Thursday, April 17, 2014

‹‹ከክርስቶስ ጋር አብረን ከሞትን አብረን እንነሳለን››

‹‹ሞቱን በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሳኤውንም በሚመስል ትንሣኤ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን›› ሮሜ 6፡5

 
 

‹‹ከክርስቶስ ጋር አብረን ከሞትን አብረን እንነሳለን››
ኢየሱስ ክርስቶስ የሞተውን አዳም ለማዳን ሥጋን ተዋሕዶ እንደሚሞት የሚያውቀው ከዘመናት በፊት ነው፡፡ ቤተልሔም ከመወለዱም በፊት የሚሞትበት ጊዜ እየቀረበ እንደሆነ፣ የሰውን ልጅ ሥጋ የለበሰውም ሞቶ ሞትን ለመግደል እንደሆነ ያውቃል የመጣበት ዓላማም ለሞመት ነው ለደቀመዛሙርቱም በተለያየ ጊዜ በምሳሌ ነገረ ሞቱንና ጊዜያቱን ነግሮአቸዋል፡፡ ‹‹በደብረታቦር ብርሃነ መለኮቱን ከገለጸበት ቀን ጀምሮ አለቆች ከጻፎችም ብዙ መከራ ይቀበልና ይገደል ዘንድ በሦስተኛውም ቀን ይነሣ ዘንድ እንዲገባው ለደቀመዛሙርቱ ይገልጥላቸው ነበር›› (ማቴ 16፡21) ለሚጠሉት ላሰቃዩት ለአይሁድ እንኳ ሳይቀር በምሳሌ ይነግራቸው ነበር ‹‹ይህን ቤተመቅደስ አፍርሱት በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ›› አላቸው፡፡ (ዮሐ 3፡19)

በመስቀል ላይ እያለም የመከራው ሰዓት አልፎ ራሱን ለሞት አሳልፎ የሰጠውም በአይሁድ ፈቃድ ሳይሆን በፈቃዱ ነው የሞተውም ስለ ራሱ ሳይሆን ስለ ሰው ልጆች የባሕርይው ፍቅር አስገድዶት ነው ‹‹መድኅን ክርስቶስ ፈጽሞ አልበደለም፣ በአንደበቱም ፈጽሞ ሐሰት አልተገኘም፣ ከኀጢዓትም ፈጽሞ የራቀ ነውና፣ እሱ ኃጢዓትንና ሞትን የሚያጠፋ ነው፣ ስለ ራሱ ሳይሆን ስለ ሰው ልጆች በደል ብሎ በፈቃዱ ራሱን መስዋዕት አድርጎ አቀረበ›› (ሃ.አበው)
ክርስቶስ ከመሞቱ አስቀድሞ ልዩ ልዩ ተአምራት በመሥራት ብዙ ሰዎች በእርሱ እንዲያምኑ ሲያደርግ በአንፃሩም ብዙ የተአምራቱ ተቀናቃኞች የሰማዩ ነገር እንቆቅልሽ ሆኖባቸው ሕይወት የሆነው ክርስቶስን ከማመን ይልቅ ‹‹እርሱን ከእኛ ይልቅ ብዙ ሰው ተከትሎታልና በዚሁ ከቀጠለ እኛ ባዶአችን እንቀራለን የሚከተለንም ሰው አናገኝም ሀገራችንም በእሱ ባመኑት ሕዝቦች ትወረራለች ስለዚህ እናጥፋው›› ብለው የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ሸንጎ ሰበሰቡ በዘመኑም ሊቀ ካህናት የነበረው ቀያፋ ስለ ክርስቶስ ሞት ‹‹ሕዝቡም ሁሉ ከሚጠፋ አንድ ሰው (ክርስቶስ) ስለ ሕዝብ ይሞት ዘንድ እንዲሻለን አታስቡም›› ብሎ ሳያስበው ትንቢት ተናገረ (ዮሐ 11፡45-53)
እውነት ክርስቶስ ካልሞተ የሰው ልጆች ከሞት ወደ ሕይወት አይሸጋገሩም ነበር የክርስቶስን ሞት የአይሁድ ሊቀ ካህናት ብቻ ሳይሆኑ አስቀድሞ ትንቢትን የተናገሩ ነቢያትና የሰሙት ቅዱሳት ሁሉ በእግዚአብሔር እጅ በተያዙበት በሲኦል ሆነው ይጠባበቁት ነበር፡፡ ክርስቶስ ካልሞተ ዓለም እንደማይድን እነርሱም ከሲኦል እንደማይወጡ ያውቃሉና የሰቀሉት አይሁድ ሞቱን ለሞታቸው ሲያጣድፉት በሲኦል ያሉ ነፍሳት ደግሞ ሞቱን ለሕይወታቸው ይጠባበቁት ነበር፡፡
የጠፉትን በጎች ሊፈልግ፣ የተበተኑትን የእግዚአብሔርን ልጆች በአንድነት፣ ሊሰበስባቸው ሞትና መውጊያውን ድል ሊያደርግ፣ በሁከት ለነበሩት ነፍሳት ሰላምን ሊሰብክላቸው የድንግል ማርያም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞተ፡፡
‹‹እውነት እውነት እላችኋለሁ የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች›› (ዮሐ 12፡24፣ 1ጴጥ 1፡19) የክርስቶስ መሰቀል እንደ ከንቱ ነገር የሚታይ አይደለም፡፡ መከራው፣ ግርፋቱ፣ መሰቀሉ፣ ሞቱ ሕይወት ነው ሰው ለራሱ ችግር መከራን ይቀበላል፡፡ እርሱ ግን ከመከራው አልፎ እኛን ለማዳን ሞተ ‹‹መልካም እረኛ ሕይወቱን ስለበጎቹ አሳልፎ ይሰጣል›› (ዮሐ 10፡14) ሰው ለወዳጁ ይሞታል እርሱ ግን ለጠላቶቹ ለእኛ ሞተ
‹‹እኛ ጠላቶቹ ሳለን በልጁ ሞት ታረቀን›› (ሮሜ 5፡10) የእርሱ ሞት የሰዎች ሁሉ ሕይወት ነውና ከእርሱ ጋር አብረን በሕይወት እንኖር ዘንድ ስለ እኛ ሞተ›› (1ተሰ 5፡10)
እንግዲህ በአንድ በደል ምክንያት ፍርድ ለኩነኔ ወደ ሰው ሁሉ እንደመጣ እንዲሁም በአንድ ጽድቅ ምክንያት ስጦታው ሕይወትን ለማጽደቅ ወደ ሰው ሁሉ መጣ፡፡ በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኀጢዓተኞች እንደሆኑ እንዲሁ ደግሞ በአንዱ መታዘዝ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ (ሮሜ 5፡18) ተብሎ እንደተጻፈ፡፡
አዳምና ሔዋን በእግዚአብሔር ላይ ጽኑ የነበረው ልባቸው በሰይጣን ሴራ ሲሸረሸር የእግዚአብሔርን ድምጽ ከመስማት ይልቅ አለመታዘዝ ዕዝነ ልቡናቸው ደፍኖባቸው ምኞታቸውን በመከተል በኀጢዓት ሲወድቁ ለኩነኔ የሚያበቃ ፍርድ ተፈርዶባቸው በፈቃዳቸው ከሰይጣን ክፉ ሃሣብ ጋር በመተባበራቸው ለዘመናት ከአምላካቸው ከእግዚአብሔር ተለይተው ኖሩ፡፡ ምንም እንኳ በመተላለፋቸው በሞት ጥላ ሥር ቢቆዩም በእግዚአብሔር ፍቅር በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ መታዘዝ ጽድቅን አገኙ ከአባታቸው በተላለፈው ኃጢዓት ደቂቀ አዳምም በኀጢዓተኝነት ተገፍተው ከሞት ቢዋገኑም ክርስቶስ ግን በሞቱ ሞትን አጥፍቶ በትንሣኤው ሕይወትን አወጀ፡፡
የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ምትሀት ሳይሆን እውነተኛ ትንሣኤ ነው ስለሆነም ከሞት ከተነሣ በኋላ ለደቀመዛሙርቱ ሥጋን እንደለበሰ ተገልጦላቸዋል፡፡ ሰላም ለእናንተ ይሁን ብሎ ታይቷቸዋል እነርሱ ተስፋ ቆርጠው በአሣ አጥማጅነት ሥራቸው ተሰማርተው ሳለ በመካከላቸው ተገልጦ ጉድለታቸውን ሞልቶላቸዋል፡፡ ከጌታችን ጋር ምሳም አንድ ላይ በልተዋል (ዮሐ 21፡1-14) ይህ የሚያሳየን የክርስቶስ ትንሣኤ እውነተኛ መሆኑን ነው፡፡ ከክፉ አጋንንት አሰራር በክርስቶስ ሰላምን ያገኘችው መግደላዊት ማርያም ውለታውን አስታውሳ በአይሁድ ሥርዓት መሠረት ለሞቱ ሽቱን ይዛ በመቃብሩ በተገኘችበት ወቅት እንደጠበቀችው ሳይሆን ቀርቶ ‹‹ሁለት መላዕክት ነጭ ልብስ ለብሰው የኢየሱስ ሥጋ ተኝቶበት በነበረው አንዱ በራስጌ ሌላውም በግርጌ ተቀምጠው አየች›› ወዲያውም ሞቷል ብላ ያለቀሰችለት ጌታዋ ከሙታን ተነስቶ በሕይወት አገኘችው ትንሣኤውንም ለደቀመዛሙርት አበሰረች (ዮሐ 20፡11-18) ሌሎችም ቅዱሳን አንዕስት እንደ ልምዳቸው ወደ ጌታም መቃብር ሽቱ ይዘው ሲመጡ መላዕክት ተገልጠውላቸው ‹‹ሕያውን ከሙታን መካከል ስለምን ትፈልጉታላችሁ? እንደ ተናገረ ተነስቷል እንጂ በዚህ የለም አላቸው›› (ሉቃ 24፡1-6)

በእርግጥም ክርስቶስ ስለትንሣኤው ‹‹ዮናስ በዓሣ አንበሪ ሆድ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንዳሳለፈ እንዲሁ የሰው ልጅ በመቃብር ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ያሳልፋል›› (ማቴ 12፡4) ብሎ እንደተናገረ ሞትን አሸንፎ ተነስቷል በሞት ላይ ሥልጣን ያለው ጌታ ከሙታን በኩር ሆኖ ተነስቷል ብኩርናውም የጻድቅ፣ የሃይማኖት የትሩፋተ ሥጋ፣ የትሩፋተ ነፍስ፣ የትንሣኤ ጀማሪነት ነው፡፡
በክርስቶስ ትንሣኤ ሞት መውጊያው ጠፍቷል መሠረቱ ተነቅሏል ጥንትም በነቢያት የተነገረለት ጌታ ሞትን ድል አድርጎ ተነስቷል፣ እግዚአብሔር ግን የሞትን ጣር አጥፍቶ አስነሣው ሞት ይይዘው ዘንድ አልቻለምና፡፡ (የሐዋ 2፡24)
ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ባይነሣ ተስፋችን ይጨልም ነበር፣ መዳናችንም የተረጋገጠ አይሆንም ነበር ያለ ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ የምንጠብቀው ድኅነት አይኖረንምና፡፡ አሁን ግን ትንሣኤውን አይተናል ከመቃብር የተነሣው ጌታ በአብ ቀኝ በክብር ተቀምጧልና በእርግጠኝነት ድነናል፡፡
ስለዚህም ትንሣኤውን ስንቀበል ከተነሣው ጌታ ጋር እንኖራለን ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውንም በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን (ሮሜ 6፡5)
ወዳጆች ሆይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምድር በተመላለሰበት ወቅት የነበረውን ሕይወትና በሞቱ ሞታችንን ደምስሶ በትንሣኤው ሕይወታችን የተረጋገጠ እንዲሆን ያደረገልን መሆኑን ለማሳት በልደቱ፣ በትምህርቱ፣ በመከራው ፣ በስቅለቱ በሞቱና በትንሣኤው ሁሉ አርአያና ምሳሌ ሆኖናል፡፡
በኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት ውስጥ መኖር ካልቻልን በኑሯችን ፍጹም ደስተኞች ሆነን መኖር አንችልም ለቅድስና ሕይወት የምንበቃውም አስቀድመን በእርሱ ሕይወት መኖር ስንችል ነው ስለዚህ ትንሣኤውን ለመምሰል መከራውን መስለን የመንግስቱ ወራሾች እንድንሆን እንወስን፡፡  

No comments:

Post a Comment