Friday, April 25, 2014

ክርስቲያን በመሆንህ ታፍራለህ?



 


ክርስቲያን በመሆንህ በሌሎች ፊት ያፈርህበት ጊዜ ነበር? ምንአልባት ከማያምኑ ጋር ምግብ ልትበላ ቀርበህ ሳለ በእነርሱ ፊት መጸለይ አሳፍሮህ ያውቃል? ወይም ማማተብ እየፈለግህ ሌሎች ስለሚያዩህ እምነት በልብ ነው ብለህ በህሊናዬ አማትቤያለሁ ያልክበት ጊዜ ይኖር ይሆን? ብቻ በአንድም መንገድ ይሁን በሌላ ከማያምኑ ጋር ስትሆን ወይም ለብቻህ ሳለህ የምታደርገውን መንፈሳዊ ነገር ሌሎች ሰዎች የሚሉህን በመፍራትና በማፈር ሳታደርገው ቀርተህ አታውቅ ይሆን? ብዙዎቻችን አምነንበታል ስለምንለው ነገር እኛ ሄደን እነሱ ዘንድ ልንመሰክር ቀርቶ ገና ለገና ያዩናል በማለት ሁል ጊዜ የምናደርገውን መንፈሳዊ ነገር ስንቀንስ ይታያል ይህ ግን ግብዝነት አይደለም ትላለህ?



ብዙ ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት ሞኝነት የሆነውን የዚህን ዓለም ሃላፊ ጥበብ ለመመስከር ብዙ ድንጋይ ሲፈነቅሉ እኛ ግን ዓለም ሞኝነት ብላ የምታስበውን የእግዚአብሔርን ጥበብ ለመመስከር ስንተጋ አንታይም፡፡ እነሱ ነውሩን እንደ ክብር ያለ ሀፍረት ሲያወሩና ሲያደርጉ መልካምና በጎ በሆነው ማፈር ምን ይባላል? ቤተክርስቲያን ስንመጣ በነገሮች ላይ የምሰጠው አስተያየት ወደ ዓለም ስንሄድ የሚቀየር ከሆነ እንደ ሁኔታው የምንቀያየር ክርስቲያኖች መሆናችን አይደለምን? ምንአልባት አንተም እንደዚህ ያለ ጸባይ እንዳለብህ እስቲ ራስህን መርምር፡፡ ጌታም ቢሆን ያስቀመጠውን አትርሳ ‹‹በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ ፣ በሰው ፊትም የሚክደኝን ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት…›› ማቴ 10፡33 እንግዲህ ዕለት ዕለት በምንሰራው መንፈሳዊ ምግባር ስለ አምላካችን ስለ ቀናች እምነታችን መመስከር ካልቻልንና ካፈርን እንዴት ነው ለእኛስ ሊመሰክርልን የሚቻለው? ስላመንበት ነገር ምንጊዜም ከመመስከር አንመለስ፡፡ በእምነት ቆመን ሁል ጊዜም እንደ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ እንበል ሁል ጊዜዘም በቃል በስራ የተሰቀለውን ክርስቶስን እሰብካለሁ ‹‹በወንጌል አላፍርምና›› ሮሜ 1፡16  ብርታቱን ይስጠን፡፡
ከምንለምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ ይልቅ እጅግ አብልጦ ሊያደርግ ለሚቻለው ለእርሱ ቸር ከሚሆን አባቱ ሕይወትን ከሚሰጥ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ለዘላለሙ ክብር ይሁን፡፡ አሜን!!!

No comments:

Post a Comment