በስመ አብ ወወልድ
ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
ይድረስ የእግዚአብሔር
መንግስት ቁልፍ በእጁ ላለ ስለ ሞተልህም ስለ ክርስቶስ ስም በሮም አደባባይ ቁልቁል ለተሰቀልህ ታማኝ ምስክር ለሆንከው ለቅዱስ
ጴጥሮስ፡፡ በጌታ ፊት በምስጋና ለጸናች ነፍስህ ሰላም እላለሁ፡፡ ጴጥሮስ ሆይ ከዚህ ምድር ከተለየህባት ጊዜ ጀምሮ ስለ ነፍሴ እየተጋህ
እንደሆነ እምነቴ ነው፡፡ ጴጥሮስ ሆይ የፈተናው ዓለም ሕይወት እንዴት ይዞሃል? ብትለኝ ልክ አንተ በመንፈስ ቅዱስ ታድሰህ በእምነትና በቅድስና ከመመላለስህ
በፊት ያለውን የቀደመ ሕይወትህን ይመስላል እልሃለሁ፡፡
ትዝ ይልሃል
ያኔ ጌታን እያየህ በባህሩ ላይ መራመድ ጀምረህ እንደ ነበር? ግን አይንህን ከጌታ ላይ አንስተህ ማዕበልና ወጀቡን ባየህ ጊዜ መስጠም
ጀመርህ፡፡ እንዲሁ ዛሬም እኔ አይኖቼን ስለ ሰው ልጆች መዳን ከተሰቀለው አምላክ ላይ እያነሳሁ የዓለምን የፈተና ወጀብና መከራውን
በማሰቤ ልቡናዬ በዝለት መስጠም ጀምሯል፡፡ በተለይ በቤተክርስቲያን አካባቢ በሚታየው ታላቅ ፈተና ወጀብ ነፍሴ ታውካለች፡፡ ግን
እንደ አንተ አድነኝ እንኳ ብዬ በፍጹም ልቤ መጮኽ ተስኖኛል፡፡ ጌታዬንም ብቻ እያየሁ እርሱን እንዳላስብ ዓለም አዚም ሳታደርግብኝ
አልቀረችም፡፡
ደግሞ በአትክልቱ
ሥፍራ በጸሎት ተግተህ ባለመገኘትህ የተነሳ ጌታን የሚይዙት በመጡ ጊዜ ስጋዊ መሳሪያ ሰይፍን አንስተህ የሰውን ጆሮ ለመቁረጥ በቅተህ
ነበር፡፡ ጌታ ግን ገሰጸህ እንጂ አልተቀበለህም፡፡ እንዲሁ እኔም ወደ መከራ እንዳልገባ በፈተና እንድጸና ተግቼ ከመጸለይ ይልቅ
በሥጋዊ ጥበብ በመመካት ስለምመላለስ የጌታ ተግሳጽ እየበዛብኝ ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ማዳን ዝም ብዬ በእምነት ተስፋ እያደረግሁ
ከመጠባበቅ ይልቅ በዚህ ዓለም ባለው ነገር ተስፋ እያደረግሁ ዘመኔ በከንቱ አለፈች፡፡
ጌታ በተያዘባት
በዚያች ሰዓትም አይሁድን ከመፍራትህ የተነሣ በርቀት ሆነህ ትከታተለው ነበር፡፡ እንደውም እርሱ መከራ ሲቀበል አንተ እሳት ትሞቅ
ነበር፡፡ ልክ እንዲሁ እኔም ምንም እንኳን አምላኬን እተከተልሁ ነው ብልም በንስሐና በቃሉ በቅዱስ ቁርባንም ለመኖር በመፍራትና
ጌታ በመጨረሻው ቀን የማይቀበላቸውን ብዙ ምክንያቶችን በመደርደር (እንደ እሳት በመሞቅ) በነፍሴ ከአምላኬ በርቀት ሆኜ እመላለሳለሁ፡፡
መንገዴ እንደ መንገዱ ሀሳቤም እንደ ሀሳቡ አልሆነም፡፡ ምን እንደሚበጀኝ አላጣሁትም ግን እጅ እግሬ በፍርሃትና በምክንያት ታስሯል፡፡
ጸሎትህ ያስፈታኝ እንጂ ሌላ ምን እላለሁ?
በጣም የሚያሳዝነው
ግን አልክድህም ያልከውን ጌታ እየማልህና እየተገዘትህ መካድህ ነው፡፡ ይህን ባየሁ ጊዜ በጣም ነበር የደነቀኝ ግን ለምን ያንተን
ብቻ አወራለሁ ካንተ መካድ እኔ መድገም አይበልጥም? ምንም እንኳ አፌን ከፍቼ በአንደበቴ አምላክን ያልካድሁት ብሆንም ዕለት ዕለት በምሰራው ስራ
ግን እርሱን የማምነው አይደለ የማውቀውም አይመስልም፡፡ ምክንያቱም ወንድሙን የማይወድ እግዚአብሔርን አያውቅም እንደተባለ ፍቅር
የጎደለኝ ለራሴ ብቻ የምኖር በመሆኔ ነው ፡ በቃልና በአንደበት ባልክድም በስራና በእውነት ስላለው ግን ያፈራሁት ፍሬ ይመሰክራል፡፡
አንተስ ብትወድቅም በንስሐ እንባ ታጥበህ ተመልሰሃል ተነስተሃልም ጌታም ንስሐን ተቀብሎታል በበጎቹም ላይ ታማኝ እረኛ አድርጎ ሹሞሃል
በመጨረሻም ሰምሯል፡፡ እኔ ግን ገና መውደቅ መነሳት በበዛበት ዓለም ውስጥ ነኝ ያለሁት ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አላፈራሁም ስለ ቀደመ
ክፉ ስራዬ ተጸጽቼ አልተመለስኩም ዛሬም በርቀት ነው እግዚአብሔርን የምከተለው፡፡ በእርሱ ቸርነት በአንተ ጸሎት ልቡናዬን ወደ እርሱ
ያቅርበው እንጂ ምን ማለት እችላለሁ፡፡ ጴጥሮስ ሆይ የመንግስተ ሰማያት በር መክፈቻ ቁልፍ ከአንተ ዘንድ ነውና ከዚህ ዓለም በተለየሁ
ጊዜ ምግባር ጎድሎኝ ሙሽራው ገብቶ በሩ እንዳይዘጋብኝ በጸሎትህ ወደ መግባቱ እንድታፈጥነኝ አደራህን እላለሁ፡፡ ጌታንም ቢሆን እንደሚከተለው
ከመለመን በቀር ምን እለው ዘንድ እችላለሁ?
‹‹አንተ እግዚአብሔር አምላኬ ነህና መልሰኝ እኔም እመለሳለሁ››
ኤር 31፡18
No comments:
Post a Comment