Friday, April 25, 2014

እንደ በግ ብረር እንደ ሰው አምርር



 


ልቤ ሆይ ቸርነትና ምህረቱ በማያልቅ በእግዚአብሔር ምህረት ዳግም ለመገናኘት ስለበቃን አምላካችንን ልናመሰግነው ይገባል፡፡ እንደ ቀደሙ ሁሉ ከሩጫህ አረፍ ብለህ እኔና አንተ ልንነጋገረው የሚገባ  ምስጢር ስላለ ቀርበህ ስማኝ፡፡ ለዛሬ ከአንተ ጋር አንድ አይነት ስህተት የሚያሳዩ ሁለት ምሳሌዎችን ለኑሮህ ወስደን ማየት ይኖርብናል፡፡

ልቤ ሆይ የመጀመሪያው እንዲህ ነው የሰው ዘመኑ እንደ ጥላ በመሆኑ ማለፉ አይቀርምና ከጥቂቱ ጊዜ በፊት በአጠገብህ የነበሩ አሁን ግን ወደዚህኛው ዓለም ላይመለሱ ያንቀላፉ ብዙዎችን አይተሃል፡፡ አንተም ምንም እንኳ ለጊዜው ሞት መኖሩንና አንድ ቀን አንተም ተራ እንደሚደርስ ብታስብም ወደ ንስሐ ሳትሸሽ ከትንሽ ከንፈር መምጠጥ በኋላ ሁሉን ረስተህ ምጽዐት እንደሌለበት ሰው ያለምን ዝግጅት ዛሬም እንዲሁ አለህ፡፡ ልክ ሕይወትህ በእጅህ ዘመንህም በቁጥጥርህ ያለ ይመስል ‹‹ነገ እደርሳለሁ ቆይ ትንሽ….›› በሚሉ ምክንያቶችህ ራስህን ትሸሽጋለህ፡፡ ይህም ነገር ሁልጊዜም በሕይወትህ ይከናወናል፡፡
ሕይወትህ ታይቶ እንደሚጠፋ እንፋሎት መሆኗን ከመርሳትህ በተጨማሪ ‹‹ቀኒቱንና ሰዐቲቱን አታውቁምና እንግዲህ ንቁ›› የሚለውን የጌታን ቃል በየጊዜው የምታስብ አይመስለኝም ማቴ 12፡13 ልቤ ሆይ ከአጠገብህ የተለየውን ሰው ስታይ አንተም ተራ እንደሚደርስህ ማሰብህ ለጥቂት ጊዜ ብቻ አይሁን፡፡ በዚህ ዓለም ጸንተህ እንደማትኖርም እየረሳህ እንዲሁ ያለ ዝግጅት አትመላለስ፡፡
ልቤ ሆይ ሌላው ደግሞ በቤተክርስቲያን ላይ እየደረሰ ስላለው መከራና ፈተና ስትሰማ በጣም ታዝናለህ ብለህም እንባህን ታፈሳለህ፡፡ ወዲያው እንዲህ እንዲህ …እናድርግ ትላለህ፡፡ ለሁሉ ነገር አንደኛ ትሆናለህ፡፡ መልካም ነበር ነገር ግን ምን ያደርጋል? ይህ ስሜት ብቻ ይሆንና ብዙም አይዘልቅም፡፡ ቤተክርስቲያን ምንም እንዳልሆነች ያለ ሀሳብ ትመላለሳለህ የህዝብህን ስቃይ ሁሉ ትረሳለህ በሩቅ ብቻ ቆመህ እንዲህ ቢሆን ኖሮ ጥሩ ነበር ማለት ትጀምራለህ እንኳን ራስህን አሳልፈህ ለመስጠት ቀርቶ ካለህ ነገር ትንሽ ለማካፈል የተዘጋጀህ አይደለህም፡፡ ከዚህ በላይ የሚሰሩትንም እንዳይሰሩ ልባቸውን በነገር ታደክማለህ፡፡
‹‹ያሳደግሁ ልጄ ሆይ….›› የሚለውን የቅድስት ቤተክርስቲያንን (በመከራ ውስጥ ያሉ የምዕመናንን)  ጩኸት እንዳልሰማህ መስለህ በራስህ ዓለም ትኖራለህ፡፡ ልቤ ሆይ እንግዲህ ከገባህበት የስሜታዊነት እንቅልፍ ንቃ፡፡ በኃጥአን እንደተመሰለች ፍየል መሸሽህ (ለበጎ ነገር መነሳትህ) ለጥቂት ጊዜ አይሁን እነሆ ከፍየል ወገን አንዱ በአውሬ የተነጠቀ እንደሆነ ሁሉ ይሸሻሉ ነገር ግን ተመልሰው እዛው ይገኛሉ፡፡ አንተም የሌላውን በሞት ከዚህ ዓለም ማለፍ አይተህ የራስህን ሞት ማሰብህ ለጥቂት ጊዜ አይሁን፡፡
አምርረህ ወደ ንስሐ በፍጹም በመሸሽ የተዘጋጀህ ሁን እንጂ፡፡ ለቤተክርስቲያ ማሰብህም እንዲሁ በከንፈር አይሁን ክርስትና በምር የሚኖሩበት ሕይወት ነውና ስለ ራስህ ሕይወትና ስለ ቤተክርስቲያን ሰላም ቸልተኛ ሆነህ አትታይ፡፡ የምዕመናንን ስቃይ እንደ ዓለም ወሬ አንድ ሰሞን ትኩስ ዜና ብቻ አታድርገው በዓለም ቤተመንግስትም ብትሆን እንደ ሙሴ ከህዝብህ መከራ መካፈልን አትሰቀቅ፡፡ ልቤ ሆይ ብዙ የምልህ ቢኖረኝም አሁን ካለህበት ድካም የተነሳ ልትሸከመው አትችልምና ነገሬን እዚህ ጋር ላቁም፡፡ ሁሌም ግን በግ ከበረረ ሰውም ካመረረ… እንደሚባለው አንተም ሰው ሁንና እያመረርህ በመኖር በኤርሚያስ ቃል ጌታን ጥራው፡፡
‹‹አቤቱ የሆነብንን አስብ ተመልከትም ስድባችንንም እይ
ርስታችን ለእንግዶች ቤቶቻችን ለሌሎች ሆኑ፡፡
ድሃ አደጎችና አባት እናት የሌለን ሆነናል
እናቶቻችን እንደ መበለቶች ሆነዋል
ውኃችንን በብር ጠጣን እንጨታችንን በዋጋ ገዛን…
ስለምን ለዘላለም ትረሳናለህ?
ስለምንስ ለረዥም ዘመን ትተወናለህ?
አቤቱ ወደ አንተ መልሰን እኛም እንመለሳለን
ዘመናችንን እንደ ቀድሞ አድስ፡፡›› ሰቆ ኤር 5

ክብርና ምስጋና ለአምላካችን ይሁን፡፡ አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment