ሰማዕታት የዚችን ዓለም ጣዕም በእውነት ናቁ
ሦሪያዊው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሊቅ ቅዱስ ኤፍሬም
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ባወደሰበት በዕለተ ሐሙስ ምስጋናው አማን መነኑ ሰማዕት ጣዕማ ለዛ ዓለም መከዐው ደሞሙ በእንተ
እግዚአብሔር ወተአገሱ ሞተ መሪረ በእንተ መንግስተ ሰማያት፤ ሰማዕታት የዚችን ዓለም ጣዕም በእውነት ናቁ ስለ እግዚአብሔርም ደማቸውን
አፈሰሱ ስለ መንግስተ ሰማያትም መራራ ሞትን ታገሱ በማለት ክብራቸውን ተጋድሏቸውን መዝግቦልናል፡፡
ሰማዕታት ማለት ምስክሮች ማለት ሲሆን ምስክርነታቸውም
ለታመነው ጌታ ለእግዚአብሔር ለጌታችንም ለመድኀኒታችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ነው በቤተክርስቲያን ታሪክ መሠረት ከ2ኛው እስከ አራተኛው
መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ያለው ጊዜ ዘመነ ሰማዕታት እየተባለ ይጠራል፡፡ ይኸውም የሆነበት ቅዱሳን ሐዋርያት ጸጋ መንፈስ ቅዱስን
ከተቀበሉ በኋላ ወንጌልን በዓለም ዞረው ሲያስተምሩ ብዙዎችን ከአምልኮተ ጣኦት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር ከገቢረ ኀጢዓት ወደ ገቢረ
ጽድቅ በመመለሳቸው የክርስቲያኖች ቁጥር ዕለት ዕለት እየጨመረ መጣ፡፡
በዚያን መጠን ዓላውያን ነገስታት የዲያብሎስ የግብር
ልጆች ጣዖት አማኞችን ስለተማረኩ በክርስቲያኖች ላይ ፈተና ያጸኑባቸው ጀመር፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትን ጨምሮ ጻድቃን ሰማዕታት በኢየሱስ
ክርስቶስ ያመኑ ወዳጆቹ አምላካቸውን ክርስቶስን ተስፋ በማድረግ ጣዖት በሚያመልኩ ነገሥታ ፊት በመቆም በጽናት በመመስከር ደማቸውን
አፍሰዋል አጥንታቸውን ከስክሰዋል ነፍሳቸውንም ለታመኑለት አምላክ ሰጥተዋል፤ ግማሾቹም በዱር በገደል፤ በግበበምድር፣ በካታኮምብ
ተንከራተዋል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ‹‹እነርሱ በእምነት መንግስታትን ድል ነሱ›› ዕብ 11፡33 በማለት ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ
አድርገው ጣዖት የሚያመልኩ ነገሥታትን ድል ከማድረጋቸውም ባሻገር ‹‹ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል
ሌጦ ለብሰው ዞሩ ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፣ በዋሻና በምድር ጉርጓድ ተቅበዘበዙ›› ዕብ 11፡38 ሲል የታመኑትን
ምስክሮች በማድነቅ ጽፎልናል፡፡
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሕያዋን
እንጂ የሙታን አምላክ አይደለምና (ሉቃ 20፡39) ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፡፡ (ዮሐ
11፡25) ብሎ ስለተናገረ ሰማዕታት በሥጋ ቢሞቱም በነፍሳቸው ሕያዋን መሆናቸውን ያውቃሉና እስከሞት ድረስ በጽናት ተጋደሉ፡፡ በሥጋ
ሞተው በነፍስ ግን ሕያዋን ከሆኑ ቅዱሳን አንዱ የሰማዕታት አለቃ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው፡፡
ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የትውፊትና
የታሪክ ማህደር በመሆኗ የቅዱሳን ጻድቃንና ሰማዕታትን ገድላቸውን ከመልክአቸው ጋር አስተባብራ በመያዝ ወርኃዊና ዓመታዊ መታሰቢያ
በዓላቸውን ታከብራለች ‹‹ይህንንም የምታደርገው ‹‹የጻድቅ መታሰቢያ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል›› መዝ 111፡6 ‹‹ዘወትር በቤቴና
በቅጥሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ መታሰቢያና ስም፣ የማይጠፋም የዘላለም ስም እሰጣቸዋለሁ›› (ኢሳ 56፡6)
ተብሎ ከተጻፈው መጻሓፋዊ እውነታ ተነስታ ነው፡፡ በመሆኑም በየዓመቱ ሚያዝያ 23 ቀን የምናከብረው የፋርሱ ፀሐይ የቤሩቱ ኮከብ
የልዳው ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ በንጉሥ ዱድያኖስ ትዕዛዝ አንገቱን በሰይፍ የተቆረጠበትና በሰማዕትነት የሞተበት ስለሆነ ነው፡፡
ጊዮርጊስ ማለት የሐይማኖት ገበሬ ማለት ሲሆን
አባቱ የቆዕደቅያ ተወላጅ የሆነ ቅዱስ አንስጣስየስ፣ እናቱ የልዳ ተወላጅ የሆነች ቅድስት ቴዎብስትያ ትባላለች ሁለቱም እግዚአብሔርን
የሚወዱ ክርስቲያኖች ነበሩ፡፡ በዘመኑ ጋላስና ጋሪሳ አንዱ በሮም ሌላው በአንጾኪያ ነግሰው ሲኖሩ የቅዱስ ጊዮርጊስ አባት በሮሙ
ንጉስ በጋላስ ትዕዛዝ በቂሣርያ ሀገር ላይ መስፍን ሆኖ ተሾመ ሁለቱ የሮም ነገስታት ጋላስና ጋሪስ ጣዖትን ያመልኩ ስለነበረ በቤተክርስቲያን
ላይ ስደት ተጀመረ፡፡ በዘመኑ የፋርሱ ንጉሥ ዱድያኖስ ገናና ስለነበር የሮምን ነገሥታት ተዋግቶ ድል አደረጋቸው፣ በጦርነት መስፍኑ
የቅዱስ ጊዮርጊስም አባት ቅዱስ አንስጣስዮስ አረፉ፡፡
በቅዱስ አንስጣስዮስ ፈንታ ሌላ መስፍንና አገረ
ገዥ ተሾመ እርሱም እግዚአብሔርን የሚፈራ ክርስቲያኖችን የሚወዱ ነበር በወቅቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ የአስር ዓመት ልጅ ነበረ፡፡ አገረ
ገዥው ቅዱስ ጊዮርጊስን ባየው ጊዜ ወደደው የሠራዊት አለቃም ይሆን ዘንድ የወታደርነት አለቅነት እንዲሰጠው የወገኖቹን ማዕረግ ጽፎ
ወደ ንጉሱ ላከው ንጉሡም መልዕክቱን በአነበበ ጊዜ ደስ አለው የመቶ አለቅነት መዓረግ ሹም ርስት ጉልት ግብርና ገፀበረከት ሰጥቶ
በሚገባ ክብር ወደ ሀገሩ መልሰው አገረ ገዥውና የሀገሩ ሰዎችም የክብር አቀባበል አደረጉለት፡፡ መስፍኑም ልጁን ሚስት ትሆነው ዘንድ
አጨለት የሀብቱም ወራሽ መሆኑን በጽሑፍ አረጋገጠለት፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ የሃያ ዓመት ወጣት በሆነ ጊዜ
የቅዱሳት መጻሕፍትን ትምህርት፣ ፈረስ ግልቢያ፣ ቀስት ማስረር፣ አደን ማደን ተማረ በሥራውም ሁሉ ብርቱ ጀግና ወታደር ሆነ፡፡ አገረ
ገዥው ቅዱስ ጊዮርጊስን ከልጁ ጋር ሊያጋባው በዝግጅት ላይ እንዳለ ፈቃደ እግዚአብሔር ባለመሆኑ ያሰበውን ሳያሳካ መስፍኑ አረፈ፡፡
ከዚህ በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤሩት ወደ ምትባል
ሀገር ሄደ የቤሩት ሀገር ሰዎች ግን ጣዖት አምላኪዎች ነበሩ፡፡ እንደ አምላካቸው አድርገው የሚያመልኩት ‹‹ደራጎን›› የሚባል ሰይጣን
ያደረበት ዘንዶ ነበር፣ ለዚህም ክፉ አውሬ የቤሩት ሀገር ነዋሪዎች ሁሉ ሴቶች ልጆቻቸውን በየተራ ይገብሩለት ነበር ይህ አስፈሪ
እንሰሳ እንደ ንስር በክንፍ ይበራል እንደ ፈረስ በእግሩ ይሰግራል፣ እንደ ዘንዶ በጅራቱ ይወናጨፋል፡፡
+ በሊባኖስ ቤይሩት የሚገኘው ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤይሩታዊትን ያዳነበት ቦታ+
ከብዙ ዘመን በኋላ የሀገሩ ሴቶች ልጆች ሁሉ ወደ
ማለቁ ተዳረሱ በዚህን ጊዜ ነዋሪዎቹ ወደ መስፍኑ ሄደው ልጆቻችን መገበር ሰለቸን ሀገር ለቀን ልንሰደድ ነው ባሉት ጊዜ እኔን ትታችሁ
ሀገራችሁን ምድረ በዳ አድርጋችሁ ከምትሄዱ ልጄን ቤሩታይትን ለመስዋዕት በፈቃዴ እሰጣለሁ አላቸው፡፡ የገዥውን ልጅ ወስደው በጫካ
ተዋት ደራጎኑን ግን አላገኙትም ከአራዊት ወገን የሚበላውን ለማደን ወደ ዱር ሄዶ ነበር፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ አደን ለማደን በጫካዎቹ ሁሉ ሲዘዋወር
የመስፍኑን ልጅ ብቻዋን ተቀምጣ አገኛት ምን እንደምትጠብቅ ቢጠይቃት ለአምላካቸው ለደራጎን መስዋዕት ትሆን ዘንድ እንደተሰጠች ለቅዱስ
ጊዮርጊስ በመጨነቅ አንተንም እንዳይበላህ ከዚህ ሂድ አለችው ቅዱሱም ሰይጣን ያደረበትን ይህንን ከይሲ አልፈራውም ቢላት አንተ ጽሕም
እንኳን ያለወጣህ ሕፃን ነህ ከአምላካችን አፍ ከደራጎን ልጆቻቸውን ማዳን ከተሳናቸው ከቤሩት ሰዎች አንተ ትበልጣለህን ብትለው ቅዱስ
ጊዮርጊስ ከአማልክት ሁሉ የሚበልጠው ምድርን የፈጠረ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ከዚህ ከተረገመ አውሬ ያድነኛል አይዞሽ አትፍሪ አላት
‹‹ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል ያመኑትንም እነዚህ ምልክቶች ይከተሉአቸዋል እባቦችን (ዘንዶዎችን) ይይዛሉ››
(ማር 16፡18) ብሏልና፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከቤሩታይት ጋር ሲነጋገር ሳለ ደራጎኑ በእግሩ እየሰረገ መጣ ቅዱስ ጊዮርጊስን ባየው
ጊዜም አንገቱን መዘዘ ምላሱንም አውለበለበ በራሱም ላይ ሊወረወር ትንፋሹንም ሊተነፍስበት ወደደ ቅዱሱ ግን ከዘንዶው ቁጣ የተነሣ
አልደነገጠም በሥላሴ ሥም በመስቀል ምልክት ቢያማትብበት ኃይሉ ደከመ መርዙ ጠፋ ‹‹ሐዋርያው ጳውሎስ የአንበሶችን አፍ በእምነት
ዘጉ እባቡንና ጊንጡን ተረጋገጡ›› (ዕብ 11፡34) እንዲል በእምነት ደራጎኑንና በእሱ ላይ ያደረውን ሰይጣን ድል አደረገው ቤሩታይትም
የደራጎኑን አንገቱን አስረሽ ጎትችው ብሎ ዝናሩን ፈትቶ ሰጣት ልጅቷም ዘንዶውን እየጎተተች ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ወደ ከተማ ገቡ
ሕዝቡም ደራጎኑ ሲመጣ ባዩ ጊዜ ልጆቻችን ጨርሷል እሱ አምላካችን ነው ለምን ይዘኸው መጣህ አሉት፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ
አምላክ የለም አሁንም ራሱን ማዳን የማይቻለውን ይህንን ሰይጣን ዘንዶ ተውና በእግዚአብሔር እመኑ አላቸው፣ ሕዝቡም በፈጣሪህ እናምን
ዘንድ ዘንዶውን ልትገድለው ትችላለህን ባሉት ጊዜ በጌታዬ በኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል እችላለሁ በማለት በተሰበሰቡበት ዘንዶውን በጦር
ወግቶ ገደለው፡፡
‹‹ጻድቃን ድል በአደረጉ ጊዜ ብዙ ክብር አለ››
(ምሳ 28፡12) ተብሎ እንደተጻፈ ቅዱስ ጊዮርጊስ በእግዚአብሔር ስም ዲያብሎስና ሠራዊቱን፣ ደራጎኑን ድል በማድረጉ ብዙ ምርኮን
ለኢየሱስ ክርስቶስ ማረከ የቤሩት ሀገር ሰዎች ሁሉ በእግዚአብሔር አምነው ተጠመቁ፡፡
ከጥቂት ወራት በኋላ ስሙ ዱድያኖስ የተባለ የፋርስ
ንጉሥ በብዙ ገናንነትና ክብር ተነስቶ የዓለምን ነገስታት ሁሉ ለራሱ አስገዛ ቅዱስ ጊዮርጊስም ንጉሥ ዱድያኖስ በፋርስ ሀገር ብዙ
ነገሥታት ማሰባሰቡን ሰምቶ ገንዘብና የእጅ መንሻዎችን ይዞ በመሄድ ከነገሥታቱ ሊገናኝ የአባቶቹንም ሹመት ሊለምናቸው ወደ ፋርስ
በመርከብ ሔደ፡፡
በሀገሩ በደረሰ ጊዜ ግን ነገሥታቱ ጌታችን ኢየሱስ
ክርስቶስን ሲነቅፍ ሰማ፣ ክርስቲያኖችንም ሲያሳድዷቸው አየ ‹‹ሐዋርያው ጳውሎስ ሙሴ በነገስታት ቤት ካደገ በኋላ የፈርኦን የልጅ ልጅ
እንዳይባል በእምነት እምቢ አለ፣ ከግብፅም ብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለጠግነት እንዲሆን አስቧልና፣
ለጊዜው በኀጢዓት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ ብድራቱን ትኩር ብሎ ተመልክቶአልና፣ የንጉሡን
ቁጣ ሳይፈራ የግብፅን ሀገር የተወው በእምነት ነበር የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ ጸንቶአልና›› (ዕብ 11፡24-28) ብሎ
እንደጻፈ ቅዱስ ጊዮርጊስ ስለ ክርስቶስ መነቀፍን መረጠ ከክርስቲያኖች ጋራ መከራን ሊቀበል ወሰነ፣ ‹‹አባቴና እናቴ የተጠቀሙበት
ምንድን ነው በኀላፊው ዓለም ሹመት ጥቅም አላገኙም ተድላ ደስታው ጠፍቶአል ወደ ፈጣሪያቸው ባዶ እጃቸውን ተመልሰው የለምን በማለት››
‹‹ሰማዕታት የዚችን ዓለም ጣዕም በእውነት ናቁ››
እንዲል ሊቁ የዓምን ክብር ንቆ ስለ መንግስተ ሰማያት ክብር አሰበ ‹‹በልቡ የላይኛውን መንገድ የሚያስብ እሱ ምስጉን ነው›› (መዝ
83፡5) ለንጉሡ እጅ መንሻ ሊሰጥ ያሰበውን ገንዘብና ስጦታ ለድሆችና ለጦም አዳሪዎች መፀወተ፣ ወደዚህስ የክህደት ሀገር ለምን
መጣሁ እግዚአብሔርን ትተው ሰይጣንን ወደ ሚያመልኩ፣ ከነዚህስ ርኩሳን መሾምን ለምን ፈለግሁ የዚህን ዓለም መንግስት አልሻም ለዘላለም
የሚኖረው ፈጣሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚያወርሰኝን መንግስተ ሰማያት እሻለሁ እንጂ ከእንግዲህስ ወዲህ በዚህ ዓለም እስካለሁ ድረስ
ወደ ሀገሬ ወደ እናቴም አልመለስም ስለ ጌታዬ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ከእሷ ተለይቼአለሁና ስለ ቅዱስ ስሙ እሞት ዘንድ ቆርጫለሁ
አለ፡፡
ከዚህ በኋላ ሰማዕቱ ፈጥኖ ሄደና በአላውያን ነገስታት
ፊት ቆሞ እኔ የክርስቶስ ወገን ነኝ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምናለሁ ሲል አሰምቶ ተናገረ፤ ለክርስቲያኖችም ለራሱም ወደ አምላኩ
ጸሎት አቀረበ፡፡ በምስክርነቱ አርአያ ሆናቸው ‹‹የምትገዛልህን ነፍስ ለአራዊት አትስጣት›› (መዝ 73፡19) ብሎ እንደጸለየ ነቢዩ
በአስተሳሰባቸው ከጨካኞች አራዊት ከማይሻሉት የአሕዛብ ነገስታት ክፋት ሰውረን ብሎ በመጸለይ ስለ ክርስቶስ መሰከረ፡፡ ነገስታቱም
ለሰባት ዓመታት ጽኑ መከራን አፈራረቁበት ‹‹ሰማዕታት ስለ እግዚአብሔር ደማቸውን አፈሰሱ፣ ስለ መንግስተ ሰማያት መራራ ሞት ታገሱ››
ተብሎ እንደተጻፈ ደሙን አፈሰሱት ሦስት ጊዜ ገደሉት የአመነው ፈጣሪ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን አስነሣው፡፡
ነገሥታቱን ይገስጻቸው ጀመር ‹‹የተሳሳታችሁ ነገስታት
ሆይ ይህን ስህተታችሁን አርቁ የክህደትን ስም አትጥሩ ሰማይንና ምድርን ያልፈጠሩትንም አማልክት ናቸው አትበሉ ይልቅስ አንድ አምላክ
ለሚሆኑ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ እንስገድ ብሎ አሰምቶ ተናገረ›› ቅዱስ ጊዮርጊስ በሕዝብ ፊት ይህን ሲናገር ንጉሥ ዱድያኖስ
በሰማው ጊዜ አስጠርቶ ሊመክረው ፈለገ ‹‹እኛ ሁላችን ክብርና ግርማን ተጎናጽፈን የምንኖረው ለአጵሎን (ጣዖት) በመገዛታችን ነው
እኔና ከመላው ዓለም የሰበሰብኳቸው ሰባ ነገስታት ከአንተ በቀር በዚህ በሦስት ዓመታት እኔ የክርስቲያን ወገን ነኝ የሚል ፈጽሞ
አልሰማንም ይልቁንስ በብዙ ክብርና ደስታ ለመኖር አምላካችን አጵሎንም ይቅር እንዲልህ መስዋዕት አቅርብ እኛ ነገሥታቱም እንደ ልጃችን
እናደርግሃለን የመንግስትንም ክብር ትቀበላለህ፤ አጵሎን ሰማይን እንደፈጠረ ኤራቅሉስም ምድርን ቀማንድሮስና አቴናም ፀሐይን እንደፈጠሩ
እወቅ ነገር ግን አንተ ክርስቶስ የምትለው ምን የሚታይ ነገር ፈጥሯል›› ባለው ጊዜ ሊቀሰማዕቱ በኢየሱስ ክርስቶሰ ፍቅር ተሸንፏልና
‹‹አንተ የተረገምክ ነህ ከአንተ ጋር ያሉትም ከሀድያን ርጉማን ናቸው አማላክት አይደሉም ጣዖታት ናችሁና እግዚአብሔር በሁላችሁም
ይፈርድባችኋል በማለት ዱድያኖስን ገሰጸው›› ንጉሥ ዱድያኖስ ግን ተቆጥቶ ‹‹እኔ አባት ከልጁ ጋር እንዲነጋገር እነግርሃለሁ አንተ
ግን በእብደትና በጎደሎ አእምሮ ትሰድበናለህ›› አለው ከነገሥታቱም አንዱ ቅዱስ ጊዮርጊስን በመገረም እያየ ከወዴት ወገን ነህ አባትህስ
ማን ነው ሀገርህስ ወዴት ነው ብሎ በፈጣሪው አማጽኖ በጠየቀው ጊዜ የአባቱን መዓረግ ሊገልጽ ባይወድም በአምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ
ስም ስለጠየቁት ለጥያቄዎች በሙሉ መልስ ሰጣቸው ነገሥታቱም የአባቱንና የእርሱን ጀግንት በሰሙ ጊዜ ፈሩ በሽንገላም በማባበልም ለጣዖታቸው
እንዲሰግድ ይህንም ከፈጸመ በዓለም ሁሉ የበላይ ባለስልጣን በመሆን እንደሚሾም ቢነግሩትም አልተቀበላቸውም፡፡
1. ቅዱስ ጊዮርጊስን በእንጨት ላይ እዲሰቅሉትና የውስጥ
ሰውነቱ እስኪታይ ድረስ ሥጋውን እንዲተፈትፉት ታዘዘ አሰቃዩትም ሰውነቱ ሁሉ በደም ተጥለቀለቀ
2. በአልጋ መልክ በተዘጋጀ የስቃይ መቀበያ ብረት
ላይ አወጡት አጥንቱ እስኪሰባበርና ሥጋው በደም እስኪጥለቀለቅ በብረት ጠርቀው አሰሩት ወዲያውም ከከተማ አውጥተው (በአፍአ) ልብሱን
ገፈው ሽርጥ አስታጥቀው በእንጨት ላይ እንዲሰቅሉትና አጥንቱን ከነሥጋው እንዲያደቁት አዘዘ
3. ረጃጅም ችንካሮች ያሉበት የብረት ጫማ አሰርተው
አጫሙት በችንካሮቹም እግሩን ከጫማው ጋር ቸነከሩት ችንካሮቹም ደሙ እንደ ውሃ እስኪፈስ እግሩን ዘልቀው ሥሩን በጣጠሱት መሄድም
በተሳነው ጊዜ አጎንብሶ እንደሚድህ ህፃን ልጅ ሄደ፤ መከራውም በጸናበት ጊዜ ፈጣሪዬ ክርስቶስ በመስቀል ላይ እንደተሰቀለ እንዴት
አላስብም ይህ የስጋ ሕመም ኃላፊ ነው ብሎ አሰምቶ ተናገረ ቅዱስ ዳዊት ‹‹ጻድቃን ጮኹ እግዚአብሔርም ሰማቸው ከመከራቸውም ሁሉ
አዳናቸው›› (መዝ 33፡17) ተብሎ ተጽፏልና፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ሰውነቴን
በመከራ አትጣላት ብሎ ጮኸ ያን ጊዜም እግዚአብሔር ፀሎቱን ሰምቶ ሊቀመላዕክት ቅዱስ ሚካኤልን ላከለት የሚያስጨንቀውንም መከራ ከእርሱ
አርቆ አዳነው፡፡
በሰውነቱም አንዳች የደም ቁስል ምልክት አልተገኘም
ሰውነቱም ጤነኛ ሆነ በነገስታቱም ፊት ለመቆም እንደገና ሄደ በንጉሡ ትዕዛዝ በተለያየ የማሰቃያ መሣሪያዎች ተደበደበ ተሰቃየ የእንጨት
አልጋ ሰርተው በሃያ ችንካሮች ከአልጋው ጋር ቸነከሩት ብዙ መከራም አጸኑበት ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን ስለ አምላክ ሲል ይህንን ሁሉ
ስቃይ በትዕግስት ተቀበለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በመከራው አጸናው፡፡ እጅን በሰውነቱ ላይ ዘርግቶ ባረከው ኃይልንም አሳደረበት
እነዚህ ከሀዲያን ነገስታት ሲያሰቃዩህ ሰባት ዓመት ትኖራለህ ብዙ ተአምራት ታደርጋለህ፣ ሦስት ጊዜ ሞተህ ሦስት ጊዜ አነሳሃለሁ
አለው፡፡
እንደገና በቅዱስ ጊዮርጊስ ሥቃዩንና መከራውን
አጸኑበት የሚንቀሳቀስ መንኮራኩሮችን የሚስቡ ብርቱዎችና ጉልበታም ወታደሮችን አዝዘው መንኮራኩሩ ተሠርቶ መጣ ሊቀ ሰማዕቱን ከእስር
ቤት አምጥተው ወደ መንኮራኮሩ ላይ አወጡት ዱድያኖስም ቀረበና ጊዮርጊስ ሆይ ለአጵሎን ብትሰዋ የመንግስትን ዘውድ ታገኛለህ ግን
ክርስቶስን ለማገልገል የቆረጥህ ብትሆን ሥጋህን ልትፈጭ በውስጧም ልትጣል ያዘጋጀኋት መንኮራኩር ናት ባለው ጊዜ ጽኑ ሰማዕት ጊዮርጊስ
‹‹ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስን ላገለግለው ቁርጠኛ ነኝ በእኔ ላይ የወደድከውን ሁሉ አድርግ አለው ወዲያው 40 ሰዎች ያዞሩት ጀመር
እጅግም ተጨንቆ ለአስር ክፍል ተከፈለ በመጨረሻም ነፍሱ ከሥጋው ተለየች›› ዱድያኖስና ሰባው ነገሥታት ይህን ባዩ ጊዜ ድምፃቸውን
ከፍ አድርገው ለሕዝቡ ‹‹እኛ ከምናመልካቸው ከአጵሎንና ከዜውስ ሌላ አምላክ እንደሌለ እወቁ፣ የጊዮርጊስ አምላክ የት አለ? እስኪ ይምጣና ከእጃችን ያድነው በማለት ተሳለቁ››
በዚህን ጊዜ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
ቅዱሳን መላዕክትን ጻድቃን ሰማዕታትን አስከትሎ መጣ አልዓዛርን ከመቃብር ባስነሳበት መለኮታዊ ሥልጣኑ ቅዱስ ጊዮርጊስንም አስነሣውና
ባርኮት እንዲህ አለው፡፡
ጊዮርጊስ ሆይ ሴቶች ከወለዱት መጥምቁ ዮሐንስን
የሚበልጠው እንደማይነሣ ከማሕበረ ሰማዕታትም ውስጥ አንተን የሚበልጥ የለም ወደፊትም አንተን የሚመስል አይነሣም ብዬ በራሴ ምያለሁ
ብሎ ከመከራው አዳነው እጁንም በሰውነቱ ላይ ዘርግቶ ባረከው ኃይሉንም አሳደረበት በክብርም አረገ፡፡
ከዚህ በኋላ ንጉሥ ዱድያኖስ በቅዱስ ጊዮርጊስ
ላይ እጅግ በርካታ ስቃዮችን ቢያደርስበትም እምነቱን ሊለውጥ ስላልቻለ የሥራይ መምህር (አስማተኛ) ሰው አስፈልጎ ስሙ አትናስዮስ
አስማተኛውን አስመጥቶ ቅዱስ ጊዮርጊስን ወደ ፍርድ አደባባይ እንዲያወጡት አዘዘ፡፡ አትናስዮስ ጽዋ አንስቶ በውስጡ ልዩ ልዩ ሥራይ
ቀምሞ የርኩሳን ስም እየጠራ ከደገመበት በኋላ እንዲጠጣው ሰጠው ቅዱስ ጊዮርጊስ በመስቀል አማትቦ ቢጠጣው ምንም ነገር ሳያገኘው
ቀረ፡፡
‹‹ያመኑትም እነዚህ ምልክቶች ይከተሏቸዋል የሚገድል
ነገር ቢጠጡ አይጎዳቸውም›› (ማር 16፡17) ብሏልና ክርስቶስ በወንጌል አስማተኛው አትናስዮስ ቅዱስ ጊዮርጊስን እንደገና ሌላ
መርዝ እቀምማሁ እርሱን ጠጥተህ ክፉ ነገር ካላገኘህ እኔ በፈጣሪህ አምናለሁ አለው፣ ጽዋውን በድጋሚ መርዝ ሞልቶ ከቀድሞው የሚበልጡ
አጋንንትን ስም እየጠራ ከደገመበት በኋላ ሰጠው ቅዱስ ጊዮርጊስ በመስቀል አማትቦ ቢጠጣው ፈጽሞ ጉዳት ሕመም ሳያገኘው ቀረ ጭራሽ
ፊቱ በራ፣ አስማተኛው አትናስዮስ ይህንን ሲያይ ከቅዱስ ጊዮርጊስ እግር በታች ወድቆ ሰገደለት ወዲያውኑ አምኖ ተጠመቀ በቅዱስ ጊዮርጊስ
ዙሪያ የነበሩት ሁሉ እጅግ ተደነቁ፣ ንጉሡ ዱድያኖስ ግን ልቡናውን በክህደት አጸና ማሳደዱን ቀጠለበት
1. ወታደሮቹን ግንድ አምጥተው ጊዮርጊስን በግንዱ
ላይ አጋድመው ከግንዱ ጋር በሦስት ችንካር እንዲቸነክሩት አዘዘ በላዩም ላይ እሳት አነደዱበት ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን አንድም ቃል
አልተናገረም ይልቁንስ ልቡናውን በሰማይ ከሰማያዊያን መላዕክት ጋር አደረገ
2. ከዚህ በኋላ አንድ መጨመቂያ ሆኖ ከተሠራ የሥቃይ
መሣሪያ ላይ አውጥተው ሰውነቱን እንዲሰነጥቁትና እንዲጨምቁት አዘዘ አንጀቱ ሁሉ ወጥቶ ከምድር ላይ እስኪዘረገፍ ድረስ እንዲሁ አደረጉበት፣
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሥቃይ ብዛት የተነሣ ነፍሱ ከሥጋው ተለየች
3. ሥጋውን በእሳት አቀጠሉት እንደ አመድም ሆነ፣
አረመኔውና ከሃዲው ንጉሥ የተቃጠለውንና እንደ አመድ የሆነውን የቅዱስ ጊዮርጊስን አጽም አፍሰው በቀፎ አድርገው ይድራስ ወደ ሚባል
ተራራ (ደብረ ይድራስ) ወስደው ምእመናን አመዱን ቅሪቱን እንኳ እንዳያገኙት በነፋስ እንዲበትኑት አስደረገ፡፡
‹‹እግዚአብሔር አጥንቶቻቸውን ሁሉ ይጠብቃል፣
ከእነርሱም አንድ አይሰበርም›› (መዝ 33፡20) ተብሎ ተጽፏልና ፤ ያን ጊዜ መብረቅ ነጎድጓድ ትልቅም ንውጽውጺታ ሆነ ምድርም
ከመሠረቷ እስክትነዋወጽ ድረስ ከሰማይ ድምጽ ተሰማ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ዓለምን በፈጠረበት በአማላካዊ ቃሉ የኔ ሆይ የመረጥኩህ
ወዳጄ ጊዮርጊስ ከሞት ተነሣ አትፍራ እኔ አዝዤሃለሁና ሲል ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስን ጠራው ያን ጊዜ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከጫጉላ ቤት
እንደሚወጣ ሙሽራ ምንም ሳይኖርበት ለሁለተኛ ጊዜ ሞቶ ተነሣ ነገሥታቱ ግን ቅዱስ ጊዮርጊስ ሕያው መሆኑን የፋርስ ህዝብ እንዳያይና
እንዳይሰድባቸው ወታደሮቹ በድብቅ እንዲያመጡት አዘዙ፡፡ የቤሩቱ ኮከብ ቅዱስ ጊዮርጊስ በፋርስ እንደ ፀሐይ አበራ ብዙዎችም ከጽናቱ
የተነሣ በኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ፡፡ በንጉሡ በዱድያስ ፊት በድብቅ አምጥተው ባቆሙት ጊዜ ‹‹አንተ ከሃዲ ከእግዲህ እፈር የሰው
እጅ ሥራ የሆኑትን ትንፋሽ የሌላቸውን ርኩሳን ጣዖቶችህንና አንተን አሳፍራችሁ ዘንድ አምላኬ ኢየሱስ ክርስቶስ እነሆ አስነሳኝ››
አለው፡፡ ዱድያኖስ ግን ብዙ ገንዘብ ሰጥቶት ከሀገር እንዲወጣ በብዙ ማባባል ለመነው፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን ‹‹ከግብጽ ብዙ ገንዘብ
ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለጠግነት እንዲሆን አስቧልና›› (ዕብ 11፡26) እንዲል ሐዋርያው ጳውሎስ ሰማዕቱ
ከዱድያኖስ የገንዘብ ሽንገላ ይልቅ ስለ ፈጣሪው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መከራ መቀበልን መረጠ፡፡ ከዚህ በኋላ ንጉሥ ዱድያኖስና ሰባው
ነገሥታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ሦስት ጊዜ ገድለውት ሦስት ጊዜ ስለተነሣ ብዙ መከራ ቢያጸኑበትም ምንም ሊያሸንፉት ስላልቻሉ አንገቱ በሰይፍ
እንዲቆረጥ የመጨረሻ ውሣኔ አስተላለፈ፡፡
ጭፍሮችም ሊገድሉት ሲዘጋጁ ጥቂት ጊዜ ስጡኝ በቅድሚያ
ስለ እነዚህ መናፍቃን ነገሥታት ፀሎት ማድረግ ይገባኛል አላቸው፣ ጭፍሮችም እንዲፀልይ ፈቀዱለት ነገስታቱ ግን በቅዱስ ጊዮርጊስ
የሞት ፍርድ ሐሴት አድርገው ይበሉና ይጠጡ ነበር ቅዱስ ጊዮርጊስ ዓይኑን ወደ ሰማይ አቅንቶ ሲፀልይ ከሰማይ ታላቅ እሳት ወርዶ
ሰባውን ነገስታትና ሠራዊቱን ሁሉ አቃጠላቸው፡፡
‹‹በኤልያስ ዘመን እሳት ከሰማይ ወርዶ ጣዖት
አምላኪዎችን ጠላቶቹን እንዳቃጠለ (2ነገ 1፡13-14) ሰባው ነገስታትም በእሳት ተቃጥለው ሞቱ፡፡ ከዚህ በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስ
ስለ ራሱ ተንበርክኮ ለፈጣሪው ምስጋና አቀረበ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ተገልጾ ቃል ኪዳን ሰጠው ‹‹ወንድም ሴትም ቢሆኑ ቢታመሙ
በመከራ ቢወድቁ ወደ ፍርድም ቢወጡ በጦር ሜዳ ወይም በወህኒ ቤት ቢሆን በባሕር በፈሳሽ በወንዝም ቢሆን በመንገድም በቀማኞች እጅ
ቢወድቁ አውሬ ቢያገኛቸው እሳት አደጋ ቢደርስባቸው ክፉ አሟሟት ቢገጥማቸው በችግር ላይ ሆነው እጅግ ተስፋ ቆርጠው በጽኑ መከራ
ቢወድቁ በስምህ ተማጥነው ሶስት ጊዜ አምላከ ጊዮርጊስ እርዳን (3) እያሉ ወደ እኔ ቢጮኹ ያን ጊዜ ራራላቸዋለሁ ፈጥኜም ለጸሎታቸው
መልስ እሰጣለሁ ከልባቸው የለመኑትን ሁሉ እፈጽምላቸዋለሁ ከመከራቸው አድናቸዋለሁ›› ብሎ ቃል ኪዳን ከሰጠው በኋላ ባርኮት ተሰወረ፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስም ወታደሮችን ቀስቅሶ ወንድሜቼ
ኑ የታዘዛችሁትን ፈጽሙ አላቸው ፊቱንም ወደ ምስራቅ መልሶ በስላሴ ሥም በመስቀል ምልክት አማትቦ አንገቱን ለሰይፍ አቀረበ ያን
ጊዜም ክብርት ራሱን ቆረጡት፡፡ ደም ውሃ ወተት በአንድ ላይ ሆኖ ፈሰሰ ጌታችን ቅዱስ ሚካኤልን ልኮ የቅዱስ ጊዮርጊስን ደሙን በብርሃን
ልብስ እንዲቀበለው አዘዘ ቅዱሳን መላዕክት እና ጻድቃን ሰማዕታት ሁሉም በደስታ ያመሰግኑ ነበር፡፡ ጌታም የቅዱስ ጊዮርጊስን ነፍስ
ተቀብሎ አሳረጋት መከራ በተቀበለችው ሰባት ዓመታት ልክ ከሕይወት አበቦች የተሰሩ አክሊሎች ያሉበት ዘውድ አቀዳጀው በዚህ ሁኔታ
የቤሩቱ ኮከብ የልዳው ሰማዕት የፋርሱ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሰማዕትነቱ ገድል ሚያዝያ 23 ቀን ተፈጸመ፡፡
ይህ ታላቅ ሰማዕት በችግራቸው ጊዜ በእምነት ለሚጠሩት
ሁሉ በፍጥነት ደርሶ ስለሚታደግ ‹‹ፍጡነ ረድኤት›› ይባላል፡፡
የሃገራችንም ባለውለታ ከመሆኑ የተነሣ የኢትዮጵያው
ገበዝ ተብሏል ሀገራችን ኢትዮጵያ በፋሽስት ኢጣሊያ በተወረረች ጊዜ በአድዋ ጦርነት ላይ የፈጸመው የትድግና ተግባር ከኢትዮጵያውያን
ኅሊና የሚጠፋ አይደለም፣ ዛሬም ሕዝባችንን ከከበበው ችግርና መከራ፣ ዘረኝነትና መለያየት ርኩሰትና ግብረሰዶማዊነት በረድኤቱ በጸሎቱ
ይጠብቅልን አሜን፡፡
ዋቢ
·
ገድለ ጊዮርጊስ
·
መልክአ ጊዮርጊስ
·
81 መጽሐፍ ቅዱስ
No comments:
Post a Comment