Saturday, April 19, 2014

‹‹ክርስቶስ በታላቅ ኃይልና ስልጣን ከሙታን መካከል ተነስቷል››

                                                                              
ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን ~~~~~~በዓቢይ ሃይል ወሥልጣን
ሮ ለሰይጣን ~~~~~~~ አግአዞ ለአዳም
ሰላም ~~~~~~~~ እምእዘየሰ
ኮነ ~~~~~~~ ፍሰሃ ወሰላም። አሜን!!!
+++ ትረጉም +++
ክርስቶስ በታላቅ ሃይሉና ሥልጣኑ ከሙታን መካከል ተለይቶ ተነሳ፤
ሰይጠንን አሰረው፤ አዳምን ነፃ አወጣው፤
ከእንግዲህ ወዲህ ፍሰሃ፣ ሰላም፣ ደስታ ሆነ!!! አሜን!


ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕያው ነውና መቃብር ይዞ አላስቀረውም፣ ትንሣኤ ነውና ሞት በእርሱ ላይ ስልጣን አልነበረውም በመሆኑም ከሦስት መዓልትና ሌሊት በኋላ መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል ሞትን ድል አድርጎ መውጊያውንም ሰብሮ በኃይሉ ተነስቷል፡፡ ‹‹ኦ መዊት አይቴ ሃሎ ቀኖትከ›› ሞት ሆይ መውጊያህ የታለ? ሲኦል ሆይ ድል መንሳትህ የታለ›› ተብሎ በትንቢት በተነገረው መሠረት ገዥውንና ኃያሉን አሸንፎ መውጊያውን ሰብሮ ጌታችን ተነስቷል፡፡




ክርስቶስ ከሙታን መካከል ተለይቶ መነሣቱ ታላቅ ክስተት ስለነበር የአይሁድን ህብረት አናውጧል፡፡ ይህ በመሆኑም በተገኘው መንገድ ሁሉ ሊቃወሙት ሞክረዋል ትንሣኤን ከመገለጡ በፊትም ሆነ ከተገለጠ በኋላ ይቃወሙት ዘንድ ታላላቅ ሙከራዎችን አካሂደዋል፡፡
መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከስቅላቱ በፊት የትንሣኤውን መልካም ዜና አብስሯል፡፡ ለደቀመዛሙርቱም በተደጋጋሚ የሰው ልጅ መከራ እንደሚደርስበት፣ የሞት ፍርድ በሚፈርዱበት በአሕዛብ እጅ ተላልፎ እንደሚሰጥ ከዚያም በሚያፌዙበትና በሚዘብቱበት አይሁድ እጅ ውስጥ እንደሚገባ በመጨረሻም ከሞተ በኋላ በሦስተኛው ቀን እንደሚነሣ ተናግሮ ነበር፡፡ ጌታችን ክርስቶስ መከራውንና ነገረ ሞቱን መናገር የጀመረው በደብረ ታርቦር ተራራ ብርሃነ መለኮቱን ከገለጠ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ሲወጡ ነበር፡፡ ‹‹ከተራራውም ሲወርድ የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሣ ድረስ ያዩትን ለማንም እንዳይናገሩ አዘዟቸው›› (ማር 9፡9) ማቴ 16፡21 ፣ ማቴ 20፡18 ፣ ማር 10፡33 ፣ ሉቃ 18፡31 ወደ ገሊላም ሲሄዱ በተለያየ አጋጣሚ ይነግራቸው ነበር፡፡
በመጨረሻም ግን የጸሎተ ሐሙስ ዕለት በድጋሚ አስረግጦ ነገራቸው ሐዋርያትም አዘኑ
1.  ስለ ራሳቸው አስበው አዘኑ፣ ሁሉን ትተን ተከትለነው ይሾመናል ይሸልመናል ስንል ጥሎን ሄደ ብለው አዘኑ (ማቴ 20፡20)
2.  ስለ ፍቅር ስለ ትህትናው አዘኑ፣ ጌታችን ምንም እንኳን የሰውን ሥጋ ለብሶ በመካከላቸው ቢመላለስም በጥንተ ተፈጥሮ ፈጣሪያቸው አባታቸው ከመሆኑም ባሻገር በመካከላቸው በተመላለሰበትም ዘመን የእጁን ተአምራት አይተዋል፣ የቃሉን ትምህርት ሰምተዋል፣ አበርክቶ መግቧቸዋል በመከራ በማዕበል ሰዓትም አጽናንቷቸዋልና እንደ ጓደኛም እንደ መምህርም ሲለያቸው አዘኑ
3.  ጥሪያቸውን አላወቁም ነበርና አዘኑ፣ ቅዱስ ጴጥሮስ ሐዋርያቱን ወክሎ ሁሉን ትተን የተከተልንህ እኛ እንግዲህስ ምን እኛገኝ ይሆን? ብሎ ጠይቋል፡፡ (ማቴ 19፡28) ጥሪያቸው ለምድራዊ መንግስት ሳይሆን ለሰማያዊ እንደነበር አላስተዋሉምና አዘኑ
4.  ‹‹ሞቱን እንጂ ትንሣኤውን አላስተዋሉም አላመኑም ነበርና አዘኑ››

‹‹የሰው ልጅ በሰዎች እጅ ተላልፎ ይሰጣል ይገድሉታልም በሦስተኛውም ቀን ይነሣል›› (ማቴ 16፡21) ነበር ያላቸው ፡፡ እንዲሁም ‹‹ከተነሣሁ በኋላ በገሊላ እቀድማችኋለሁ ብሏቸው ነበር›› ማር 14፡28 ከዚህም በተጨማሪ የዮናስን ምልክት መሆን በምሳሌ ገልጦላቸው ነበር (ማቴ 12፡38) ነገር ግን መጻሕፍትን ባላማስተዋላቸው አዘኑ እሱ ግን ‹‹ሐዘናችሁ ወደ ደስታ ይቀየራል፣›› ዮሐ 16፡20 በማለት በምሳሌ አጽናናቸው ‹‹ሴት ልጅ ልትወልድ በቀረበች ጊዜ ታዝናለች (ምጥ ያስጨንቃልና) ከወለደች በኋላ ግን ኀዘኗ ወደ ደስታ ይለወጣል›› (ማቴ 16፡21)
ሊቀ ካህናቱና ፈሪሳውያን ግን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ትንሣኤው የተናረውን አውቀው ወደ ጲላጦስ ቀረቡና እንዲህ አሉት ‹‹ገዥ ሆይ ያ አሳች ገና በሕይወቱ ሳለ ከሦስት ቀን በኋላ እነሣለሁ እንዳለ ትዝ አለን እንግዲህ ደቀ መዛሙርቱ መጥተው በሌሊት እንዳይሰርቁት ለሕዝቡም ከሙታን ተነሣ እንዳይሉ የኋለኛይቱ ስህተት ከፊተኛይቱ የከፋች ትሆናለችና መቃብሩ እስከ ሦስት ቀን ድረስ እንዲጠበቅ እዘዝ አሉት›› (ማቴ 27፡62-64)
አይሁድ ‹‹ፊተኛይቱ ስሕተት›› ብለው ቅጽል ከሰጡትና ክርስቶስ ከሰጣቸው መመሪያዎች ይልቅ ትንሣኤው በእነርሱ ላይ አደጋ የሚያመጣባቸው መስሎ እንዲታያቸው ያደረጋቸው አስፈሪ ክፉ ትዕይንት ምንድን ነው?
የክርስቶስ ትንሣኤ የእርሱን እውነተኛነት ያረጋገጠና ትንቢቶች ሁሉ እውነተኛ መሆናቸውን የገለጠ ነው ትንሣኤው እርሱ ኃያል መሆኑን አረጋግጧል፡፡ መከራ ስቅላት የደረሰበትም የሰው ልጆችን ሁሉ ለማዳን እንጂ ደካማ ስለሆነ አልነበረም እነዚህ ሁሉ ነገሮች ሰዎች በእርሱ ላይ የበረታና የጠበቀ እምነት እንዲኖራቸው መርተዋል፡፡
ስለሆነም አይሁድ የክርስቶስን መነሣት ለመቃወም የሚችሉትን ጥንቃቄ ሁሉ አድርገዋል፡፡ ሌላው ቢቀር በመቃብሩ መግቢያ ላይ ትልቅ ድንጋይ በማንከባለል ገጥመውት ሄደዋል፡፡ እነርሱ በድንጋይ ላይ ማኅተም በማድረግ መቃብሩ እንዲጠበቅ ከማድረጋቸውም ሌላ ጠባቂ ዘበኞች አስቁመዋል፡፡ (ማቴ 28፡66) የሚገርመው ግን ይህን ሁሉ ከመዘጋጀት ቀን በኋላ በሰንበት ምሽት በማድረጋቸው ምንም አላፈሩም ነበር፣ መድኀኒታችን ክርስቶስ የዓይነ ሥውሩን ዓይኖች በሰንበት ቀን ስለፈወሰ ግን ከሰውት ነበር›› (ዮሐ 9፡14-16) ዳሩ አበው በምሳሌ በሞቀ ውሃ መታጠብና በሰው መፍረድ ቀላል ነው ይሉ የለ፡፡
ትንሣኤውን በመቃወም የተከናወነው እያንዳንዱ ድርጊት ትንሣኤው ለመገለጡ ማስረጃና ምስክር ከመሆኑም ባሻገር በድንጋይ ላይ የታተመው ማኅተምና በባዶው መቃብር ደጃፍ ላይ የቆሙት ጠባቂዎች የክርስቶስ ትንሣኤ እውነት መሆኑን አረጋግጠዋል፣ በመሆኑም ጌታችንና አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን መካከል በታላቅ ኀይልና ሥልጣን ተለይቶ ተነስቷል፡

በትንሣኤውም
1.  የቤተ ክርስቲያንን ምሥረታ እውን አድርጓል
የጥብርያዶስ ባሕር፣ ቤተ ኢያኢሮስ፣ የሰማይ መንግስት ኤምባሲ፣ የክርስቶስ እንደራሴ የታላቁ ንጉሥ ሙሽራ ሕዝቦችን ለድኀነት የምትጠራ ቤተክርስቲያን ለመመስረት የበቃችው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት በመነሣቱ ነው፡፡ እርሱ ከሞት ባይነሣ ኖሮ የቅርብ ተከታዮቹ ተስፋ ቆርጠው ወደ ቀድሞ ተግባራቸው በተመለሱ ነበር (ዮሐ 21፡1-7) አማንያንም በተበተኑ ነበር ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን አስረግጦ ሲያስተምር ‹‹ትንሣኤ ሙታንስ ከሌለ ክርስቶስ አልተነሣም ክርስቶስ ካልተነሣ እንግዲያስ ስብከታችን ከንቱ ናት እምነታችንም ደግሞ ከንቱ ናት እስካሁንም ድረስ በኀጢዓታችን ነን፣ በክርስቶስ ያንቀላፉትም ጠፍተዋል በዚች ሕይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ያደረግን ከሆነ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን : አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፊት በኩራት ሆኖ ተነስቷል›› (1ቆሮ 15፡12-20)
በመሆኑም የጌታችን መነሳት አንዲት መንፈሳዊት አስተዳደር በምድር ተቀምጦ የሰማይ ይለፍ (ቪዛ) የምትሰጥ ቤተ ክርስቲያንን ወልዷል፡፡
2.  አንገታችንን ቀና አድርገን እንድንሄድ ረድቶናል
 በጌታችን ትንሣኤ ነውራችን ተንከባሏል ኀፍረታችን ተወግዷል ዓለም ብዙ ክርስቶሶችን ይዛ ብዙ የእምነት ድርጅቶችን ፈብርካለች ነገር ግን ማንም እንደ እውነተኛው ክርስቶስ በቃሉ የተገኘ የለም፣ ማንም በክርስቶስ ደም እንደተመሠረተችው በትንሣኤው ምሥረታዋ እውን እንደሆነው እንደ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ንጽሕት ቅድስት የለም፡፡
የሁሉም የእምነት ድርጅቶች መሥራች ከመቃብር በታች ሥጋቸው በስብሷል አጽማቸው ፈርሷል
·         መካ መዲና ብንሔድ የእስልምናው መስራች የመሐመድ አጽም በመቃብር ውስጥ ነው
·         ወደ ሕንድ ወይም ፓኪስታን ብንሔድ የሒንዱና ሲክ መስራቾች የነራጂፋ ጋንዲ ወይም የሌሎች አጽም ከመቃብር በታች ነው
·         ወደ ጃፓን ወደ ቻይና ብንሔድ የቡድሐ እምነት መስራች የነ ሽንቶንና ሌሎችም አጽም ከመቃብር በታች ነው፡፡
ወደ ኢየሩሳሌም ጎልጎታ ግን ብንሔድ ግን የኛ ጌታ መድኀኔዓለዘም በመቃብር ውስጥ የለም፣ መቃብሩ ባዶ ነው ‹‹እንደ ተናገረ ተነስቷል›› (ማቴ 28፡6) በየትኛውም ዘመን ሊሰበክ የሚገባው ልዩ የስብከት ርዕስ የማይጠፋ የማይደበዝዝ እውነት ይህ ነው፡፡
በዘብዙ ፍርሃቶች ለደቀቀው ለዛሬው ትውልዳችን የቤተ ክርስቲያን ድምጽ ‹‹ክርስቶስ ከሙታን መካከል ተነስቷል›› የሚል ነው ትንሣኤው የአንድ ታለቅ እውነት ማረጋገጫ ነው እርሱም የመዳናችን ማኅተም ነው፡፡
3.   ለደካሞች ኃይልን ሰጥቷል
የደካሞች ትልቅ ብርታታቸው ኀያል አምላክ እንዳላቸው ማመን ነው አዎ አምላካችን ኃያል ገናና ትልቅ ነው፡፡ ለደካሞች ሁሉ ትምክህት ሊሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ተነሥቷል ሐዋርያው ጴጥሮስ ቀድሞ ፈሪ ስለነበረ በአንዲት ገረድ ፊት እንኳ ሳይቀር ክርስቶስን ክዷል፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ከተነሣ በኋላ ግን በመንፈስ ቅዱስ ሙላት በሦስት ሺህ ሕዝብ ፊት የኢየሱስ ክርስቶስን አዳኝነትና አምላክነት መስክሯል (ማቴ 26፡69፣ ሐዋ 2፡14-42) የክርስቶስ ትንሣኤ በእውነት ለደካሞች ኃይልን ሰጥቷል፡፡
4.  ለእውነት ዋጋ ለመክፈል ኃል ሆኗል
የጌታ ትንሣኤ ወደ እውቀት ደረጃ ከፍ የሚያደርግ ሳይሆን ወደ እምነት ደረጃ ከፍ የሚያደርግ ነው፡፡ ብዙዎች እውነትን የሚወዷት ዋጋ ካላስከፈለች ብቻ ነው የትንሣኤው ኃይል ግን ለእውነት ዋጋ ለመክፈል የብዙዎችን ልብ አጠንክሯል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ባይነሣ ኖሮ ደቀመዛሙርቱ ለስብከት ባልወጡ በአደባባይም በድፍረት ባልቆሙ ነበር፡፡ ሐዋርያው ጴጥሮስ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ባይነሣ ኖሮ በሮም አደባባይ የቁልቁሊት ባልተሰቀለ ነበር እውነት ላልሆነ ነገር ራሱን አይሰጥም ነበረና ክርስቶስ ባይነሣ ኖሮ ደቀመዛሙርቱ ሁሉ የሰይፍ ስለትን ባልተጋፈጡ ነበር አዎን ኢየሱስ ክርስቶስ ተነስቷል፡፡
 

5.  የእኛን ትንሣኤ አብስሯል
የሰው ልጆች ሁሉ በሞት ፍርሃት ውስጥ ይኖሩ ነበረ በመቃብር ላይ ሲኦል፣ በሥጋ ሞት ላይ የነፍስ ሞት ተፈርዶባቸው ይኖሩ ነበረ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ኃይለኛውን ጥሎ ሞትን ድል አድርጎ በመነሣቱ ታሪካችን ከመቃብር በላይ ጉዞአችንን ከሲኦል በላይ አድርጎታል፡፡ ትነሣኤው የነፍስን አርነት ብቻ ሳይሆን ሥጋንም ለዘላለም የመቃብር ግዞተኛ ሆና እንዳትቀር ያደረገ ነው፡፡
ስለዚህም የሥጋ ሞት ትርጉሙ መጥፋት ሳይሆን የአድራሻ ለውጥ፣ ዕረፍት ደግሞም ማንቀላፋት ነው የተባለው በትንሣኤ ነው ኢየሱስ ክርስቶስ የተነሣው የእሱን ኃያልነት ለማሳየት ሳይሆን የእኛን ትንሣኤ ለማብሰር ነው፡፡ (1ቆሮ 15፡20) እርሱ በሥልጣኑ ተነስቷል፡፡ እኛ ደግሞ በእርሱ ሥልጣን እንነሣለን ፈርሰን በስብሰን አንቀርም ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ሁሉ በኩር (ቀዳሚ) ሆኖ ተነስቷል እኛም የሚፈርሰው አካላችን የማይፈርስ ሆኖ ሞት የሰለጠነበት ማንነት በሕይወት ገኖ ይነሣል (2 ቆሮ 5፡1-5)
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሣኤው ያሸነፈው ጊዜያዊ ጠላትን ሳይሆን ዘላለማዊ ጠላትን በሰው ጥበብና ኃይል የማይረታውን ሞትን ነው ታላላቅ ግዛቶችን ያስተዳደሩ ታላላቅ ነገስታት ሞትን መግዛት አልቻሉም ሁሉንም ገዛቸው እንጂ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ሞትን ድል አድርጎ ተነሣ፡፡ የታላላቅ ሃይማኖት መሪዎች ሁሉ መቃብራቸው አጽም አለበት የኢየሱስ ክርስቶስ መቃብር ግን ባዶ ነው፡፡ ተነስቷል ተነስቶም በክብር አርጓል የሰው ልጆች ዕውቀት መጠቀ በሚባልበት በዛሬው ዘመን ጠቢባን ሰውን በቤተ ሙከራ ለመሥራት ሲያስቡ የሞትን መድኀኒት ለመሥራት ግን አስበውም አያውቁም ይህ የሚያሳየው ሞት የጠቢባንና የነገሥታት አእምሮ ሳይቀር የገዛ መሆኑን ነው ሁሉም የተሸነፈለት ሞት ግን በክርስቶስ ትነሣኤ ድል ተነስቷል፡፡ የአካል ብቻ ሳይሆን የኅሊናም ገዥ ወይም ፍርሃት ሆኖ የኖረው ሞት በጌታችን ትንሣኤ ማን ሞትን ይክፈለው? ብለው ተመኝተው ነበር ለሞትም ሞትን የከፈለው የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ለዘመናት ሁሉ መቃብር በር የለውም ተብሎ ታውጆ ነበር በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ግን መቃብር በር አግኝቷል ዛሬ ፍርሃት የሆኑብን ባለጋሮች ከሞት ይልቅ ኃይለኞች አይደሉም እንኳን እነሱን ሞትን ባሸነፈ ጌታ ስለምናምን አንፈራቸውም፡፡ ሞት ለዘመናት በሰዎች ላይ በድል ፎክሯል እኛም በተራችን በሞት ላይ ፎክረናል ‹‹ሞት ሆይ መውጊያህ የታለ?›› ሲኦል ሆይ ድል መንሳትህ የታለ?›› (1ቆሮ 15፡55)
በሞት ላይ በድል እንድንዘምር ያደረገን የጌታችን ትንሣኤ ነው ብርቱ የሆነው ሞት ሳይሆን የበረታው ፍቅር ነው፡፡ ለዘላለም የክርስቶስ ፍቅር እንደበረታ ይኖራል እምነታችን በሞት ሳይሆን ሕያው በሆነው በእግዚአብሔር ልጅ ፍቅር ነው፡፡
እርሱ እንዳይነሣ ቋጥኝ ተገጠመ፣ የሮማ ምርጥ ወታደሮች ዘብ ቆሙ ጉቦ ተከፈለ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የነገስታት ማኅተም ያረፈበትን መቃብር ድል ነሥቶ ወጣ ዛሬም እንዳይነሣ ስሙ እንዳይጠራ ዘብ የቆሙ ብዙዎች ቢሆኑም ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ሞትና የሞት ልጆች ላይዙት ለዘላለም ተነስቷል ጠላት ቢከፋውም እርሱ ስም ይከብራል፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሞት ስለተነሡ ስለ ብዙ ሰዎች ተጽፏል ታዲያ የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው? ስንል እነዚያ ሁሉ ቢነሡ ዳግመኛ ሞተዋል ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ዳግመኛ ሞት ላይዘው ተነሥቷል (ሮሜ 6፡9) እነሱ አስነሺ አላቸው ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በራሱ ኃይልና ሥልጣን ከሙታን መካከል ተለይቶ ተነሥቷል፡፡ ሲነሣም መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል መቃብሩ እንደተዘጋና እንደታተመ ተነሥቷል፡፡
እርሱ ከብላቴናዋ ከድንግል ተወለደ፣ በከብቶች በረት ተጣለ የእንሰሳትን ትንፋሽ ሞቀ፣ ራሱን የሚያስጠጋበት ቤት አጥቶ ተንከራተተ በተውሶ ጀልባ ተጓጓዘ፣ በመጨረሻም በተውሶ መቃብር ተቀበረ እኛን ሊያበለጽግ በሁሉ ደሃ ሆነ፡፡ ከትንሣኤው በኋላ ግን በማይጨበጥ ኀይል ሊመዘን በማይችል ብልጥግና ሊነገር በማይችል ልዕልና ለዘላለም ይኖራል፡፡

No comments:

Post a Comment