Saturday, November 30, 2013

"ስለ ጽዮን ዝም አልልም" (ኢሳ 62:1)




ይህንን የተናገረው ልዑለ ቃል ኢሳይያስ እግዚአብሔር የራቀውን አቅርቦለት የረቀቀውን አጉልቶለት ትንቢት በሚናገርበት ዘመን ሲሆን  ጽዮን የሚለው ስም እንደአገባቡ ይፈታል ልብስ በየፈርጁ እንዲለበስ የቅዱሳት መጽሐፍት ቃልም በስልት በስልቱ ይተረጉማል መጽሓፍ ቅዱስ በትርጉሜ ስልት ሲበለት መልክ መልክ አለው አንዱ ቃል እንደያገባቡ የተለያየ ትርጓሜ ይሰጣል በመሆኑም ከላይ በርዕሳችን የተጠቀሰው የነቢዩ ኢሳይያስ ትንቢት ብንመለከት ቃሉ ህብርነት ያለው ሆኖ ይገኛል ጽዮን የሚለው ቃል ኢየሩሳሌም ቤተክርስቲያን መንግስተ ሰማያት ወይም ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ ተብሎ ሊተረጎም ይችላል ኢየሩሳሌም ቤተእስራኤል (ቤተ ያዕቆብ) ቤተ መቅደስ ተብሎ የሚፈታበት ጊዜ አለ በሌላ ሥፍራ ደግሞ የቃሉ አገባብ ኢየሩሳሌም ድንግል ማርያም ወይም መስቀል ክርስቶስ ተብሎ ሊተረጎም ይችላል እንግዲህ አርዕስትን ተመልክቶ ስለምን እንደተነገረ በማስተዋል ካላዩት ካልመረመሩት በዘፈቀደ እንተርጉም ቢሉት ምስጢሩ ሊገኝ አይችልም ትርጓሜውም የተሳሳተ ይሆናል ከምሥጢር ዳህፅ(መሰናክል) ለመጠብቅ መጻሕፍት መመርመር መምህራንን ማነጋገር በጸሎት በትህትና እግዚአብሔርን ግለጽልን በማለት: ይህን ቃል የተለያየ ትርጉም እንዳለው ለማሳየት በምሳሌ እንመልከት:-


፩ኛ) ወደ ጽዮን ተራራና ወደ ሕይው እግዚአብሔር ከተማ ደርሳችኋል ( ዕብ 12፡22) ከዚህ ላይ የጽዮን ተራራ ያላት ሰማያዊት ኢየሩሳሌምን (መንግስተ ሰማያትን) ነው መንግስተሰማያትም የእግዚአብሔር ክብር ስለማያበራለት መብራቷም በጉ ስለሆነ: ፀሐይ ጨረቃ የሚያስፈልጋት ከተማ በመሬት ላይ የለችም ኢየሩሳሌም ወይም የዳዊት ከተማ የተባለችው ደብረ ጽዮን (የጽዮን ተራራ) አይደለችም ሰማያዊት ኢየሩሳሌም መንግስተ ሰማያት መሆኗን ያስተውላል በመሆኑም የጽዮን ኢየሩሳሌም መንግስተሰማያት ደብረ ጽዮን ወይም ኢየሩሳሌም ሰጥተን ብንተረጉም በምስጢር እንስታለን ፣ በትርጉም እንገድፋለን ፡፡
፪) ጽዮን የሚለው ቤተመቅደስን ነው; የቃል ኪዳኑ ታቦት በመቅደስ ይኖራልና በጽዮን ታቦተ ጽዮን መቅደሱም የጽዮን መቅደስ ተብሏል "የእግዚአብሔር ታቦት የገባበት ሥፍራ ሁሉ ቅዱስ ነው"(1መጽ ነገ   8፡11) እንዲሁም አቤቱ ለአንተ በጽዮን ምሥጋና ይገባል እንዲል ዳዊት በመዝሙሩ በጽዮን በተራራው: በጽዮን በቤተ መቅደስ ምሥጋና ይቀርባል ዝማሬ ይዘመራል ቅዳሴ ይቀደሳል ሰዓታትና ማህሌት ይቆማል ቃለ እግዚአብሄር ይነገራል ስብሀት እግዚአብሄር ይፈሳል በቤተመቅደስ ያዘኑ ይጽናናሉ ያለቀሱ እንባቸው ይታበሳል የተጨነቁ ይረጋጋሉ:: በቤተመቅደስ እግዚአብር:-
·     ስላደረገልን ነገር ሁሉ ምስጋና እናቀርብበታለን
ስለማይነገር ስጦታው እግዚአብሄር ይመስገን (2ቆሮ9፡15) አድርገህልናልና አመሰግንሀለሁ (መዝ 51፡9)
·     ለጥያቄዎቻችን መልስ እናገኝ ዘንድ ኃጢአታችን ይሰረይ ዘንድ ታሪካችን ይቀየርልን ዘንድ ወጥመዳችን ይበጣጠስልን ዘንድ ቀንበራችን ይሰበርልን እንቆቅልሻችንም ይፈታ ዘንድ ከእግዚአብሄር ዘንድ የምንነጋገርበት ሥፍራ የጽዮን ተራራ ቤተመቅደሱ ስለሆነ ልዑለ ቃል ኢሳይያስ ስለ ጽዮን ዝም አልልም ስለ ኢየሩሳሌም ( የሰላም ሀገር) ቤተ መቅደስም ጸጥ አልልም አለ
፫) ጽዮን የሚለው ቃል የሚያመለክተው ክርስቶስ ስለተሰቀለበት ዕፀ መስቀል ነው: በመመስገኛው ተራራ በጽዮን እነግሳለሁ ይላልና (መዝ 2፡6) መስቀሉን መንግስት አድርጎ በመስቀል ተቅሰሎ ሳለ የመንግስት ሥራ ሠርቷል ጌትነቱን አምላክነቱን አዳኝነቱን ገልጾበታል የመንገስት ሥራ በመስቀል ስለተሠራበት መስቀል ኃይልነ መስቀል ድንዕነ መስቀል ቤዛነ ይባላል መስቀሉንና የተተከለበትን ሥፋራ ደብረ ቀራንዮ ደብረ መቅደሱ የመመስገኛው ተራራ ይላቸው ከዚህ አስቀድሞ ጌታችን ለቤዛ ዓለም ሳይሰቀል በፊት በቀራንዮ ተራራ መላዕክት በቀትር እየመጡ ያመሰግኑ ይቀድሱ ነበር ጌታ በተሰቀለ ጊዜ እንደልማዳቸው ሊያመሰግኑ ቢመጡ ተሰቅሎ ቢያዩት ደንግጠው በመስቀሉ ዙሪያ እነደ ሻሽ ተነጥፈው እንደ ቅጠል ረግፈው "ለከ ኃይል" ኃያል መባል ይገባሀል ኃይል ለአንተ ይሁን "ለከ ጽንእ" ጽኑ ብርቱ መባል ይገባሀል ጽንዓት ብርታት ለአንተ ይሁን እያሉ አመስግነውታል ፡፡


-በሌላው ዳዊት አምባይቱን ጽዮንን ያዘ እርሷም የዳዊት ከተማ ናት (2ሳሙ 5:7)" እንዲኁም ዳዊትም ኄዶ የእግዚአብሄርን ታቦት ከአቢዳራ ቤት ወደ ዳዊት ከተማ አመጣው ተብሎ እንደተጻፈ የጽዮን ተራራ (አምባ) የተባለችው ሰማያዊት ኢየሩሳሌም አይደለችም በቁሙ ዳዊት የነገሠበት መናገሻ ከተማው ናት እንጂ(2ሳሙ6:12)
በመሆኑም ነቢዮ ኢሳይያስም ቅጥርዋ ፈርሶ ውስጧ ተመዝብሮ ሕዝቧ ተማርኮ ወደ ፋርስ ባቢሎን ምድር ወርደው ሀገሪቱ ባድማ ሆና ነበርና ከእንግዲህ ወደህ የተተወ አትባይም ምድርሽም ከእንግዲህ ወዲህ ውድማ አትበል (ኢሳ 62:4) ሀገሪቷ ስትመዘበር ቅጥርዋ ሲፈርስ ብዙዎች ከሰይፍ የተረፉት በረሃብ ሲቀጡ በመንፈስ ተመልክቶ ስለ ጽዮን ዝም አልልም ስለ ኢየሩሳሌምም ጸጥ አልልም አለቅሳለሁ እጮሃለሁ በማለት ተናገረ;
፬) የቃል ኪዳኑን ታቦት ጽዮን ይለዋል (2ሳሙ6:12) በእግዚአብሄር ጣት የተጻፉ አስርቱ ትእዛዛት ያሉበት ሕዝቡንም ይባርክበት የነበረው የቃል ኪዳን ታቦት ኢያሱ ባህረ ዮርዳኖስን ለሁለት የከፈለበት ታቦት በኃላም የአቢዳራን ቤት የባረከችው ዳጎንን የሰባበረችው ታቦት ዳዊትም ከአቢዳራ ቤት ወደ ዳዊት ከተማ ወደ ጽዮን ስላመጣት ታቦቲቱም በጽዮን (በጽዮን ተራራ) ስላረፈች በቦታው ታቦተ ጽዮን ( የጽዮን ታቦት) ተብላለች (ዘጸ 3:18 ፣ ኢያ 3:14-17)
፭) "አቤቱ ስለፍርድህ ጽዮን ሰምታ ደስ አላት" (መዝ 96:8) በዚህ የመጽሕፍ ቅዱስ ክፍል ጽዮን ያላት በቁሙ የዳዊትን ከተማ ወይንም ኢየሩሳሌምን ከፍ ብሎም የእግዚአብሔርን ከተማ ኢየሩሳሌም ሰማያዊትን ነው ተብሎ ቢተረጎም ስህተት ነው ለምን ቢባል ቦታው ግእዕዛን የለውምና እንደ ሰው የደስታ ወይም የኃዘን ስሜት ተራራ; ከተማ ; ሰማይ እንደማይሰማቸው የታወቀ ነውና በመሆኑም ትክክለው ትርጉም ሲፈለግ የእግዚአብሔርን ፍርድ ሰምታ ደስ ያላት ጽዮን ማናት ቢሉ በቀጥታ ስለቤተ ያእቆብ ስለ ትሩፋን የተነገረ መሆኑን ማስተዋል ይቻላል፡፡



፮ኛ)   ጽዮን  የተባለችው ድንግል ማርያም ናት

"እግዚአብሔር ጽዮንን መርጦአታልና፥ ማደሪያውም ትሆነው ዘንድ ወድዶአታልና፥ይህች ለዘላለም ማረፊያዬ ናት፤ መርጫታለሁና በዚህች አድራለሁ።አሮጊቶችዋን እጅግ እባርካለሁ፥ ድሆችዋንም እንጀራ አጠግባለሁ። ካህናቶችዋንም ደኅንነትን አለብሳቸዋለሁ፥ ቅዱሳኖችዋም እጅግ ደስ ይላቸዋል።" በዚህ የመጽሕፍ ቅዱስ ክፍል ጽዮን ያላት ድንግል ማርያም ናት (መዝሙር 132 :13-16) ምዕመናኖቿን በቃል ኪዳኑ በእናትነቷ በምልጃዋ የሚያምኑትን ፈጽሜ አከብራቸዋለሁ ድሆቿ ነዳያንን ነፍስን አክለ ሥጋ አክለ ነፍስ ብእለ ሥጋ ብዕለ ጸጋን ሰጥቼ ደስ አሰናቸዋለሁ የሥጋ የነፍስ እህልን የሥጋ ብልፅግናና የነፍስ ሀብተጸጋን ሰጥቼ ደስ አሰኛቸዋለሁ ማለት ነው አንድም ሥጋውን ደሙን ልጅነትን ( ከሥላሴ በጥምቀት መውለድን ) ሰጥቼ ደስ አሰኛቸዋለሁ: ካህናቶቹንም አገልጋዮቿን ሕይወተ ሥጋ ሕይወተ ነፍስ ሰጥቼ በሕይወት እንዲኖሩ አደርጋቸዋለሁ ጽድቃንን በርሷ የሚታመኑበት ቅዱሳን መንፈስ ቅዱስ ተቀብለው ደስ ይላቸዋል፡፡

ሰላምን (ኢየሱስ ክርስቶስን )ሀገር በተባለው ማህፀን ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን የፀነሰች ድንግል ማርያም ናት "ህፃን ተወዶልናል ወንድ ልጅም ተሰጥተኖል አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል ስሙም ድንቅ መካር ኃያል አምላክ የዘላለም አባት የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል (ኢሳ9:6) እርሱ ሰላማችን ነውና ( ኤፌ 2:14 )ተብሎ እንደተጻፈ የእግዚአብሄር ከተማ የሰላም ሀገር የተባለች ጽዮን እንደሆነች በዝማሬው ነግሮናል "ነኪር ነገሩ በእንቲአኪ ሀገር እግዚአብር አንቺ የእግዚአብሔር ሀገር ሆይ በአንቺ የተደረገው ግሩም ነው" (መዝ 86:3)
"አንሰ ተሠየምኩ ንጉሠ በላዕሌሆሙ በጽዮን በደብረ መቅደሱ" እኔ ግን ( እኔስ ) በመመስገኛው ተራራ ንጉሥ ሆኜ ተሾምኩባቸው (መዝ 2:6) የጽዮን ተራራ የተባለችው ድንግል ማርያም ናት ምክንያቱም ደብረ ጽዮን ( የጽዮን ተራራ) አምባ መጠጊያ እንደነበረች ሁሉ ድንግል ማርያምም አምባ መጠጊያ ናት በቁሙም ቃሉ ጽዮን ማለት አምባ መጠጊያ ማለት ነው እመቤታችንም ለኃጥአንና ለጻድቃን ለክርስቲያን ሁሉ በእናትነቷ በአማላጅነቷ በተሰጣት የምህረት ቃል ኪዳን አምባ መጠጊያቸው ናትና በዚህ ምክንያት እመቤታችን ፀወነሥጋ ዐወነ ነፍስ ፀወነ ጽድቃን ወኃጥአን ትባላለች ደብረ መቅደስ አላት ዘጠኝ ወር ከእምስት ቀን መድኃኔዓለም ክርስቶስ ማህፀኗን ዓለም አድርጎ ተመስግኖበታልና በነገረ ማርያም "ድንግል አድነነት ርዕስ መንገለ ከርሣ" የሚል ቃል አለ መላዕክቱ በማህፀን ያለውን ፈጣሪያቸውን ሲያመሰግኑት ለመስማት አንገቷን ወደ ማህፀኗ ዘንበል::
በማድረግ ቅዳሴያቸውን ታደምጥ ነበርና ነው (ዮሐ 1-42) በድንግል ማርያም ማህጽን በእውነተኟይቱ ደብር ቤተ መቅደስ በጽዮን በተዋህዶ የከበረው የነገሠው የእግዚአብሄር የባሕሪ ልጅ መሲህ( ክርስቶስ) የነፍሳችን የሥጋችን ንጉሥ የጌቶች ጌታ የነገስታት ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ( ራዕ 19:11-16) ሉቃ 1:30) ድንግል ማርያምን ለእናትነት ለዙፋንነት ለማደሪያነት የመረጠ እግዚአብሄር ነው ልዑል ማደሪያውን ቀደሰ (መዝ 45-4) የወደደውን የጽዮን ተራራ መረጠ እግዚአብሄር ድንግል ማርያምን መረጠ ማደሪያውን ለየ: ቀደሰ በመዝሙረ ዳዊት 77:68 ላይ "የይሁዳን ሕዝብ መረጠ የወደደውን የጽዮንን ተራራ" ተብሎ እንደተጻፈ ከይሁዳ ነገድ የሆነችውን ድንግል ማርያምን መርጦ አደረባት ቅድስት ንጽሕት ናትና
"እግዚአብሔር በቅድስናው ዙፋን ይቀመጣል" (መዝ 46:8) ስለተባለ ማህፀኗን አለም: ዙፋን አድርጎ ነገሰባት (መዝ 131:13) ታዲያ እግዚአብሔር የመረጣት ማን ይቃወማል (ሮሜ 8-34) እንኳን እግዚአብሔር ያከበረውን እግዚአብሔር የሾመው ቀርቶ ሰው የመረጠውና የሾመው እንኳ ይከበራል
ድንግል ማርያም የህያዋን ሁሉ ደስታ ናት "የምድር ሁሉ ደስታ የጽዮን ተራራ ነው" (መዝ 47:2) ተብሎ ተጽፏልና ለጊዜው የምድር ሁሉ ሲል የአዳም ልጆች የሥጋ ለባሾች ሁሉ ደስታ ቤተመቅደስ ነው ሲል ነው በተፈጠርንበት ምድር ይለናል ከአፈር ተፈጥረናልና ፍጻሜው ግን የሕያዋን ሁሉ የምድር ሁሉ የሥጋ ለባሾች ሁሉ ደስታ በእመቤታችን በድንግል ማርያም ነው ለምን ቢሉ" በእንተ ሔዋን ተፅው ኖኅተ ገነት ወበእንተ ማርያም ድንግል ተረኅወ ለነ ዳግመ" ( ውዳሴ ማርያም ዘኃሙስ: ቅዱስ ኤፍሬም) በሔዋን ያጣነውን ገነት :ያጣነውን ደስታ በእመቤታችን በድንግል ማርያምማ የደስታችን መፍሰሻ የጽዮን ተራራ እናታችን ሆና ተሰትታናለች (ዮሐ19-26) በመሆኑም ትንቢት የተነገረላት ሱባኤ የተቆጠረላት ከአምላ
ችን የተሰጠችን ጸጋችን በረከታችን አክሊላችን ሞገሳችን ናት መወጣጫ መሰላላችን መሸጋገሪያችን ድልድያችን እመቤታችን ናት ፡፡


ልዑለ ቃል ኢሳይያስ ስለ ጽዮን ዝም አልልም ያለው የማይታየው የማይዳሰሰው የማይጨበጠው ወይም በቦታና በዘመን የማይወሰነው አምላክ ከድንግል ማርያም በነሳው ሥጋ ስለታዬ ስለተዳሰሰ ከእኛ ጋር ስለሆነ መርገማችን ስለሻረልን እንባችን ስላበሰለን እንቆቅልሻችን ስለፈታልን ወጥመዳች ስለበጣጠሰልን ከሞት ወደ ሕይወት ስላሸጋገረን ጽዮን የድህነታችን ምክንያት ናትና ስለ ጽዮን ዝም አልልም አለ:: እኛም የዘመነ ሐዲስ ክርስቲያኖች ስለ ጽዮን ዝም አንልም ቀደምት አበው በምሳሌአቸው ነቢያት በትንቢታቸው ሐዋርያት በስብከታቸው ሊቃውንቱም አባሕርያቆስ በቅዳሴው ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴው አባ ጊዮርጊስ በሰአታቱ አባ ጽጌ ድንግል በማህሌቱ ቅዱስ ያሬድም በዜማው ስለ እመቤታችን ዝም አላሉም ይልቁንም ጽዮንን ክበቡአት በዙሪያዋም ተመላለሱ (መዝ47-12) ነው ያሉት : አቁራሪተ መት ነሽና አማልጂን አስምሪን ይቅርታን አስጪን የእናት ልመና ፊት አያስመልስ አንገት አያስቀልስምና ከልጅሽ ከወዳጅሽ ምህረትን አሰጪን እያልን ልንከባት ይገባል ::ነቢዩ ኢሳይያስ ስለ ጽዮን ዝም አልልም ማለቱ በምሥጋና በውዳሴ በዝማሬ በቅዳሴ ማለቱ ነው በመጽሐፍ "ጻድቃን ሆይ በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ ለቅኖች ምስጋና ይገባል"ተብሎ ተጽፏልና :: ለቅኖች ምስጋና የሚገባ ከሆነ እመቤታችን ደግሞ ከቅኖች በላይ ከጻድቃን በላ ናትና ምስጋና ይገባታል መላዕክት እንኳ እመቤታችን አመስግነዋል ..ጌታ ከአንቺ ጋር ነው አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ (ሉቃ 1-41) ድንግል ማርያም ራሷ እነሆ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል (ሉቃ 1-48) ለዚህም ነው እኟም የምናመሰግናት የምንዘምርላት የምናከብራት ከፍ ከፍም የምናደርጋት " ሰው ሁሉ እናታችን ጽዮን ይላል በውስጧም ሰው ተወለደ (መዝ 86:5)" እንዲል ቅዱስ ዳዊት የአዳም ዘር ሁሉ እናታችን እመቤታችን እያለ ያመሰግናታል፡፡


No comments:

Post a Comment