Thursday, April 10, 2014

አቤቱ እባክህ አሁን አድን-ሆሳዕና



የዛሬ 1970 ዓመት አካባቢ በነገስታቱ ዘንድ ታይቶ የማይታወቅ አዲስ ነገር በኢየሩሳሌም ታየ፣ ነገስታት በጠባቂ ወታደር ታጅበው በልዩ ፈረስ ሲሰግሩ ለንጉስነታቸው ዘውድ ሲደፋላቸው የአበባ ምንጣፍ ሊነጠፍላቸው ሲገባ አዲሱ ንጉሥ የነገስታት ንጉስ ሆኖ ሳለ በተለየ ሁኔታ ለነገስታት ክብር ባልተለመደ ዘይቤ ወደ ኢየሩሳሌም ብቅ አለ፡፡



ይህ ንጉስ የክብር: ክብር: ክብር ምሥጋና ይግባውና ወደ ኢሩሳሌም ሊገባ በቀረበ ጊዜ የደብረ ዘይት አጠገብ ከምትሆን ቤተ ፋጌ ደረሰ ‹‹ወቀሪቦ ኢየሩሳሌም በጽሐ ቤተ ፋጌ እንተ ገቦ ደብረ ዘይት›› ቤተ ፋጌ ማለት የበለስ ቤት የተመሳቀለ መንገድ ማለት ሲሆን፣ ወደ ኢየሩሳሌምም በደረሰ ጊዜ ከአገልጋዮቹ ሁለቱን ላከ፣ አላቸውም! ‹‹ወይዕተ ጊዜ ትረክቡ›› በፊታችሁ ወዳለው ሀገር ሂዱ በዚያም በደረሳችሁ ጊዜ አህያዋ ከውርንጫዋ ጋር ታስራ ታገኛላችሁ ፈታችሁም አምጡልኝ ‹‹ፍትሕዋን ወአምጽእዋን ሊተ›› ማንም አንዳች ቢጠይቃችሁ ጌታቸው ይሻቸዋል በሉ ‹‹እግዚኦሙ ይፈቅዶሙ›› በሉ፡፡
ይህ ንጉሥ ደጉ ሣምራዊ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ሰው ሁሉ ከኃጢዓት እስራት የሚፈታበት ጊዜ እንደደረሰ ለማጠየቅ ፈታችሁ አምጡልኝ አለ ለምን ቢሉ በጥንተ ተፈጥሮ በእጆቹ አበጃጅቶ በመዳፉ ቀርጾ ፈጥሯቸዋልና ሸክላ ሰሪ ዕቃውን እንዲሻ ይፈልጋቸዋል በሉ አለ አህያና ውርንጫ የተመሰሉት አዳምና ልጆቹ ሲሆኑ አህዮቹ ታስረው የነበረው በመንደር በሲኦል ምሳሌ በሆነው ሥፍራ ነበር ገመዱም የኃጢዓት ምሳሌ ነው፤ አዳምና ሔዋን በፍዳ ኩነኔ በመርገመ ሥጋ በመርገመ ነፍስ ታስረው ነበርና (ምሳ 5፡22)
ጌታም በአህያይቱና በውርንጫይቱ ተቀመጠባቸውና ወደ ኢየሩሳሌም አቀና አስቀድሞ በነቢዩ በዘካርያስ ‹‹አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ (ህዝበ እስራኤል ሆይ) እጅግ ደስ ይበልሽ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ እልል በይ እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው ትሑትም ሆኖ በአህያ በአህያይቱም ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል›› ተብሎ ተጽፏልና (ዘካ 9፡9) ወደ ከተማው ወደ ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ ግን ሀገሪቱን አይቶ አለቀሰ (ሉቃ 19፡41)






·         በሞት መንደር በሙታን መካከል ትንሣኤና ሕይወት ሲገለጥ ባለማስተዋላቸው አለቀሰ
·         መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል የማያስተውሉ የአይሁድን ሰውነት ሰዱቃውያንና ፈሪሳውያንን አይቶ አለቀሰ
·         ከዲያብሎስ የተነሣ ሰላም አጥተው በታወኩት መሀል ‹ለሕዝብና ለአሕዛብ ሰላምን ያመጣ ዘንድ በአህያ ይመጣል› ተብሎ በተጻፈው መሠረት ሰላማቸው ሲመጣ ባለማስተዋላቸው አለቀሰ (ዘካ 9፡9)
·         ጽድቅ ልምላሜ አጥተው በደላቸው እንደ ነፋስ ባደረቃቸው ቅጠሎች መካከል የደረቀውን ያለመልም ዘንድ ዝናመ ምህረት ሲገልጥ ባለማስተዋላቸው አለቀሰ
·         ጽድቅን በተራቡትና በተጠሙት መካከል አማናዊ መብልና መጠጥ ሆኖ ሲገለጥ ባለማስተዋላቸው አለቀሰ
·         በሕሙማን መካከል ፈውስ በጠፋበት ዘመን ባለመድኀኒቶች ተስፋ በቆረጡበት ዘመን መድኀኒቱንና የመዳንን ቀን አላወቁምና አለቀሰላቸው:



             ደቀመዛሙርቱም ሄደው እንዳዘዛቸው አደረጉ አህያይቱንና ውርንጫዋንም አመጡለት ልብሳቸውንም በእርሱ ላይ ጫኑ ተቀመጠባቸውም ከሕዝቡም እጅግ ብዙዎች ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፣ (ማቴ 21፡7) ደቀመዛሙርቱ ኮርቻውን የሚቆረቁረውን ትተው የሚመቸውን ልብሳቸውን በአህያይቱ ላይ ማድረጋቸው የማትመቸውን የምትቆረቁረውን በኮርቻ የተመሰለችውን ኦሪትን ሳይሆን አዲስና የምትመች ህገ ወንጌልን አመጣህልን ሲሉ ነበር፡፡
ሕዝቡም ልብሳቸውን በመንገድ ላይ ማንጠፋቸው ልብስ በአካል ያለውን ጠባሳ፣ ቆሻሻ ቁስል እንደሚሸፍን እነርሱም እንጂ ነቢዩ ኢሳይያስ ‹‹እኛ ግን የመርገም ጭቃዎች ኀጢዓተኞች ነን›› እንዲል አቤቱ አምላካችን ሆይ ከባቴ አበሳ ነህ ኀጢዓታችንን የሸፈንህልን በደላችን የማትቆጥርብን ነህ ሲሉ ልብሳቸውን አነጠፉ ‹‹አቤቱ ኀጢዓትንስ ብትጠባበቅ በፊትህ ማን ይቆማል?›› መዝ 129፡3 በማለት መዝሙረኛው የምህረቱ ካባ ባይሸፍነን ቆመን መስበክና መዘመር፣ መቀደስና ማስቀደስ የማንችል ከመሆናችን ባሻገር ወደ ቅድስናው ሥፍራም የምንገባው በምህረቱ እንደሆነ ጽፎልናል ‹‹እኔ ግን በምህረትህ ብዛት ወደ ቤትህ እገባለሁ አንተን በመፍራት ወደ ቅድስናህ መቅደስ እሰግዳለሁ›› (መዝ 5፡7)
አንድም ልብሳቸውንና የዘንባባውን ዝንጣፊ መሬቱ ላይ ሳይቀር ጎዘጎዙለት ይህንንም ያደረጉት ለአንተም ሆነ አንተን ለተሸከመችው አህያም ክብር ይገባታል ሲሉ አነጠፉለት ጌታን በሆሳዕና ዕለት ለተሸከመችው አህያ ክብር የሚገባ ከሆነ እንግዲህ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን አምላክን በድንግልና የፀነሰች በማህፀኗ የተሸከመች እመቤታችን፣ የአብ ሙሽራው የወልድ እናቱ የመንፈስ ቅድስም ንጹሕ አዳራሽ የተባለች ንጽሕት እመቤት ምን ያህል ክብር ይገባታል፡፡ በመጽሐፍ ‹‹ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል›› (ሉቃ 1፡48) ተብሎ ተመዝግቧልና ከዚህ ትውልድ ለመቁጠር ድንግል ማርያምን ማመስገን ግድ ይላል፡፡
ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ደቀመዛሙርትህ ለምን ይዘምራሉ ብለው በሕዝቡ ላይ እንዳጉረመረሙ ዛሬም አምላክን የተሸከመችውን ድንግል ማርያምን ለምን አከብራችኋት እመቤቴስ ለምን አላችኋት ብለው ለሚያጉረመርሙ የእግዚአብሔር ዙፋን የመለኮት ማደሪያ ሆናለችና ክብር ምስጋና ይገባታል ብሎ መገሰጽ ይገባል፡፡
         በሌላው እስራኤላውያን በሚያውቁት ልማድ ቅጠል አንጥፈዋል ጨርቅ ጎዝጉዘዋል፤ በባሕላቸው የተመረጠ ለንጉሥነት ሲታጭ ይህን ያደርጉ ነበርና ‹‹2ኛ ነገ 9፡1-13 የተመረጠው እዩ ለንጉሥነት በታጨ ጊዜ በዘመኑ የነበሩት ሰዎች እኩሌቶች አንጥፈዋል እኩሌቶችም ጋርደዋል፣ ሌሎችም የቅጠል ዝንጣፊ እየቆረጡ ከመንገድ ያነጥፉ ነበር››
ጌታ ከቤተ ፋጌ ወደ ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ ሕዝቡ ያነጥፉለት የነበረውን የቅጠል ዝንጣፊ ከአራቱ ወንጌላውያን ቅዱስ ዮሐንስ ‹‹የሰሌን ዝንጣፊ ይዘው ከኢየሩሳሌም ፈጥነው መጡ›› በማለት ቅጠሉ ዘንባባ መሆኑን ገልጸዋል (ዮሐ 12፡12-13)
በዚህም ትውፊት መሠረት በነቢያትና በሐዋርያት መሠረትነት ላይ የታነጸችውና የማዕዘኑ ራስ ኢየሱስ ክርስቶስ የሆነላት ኦርቶዶሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የጌታን የሆሳዕና በዓል በዘንባባ ቅጠል በሰሌን ዝንጣፊ ታከብራለች፡፡


 
ይኸውም የሆነበት
፩ኛ፦ዘንባባ የደስታ መግለጫ ስለሆነ
የሕዝብና የአሕዛብ አባት፣ አበ ብዙኀን የተባለ አብርሃም ይስሐቅን በስተርጅና በወለደ ጊዜ ደስታውን ለመግለጽ የዘንባባ ዝንጣፊ ይዞ በመሠዊያው ዙሪያ እየዞረ ሰባት ቀን አመስግኗል፡፡ ‹‹ኩፋ 13፡21 አብርሃም የሰሌኑን ጫፍ ለጋውን ያማረ የእንጨቱንም ፍሬ ይዞ በየቀኑ ዘንባባውን ይዞ ሰባት ቀን የመሰዊያውን ዙሪያ ይዞር ነበር›› አብርሃም በዘርህ ምድር ይባረካል የተባለለትን ይስሐቅን በተቀበለ ጊዜ ዘንባባ ይዞ እንዳመሰገነ እኛም በአዳም ስህተት ምክንያት ተረግሞ የነበረውን ምድር በደሙ የሚባርከው የአብርሃም ዘር የይስሐቅ ምሳሌ ኢየሱስ ክርስቶስ መጣ ስንል የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘን ሆሳዕና ጌታ ሆይ አሁን አድን እያልን እናመሰግናለን፡፡ (ዘፍ 3፡17 ፣ ማቴ 1፡1 ፣ ዘፍ 22፡2)
፪ኛ፦ ቤተ እስራኤልም ከግብፅ ባርነት ነጻ ስለወጡ የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው አመስግነዋል
እስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት ከፈርኦን አገዛዝ በዘጠኝ ጽኑ ተአምራት በአስረኛ ሞተ በኩር ነጻ አውጥቶ የኤርትራን ባሕር ከፍሎ ውሃውን እንደሳር ክምር እንደ ግርግዳ አቁሞ ስላሻገራቸው እግዚአብሔር ያደረገላቸውን ነገር አስበው የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው የዘራነውን ፍሬ የባረክህ ይህንም ጸጋ የሰጠኸን አምላክ ሆይ ምስጋና ይገባሃል ሲሉ አመስግነዋል፡፡ ‹‹ዘሌ 23፡40 በመጀመሪያው ቀን የመልካም ዛፍ የሰሌን ቅርንጫፍ የለመለመውንም ዛፍ ቅርንጫፍ የወንዝም አያ ዛፍ ወስዳችሁ በእግዚአብሔር ፊት ሰባት ቀን በምስጋና ደስ ይበላችሁ››
እኛም በፈርኦን ከተመሰለው ከዲያብሎስና ሠራዊቱ የዘመናት ግዞትና በግብፅ ከተመሰለው ከሲኦል የባርነት ቀንበር ነጻ ልታወጣን የባርነታችን ቀንበር ልትሰብር መርገማችን ልትሽር በአህያና በውርንጫ ተቀምጠህ መጣህ አቤቱ እባክህ አሁን አድን ሆሳዕና ስንል የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘን እናመሰግነዋለን፡፡





፫ኛ፦ ዘንባባ የድል ምልክት ነው
ዮዲት ሆሎፍርኒስ የተባለውን የእስራኤል ጠላት አሸንፋ ድል በተጎናጸፈች ጊዜ ሕዝቡ የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው እሷን ስለጀግንነቷ እግዚአብሔርን ስለረዳቸው አመስግነዋል፡፡ ‹‹መጽ.ዮዲት 15፡12 የእስራኤልም ሴቶች ሁሉ ያይዋት ዘንድ ይመርቋትም ዘንድ ሮጠው ወጡ ደግ በዓልን አደረጉላት ዘንባባውንም በእጇ ያዘች ከእርሷ ጋራ ላሉ ሴቶች ሰጠች እነሱም አመሰገኗት››
እኛም ለ ሺህ መቶ ዘመን በላያችን ላይ ሰልጥኖ የነበረውን ጠላታችን ዲያብሎስን አከርካሪውን መትቶ ድል በማድረግ የሞትን መውጊያ ሠብሮ ትንሣኤን ያወጀውን ብቸኛውን ንጉስ ኢየሱስ ክርስቶስን አሁንም እባክህ አድን ሆሳዕና ስንል የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘን እናመሰግናለን፡፡  
፬ኛ፦ ድል የነሡት ጻድቃን በሰማይ በኢየሩሳሌም የብርሃን ዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው ነጭ ልብስ ለብሰው በዙፋኑና በበጉ ፊት ለምስጋና ይቆማሉና፡፡
‹‹ራዕ 7፡9 ከዚህ በኋላ አየሁ እነሆም አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ ነጭ ልብስም ለብሰው የዘንባባም ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆሙ በታላቅም ድምጽ እየጮኹ በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው  ለአምላካችን  ለበጉ ማዳን ነው፡፡" ይላሉ::
  እኛም አምላካችን የታረድከው በግ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ እባክህን አሁን አድን ሆሳዕና በአርያም ለሰማያዊት ኢየሩሳሌም አብቃን የብርሃን ዘንባባ ይዘው ከሚያመሰግኑህ ከተመረጡትና ከቅዱሳኑ ጋራ ቁጠረን እያልን ለሰማያዊት ኢየሩሳሌም ምሳሌ በሆነችው ቅድስት ቤተክርስቲያን የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘን በአህያ ውርንጫ የተገለጸውን ንጉሥ እናመሰግናለን፡፡ ‹‹አቤቱ እባክህን አሁን አድን፣ አቤቱ እባክህን አሁን አቅና መተማመን ከሰው ልጆች ጠፍቷልና በምህረትህ ተመልከተን እያልን እንማጸናለን›› (መዝ 117፡25) በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ብሩክ ነው፣ በተወደደችው ዓመት የወደቁትን ሊያነሣ የተረሱትን ሊያስታውስ የሚመጣ በእውነት ብሩክ ነው፡፡

 
    አይሁድ ይህ የከበረ ንጉሥ ራሱን ዝቅ አድርጎ ባልተለመደ ሁኔታ ሲመጣ እንዳያመሰግኑት አፋቸው ተያዘ ‹‹እም አፈ ደቂቅ ወሕጻናት አስተዳሎከ ስብሐተ፤ ከሕጻናትና ከሚጠቡት አንደበት ምስጋናን አዘጋጀህ (መዝ 8፡2)›› ተብሎ ተጽፏልና፣ ሕጻናት ሲያመሰግኑ እነሱንም እንዳያመሰግኑ ከለከሉ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ያመሰግናሉ አላቸው ,
አንድም የቢታንያ ድንጋዮች በሰው አፍ ተናግረው ለምስጋና ተነስተዋልና፡፡ ‹‹ሆሳዕና ሆሳዕና በሌላው ሕዝብና አሕዛብን አንድ ሊያደርግ መጥቷልና አሕዛብን ድንጋዮች ያመሰግናሉ አለ አቤቱ እባክህ አሁን አድን ይላሉ ለጊዜው እስራኤላውያን በሮማውያን ቅኝ ግዛት ተይዘው ባርነት ሰልችታቸው ቀንበሩ ከብዷቸው ነበረና የሥጋ ጩኸት አቤቱ እባክህ አሁን አድን፣ ንጉሥ ሆይ እባክህ አሁን አቅና ብለው ተማጽነዋል፡፡ ፍጻሜው ግን አቤቱ በነፍሳችን አድነን አሳዳጃችን በአንገታችን ላይ ነውና፣ ከመርገመ ሥጋ ከመርገመ ነፍስ አድነን፣ የሺህ መቶ  የመከራው ዘመን በዛብን ሲሉ ነበር ሆሳዕና አቤቱ አሁን አድን ያሉት እኛም አቤቱ እባክህ አሁን አድን ብለን እንማጸን፡፡
        በተለይ እኛ ኢትዮጵያውያን የምናለቅስበት የምንጮህበት ዘመን ነው፡፡
   ·   መለያየት ሰይፍ ነው፣ ፍቅር ማጣት ሰይፍ ነው በዘረኝነት አባዜ ተይዘን በወንዝና በጎጥ ተከፋፍለን የመከባበር ባህላችንን ጥለን ሰይፍን ካነገብን ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ሆሳዕና አቤቱ አሁን አድን ብለን እንማጸነው፡፡
·         ሕዝባችን ከመከራውና ከችግሩ የተነሣ የተሻለ ነገርን ፍለጋ የዳቦ ቅርጫት ይዞ ከቀየውና ከባድማው ተነቅሎ ወደ ባዕድ ሀገር በአሕዛብ መንደር ሳይቀር ግዞተኛ ከሆነ ሰነበተ ‹‹አቤቱ ሕዝብህን አድን ርስትህንም ባርክ›› (መዝ 127፡9) በተሰደድንበትም ሀገር ግርማ ሞገስ ሁነን ከፊት ቅደምልን ከኋላም ተከተለን ነገራችንን ሁሉ አከናውንልን ሆሳዕና እባክህ አሁን አድን ብለን እንማጸነው
·         ሀገረ እግዚአብሔር የክርስቲያን ደሴት የተባለች ሀገራችን ኢትዮጵያውያ  የአሕዛብና የመናፍቃን መነኸሪያ ከመሆኗ ባሻገር ርኩሰት የሚፈጸምባት የግብረ ሰዶም ነውር የታየባት ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን ስላመለኩ በሥርዓት ስለተመላለሱ በአክራሪነት በአሸባሪነት የሚከሰስባት ምድር እየሆነች ነውና፡፡ አቤቱ እባክህን አሁን አድን ነውራችንንም አንከባልልን እያልን ‹‹በፊቱ ኢትዮጵያ ይሰግዳሉ›› መዝ 71፡9 ተብሎ ተጽፏልና በልባችን ጉልበት እየሰገድን እንማጸነው
·         ለዓለም ሰላም የምትሰብከውና የምትጸልየው ቤተክርስቲያንም ‹‹አቤቱ ደግ ሰው አልቋልና አድነን›› (መዝ 11፡1) እንዳለ መዝሙረኛው ይቅርባይና ታጋሽ ለመንጋው ግድ የሚለው ፍቅርን በተግባር የሚገልጽ ቅንና የዋህ አገልጋዮችን በማጣቷ በውስጥም በውጪም በፈተና ተከበን በጭንቀት ላይ ነንና ‹‹ለዝናም ደመናን የሚያደርግ አምላክ›› ለእኛም የምህረትን ዘመን ያሳየን ዘንድ አቤቱ እባክህ አሁን አድን ሆሳዕና ብለን እንማጸነው፡፡
·         እግዚአብሔርን የሚያስቀድሙ ሕዝቡን የሚያከብሩ ድሃ የማይበድሉ ፍርድ የማያጓድሉ መማለጃንና ጉቦን የማይቀበሉ የሀገር ፍቅር ያላቸው ባለስልጣናትን፣ ነውርንና ሽንገላን በከንቱም ደም ማፍሰስን የናቁ ሹማምንትን አጥተን የዕለት ተዕለት የኑሮ ውድነት ከብዶን ተጨንቀናልና እንባችንን ከዓይኖቻችን አብስልን አቤቱ እባክህ አሁን አድን ሆሳዕና ሆሳዕና ሆሳዕና…  ብለን እንማጸነው::  

No comments:

Post a Comment