የቅዱሳን አማላጅነት በአፀደ -ሥጋ
የአማላጅነት ትምህርት
በዘመነ አበው በህገ ልቡና፣ በዘመነ ኦሪት በመጻሕፍተ ብሉያት በዘመነ ሐዲስ በመጻህፍተ ሐዲሳት የነበረና አሁንም ያለ ወደፊትም
የሚቀጥል ትምህርት እንጂ ከጊዜ በኃላ ድንገት የመጣ አይደለም፡፡ ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናችንም የቅዱሳት መጻሕፍትን
የሐዋርያትንና የሊቃውንትን ትምህርትና ትውፊት ታስተምራለች፡፡ አማላጅነት እግዚአብሔር የሚፈቅደውና የሚወደው እንጂ ሰው ሰራሽ ልማዳዊ
ወግ አይደለም ከቤተክርስቲያን ታሪክ እንደምንረዳው ክርስትና ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ የአማላጅነት ትምህርት ያለ እንጂ በኋላ
ጊዜ ብቅ ያለ አይደለም፡፡
ዛሬ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በተለይ በሀገራችን ውስጥ በየአውቶቢስ ማቆሚያው
በመናፈሻዎች፣ በሠረግ ቤት፣ በለቅሶ ቤት፣ በሆቴሎች፣ በመሥሪያ ቤቶች ፣ በትምህርት ቤቶች፣ በመኖሪያ አካባቢዎች በገጠር በከተማ
እጅግ አከራካሪና አወዛጋቢ የሆነው አቢይ ጉዳይ በአማላጅነት ላይ የሚነሳው አቢይ ጥያቄ ነው፡፡ ሰዎች ስለአማላጅነት ያላቸው አቋም
የሚከተሉትን እምነት የሚጠቁም በመሆኑ ያ ብዙ ውጣ ውረድ የሰዎችን እምነት አቋም መለያ ሆኗል ከዚህም የተነሣ ወላጆችና ልጆች ባል
ከሚስት ጓደኛ ከጓደኛ ጎረቤት ከጎረቤት ወዘተ ተቆራርጧል ተለያይቷል፡፡ እኛ ኦርቶዶክሳውያን ፃድቃን ሰማዕታት ቅዱሳን መላዕክት
ይልቁንም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያማልዱናል ከፈጣሪያችን ዘንድ ያስታርቁናል ብለን የምናምነው እምነት የምንቀበለው ትምህርት
የቅዱሳንን አማላጅነት ለማይቀበሉት ወገኖች ጆሮን የሚያሳክክ የእግዚአብሔርን ክብር የሚነካ ትምህርት መስሎ ይታያል፡፡ በሌላ በኩል
ደግሞ፣ የቅዱሳንን አማላጅነት የሚቃወሙት ወገኖች ክብር ምስጋና ይግባውና የባሕሪ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስን አማላጃችን ነው የሌሎችን
ፍጡራን ረዳትነት አንሻም የሚለው ትምህርት ለእኛ ለኦርቶዶክሳውያን ጆሮ የሚዘገንንና የሚቀፍ ከመሆኑ ባሻገር ምንፍቅናና ክህደትም
ጭምር ነው፡፡
በሃይማኖት የምንመስላቸው ጥንታውያን የሆኑት የእስክንድርያ ፣ የሦርያ፣ የሕንድና
የአርመንያ አቢያተ ክርስቲያናት የቅዱሳንን አማላጅነት በሚገባ ይቀበላሉ፡፡ እንዲሁም በሃይማኖት ቀኖና ዶግማ ከእኛ የሚለዩት ጥንታውያን
የሆኑት የሮም ካቶሊክና የግሪክ ፣ የራሽያ፣ የሮማንያ ኦርቶዶክስ አቢያተ ክርስቲያናትም እንዲህ የአማላጅነትን ትምህርት ተቀብለዋል
የቅዱሳንን አማላጅነት የሚቃወመው ትምህርት ብቅ ማለት የጀመረውና በኋላም የተስፋፋው ከ13ኛው -16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ውስጥ
ይልቁንም በተሃድሶ (Reformation) እንቅስቃሴ ጊዜ ነው፡፡
የታሪክ ምስክርነት ካየን ይህ ትምህርት በቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ በተለያዩ
ዘመናት እንደተነሱ የኑፋቄ አስተሳሰቦች በፍፃሜ ዘመን እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውሃ ፈሳሽ የተፈጠረ እንግዳ ትምህርት እንጂ ከጥንት
ከመሠረት የመጣ አይደለም፡፡ በመሆኑም በየጊዜው የጥንቱን ትምህርት እየተው በእንግዳ ትምህርት መወሰድ እንደማይገባ ቅዱሳት መጻሕፍት
ያስጠነቅቃሉ፡፡ (ዕብ 13፡8)
1. ማማለድ ምንድን ነው?
ማማለድ የሚለው ቃል በግዕዝ ቋንቋ "ተንበለ" አማለደ ከሚለው ግስ የተገኘ ሲሆን
ትርጉሙም አንዱ ስለሌላው ለመነ ጸለየ ማለት ነው፡፡ ማማለድ ማለት አንዱ ስለሌላው ችግር መቃለል መጸለይ መለመን ማለት ነው ፡፡
ይህ ትርጉም በማንኛውም ኅብረተሰብና ግለሰብ ዘንድ ግልጽና የተረዳ ነው ምክንያቱም በቀን ተቀን ሕይወታችን የምናየውና የምንተገበረው
ጉዳይ ስለሆነ ነው፡፡ ከትርጉሙ ስንነሣ በአማላጅነት ተግባር ውስጥ ሦስት ወገኖች ያሉ ሲሆን እነሱም አማላጅ ተማላጅና የሚማለዱለት
ናቸው ሦስቱም ለአማላጅነት ስምረት የተለያየ ድርሻ አላቸው፡፡
ሀ/ አማልጅ
ማማለድ ለፍጡራን ባሕሪ የሚስማማ የትህትና ሥራ በመሆኑ አማላጆች ብዙ ናቸው
በአጠቃላይ ሲነገር ቅዱሳን ሰዎችና ቅዱሳን መላዕክት ሲሆኑ እመቤታችን ደግሞ የአማላጆች ሁሉ የበላይ ነች የአማላጆች ተግባር በኃጢአን
ፈንታ ስለኃጥአን ወደ እግዚአብሔር ምልጃ ማቅረብ ነው ቅዱሳን ሰዎች በሕይወተ ሥጋ ሳሉ በጾም በስግደት በቁመት ወዘተ በጠቅላላ
አስጨናቂ የሆኑ መከራዎችን እየተቀበሉ ልክ ለራሳቸው እንደሚለምኑ አድርገው ስለኃጥአን ያማልዳሉ እንዲያውም አንዳንዱ ቅዱሳን የራሳቸውን
ዘላለማዊ ደኅንነት በኃጥአን መጽደቅ በመለወጥ ወደ ፈጣሪያቸው እንደሚለምኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመዝግቦ እናነባለን፡፡
‹‹ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተመልሶ ወዮ አኒህ ሕዝብ ታላቅ ኃጢአት ሠርተዋልና
ለራሳቸውም የወርቅ አማልክት አድርገዋል አሁን ይህን ኃጢአታቸውን ይቅር በላቸው ያለዚያ ግን ከጻፍከው መጽሐፍ እባክህ ደምስሰኝ››
አለ (ዘዳ "2-"1) በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ብዙ ኀዘን የማያቋርጥ ጭንቀት በልቤ አለብኝ ስል በክርስቶስ ሆኜ እውነት እናገራለሁ
አልዋሽም ኅሊናዬም በመንፈስ ቅዱስ ይመሰክርልኛል በሥጋ ዘመዶቼ ስለሆኑ ስለወንድሞቼ ከክርስቶስ ተለይቼ እኔ ራሴ የተረገምሁ እንደሆን
እጸልይ ነበርና በማለት ገልጸአል›› (ሮሜ9፡1-3)፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ኤልያስም ስለ ጣዖት አምላኪ ወገኖች
ተነክቶ ከአባቶቼ አልበልጥምና ውሰደኝ አለ››
ለ/ ተማላጅ
ተማላጅ ማለት የአማላጆችን ጸሎት ልመና ወይም ምልጃ ተቀባይ ወይም የምልጃ የልመና
የጸሎት መድረሻ ማለት ነው፡፡ በሃይማኖታችን ትምህርት ውስጥ የጸሎት ሁሉ መድረሻ እግዚአብሔር ነው ተማላጄ እግዚአብሔር እንደ አማላጆች
ብዙ አይደለም አንድ ነው እንጂ አንድ እግዚአብሔር ስንል አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስን ማለታችን ነው እግዚአብሔር አንድ ሲሆን ሦስት፣
ሦስት ሲሆን አንድ ነው ይህም አንድነቱ ሦስትነቱን ሳይጠቀልለው ሦስትነቱ አንድነቱን ሳይከፍለው፣ ሦስቱ አካላት በአንድ ጌትነት፣
በአንድ ስልጣን ፣ በአንድ ክብር ፣ በአንድ መለኮት፣ በአንድ መንግስት፣ በአንድ ፈቃድ በሰማይና በምድር የሚገኙ የፍጡራንን ምስጋናና
ልመና ጸሎት ተቀብለው የፈቃዳቸውንና የቸርነታቸውን ሥራ ይፈጽማሉ፡፡ በሦስቱ አካላት በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ መካከል የበላይና
የበታች ጸሎት አቀባይ የለም ‹‹በሰማይና በምድርም ከምድርም በታች በባሕርም ላይ ያለ ፍጥረት ሁሉ በረከትና ክብር ምስጋናም ኃይልም
ከዘላለም እስከ ዘላለም በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለበጉ ይሁን ሲሉ ሰማሁ፣ አራቱም እንሰሶች አሜን አሉ ሊቃናቱም ወድቀው ሰገዱ››
(ራእ 5:.03-04)
ሐ/ የሚማለዱለት
አማላጆች ወደ እግዚአብሔር ምልጃ የሚያቀርቡት ስለኃጥአን ሰዎች መዳን ነው ርኩሳን
መናፍስት ቢኖሩም የአማላጅነት በረከትና ቸርነት የተፈቀደውና የሚያገለግለው ለኃጢአን ሰዎች ብቻ ነው የሚጸለይለት ወይም የሚማለድለት
ሰው ወይም ሕዝብ በአማላጅነት ስራ ውስጥ የራሱ ድርሻ አለው ይኸውም በአማላጁ ጸሎት በተማላጅ ችርነት ማመንና ከሚሠራው ኃጢዓት
የሚመለስ ተነሣሒ ልቡና ያለው መሆን አለበት፡፡
ነገር ግን አማላጆች አሉልኝ ብሎ በኃጢዓት ላይ ኃጢዓት ቢሠራ አማላጆች ቅዱሳንን
የኃጢዓታችን ተባባሪ እግዚአብሔርን ደግሞ የማይፈርድ ፈጣሪ ማድረግ ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር የአማላጆችን ምልጃ የማይቀበልበት ጊዜ
አለ ይህም የሚሆነው የሚማለድለት ኀጥኡ በሠራው ኃጢዓት የማይጸጸትና በዚያው የሚጸና ሲሆን ነው፡፡ ለዚህም ቅዱስ መጽሐፍ ‹‹እግዚአብሔርም
ሳሙኤልን በእስራኤል ላይ እንዳይነግሥ ለናቅሁት ለሳኦል የምታለቅስላት እስከመቼ ነው›› (1ሳሙ 06.1) እንዲሁም እንግዲህ አልሰማህምና ስለዚህ ሕዝብ አትጸልይ ስለ እነርሱም ልመናና ጸሎት አታድርግ አትማልድላቸው እነርሱስ በይሁዳ
ከተሞች ውስጥና በኢየሩሳሌም አደባባይ ላይ የሚያደርጉትን አታይምን ያስቆጡኝ ዘንድ ለሰማይ ንግስት እንጎቻ እንዲያደርጉ ለሌሎችም
አማልክት የመጠጥ ቁርባን እንዲያፈሱ ልጆች እንጨት ይሰበስባሉ አባቶችም እሳት ያነዳሉ ሴቶችም ዱቄት ይለውሳሉ እኔ ያስቆጣሉን? ይላል እግዚአብሔር ……….›› (ኤር 7.07.!) በተጨማሪ ‹‹እግዚአብሔርም እንደዚህ አለኝ ሙሴና ሳሙኤል በፊቴ ቢቆሙም ልቤ ወደ ዚህ ሕዝብ አይዘነበልም ከፊቴ ጣላቸው
ይውጡ›› (ኤር 05.1) በማለት ያስረዳል፡፡
2. የቅዱሳን አማላጅነት ለምን አስፈለገ?
የቅዱሳን አማላጅነት ያስፈለገበት ምክንያት አንድም ጸሎታችን በፍጥነት ወደ እግዚአብሔር
ስለሚደርስልን ሌላው ፈጣሪያችን የወዳጆቹን ይልቁንም የእናቱን የድንግል ማርያምን ጸሎት ተቀብሎ ስለቅዱሳን ፣ በተለይም ስለ እናቱ
ብሎ የቸርነቱን ሥራ ስለሚሠራልን ችግራችንን ስለሚያቃልልን ነው፡፡ የቅዱሳንን ጸሎት ከኀጥአን ጸሎት ይልቅ እንደሚሰማ መጽሀፍ ቅዱስ
እንዲህ ይገልፃል፣ ‹‹የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደ ጻድቃን ጆሮቹም ወደ ጩኸታቸው (ልመናቸው) ናቸው›› (መዝ 33.13-20) በተጨማሪም (ምሳ 10.24) ፣ (ምሳ 15፡8) ፣ (ምሳ 15፡29) ፣ (ዮሐ 15፡7) ፣ (ያዕ 5፡16-18)፣ (ራዕ 8፡3-4) ያሉትን ያገናዝቡ፡፡
የቅዱሳን ጸሎትና ልመና በፈጣሪ ዘንድ ተወዳጅ ሊሆን የቻለው ቅዱሳን ሰውነታቸውን
ከቂም ከበቀል ከኀጢዓት ስላነጹ እግዚአብሔር የማይወደውን ልመና ስለማይለምኑና ልመናቸው እንደሚፈጸም በፍጹም ልብ አምነው ስለሚጸልዩ
ነው፡፡ ይህንንም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይገለጽልናል፡፡
‹‹የጻድቃን ምኞት በጎ ብቻ ነው የኀጥአን ተስፋ ግን መቅሰፍት ነው›› ፣
‹‹የጻድቃን ሐሳብ ቅን ነው የኀጥአን ምክር ግን ተንኮል ነው››፣ ‹‹በዚያን ጊዜ የዘብዴዎስ ልጆች እናት ከልጆ ጋር እየሰገደችና አንድ ነገር እየለመነች ወደ ጌታ ቀረበች እርሱ ምን ትፈልጊያለሽ አላት እርሷም እነዚህ ሁለት ልጆች አንዱ
በቀኝህ አንዱ በግራህ በመንግስትህ እንዲቀመጡ እዘዝ አለችው ጌታችን ኢየሱስም የምትለምኑትን አታውቁም አላት››፣ ‹‹ስለዚህ እላችኋለሁ
የጸለያችሁትን የለመናችሁትንም ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ ይሆንላችሁማል›› (ምሳ 11፡23 ፣ ምሳ 12፡5 ፣ ማቴ 20፡20-22፣
ማር 11፡24) ቅዱሳን ሰዎችና ቅዱሳን መላዕክት ኀጥአን ምህረትን ሲያገኙ እጅግ ደስ ይላቸዋል፡፡ እግዚአብሔርም የሚወዳት ቅድስት
እናቱና የሚወዳቸው ቅዱሳን ወዳጆቹ ስለሀጥአን ምህረት ሲለምኑት እናቱና ወዳጆቹን ለማስደሰት ሲል ልመናቸውን ሰምቶ ይፈጽምላቸዋል፡፡
ይህንም ጌታችን በወንጌል ‹‹እላችኋለሁ ንስሐ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኙ
ጻድቃን ይልቅ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል›› ‹‹እላችኋለሁ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር
መላዕክት ፊት ደስታ ይሆናል›› (ሉቃ 15፡7) ‹‹በዚያን ቀንም ከእኔ አንዳች አትለምኑም እውነት እውነት እላችኋለሁ አብ በስሜ
የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል እስካሁን በስሜ ምንም አለመናችሁም ደስታችሁ ፍጹም እንዲሆን ለምኑ ትቀበሉማላችሁ›› (ዮሐ 16፡23)
የቅዱሳን አማላጅነት የእግዚአብሔርን ክብር የሚጋፋ ሳይሆን የበለጠ ፈጣሪን የማክበር
ምልክት ነው ይህም በመሆኑ እግዚአብሔር ራሱ ሰውን ወደ አማላጅ የመራበት ጊዜም አለ አምላካችን እግዚአብሔር በሰው ልጆች ላይ መቅሰፍት
ከማምጣቱ በፊት ለወዳጆቹ ያሳውቃል፡፡ ለምሣሌ ዓለምን በደመሰሰውን የጥፋት ውሃ መምጣት ለኖህ፣ የሰዶምና የገሞራን ጥፋት ለአብርሃም
የነነዌን ሰዎች ኃጢዓት ለዮናስ፣ የእስራኤልንም መማረክ መበዝበዝና ቅጥር መፍረስ ለነቢያት ገልéEል፡፡
እግዚአብሔር ለወዳጆቹ አስቀድሞ የሚገልጽበት ምክንያት፡-
1. ሕዝቡን አስተምረውና መክረው ከገቢረ ኃጢዓት ወደ ገቢረ ጽድቅ ከአምልኮተ ጣዖት
ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር በንስሐ እንዲመልሱትና የማይመለሰውንም በተሰጣቸው ሥልጣን እንዲዘልፍና እንዲገስጽ (ዘዳ 14፡27፣ ሐዋ
5፡5ና10)
2. ስለ ሕዝቡ ኃጢዓት እግዚአብሔርን መዓቱን በምህረት ቁጣውን በትዕግስት እንዲያማልዱ
እና
3. ሕዝቡ እንዲመለስ በትምህርታቸው ከማስተማራቸው ባሻገር በሕይወታቸው ብርሃን ሆነው
በጨለማው ዓለም እንዲያበሩ ነው፡፡
በአፀደ ሥጋ (በሕይወተ ሥጋ) ያሉ ቅዱሳን እንደሚያማልዱ በርካታ መጽሐፍ ቅዱሳዊ
ማስረጃዎች አሉ በመሠረቱ ማንኛውም ክርስቲያን ለሌላው ወንድሙ እንዲፀልይ ታዟል (ያዕ 5፡16) ባለቤቱ መድኃኔዓለም ያስተማረን
‹‹አቡነ ዘበሰማያት›› ጸሎት ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለሌላውም ጭምር የምንጸልየው ጸሎት ነው ምልጃ በክርስቲያኖች የጸሎት ተግባር
ውስጥ ሰፊ ሥፍራ አለው፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን በመጽሐፍ ሲያብራራ ‹‹እንግዲህ እግዚአብሔርን በመምሰልና
በጭምትነት ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለሰዎች ሁሉ ስለነገስታት ስለመኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ
ከሁሉ በፊት እመክራለሁ ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ
የሚያሰኝ ይህ ነው›› (1ጢሞ 2፡1-4) ‹‹ጌታ ቅርብ ነው በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን
አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ›› (ፊልጵ 4፡6) ብሏል፡፡
ነቢዩ ኢሳይያስም ‹‹እግዚአብሔርም ላይ ፍርድም ስለሌለ ተስፋ ሰውም እንደሌለ
አየ ወደ እርሱም የሚማልዱ እንደሌለ ተረዳ ተደነቀም (ኢሳ 59፡16) ብሏል፡፡ ጌታችንም በወንጌል በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች
ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ የሚረግሟችሁን መርቁ ለሚጠሏችሁም መልካም አድርጉ፣ ስለሚያሳድዷችሁም ጸልዩ›› (ማቴ 5፡43-47)
በማለት እንኳን ለወዳጆቻችን ለጠላቶቻችንም ቢሆን መፀለይ እንደሚገባ አዘናል አማላጅነት በሁሉ የታዘዘ ቢሆንም የቅዱሳን አማላጅነት
ግን የላቀና የከበረ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ፈጣን ምላሽ የሚያስገኝ ስለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽና በማያሻማ መልኩ ይተርክልናል፣
ለምሳሌ ያህልም የሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃዎች እንመልከት፣
1. በዘፍ 18፡16-33 ውስጥ ቅድስት ሥላሴ በአብርሃም ቤት በእንግድነት ከተገኙ
በኋላ ወደ ሰዶምና ገሞራ ሲሄዱ ‹‹እኔ የማደርገውን ከአብርሃም እሰውራለሁን በማለት ስለሰዶም ኃጢዓት በነገሩት ጊዜ አብርሃም እንዴት
እንደ ማደማለደ ይገልጻል›› የአብርሃም ምልጃ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ቢኖረውም በከተማይቱ 1 ፃድቃን ስላልተገኘ አንድ
ሎጥ ብቻ በመገኘቱ ከተማይቱ ወደመች
2. ‹‹በዘፍ 19፡18-22 የተናገርካትን ከተማ እንዳላጠፋት እነሆ በዚህ ነገር
የለመንከኝን ተቀብያለሁ›› በማለት እንደሰዶምና ገሞራ ልትጠፋ የነበረች ከተማ ሎጥ ሸሽቶ ስላረፈባት መላዕክት ስለሎጥ ልመና ሳያጠፏት
ትቷታል፡፡
3. ‹‹በዘፍ 20፡1-18›› የጌራራ ንጉሥ አቤሚሊክ የአብርሃምን ሚስት ሳራን ለሚስትነት
ስለወሰዳት እግዚአብሔር ተቆጥቶ ቤተሰቡን በሙሉ እንደሚቀስፍ እንዲህ አለው ‹‹እኔ ደግሞ በፊቴ ኃጢዓት እንዳትሠራ ከለከልሁህ ስለዚህም
ትነካት ዘንድ አልተውኩህም አሁንም የሰውየውን ሚስት መልስ ነብይ ነውና ስለአንተ ይጸልያል ትድናለህም ባትመልሳት ግን አንተ እንድትሞት
ለአንተ የሆነውም ሁሉ እንዲሞት በእርግጥ እወቅ›› አለው ንጉሡም እንደታዘዘው አደረገ ‹‹አብርሃምም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ እግዚአብሔርም
አቤሚሊክን ሚስቱንም ባሪያዎቹንም ፈወሳቸው በአብርሃም ሚስት በሣራ ምክንያት በአቤሚሊክ ቤት ማህፀኖችን ሁሉ በፍጹም ዘግቶ ነበርና››
በማለት ተገልéEል፡፡
4. ዘፀአ "2-7-04 ላይ እስራኤላውያን የወርቅ ጥጃ ባመለኩ ጊዜ ‹‹እግዚአብሔር ሙሴን እኔ ይህን ሕዝብ አየሁት እነሆም አንገተ ደንዳና ሕዝብ
ነው አሁንም ቀጣዬ እንዲቃጠልባቸው እንዳጠፋቸውም ተወኝ አንተንም ታላቅ ሕዝብ አደርግሀለሁ›› ብሎታል ነገር ግን እግዚአብሔር ሙሴን
ሳያማክር ማጥፋት ይችል ነበር ‹‹እንዳጠፋቸውም ተወኝ›› የሚለው አነጋገር አትማልድላቸው እንደማለት ነው፣ ሙሴ ግን ወደ ፈጣሪው
ስለማለደ ‹‹እግዚአብሔርም በሕዝቡ ላይ ሊያደርግ ስላሰበው ክፋት ራራ›› ይላል ይህን የሙሴን አማላጅነት ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ
በእግዚአብሔር ፊት መቆም ብሎታል ‹‹በኮሬብ ጥጃን ሠሩ ቀልጦ ለተሠራ ምስልም ሰገዱ ሣር በሚበላ በበሬ ምሣሌ ክብራቸውን ለውጠውታል
ነገርንም በግብፅ ድንቅ ነገርንም በካም ምድር ግሩም ነገርንም በኤርትራ ባሕር ያደረገውን ያዳናቸውንም እግዚአብሔርን ረሡ እንዳያጠፋቸውም
ቁጣውን ይመልስ ዘንድ የተመረጠው ሙሴ በመቅሠፍት ጊዜ በፊቱ ባይቆም ኖሮ ያጠፋቸው ዘንድ ተናገረ›› (መዝ 105፡19-23)
5. በኢትዮጵያዊት ሚስቱ ምክንያት አሮንና ማርያም በወንድማቸው በሙሴ ላይ ስላንጎራጎሩበት
እግዚአብሔር ለሙሴ ተቆርቁሮ ከገሠጻቸው በኋላ እህቱ ማርያም ለምጻም ሆነች በዚህን ጊዜ አሮን ደንግጦና ተጸጽቶ ‹‹ጌታዬ ሆይ ስንፍና
አድርገናልና በድለንማልና እባክህ ኃጢዓት አታድርግብን›› በማለት ወንድሙን ሙሴን ለመነው ሙሴም ወደ ፈጣሪው አማልዶ ከለምéE ተፈውሳለች›› (ዘኁ 12፡1-15)
6. እስራኤላውያን ስለዔናቅ ልጆች በሰሙ ጊዜ ግብፅ ለመመለስ አሰቡ በሙሴና በአሮንም
ላይ አንጎራጎሩ እግዚአብሔርም ሙሴን ‹‹ይህ ሕዝብ እስከመቼ ይንቀኛል በፊቱ ባያረግሁት ሁሉ እስከመቼስ አያምንብኝም ከርስታቸው
አጠፋቸው ዘንድ በቸነፈር እመታቸዋለሁ›› ሲለው ሙሴ እንደወትሮው ወደ አምላክ ጸለየ ‹‹ይህ ሕዝብ ከግብፅ ምድር ካወጣህ ጊዜ ጀምሮ
ይቅር እንዳልካቸው እባክህ እንደ ምህረትህ ብዛት የዚህን ሕዝብ ኀጢዓት ይቅር በል አለው›› ‹‹እግዚአብሔርም እንደቃልህ ይቅር
አለሁ›› አለው ይላል፡፡ (ዘኁ 14፡1-20)
7. ዳታንና አቤሮን በምቀኝነታቸው ከነቤተሰቦቻቸው ምድር ስለዋጠቻቸው ሁለት መቶ
ሃምሳ ሰዎች ደግሞ በትዕቢታቸው እሳት ከሰማይ ወርዶ ስለበላቸው ‹‹የእስራኤል ልጆች ማህበር ሁሉ እናንተ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ገድላችኋል ብለው በሙሴና በአሮን ላይ አንጎራጎሩ››
‹‹እግዚአብሔርም ተገልጾ ሙሴን ከዚህ ማህበር መካከል ፈቀቅ በሉ እኔም በቅጽበት አጠፋቸዋለሁ አለ›› ሙሴና አሮንም በግንባራቸው
ወድቀው ጸለዩ፣ ሙሴም አሮንን ‹‹ፍጠንና ውሰድ ከመሰዊያውም ላይ እሳት አድርግበት ዕጣንም ጨምርበት ወደ ማህበሩ ፈጥነህ ውሰደው
አስተሰርይላቸው ከእግዚአብሔር ፊት ቁጣ ወጥቷልና መቅሠፍትም ጀምሯል›› አሮንም ሙሴ እንዳለው አደረገ መቅሠፍቱም ተከለከለ (መኁ
16፡41-50)
8. እግዚአብሔር አልያዝ፣ በልዳዲስና፣ ሶፋር የተባሉትን የኢዮብን ጓደኞች እንደ
ባሪያዬ እንደ ኢዮብ ቅንን ነገር ስለ እኔ አልተናገራችሁምና ቁጣዬ ነድዷል አሁን እንግዲህ ሰባት ወይፈኖችንና ሰባት አውራ በጎች
ይዛችሁ ወደ ባሪያዬ ወደ ኢዮብ ዘንድ ሂዱ የሚቃጠልንም መስዋዕት ለራሳችሁ አሳርጉ ባሪያዬም ኢዮብ ስለ እናንተ ይጸልያል እኔም
እንደ ስንፍናችሁ እንዳላደርግባችሁ ፊቱን እቀበላለሁ እንደ ባሪያዬ ቅን ነገር አልተናገራችሁምና›› ስላላቸው በአምላክ እንደታዘዘ
አደረጉ ኢዮብም ስለጓደኞቹ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ እግዚአብሔርም የኢዮብን ፊት (ጸሎት) ተቀበለ ይላል (ኢዮ 42፡1-9)
9. በትንቢተ ኤርሚያስ
42፡1-12 ላይ እንደተለጸው ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቅ ድረስ ሕዝቡ ሁሉ ወደ ኤርሚያስ ቀርበው ‹‹እባክህ በፊትህ ልመናችን ትድረስ
አምላክህም እግዚአብሔር የምንሄድበትን መንገድና የምናደርገውን ነገር ያሳየን ዘንድ ስለእኛ ስለዚህ ቅሬታ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር
ጸልይ አሉት›› ‹‹ኤርሚያስም እነሆ እንደቃላችሁ ወደ እግዚአብሄር እጸልያለሁ የሚመልስላችሁን ሁሉ እነግራችኋለሁ ከእናንተ ምንም
አልሸሽግም አላቸው፡፡
10. በሐዲስ ኪዳን ውስጥ አንዲት ከነአናዊት ሴት ‹‹ጌታዬ የዳዊት ልጅ ማረኝ ልጄን
ጋኔን ክፉኛ ይዟታል ብላ ጮኸች ፣ ጌታችንም ምንም ሳይመልስላት ዝም ባለ ጊዜ ሐዋርያት ቀርበው እንደባለሟልነታቸው በኋላችን ትጮኀለችና
አሰናብታት እያሉ ለመኑት›› ጌታም የሐዋርያትን ልመና ሰምቶ የሴትየዋን እምነት አይቶ የለመነችውን ልጇን ፈወሰላት (ማቴ 15፡21-28)
11. ቅዱስ እስጢፋኖስ አይሁድ በሚወግሩት ወቅት ተንበርክኮ ‹‹ጌታ ሆይ ይህን ኃጢዓት
አትቁጠርባቸው›› በማለት ለምኖላቸዋል (ሐዋ 7፡60)
12. ቅዱስ ያዕቆብም ‹‹ትፈወሱም ዘንድ እያንዳንዱ ሰው ስለ ሌላው ይጸልይ የጻድቅ
ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች›› በማለት ሐዋርያዊ መመሪያ ሰጥቷል በተጨማሪም 2ቆሮ 5፡18-21 እና ዮሐ 5፡16
ይመልከቱ በዚህ መሠረት ቅዱሳን ሰዎች ስለኃጥአን የሚለምኑት ልመና ተቀባይነት ስላለው በአማላጅነት መጠቀም ታላቅ ብልህነት ነው፡፡
ቅዱሳን በአፀደ ሥጋ ሳሉ ማማለድ ብቻ ሳይሆን ይፈርዳሉ እግዚአብሔር ሙሴን ‹‹በፈርኦን ላይ አምላክ አድርጌሃለሁ›› (ዘፀ
7፡11) ነው ያለው፣ ጌታችንም ሐዋርያትን በአስራ ሁለቱ ነገድ ላይ እንዲፈርዱ (ማቴ 19፡28-29) ነግሯቸዋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም
ቅዱሳን በዓለም ላይ እንዲፈርዱ አታውቁምን? በማለት አስተምሯል (1ቆሮ 6፡2) ስለዚህ ቅዱሳን የመፍረድ ሥልጣን (የጸጋ አማልክት) ከሆኑ ይልቁንስ ስለኃጥአን ከጌታ
ዘንድ በጸሎትና በምልጃቸው እንደምን ምህረትን አያሰጡም?
No comments:
Post a Comment