቀርም እንደ እኛ ሰው ሆነ፡፡ ነቢያት ትንቢት እንደተናገሩለት በቤተልሔም ተወለደ፤ ፈጽሞ አዳነን፣ ወገኖቹም አደረገን፡፡›› ቅዱስ ኤፍሬም
ሶሪያዊ በጌታችን ድንቅ ልደት የተደረገልንን ድንቅ የማዳን ሥራ በተናገረበት ድርሳኑ ላይ ነው እንዲህ ብሎ የጻፈው፡፡
ሰው ሆይ! ፈጽመህ ደስ ይበልህ!!! ፍጹም መዳን ይሆንላችሁ ዘንድ በስሙ አምናችሁ ለአምላክነቱ የምትገዙለት የክርስቶስ ወገኖች በእናቱም በወላዲተ አምላክ በድንግል ማርያም ፍጹም አማላጅነት የምትታምኑ የተዋሕዶ ልጆች ሁላችሁ እንኳን ደስ አላችሁ፣ እንኳን ደስ አለን፡፡ እንኳን አደረሳችሁ፣ እንኳን አደረሰን፡፡ እነሆ የጌታችንን የልደቱን ጥንተ ነገር አምጥተን መጻሕፍትን ጠቅሰን መምህራንን ዋቢ አድርገን እንነግራችሁ ዘንድ እንወዳለን፡፡
አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናች ክብርት እመቤታችን አምላክን ከመውለዷ ከ1520 ዓመት በፊት የፈላስፋዎችን የፍልስፍና መጽሐፈ ሕግ መርምሮ የሚያውቅ በለዓም የሚባል አንድ ታላቅ ፈላስፋ ነበረ፤ እርሱም የፈላስፎች ሁሉ አለቃ ነው፡፡
ከዕለታትም በአንደኛው ቀን ከአዳም እስከ ሙሴ ዘመን ያሉትን የሰዎች ትውልድ ቁጥር የያዙ የፍልስፍና መጻሕፍትን ሁሉ ሰበሰበ፡፡ ዳግመኛም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ በየጊዜው የሚነሡትን የሰዎች ቁጥርና ትንቢት የያዘ መጽሐፍ አቅርቦ መረመረ፡፡ እነዚህንም መጻሕፍት ገልጦ ሲመረምር በውስጣቸው አምላክን የወለደች ክብርት እመቤታችንን አገኛት፡፡ ባገኛትም ጊዜ እርሷ ድንግል ስትሆን ልጇን ክርስቶስን ታቅፋ አያት፤ በአጠገቧም ታላቅና ብሩህ ኮከብ ነበረ፡፡ በዚያን ጊዜም በለዓም ቀደ መዝሙሩን ዘረደሸትን እና ከእርሱ በታች ያሉትን ፈላስፎች ሁሉ ሰብስቦ በብራናው ላይ የተሣለውን የእመቤታችንንና የልጇን የመድኃኔዓለምን ሥዕል በአጠገባቸውም ያለውን ኮከብ አሳያቸው፡፡ ፈላፋው መሰግልም በእርሱ ዘንድ ለተሰበሰቡት ፈላስፎች ‹‹ይህ ኮከብ በእናንተ ዘመን ወይም በልጆቻችሁ ዘመን ምልክት ቢያሳይ ወይም ቢገለጥ የዚያን ጊዜ ድንግል ከነልጇ ወዳለችበት መርቶ ያደርሳችሁ ዘንድ እርሱን ተከተሉት›› አላቸው፡፡ ይህንንም ምልክት ከነገራቸው በኋላ ፈላፋው በለዓምና የእርሱ ተከታዮች ሁሉ ሞቱ፡፡ ነገር ግን በሕይወት ያሉትና ከእነርሱም በኋላ የተነሡት ሰዎች ያችን ሥዕል በቤተ መዛግብት ውስጥ አኖሯት፡፡ ያችም ሥዕል ለሚጎበኟት ሁሉ በኋለኛው ዘመን የሚደረገውን አባቶቻቸው የተናገሩትን ትንቢት ይነግሯቸው ነበር፡፡
ከአንድ ሺህ አምስት መቶ ዓመታት በኋላ ጌታችን በቤተልሔም ሊወለድ ሁለት ዓመት ሲቀረው ያ ኮከብ በሀገራቸው ላይ በግልጽ ታየ፡፡ በዚያ ጊዜም ያንን ሥዕል ከቤተ መዛግታቸው አወጡና በሥዕሉ አጠገብ ያለውን የኮከብ ሥዕል ቢመለከቱ በአየር ላይ ከተገለጸላቸው ኮከብ ጋር አንድ መልክ ወይም ትክክል መሆኑን አረጋገጡ፡፡ አባታቸው ዘደረሸት እንዳስረዳቸው የሀገሩ ፈላስፎችና መኳንንቶች ሁሉ ከሠራዊቶቻቸው ጋር እጅ መንሻውን ይዘው ሥዕሉን ተሸክመው ለመሄድ ተነሡ፡፡ ኮከቡም ከሰው ቁመት ርቀቱ 75 ሜትር በሆነ ከፍታ ላይ ሆኖ በፊት በፊታቸው ይመራቸው ነበር፡፡ ከእነርሱ ወገን ያልሆነ ልዩ ጠባይ ወይም ባሕል ወይም ቁም ነገረኛ ያልሆነ ሰው የተከተላቸው ወይም በመሀላቸው የተገኘ እንደሆነ ኮከቡ ይሰወራቸው ነበር፡፡ ነገር ግን እነርሱ ከእርሱ ወገን ያልሆነውን ተመራምረው ከመካከላቸው ባስወገዱት ጊዜ ኮከቡ እንደቀድሞው ተገልጾ ይመራቸው ነበር፡፡ በመሸም ጊዜ ወደ ማደሪያ ቦታ ያደርሳቸውና ሲነጋ ዳግመኛ ይመራቸዋል፡፡ ኮከቡም መልኩ በብዙ ዓይነት ልውጥ ነበር፡፡ ሕፃን የታቀፈች ድንግል ብላቴናን ይመስላል፡፡ በእንዲህ ዓይነት ጉዞ እየተጓዙ ጌታችን ከተወለደበት ቦታ ኢየሩሳሌም በሁለት ዓመት ደረሱ፡፡
ኢየሩሳሌም እንደደረሱ ያ እየመራ ያመጣቸው ኮከብ ተሠውራቸው፡፡ እነርሱም እጅግ አዝነው የሚያደርጉትን አላወቁም ወደ ከተማ ገብተው ስለተወለደው ንጉሥ ጠየቁ፡፡ የእነዚህም ሰዎች አጠቃላይ ቁጥራቸው ሠላሳ ሺህ ነው፣ ነገሥታቱም ሦስት ናቸው፡፡ ለእያንዳንዱ ንጉሥ 10 ሺህ ሠራዊት ነበረውና ሄሮድስ ይህን ያህል ሰው የተወለደውን የአይሁድን ንጉሥ ለማየት መምጣታቸው እጅግ አስደነገጠው፡፡ መላዋ ኢየሩሳሌምም ከሄሮድስ ጋር ታወከቸ፡፡ ሄሮድስም የካህናት አለቆችንና የሕዝቡን ጸሐፊዎች ጠርቶ ‹‹ክርስቶስ በየት ይወለዳል?›› አላቸው፡፡ እነርሱም ‹‹በነቢይ ‹የአፍራታ ዕፃ ቤተልሔም አንቺም ከይሁዳ ነገሥታት አታንሺም ወገኖቼ እስራኤልን የሚጠብቅ ንጉሥ ካንቺ ይወለዳልና› ተብሎ ተነግሯልና በቤተልሔም ይወለዳል›› አሉት፡፡ ከዚህም በኋላ ሄሮድስ ሰብዓ ሰገልን ጠርቶ ኮከቡ የታየበትን ዘመን ከእነርሱ ተረዳ፡፡ ‹‹ሄዳችሁ የሕፃኑን ነገር መርምራችሁ ያገኛችሁት እንደሆነ እኔም መጥቼ እሰግድለት ዘንድ በእኔ በኩል ተመልሳችሁ ኑ›› አላቸው፡፡ እነርሱም የነገራቸውን ሰምተው ከንጉሡ ዘንድ ሄዱ፡፡ እነሆ ያ በምሥራቅ ያዩትና ይመራቸው የነበረው ኮከብ ዳግመኛ ወደ ቤተልሔልም እስኪያደርሳቸው ድረስ ይመራቸው ነበር፡፡ ሕፃኑም ካለበት ዋሻ ላይ ደርሶ ቆመ፡፡ ኮከቡንም ባዩት ጊዜ እጅግ ደስ አላቸው፡፡ ሕፃኑንም ድንግል እናቱ በክንዷ እንደታቀፈችው እነርሱ ከያዙት ሥዕል ጋር አንድና ትክክል ሆኖ ሆኖ ባገኙት ጊዜ እጅግ አደነቁ፤ ፈጽመውም ተደሰቱና እጅ ነሱት፤ ወድቀውም ሰገዱለት፡፡ ሣጥናቸውንም ከፍተው ወርቅ፣ ዕጣን፣ ከርቤውን እጅ መንሻ አቀረቡለት፡፡ ከዚህም በኋላ ወደ ርጉም ሄሮድስ እንዳይመለሱ በሕልም ተረድተው በሌላ መንገድ ወደሀገራቸው ተመለሱ፡፡ አምላክ በሥጋ ስለመገለጡ ዓዋጅ ነጋሪዎችና ሰባኪዎች ሆኑ፡፡
ይህችም ዕለት ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ብሎ ትንቢት የተናገረላት ናት፡- ‹‹እነሆ ድንግል ፀንሳ ወንድ ልጅ ትወልዳለች፣ ስሙንም ዐማኑኤል ትለዋለች፣ትርጓሜውም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሆነ ማለት ነው፡፡
ስለዚህችም የበከረች ድንግል ነቢይ ሕዝቅኤል ‹‹እግዚአብሔርም አለኝ ‹ይህች በር ተዘግታ ትኖራለች፣ አትከፈትም፣ የሚገባበትም የለም የእስራኤል ፈጣሪ እግዚአብሔር እንደተዘጋች ይገባባታልና ተዘግታ ትኑር››› አለ፡፡
ነቢዩ ዳንኤልም ‹‹ሌሊት በራእይ አየሁ ‹እነሆ ታላቁ እንደ ሰው ልጅ በሰማይ ደመና መጣ፤ ዘመኑን ወደሚያስረጅ ደረሰ፣ ከፊቱም አቀረቡት፣ የዘላለምአገዛዝ፣ ጌትነት፣ መንግሥት ተሰጠው፡፡ ሕዝቡና አሕዛቡ ሁሉ መንደር መንድረው የሚኖሩትና ነገዱም ነገሥታቱም ሁሉ ይገዙለታል፤ አገዛዙም የዘላለም አገዛዝ ነው፤ መንግሥቱም የማያልፍ የማይጠፋ ነው››› አለ፡፡
ዳግመኛም ኢሳይያስ ‹‹እግዚአብሔር እንደ እኔ የሥጋ መጋረጃ በመጋረድ ተገለጠልኝ›› አለ፡፡ አሁንም ደግሞ ‹‹አዲስ ሰማይ አዲስ ምድር እሠራ ዘንድ አለኝ›› አለ፡፡ ሁለተኛም ‹‹በእሴይ ሥር በትር ትወጣለች፣ ከእርሷም ጽጌ አበባ ይወጣል›› አለ፡፡ ዳግመኛም ‹‹ሕፃን ተወልዶልናልና ወንድልጅም ተሰጥቶናልና ይኸውም ሥልጣን በጫንቃው የሆነ ክርስቶስ ነው፣ ስሙም ድንቅ መካር፣ ኃያል አምላክ፣ የዘላለም አባት፣ የሰላም አለቃ ይባላል›› አለ፡፡
ነቢዩ ኤርምያስም ስለ እግዚአብሔር ‹‹በዚያን ወራት ለዳዊት ብርሃንን አወጣለሁ፣ በምድርም የቀና ፍርድን ያደርጋል፣ እግዚአብሔርም ያመኑትን ያድናቸዋል›› አለ፡፡
ኤልሳም ‹‹እግዚአብሔር ከሰማይ ይወርዳል፣ በእስራኤል ልጆች አደባባይም በመመላለስ ለሕዝቡ ዕውነትን ያስተምራቸዋል፡፡ ከአብርሃም ልጅነት ልዩ ከሆኑወገኖች በቀር አሕዛብ ሁሉ ይታዘዙለታል›› አለ፡፡
ናሆምም ‹‹እግዚአብሔር በእኔ አርአያ ይመጣል፣ ልብሱም እንደልብሴ ነው›› አለ፡፡
ኢዩኤልም ‹‹የእግዚአብሔር ዙፋን የሆነች ብላቴና ድንግልን አየሁ፣ እርሷም እንደ እሳት ያልባት ነበር፡፡ ስለእርሷ ‹ይህች ማናት/› ብዬ ኪሩብን ጠየቅሁት፡፡ እርሱም ‹ከአዳም ልጆች የተመረጠች የእግዚአብሔር ዙፋን ይህች ድንግል ናት፣ በእርሷም የተጎሳቆሉ አሕዛብ ይድናሉ፤ ለአመነባትም ረድኤትና መጠጊያ ናት› ብሎ ነገረው፡፡››
ዳዊትም በመዝሙሩ ‹‹እግዚአብሔር አንተ ልጄ ነህ፣ ዛሬም በተዋሕዶ ወለድኩህ አለኝ፡፡ ለምነኝ አሕዛብን ርስት አድርጌ እሰጥሃለሁ፣ ግዛትህም በመላውዓለም ነው፡፡›› ዳግመኛም አብ አለ ‹‹ቀዳማዊ ወልድ በኃይል ቀን ካንተ ጋራ ሳለሁ ከአጥቢያ ኮከብ በፊት ከሆድ ወለድኩህ፣ እንደ መልከ ጸዴቅ ሥርዓት አንተ የዓለሙ አገልጋይ ካህን ነህ ብሎ እግዚአብሔር ማለ፣ ከማለም አይፀፀትም፡፡››
ቤዛ ይስሃቅ በግዕ ከኅቱም ዕፀ ሳቤቅ እንደተገኘ፣ ለእስራኤልም በበረሃ ውስጥ ከኅቱም ዓለት ውኃ እንደፈለቀ፣ የደረቀ የአሮን በትርም እንደለመለመችና እንዳፈራች፣ በሶምሶንም እጅ ውስጥ ከአህያ መንጋጋ አጥንት ውኃ እንደፈሰሰ እንዲሁ የጌታችን ልደት በኅቱም ድንግልና ሆነ፡፡ በዕፀ ጳጦስ ውስጥ እሳት እንደነደደች፣ ዕፂቱም እንዳልተቃጠለች እንዲሁ የመለኮቱ እሳት ድንግልን አላቃጠላትም፡፡ ምስጋና ለእግዚአብሔር ይሁን ለዘላለሙ አሜን፡፡
ዳግመኛም ዛሬ ልደታቸው ከጌታችን ጋር የተባበረላቸው ብዙ ቅዱሳን አሉ፡፡ አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ፣ ቅዱስ ላሊበላ፣ ቅዱስ ነዓኩቶ ለአብ፣ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ፣ ቅዱሳን ነገሥታት አብርሐ ወአጽብሓ፣ አቡነ አካለ ክርስቶስ፣ አቡነ መዝራእተ ክርስቶስ፣ መስፍኑ ኢያሱ፣ የገርአልታው አቡነ ዳንኤል፣ ዳግማዊ ቂርቆስ ዘቡልጋ እነዚህ 11 ቅዱሳን ልደታቸው ከጌታችን ጋር የተባበረላቸው ናቸው፡፡ በረከታቸው ይደርብን፡፡
ሌሎችም ዕረፍታቸው ሆኖ በዓመታዊ በዓላቸው የሚታሰቡ ቅዱሳን አሉ ነገር ግን በዚህች የበዓላት ሁሉ ራስ በሆነች እጅግ በከበረቸ የጌታችን የልደት በዓል ዕለት ገድላቸውን ልናወሳ አልወደድንም፡፡ ከወርሃ ጥር ጋር አብረን እናየዋለን፡፡ በዚህች ዕለት ግን ከበዓለ ልደት ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ነጥቦች እናያለን፡፡
ነቢያት በትንቢታቸው ‹‹በሬ የገዢውን አህያም የጌታውን ጋጣ አወቀ›› (ኢሳ 1፡3)፣ ‹‹አቤቱ ድምፅህን ሰምቼ ፈራሁ ሥራህንም አይቼ አደነቅሁ፤ በሁለት እንስሳ መካከል አየሁህ›› (ዕን ፫፥፪) ብለው እንደተናገሩት ጌታችን በበረት ውስጥ አህያና ላም ትንፋሻቸውን ገብረውለታል፡፡ የሌሊቱን ቁር ለመግለጽ ነው፡፡ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም ዓለምን የሚገዛው በኪሩቤል ሠረገላ ላይ የሚቀመጠው የባሕርይ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ በከብቶች በረት የመወለዱን ነገር በማንሣት በአድናቆት ‹‹በበረት ውስጥ የዓለም ገዢ መተኛት እጅግ ድንቅ ነው፤ በበረት ከጽርሐ አርያም ይልቅ ረዘመ፤ ከምድር ዳርቻም ሰፋ፤ ሕዝቅኤል ካየው ሠረገላ ዳንኤልም ካየው ኪሩባዊ ዙፋን በረት በለጠ (ሕዝ 1፡18-23፣ ዳን 7፡9)፤ በረት ነባቢ ለሆነ መሥዋዕት መሻተቻ መንበርን ሆነ፤ ይኸውም የቅድስቲቱ እንቦሳ ልጅ ንጹሕ በግ ነው፤ ሰማይና ምድና የማይወስኑትን በረት ቻለው፤ ወሰነውም›› አለ፡፡
በሌሊት መንጋቸውን የሚጠብቁ እረኞች ነበሩ፡፡ መልአኩ መጥቶ እንዲህ አላቸው፡- ‹‹እነሆ! ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና፡፡ ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ›› አላቸው፡፡ ሉቃ 2፡10-12፡፡ ከመለአኩም ጋራ ሠራዊተ መላእክት መጥተው ‹‹ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ለዕጓለ እመሕያው-ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ›› አሉ፡፡ ቅዱሳን መላእክትም ከእነርሱ ተለይተው ወደ ሰማይ በወጡ ጊዜ እረኞቹ እርስ በርሳቸው ‹‹እንግዲህ እስከ ቤተ ልሔም ድረስ እንሂድ፣ እግዚአብሔርም የገለጠልንን ይህን የሆነውን ነገር እንይ›› ተባባሉና ፈጥነው መጡ፡፡
ማርያምንና ዮሴፍን ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙ፡፡ አይተውም ስለዚህ ሕፃንየተነገረላቸውን ነገር ገለጡ፤ የሰሙትን ሁሉ እረኞቹ በነገሩአቸው ነገር አደነቁ፤ የብርሃን እናቱ እመ አምላክ ግን ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ እያሰበች ትጠብቀው ነበር፡፡ ሉቃ 2፡13-19፡፡
መላእክትም ሰማይ መንበሩ ምድር የእግሩ መረገጫ የሆኑለት አምላክ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ በጎል ተኝቶ በጨርቅ ተጠቅልሎ አይተውት ደስ ብሏቸው ወደ ሰማይ ቢያርጉ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በዕሪና ከመንበሩ አይተውት ‹‹ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት›› ብለው አመስግነውት በጣዕም ላይ ጣዕም፤ በጸጋ ላይ ጸጋ ተጨምሮላቸው ደስ ብሏቸዋል፡፡ ልደቱን ይሹታልና፤ መላእክትም ብቻ አይደሉም እንስሳትም አራዊትም ደስ ብሏቸዋል፡፡ ይህም ሊታወቅ አንድ ባሕታዊ ቋርፍ ሲምስ ምዳቋ ‹‹ዮም ተወልደ መድኃኔዓለም ዮም ተወልደ ቤዛ ኵሉ ዓለም ዮምተወልደ ከሣቴ ብርሃን›› እያለች ስትዘል አይቷል። በጌታችን በልደቱ የባሕር ውኃ ወተትና ማር ተራሮች እንጀራ እንጨቶችም የበረከት ፍሬ ሆነዋል፡፡ ልደቱንም በኮከብ ተረድተው ሰብአ ሰገል (የጥበብ ሰዎች) ስማቸውም ማንቱሲማር፣ ሜልኩ በዲዳስፋ የተባሉ የፋርስ ነገሥታት ከገነት የተገኘ ወርቅ፣ ዕጣን ከርቤ አምጥተው ገብረውለታል፡፡
ይህንንስ ከምን አገኙት? ቢሉ አዳም ከገነት ከወጣ በኋላ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ቅዱስ ገብርኤል እና ቅዱስሩፋኤል ወርቅ ዕጣን ከርቤ አምጥተው ሰጡት፡፡ እርሱ ለሔዋን ሰጣት። ሔዋን ለሴት ሰጠችው። ከሴት ሲወርድ ሲዋረድ ከኖኅ ደረሰ። ኖኅ ከመርከብ ከወጣ በኋላ ለሴም ሰጠው። ሴም መልከጼዴቅን አስጠበቀው፤ መልከጼዴቅ ለአብርሃም ሰጠው። ከአብርሃም ሲወርድ ሲዋረድ በዳዊት በሰሎሞን አድርጎ ከአካዝ ደረሰ። በሱ ዘመን ቴልጌልፌልሶር ማርኮ ወስዶ ከቤተ.መዛግብቱ አኑሮታል። አባታቸው ዥረደሽት ይባላል፤ ፈላስፋ ነበር። አንድ ቀን በቀትር ከውኃ ዳር ሆኖ ሲላሰፍ በሰሌዳ ኮከብ ድንግል ሕፃን ታቅፋ አየ። ያየውን በሰሌዳ ቀርጾ አስቀመጠው። ሲሞት ልጆቼ እንዲህ ያለ ኮከብ ሲወጣ ባያችሁ ጊዜ ሰማያዊንጉሥ ይወለዳልና ይህን ወስዳችሁ እጅ ንሱ ብሎ ሰጥቷቸዋል። አንድም በለዓም ‹‹ከያዕቆብ ቤት ኮከብ ይወጣል›› ያለውን ሰምተው ይዘው መጥተዋል፡፡ዘኅ 20፡17፡፡
አንድም ትሩፋን በባቢሎን ሳሉ ነገሥተ ተርሴስ ወደ ስያት ስጦታ (ገጸ በረከት) አመጡ፤ ንግሥተ ሳባ ወዓረብ እጅ መንሻ ያመጣሉ እያሉ ሲጸልዩ ይሰሙ ነበረና ይኸን ይዘው መጥተዋል፡፡ አንድም ባሮክ አቴናወርዶ ነበር። ያን ጊዜ ዛሬ የሀገራችሁን ንጉሥ የሚገብረውን ወርቅ ኋላ ከእኛ ወገን ንጉሥ ሲወለድ ይገብረዋል ብሎ የነገራቸውን ይዘው ነው።
የተወለደ ዕለት ኮከቡን አይተው አባታችን የነገረን ደረሰ ብለው 12 ሆነው ሠራዊቶቻቸውን አስከትለው ተነሱ። ብዙም ሳይርቁ ጠላት ተነስቶባቸው ዘጠኙ ተመለሱ። እኒህ ሦስቱ ግን ኮከቡ እየመራቸው ኢየሩሳሌም ደርሰው በሄሮድስ በኩል አድርገው ቤተልሔም ወርደው አግኝተው ገብረውለታል።


ምሥጢሩም፡-
ወርቅ መገበራቸው: ይኸን የምንገብርላቸው ነገሥታት ቀድሞም ፍጡራን ኋላም ኀላፍያን ናቸው። አንተ ግን ቀድሞም ያልተፈጠርህ ነህ፤ ኋላም የማታልፍ ነህ ሲሉ፤ አንድም ወርቅ ጽሩይ ነው፤ ጽሩየ ባሕርይ ነህ ሲሉ፤ እንዲሁም በአንተ ያመኑ ምዕመናንም ጽሩያነ ምግባር ወሃይማኖት ናቸው ሲሉ። አንድም ወርቅ የሃይማኖት ምሳሌ ነው። የሃይማኖት ጽሩይነቱና ግብዝነቱ የሚታወቅ መከራ ሲቀበሉበት ነውና።
ዕጣን መገበራቸው፡- ይኸንን የምናጥናቸው ጣዖታት ቀድሞም ፍጡራን ኋላም ኀላፍያን ናቸው። አንተ ግን ቀድሞም ያልተፈጠርህ ኋላም የማታልፍ ነህ ሲሉ። አንድም ዕጣን ምዑዝ ነው፤ አንተም በባሕርይ ምዑዝ ነህ ሲሉ እንዲሁ ደግሞ በአንተም የሚያምኑ ምእመናንን ምዑዛነ ምግባር ወሃይማኖት ናቸው ሲሉ። አንድም ዕጣን የተስፋ ምሳሌ ነው። ዕጣን ከሩቅ እንዲሸት ተስፋ ያልያዙትን እንደያዙት ያላዩትን እንዳዩት ታደርጋለችና።
ከርቤ መገበራቸው፡- ምንም ቀድሞ ያልተፈጠርህ በኋላም የማታልፍ ብትሆንም በሰውነትህ መራራ ሞትን ትቀበላለህ ሲሉ፤ አንድም ከርቤ የተሰበረውን ይጠግናል፤ የተለየውን አንድ ያደርጋል። አንተም ከማኅበረ መላእክት የተለየ አዳምን አንድ ታደርገዋለህ፤ ጽንዓ ነፍስ ሰጥተህ ታጸናዋለህ ሲሉ። አንድም በዕለተ ዓርብ ያቀምሱታልና ከርቤ አመጡለት። ከርቤ የምዕመናን ምሳሌ ነው። በፍቅር አንድ ይሆናሉና። ከርቤ የፍቅር ምሳሌ ነው። ከርቤ አንድ እንዲያደርግ ፤ ፍቅርም አንድ ታደርጋለችና።
በአጠቃላይ ሰብአ ሰገል ወርቅ፣ እጣን ከርቤ የገበሩለት ሃይማኖት፣ ፍቅር፣ ተስፋ፣ ገንዘቦችህ ናቸው ሲሉ ነው። በሌላ መልኩ ወርቅ ለመንግሥቱ፣ ዕጣን ለመለኮቱ፣ ከርቤ ለሞቱ ምሳሌ ናቸው።
ሰብዓ ሰገል እጅ ነስተው ከወጡ በኋላ አንዱ እንዴት ያለ ሽማግሌ ነው ብሎ አደነቀ። ሁለተኛው የምን ሽማግሌ ጎልማሳ ነው እንጅ አለ። ሦስተኛው ደግሞ ሕፃን ነው እንጂ አለ። ገብተን እንይ ተባብለው ቢገቡ ሽማግሌ መስሎ ለታየው ጎልማሳ፤ ጎልማሳ መለስሎ ለታየው ሕፃን፤ ሕፃነ መስሎ ለታየው ሽማግሌ መስሎ ታያቸው። ወጥተው እንዳንተ ነው እንዳንተ ነው ይባባሉ ጀመር። መልአኩ መጥቶ እንደሁላችሁም ነው አላቸው። በጆሮ የሰሙትን በዓይን ቢያዩት ይረዳል ብለው ለሦስተኛ ጊዜ ገቡ። ሽማግሌ ጎልማሳ መስሎ ለታየው ሕፃን፤ ጎልማሳ ሕፃን መስሎ ለታየው ሽማግሌ፤ ሕፃን ሽማግሌ መስሎ ለታየውጎልማሳ መስሎ ታያቸው። እጹብ እጹብ ብለው አመስግነው፤ አምላክነቱን ተረድተዋል። በሚሄዱበትም ጊዜ እመቤታችን የገብስ እንጀራ ጋግራ ሰጠቻቸው። ሀገራቸው እስኪገቡ ድረስ ከሠራዊቶታቸው ጋር (እያንዳንዳቸው አስር ሺህ፤ አስር ሺህ ሠራዊት) ሲመገቡ ቆይተው ከከተማቸው ሲደርሱ ይህን ቅዱስ ምግብ ከከተማችን አናስገባም ብለው ከከተማው በር ቀብረውት ገቡ። ደርሳችሁ መጣችሁን? አሏቸው። አዎን በአርባ ቀን መጣነው፤ እናቱም የሰጠችንን የገብስ እንጀራ እኛ እና ሠራዊቶቻችን ስንመገበው መጥተን ከከተማችን አናገባም ብለን ከከተማው በር ቀብረነዋል አሏቸው። አሳዩን አሉ። ተያይዘው ቢሄዱ ሲጨስ አግኝተውታል።
የልደት በዓል መቼ መከበር ጀመረ? ቀኑስ ምን ቀን ይውላል?
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበትን እርግጠኛውን ዕለት ለማወቅ የአስትሮኖሚ፣ የአርኬዎሎጅና የታሪክ ምርምር ሰዎች /ሊቃውንት/ ብዙ ጥናት አድርጓል፡፡ ዳሩ ግን በአንድ ሐሳብ ሊስማሙ ባመቻላቸው፣ የክርስቲያኑ የቀን መቈጠሪያዎች በዚሁ ሁኔታ አንድ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡ ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ መከበር የተጀመረው ከአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ እንደሆነ ታሪክ ያስረዳል፡፡ ለዚህም በጎርጎርዮሳውያን የዘመን ለቈጣጠር የሚጠቀሙት የዓለም ሕዝቦች የክርስቶስን ልደት እኛ ኢትዮጵያውያን ከምናከብረው የልደት በዓል 13 ቀን ቀድመው ያከብራሉ፡፡ የሮም ቤተ ክርስቲያን የጌታችን ልደት በታኅሣሥ 25 ቀን ታከብር እንደ ነበር ከ336ዓ.ም ጀምሮ ግልጽ ነው፡፡ ይህ ቀን በአህዛብ ዘንድ የፀሐይ በዓል እየተባለ ይከበር ስለነበር ክርሰቲያኖች ይኽንን የጣኦት አምልኮ ጠባይ ያለውን በዓል ለማጥፋት ሲሉ የጌታን ልደት በዚሁ ቀን ማክበር ጀመሩ፡፡ የምሥራቅ ቤተ ክርስቲያንም ቅድሚያ ሰጥታ የምታከብረው እ.ኤ.አ ጥር 6 ቀን የሚውለን የኤጲፋንያ በዓል ነበር፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግንየጌታን ጥምቀቱና ልደቱን ጥር 6 ቀን ስታከብር እንደቆየች የእውቀትና የታሪክ መድበል /ኢንሳይክሎፕዲያ/ ይገልጻል፡፡
*ቤተ ክርስቲያን አንዲት ስትሆን በክርስቲያን ዓለም ውስጥ እንዲህ ያለ ልዩነት እንዴት ሊፈጠር ቻለ?በመሠረቱ ዓለም ከመለያየት በስተቀር አንድ ለመሆን ያሰበበት ወቅት ምን ጊዜ የለም፡፡ (በታሪክ እንደምንረዳው) ልዩነቱ እንዴት እንደሆነ እንመልከት
*ከጌታ ልደት አስቀድሞ /በፊት/ በ46ዓ.ዓ ጁሊዮስ የተባለው የሮማ ቄሣር በጊዜው የከዋክብት መርማሪ የነበረው ሶስግነስን አስጠርቶ ተመሰቃቅሎ የነበረውን የዘመናት አቈጣጠር እንዲያስተካክል አዘዘው፡፡ ይኸም፣ ሊቅ ፈቃደኛ ሆኖ ዓመቱንም በ12 ወሮች ከፋፍሎ እያንዳንዱን ወር ከየካቲት በስተቀር በማፈራረቅ 31 እና 30 ቀናት እንዲኖራቸው አድርጎ አዘጋጀ፡፡ የካቲት ወር ግን 29 ቀን እንዲኖረው አደረገ፡፡ ነገር ግን በየአራቱ ዓመቱ አንድ ቀን ትርፍ ስለሚመጣ በአራተኛው ዓመት የካቲት 30 ቀን እንዲሆን ወሰነ፡፡ ጁሊየስ ቄሣርም የሮማው ሕዝብ በዚሁእንዲገለገል አዋጅ አወጀ፡፡ በተጨማሪም ጁሊየስ የዓመት መለወጫ መጋቢት የነበረውን ለውጦ /አዛውሮ/ ጥር እንዲሆን አደረገ፡፡ በዚሁም የጁሊየስን የዘመን አቈጣጠር ብዙ ሀገሮችለ1500 ዓመታት ያህል ሲገለገሉበት ቈይተዋል፡፡ ምክንያቱም የዓመቱ ቀናት ተቀምረው 365 ቀን ከሩብ ሊሆን መቻላቸው ነበር፡፡ ይህም ሆኖ የጁሊየስ አቈጣጠር ህጸጽ አልታጣበትም ምክንያቱም 11 ደቂቃ ከ14 ሰኮንድ ትርፍ ያሳይ ነበርና፡፡ ከዚህም የተነሳ እ.ኤ.አ በ1582ዓ.ም የነበረው የሮማው ፖፖ ጎርጎርዮስ /ስምንተኛ/ የከዋክብትን ሊቃውንት ሰብስቦ ከተመካከረበት በኋላ የዘመኑ አቈጣጠር ተሻሽሎ እንዲሰራበት አዋጅ አስተላለፈ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በጎርጎርዮስ የዘመን አቈጣጠር መቈጠር ጀመረች፡፡ በእምነት ተከታዮቻቸው የሆኑትም አገሮች ተቀብለው ወድያውኑ በሥራ ላይ ሲያውሉት የጀርመን ግዛቶች ግን እስከ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ በጁሊዮስ አቈጣጠር ይጠቀሙ ነበር፡፡ እንግሊዝም ብትሆን አዋጁን የተቀበለችው በ1752ኛ.ም እ.ኤ.አ ነው፡፡ ከዚያ ወዲህ ግን ምዕራባውያን አገሮች ተቀብለውታል፡፡ይህም ሊሆን የቻለው በ1582ዓ.ም የተጨመሩት 10 ቀናት ተጠራቅመው ጎርጎርዮስና ጁሊዮስ በተባለው የዘመን አቈጣጠር መኻከል ልዩነት ስለፈጠሩ ነው፡፡
*በዘመን አቈጣጠር ልዩነት የተነሣ የምዕራባውያንና ኢትዮጵያውያን የልደት በዓልን በማክበር በ13 ቀናት ይለያያሉ፡፡ ይሁን እንጂ በመጀመሪያው እንደተናገርኩት ዓለም ብዙ ጊዜ ስለ ዘመን አቈጣጠር ችግር ገጥሟት እንደ ነበረ ግልጽ ቢሆንም ኢትዮጵያ ግን በዘመነ ኦሪትም ሆነ በዘመነ ሐዲስ እንደ ንጋት ኮከብ የሚያበሩ ልጆች ስለነበሯት በቊጥር ግራ አልተጋባችም፡፡ ቀድሞም ዛሬም ባህልዋንና ቀመርዋን እንደያዘች ትገኛለች፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ አቈጣጠር ደግሞ እንደሚከተለው እንመልከት፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አቈጣጠርበዘመናችን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የጌታ ልደት ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት እንደሚያከብሩት ለምን አታከብርም? የሚል ጥያቄ በየአቅጣጫው ከተሰማ ውሎ አድሯል፡፡ አንድ ነገር መታወቅ ያለበት ግን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በዓለ ልደትን 29 ቀን የምታከብረው ብቻዋን ሳትሆን ከእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ጋር በመሆኑ ነው፡፡
*በቀን አከባበር ስለተፈጠረው መለያየት ምክንያቱንና የነገሩን ምንጭ ከእነማስረጃው አትቶ "በእንተ ልደት ድንግልናዌ" በሚል ርዕስ የእስክንድርያው ሊቅ ዮሐንስ አቤል ሄረም ጽፎት ይገኛልና ከዚያ መመልከት ይጠቅማል /አንቀጽ 84/ ዓይነተኛ ጉዳዩ ግን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃነት የተመሠረተ ነው ብላ ስለአመነችበት እንጂ ብዙ ዘመናት ሲሠራበት በመቈየቱ ወይም ደግሞ የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ስለምታከብረው ብቻ አይደለም፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት ስለ አለው ማስረጃ እንደሚከተለው እንረዳለን፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ የተጸነሰበትም ቀን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በድንግል ማኅፀን ለተጸነሰበትና ለተወለደበት ቀን መነሻ ሆኖ የሚገኝበት አለ፡፡ ይኸንም ለመረዳት ወንጌላዊ ሉቃስ የጻፈውን እንመልከት፡፡
*በይሁዳ ንጉሥ በሄሮድስ ዘመን ከአብያ ክፍል የሆነ ዘካርያስ የሚባል አንድ ካህን ነበረ፡፡ ሚስቱም ከአሮን ልጆች ነበረች፡፡ ስምዋም ኤልሳቤጥ ነበረ፡፡ ሁለቱም በጌታ ትእዛዝና ሕግጋት ሁሉ ያለነቀፉ እየሄዱ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ፡፡ ኤልሳቤጥም መካን ነበረችና ልጅ አልነበራቸውም፣ ሁለቱም በዕድሜያቸው አርጅተው ነበር፡፡ እርሱም በክፍሉ ተራ በእግዚአብሔ ፊት ሲያገለግል፣ እንደ ካህናት ሥርዓት ወደ ጌታ ቤተ መቅደስ ገብቶ ለማጠን ዕጣ ደረሰበት፡፡ በዕጣንም ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ በውጭ ቁመው ይጸልዩ ነበር፡፡ የጌታም መልአክ በዕጣኑም መሠዊያ ቀኝ ቆሞ ታየው፡፡ ዘካርያስም ባየው ጊዜ ደነገጠ፣ ፍርሃትም ወደቀበት፡፡ መልአኩም እንዲህ አለው፡፡ ዘካርያስ ሆይ ጸሎትህ ተሰምቶልሃልና አትፍራ፣ ሚስትህ ኤልሳቤጥም ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፣ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ ደስታና ተድላም ይሆንልሃል፣ በመወለዱም ብዙዎች ደስይላቸዋል፡፡ በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናልና /ሉቃ.1፡5-15/፡፡
*ወንጌላዊ ከተረከው የተገኘ ቅርጸ ሐሳብ የቱ ነው? ተብሎ ቢጠየቅ ትክክለኛ ጥያቄ ሆኖ ይገኛል፡፡ ፍሬ ሐሳቡ መልአኩ ገብርኤል ለዘካርያስ ስለመጥምቁ ዮሐንስ መወለድ ያበሠረበት ጊዜ መቼ ነው? የሚለው ነው፡፡ ይኸ በዕብራውያን ዘንድ በዓለ አስተሥርዮ ተብሎ ይከበር የነበረው ቀን መሆኑነው፡፡ በዓለ ሥርየትም ሲባል ደግሞ በዕብራውያን አቈጣጠር በሰባተኛው ወር ማለት /ጥቅምት አሥር ቀን የሚውል ታላቅ በዓል ነው/ /ዘሌ.16፡29-34/፡፡ /ዘኊ.29፡7-11/፡፡
*እነሆ ዘካርያስ ወደ ቤተ መቅደስ በገባ ጊዜ መልአኩ ያበሠረው በዚህ ጊዜ ነው፡፡ /ሉቃ. 1፡8-10፡21/፡፡ ይህ ዘካርያስ የተበሠረበት ቀን በአይሁድ በዓለ ሥርየት የዋለበት በዕብራውያን የዘመን አቈጣጠር ጥቅምት 10 ቀን ለመሆኑ ከጥንት አባቶች ዮሐንስ አፈወርቅ ማር.ዮሐንስ መስክረዋል፡፡ አሁንም ደግሞ ይህ ቀን ከኢትዮጵያ የቀን አቈጣጠር ያለው ተዛምዶ እንደሚከተለው ነው፡፡ መጀመሪያ ነገር በባሕረ ሐሳቡ የአቈጣጠር ሕግ እንደሚታወቀውሁሉ 5500ዓመተ ዓለምን በዐቢይ ቀመር፣ በንዑስ ቀመር፣ በማዕከላዊ ቀመር ተተንትኖ ተከፋፍሎ ውጤቱ የ5500 ዓመተ ዓለም ተረፈ ቀመር 9 ሆኖ ስለሚገኝ አንድን ለዘመን አትቶ መንበሩ 8ይሆናል፡፡ 8x11=88-60=28 አበቅቴው 28 ካለፈው የተያዘ 11የጨረቃ እና ዕለቱ 28 አበቅቴ ሲደመር ሠረቀ ሌሊቱ፣ 10 ሆኖ መጥቅዑም 2 ይሆናል፡፡ በሠረቀ ሌሊቱ 10+4=14 ጨረቃ ሆነ፡፡ እንግዲህ 14 የጨረቃ ሌሊት ይዘን እስከ መስከረም 16 ቀን ብንሄድ በዚያን ጊዜ የጨረቃ ብርሃን 29 መሆኑን ያሳየናል፡፡ መስከረም 18 ቀን ደግሞ የጨረቃ ብርሃናዊ ልደት ነው፡፡ የአይሁድ የቀዳማዊ ወርኅ ታሥሪን /መባቻ/ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ፀሐያዊ አቈጣጠር መስከረም ስለ አላለቀ እንዲህ እያልን እሰከ መስከረም 27 ቀን እንሄዳለን፡፡ በዕብራውያን ጥቅምት 10 ቀን ሲሆን በእኛ ደግሞ መስከረም 27 እንደነበረ እንረዳለን፡፡ በዚሁ ዘካርያስ ልጅ እንደሚወልድ ተበሠረ፡፡ ዘካርያስም ይህን አገልግሎት ከፈጸመ በኋላ ከበዓለ ሥርየት በኋላ እስከ 15ኛው የጥቅምት ጨረቃ በዓል ስለአልነበረ ወደ ቤቱ ገባ መጥምቁ ዮሐንስ ተጸነሰ፡፡ ይህም ሊቁ ኢትዮጵያዊው ቅዱስ ያሬድ ከሁለት ቀንም በኋላ ኤልሳቤጥ ጸነሰች፡፡ በማለት አስረድቶናል፡፡ አቡን /ብርሃነ ሕይወት/ ድጓ የታኅሣሥ ገብርኤል/ ቅዱስ ያሬድ ከሁለት ቀን በኋላ ኤልሳቤጥ ጸነሰች ያለው ቀንና ዘካርያስ ልጅ እንደሚወልድ እስከ ተበሠረበት ድረስ ያለው ቀን ብንደምረው ከመስከረም ይዘነው የመጣን 27 ቀን፣ የክህነት አገልግሎቱን ፈጽሞ ወደ ቤቱ እስከ ተመለሰበት ድረስ ያለው ጊዜ 3 ቀን፣ 27+3=30 ቀናት ይሰጠናል፡፡
*ሐዋርያው ሉቃስ ወደ ጻፈው ቃል እንመለስ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ኤልሳቤጥ ከጸነሰች በስድስተኛው ወር ወደ ቅድስት ድንግል ማርያም መላኩ፣ እና ቅዱስ ሉቃስም ዮሐንስ ከተጸነሰ በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስም በስድስተኛው ወሩ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን፣ ከነፍስዋ ነፍስን ነሥቶ ሰው የሆነበት ዕለት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የትርጓሜና የቊጥር መምህራን በማያሻማ መልኩ ተንትነው ቀምረው ለዚህ ትውልድ ማድረሳቸው እግዚአብሔር ከእነሱ ጋር እንደ ነበር ቋሚ ማስረጃ ነው፡፡ እንግዲህ የዮሐንስ ትንቢታዊ መጸነስ ክርስቶስ ሰው ለሚሆንበት ቀን የዕለታት ፋናው እያበራ ክርስቶስ ተጸንሶ እስከ ተወለደበት ዕለት ያደርሰናል፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጋቢት 29 ቀን ተጸንሶ ታኅሣሥ 29 ቀን ስለመወለዱጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መቼ ተጸንሶ መቼ እንደተወለደ ለማወቅና ለመረዳት ሐዋርያው ሉቃስ ወደተለመልን የአኀዝ ቊጥር እንመለሳለን፡፡ እነሆም በስድስተኛው ወር መልአኩ ገብርኤል በናዝሬት ወደም ትኖር ወደ ድንግል ማርያም ተልኮ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደምትጸንስና እንደምትወልድ ነገራት /ሉቃስ. 1፡26-38/ ይህም ቀን በኢትዮጵያ አቈጣጠር መጥምቁ ዮሐንስ ከተጸነሰበት ዕለት ጀምሮ ተቈጥሮ መጋቢት 29 ቀን መሆኑ እንገነዘባለን፡፡ ለምሳሌ ጥቅምት፣ ኅዳር ታኅሣሥ፣ ጥር፣ የካቲት፣ መጋቢት ድምር 6 ወር ነው፡፡ስለዚህ መጋቢት 29 ቀን ቃል /ቃለ እግዚአብሔር ወልድ/ ሰው ሥጋ የሆነበት፤ በድንግል ማኅፀን ያደረበት፤ በዓለ ትስብእት ነው፡፡ አሁን /ሰው የመሆኑ/ ሰው የሆነበት ቀን ከተረዳን፤ የተወለደበት ቀንና ወር ለማረጋገጥ ከመጋቢት 29 ቀን እስከ ታኅሣሥ 28 ቀን ጳጒሜን ጨምሮያለው ጊዜ 275 ቀናት ይሆናሉ፡፡ ይህም 275 ለ30 ሲካፈል 9 ወር ከአምስት ቀን ይሆናል፡፡ ይህም ማለት ከመጋቢት 2 ቀን፣ ከሚያዝያ እስከ ኅዳር መጨረሻ ወር ያሉት ወራት (8x30=240) ቀናት፣ 5 ቀናት የጳጒሜን፣ 28 ቀን ከታኅሣሥ፤ አጠቃላይ ድምር 275 ቀናት ናቸው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከርሠ ድንግል 9 ወር ከአምስት ቀን ከቈየ በኋላ በዕለተ ሠሉስ ታኅሣሥ 29 ቀንበ1ዓ.ም ከሌሊቱ 7 ሰዓት እስከ 10 ሰዓት ባለው ጊዜ በቤተልሔም ተወለደ፡፡ /ጊዮርጊስ ወልደ አሚድ ገጽ 158 እና 159/፡፡
ይህም በሒሳባዊ መንገድ የሚደረስበት ስለሆነ አያጠራጥርም፡፡ ሕጋዊ የሆነ የወንድ ልጅ በእናቱ ማኅፀን ተጸንሶ እስከሚወለድበት ጊዜ ድረስ የሚቈይባቸው ቀናት ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ለመሆኑ ከብዙ ዘመናት ጀምሮ ታምኖበት የቈየ ነው፡፡ አንዳንድ የቀናት መብዛትና ማነስ የሚታየው ህጸጽ አይነካውም /ኢሳ 7፡14፣ ገላ4፡4/፡፡ እነሆ ምሥራቃዊ ኮከብ ሰብአ ሰገልን የተወለደው ሕፃን እስከ አለበት ቦታ እየመራ እንዳደረሳቸውሁሉ ወንጌላዊው ሉቃስም እያነጣጠረ ያመለከተው ዘካርያስ የተበሠረበት ኮከባዊ ቀንም ፋናውን እየተቈጣጠረች ለምትከታተል ኢትዮጵያዊት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕፃኑ ኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ተወለደበት እንዳደረሳት ታምናለች፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያዊት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጌታን ልደት ታኅሣሥ 29 ቀን በታላቅ ምሥጋና ታከብረዋለች፡፡ /ማቴ. 2፡1-11፣2ጴጥ.1፡19-21/፡፡
ከኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጋር በዓለ ልደትን የሚያከብሩ አገሮች ወይም አብያተ ክርስቲያን፣ ግብጽ፣ ሶርያ፣ ህንድ፣ ኢትዮጵያ፣ አርመን ሲሆኑ ከሩቅ ምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ደግሞ የግሪክ ኦርቶዶክስ የሩሲያ ቤተ ክርስቲያን ናቸው፡፡ አውሮፓውያን በዓለ ልደትን የሚያከብሩት ከእኛ 13 ቀናት ቀደም ብለው ነው፡፡ ይህም ማለት በእኛ አቈጣጠር ታኅሣሥ 16 ቀን ነው እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቈጣጠር December 25 ቀን ነው፡፡ ልዩነቱ ለማወቅ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በዓለ ልደትን የምታከብረው ታኅሣሥ 29 ቀን ነው ይህም ማለት ከ29-16=13 ቀናት ወይም 16+13=29 ቀን ይሆናል፡፡ ይህ ቁጥር የሚያሳየን አውሮፓውያን ከእኛ በ13 ቀናት ቀድመው በዓለ ልደትን ሲያከብሩ ኢትዮጵያውያን ግን ከ13 ቀናት በኋላ ቈይተው ታኅሣሥ 29 ቀን በዓለ ልደትን ያከብራሉ፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ታኅሣሥ 29 ቀን ለመወለዱ የመሰከሩ ሊቃውንት
1. ማሪ.ኤፍሬም ሶርያዊ
2. ሰዒ.ድ ወ/በጥሪቅ
3. መበንጋዊ/ማኅቡብ
4. ጊዮርጊስ ወልደ አሚድ
5. ወልደ መነኮስ
6. በዲድስቅልያ አንቀጽ 29 ገጽ 37
7. የኢትዮጵያ መምህራን ሁሉ ናቸው
‹‹በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ታላቅ ብርሃን ወጣላቸው፤ በቅዱሳን ላይ የሚያድር እግዚአብሔር እኛን ለማዳን ልዩ ከሆነች ድንግል ሰው ሆኗልና ኑ ይህን ድንቅ እዩ፤ ስለተገለጠልን ምሥጢር ምስጋና አቅርቡ፤ ሰው የማይሆን ሰው ሆኗልና ቃል ተዋሕዷልና ጥንት የሌለው ሥጋ ጥንታዊ ቀዳማዊሆነ፣ ዘመን የማይቆጠርለት መለኮት ዘመን ተቆጠረለት፡፡ የማይታወቅ ተገለጠ፣ የማይታይ ታየ፣ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ በእርግጥ ሰው ሆነ፡፡››
‹‹ሰው ሆይ! ፈጽመህ ደስ ይበልህ፣ እግዚአብሔር ዓለሙን ወዶታልና አንድ ልጁንም የሚያምንበት ሁሉ እስከ ዘለዓለም ፈጽሞ ይድን ዘንድ አሳልፎ ሰጥቷልና ልዑል ክንዱን ሰደደልን፡፡››
ሰው ሆይ! ፈጽመህ ደስ ይበልህ!!!ፍጹም መዳን ይሆንላችሁ ዘንድ በስሙ አምናችሁ ለአምላክነቱ የምትገዙለት የክርስቶስ ወገኖች በእናቱም በወላዲተ አምላክ በድንግል ማርያም ፍጹም አማላጅነት የምትታምኑ የተዋሕዶ ልጆች ሁላችሁ እንኳን ደስ አላችሁ፣ እንኳን ደስ አለን፡፡ እንኳን አደረሳችሁ፣ እንኳን አደረሰን፡፡
(ምንጭ፡- ተአምረ ማርያም፣ ስንክሳር ዘውርሃ ታኅሣሥ፣ ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ሰ/ት/ቤት እና የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ያዘጋጇቸው ጽሑፎች)



ዓለምን የቀየረው የከበረው የክርስቶስ ልደት

 


ዓለም ካስተናገደቻቸው የታላላቅ ሰዎች፣ ነገሥታት ወይም ቅዱሳን ልደት ሁሉ የከበረው ልደት የትልቁ የክርስቶስ ልደት ነው።

የሁሉም ልደት የሚከበረው በተወሰኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ብቻ ሲሆን የክርስቶስ ልደት ግን በዓለም ሁሉ ውስጥ ባሉ አማኞችም ሆነ በፈላስፎችና በኢአማንያንም ዘንድ ሳይቀር ይታሰባል ይታወቃልም ።
ይህም የሆነበት ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደበት በተወደደችው ዓመት የዓለም ሚዛን በአማንያንም በኢአማንያንም ዘንድ የተዛባበት ወቅት ስለነበረ ነው። አማኞቹ አዳማውያን በመንፈሳዊው ሕይወት በዲያብሎስ ቅኝ ግዛት ጀርባቸው ጎብጦ ነፍሳቸው ዝሎ ግዞተኞች ሆነው ነበረ።
በአንጻሩ ዓለም በተለይ ከአባታቸው አብርሃም ወገን ክርስቶስ የተወለደው ዕብራውያን በተደጋጋሚ ጦርነትና በቅኝ ግዛት ተሰቃይተው በኢኮኖሚም ቢሆን ከስረው የነበረበት ዘመን ነበረ። ጥበብ ጠፍቶ ጠቢባን ዕውቀታቸው ለዛውን ባጣበት ወቅት የአብርሃም ተስፋ እንባን የሚያብሰው መንግስትን የሚመልሰው ጥበብ ክርስቶስ ተወለደ ከሚል የምስራች በላይ ምን ደስታ ይኖራልና።
ዓለም ሁሉ ጭው ብሎ ሰዎች ለመኖር ምንም ዋስትና ባላገኙበት በዚያ ዘመን ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም ተስፋ ሆኖ በዓለም ላይ አዲስ ብርሃን ከማብራት በላይ ምን ትልቅ ዜና ይኖራል(ሉቃ ፪፥፲-፲፪)
የዓለምን ሚዛን የሚቀይረው ወንድ ልጅ ፣ ንጉሥ ተወለደ የሚለው ቃል ሙት የሚቀሰቅስ ድምጽ ነበር። እውነትም የሚታይ ነገር ባይኖር ሁሉም ነገር ተስፋ አስቆራጭ በሆነበት ዘመን ሁሉን አዲስ የሚያደርግ ንጉሥ የመወለዱ ዜና የተቆረጠ ተስፋን የሚቀጥል ነበር።
ዛሬም ጥያቄዎች የበዙበትና ሰዎች ለመኖር ምክንያት ያጡበት ዘመን ይመስላል። ራስ ወዳድነት ነግሷል ሰው ሠራሽ ደስታዎችም የቆርቆሮ ጩኽት ሆነዋል ሰው እንደ አበደ ውሻ እርካታን አጥቶ ይቅበዘበዛል፤ ስልቹነትም ወረተኛ አድርጎታል የመኖር ቁም ነገሩ ገንዘብ ሆኗል፣ ሕግ ሚዛናዊነትን አጥቶ ድሆችን ሲገዛ ባለጠጎች ግን ይገዙታል፤ ታማኝነት ጊዜ ያለፈበት ሆኗል፤ ትልቁ ተቋም ቤተሰብና ትዳር ፈርሷል ፣ አደንዛዥ ዕፅ ና ግብረ ሰዶማዊነት ብልጭልጩ ዓለም ትውልዱን ማርከውታል። ጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች ፣ የተፈጥሮ አደጋዎች ፣ረሃብና ቸነፈር ሥጋት ሆነው ሳለ ሌላ የጦርነት ሥጋት ደም መፋሰስና እርስ በእርስ መጨካከን ትውልዱን አስጨንቆታል፣
ሕይወት ለብዙዎች ትርጉም የለሽ ሆኗል ብዙዎች እንደ ሸማኔ መወርወሪያ ቁም ነገርና ዝቅጠት ላይ ደርሰው ይመላለሳሉ። ብቻ ምን አለፋን ትውልዱ ለወንድሜ ከማለት ይልቅ የራስ ወዳድነት አባዜ ተጸናውቶት ከእናቱ መሃረብም ቢሆን ይሰርቃል፣ የእናቴ ልጆች ተጣሉኝ እንዳለ ዮሴፍ የእናቱን ልጅ ወንድሙን በግፍ እንደ ቃኤል ይገድላል።የረጋ ምንነት ሲጠፋ ሰው ራሱን ማግኘት በፍጹም አልቻለም።
ታዲያ ይህ ሁሉ ቢሆን እንኳ በጭራሽ ቀኑ አልጨለመም፣ እንዲያውም በጨለማ ለሄደው ሕዝብ ሁሉ ብርሃን ወጣ እንጅ (ኢሳ ፱፥፪) ፣የሰው እንጅ የእግዚአብሔር መልካምነት አላለቀም ፣ የተስፋችን የክርስቶስ ልደትም ሁልጊዜ አዲስ ነው ፣ የዓለምን ሚዛን የሚቀይረው ወንድ ልጅ ተወለደ የሚለው ዜና ዛሬም ትኩስ ዜና ነው፣አለቅነት በጫንቃው ላይ የሆነ ድንቅ መካር ኃያል የሰላም አለቃ ነውና (ኢሳ ፱፥፮)
ከሁኔታዎች በላይ የሆነው ታላቁ የምስራች፣ አእምሮን ሁሉ የሚያልፈው ሰላም ክርስቶስ ወወለዱ ነው። ታላቁ ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በሰዓታት ድርሰቱ " ሞገድ የማይቀርበው መርከባችን ፣ ብል የማያበላሸው መዝገባችን የእግዚአብሔር ልጅ ነው"። እንዲል ጨለማ ያላሸነፈው ለሁላችን የወጣው የጽድቅ ፀሐያችን አማኑኤል ነው(ሚል፬፥፪)። ዓለም የሌላት ያለው ጥበብ እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በፈረሰው ግርግዳ በኩል የሚቆም ጉድለታችን የሚሞላ ሙላታችን መሲሑ ነው። ዛሬ ሁላችን የሰው ልጆች በተለይ እኛ ኢትዮጵያውያን በዙሪያችን ያሉት የእኛ የሆኑት ወገኖቻችንም ሆኑ ክስተቶች ሁሉ በእጅጉ ያስፈራሉ ፣ ነገር ግን ከወደቅንበት ተነስተን በእምነት ሆነን ክርስቶስን ካየን ልደቱን ካስተዋልን በሁሉ ነገር ላይ እንደፍራለን እንጽናናለን። መድኃኔዓለም ክርስቶስ በሁሉ ነገር ላይ ስልጣን አለው። ረቂቃኑ ነፋሳትና የባህር ማዕበል እንኳ የሚታዘዙለት እርሱን ብናምነው ጌታችን ነው ፣ የማይታለፈውን እናልፋለን ፣ ክፉውን ዘመን እንሻገራለን። (ማቴ፰፥፳፯)


ከሰው ልጆች የሃይማኖት መጥፋት ዓለምን ሥርዓት የለሽ ቢያደርጋት የሕግ የበላይነት ቢጠፋ፤ መልካም ሰው በመብራት ተፈልጎ ቢታጣ ፤ ሰው ለሰው መድኃኒቱ መሆኑ ቀርቶ ፍርሃቱ ቢሆንም እንኳ በእምነት ከሆንን "መንግስትና ኃይል የእግዚአብሔር ናትና " በምንም አንፍራ አንሸበር ጸንተን እንቁም። (ማቴ፮፥፲፫) ሁኔታዎች ከምንጊዜውም በላይ አደጋ ያንዣበበት ጊዜ መሆኑን ቢያሳዩም በክርስቶስ ለሚያምን ግን በጽናት ይህን ያልፋል። በቤተክርስቲያናችን የኪዳን ጸሎት "መናፍስት ያመጡትን የጎርፉን ፈሳሽነት ፀጥ ያደረግህልን ፤ ከጥፋት አድነህ የሕይወት ወደብ የሆንከን ፣የዘላለም ድኅነት ያለበት መሸሻ የሆንከን ፣በማዕበል የተጨነቁትን የምታድን አንተ ነህ።" እንዲል ሁሉን መሻገሪያ ወደባችን ሰላማችን ክርስቶስ ነው።
የሰው ልጆች ከኖሩበት ብዙ የታሪክ ምእራፍ እንዲህ እንዳለንበት ዘመን ራሳቸውን በሥልጣኔና በቴክኖሎጅ የለወጡበት ዘመን የለም። ሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የዕውቀትና የመረጃ ዘመን ነው። አለም አንድ መንደር ሆናለች፣ አንድ ሰው ስለ ሰፈሩ ከሚያውቀው በላይ ስለ ዓለም በቂ ግንዛቤ አለው። ነገር ግን ዓለም በዘመናችን በብዙ ያልተመለሱ ጥያቄዎች ተሞልታለች። የነፍስን ባሕርይ የሚሞላ ዕውቀት እንጅ የመንፈስን ጥም የሚያረካ ነገር ጠፍቷል፣ ከትውልዱ ቅድስናና ፍቅር ርቋል (፪ጢሞ ፫፥፩-፱) ። ያለ እግዚአብሔር ጣልቃ ገብነት ሕይወት አስቸጋሪ መሆኗ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ እውን ሆኗል። እግዚአብሔር ግን ላለብን የሥጋና የነፍስ ጥያቄ ከልጁ የተሻለ መልስ አይሰጠንም። ለዛሬና ለወደፊት ጥያቄዎቻችን ሙሉ መልስ አድርጎ አንድያ ልጁን በዳግም ልደት ሰጥቶናልና ። ክርስቶስ ካለን ለጥያቄዎች ሁሉ መልስ አለን ፣ ክርስቶስ ከሌለን ሁሉ ነገር ጥያቄ ይሆንብናል።
እግዚአብሔር የሰው ልጆችን በእጆቹ አበጃጅቶ በመዳፉ ቀርጾ የፈጠረው ለውርደትና ለጥፋት ሳይሆን ለክብር ነው። ሰው ግን ክቡር ሆኖ ሳለ ክብሩን አላወቀም እንዲል ነቢዩ (መዝ፵፰፥፲፪) ከታሰበለት ደረጃ በመውረድ ማለቂያ ለሌለው ለዚህ ሁሉ ምስልቅል መዳረጉ የእምነት መጉደልና የኃጢአት ውጤት ነው። የእግዚአብሔር ሃሳብ አሰናካይነት የለውምና ዛሬ በእምነት በንስሐ ተመልሰን በልደቱ የምሥራች ሐሴት ካደረግን እርሱ ሁሉን አዲስ ሊያደርግ የታመነ ነው። (ራዕ ፳፩፥፭) በታማኝነትና በጽድቅ የተሞላች መንግስቱን ይመሠርታል (ኢሳ ፲፩፥፩-፱) ተብሎ እንደተጻፈ የጌታችን ልደት ላለፉት ፳፻ ፲፫ ዓመታት ቀስትና ጦርነትን ሽሯል፣ ፍትህን አጽንቷል፣
የታሰሩትን ፈቷል። የመጣው ለድሆች የምሥራችን ይሰብክ ዘንድ፣ልባቸው የተሰበረውን ይጠግን ዘንድ ፣ ለተማረኩት ነጻነትን ለታሰሩት መፈታትን የሚያለቅሱትንም ያጽናና ዘንድ ነውና (ኢሳ፷፩፥፩-፮)።
እንደ ንጉሥ ይነግሣልና እርሱ በፍቅር በትር የሚገዛ ገዥ ነው፣ የእግዚአብሔር መቅደስ በሰዎች መካከል ይሆን ዘንድ፣ ጸብና ክርክር እንዲወገድ የክርስቶስን የልደት ዜና እኛ በንስሐ ልደት ተወልደን እናክብር (ኢሳ፲፩፥፩-፬)።
ይህ ሲሆን ሰው ሰውን የማይጠግበው ይሆናል ፣ የታወከው የዛሬው ሥርዓት በእግዚአብሔር የሰላም ወንዝ ይለመልማል። የተበላሸው የሰው ልጆች የሞራል ልሽቀትና ግብረገብነት ይስተካከላል። በሰላም አገር በኢትዮጵያም ዘረኝነት ጦርነትና ደም መፋሰስ ያለፈ ሥርዓት ይሆናል (ኤር ፳፫፥፩-፭)። ሁላችንንም ለኃጢአት የሚፈትነን አሮጌውን ተፈጥሮ የፈሪሳውያን እርሾ በክርስቶስ ይለወጣል።(ሮሜ ፰፥፳፫፤ ፪ ቆሮ ፭፥፩፥፭) እርግማን ሁሉ በበረከት ይለወጥልናል፣ ሰላም መኖሪያችን ፍቅርም ምግባችን ይሆናል ፣ እንደ ሸማም የምንደርበው የዘወትር ኩታ ይሆንልናል።
በከብቶች በረት ራሱን ዝቅ አድርጎ በትህትና ለእኛ ክብር ከተገለጠው ጌታ ጋር በማያልፍ ሕይወት እንኖራለን።