Friday, November 15, 2013

አቤቱ የሆነብንን አስብ





አቤቱ የሆነብንን አስብ
ይህን የሰቆቃና የተማጽኖ ልመና ወደ እግዚአብሔር ያቀረበ ታላቁ ነቢይ ኤርሚያስ ሲሆን ኤርሚያስ ማለት የቃሉ ትርጉም እግዚአብሔር ከፍ ያደርጋል እግዚአብሔር ያነሳል ማለት ነው፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር ከወደቅንበት አዘቅት ከተጣልንበት መከራ ያንሳን ከፍ ከፍ ያድርገን፡፡
ዘመኑ ክብር ከእስራኤል የለቀቀበት የይሁዳ (የእስራኤል) ክፋት የባሰበት ፍርድ የተጓደለበት ደሀ የተበደለበት አምልኮ ጣዖትና ክህደት በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል የተስፋፋበት ክፉ ዘመን ነበር፤ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ያ ዘመን ከዛሬው ከኢትዮጵያውያን ዘመን ጋራ የሚመሳሰልበትን አመስጥረው ያስተምራሉ፡፡
ዛሬም ከእኛ ከኢትዮጵያውያን ክብር ጓድሏል መተማመን ጠፍቷል ወንድም በወንድሙ ላይ እተነሣ ፍቅር በመካከላችን ቅዝቅዟል ፍርድ ተጓድሏል ደሀ ተበድሏል በገዛ ሀገራችን ሳይቀር እንደ መጻተኛ የሰሜኑ፣ በደቡብ፣ የምስራቁ ከምዕራብ ተዘዋውሮ እንዳይሰራ ጎጆ ቀልሶ ኑሮ መሥርቶ ወልዶና ከብዶ እንዳይኖር በዘረኝነት አጥር ተከልሎ በገዛ ሀገሩ ስደተኛ በባዕድም ሀገር በአሕዛብም ምድር ሳይቀር ከርታታና ተስፋ ቢስ ሆነናልና፡፡




‹‹የእስራኤል ዘሥጋ ዘመን ከክፋት የተነሣ ተበላሸ ከኃጢዓትም የተነሣ አረጀ››
‹‹ትውልድ ሁሉ ወደ አባቶቻችን ተከማቹ ከእነዚህም በኋላ እግዚአብሔር ለእስራኤል ያደረገውን ሥራ ያላወቀ ሌላ ትውልድ ተነሣ›› ተብሎ እንደተፃፈ አባቶቻቸው በቃዴስ በረሃ አርባ ዘመን ተጉዘው የወረሷትን የከነዓንን ምድር ከተረከቡ በኋላ እግዚአብሔር ለአባቶቻቸው ያደረገውን ከግብጽ የባርነት ምድር ከፈርኦን አገዛዝ በዘጠኝ ጽኑ ተአምራት በአስረኛው ሞተ በኩር በአስራ አንደኛ ስጥመተ ኤርትራ ባሕር ባሕሩን ለሁለት ከፍሎ ውሃውን እንደ ሳር ክምር እንደ ግርግዳ አቁሞ በደረቅ መሬት ያሻገራቸውን እግዚአብሔርን ረሱ ታሪክን አዛቡ ‹‹ባሪያዎች እንዳትሆኗቸው ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሄር አምላካችሁ ነኝ የባርነታችሁን ቀንበር ሰብሬአለሁና ቀና ብላችሁ እንድትሄዱ አድርጊያለሁ›› (ዘሌ 26፡13) ያላቸውን ዘነጉ፤
በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝግቦ እንደምናነበው ባለሥልጣናቱ መሪዎቹ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረጉ በእግዚአብሔርዘም አፍ በተናገረው በነቢዩ በኤርሚያስ ፊት ራሳቸውን አላዋረዱም ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር እንዳይመለሱ አንገታቸውን አደነደኑ ልባቸውን አጠነከሩ፤ ደግሞ የካህናቱ አለቆች ሁሉ ሕዝብ እንደ አሕዛብ ያለ ርኩሰትን ሁሉ መተላለፍን አበዙ በኢየሩሳሌምም የተቀደሰውን የእግዚአብሔርን ቤት አረከሱ ይህም ሆኖ ግን የአባቶቻቸው አምላክ እግዚአብሔር ለሕዝቡና ለማደሪያው ስላዘነ ማለዳ ተነስቶ በመልዕክተኞቹ እጅ ወደ እነርሱ ይልክ ነበር እነርሱ ግን የእግዚአብሔር ቁጣ በሕዝቡ ላይ እስኪወጣ ድረስ ፈውስም እስከማይገኝላቸው ድረስ በእግዚአብሔር መልዕክተኞች ይሳለቁ ቃሉንም ያቃልሉ በነቢያቱም ላይ ያፌዙ ነበር›› (2ዜና 36፡11-16)


እግዚአብሔርን ረሱ አምላካቸውን አስቀየሙ ንጹሕ ደምን አፈሰሱ ሽማግሌዎችንና አዛውንቱን ገፉ እውነትን አቃለሉ ኃጢዓትን አብዝተው ሰሩ፤ ኃጢዓትና በደል ደግሞ አክሊልን ታስነጥቃለች ከጸጋ ታራቁታለች በረከትንና ክብርን ታሳጣለች ‹‹በደላችሁን እነዚህን ኃጢዓታችሁም መልካሙን ነገር ከለከለቻችሁ›› (ኤር 5፡25) ተብሎ እንደተፃፈ ሁሉን አጡ፡፡
የእግዚአብሔር ቁጣ ነደደች ሕዝቡን ሕዝቤ፤ የበኩር ልጄ፤ እናንተን የነካ የዓይኔን ብሌን እንደነካ ነው ያለ እግዚአብሔር ‹‹እነሆ በዚህ ወገን ላይ በክፉ አስባለሁ ዘመኑ ክፉ ነውና ቀጥ ብላችሁ፤ አትሄዱም›› (ሚክ 2፡3) በማለት በነቢያቱ ተናገረ እጥላችኋለሁ አዋርዳችኋለሁ ክብሬን ለሌላ አምልኮቴን ለባዕድ ሰጥታችኋልና አለ ሰው ቢጥል እግዚአብሔር ያነሳል፤ ሰው ሲያዋርድ እግዚአብሔር ያከብራል፤ እግዚአብሔር ካዋረደ ማን ያነሣል እግዚአብሔር ከተቆጣ ማን ጸንቶ በፊቱ ይቆማል፡፡
‹‹እግዚአብሔር በሕዝቡ ፊት ባለፈ ጊዜ ምድር ትናወጣለች ተብሎ ነውና የተፃፋ፡፡›› (መዝ 67፡7)
በዘመኑ የነበሩት ከአበይት ነቢያት ኤርሚያስ ከደቂቀ ነቢያት ዕንባቆም ፍርድ ሲጓደል አብዝተው ጮኹ ወደ እግዚአብሔርም አሳሰቡ ‹‹አቤቱ እኔ ስጮህ የማትሰማው እስከመቼ ነው? ስለ ግፍ ወደ አንተ እጮሀለሁ አንተም አታድንም በደልንስ ስለምን አሳየኸኝ ጠማምነትንስ ስለምን ትመለከታለህ? ጥፋትና ግፍ በፊቴ ነው ጠብና ክርክር ይነሣሉ ስለዚህ ሕግ ላልቷልና ፍርድም ድል ነስቶ አይወጣም ኃጢዓተኛ ጻድቅን ይከባልና ስለዚህ ፍርደ ጠማማ ሆኖ ይወጣል›› (ዕንባ 1፡2-4)
ቅን ፍርድ እውነተኛ ፍርድ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነውና ፍርድን ያደርግ ዘንድ መጣባቸው ‹‹እናንተ የምትንቁ ሆይ አንድ ቢተርክላችሁ ስንኳ የማታምኑትን ሥራ በዘመናችሁ እሰራለሁና እዩ ተመልከቱ ተደነቁ እነሆ የእነርሱ ያልሆነውን መኖሪያ ይወርሱ ዘንድ በምድር ስፋት ላይ የሚሄዱትን መራሮችንና ፈጣኖችን ሕዝብ ከለዳውያንን አስነሳለሁ እነርሱ የሚያስፈሩና የሚያስደነግጡ ናቸው ፍርዳቸውና ክብራቸው ከራሳቸው ይወጣል ፈረሶቻቸውም ከነብር ይልቅ ፈጣኖች ናቸው፤ ከማታም ተኩላ ይልቅ ጨካኞች ናቸው፤ ሁሉም ለግፍ ሥራ ይመጣሉ›› (ዕንባ 1፡5-11) በማለት ለአሕዛብ አሳልፎ ሰጣቸው ዘመናቸው ከግፍ የተነሣ ተበላሸባቸው ይህንን ባየ ጊዜ ነቢዩ ኤርሚያስ አቤቱ የሆነብንን አስብ ዘመናችንንም እንደቀድሞው አድስልን አለ፡፡ የእስራኤል ዘመን በምን ተበላሸ? የእኛስ የኢትዮጵያውያን ዘመን በምንና እንዴት ተበላሸ? በቃሉ መስታዎትነት አነጻጸርን እንመልከት፤ ራሳችንንም እንመርምር ‹‹በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ ራሳችሁን ፈትኑ ተብሎ ተጽፏልና (2ቆሮ 13፡5)›› እግዚአብሔር ማስተዋሉን ይስጠን
1. ዘመናቸው በሰይፍ ተበላሸ
‹‹ስለዚህ የከለዳውያንን ንጉሥ አመጣባቸው እርሱም ጎልማሶቻቸውን በቤተመቅደሱ ውስጥ ሳይቀር በሰይፍ ገደሏቸው ጎልማሳውን ቆንጆይቱን ሽማግሌውንና አሮጌውን አልማረም ሁሉንም በእጁ አሳልፎ ሰጠው የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃ ሁሉ ታላቁንና ታናሹን የእግዚአብሔርንም ቤት መዝገብ የንጉሱንና የአለቆቹን መዝገብ እነዚህን ሁሉ ወደ ባቢሎን ወሰደ የእግዚአብሔርንም ቤት አቃጠሉ የኢየሩሳሌምን ቅጥር አፈረሱ አዳራሾቿን በእሳት አቃጠሉ መልካሙን ዕቃዋን ሁሉ አጠፉ ከሰይፍም ያመለጡትን ወደ ባቢሎን ማረካቸው›› (2ዜና 36፡17-21)
እስራኤል በዚህ ዘመን ውስጥ በዙ ሕዝባቸውን በሰይፍ አጡ የንፁሐንን ደም አፍሰው ነበርና የነሱም ደም በቤተመቅደስ ሳይቀር ፈሰሰ ‹‹የጻድቃንን ደም በውስ×EE ስላፈሰሱ ስለ ነቢያቶቿ ኃጢዓትና ስለ ካህናቶቿ በደል ይህ ሁሉ ሆነ›› ሰ.ኤር 4፡13
እኛም ኢትዮጵያውያን መታወቂያችን ጦርነት ነው ለበርካታ ዓመታት በባዕድ ጦርም ሆነ እርስ በእርስ ጦርነት ብዙ ወገኖቻችን በሰይፍ አጥተናል አሁንም ድረስ እያጣን ነው በተለይ ከተወሰኑ አሥርት ዓመታት ወዲህ የአንዲት ኢትዮጵያ ልጆች ሆነን ነገር ግን በዘርና በጎጥ በወንዝም ተከፋፍለን በሰይፍ እየተላለቅን ልንጠፋፋ ተቃርበናል፡፡ ‹‹ነገር ግን እርስ በእርሳችሁ ብትነካከሱና ብትበላሉ እርስ በእርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ›› (ገላ 5፡15) እንዲል ሐዋርያው ባለማስተዋል በመጥፊያ ዋዜማ ላይ ደርሰናል ሲሆን በፍቅራችን በእንግዳ ተቀባይነታችን በባሕላችን ያለንን በመከባበር ይዘን ‹‹ቢቻላችሁስ ከሰው ሁሉ ጋራ በሰላም ኑሩ›› (ሮሜ 12፡18) ተብለን ሳለ  ለአሕዛብና ለጎረቤቶቻችን በፍቅር ኑሯችን ምሳሌ መሆን ሲገባን በመለያየት ሰይፍ ዘመናችንን እያበላሸን ነው፡፡ ሰይፍን መተላለቅን በማጥፋት ሰይፋችን ወደ ሰገባው መልሰን በትዕግስትና በመከባበር በመሆን ዘመናችንን ለማደስ ቆርጠን እንነሳ፡፡
2.    ዘመናቸው በረሃብ ተበላሸ
ሰይፍ ወይም ጦርነት አስከፊ ገጽታው ደም ማፍሰሱ ወገን ማጥፋቱ ብቻ ሳይሆን ለቋሚውም ጠባሳ ትቶ ጦስ ሆኖ ማለፍ ነው ጦርነት የሀገርንና የሕዝብ ኢኮኖሚ ስለሚያቃውስ ለረሃብ፣ ለችግር፣ ለተመጽዋችነት ይዳርጋል፡፡
እስራኤል ‹‹ሁሉን አብዝቶ ስለሰጠህ አምላክህን እግዚአብሔርን በፍሰሐና በሐሴት አላመለክምን በርሀብና በጥማት በራቁትነትም ሁሉንም በማጣት እግዚአብሔር ለሚልክብህም ጠላቶችህ ትገዛለህ›› (ዘዳ 28፡47) ተብሎ እንደተጻፈ መና ከሰማይ አውርዶ የመገባቸውን ውሃን ከጭንጫ አፍልቆ ያጠጣቸውን ቀን በደመና ሌሊት በብርሀን አምድ የሲናን በረሃ አሻግሮ ምድረ ርስት ያወረሳቸውን እግዚአብሔርን በፍሰሐና በሐሴት በማመስገን ፈንታ ውለታውን በመርሳታቸው ከከለዳውያን ሰይፍ የተረፉት ወደ ባቢሎን ተማረኩ ተሰደዱ፡፡
በርሃብም ተቀጡ ነቢዩ ኤርሚያስ ሰቆቃውን ጩኸቱን የረሃቡን እስከፊነት ሲጽፍ ‹‹ጡት የሚጠባው የሕፃን ምላስ ከጥም የተነሣ ወደ ትናጋው ተጣበቀ ሕፃናት እንጀራ ለመኑ የሚቆርስላቸውም የለም ፊታቸው ከጥቀርሻ ይልቅ ጠቁሯል በመንገድም አልታወቁም ቁርበታቸው ወደ አጥንታቸው ተጣብቋል ደርቋል እንደ እንጨት ሆኗል በሰይፍ የሞቱት በረሃብ ከሞቱት ይሻላል እነዚህ የምድርን ፍሬ አጥተው ተወግተውም ቀጥነዋል የሩኁሩኆች ሴቶች እጆች ልጆቻቸውን ቀቅለዋል›› (ሰ.ኤር 4፡4፡11) አዎ እግዚአብሔር መዓቱን ፈጽሟል ጽኑ ቁጣውን አፍስሷልና ስብራቻቸው የከፋ ነበር፡፡
እኛም ኢትዮጵያውያን የማንነታችን ታሪክ ካበላሸው ጥቁር ጠባሳ ሆኖ ካለፈው ገጽታችን መካከል አንዱና የዓለም የመገናኛ ብዙኃን ሳይቀር የዘገቡት እኛም እስካሁን እያፈርንበት ያለነው ዘመናችንን ያበላሸው ረሀብተኝነታችን ነው ከዚህም የተነሣ የምዕራቡ ዓለም የኢኮኖሚ ጥገኛ ለማኝና ተመጽዋች ሆነናል ብዙ ወገኖቻችንም በርሃብ ሰይፍ አጥተናል አሁንም ድረስ ሕዝባችን በዚህ ሰይፍ ሰለባ እየሆነ ነው፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ ‹‹ለኢትዮጵያ ሰዎች ምግባቸውን ሰጠኋቸው›› ተብሎ እንዳልተጻፈልን እኛ ግን እያለን የሌለን የባለፀጋ ደሃ ሆነን ቅርጫት ተሸክመን የዳቦ ፍርፋሪ ለመልቀም በባዕድ ሀገር በአሕዛብ መንደር ሳይቀር ስደተኛና መጻተኛ ሆነናል፡፡ ነቢዩ ‹‹ለግብፃውያንና ለአሦራውያን እንጀራን እንጠግብ ዘንድ እጅ ሰጠን›› (ሰ.ኤር 5፡6)
እናንተ እስራኤላውያን ለእኔ እንደ ኢትዮጵያውያን አይደላችሁም ተብሎ የተነገረልን የድንግል ማርያም የአስራት ልጆች እምነት በሌላቸው እግዚአብሔርን በማያውቁት በአሕዛብ መካከል የሚሻግተውንና የሚበሰብሰውን እንጀራ ስንለምን በተናቁት ጣዖትን በሚያመልኩት አሕዛብ ክብራችን ተዋረደ የወንድሞቻችን ደም እንደ ውሻ ደም በሜዳ ፈሰሰ እህቶቻችን ልዕልናቸው ክብራቸው ተገሰሰ ንጽህናቸው አደፈ ጎደፈ ኤርሚያስ ‹‹ስለወገኔ ሴት ልጅ ቅጥቃጤ ዓይኔ ውኃ አፈሰሰች እግዚአብሔር ከሰማይ እስኪጎበኘንና እስኪመለከት ድረስ ዓይኔ ሳታቋርጥ ዝም ሳትል እንባ ታፈሳለች›› (ሰ.ኤር 3፡47) እንዲል እኛም ትላንት በሳውዲ አረቢያ እንጀራን ፍለጋ ሄደው ደማቸው ለፈሰሰው ወንድሞች ክብራቸው ለተነካው እህቶች ስብዕናቸው ለተገሰሰው ኢትዮጵያውያን፤ እንዲሁም በየጊዜው የዚህ መከራ ገፈት ቀማሽ ለሆኑትና በመካከለኛው ምስራቅ በተለያየ ምክንያት ለአሰሪዎቻቸው በሚደርስባቸው ግፍና ጫናም ሆነ ከጭንቀት የተነሣ አዕምሯቸውን ለሚስቱ ራሳቸውን ለሚያጠፉ በግፍ ለሚገደሉ ሁሉ ሰው መከራቸውን ባያይም እግዚአብሔር ያያልና ሳናቋርጥ እናሳስባለን እግዚአብሔርን እንማጠናለን፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ረጅም ዕቅድ አቅደው ተስፋ ሰንቀው ከሞቀ ቤታቸው ወጥተው ከዘመዶቻቸው ተለይተው የስደትን ጉዞ ጀምረው በተለያየ ምክንያት በመንገድ ለቀሩት በአውሬ ለተበሉት፣ በባህር ለሰጠሙት፣ በግብፅና በሜክሲኮ በረሃ ለቀሩት ሁሉ ወደ እግዚአብሔር እንማልዳለን፤ በተለያዩ ክፍለ ዓለማት ፍርድ ለሚጓደልባቸው ሰብዓዊ መብት ለተነፈጋቸው ኢትዮያውያን ሁሉ ቢመሽም ይነጋል ቢጨልምም ብርሃን ይወጣል የአባቶቻችን አምላክ እንደገና ያየናልና አንዘን በመሠረቱ ልብ ብለን አስተውለን ከሆነ በእውነት እግዚአብሔር ሊናገረን ሊገስፀን ፈልጎ እንጂ ‹‹እርሱ በክፉዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣል በኀጥአንና በጸድቃንም ላይ ዝናምን ያዘንማል ለማያመሰግኑት ለክፉዎችም ቸር ነው›› (ማቴ 5፡45 ፤ ሉቃ 6፡35) ተብሎ በወንጌል እንደተፃፈ እንኳንስ ለእኛ ለኢትዮጵያውን ስማችን ከአርባ ጊዜ በላይ በመጽሐፍ ለተመዘገበው ለልጆቹ አሕዛብንም በምህረቱ በቸርነቱ ያኖራል፡፡ ነገር ግን በትውልዳችን እግዚአብሔርን ያስቀየምንበት የበደልንበት ነገር ካለ ራሳችንን እንመርምር በንስሐም እንመለስ እንደዚያ ካደረግን የሁሉ ዓይን አንተን ተስፋ ያደርጋል አንተም ምግባቸውን ትሰጣቸዋለህ (መዝ 144፡15) ተስፋ ያደረግነው እግዚአብሔር ኢትዮጵያን የበረከት ሀገር ያደርጋታል፡፡
3. ዘመናቸው በበሽታ ተበላሸ
እስራኤል የእግዚአብሔርን መንገድ ስለተው ውለታውን ስለዘነጉ ስለተሰጣቸውም ነገር ማመስገንን ቸል ብለው በአሕዛብ ግብር በአመንዝራነት በዝሙት ስለተላለፉ ‹‹እግዚአብሔር ፈውስ በሌለው በክፉ ቁስል ጉልበትህንና ጭንህን ከእግር ጥፍርህም እስከ ራስ ፀጉርህ ይመታሀል›› (ዘዳ 28፡35) ተብሎ እንደተጻፈው ከሠይፍና ከረሃብ የተረፉት በበሽታና ፈውስ በሌለውም ደዌ ተቀጡ ብዙ ወገኖቻቸውንም በዚህ መቅሰፍት አጡ፡፡
ኢትዮጵያውያን ብዙ ወገኖቻችን ፈውስ በሌላው መቅሰፍት ላለፉት አራት አስርት ዓመታት አጥተናል አሁንም እያጣን ነው ‹‹ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊነቱን ነብር ዥንጉርጉርነቱን ይቀይራልን›› ነገር ግን የሰው ፈላጊ የራሱን ያጣል እንደተባለው የሩቅ ናፋቂ ሆነን ጨዋነታችን ግብረገብነታችን ሥነ ምግባራችን በመተው የምዕራቡን ዓለም ለመምሰል ባደረግነው ሙከራ አመንዝራነትና ዝሙትን እንደዘመናዊነት ተለማመድን ልቅ ግንኙነት፣ ዝሙት ለበሽታ ያጋልጣል ነገር ግን በፕላስቲክ (በላስቲክ) ይቻላል ብሎ ዓለም ኃጢዓትን በአደባባይ ሲያውጅ እኛም ተቀብለን አስተጋባን፤ ሌላው ቀርቶ ትውልድ የተቀጣበትን እግዚአብሔር ምድርን ከፍሎ ከሰማይ የፈላ ውሃን አውርዶ የሰዶምንና በኖህ ዘመን የነበሩ ሰዎችን ያጠፋበትን የግብረሰዶማዊነት ነውር በቅድስት ሀገር በኢትዮጵያ ፈጸምን እግዚአብሔር እስራኤልን ‹‹እኔ በክፉ ቁስል መታሁህ›› (ሚክ 6፡13)  እንዲል ብዙ ትውልዳችን በመቅሰፍት ተመታ እግዚአብሔር ብዙ ዘመን በአንድም በሌላም ተናገረን ግን አላስተዋልንም ‹‹ደግሞም በአልጋ ላይ በደዌ ይገስጸዋል አጥንቱንም ሁሉ ያደነዝዛል ሕይወቱም እንጀራን ነፍሱም ጣፍጭ መብልን ትጠላች ሥጋው እስከማይታይ ድረስ ይሰለስላል ተሸፍኖ የነበረውም አጥንት ይገለጣል›› ኢዮ 33፡19 ተብሎ እንደተጻፈ ለሀገር ለወገን ይጠቅማሉ፤ ሀገር ተረክበው ይመራሉ የቤተሰብ አስተዳዳሪ ይሆናሉ ትውልድ ይተካሉ ተብሎ ተስፋ የተጣለባቸው ብዙዎች በዝሙት መቅሰፍት እንደ ቅጠል ረገፉ ሕፃናትም ወላጅ አልባ ሆኑ አሳዳጊ አጡ አዛውንትም ×Eሪ ቀባሪ አጡ እስካሁንም ሕዝባችን በዚህ መቅሰፍት እየተቆጣ ነው አዎ ዘመናችን በእጅጉ ተበላሸ፤ ወኔያቸው ተሰልቦና ቅስማቸው ተሰብሮ እንዳልሆነ ሆነው ያ በቁጥር በርካታ ናቸው በመጽሐፍ ‹‹ሥብራትህ የማይፈወስ ቁስልህም ክፉ ነው›› (ኤር 30፡12) አሁንም ካልተመለስን ቀና ብለን አንሄድም በጎውን ዘመንም አናይም፡፡
እግዚአብሔር እንደገና እንዲያየን ዘመናችን እንዲታደስ ምን እናድርግ?
1.  በፍቅር ሆነን በአንድነት እንነሳ፡
ዘመናችን እንዲታደስ መጥፎው ታሪካችን በመልካም እንዲቀየር እግዚአብሔር በምህረት እንዲያየን በፍቅር እንመላለስ በኅብረት እንቁም ‹‹በፍቅር ተመላለሱ›› (ኤፌ 5፡2) አይደል የተባልን!! አንዳንዶቻችን አይደለም የኢትዮጵያዊነት ወጉ የክርስትናውም መስመርና ውል የጠፋን እንመስላለን የአንድ እናት ቤተክርስቲያን ልጆች በብዙ ነገር ተከፋፍለን፤ ተቃቅረን ፣ ቂምን አርግዘን ለበቀል እየተጣደፍን እየተተቻቸን ሆድና ጀርባ ሆነን ጉዞ ከጀመርን ቆየት ብለናል ነገር ግን እርስ በእርሳችን ሳንግባባ እግዚአብሔር በመካከላችን አይገባምና ድካማችን ከንቱ እንዳይሆን ሐዋርያው ጳውሎስ ‹‹እንግዲህ እንደ እግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳን ሆናችሁ የተወደዳችሁም ሆናችሁ ምህረትን ርህራሔን ቸርነትን ትህትናን የዋህነትን ትዕግስትን አድርጉ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው ይቅር ተባባሉ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱ›› (ቆላ 3፡12)
አዎን ፍቅር ነውርን ገመናን ኃጢዓትን ሸፍኖ ከመቅሰፍት ይታደጋልና በፍቅር እንሁን ‹‹ፍቅር የኃጢዓትን ብዛት ይሸፍናልና ከሁሉ በፊት እርስ በእርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ›› 1ጴጥ 4፡8 (ሮሜ 13፡8-10)
2.  ወደ ልባችን እንመለስ
ልባችን ከሸፈተ ከቤታችን ከክብራችን ከማዕረጋችን ከወጣን ቆየን ብዙ ወጣቶች ኢትዮጵያዊ ከመባል ቻይናዊ ወይም ህንዳዊ፣ አውሮፓዊ ወይም አሜሪካዊ ተብሎ መጠራትን ይምርጣሉ፤ አንዳንዶችም ኢትዮጵያ ውስጥ ሰው ሆኖ ከመፈጠር ከመኖር በባዕድ ሀገር እንሰሳ ሆነን መኖር ይሻለናል እስከማለት ደርሰዋል፤ የአሕዛብንም ግብር ርኩሰትን ዝሙትን አደንዛዥ ዕፆችንና ተዛማች ሱሶች ምርኮኛ ሆነናል፡፡
ወደ ክርስትናውም ስንመጣ አባቶቻችን ያቆዩልንን ወግ ማዕረጋችን ትውፊታችን ተዋህዶ እምነታችን በመተው ኃይማኖት እንደፋሽን እየቀያየርን ያለን ብዙ ነን፤ በውስጥ ያለነውም ቅርሳችን በቅርስነት ከመጠበቅ ይልቅ ታሪካችን በታሪክነቱ ከመተረክ ይልቅ አበው ሐዋርያት በስብከታቸው ሰማዕታት በደማቸው ቀለምነት በአጥንታቸው ብዕርነት ያቆዩልንን እምነት እንደ አባቶቻችን ከመኖር ይልቅ ማደስ መሸራረፍ ፈለግን ቃሉ ደግሞ ‹‹አባቶችህ የሰሩልህን የድንበር ምልክት አታፋርስ›› ይላልና የነሱ አጥንት እሾህ ሆኖ እንዳይወጋን ደማቸው እንዳይፋረደን አሁን ወደ ልቡናችን እንመለስ በሉቃ 15፡17 ከአባቱ ኮብልሎ ከቤቱ የጠፋው ልጅ ወደ ልቡ ሲመለስ በመከራ ውስጥ ሲማር መሳሳቱን አስተዋለ ወደ አባቱም መጥቶ ይቅርታ ጠየቀ እኛም ልዑለ ቃል ኢሳይያስ ‹‹እነሆ አንተ ተቆጣህ እኛም ኃጢዓት ሠራን ስለዚህም ተሳሳትን›› (ኢሳ 64፡5) ብሎ እንዳስተማረ ወደ ልባችን እንመለስ፡፡
3.  ንሰሐ እንግባ
ሰይፍንም መቅሰፍቱንም ስደቱንም አየነው ዘመናችንም መበላሸቱን መጻሕፍት ከሚናገሩት ጻሕፊያን ከሚጽፉት ሰባኪያን ከሚሰብኩት በላይ በድርጊት እያስተዋልነው ነው ታዲያ ነቢዩ እንዳለ ‹‹ደግሞስ አመፃን እየጨመራችሁ ለምን ገና ትቀሰፋላችሁ ራስ ሁሉ ለሕመም ልብ ሁሉ ለድካም ሆኗል›› (ኢሳ 1፡5) እስከመቼ ባልተሰበረ ልብ በበደል በኃጢዓት ፍርድ በማጓደል ደሀ በመበደል ንጹህ ደም በማፍሰስ እንቆያለን ፣ የመዳን ቀን ዛሬ ነውና እንመለስ አምላካችን እግዚአብሔር የምህርት እጁ ሁል ጊዜ እንደተዘረጋች ናት ‹‹ኑና እንዋቀስ ነው›› የሚለው (ኢሳ 1፡18) የዛሬውን መመለሳችን ያያልና ተመልሰን በሕይወት እንኑር ‹‹የሟችን ሞት አልፈቅድምና ተመለሱና በሕይወት ኑሩ›› ያለ እግዚአብሔር (ሕዝ 18፡30) አያሳፍረንም ‹‹ኑ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ እርሱ ሰብሮናልና እርሱም ይፈውሰናል›› (ሆሴ 6፡1)
4.  ወደ እግዚአብሔር እንጩህ
ምርኩዛችን በሚሰበረው ወንበራቸው በሚገለበጠው ጋሻቸውና ጦራቸው በማያድነው በኃያላን ባለሥልጣናት በኃጢዓትና በምድራዊ ሀብት በበለፀጉት ሀገሮች የተደገፍንበት ወደ እነርሱ የጮህንበት ጊዜ ይብቃን፡፡
በቅዱስ መጽሐፍ ‹‹ኢትዮጵያ እጆቻን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች›› ተብሎ ነበር የተመዘገበልን ነገር ግን በእውነት እጃችን ገና አላነሣንም ባለማወቅና ባለማስተዋል ብዙ ዘመን መፍትሔ ወደማይሰጡት የራሳቸውንም ችግር መፍታት ወደ ማይችሉት ወደ ሥጋ ለባሾች አመለከትን፡፡
‹‹ልብ ካላየ ዓይን አያይም›› አንዲሉ አበው መንገዳችን እንመርምርና እንፈትን ልባችን ከእጃችን ጋር በሰማይ ወዳለው ወደ እግዚአብሔር እናንሳ›› ከነቢዩም ከኤርሚያስና ከዳዊት ጋር እንዲህ በማለት ወደ እግዚአብሔር እንጩህ
‹‹ እስከማዕዜኑ እግዚኦ ትረስዐነ ለግሙራ
  እስከማዕዜኑ ትመይጥ ገጻከ እምኔነ
  ነጽረነ ወሰምአነ እግዚኦ አምላክነ›› መዝ 12፡1
አቤቱ እስከመቼ ፈጽመህ ትረሳናለህ?
እስከመቼስ ፊትህን ከእኛ ትሰውራለህ?
አቤቱ አምላካችን እየን ስማንም
‹‹አቤቱ የሆነብንን አስብ ተመልከት ስድባችንንም እይ አክሊል ከራሳችን ወድቋል ኃጢዓት ሠርተናል ወዮልን ስለዚህ ልባችን ታሟል ዓይናችንም ፈዝዟል ስለምን ለዘላለም ትረሳናለህ? ስለምንስ ለረጅም ዘመን ትተወናል? አቤቱ ወደ አንተ መልሰን እኛም እንመለሳለን፤ ዘመናችንንም እንደቀድሞው አድስ፡፡›› አሜን (ሰ.ኤር 5)
እስራኤልን ከ70 ዘመን በኋላ እንደገና እንዳያቸው በምህረት እንደጎበኛቸው እኛንም ክፉ ባየንባቸው ዘመኖች ፈንታ ደግ ያሳየናል በዘመኑም ጽድቅ ያብባል ትንሣኤያችንም ሩቅ አይሆንም፡፡
የኢትዮጵያን ትንሣኤ ፈጥኖ ያሳየን አሜን

No comments:

Post a Comment