Tuesday, November 5, 2013

ደብዳቤ



ደብዳቤ
ደብዳቤ ከዘመድ ከወዳጅ ወይም ከተለያየ ሥፍራ በየጊዜው ይደርሰን ይሆናል አሊያም ተፅፎልን ላያውቅ ይችላል፣ ሆኖም ግን ደርሶናል ብለን እናስብና… በወረቀት ላይ በቀለም የፃፍነው ደብዳቤያችንን ወደ ፖስታ ቤት ለመላክ ከመውሠዳችን በፊት ፖስታ ቴምብር ወይም መግዣ ገንዘብ ማዘጋጀት አለብን፡፡ ከዚያ በኋላ የተፃፈውን ደብዳቤ አሽገን በላዩ አድራሻውን ጽፈን ቴምብር ከለጠፍን በኋላ ወደ ተላከለት ሰው እንዲደርስ የፖስታ መሠብሰቢያ ሣጥን ውስጥ እንከታለን የፖስታ ቤት ሠራተኛውም ምልክት (ማህተም) አድርጎ ይልከዋል፡፡ ጉዞ ወደ ተቀባይ…… ከቀናት በኋላ ተቀባይ ይደርሰዋል ምንም ይሁን ምን ደብዳቤ ከወዳጅ ከዘመድ በተለይም ከሚወዱት ሰው ሲመጣ ያስደስታልና ደስ ይለዋል…. ፖስታውን ከፍቶ ያነባል መልዕክቱ እስኪፈፀምም ድረስ ይሁን ለትዝታና ለማስታወሻነት ደብዳቤው ሥፍራ ተሰጥቶት ይቀመጣል፡፡ ደብዳቤ መንፈሳዊ አስተማሪ ከመሆኑ ባሻገር ምሳሌ ነው ከእግዚአብሔር ወደ ዓለም በፖስታ ወይም በሥጋዊ ሰውነት ውስጥ ታሽገን የተላክን ደብዳቤዎች ነን ‹‹በእጃቹ አበጃጅቶ የሠራን በመዳፉ የቀረፀን እርሱ ነውና እርሱ ፈጠረን እርሱ ሰራን›› ‹‹ሐዋርያውም ለክብሩ እንሆን ዘንድ ከዘመናት በፊት በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን ነው ያለው›› እኛ ፍጥረቱ ነንና እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን (ኤፌ 2፡10)


እንዲሁም ፖስታው ላይ በተለያዩ ጌጣጌጦች አልያም ቴምብር እንደሚለጣጠፍበት እኛም ሩቅ ወይም ቅርብ ለመጓዝ በብዙም ሆነ በጥቂቱ በማህበራዊ ፣ በኢኮኖሚ ፣ በትምህርትና በባህል በዚህ ዓለም የምንፈልገውን እንድናገኝ በፖስታው ላይ የተለያዩ ውብ የሆኑ ቴምብሮችን ወይም መለያዎችን ስም ክብር ማዕረግና ዝና…. ልንለጥፍ እንችላለን፡፡ አስገራሚው ነገር ግን የብዙዎች ትጋት ፖስታውን ወይም የሥጋዊ ማንነታችን ከማሳመር ላይ ሆኖ ለደብዳቤው መልዕክት ግን ቦታ አለመስጠታችን ነው፡፡
በሕይወት ጉዞ መጨረሻ ሁሉ እንዳልነበረ ይሆናል ታላቁ ሰባኪ በጥሪ ይወስደናል አስቀድሞ ወደዚህ ምድር የመጣችው ደብዳቤ ከባለቤቷ እጅ ትገባለች መክሊቱ ትርፍ አለው ወይስ ተቀብሮአል፣ ምን መልዕክት በውስጧ እንዳለ መነበብ ይጀምራል፡፡
በዚያን ጊዜ ሁሉ ይገለጣል፣ ዳሩ የሸክላው ባለቤት ስለ ሸክላው ውጫዊ ክፍል ጉዳዩ አይደለ፣ የፖስታው ባለቤት በፖስታው ላይ ስለ ለጠፍነው ማዕረግ፣ ዝና ፣ ዶ/ር፣ ፕሮፌሰር፣ ጳጳስ፣ ቄስ…… ወዘተ  ጉዳዩ አይደለም እርሱ ከመልዕክቱ ነው ጉዳዩ ምግባር ከሀይማኖት አስተባብሮ የያዘ የዚያን ጊዜ እርሱ መዓዛው እንደማረ ጽጌረዳ አበባ ነው፡፡ አቤት የዚያን ጊዜ ፖስታው ሲከፈት የነፍስ ሁኔታ ከቶ መግቢያዋ የት ይሆን በታላቁ ንጉሥና ዳኛ ፊት በምድር ተነባቢ ፊደል ሆኖ ሰማያዊ ዜግነት ያለው ሰው ምንኛ ዕድለኛ ነው ለዚህም ነው ትጉሁ ሐዋርያ ‹‹እናንተ የምትነበቡ መልዕክቶቻችን (ደብዳቤዎቻችን) ናችሁ›› በማለት የተናገረው፡፡
አንድ የምናውቀው ዘመድ ፣ ጓደኛ ወይም ቤተሰብ ባዶ ፖስታ አሽጎ በቴምብር አስውቦ ቢልክልን ምን እንላለን? መድኀኔዓለም ከባዶነት ያውጣን፣ እናስተውል በሥጋዊ ሕይወታችን ያሰብነው አልሳካ ሲለን ባዶነት ተሰምቶን ስናዝን ስንናደድ መታየታችን አይቀርም ባዶ ሕይወት ይዘን ነፍሳችን ተርባ መንገዱና ሐሳቡ ከእኛ ጋር ተለያይቶ መልዕክት የሌለን ሰዎች ሆነን ሲመለከት እግዚአብሔር እንዴት ያዝን ለቤዛነት ቀን የታተምንበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ ከማሳዘን ያውጣን (ኤፌ 4፡30) የጽድቃችን ፍሬ አሳድጎ ለሥራ አነሣሥቶ ባዶነታችን ይሙላ ‹‹በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራ ለመሥራት አንታክት›› (ገላ 6፡9) ካልታከትን እንደተስፋው ቃል መሠረት በወቅቱ እናጭዳለን፡፡
ወስብሃት ለእግዚአብሔር

No comments:

Post a Comment