ጌታችን መድኀኒታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ ከተሰቀለ በኋላ በመስቀል ላይ ሆኖ የተናገራቸው 7ቱ አጻርሐ መስቀል በመባል የሚታወቁት የአሸናፊነት የድል ጩኸቶች
ናቸው፡፡
1. ‹‹ኤሎኼ ኤሎኼ ኤልማስ ላማ ሰብቅታኒ››
አምላኬ አምላኬ
ለምን ተውኸኝ ማለት ነው (ማቴ 27፡46) ይህን አሰምቶ የተናገረው በ9 ሰዓት ነው እርሱ አምላክ ሆኖ ሳለ አምላኬ አምላኬ ለምን
ተውከኝ ብሎ የተናገረው ለምንድን ነው፣ ቢሉ ከሕገ-እግዚአብሔር ርቆ ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን የተተወ አዳምን ሥጋ ተዋሕዶ
ፍጹም ሰው መሆኑን ለመግለጥ ነው፡፡
·
አንድም ተላልፎ ስለተሰጠለት ስለ አዳምና ስለልጆቹ ተገብቶ የተናገረው ቃል እንጂ እርሱ እውነተኛ
አምላክ ነው፡፡ ክርስቶስ በብዙ ሥፍራ በመጽሐፍ ቅዱስ ሁለተኛው አዳም እየተባለ ተጠርቷልና፡፡
1ኛ ቆሮ
15፡45-47 ‹‹ፊተኛው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ ተብሎ ተጽፎል ኋለኛው አዳም ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ›› ተብሎ ስለተጻፈ
እንጂ ኢየሱስ ክርስቶስማ ‹‹ከሰማይ የሚመጣው እርሱ ከሁሉ የሚበልጥ ነው›› ተብሎለታል (ዮሐ 3፡31)
ስለዚህም ስለ
አዳም ተገብቶ የአዳምን መከራ ተቀበለ የአዳምን ጩኸት ጮኸ፣ ሕመም የሚሰማማውን ሥጋ እንደለበሰ ለማመልከት ታመመ፣ የባሪያውን መልክ
ይዞ በትህትና ሰው ሆኖ ተገልጧልና ራሱን አዋረደ እስከ መስቀል ሞትም እንኳ ሳይቀር ታዘዘ (ፊልጵ 2፡7)
ይህ የለበሰው
ስጋ ይራባል፣ ይጠማል፣ ይታመማልና ጌታም በለበሰው ሥጋ የተቸነከረው ችንኳር ያሰቃያል፣ ያቆስላል ያማልና አምላኬ አምላኬ ብሎ አባቱን
ተጣራ (ኢሳ 53)
·
‹‹በመዝ 21፡1›› ላይ የተጻፈው የትንቢት ቃል ይፈጸም ዘንድ፣ በዙሪያው ተሰብስበው ለነበሩት
አይሁድ ይህ ለእኔ ተጽፏልና ሂዱና ሕግና ነቢያትን አንብቡ ሲል ነበረ አይሁድ የነቢያትንና የሙሴን መጻሕፍት ያውቁ ስለነበር ይህ
የተነገረ ስለ እርሱ እንደሆነ እንዲያምኑ ነበር፡፡
·
በሌላው ለአቅርቦተ ሰይጣን ነው ይህንን ቃል የተናገረ ምክንያቱም ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ የሰው
ልጆችን ሁሉ እየተቆራኘ ሥጋን በመቃብር ያስቀር ነበር፣ ነፍስንም በሲኦል ያወርድ ነበረ፣ በመሆኑም ለ5500 ዘመን ንጉሥ ዲያብሎስ
ነበረ፡፡ ከዚህም የተነሣ አምላካችን ሰውን ሥጋ ለብሶ ቢመለከተው ደካማ ሰው መስሎት ሥጋውን ከነፍሱ ሊለይ ሲጠጋ በነፋስ አውታር
በእሳት ዝንዥር (ሰንሰለት) አስሮ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል በመውረድ ሳላምን አወጀ የታሰሩትን ነጻ አውጥቷል፡፡
2. ‹‹አባ ሥረይ ሎሙ እስመ በዘኢየአምሩ ይገብሩ›› አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር
በላቸው (ሉቃ 23፡34)
ይህንንም ማለቱ
ከስቅላቱ ሳያውቁ የተሳተፉ አሉና እነሱን እያወቁ ከሰቀሉት ለመለየት ነው
3. ‹‹ዮም ትሄሉ ምስሌየ ውስተ ገነት››
ዛሬ በገነት
ከእኔ ጋር እንድትኖር በእውነት እነግርሃለሁ (ሉቃ 23፡43) የተሰቀለውና የሞተው በአምላክነቱ አምነው ለሚማጸኑት ሁሉ ቀድሞ ያጧትን
ርስት ለመስጠት መሆኑን ሲገልጥ ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትኖራለህ አለ፡፡
4. ‹‹ነዋ ወልድኪ ወነዋ እምከ››
‹‹እነሆ ልጅሽ
አነኋት እናትህ›› (ዮሐ 19፡26-27) ጌታ ይህን ቃል የተናገረው የሚወዳትን እናቱን እመቤታችንንና የሚወደውን ሐዋርያ ፍቁረ-እግዚአ
በመባል የሚታወቀውን ዮሐንስን ከእግረ መስቀሉ ሥር ቆመው ባየ ጊዜ ‹‹አንቺ ሴት እነሆ ልጅሽ እነኋት እናትህ›› በማለት
·
በድንግልና ለኖረው በድንግልና የኖረችውን አደራ ሰጠ
·
በደረቱ ተጠግቶ ምስጢርን ለሰማው ለተወያየው በደረቷ ያቀፈችውን የምስጢር እናቱን አደራ ሰጠ
·
መለኮትን በማህፀኗ ለተሸከመችው የመለኮትን ነገር አምልቶና አስፍቶ ለጻፈው አደራ ሰጠ
አምላካችን እግዚአብሔር
ለእመቤታችን ያለውን ፍቅሩን የገለጸው የሚወደውን ደቀመዝሙር በመስጠት ነው፡፡ ስጦታ የፍቅር መግለጫ ስለሆነ የእናት ልመና ፊት
አያስመልስ አንገት አያስቀልስምና ሲሆን በውድ ካልሆነም በግድ እናትነቷን እንቀበላለን፡፡
ልጅሽ ማለቱ
በዮሐንስ እኛን ለእርሷ መስጠቱ ነውና ልጆችሽ ማለቱ ነው፣ እነኋት እናትህ ማለቱም በዮሐንስ ለእኛ እሷን መስጠቱ ነውና እናታችሁ
እነኋት ሲል ነው፤
ዮሐንስም ወደ
ቤቱ ይዟት ገባ እኛም ከእግረ መስቀሉ ደርሰን፣ የአምላክ ስጦታ የሆነች እናታችንን ወደ ቤታችን ይዘን መግባት እንደሚገባን ያስተምረናል፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ
ከሌሎች ደቀመዛሙርት ሁሉ የመለኮቱን ነገር አምልቶና አስፍቶ የጻፈው የምስጢር መዝገብ የሆነችው እመቤታችን ከእርሱ ጋር አስራ አምስት
ዓመት ተቀምጣ ነበርና፡፡ ከእመቤታችን በረከትን ተባርኮ ምስጢር ተገልጾለት ነው፡፡ በ2ኛሳሙ 6፡11 ታቦተ ጽዮን ወደ አቢዳራ ቤት
በገባች ጊዜ ቤቱ ተባርኮላታል እመቤታችን የቤታችን በረከት ናትና ወደ ቤታችን ይዘናት እንግባ፡፡
5. ‹‹ከመ ይብጻሕ ቃለ መጽሐፍ ይቤ ጻማዕኩ›› ተጠማሁ (ዮሐ 19፡28)
ሀ/ በመጽሐፍ
በመብሌ ውስጥ ሐሞት ጨመሩ ያለው ይፈጸም ዘንድ ተጠማሁ አለ
ለ/ አንድም
አምላክ ጥማትና ረሃብ የሚስማማውን የድንግል ማርያምን አዳምን የአዳምን ሥጋ ስለለበሰ በለበሰው ሥጋ ተጠማሁ አለ እንጂ በመለኮታዊ
ባሕርይው መራብ መጠማት የለበትም፡፡
ሐ/ የእኛን
የጽድቅ ጥማት ያረካ ዘንድ ተጠማሁ አለ ጽድቅ ልምላሜ ጠፍቶብን እንደ ቅጠል ደርቀን ረግፈን ነበርና (ኢሳ 64 በመዝ 21፡15
ላይ አዳምን ተገብቶ (ሰውን ልጆችን ተገብቶ) ‹‹ኃይሌ እንደ ገል ደረቀ በጉሮሮዮም ምላሴ ተጣጋ›› እንዲል
መ/ አንድም
ተጠምቶ የነበረው የእኛን መዳን ነው፡፡ በኃጢዓት ተጠምቶ የነበረውን የእኛን ሕይወት በፈውስ በምህረት ያረካ ዘንድ ተጠማሁ አለ
‹‹አይሁድ ግን
ሐሞትና ከርቤ ሰጡት እሱ ግን መራራ ስለነበረ ተፋው›› እኛም ዛሬ ልክ እንደ መራራው ሐሞት እንደተፋ መስዋዕታችን የተወደደ፣ ሕይወታችን
በቅድስና የከበረ ነውር ነቀፋ የሌለበት፣ መስዋዕታችንም እንደ ቃየል የተናቀ እንዳይሆን በጽድቅ ማደግ ይኖርብናል፡፡
‹‹ራዕ 3፡16
እንዲሁ ለብ ስላልህ በራድ ወይም ትኩስ ስላልሆንህ ከአፌ ልተፋህ ነው››
6. ‹‹አባ አመሐፅን ነፍስየ ውስተ እዴከ›› አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ (ሉቃ
23፡46)
ሀ/ መድኀኔዓለም
ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ቃል መናገሩ ለአምላኩ ራሱን አደራ የሚሰጥ ሥጋንና ነፍስን መዋሐዱን ለማጠየቅ እንጂ እሱስ ዓለምና በውስጧ
ያለው ሁሉ በእጁ የተያዘች አምላከ አማልክት ነው፡፡ (መክ 12፡7)
ለ/ አንድም
ነፍሳትን ከሲኦል ያወጣልና፣ ይማርካልና
‹‹በአካለ ነፍስ
ወደ ሲኦል ወርዶ ሲኦልን በዘበዘ ምርኮን ተካፈለ ሰላምን ለታሰሩት ሰበከ›› (1ጴጥ 3፡19)
ሐ/ሌላው ሞትን
ድል አድርጎ እንደሚነሳ ሲያጠይቅ ነው ‹‹ዮሐ 10፡17-18 ነፍሴን ደግሞ አነሳት ዘንድ እኖራለሁና ስለዚህ አብ ይወደኛል እኔ
በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም ላኖራት ስልጣን አለኝ ደግሞም ላነሳት ስልጣን አለኝ ይህችን ትዕዛዝ ከአባቴ
ተቀበልሁ››
ይህች ነፍስ
ዲያብሎስና ሠራዊቱን ድል ያደረገች ነፍስ እንዲሁም ነፍሳትን ከሲኦል እስራት ከዲያብሎስ አገዛዝ ከወኅኒ ነፃ ያወጣች ናት፡፡ ስለዚህ
ይህ ቃል የአሸናፊነት የድል ቃል ኃያል ቃል ነው፡፡
መ/ በሌላው
በመጽሐፍ ‹‹ስለዚህ ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መከራን የሚቀበሉ መልካምንም እያደረጉ ነፍሳቸውን ለታመነ ፈጣሪ አደራ ይስጡ››
(1ጴጥ 4፡19) ተብሎ ቀዳሚ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስም ‹‹ጌታ ኢየሱስ ሆይ ነፍሴን ተቀበል›› (ሐዋ 7፡59) እንዳለ እናንተም
መልካሙን ገድል ስትጋደሉ ነፍሳችሁን ለታመነው ፈጣሪ አደራ ስጡ ሲለን ነው፡፡
7. ‹‹ወይቤ ተፈጸመ ኩሉ››
የተጻፈው ሁሉ
ደረሰ ተፈጸመ አለ (ዮሐ 19፡30) ይህም ማለቱ ትንቢተ ነቢያት መድረሱንና በመጽሐፍ ስለ እኔ የተነገረው ሁሉ ተፈጸመ (ዘዳ
18፡18 ፣ ዘፍ 49፡10 ፣ ኤር 23፡5 ወዘተ)
አዳምና ልጆቹ
ከገነት ተባረው በመቃብር ተወስነው መኖራቸው አበቃ፣ ርስታቸው ገነትን እንዲወርሱ የሚያደርገው የማዳን ሥራ ተፈጸመ ሲል ነው፡፡
ደህንነታች የተረጋገጠው በሞቱ ነውና የጥል ግርግዳ ይፈርስ ዘንድ ተፈጸመ ከእግዲህ ወዲህ አለምንም አላማልድም አልጾምም አልጸልይም፡፡
(ዮሐ 16፡25-28)
እርሱ ጌታችን
ክርስቶስ ራሱን ቤዛ አድርጎ ዋጋ ከፍሎ ራሱ መስዋዕት አቅራቢ፣ ራሱ መስዋዕት፣ ራሱ መስዋዕት ተቀባይ ሆኖ ከራሱ ጋር አስታርቆናል፣
ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋርም አስታርቆናል፣ ለራሱም ማርኮናል ስለዚህም በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች
እንበልጣለን፡፡ (2ቆሮ 5፡18-21)
No comments:
Post a Comment