Thursday, April 24, 2014

‹‹መሳለቂያ እንዳንሆን ተነስተን የኢሩሳሌምን ቅጥር እንስራ›› (ነህ 2፡17)




ይህንን ቃል የተናገረው እስራኤላዊው ነህምያ ሲሆን ዘመኑ የኢየሩሳሌም ቅጥር የፈረሰበት ምድሯ ምድረ በዳ ሆኖ ቤተልሔም ቂያ በቅሎባት ዳዋ ለብሳ አራዊት የሚፈነጩባት ባድማ የሆነችበት ጊዜ ነበር፡፡
ሕዝበ እግዚአብሔር የተባሉ እስራኤል በያዕቆብ ልጅ በዮሴፍ ምክንያት ሀገራቸውንና ርስታቸውን ትተው ወደ ግብጽ ሀገር ተሰደው ወልደው ከብደው በዝተው ይኖሩ ነበረ፡፡ እግዚአብሔርም ከዮሴፍ ጋር ስለነበር ዮሴፍ በነበረበት ዘመን ሁሉ በደስታ ኖሩ፡፡
ዮሴፍ ከሞተ በኋላ ግን ዮሴፍን የረሣ ንጉስ ተነሣና እስጨነቃቸው ለአራት መቶ ሠላሳ ዓመትም በባርነት ከኖሩ በኋላ ወደ እግዚአብሔር በመጮሃቸው ተአምራትን አድርጎ ባሕርን ከፍሎ ውሃውን እንደ ሣር ክምር እንደ ግርግዳ አቁሞ በደረቅ መሬት አሻግሮ ማርና ወተት የምታፈሰውን ርስታቸውን ከነዓንን አወረሳቸው፡፡ በከነዓን ምድር እፎይ ብለው በሰላም መኖር ጀመሩ ዘመናት ነጎዱ ጊዜያት ተቀየሩ ትውልድ ሁሉ ወደ አባቶቻቸው ተከማቹ (መሳ 2፡10) እግዚአብሔር ለአባቶቻቸው ያደረገውን ውረታ የረሳ ትውልድ ተነሣ፡፡ አዲሱ ትውልድ ታሪክን ዘንግቶ የአባቶቹን የሙሴንና የኢያሱን አደራ አቃሎ ጣዖትን አመለከ፣ በኃጢዓት ተከሰ፣ በሥነ ምግባር ብልሹነት ከአሕዛብም የከፋ ሥራን ሰሩ በዚህ ጊዜ ነበር እግዚአብሔር ጨካኞችንና ክፉዎችን ከለዳውያንን አስነስቶ ብዙዎችን በሰይፍና በረሃብ ከዚያም የተረፉትን በባቢሎን በግዛት በስደት ቀጣቸው፡፡ ኢየሩሳሌምም ቅጥሯ ፈረሰ ቅርሶቿ ተመዘበሩ በባድማ ሆነች ሽማግሌዎቿንና አሮጊቶቿን ሴቶችና ሕጻናቶቿን በግፍ ተነጠቀች (2ነገ 36፡11-23)
ሐዋርያው ጳውሎስ ሌላውን ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ነገር ነው (2ቆሮ 11፡28) እንዲል ሃያ ዓመታትም ካለፉ በኋላ የኢየሩሳሌም ቅጥር መፍረስ ያስጨነቃቸው ደጋጎች አባቶች ስለራሳቸውና ስለ ሕዝቡ ኃጢዓት መስዋዕትን እያቀረቡ እግዚአብሔርን ይማጸኑ ነበር፡፡ (ነህ 1፡5-11) ከነዚህ ቅዱሳን አባቶች መካከል አንዱ ነህምያ ነው ነህምያ ምንም እንኳን በተሰደደበት በባዕድ ሀገር በንጉሥ ቤት በጠጅ አሳላፊነት ተቀጥሮ (ነህ 1፡11) በምቾት ቢኖርም የአባቶቹን ርስት ግን አልረሳም ‹‹ነቢዩ ዳዊት ኢየሩሳሌም ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ ባላስብሽ ምላሴ ከትናጋዬ ትጣበቅ›› እንዲል ነህምያ ጊዜ የሰጠውን እግዚአብሔርን ተስፋ አድርጎ ከሃያ ዓመት በኋላ የፈረሰውን ሊሠራ መንፈሱን አበርትቶ ተነሳ፡፡ በሀገሪቱ ለወሬ ነጋሪ ከመከራና ከሰቆቃ የተረፉትን ሰዎች ስለ ኢየሩሳሌም ሁኔታ ባጠያየቀ ጊዜ ‹‹በዚያ ሥፍራ ያሉት ከምርኮ የተረፉት ቅሬታዎች በታላቅ መከራና ስድብ ላይ እንደሆኑ የኢየሩሳሌምም ቅጥር እንደፈረሰ በሮቿም በእሳት እንደተቃጠሉ ነገሩት›› (ነህ 1፡3) ይህንንም በሰማ ጊዜ ነህምያ ተቀመጠ አለቀሰ አያሌ ቀንም አዘነ፣ በሰማይ አምላክም ፊት ይጾምና ይጸልይ ነበር (ነህ 1፡4) ከዚህ በላይ ምን ሐዘን አለ ከእናት ሞት በላይ ምን መከራ አለ በመሆኑም ነህምያ ስለ ኢየሩሳሌም አዘነ፡፡
ኢየሩሳሌም የቤተክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ በኢየሩሳሌም ማርና ወተት እንደሚፈስ በቤተክርስቲያን በማር የተመሰለ ብሉይ ኪዳን በወተት የተመሰለ ሐዲስ ኪዳን ይነገርባታል፡፡ በኢሩሳሌም ጌታ የተወለደባት ቤተልሔም እንዳለች በቤተክርስቲያን የአማናዊው ሕብስት (እንጀራ) ምንጭ ቤተልሔም አለች፡፡

አንድም በኢሩሳሌም መድኀኒታችን ሰላማችን የወለደችው የድንግል ማርያም ምሳሌ የሆነች ቤልሔም እንዳለች በቤተክርስቲያን የአማናዊው ሕብስት (እንጀራ) ምንጭ የሆነችው ቤልሔም አለች፡፡ ‹‹ቤተ ክርስቲያን ለሰማያዊው መንግስት መግቢያ ቪዛ የምትሰጥ ምድራዊት አምባሳደር የሰማያዊው ኢየሩሳሌም ምሳሌ ነች ማንኛውም ክርስቲያን ከምድራዊው ወደ ሰማያዊው ቤት ለማለፍ በዚች ቤክርስቲያን የይለፍ ማግኘት ይኖርበታል ቤተክርስቲያን በሚታይ አገልግሎት የማይታይ ጸጋ የሚሰጥባት የእግዚአብሔር የጸጋው ግምጃ ቤት ናት፣ ከጸጋ የተራቆተ ጸጋ የሚለብስባት ጽድቅን የተጠሙ ጠጥተው የሚረኩባት ምንጭ ናት (ኢሳ 55፡1)
ቤተክርስቲያን ከጥቂቱ ማዕድ ብዙዎች ከእግዚአብሔር በረከት ተመግበው የሚጠግቡባት የጥብርያዶስ ባሕር ናት (ማቴ 14፡15) ቤተክርስቲያን ዓይነ ሥውሮች የሚበሩባት፣ ለምጻሞች የሚነጹባት ሙታን የሚነሱባት ቤተ ኢያኢሮስ ናት (ማቴ 9፡24) ቤተ ክርስቲያን ዘማዊ ድንግል፣ ቀማኛውና ሌባው መጽዋች የሚሆንባት ቤተ ዘኪዮስ ናት (ሉቃ 14፡1)
ቤተ ክርስቲያን ሰላም ላጡ ሰላምን፣ ዕረፍት ላጡ ዕረፍትን ላዘኑ መጽናናትን የምታስገኝ የመጽናናት የበረከት ተራራ ከመሆኗም ባሻገር የቱሪስት መነኻሪያ ሥፍራ የኢኮኖሚ ምንጭ በመሆን የሀገርና የወገን ቅርስ ናት፡፡
ነገር ግን ይህን ሁሉ አስተባብራ የያዘች ተቋም ስትወድቅ የሚያነሳ መብቷ ሲነካና ስትጠቃ አለሁ ባይ ተቆርቋሪና ተጠያቂ አካል በማጣት ቅርሷ ሲመዘበርና ሲፈርስ የፈረሰውንም የሚጠግን የተመዘበረውን የሚያስመልስ ጠበቃ እያጣች በተለያዩ ጊዜያት በደል ሲደርስባት ይስተዋላል፡፡
ከዚህም የተነሣ ቅጥሯ ሲፈርስ መንገድ ኃላፊው ሁሉ ሰብሏን ይቀጥፋል፣ የዱር እርያም ያረክሰዋል የአገር አውሬም ይሰማራባታል፣ አሕዛብም ወደ ርስቷ ገብተው የቅድስናውን መቅደስ ያረክሳሉ (መዝ 78፡1 ፣ መዝ 79፡12)
በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በተለይ በገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍል ከንዋያተ ቅዱሳት ዕጥረት የተነሣ የተዘጉ በዘመን ማርጀትና በገንዘብ እጦት ምክንያት ሙሉ በሙሉ የፈረሱ አለበለዚያም በከፊል ፈርሰው ዝናብና ፀሐይ እየተፈራረቀባቸው አገልግሎት የሚሰጡ በርካታ አቢያተ ክርስቲያናት አሉ፡፡
አሁን እንደ ነህምያ የቤተክርስቲያን ቅጥር መፍረስ ሊያስጨንቀንና ግድ ሊለን ይባል፣ ነህምያ የሀገሩንና የርስቱን ክፉ ጊዜ ከሰማ በኋላ ሐዘንተኛ ሆነ ከልቡም ሐዘን የተነሳ ፊቱ ጠቆረ ገረጣ ‹‹ቀድሞ ግን በንጉሡ ፊት ያለ ሐዘን ይኖር ነበርና ንጉሡም ሳትታመም ፊትህ ለምን አዘነ? ይህ የልብ ሐዘን ነው እንጂ ሌላ አይደለም አለው›› (ነህ 2፡1)
ነህምያ ንጉሥን አስፈቅዶ ደብዳቤ አጻፈ የሚያስፈልገውንም ዕርዳታ ይዞ የፈረሰውን የኢየሩሳሌም ቅጥር ለመሥራት ሕዝቡን ያስተባብር ዘንድ ወደ ሀገሩ አቀና፡፡

ሕዝቡንም ሰብስቦ እንዲህ ሲል ነገራቸው ‹‹እኛ ያለንበትን ጉስቁልና ኢየሩሳሌም እንደፈረሰች በሮችዋም በእሳት እንደተቃጠሉ ታያላችሁ አሁንም ከእንግዲህ ወዲህ መሳለቂያ እንዳንሆን ተነሥተን የኢሩሳሌምን ቅጥር እንስራ የአምላኬ እጅ በእኔ ላይ መልካም እንደሆነች ንጉሡ የነገረኝን ቃል ነገርኋቸው›› (ነህ 2፡17)
ሕዝቡም እንነሳና እንስራ አሉ፣ እጃቸውንም ለበጎ ሥራ አበረቱ ሐሮናዊው ሰንበላጥ ባሪያውም አምናዊው ጦቢያ ዓረባዊውም ጌሳም በሰሙ ጊዜ በንቀት ሳቁበት ከዚህም አልፈው በጎ ሥራውን ያደናቅፉ ዘንድ ክፉ ወሬን በማስወራት በጠላትነት ተነሱበት ነህምያ ግን እግዚአብሔርን አስቀድሞ እንዲህ በመጸለይ ‹‹አቤቱ የሰማይ አምላክ ሆይ ለሚወዱህና ትዕዛዝህን ለሚያደርጉ ቃል ኪዳንና ምህረትን የምትጠብቅ ታላቅና የተፈራህ አምላክ ሆይ እኔ ባሪያህ ዛሬ በፊትህ ስለ ባሪያዎችህ ስለ እስራኤል ልጆች ሌሊትና ቀን የምጸልየውን ጸሎት ትሰማ ዘንድ ጆሮህን አድምጥ ዓይኖችህም ይከፈቱ በአንተ ላይም ያደረግነውን የእስራኤል ልጆች ኃጢዓት እናዘዝልሃለሁ እኔና የአባቴም ቤት በድለናል እኛም በአንተ ላይ እጅግ ክፉ ሠርተናል ለባሪያህም ለሙሴ ያዘዝከውን ትዕዛዝና ሥርዓት ሕግም አልጠበቅንም አሁንም ብትተላለፉ በአሕዛብ መካከል እበትናእኋለሁ ወደ እኔ ብትመለሱ ግን ትዕዛዜንም ብትጠብቁ ብታደርጓትም ከእናንተ ሰዎች እስከ ሰማይ ዳርቻ ድረስ ምንም ቢበተኑ ከዚያ እሰበስባቸዋለሁ ስሜም ይኖርበት ዘንድ ወደ መረጥሁት ስፍራ አመጣችዋለሁ ብለህ ለባሪያህ ለሙሴ ያዘዝከውን ቃል እባክህ አስብ እነዚህም በታላቅ ኃይልህና በብርቱ እጅህ የተቤዥሃቸው ባሪያዎችህና ሕዝብህ ናቸው ጌታ ሆይ ጆሮህ የባሪያህን ጸሎት ስምህንም ይፈሩ ዘንድ የሚወድዱትን የባሪያዎችህን ጸሎት ያድምጥ ዛሬም ለባሪያህ አከናውንለት ምህረትንም ስጠው›› (ነህ 1፡5-11) ብሎ ነበርና የተነሣው ‹‹የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል እኛ ባሪያዎቹ ተነስተን እንሰራለን ብሎ ተነሥቶ የኢየሩሳሌምን ቅጥር እንደገና ሰራ››
ነቢዩ ዳዊት ‹‹ለጎረቤቶቻችን ስድብ ሆንን በዙሪያችንም ላሉ ሳቅና ዘበት›› (መዝ 79፡4) ይላልና እኛም መሳቂያ መሳለቂያ እንዳንሆን የፈረሰውን መቅደሳችንን አቅማችን በሚችለው ሁሉ ተነስተን እንስራ ለዚህም ከሁሉ አስቀድመን የእግዚአብሔርን ፈቃድ በጾምና በጸሎት እንጠይቅ ምናልባት ለአንዱ ሰው ከባድ መስሎ የሚታየው በአንድነት ሆነን በምንችለው አቅም ከተነሳን አበው ለሺህ ፍልጥ ማሰሪያው ልጥ ይላሉና በተባበረ እጅ በፍቅር ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ አድርገን ከተነሣን አይደለም የፈረሰውን መጠገን አዲስ መገንባት እንችላለን፡፡
በመሆኑም መሳለቂያ ላለመሆን

1.  ጀማሪዎች ብቻ አንሁን
በጎ ነገር ጥረትና ትጋት ይጠይቃል ከምንም በላይ መልካም ስራ ፈተናና እንቅፋት ስለሚኖርበት ጥበብና ትዕግስት ይጠይቃል ነህምያ ስራውን ሲጀምር ሰንበላጥና ጦቢያ በንቀት ተነስተው ተሳልቀውበታል የእንቅፋት ድንጋይም አስቀምጠዋል ከዚህ አልፎ ተርፎ በሕይወቱ እንኳ ሳይቀር በሕልውናው ላይ መጥተውበት ነበር (ነህ 6፡1-3) ነገር ግን ፈተናውን ሁሉ አልፎና ተቋቁሞ በመጽናት የፈረሰውን የኢየሩሳሌም ቅጥር ሠርቷል፡፡ ዛሬ ብዙ ሰዎች በጎ ሥራን በስሜት ተነስተው ይጀምራሉ ለመፈጸም ግን ይንገዳገዳሉ ጀማሪም ሆነው ይቀራሉ፡፡
2.   ተናጋሪ ብቻ ሳይሆን የተግባር ሰዎች እንሁን
ነህምያ በልቡ ያሰበውን ከእግዚአብሔር ጋር ተነጋግሮ ከሕዝቡ ተማክሮ በተግባር ፈጽሞታል፡፡ በዚህ ባለንበት በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ብዙ የሚያወሩና የሚያስወሩ ችግርን የሚጠቁሙ ስህተትን የሚያንቆለጳጵሱ ብዙ ናቸው፡፡ ነገር ግን ለችግሮችና ለስህተቶች መፍትሔ የሚያዘጋጁ የፈረሱትን ለመሥራት ዕቅድን የሚያቅዱ ሰርተው የሚያሳዩ ሰዎች ፈልጎ ማግኘት አስቸጋሪ እየሆነ ነው አንዳንዶችም ከቁጥር የማይገባውን ጥቂቱን ሥራቸውን አግዝፈው ሲያነሱ ሲጥሉ ለተሸለ ሥራና ዕድገት ጥረት ሳያደርጉ ይቀራሉ፡፡
ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹ብዙዎች በጎነታቸውን ያወራሉ፣ መልካም የሆነውን ግን ማን ያገኘዋል›› ይለናል በመሆኑም ለመልካም ሥራ ተናጋሪ ብቻ ሳይሆን የተግባር ሰው ሰርቶ የሚያሰራ በዓላማው የጸና ሰው ያስፈልጋል፡፡ ‹‹ለበጎ ሥራም ለመነቃቃት በፍቅርና በህብረት መቆምን ግድ ይላል›› (ዕብ 10፡23)
3.  እጃችን ላይ ያለውን እንዳናስወስድ አጽንተን እንያዝ

አበው በምሳሌ ‹‹በእጅ የያዙትን ወርቅ እንደ መዳብ ይቆጥሩታል›› እንዲሉ ኢትዮጵያ ሀገረ እግዚአብሔር ‹‹የክርስቲያን ደሴት በመሆኗ›› ብዙዎቻችን እንስማማለን ይህም የሆነበት ክርስቲያኖች ብቻ የሚኖሩባት ሀገር ማለት ሳይሆን
·         ኢትዮጵያ እግዚአብሔርን ያላመለከችበት ዘመን የለም፡፡ በሦስቱም ሕግጋት በህገ ልቡና፣ በህገ ኦሪትና በህገ ወንጌል በአምልኮተ እግዚአብሔር ጸንታ የኖረች ሀገር ስለሆነች የክርስቲያን ደሴት ናት፡፡
·         በሌላው በዓለም ቅርስነት (UNESCO) ከተመዘገቡትም ሆነ ካልተመዘገቡት ነባራዊ ዕሴቶች በመነሳት ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት
·         በቱሪዝም የሀገር ገቢ የኢኮኖሚ ምንጭነት ቀዳሚውን ቦታ የሚይዙት ጥንታውያን አቢያተ ክርስቲያናት በመሆናቸው ኢትዮጵያን የክርስቲያን ደሴት ያሰኛታል፡፡
·         ቤተ ክርስቲያን የደን ሚኒስቴር በመሆን የሀገሪቱን የደን ሀብት በመጠበቅና የትምህርት ሚኒስቴር በመሆን ፊደል ቀርጻ ብራና ዳምጣ ትውልድን ስታስተምር የኖረችና እያስተማረች ያለች በመሆኗ የክርስቲያን ደሴት ናት
·         በሞራልና በሥነ ምግባር የታነጹ ለሀገርና ለወገን የሚጠቅሙ ኃላፊነትን የሚረከቡ ዜጎችን በማፍራት ቀዳሚውን ሥፍራ ይዛ የምትገኘው ተቋም ቤተክርስቲያን በመሆኗ ኢትዮጵያን የክርስቲያን ደሴት ያሰኛታል፡፡
ነገር ግን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ይህን እውነታ የሚቃወሙና የሚያዳክሙ ነገሮችና ሁኔታዎች እየተስተዋሉ መምጣታቸው ሁላችንም ከማስጋት አልፎ ትላንትና በግብፅና በኢሩሳሌም የሆነው ብኩርናን የመቀማት ክስተት በኢትዮጵያ የማይሆንበት ምንም ዓይነት ነገር የለም፡፡ የኤፌሶን ከተማ ትላንት እነ ቅዱስ ዮሐንስ (ሐዋርያ) እንዳልወጡበት እንዳልወረዱበት እነ ቅዱስ ጳውሎስ ደክመው ወንጌል እንዳልሰበኩባት ዛሬ የአሕዛብ መነኻሪያ ሆናለች፡፡ እኛም ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት፣ ይህን ያህል የክርስቲያን ብዛት አለን፣ በርካታ ታሪካዊና ጥንታዊ አቢያተ ክርስቲያናት አሉን ብለን እንዳላወራን ዛሬ የአሕዛብ ቤተ ጣዖት የቤተክርስቲያንን ቁጥር በእጥፍ እየበለጠ ነገር ከመገልበጡ በፊት በእጃችን ያለውን አሳልፈን እንዳንሰጥ ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ አድረግን በፈረሰው በኩል በፍቅርና በህብረት እንቁም መሳለቂያም እንዳንሆን ተነስተን የፈረሱትን ቅጥሮች እንስራ፡፡  

No comments:

Post a Comment