Wednesday, November 13, 2013

ክፍል ሁለት ‹‹የእግዚአብሔር ቃል›



ክፍል ሁለት
 ‹‹የእግዚአብሔር ቃል›
                           






                                                      2/ የእግዚአብሔር ቃል እግዚአብሔር ነው
እግዚአብሔር የሚለው ስም የተወደደ ፣ የተቀባ ወይም የግብር ስም ያይደለ የባህርይ ስም ነው፡፡ እግዚአብሔር በየቋንቋው የተለያዩ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ስሞች አሉት፤ ነገር ግን ሁሉም ባሕርያዊ ስለሆኑ እና እግዚአብሔርም በባሕሪው አንድ ስለሆነ በአንድነት ፈጥሮ በሚገዛበት በባሕሪይ የግብር ስሙ በመጥራት ይተባበራሉ ወይም አንድ ይሆናሉ በየአንዳንዱ ቋንቋ ውስጥ ያለውን የእግዚአብሔርን ስም ትርጉም ብንመረምር የምናገኘው እያንዳንዳቸው እግዚአብሔርን የሚጠሩት በኃያልነት፣ በፈጣሪነት፣ በዘላለማዊነት፣ በቸርነትና ሁሉን አድራጊነት መሆኑ ነው ስለዚህ ይህን መሆን የሚቻለው ፍጡር ባለመኖር ለእግዚአብሔር ብቸኛ የባሕሪ ስሙ ሲሆን ለፍጡር ሊሰጡት የማይገባ ቢሰጡትም የማይስማማው ነው፡፡ ይህም በመሆኑ በየቋንቋው ያለ የእግዚአብሔር ስሞች ባሕሪውን ይገልጣሉ፤ እንደ ስሞቹ እንደሚሰራም ያረጋግጣሉ፡፡ (ዘፀ 15፡3 ፣ አሞ 4፡13)
እግዚአብሔር የሚለው ስም የአብ የወልድ የመንፍስ ቅዱስ የወል መጠሪያ ስም ነው የአንፆኪያው ሊቀጳጳስ ቅዱስ ባስሊዮስ ‹‹እኔስ እግዚአብሔር ባልኩ ጊዜ ስለ አብ ስለወልድ ስለ መንፈስ ቅዱስ ነው›› እንዲል እግዚአብሔር የሥላሴ የአንድነትም የሦስትነትም መገለጫ ነው ‹‹እግዚአብሔርም እንዲህ አለ ሰውን በመልካችን እንደምሳሌአችን እንፍጠር›› ዘፍ 1፡26 ቅዱስ አትናቲዎስም ‹‹አብ አምላክ ነው፣ ወልድ አምላክ ነው መንፈስ ቅዱስ አምላክ ነው ስንል እግዚአብሔር አምላክ ነው ማለታችን ነው›› በማለት ነው ያስተማረው፡፡




በመሆኑም ከዚህ በመነሳት የእግዚአብሔር ቃል የተባለውን የጌታችንን የመድኀኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን እግዚአብሔርነት መጻፍ እንጀምራለን የክርስቶስን እግዚአብሔርነት በምንናገርበት ጊዜ አንዳንድ ወገኖች እግዚአብሔር የሚለውን ስም ለአብ ብቻ ስለሚሰጡ ክርስቶስ አብ ነው አብ ክርስቶስ ነው እንዳልን አድርገው ያቀርባሉ የተዋህዶ እምነት አስተምህሮና ግንዛቤ ግን ከዚህ የተለየ ነው ‹‹እኛ ከሐዋርያት እንደተማርነው በመጽሐፍ ቅዱስ (በማቴ 10፡16) ቅዱስ ጴጥሮስ መንፈስ ቅዱስ ገልጾለት ‹‹አንተ ክርስቶስ የሕያው የእግዚብሔር ልጅ ነህ›› ባለው መሠረት፣ ሐዋርያው ናትናኤልም ‹‹መምህር ሆይ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ›› (ዮሐ 1፡50)፣ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባም ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አምናለሁ›› (ሐዋ 8፡37) ብለው በሰጡት ምስክርነት መሠረት ከእግዚአብሔር የተወለደ እግዚአብሔር ከአምላክ የተወለደ አምላክ ብለን እናምናለን፡፡
ከዚህ ውጪ መናፍቃን ይላሉ እንደሚሉት አብና ወልድን በአካል አንድ እግዚአብሔር አንልም፤ በአካል ፍጹም ተካፍሎ ፍጹም ተፈልጦ ያላቸው ናቸው ‹‹ሠለስቱ ምዕት ፤ አብ ወልድ ነው መንፈስ ቅዱስ ነው፣ ወልድም አብ ነው መንፈስ ቅዱስ ነው ፣ መንፈስ ቅዱስ አብ ነው ወልድም ነው ብለው የሥላሴ አካል አንድ ነው ስም ግን ሦስት ነው የሚሉ የነሰባልዮስን የረከሰች ሃይማኖት እናወግዛለን አንድ አካል ሦስት ስም የሚሉ እነዚህ ከእኛ የተለዩ ከሃይማኖታቸው የወጡ ናቸው›› (ሃይማኖት አበው ዘሰልስቱ ምዕት ገጽ 33 ም 19)
የአብና የወልድ አካላት ተከፍሎ እንደተጠበቀ ሆኖ አንድ የሚሆኑት በመለኮት ፣ በአገዛዝ፣ በሥልጣን፣ በመፍጠር ነው በመሆኑም የእግዚአብሔር ቃል (የእየሱስ ክርስቶስ) እግዚአብሔርነት ቀጥለን በምንገልፀው አስተምህሮ መሠረት ነው፡፡
1. በቀዳሚነት
‹‹በመጀመሪያ ቃል ነበረ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ ቃልም እግዚአብሔር ነበር›› (ዮሐ 1:1) ይህ ምስጢራዊ ዓረፍተ ነገር ከፍተኛ ትርጉም ያለው ወሳኝና አስተውሎት የሚጠይቅ ነው የጥቅሱ መልዕክት፡

‹‹በመጀመሪያ ቃል ነበረ›› ሲል የቃልን ቀዳማዊ ሕልውና አኗኗርን ይገልጻል፤ ‹‹ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ›› የሚለው ደግሞ ከእግዚአብሔርነት ሕልውና ሳይለይ በተለየ አካሉ በተወላዲነት ግብሩ በባሕሪ አባቱ በአብ ዘንድ ነበር ማለት ነው፡፡
በሁለቱ ሀረጎች የቃልን ቅድምናውንና በሕልውና ተገዳዳሪው እግዚአብሔር አብ መሆኑን ካስረዳን በኋላ ‹‹ቃልም እግዚአብሔር ነበረ›› ይላል ምስጢሩም በተለየ አካል ቃል፤ በተለየ ግብሩ ወልድ ቢባልም የባሕሪ አምላክ እግዚአብሔር ነው፤ ማለት ነው፡፡
ወንጌላዊ ዮሐንስ መጀመሪያ የቃልን ቅድምናና እግዚአብሔርነት የፃፈበት ዋና ዓላማ በተዋህዶ ኢየሱስ ክርስቶስ የተባለው አምላክ ቅድመ ተዋህዶ በሥጋ ከመገለጡ በፊት ቃል በመባል ሲሰለስ ሲቀደስ ሲመለክ የነበረ ልዑለ ባሕሪ እግዚአብሔር መሆኑን ለማስረዳት ነው ምክንያቱም ቀጥሎ (በዮሐ 11፡14) ላይ የቃልን ሥጋ መዋሀድ ስለሚገልጽ ቅድምናውንና ህልውናውን አስቀደመ ከዚያም ስለ ምስጢረ ተዋህዶ ሲያስተምር ‹‹ቃልም ሥጋ ሆነ ፀጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ›› (ዮሐ 1፡14) አለ፡፡
‹‹ቃል›› (በዮሐ 1፡1) እንዳየነው እግዚአብሔር ነው ነገር ግን ወንጌላዊው ዮሐንስ እግዚአብሔር ሥጋ ሆነ አላለም፤ እንዲህ ቢል ኖሮ አብና መንፈስ ቅዱስ ስጋ ሆኑ ባሰኘ ነበር ምክንያቱም እግዚአብሔር የሚለው ሥም ባሕሪያዊ የሆነ የሦስቱ አካት የባሕሪይ አንድነት ሥም ነውና፡፡
በእግዚአብሔርነት አንድ ከሆኑት ከሦስቱ አካላት አንዱ ቃል በተለየ አካሉ በተወላዲነት ግብሩ ከስጋ ስለተዋሃደ ቃልም ሥጋ ሆነ አለ ወንጌላዊው ትኩረት የሰጠው ለቃል ሥጋ መሆን ብቻ አይደለም የአብና የመንፈስ ቅዱስን ሕልውና ከቃል ጋር እያገናዘበ በአንድነት ያለውን ሦስትነት ጭምር ነው፡፡
‹‹ቃልም ሥጋ ሆነ›› ሲል ያ በተለየ አካሉ ቃል የተባለ እግዚአብሔር ስጋ ሆነ ማለት ነው ቅድመ ተዋህዶ ቃል የራሱ አካልና ባሕርይ እንደነበረው ሁሉ እንዲሁም ሥጋ የራሱ አካልና ባሕርይ ነበረው ድኅረ ተዋህዶ ቃልና ሥጋ በሁለት ባሕርይ በሁለት አካል የሚገኙ አይደሉም፡፡ ከሁለት አካል አንድ አካል ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ በተዋህዶ አንድ ሆነዋል ተዋህዶው በአካልም በባሕርይም ነው፤ ምንታዌ የለም፡፡ ምክንያቱም ባሕርይ ከአካል፤ አካልም ከባሕርይ ተለይቶ አይገኝም አይዋሃድም ባሕርይ የሌለው አካል ሕልውና የለውም አካልም ያለባህርይ አይኖርም፡፡
የቃልና ሥጋን ተዋህዶ ከሁለት አካል አንድ አካል ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ ሆነ ስንል ተዋህዶ ማለታችን ነው ወንጌላዊው ዮሐንስ ቃልም ሥጋ ሆነ እንዳለው፡፡ ሆነ ሲባል ግን ተለወጠ፤ መለኮት ከሥጋ ተቀላቀለ፤ ተደባለቀ ማለት አይደለም ውሕደቱ በሊቃውንት አባቶች ምሳሌአዊ አገላለጽ እንደ ነፍስና ሥጋ ተዋህዶ፤ እንደቃልና ምላስ ተዋህዶ፤ እንደ ብረትና እሳት ተዋህዶ፣ እንደብርሃንና ዓይን ተዋህዶ ያለ ተዋህዶ ምንታዌ የሌለበት ፍጹም ተዋህዶ ነው ስለዚህ ግዙፉ ሥጋ ግዙፍነቱን ሳይለቅ በተዐቅቦ ረቂቁን መለኮት ሆነ፤ ውስኑ ሥጋ ውስንነቱን ሳይለቅ በተዐቅቦ ምሉዕ ሆነ፤ ጠባቡ ሥጋ ጠባብነቱን ሳይለቅ በተዐቅቦ ሰፋዕ ሆነ እነዚህን ዓረፍተ ነገሮች በማብራሪያ እንያቸው፡-
ለምሣሌ ፡- የዓይንን ብሌንና ብርሃንን እንውሰድ፤
የስናፍጭ ቅንጣት የምታህል የዓይናችን ብሌን እጅግ ትንሽ ናት የዚህ ዓለም ብርሃን ግን በዚህ ዓለም የሞላ ነው ነገር ግን የስናፍጭ ቅንጣት የምታህል የዓይናችን ብሌን በዚህ ዓለም ከሞላው ብርሃን ጋር ተዋህዳ ሰማይ መሬቱን ዳገት ቁልቁለቱን ምንም ካልጋረዳት ከማይደረስበት ሁሉ ትደርሳለች የሥጋም ከመለኮት መዋሃድ እንደዚህ ነው፡፡
በመቀጠልም ‹‹ጸጋና እውነትን ተመልቶ በእኛ አደረ›› ይላል ከመጀመሪያው ሐረግ ሆነ የሚለው በመውሰድ ሌላውን ሳይገነዘቡ ሰው ወደ መሆን ተለወጠ የሚሉ እንዳይኖሩ ለማቀበያ ነው፡፡ ሰው ወደ መሆን ከተለወጠ ማዳኑ ከወዴት ይኖራል? ሰውስ ሰውን ያድነው ዘንድ ይቻለዋልን?  (ኢሳ 48፡11)
አንድም  ‹‹ጸጋንና እውነትን ተመልቶ በእኛ አደረ›› ሲል ክርስቶስ በምዕመናን ልቡና በጸጋው አደረ ሥጋን በመዋሐድ በመካከላቸው በእውነትና በጻጋ ተመላለሰ እውነትና ጸጋን አደለ ማለት ነው፡፡
በዮሐ 1፡18 ላይ መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን  ያየው አንድ እንኳ የለም ይላል ከቃሉ እንደምንረዳው፤ ክርስቶስ ስለታየ እግዚአብሔር አይባልም ወይም አይደለም አይልም፡፡የጥቅሱ ምስጢር እግዚአብሔር በባሕሪይው አልታየም የሚል ነው በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጇ ተረከው ስለሚል የንባቡ ትርጉም እግዚአብሔር አብ አልታየም የሚል ሆኖ እናገኘዋለን፤ ትክክልም ነው ግብሩ ወላዲ እንጂ ተወላዲ ስላይደለ ሥጋን ተዋህዶ መወለድ አላሻውም መንፈሳዊ አካልም ሥጋን ባለመዋሀዱ መንፈስ ነውና አልታየም የአብ አለመታየት ግን በምንም መልኩ የወልድን እግዚአብሔርነት አያስቀርም እንዲያውም ከላይ  እንዳየነው (በዮሐ 1፡1) የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ በመሆኑ እግዚአብሔር የተባለው፤ ከአባቱ ያልተለየ ወልድ ገለፀው፤ ስለእርሱ ተናገረ፤ የባሕርይ አባቱ ስለሆነ በማየት ያውቀዋልና፡፡ (ማቴ 11፡27 ፣ ሉቃ 10፡22 ፣ ዮሐ 3፡11-32 ፣ ሐዋ 8፡54)
‹‹ቃል›› (በዮሐ 1፡1) ላይ በተጻፈው መሠረት እግዚአብሔር በመሆኑ ዮሐንስ አካላዊ ቃልን በቃልነቱ  ያለ ተዋህዶ ሥጋ አየነው አለላም፤ የማይታይ በመንፈስ የሚሰገድለት ነበርና ‹‹እግዚአብሔር መንፈስ ነው›› እንዲል ወንጌል ‹‹ቃል›› ለመታየት ሥጋን መዋሐድ ስለነበረበት ሥጋን ተዋህዶ ታየ፤ ዮሐንስም ፤ አየን ያለው ቃል ሥጋ ሆነ ካለ በኋላ ነው ወልድ በተለየ አካሉ በተዋህዶ በሥጋ በመታየቱ አብ እንደታየ ተነገረ፤ አብ ግብሩ ተወላዲ ሆኖ ተወልዶ ቢሆን ኖሮ ወልድ ያደረገውን ያደርግ ነበርና ምክንያቱም በእግዚአብሔርነት አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ ናቸውና ለዚህም ነው ክርስቶስ ‹‹እኔን ያየ አብን አይቷል፤ እኔንም አባቴም አያችሁ›› ያለው (ዮሐ 1፡14-18፣ ዮሐ 14፡9 ፣ ዮሐ 15፡24 ዮሐ 16፡15)
በመሆኑም በዚህ ንዑስ ርዕስ ሥር ልንይዘው የሚገባን ጭብጥ ቀዳማዊ ቃል በቅድምና እግዚአብሔር ሆኖ ሲኖር ሳለ ዘመኑ ሲደርስ ለሰው ልጆች ድህነትን ለመስጠት ሥጋን ተዋህዶ ሰው መሆኑን ነው እግዚአሰብሔር ሆኖ በሥጋ መገለጥ ያለ ጥርጥር ታላቅ ነውና (ገላ 4፡4፣ ቆላ 1፡20 ፣ 1ኛ ጢሞ 8፡16 ፣ 1ኛ ዮሐ 1፡2፣ ዕብ 7፡26፣ 1ጴጥ 1፡21)
2. በብሉይ በሐዲስ (የነቢያትና ሐዋርያት ምስክርነት)
ብሉይ ኪዳን ከእግዚአብሔር ሕግና ከእግዚአብሔር ሕዝብ ታሪክ በተጨማሪ የክርስቶስን መምጣት የሚያበስር የነቢያት መጽሐፍ ነው፡፡ በዚህ መጽሐፍ ስለ እግዚአብሔር የተተነበዩት ትንቢቶች በሐዲስ ኪዳን በጌታችን በመድኃኒታችን በእየሱስ ክርስቶስ ተፈጽመዋል፡፡ ከዚህ የምንረዳው ክርስቶስ በሐዲስ ኪዳን ብቻ ሳይሆን በብሉይ ኪዳንም የነበረ ወደፊትም የሚኖር እግዚአብሔር መሆኑን ነው፡፡
‹‹የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርን ቀድሱት የሚያስፈራችሁ የሚያስደነግጣችሁ እርሱ ይሁን እርሱም ለመቀደስ ይሆናል ነገር ግን ለሁለቱ ለእስራኤል ቤቶች በእንቅፋት ድንጋይና ለማሰናከያ ዓለት ይሆናል፤ ብዙዎች በእርሱ ይሰናከላሉ ይወድቁማል ይሰበሩማል፤ ይጠመዱማል፤ ይያዙማል፤›› (ኢሳ 8፡13-14) ‹‹እነሆ የብዙዎች ልብ ሃሣብ ይገለጥ ዘንድ ይህ በእስራኤል ላሉት ለብዙዎች ለመውደቃቸውና ለመነሳታቸው ለሚቃወሙትም ምልክት ተሾሞአል›› (ሉቃ 2፡34) ለሚያምኑ ግን አናጢዎች የጣሉት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ የእንቅፋትም ድንጋይ የማሰናከያም ዓለት ሆነ የማያምኑ በቃሉ ይሰናከላሉና ለዚህ ደግሞ የተመደቡ ናቸው (1ጴጥ 2፡6-8)
በኢሳ 8፡14 ስለ እግዚአብሔር የተነገረው በሉቃስ ወንጌልና በጴጥሮስ መልዕክት በክርስቶስ መፈጸሙ ወልድ በተለየ አካሉ እግዚአብሔር መሆኑን ያስረዳል ‹‹የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል›› (ኢዩ 2፡32) ‹‹የጌታን ሥም የሚጠራ ሁሉ ይድናል›› (ሐዋ 2፡21-22) (ሮሜ 10፡18)
ኢዩኤል ነቢይ እንደጻፈው መዳን የእግዚአሔርን ሥም በመጥራት ብቻ ነው፡፡ የሐዋርያት ሥራና የሮሜ መልዕክት የክርስቶስን ሥም የጠራ ይድናል ይላሉ፣ ጌታ የተባለ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው ፍጡር የሆነ የሰውም ሆነ የመላዕክት ስም አያድንምና ክርስቶስ እግዚአብሔር መሆኑን ያስረዳሉ (ኢሳ 43፡11) ሁለት ጌቶች አሉ እንዳይባል (2ቆሮ 12፡5) ጌታም አንድ ነው ይላል፡፡
በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቁጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም (ዮሐ 3፡36) እነርሱም በጌታ በኢየሱስ ስም እመን አንተና ቤተሰቦችህ ትድናላችሁ አሉት›› (ሐዋ 16፡31) ‹‹በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ይሰቀል ዘንድ ይገባዋል›› (ዮሐ 3፡15)
‹‹የእግዚአብሔርን መንገድ በምድረ በዳ ጥረጉ ለአምላካችንም ጎዳና በበረሃ አስተካክሉ›› (ኢሳ 40፡3) ይህ ጥቅስ መንገድ የሚጠረግለትና የሚመጣው እግዚአብሔር እንደሆነ ተናግሮ ሳለ በማርቆስ 1፡1-3 ትንቢት ተነግሮለት የመጣው ክርስቶስ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ስለዚህ ይመጣል የተባለው እግዚአብሔር ክርስቶስ ከሆነ እግዚአብሔር ነው እግዚአብሔር ሳይሆን እግዚአብሔር እየተባለ ትንቢቱን ፈፀመ እንዳይባል መጽሐፍ ቅዱስ እኔ እግዚአብሔር ነኝ ስሜ ይህ ነው ክብሬን ለሌላ ምስጋናዮንም ለተቀረፀ ምስሎችም አልሰጥም›› ይላል (ኢሳ 42፡8 ፤ ኢሳ 48፡11 ፤ ዘፀ 32፡39)
3. በክብር
የእግዚአብሔር ቃል እግዚአብሔር ነው ስንል በባሕርይ ክብሩ ከባሕርይ አባቱ ከእግዚአብሔር አብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የተስተካከለ ነው ማለት ነው፡፡
አምልኮት፤ የባሕርይ ስግደት፤ በአጠቃላይ የባሕርይ ክብር የሚገባው ለእግዚአብሔር ብቻ ሆኖ ሳለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ለእግዚአብሔር ብቻ የሚገባውን ክብርና ስግደት አምልኮ ተቀብሏል በመጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ሥፍራ ይህ ተመዝግቧል፡፡
ሀ/ ‹‹አስራ አንዱ ደቀመዛሙርት ግን ኢየሱስ ወዳዘዛቸው ተራራ ወደ ገሊላ ሄዱ ባዩትም ጊዜ ሰገዱለት (ማቴ 28፡16፣ የሐ 9፡38 ፣ ሉቃ 24፡52)
·         ወደ ቤትም ገብተው ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት ወድቀውም ሰገዱለት ሳጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን ከርቤም አቀረቡለት (ማቴ 2፡11)
·         የታረደው በግ ኃይልና ባለጠግነት ጥበብም ብርታትም ክብር ምስጋናም በረከትም ሊቀበል ይገባዋል አሉ በሰማይና በምድር ከምድርም በታች በባሕርም ውስጥ ያለ ሁሉ በረከትና ክብር ምስጋናም ኃይልም ከዘላለም እስከ ዘላለም በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለበጉም ይሁን ሲሉ ሰማሁ አራቱም እንሰሶች አሜን አሉ ሊቃናቱም ወድቀው ሰገዱ›› (ራዕ 5፡12-14)
ለ/ የሁሉ ጌታ በሚሆን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እየሰበከ ይህን ቃል ወደ እስራኤል ልጆች ላከ (የሐዋ 10፡36)
ሐ/ አውቀውትስ ቢሆን የክብርን ጌታ ባልሰቀሉትም ነበር (1ኛ ቆሮ 2፡8)
መ/ ‹‹በሰማይና ከምድርም በታች ያለ ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበርከኩ›› (ፊልጵ 2፡6 ፣ ማቴ 11፡27 ፣ ማቴ 12፡8 ፣ ማቴ 16፡16 ፣ ማቴ 26፡64 ማር 8፡38 ፣ ዕብ 1፡5-10)
በዚህ ክብር የሚታወቀው እግዚአብሔር፤ በተለየ አካሉ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆኖ እናገኘዋለን ነገር ግን ክርስቶስ እግዚአብሔር ባይሆን ኖሮ ይህን ክብር መቀበል እንደማይችል የሚከተሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ይነግሩናል፡፡
ሠ/ የተቀረፀውን ምስል ለአንተ አታድርግ አትስገድላቸው፤ አታምልካቸው (ዘፀ 20፡5 ፣ ዘዳ 5፡4-22 ፣ ኤር 10፡3-11፣ 2ነገ 22፡16-22)
ረ/ እኔ ስል ራሴ አደርገዋለሁ ስሜ ተነቅፎአልና ክብሬን ለሌላ አልሰጥም (ኢሳ 48፡11 ፣ ኢሳ 42፡8)
ሰ/ ለሌላ አምላክ አትስገድ ከግብፅ ምድር ያወጣሁህ እኔ እግዚአብሔር ነኝና (መዝ 80፡10)
ሸ/ አምላክህን እግዚአብሔርን ፍራ እርሱንም አምልክ በስሙም ማል በመካከልህ ያለው አምላክ ቀናተኛ አምላክ ነውና ሌሎችም አማልክት አትከተል (ዘዳ 6፡13-14)
ቀ/ ሂድ አንተ ሰይጣን ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፏል አለው (ማቴ 4፡10)
እነዚህ ሁሉ የክርስቶስን እግዚአብሔርነት የሚያረጋግጡ ጥቅሶች ናቸው ፍጡር እየተሰገደለት እንዲመለክ አልተፈቀደም ከላይ የተገለፁት ጥቅሶች የአክብሮት (የጸጋ) ስግደት የሚያመለክቱ አይደለም የዚህ ዓይነቱ የስግደት አቀራረብ አምልኮአዊ ወይም የባሕርይ ነው እየተመለከ እግዚአብሔር አይደለም ከተባለ ምን እየሆነ እግዚአብሔር መሆን ነበረበት? እናስተውል
4. በፈጣሪነት
የእግዚአብሔር ቃል ፈጣሪ ስለሆነ እግዚአብሔር ነው በዘፍጥረት 1፡1 ፍጥረታትን እግዚአብሔር እንደፈጠረ ተጽፏል፡፡ እንዲሁም (በኢሳ 44፡24፣ ኢሳ 40፡13፣ ሮሜ 11፡13) እግዚአብሔር ብቻውን እንደፈጠረ አማካሪም እንዳልነበረው ከገለጸ በኋላ ያለ ክርስቶስ ምንም ምን የተፈጠረ ነገር እንደሌለ ስለሚናገር ፈጠረ የተባለ እግዚአብሔር በተለየ አካሉ በማይካፈል ባሕርይው ወልድ መሆኑን ያረጋግጥልናል፡፡
ሀ/ ‹‹በእግዚአብሔር ቃል ሰማዮች ፀኑ›› (መዝ 32፡6-9)
ለ/ ‹‹ሁሉ በእርሱ ሆነ ከሆነውም አንዳችስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም›› (ዮሐ 1፡3)
ሐ/ ‹‹እርሱ የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው፤ የሚታዩትና የማይታዩትም ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቃነት ወይም ሥልጣናት በሰማይና በምድር ያሉ ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኩር ነው››
መ/ ዓለሞች በእግዚአብሔር ቃል እንደተዘጋጁ ስለዚህም የሚታየው ነገር ከሚታዩት እንዳልሆነ በእምነት እናስተውላለን (ዕብ 11፡3)
ሠ/ ሰማያት ከጥንት ጀምረው ምድርም በእግዚአብሔር ቃል ከውኃ ተጋጥማ በውኃ መካከል እንደነበሩ ወደው አያስተውሉምና በዚህ ምክንያት ያን ጊዜ የነበረ ዓለም በውሃ ሰጥሞ ጠፋ አሁን ያሉ ሰማያትና ምድር ግን እግዚአብሔርን የማያመልኩት ሰዎች እስኪጠፋባት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ተጠብቀው በዚያ ቃል ለእሣት ቀርተዋል፡፡ (2ኛ ጴጥ 3፡5-7) ይቆየን


ይቀጥላል

No comments:

Post a Comment