Friday, April 25, 2014

የነፍስ ሕልም

 



የነፍስ ሕልም
በውስጣችሁ ሳለሁ ምናልባት ስሜን ለማታውቁት ነፍስ እባላለሁ፡፡ በዘመናት ሁሉ ስሻውና ስመኘው የነበረው ጊዜ በአምላኬ ፊት ቀርቤ በልቤ የተቀበሩ ጥያቄዎችን አንስቼ እርሱን መጠየቅ ነበር ያሳሰቡትን የማይረሳ የጠየቁትን የማይነሳ አምላክ ፈቅዶልኝ በፊቱ ቀረብሁ፡፡ ከሙሴ ጀምሮ እስከ ባለራዕዩ ወንጌላዊው ዮሐንስ ያሉት እና የእነርሱም መንገድ የተከተሉት አበው እየረዱኝ ዓለምን በያዘበት ክንዱ ተደግፌ ጌታን ፊት ለፊት ማናገር ጀመርሁ፡፡

ነፍስ፡- ጌታ ሆይ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደሆንና ጥቂት ጊዜ ቢኖርህ አንተን መጠየቅ የምፈልጋቸው ልቡናዬን የሞሉ ብዙ ጥያቄዎች አሉኝ፡፡
ጌታ፡- ልጄ ሆይ ጊዜን የፈጠርኩ የጊዜ ባለቤት መሆኔን ረሳሽ? ወይስ እኔም እንደ ምድራዊ አባት ከአንቺ ጋር ለመሆን ጊዜ ያቆመኝ ዘመን ይገድበኝ ዘንድ አሰብሽ? በእኔ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት ሺሁም እንደ አንድ ቀን መሆኑን አታውቂምን? ከጊዜ ሁሉ በላይ የሆንሁ ጊዜን የፈጠርሁ ጊዜን የምገድብ ነኝና የምትሺውን ጠይቂኝ ይሰጥሽማል፡፡ 1ጴጥ 3፡8
ነፍስ፡- ጌታ ሆይ የማስተዋል ድክመቴን ታውቀዋለህና ይቅር በለኝ፡፡ ስለ አንተ ከብዙዎች ብዙ ነገር ሲባል ሰምቻለሁ ይሁን እንጂ አሁንም እኔን ማሳረፍ ጥማቴንም ማርካት የሚቻለውን ቃልህን እናፍቃለሁ ዛሬ አንተ ስለራስህ ንገረኝ፡፡
ጌታ፡- ልጄ ሆይ ስለ እኔ ምንም ያህል አልሰማሽም ምክንያቱም ሰዎች ብዙ ጊዜ ይሳሳታሉና ነው አንዱ እንዲህ አንዱም እንዲያ ይላል፡፡ ሌላው ቀርቶ ምንም በቃላቸው ስህተት ባይኖርባትም የነቢያትና የሐዋርያት አንደበት እንኳ እኔን እንደሚገባው መግለጽ አይችሉም፡፡ ሰው በሚገባው በሰው ቋንቋና ምሳሌ ተናገሩ እንጂ ስለ እኔ ሙሉ በሙሉ ለመናገር የሚችል የለም፡፡ ምድር ሰሌዳ ባህር ቀለም ብትሆንም ስለ እኔ የጠብታን ያህል ማንም ሊናገር አይችልም፡፡ እኔን ለማወቅ ስላለሽ ጉጉትና ጥያቄሽን ለመመለስ ግን ‹‹ያለና የሚኖር እኔ ነኝ›› ዘጸ 3፡14 ፣ ራዕ 1፡8
ነፍስ፡- እነሆ በፊትህ ሞገስን ካገኘሁ ዘንድ እኔ ባሪያህ ሌላ ጥያቄ አለኝ ብዙ ጊዜ ሳስበው የሚደንቀኝ ማሰብ እስከማልችል የምደርስበት ነገር አለ፡፡ እርሱም ለምን ሰው መሆን አስፈለገህ?
ጌታ፡- ልጄ ሆይ ሰው መሆንማ ያስፈለገኝ ስለ አንድ ነገር ነው፡፡ ስለ አንቺ ስለ አንቺ ብቻ
ነፍስ ፡- አባት ሆይ እኔ ግን እኮ ሀጢዓተኛ ነኝ እንደተባለው የተፈረደብኝ ሞት እንኳ ሳይቀር የሚገባኝ ነበር፡፡ አንተ ግን በአደባባይ ስለ እኔ በጥፊ ትመታ መከራን ትቀበል እስከሞት ደርሰህ ሕማሜን ትቀበል ዘንድ ምን አተጋህ? ከእኔ የሚገኝ በጎ ነገር ሳይኖር ሁሉ ያንተ ሆኖ ሳለ ወንደቤው ተፈትቶ አንተ ትታሰር ዘንድ እኔ ነጻ ሆኜ አንተ ትያዝ ዘንድ ለምን ጌታ ሆይ ለምን?
ጌታ፡- ልጄ ሆይ በቅድሚያ ስለራስሽ ደግና እውነት ብለሻል፡፡ ቦታሽንም አውቀሻል እንደ አንቺ ቢሆን ሞት ቢያንስሽ እንጂ አይበዛብሽም በዘመኑ ሁሉ ሌሎች ፍጥረታት ቦታቸውን ሲያውቁ ትዕዛዜን ሲያከብሩ አዘንቺ ግን በብዙ ነገር ታምፂ ነበር፡፡ ነገር ግን ልጄ ሆይ አንድ ያልተረዳሽው ደግመው ደጋግመው ቢነግሩሽ ያልገባሽ ነገር አለ እርሱም ፍቅር ነው ልጄ ሆይ ማንም ከእኔ ጋር ታግሎ ማሸነፍ አይችልም ሁሉን በመዳፌ ጨብጬ ይዣለሁና፡፡ አህዛብ ሁሉ በገንቦ ውስጥ አንዳሉ ጠብታ ናቸው ይሁን እንጂ አንድ ሃይል ጠራኝ ከዙፋኔም ስቦ ለሞት አደረሰኝ እርሱም ለአንቺ ያለኝ ፍቅር ነው ልጄ ሆይ አንድ ነገር እወቂልኝ በጣም ነው የምወድሽ በእኔ ዘንድ እጅግ ተወዳጅ ነሽ ራስን አሳልፎ ለሚወዱት ከመስጠት በላይ ምንም የሚበልጥ ፍቅር የለም እንጂ ስለ አንቺ የማልሆነው አልነበረም፡፡ እናት አባትሽ ላንቺ በጣም የሚቀርቡ የሚመስሉሽ ሁሉ እንደሚወዱሽ ታስቢያለሽ? እነርሱ ቢወዱሽ ጉድለትሽን ድክመትሽን ሀጢዓትሽን እስኪያውቁ ድረስ ነው፡፡ ያውም እኔ በሰጠዋቸው ጸጋ እኔ ግን እስከ ኃጢዓትሽ ነው የተቀበልሁሽም ወደድሁሽም አባቴም ስለአንቺ መዳን እኔን አሳልፎ እስከመስጠት ደርሶ ስለ አንድያ ልጁ አልራራም፡፡ ኢሳ 1፡3 ፣ ዮሐ 15፡1 ዮሐ 4 ሮሜ 5፡6 ፣ ሮሜ 8፡32
ነፍስ፡- ባሪያህ እናር ዘንድ ከፈቀድህልኝ አሁንስ በእኔ ላይ ዓላማህ ምንድን ነው?
ጌታ፡- ልጄ ሆይ ባንቺ ላይ ያለኝ ዓላማ ለዘላለሙ ፍቅር ነው፡፡ መኃል 2፡4
ነፍስ፡- ለምንድን ነው ታዲያ እንዲህ እየወደድከኝ ሳለ መከራና ፈተና በዝቶ የሚያስጨንቀኝ?
ጌታ፡- ልጄ ሆይ መከራና ፈተና ስለብዙ ነገር ወዳንቺ ይመጣል፡፡ እኔን እንዳትረሽ ከበፊቱ ይልቅ ጸጋን አበዛልሽ በተለይ ደግሞ ብዙ ጊዜ ቀናውን መንገድ ስለምትሸሽ ይመጣል፡፡ በቃሌ ብነግርሽም በሰው አድሬ ብመክርሽም አትሰሚኝም ስለዚህ ልጄ ስለሆንሽ እንድትጠፊብኝ ስለማልሻ በጥቂቱ እንደቸርነቴ አቀጣሻለሁ፡፡ አባት ልጁን እንዲቀጣ ማለት ነው፡፡ ስጋዊ አባት ለጊዜያዊ ጥቅም ይቀጣል እኔ ግን ከክብሬ እንድትካፈይ በመጠን እገስጽሻለሁ፡፡ ‹‹ምነው አባቴ ጨምሮ በቀጣኝ የት በደረስሁ›› የሚሉ ያንቺ ወገኖችን አልሰማሽምን? እኔማ ብትመለሽ ምን ያህል ክብር እሰጥሽ ዘንድ አዘጋጅቻለሁ መሰለሽ?፡፡ ስለዚህ ልጄ ስለሆንሽ ለመቀጣት ታገሽ አባቱ የማይቀጣው ግን ልጅ አይደለም፡፡ ዕብ 12፡5
ነፍስ፡- ጌታዬ እሺ እርሱስ ይሁን ግን መልካም እያደረግሁ በጎ እየሰራሁም ሳይቀር ብር ሲገባኝ ብዙ ጊዜ መከራ ደርሶብኛል ይህስ ለምን ይሆናል?
ጌታ፡- ልጄ ሆይ በመጀመሪያ ይህን አወቂ አንቺ ስለ ክብርሽ እደሜ ልክሽን የሚደርስብሽ ፈተናና መከራ እኔ አንዲት ሰዓት ስለ አንቺ የተቀበልኩትን ስቃይ እንኳ አያህልም፡፡ ልጄ ሆይ በሚመጣው ዓለም ካዘጋጀሁልሽ ክብርና ደስታ ጋር ሲተያይ የዚህ ዓለም መከራሽ ምንም ማት አይደለም፡፡ ደግሞ ኃጢዓት አድርገሽ ስትጎሰሚ መከራ ቢደርስብሽና ብትታገሽ ምን ክብር አለው? በጎ አድርገሽ መከራን ብትታገሽ ግን ከእኔ ዘንድ ክብር አለሽ፡፡ እሳት ባይኖር ወርቅና መዳቡ እንዴት ይለያሉ? እንዲሁ ለእኔ ያለሽ ታማኝነትና ፍቅር በመከራ ውስጥ ታምነሽ ካልገለጽሽው እንዴት ትገልጪዋለሽ? ወርቅን እሳት አያሳስበውም ምክንያቱም በእሳት ውስጥ ሲያልፍ ነው ወርቅነቱ የሚታወቅለትና የሚመሰከርለት፡፡ እንዲሁ መከራ በጎ የሚያደርጉትን ሊያሳስባቸው አይገባም በመከራ በመታገሳቸው ጽድቃቸው ትወጣለች በጎነታቸውም በሁሉ ይታወቃል ይልቅስ መከራን ይሹታል ጸጋዬ ይበዛላቸው ዘንድ፡፡ በእነርሱም ድካም የእኔ ሃይል ይገለጥ ዘንድ ስለዚህ በሁሉ ታጋሽ ሁኚ እንጂ ቶሎ አትሰልቺ አትታክቺም፡፡ የውጪው ሰውነትሽ ቢጠፋም ውስጥሽ ዕለት ዕለት ይታደሳልና ምን ጊዜም ግን ክብር ይገባኛል ብለሽ አታስቢ፡፡
ፍቅሬንም ደግሞ በሚያልፍ መከራና ፈተና አትመዝኚው፡፡ እኔ ለንቺ ያለኝን ፍቅር የሚለውጠው ምንም ነገር የለምና፡፡ 1ጴጥ 4፡12 ፣ ሮሜ 8፡18 ፣ ዕብ 12፡10
ነፍስ፡- ይህ መከራና ፈተና ሀዘኑስ እስከ መቼ ነው?
ጌታ፡- ልጄ ሆይ በዓለም እስካለሽ መከራ አለብሽ ግን አትፍሪ እኔ ዓለምን አሸንፈዋለሁና ዓለምን የሚያሸንፈው በእኔ ላይ ያለ እምነትሽ ነው፡፡ በእኔ በአባቴ በመንፈሴም እመኚ ከእጄ ማንም አይነጥቅሽም ወደ እኔ የመጣውን በፍጹም ወደ ውጪ አልጥልምና፡፡ ዮሐ 16፡33 ፣ ዮሐ 5፡4 ፣ ዮሐ10፡29
ነፍስ፡- እንዲህ ከሆነ ጌታ ሆይ ለእንደ እኔ አይነቱ ኃጢዓተኛስ ምን ተስፋ አለ?
ጌታ፡- ስለ በደልሽ ታልፌ በመሰጠሬ ደሜን በማፍሰሴ ያቆምኩልሽ ንስሐ አለ፡፡ ንስሐ ፍጹም ወደ እኔ መመለስ ነው ትወጅው የነበረውን ኃጢዓት በእ ፍቅር መለወጥ ነው ሰው ለሁለት ጌቶች ሊገዛ አይቻለውም፡፡ አንዱን ይተዋል ሌላውንም ይከተላል አንቺም እንዲሁ ለእኔና ለዓለም መገዛት አትችይም ወይ የኔ አልያም የዓለም ነሽ፡፡ ብዙ ጊዜ የምትወድቂው ለእኔ ያለሽ ፍቅር ሲቀንስ ሰውን ከእኔ አብልጠሸ ስትወጂ ነው፡፡ ግን ብትወድቂም በንስሐ ከእኔ ጋር ትታረቂያለሽ እኔም ስለስሜ ስል በደልሽን እፍቃለሁ፡፡ ልጄ ሆይ መቼም በዓለም ውስጥ ብዙ አሳቾች አሉ ያንቺም ስጋ ምድራዊውን ወዳጅ ስለሆነ ወደ ኃጢዓት ያመዝናል፡፡ በሌላ በኩል ጠላትሽ ዲያብሎስም አይተኛልሽም ስለዚህ ምናልባት ደግመሽ ኃጢዓት ብትሰሪ እንኳ የንስሐን መንገድ ሰርቼልሻለሁ፡፡ እርሷም ዘማዊውን ድንግል ሌባውን መጽዋች አሳዳጁን ተሳዳጅ ታደርጋለች ስለዚህ ብትወድቂ እንኳ ተስፋ ባለመቁረጥ በንስሐ ተመለሽ፡፡ እኔም ያለፈውን ኃጢዓትሽን ከቶ አላስብም ጻድቅ ሰባት ጊዜ ይወድቃል ምሶ ግን ይነሳል እንጂ ተስፋ ቆርጦ አይቀርም፡፡ ወድቆ መቅረት ዲያብሎሳዊ ነው ወድቆ መነሳት ግን አዳማዊ ነው፡፡ ንስሐን ያዘጋጀሁት ኃጢዓትን ለማይሰሩ ለማይበድሉም አይደለም መድኃኒት ለጤነኞች አያስፈልጋቸውም ለበሽተኞች እንጂ እንዲሁ ንስሐ በኃጢዓት ለወደቁት ነው እኔም እንኳ ወደ ዓለም የመጣሁት የጠፋውን ላድንና ልፈልግ ነው፡፡ ንስሐ መግባት በማያስፈልጋቸው በመላእክቶቼ ፊት በአንድ ኃጥዕ መመለስ ምክንያት ታላቅ ደስታ ይደረጋል፡፡ ያለፈው ዘመንሽ ምንም ቢሆን አላስበውም የመጨረሻሽን እንጂ የመጀመሪያውን ስራሽን አላይምና፡፡ ብቻ በመንፈስ ጀምረሽ በስጋ እንዳትፈጽሚ ተግተሽ ጸልይ፡፡ ሌላ ሸክም አልጭንብሽም እስክመጣ ግን ያለሽን አጽንተሽ ያዥ፡፡ ማቴ 6፡24 ፣ ሕዝ 33 ፣ ማቴ 9፡12 ፣ ራዕ 2
ነፍስ፡- ግን ብዙ ጊዜ እሰነካከላለሁ ስራዬን ብናዘዝም መልሼ ያንኑ ኃጢዓት እሰራለሁ ምን ላድርግ?
ጌታ፡- መልሰሽ ንስሐ ግቢ ደግመሽም ኃጢዓትን አትስሪ፡፡ ዮሐ 8፡11
ነፍስ፡- እስከመቼ እንደዚህ እኖራለሁ?
ጌታ፡- ከዚህ ከመከራና ከፈተናው ዓለም እስክትለይ ድረስ፡፡
ነፍስ፡- ጌታ ሆይ (በውስጣችሁ ያለሁ የእኔ የነፍስ ጥያቄስ የሚያልቀው መች ይሆን) 
‹‹በጠራሁህ ቀን ቀርበህ አትፍራ አልህ ጌታ ሆይ ስለ ነፍሴ ተሟግተህ ሕይወቴን ተቤዥህ›› ሰቆ. ኤር 3፡57
ከምንለምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ ይልቅ እጅግ አብልጦ ሊያደርግ ለሚቻለው ለእርሱ ቸር ከሚሆን አባቱ ሕይወትን ከሚሰጥ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ለዘላለሙ ክብር ይሁን፡፡ አሜን!!!




No comments:

Post a Comment